ሙሉነህ ዮሐንስ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ምላሽ “በኤርትራ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ነፃነት የሚወስድ መንገድ የለም” በሚል አባኪያና ጓደኞቹ ለጻፉት

በመጀመሪያ ጓደኛየ አባኪያ ሠላም ላንተና ለጓደኞችህ ይሁን! ሰሞኑን ኢትዮጵያ ዛሬ (www.ethiopiazare.com) ድረ-ገጽ ላይ ያወጣችሁትን ጽሑፍ በግርምትና በአንክሮ ደጋግሜ አነበብኩት። ይህን እንደሳማ የሚቆጠቁጥ አርዕስት ደፍራችሁ ለውይይት ስላቀረባችሁት እያመሰገንኩ፤ አስተሳሰባችሁ ግን አስደንግጦኛል፤ አጥብቄም እቃወመዋለሁ። ኢትዮጵያውያን ወገኖች የኤርትራን ጉዳይ በዚህ መልኩ ያዩታል የሚል ግምት አልነበረኝም። አስተያየቴን በግል ልሰጣችሁ አስቤ ነበር። የጉዳዩን አደባባይ መውጣትና ለኢትዮጵያችን ሊኖረው የሚችለውን አደገኝነት ሳስበው እንዲሁም የውይይት ግብዣችሁን ሳክልበት በይፋ ምልከታየን ማድረስ መረጥኩ።

 

(የአባኪያንና ጓደኞቹን ጽሑፍ ለማንበብ “እዚህ ይጫኑ!”) ወደ ምልከታየ ከመግባቴ በፊት ላንተም ሆነ ላንባቢዎች ግልፅ ማድረግ የምፈልገው ጽሑፌ የኔው የግሌ አስተሳሰብ ብቻ መሆኑን ነው። በተጨማሪም በተፃፈው አርዕስት ላይ የምሰጠው አስተያየት ፀሐፊዎቹ የሚደግፉት የሚመስለውን የትግል ስልት የመቃወም ወይም የመደገፍ አይደለም። ይልቁንስ የትኩረት አቅጣጫየ እንደ መንግሥትም፤ እንደ ሀገርም፤ እንደተቃዋሚም ቢታሰብ የኤርትራ ገዥ ቡድን ለኢትዮጵያ የነፃነት አጋር ሳይሆን እንዴት የስጋት ምንጭ እንደሆነ ማሳየት ነው። Take it as an academic discourse

 

ኢትዮጵያ ሀገራችን በወያኔ ጨቋኝ ያገዛዝ ቀንበር ስር ከወደቀች ለአቅመ-ኣዳም የደረሰን ጎረምሳ ዕድሜ አስቆጥሯል። ለለውጥ አጥጋቢ ሙከራ እንኳ የተደረገው በምርጫ 97 ነው። ወያኔን በምን የትግል ስልት እንታገለው የሚለውን ቁርጥ አቋም እንደ ህዝብም እንደ ተቃዋሚም ጥርት ብሎ ሳይያዝ ብዙ ዓመታት ነጉደዋል። ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ያላገኙ ወገኖች አሁንም የትየለሌ ናችው። የወያኔንም ቀሪ ዕድሜ በዚህ ክንድ መለካት ይቻል ይሆናል።

 

