Ethiopian Flag

ለሌሎች አገሮች ሳይቀር የነጻነት አርማ የሆነው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ

አገሬ አዲስ

ስለ ኢትዮጵያ አገራዊ አመሠራረት ሁለት ተጻራሪ ኃይሎች፣ አገር ወዳዶችና ጎሠኞች የሚሰጡት አስተያየት እንደ አቋማቸው የተለያየ ነው።

በኢትዮጵያዊ አገር ወዳዶች በኩል ታሪክን መነሻ በማድረግ የሚቀርበው አመለካከት፤ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መነሻ፣ ከብዙ አገራት በፊት ሥርዓት ገንብታ የኖረች፣ የብዙ ዘመናት ታሪክ ያላት፣ ከቀይ ባሕር ማዶና መለስ የተንሰራፋ ሰፊ ድንበር የነበራት፣ ለሌሎች አገራት ሥልጣኔና ምስረታ ምሳሌና ምልክት የሆነች አገር ናት። እንደማንኛውም አገር የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ፣ የተለያዩ እምነቶች ተከታይ፣ የብዙ ባህል ባለቤት የሆነ ሕዝብ የኖረባትና የሚኖርባት አገር ናት። አገራዊ ግንባታዋም ሌሎች አገሮች ከተከተሉት አይለይም። ምንም እንኳን በሂደቱ ወቅት በአንድነትና በፀረ አንድነት ኃይሎች መካከል ግጭት መካሄዱ ባይካድም፣ ከአንዳንዶቹ ፍጹም አረመኔያዊ ከሆነ አገራዊ አመሠራረት በተሻለ መልኩ፣ በመከባበርና በመግባባት ብሎም በመፈቃቀድ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማቆምና አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ሁሉም ዜጋ የሚችለውን መስዋእትነት ከፍሏል። በተደጋጋሚ ከውጭ የመጡ ጠላቶቹን ተባብሮ በመመለስ ነጻነቱን አስከብሯል። በዚህ የጋራ ርብርቦሽና የእኛ ባይነት መንፈስ የተገነባች አገር በየወቅቱ በተነሱ የውጭ ጠላቶችና የሥልጣን ፍቅር ባሳበዳቸው መሪዎች ተንኮልና በሚፈጥሩት ውዝግብ የሕዝቡ ሰላምና አብሮነት ፈተና ውስጥ ሲገባ፣ ያገሪቱም እድገት ተሰናክሎ፣ አንድነቷም ተቦርቡሮ በቀበኞች እየተቆራረሰች ከአገራት በፊት የነበረችና የነጻነት ምልክት የሆነች አገር፤ አሁን ከአገራት ሁሉ ኋላ ቀርታ፣ ለዓለም ሕዝብ በርሃብ፣ በግጭትና በስደት የመቀጣጫና የማስፈራሪያ ምሳሌ ለመሆን መብቃቷን በቁጭት ይናገራሉ።

