Abadula Gemeda & Bereket Simon

አባዱላ ገመዳ እና በረከት ስምኦን

ወጋገን ከስቶክሆልም

የኢትዮጵያ ሕዝብ ስቃይና መከራ፣ የዘር መድሎና የበታችነት ኑሮ፣ መንግሥታዊ ውሸትና ቅጥፈት፣ ቡድናዊ ዝርፊያና የአገር መራቆት፤ አንገሽግሾት በላዩ ላይ ተጥሎ የነበረውን የፍርሃት ድባብ አፈራርሶ ለመሠረታዊ አዲስ ለውጥ ቆርጦ ተነስቷል። ዛሬ ከትግራይ ክልል በስተቀር በመላው አገሪቱ የሕዝብ ጥያቄ አንድና አንድ ነው።

"የኢሕአዴግ አገዛዝ በቃን!"

ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳለፉት 27 ዓመታት ኢሕአዴግ ይህን ይህን አሟላልን የሚል ጥያቄ የለውም። ጠይቆ ጠይቆ፣ ታግሶ ታግሶ ጠብ ያለለት አንዳችም ነገር እንደሌለ ከራሱ የበለጠ ማስረጃ አላስፈለገውም። ይልቁንም ኑሮውና ተስፋው ከዓመት ዓመት ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆ በመጣ ቁጥር ሕዝባዊ ቁጣውና ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ እየባሰ መጣ። እንግዲህ፦

  1. ሕዝብ የተሸረበበትን የከፋፍለህ ግዛ እምቢ ብሎ በአንድነት በተቃውሞ በተነሣበት ወቅት፣
  2. የነገ የአገርና የታሪክ ተረካቢ ወጣቶች በየዩኒቨርስቲዎች መንግሥታዊ ተቃውሟቸውን በሚያስተጋቡበት ወቅት፣
  3. በጎሣ ፖለቲካ ተበታትነውና ተቃቅረው ይተያዩ የነበሩ ብሔረሰቦችና ማኅበረሰቦች ልዩነቶቻቸውንና ጥላቻዎቻቸውን ሁሉ መንግሥታዊ ሤራ መሆኑን ተረድተውና አውግዘው ለመንግሥታዊ ለውጥ በተመሙበት ወቅት፣
  4. ሕዝባዊ ፖሊሶች ከሕዝብ ጎን ቆመው እብሪተኛውንና ሆድ አምላኩን ገዳይ የአጋዚ ጦር በሚፋለሙበት ወቅት፣
  5. የስም ጠ/ምሩ በከፍተኛ የሥራ ድክመት አንገቱን በደፋበትና በርሬ የት ልግባ ባለበት በዚህ የሕዝባዊ ነውጥ ወቅት፣
  6. በአገሪቱ መመሪያ ሰጭውና መመሪያ ተቀባዩ ባልታወቀበት እና መንግሥት እንደመንግሥት ያለውን ሁኔታ ሊቆጣጠር ባልቻለበትና መንግሥታዊ መዋቅሩ ሁሉ ከጉያው እየተመዘዘ በመፈራረስ ላይ ባለበት፤

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ "ኢሕአዴግ ሥልጣን ልቀቅ!" እያለ ቁጣውንና ሕዝባዊ ድምጹን በአንድነት በሚያስተጋባበት በዚህ የመንግሥት መወገጃ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ፤ እነዚህን ዓይን አውጣ ስሟቸው። ”መቼስ ምንይደረግ!?” ይላሉ - መቼስ ምን ይደረግ!?