ሠላማዊ የትግል ስልትን መርጠው ሀገር ቤት የሚንቀሳቅሱት genuine ተቃዋሚ ፓርቲዎች የማያወላዳ አቋም ወስደዋል። አፈናው አላላውስ ባለበት የኢትዮጵያ ምድር ትንሿን ቀዳዳ በርግደው ነፃነትን ለህዝባችን ለማጎናፀፍ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ላይ ናቸው። በቆራጥነትም ሊደገፍ የሚገባ ትግል ነው። የኔም ምኞትና ተስፋ ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ዳር ደርሶ ዘላቂ ሠላምንና ብልፅግናን ማየት ነው። ከዚህ ባንፃሩ ደግሞ ወያኔ ከሥልጣን ሊወገድ የሚችለው በኃይል ብቻ ነው ብለው የሚያምኑና የትግል ስልታቸውን በዛ መልኩ ቀይሰው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ። የትጥቅ ትግልን እየሞከሩ ያሉት እነዚህ ኃይሎች አንዱ አብይ ችግራቸው የሚምስለው ትግላቸውን በዋናነት የሚያስተባብሩበት ነፃ መሬት ጉዳይ ነው። ሌላው ደግሞ እንደዚህ አይነት ኃይሎችን በበቂ በመርዳት ሊተማመኑበት የሚችሉት ልዕለ ኃያል ሀገር አለመኖር ነው። ያም የሆነው አሁን ያለው የዓለምና የአካባቢያችን ፓለቲካ ሁኔታ የትኩረት አቅጣጫው የአስልምና አክራሪዎች ተብለው የተፈረጁ ቡድኖችን በማሳደድና የጥሬ ምርቶችን በማካበት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ነው። በኢትዮጵያም ምድር ይሁን በሌላ ጨቋኝ መንግሥታት ስር እየዳሸቁ ለሚገኙ ህዝቦች ደንታ ያላቸው መንግሥታት በዓለም ፈልጎ ማግኘት ካለመቻሉም በላይ፤ ይባሱንም ለመከራችን መርዘም ቀጥታ ተጠያቂ የሚሆኑባቸው ደርዘን የክስ ስንክሳር መደርደር ይቻላል። ቁምነገሩ ግን እዚሁ እኛው ጉያ ስር ነው። በረዥሙ ታሪካችን የገጠሙንን ታላላቅ ፈተናዎች እንዴት እንደተወጣናቸው ዞር ብለን ልንመረምር ይገባል። አሁን እየተበረዙ የሚገኙትን ብሔራዊ የጀግንነት፣ ሀገርን የማስቀደም፣ ረዥሙን የነፃነት ታሪካችንን እሴቶች ላለንበት ትውልድና ዘመን ማስጨበጥን ይጠይቃል። ትንሣኤያችንን በብሔራዊ እልህ ማወጅ አለብን።

 

ለመንደርደሪያ ይህን ካልኩ ወደተነሳሁበት አርዕስት ልመለስ። በእኔ አስተሳሰብ ይዞት በኖረውና አሁንም ባለበት ባህርይው እንዲሁም አፈጣጠሩን ስናጤን ሻዕቢያ እንደገዥ ቡድን ኤርትራም እንደሀገር በሚከተሉት ምክንያቶች ለኢትዮጵያ የስጋት ምንጭ እንጂ የነፃነት አጋር ሊሆኑ አይችሉም።

 

1. የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ በጎ ሊያደርግ ባህሪይው አይፈቅድለትም አባኪያና ጓደኞቹ ሻዕቢያን እንደአጋር አድርገን እንድናየው የሚያቀርቡት መከራከሪያ ነጥብ ወያኔን በማስወገድ ላይ የጥቅምና የቁጭት አንድነት አለን በማለት ነው። መታወቅ ያለበት ግን የእነኢሳያስ ቁጭትና ጥቅም ከእኛ ከኢትዮጵያኖች ጋር ምንም ተዛምዶ የለውም። የነሱ እልህና ቁጭት አሁን ባለው ወያኔ ላይ ብቻ ሳይሆን ባለፉትም በሚመጡትም መንግሥታት ላይ እንደሚሆን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለኢትዮጵያ ያላቸው ጭፍን ጥላቻና የበቀል ስሜት በኖ ጠፍቷል ብትሉኝ ልቀበለው አልችልም፤ እማኝም መጥራት ይሳናችኋል። የተዳከመች ኢትዮጵያን መመኘት ብቻ ሳይሆን እንድትኮሰምንም የኤርትራ መንግሥት የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። ታዲያ ለዚህ ዓላማቸው ተፈፃሚነት የሚረዱ ኃይሎችን ይረዳሉ እንጂ ለምን ብለው ለኢትዮጵያ ልዕልና የሚታገል ኃይል ይደግፋሉ ልትሉኝ ነው? ምናልባት እነዚህ ኃይሎች ለሻዕቢያ ተንበርካኪ ሆነው ካልተቀረፁ በቀር ሻዕቢያም ጊዜውንና ንብረቱን የሚያባክንበት መላምት አይታየኝም። ከዚሁ ጋር ሊጤን የሚገባው ከኤርትራ ጀርባ ሆነው በሀገራችን ላይ መሰሪ ፖሊሲያቸውን የሚያራምዱ አሉ። እነ ግብፅ እና ራቢጥ የዐረብ መንግሥታት እነሻዕቢያን ኮትኩተው እዚህ ያደረሱት ለፅድቅ ሳይሆን ለጥቅማቸው ነው። ሠላም የሰፈነባት ኢትዮጵያ መኖር ለልማት ዝግጁ ስለሚያደርጋትና ወንዞቿን ለመጠቀም ስለምትችል ለነግብፅ የራስ ምታት ነው። እስካሁንም እንድምናየው እኛን መቧቀሱ ሲሳካላቸው ኖሯል። እነዚህ ኃይሎች ኤርትራን እንደዋና መሣሪያ እንደሚጠቀሙባት የተጋረደበት ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ኃይል ካለ አውቆ የተኛ መሆን አለበት።