በጠባብ ጎሠኞችና በጠላቶቿ ዓይን ደግሞ፤ ኢትዮጵያ ማለት ያልሠለጠነ፣ ካውሬ የማይሻል፣ የማይግባባ፣ የማይተዋወቅ፣ እርስ በርሱ የሚፋጅ፣ ሃይማኖት የሌለውና ፈጣሪን የማያውቅ አረመኔ፣ አንዱ ሌላውን ውጦና አስገብሮ፣ በባርነት ይዞ የኖረባትና የሚኖርባት፣ ደሃና ኋላ ቀር አገር ናት። ስለተፈጥሮ ሀብቷ፣ ስለረጅም ታሪኳ፣ በዓለም ታሪክ ውስጥ ስለነበራት ቦታና ድርሻ፣ ሕዝቡ ያለውን ሰብአዊ ሥነምግባርና አብሮ የመኖር ትስስሩንና ታሪኩን ይክዳሉ። ለነሱ ኢትዮጵያ ማለት ሌሎች በነጻነት ይኖሩ የነበሩትን አገሮች (Nations) አፈራርሶ የበላይነት ባገኘ ጎሣ የተፈጠረች አገር ናት። ስለሆነም እያንዳንዱ ጎሣ የራሱን ክልል ከልሎ ከሌላው ተነጥሎ ነጻ መንግሥት ማቋቋም አለበት ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ አገርና ዜግነት (Nation and Nationalities) የሚለውን ዓለም አቀፍ ግንዛቤ ብሔር ብሔረሰብ የሚል የተሳሳተ ትርጉም ያለው ትንታኔ በመስጠት የተዛባ አመለካከታቸው ሕጋዊነት እንዲኖረው ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው። ይህ በውጭ አገር ሰርጎ ገቦችና በአገር ውስጥ ተባባሪዎቻቸው በዴሞክራሲና በእኩልነት ስም ጎሣን የጠቀመ መስሎ ኢትዮጵያን በማፈራረስ ሴራ ከሰባ ዓመት በፊት የዘሩት የጥፋት ችግኝ ጎምርቶ ኢሕአዴግ የሚባል ፍሬ ካፈራ ሃያ ስምንት ዓመት ሆኖታል። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተወለደው ትውልድ ስለነባሩ ያገሩ ታሪክ ሳያውቅ ለሚረጭለት አጥፊ ታሪክ ሰለባና ጭፍራ በመሆን የረጅም ዘመናት ታሪክ ባለቤት የሆነችውን አገሩን እንዲጠላና ለነጮች መሰሪ የምዝበራ ዓላማ መሣሪያ ለመሆን ላይ ታች ሲል ይታያል። እራሱን ከሌላው ወገኑ ነጥሎ በጠላትነት መስመር ውስጥ አሰልፎ ሌላውን ወገኑን መጤና ሰፋሪ እያለ ሲገልና ሲያፈናቅል ያሳለፈው ጊዜ ለወደፊቱ ሊጠፋበት የሚችል አደጋ እንደሚሆንበት ለማዬት ከከለለው የጎሠኝነት እንቅልፉ አልነቃም። አሁንም የነገሩትን ራስን የመጥላት ዘመቻ እያስተጋባ በራሱ ላይ ቢላዋ እየሳለ ነው። ለኢትዮጵያዊ ማንነቱ ምሰሶና አጋር የሆነውን ወገኑን በተለይም የአማራውን ማኅበረሰብ እንደ ዋና ጠላት በመቁጠር ኃይሉን ንዶና አመንምኖ አገሩን ለማፈራረስና ለውጭ ኃይሎች ዘረፋ የተመቸ ደካማ የጎሣ መንደር ለመፍጠር በነጻነት ስም የሚያደርገው ትግል ስህተት መሆኑን አሁንም አልተረዳም። ሌላው ቀርቶ ከጎረቤት አገር ከሶማሊያ አልተማረም።

በፀረ ኢትዮጵያነት የተሰለፉት የየጎሣው መሪዎች ነን ባዮች ራሳቸውን የአንድ ትልቅ አገር ዜጋ ከማድረግ ይልቅ የተወሰነ ቁራሽ መሬት ባለቤት ወይም ምስለኔ ለመሆን፣ ለዚያ ትንሽነት ሲሰግሩ ማየትን የመሰለ ኋላ ቀርነት የለም። በዚህ ላይ ነጮች ኋላ ቀር ብለው ቢሉ ስህተት አይሆንም፤ ከትልቅነት ትንሽነትን ከመምረጥ ሌላ ምን ኋላ ቀርነት ይኖራልን? ሰብአዊ ፍጡርን ለዚያውም በመዋለድ በእትብት የተሳሰረን ወገኑንና ዘመዱን፣ የአንድን አገር ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋና በሚከተለው እምነት የተነሳ ከመጥላትና ከመሸንሸን ሌላ ምንስ አውሬነት ይኖራል? ”እኛና የእኛ” የሚለው መንፈስ ተዳክሞ፤ ”እኔና የእኔ” በሚለው ከተተካ ምን ዐይነት ጠንካራና ነጻ አገር፣ ምንስ ዐይነት እድገት ይታሰባል?