”ከእኛ ወዲያ አገሪቱ ሰው የላትም። ስለዚህ ወደ ቀድሞው ሥልጣናችን ተመልሰናል።"

  1. በረከት ሰምኦን
  2. አባ ዱ....ላ ገመዳ

ሕዝባዊ እምቢተኛነት ትናንትና በሊቢያ፣ በግብፅ፣ በኢራቅ፣ በቱኒዚያ እና በሌሎችም አገር መሪዎችና ባለሥልጣናት ላይ ያስከተለውን ውርደትና ጥቃት አለማጤን ባዶነት ነው። ከሁሉም በላይ የጋዳፊንና ሳዳም ሑሴንን አሟሟት ለሰከንድ አለማሰብ ደግሞ ባዶነት ብቻ ሣይሆን ባዶነትም፣ እውርነት፤ ሲዘልቅም የአስተሳሰብ ንቅዘትም ነው። አለመታደል ሆኖ አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ መሪዎችና ባለሥልጣናት ላለመስማት ጆሯቸውን ደፍነውት እንጅ፤ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተወዳጁ ባራክ ኦባማ (ተወዳጅነታቸው ለአገራቸው በአገራቸው ቢሆንም)፤ የሚሰማ ጠፋ እንጅ ጠንከርና ሰላ ያለ ምክርም ትችትም ሰንዝረው ነበር። እንዲህ ነበር እያሉት፣

”ሥልጣን ለሀብት/ለገንዘብ ከሆነ ይገኛል አግኝታችኋልም። ከዚህ በኋላ ግን ሥልጣን ልቀቁ (Step-Down)” ነበር ያሉት። በዚህም አላቆሙም እራሳችሁ ባወጣችሁት ሕገመንግሥት ራሳችሁን ዳኙም ብለዋል። አያይዘውም። "እኔ በሕገመንግሥታችን መሠረት ከአሁን በኋላ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር አልችልም። ሕጉ ይከለክለኛል። አውቃለሁ በመሪነት ዘመኔ በርካታና ጠቃሚ ሥራዎችን ሠርቻለሁ። ስለዚም ለምርጫ ብወዳደር እርግጠኛ ነኝ አሸንፋለሁ። ነገር ግን ሕጉ አይፈቅድልኝም።”

እነ አቶ በረከት የባራክ ኦባማ በራስ መተማመን ከምን የመጣ መሰላችሁ? በትምህርት እንዳትሉኝና እነ ዶ/ር ሣሞራና አባዱላ ደረታቸውን እንዳይነፉ። ትምህርት ሕዝብና አገርን ለማገልገል ታላቅ ድራሻ ቢኖረውም፤ በአገርና ሕዝብ መውደድ፣ በቀናነትና ሰብአዊ አመለካከት ታጅቦ በሕግ የበላይነት ካልተገራ ብሔራዊ ፋይዳ አይኖረውም። ለአቶ በረከትና አባ ዱላ ሥልጣን ማለት እንደከረንቡላ ቤት በፈለጉ ጊዜ እሚመላለሱበት ዐይነት ወይም የድድ ማስጫ መደበሪያ ነው። እናም ሲደብርና አላግባብ በግል የተከማቸው ሀብታቸው የእነሱን የዕለት ተዕለት እይታ ሲፈልግ መንግሥታዊ የሥራን በቃኝና በለቅቄአለሁ ሰበብ ሾልኮ መሄድ። ደሞ ለመሄድ የትኛው ተጠያቂነት ሊያስፈራቸው።

የግል ሠራዊት መልክ መልክ ሲይዝላቸው ደግሞ ተመልሶ መምጣት። ደሞ ለመምጣት የትኛው አካል አትመጡም ሊላቸው። ቀድሞውኑ ሂዱ ያላቸው ሲመለሱም እኛን ለማደናገር በጭብጨባ ይቀበላቸዋል።

ይህ ተግባር በአገር መቀለድ ነው። ሲሻገርም ሕዝብን ከትንኝ አሳንሶ ማየት ነው። እናም ይህ ንቀት፣ ይህ ትዕቢት፣ ይህ ማንአለብኝነት፤ በሕዝባዊ እምቢተኛነት በቃ ተብሎ ሥርዓቱ ፍፃሜ ያገኝ ዘንድ ወቅታዊ  መፈክሩ፤

”ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም!” ነው።

ከዚህ በኋላ በኢሕአዴግ ሹም ሽር ኢትዮጵያ አትመራም።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!