 

2. ከኤርትራ ጋር ያልተወራረደ ሂሳብ አለን እነኢሳያስ በእነመለስ አጨብጫቢነት ነፃነት ሲያውጁ በሀገሮች መካከል ባግባቡ ያልተፈፀሙ የዜግነት፣ የድንበር፣ የሀብት/ንብረት ርክክብ አበይት ጉዳዮች አሉ። ሪፈረንደም ተብየው አስገራሚ ድራማ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች ነፃነትን ወይም ባርነትን ምረጡ ተብለው የተገደዱበት ጉዳይ ነው። የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም አይነት ሃሳብ ሳይሰጥበት ድራማው ከመጠናቀቁም በላይ በጭንቅ ላይ እንኳ እያሉ ኢትዮጵያዊነትን የመረጡ ወገኖች ዕጣ ፈንታ በቅጥ አይታወቅም። ለኤርትራ ነፃነት መውጣት እውቅና መስጠት የሚቸግራቸውም ወገኖች በቂ ምክንያት አላቸው። አንዱም ምክንያት ኢትዮጵያዊነታቸው እንዲቀጥል የሚታገሉት የአፋር ወገኖች ጉዳይ እና የነዚሁ ወገኖች መኖሪያ የሆነው የአሰብ ራስ ገዝ አስተዳደር ጉዳይ ነው። በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ኤርትራ ነፃነት ስታውጅ ከኢትዮጵያ ያላት ወሰን የአሰብን ራስ ገዝ አይጨምርም። ይህ በሰፊው ተብሎለታልና በባሌም ይሁን በቦሌ ተቆርቋሪ መንግሥት ሲኖረን በሰፊው የሚታይ ጉዳይ ይሆናል።

 

ስለአሰብ ሳነሳ አንድ ታዋቂ የሆነ የአየር ኃይል ባልደረባ የነበር ወዳጀ ያጫወተኝን ላካፍላችሁ። ይኽው ሰውዬ በታሪክ አጋጣሚ በወቅቱ የኤርትራ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ከሆነው ባለሥልጣን ጋር የመጨዋወት ዕድል ይገጥመውና ባጋጣሚ የአሰብ ጉዳይ ይነሳል። ይኽው የሻዕቢያ ባለሥልጣን ያለው “አሰብ ወያኔ በገፀ-በረከት ያስረከበን ስጦታ ናት” የሚል ነበር። እንግዲህ በተጨማሪም ኤርትራ ውስጥ ደብዛቸው የጠፋ አያሌ ወገኖች አሉ። ይህ ሁሉ ያልተወራረደ ሂሳብ እያለ ምን አይነት አቋም ያለው የኢትዮጵያ ኃይል ነው ከኤርትራ ጋር የሚሰለፈው? ለተጠቀሱት ሂሳቦች ደንታ ስለሌለው ቡድን ከሆነ የምታወሩት ሊያስኬዳችሁ ይችላል፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ጋር ግን ምንም ግንኙነት ስሌለው የሃሳብ ማደፍረስ ሥራ ያስመስልባችኋል። ሚናችሁን ለዩ ውዥንብር (confusion) አትፍጠሩ።

 

3. በኤርትራ መንግሥት ቁጥጥር ስር የወደቀ ባለሀብት እርግጥ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ተሞክሮ በገሃድ እንኳ የሚታወቀው አስር ዓመት ሙሉ በሻዕቢያ ጉያ ስር የተወሸቁ ሦስት አራት የሚሆኑ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች/ድርጅቶች አንድ መንደር ነፃ ሳያወጡ የኢሳያስ ማስፈራሪያ ቡችሎች ሆነው ቀርተዋል። እንዲያውም አብዛኞቹ እነዚሁ ኃይሎች ጠባብ ብሔርተኞች ከመሆናቸው የተነሳ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ደንታ የላቸውም፤ ጣራ እናፍርስ ቢሏቸው ቀድመው መሰላል ላይ የሚወጡ ናቸው። ተደናግረውና እንሞክረው ብለው ኤርትራ የገቡ ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ ቡድኖችና ስመጥር ግለሰቦች ግን በሻዕቢያ ስውር እጅ ደብዛቸው እየጠፋ እንደሚገኝ ከጎናቸው የነበሩ ሰዎች ደባውን በተደጋጋሚ አጋልጠዋል። ስለዚህም እነ አባኪያ የምትዘምሩልን የኤርትራ የተጋነነ አለኝታነት ከምን የመጣ ነው? በቅጡ ደግማችሁ አስቡበት።

 

4. ሻዕቢያ የጠላቴ ጠላት ስለሆነ ወዳጄ ነው የሚለው ቀመር ዘላቂ የስጋት ምንጭነቱን እንዳናይ የሚያደርግ አደገኛ አስተሳሰብ ነው ሻዕቢያና ወያኔ ላለንበት ውጥንቅጥ እኩል ተጠያቂ ናቸው። በስግብግብነትም ይጣሉ በድንቁርና ባህሪያቸው፣ ሻዕቢያና ወያኔ ኢትዮጵያ እንደሀገር ጠንካራ ሁና እንዳትቀጥል ክፋቷን አብረው እንደቀመሯት ተጣልተው የሚወጡ የነሱ ጉምቱ ባለሥልጣኖች የነበሩቱ ሳይቀሩ እየመሰከሩ ነው። እናም ሁለቱም ቡድኖች ለኢትዮጵያ ባልተናነሰ መልኩ አደገኛ ቀመር አላቸው። ሻዕቢያ ከስህተቱ ተምሯል ብላችሁ ምስክር መቆማችሁ አስገራሚ ነው። ምን አይነት አስተሳሰቡ ነው የተቀየረው? እንደኔ እንደኔ ያሰጋል ብዬ የማስበው በሆነ ምክንያት ሻዕቢያና ወያኔ ዞረው ቂጥ ገጥመው የባሰውን ጉድ እንዳይሠሩን ነው። ምንስ የሚከለክላቸው ነገር ያለ ይመስላችኋል? ከላይ የጠቀስኳቸውን ነጥቦች ጨምረን ስናይ ሻዕቢያ የጠላቴ ጠላት ስለሆነ ወዳጄ ነው የሚለው እሳቤ የዋህነት ያጠቃዋል አደገኛም የፖለቲካ ስሌት ነው።

 

5. እና ምን ይሁን? እውን ሌሎች አማራጮች የሉም? እኔ መቼም የትጥቅ ትግል ለማድረግ አማራጭ ሀገሮችን የመደርደር ዓላማ የለኝም። ይሁንና እነአባኪያ ከካናዳ ሆነው እንደሚነግሩን “በኤርትራ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ነፃነት የሚወስድ መንገድ የለም” ከሌሎች ሀገሮች ጋርም ግንኙነት ለመመስረት ብቸኛ ድልድይ ኤርትራ ናት የሚለው መላምታቸው ያቅረኛል። ስለኤርትራ የተጋነነ ግምት/ተስፋ እየያዙ ያሉ የኢትዮጵያውያን ቁጥር በአንድ እንኳ ማደጉ ለኔ አሳሳቢ ነው። ለሻዕቢያ እዚህ መድረስ በድንቁርናም ይሁን በመሰሪነት ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድጋፍ ያበረከቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ስህተት በዚህም ትውልድ ሲደገም ማየት ጅልን እባብ ሁለቴ ይነድፈዋል ያስብላል።

 

በጽሑፌ መነሻ እንዳልኩት ነገሩን እንደ academic discourse ብንወስደው ብዙ መላምቶችን ወይም ተፎካካሪ ሃሳቦችን ማንሳት አይቻልምን? ለመሆኑ መሣሪያ አንስተን ወያኔን እንዋጋለን የሚሉ ኃይሎች የትግላቸውን እንብርት ኢትዮጵያ ለማድረግ ለምን አይደፍሩም/አያስቡም? ተብለው ቢጠየቁ ምን መልስ አላቸው? ሩቅ ሳንሄድ እንኳ በሱዳን፣ በታላቁ የአፍሪካ ኃይቅ ዙሪያ ያሉ ጠንካራ የመንግሥታት ተቃዋሚ ሸማቂዎች፣ እዚሁ በቅርቡ ደግሞ እነመለስን ሰንገው ይዘው ያሉ የሶማሊያ ተዋጊዎች እና የመሳሰሉት በዋነኝነት የሚንቀሳቀሱት በራሳቸው ነፃ መሬት አይደል እንዴ?

 

6. የእኔ ፀሎት እንደ ኤርትራ ባለ የውጭ ኃይል ቁጥጥር ስር ከሚወድቅ የኢትዮጵያ ትግል ይሰውረን! ለሀገራችን የምናደርገውን ትግል በቅጡ እንመርምር።

 

የአንድነት ኃይሎች ኢትዮጵያን እንደሚታደጉም ተስፋ አደርጋለሁ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይታደግ ዘንድ ተግታችሁም ፀልዩ።


 

አስተያየት ካላችሁ ሙሉነህ ዮሐንስ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ነኀሴ 26 ቀን 2000 ዓ.ም. September 1, 2008

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