ኢትዮጵያዊ በዘመናት መስተጋብር ያተረፈውን ውህደትና ታሪክ ሽረው፣ ሕዝቡን በቋንቋው ረድፍ አሰልፈው፣ የመሬት ድንበር ከልለው፣ እርስ በርሱ በማናከስ ኢትዮጵያን የማፈራረሱን ሂደት ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት "ሕገ መንግሥት" በሚል ሽፋን "ሕገ በትን" አውጆ ከመንቀሳቀስ ሌላ ምን የአገር ጠላትነት ይኖራል? ያንንስ ሕግ ለአገር አንድነትና ለሕዝብ እኩልነት ይጠቅማል ብሎ የሚቀበል ምን ዐይነት አዕምሮ ያለው ዜጋ ነው? ለምን ከሌሎቹ አገሮች ሥርዓት መማር አልተቻለም? ነገሩ አውቆ የተኛ ቢጠሩት ወይ አይልም ነው። ይህንን ራስ ጠል ድክመት ተሸካሚና ወጣቱን ትውልድ የሚበክሉት ተምረናል የሚሉ የሥልጣን ጥመኞች የሆኑ የየጎሣው ተወላጆች ናቸው። የሚገርመው ነገር ግን፣ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ፣ ልዩ ልዩ ባህልና እምነት ያለው ሕዝብ በአንድነትና በሰላም በሚኖርበት አገር ውስጥ እየኖሩና በእኩልነት እንዲታዩ፣ መብታቸውም እንዲከበርላቸው እየጮኹ፤ ተወለድንበት ለሚሉት አገርና ሕዝብ ግን የዘረኝነትና የልዩነት መርዝ መርጨታቸው ነው። ይህ ደግሞ ከወንጀልም በላይ ወንጀል ነው። የጎሠኝነት ውጤትና ጣራው ፋሽዝም ነው። የፋሽዝም ፀረ አንድነትና ኢሰብአዊነት ነው። በአገራችን የተከሰተው ጎሠኝነት የሂትለርን ተከታዮች በዓለም ፍርድ ቤት ካስቀጣው ወንጀል ቢበልጥ እንጂ አይተናነስም። የሚበልጥበት ምክንያት ባልታጠቀና የጦር ኃይል በሌለው ደሃ ገበሬ ሕዝብ፣ ሕፃንና አዛውንት ላይ የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋና በደል በመሆኑ ነው።

ሰፊው ሕዝብ የእርስ በርስ ጥላቻ የለበትም፤ ለዘመናት አብሮ በሰላምና በአንድ አገር ልጅነት መንፈስ ባህልና ቋንቋውን እምነቱንም ጭምር ተወራርሶ የኖረ ነው። ከሃምሳ ዓመት ወዲህ በስሙ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚሹ የጎሠኝነት ፍልስፍና በሚከተሉ ጥቂቶች ሲረጭ የኖረው እርኩስ መንፈስ አሁን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ድል እየሆነ መጥቷል፤ ቢያንስ ቢያንስ ኢትዮጵያ የሚለው አገራዊ መለያ ጎልቶ በተቀናቃኞቹ አንደበት ሳይቀር እየተነገረለት ነው። ይህ ግን በቂ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል። ጎሠኝነትን የሚያጎላውና የሚንከባከበው፣ የጥፋት እውቅና (licence to distroy) የሚሰጠው "ሕገ መንግሥት" ተብዬው የጎሠኞች መሳሪያ በኢትዮጵያዊነት ላይ መሰረት ባደረገ፣ የአገርን አንድነት በሚያረጋግጥ፣ የዜጎችን ደህንነት በሚያስከብር፣ የዜጎችን መፈናቀል በሚከላከል፣ መንግሥትን በሚቆጣጠርና ከስሩ ባደረገ፣ ሕዝብ በተሳተፈበትና ባጸደቀው እውነተኛ ሕገመንግሥት መተካት ይኖርበታል። ያ እስካልሆነ ድረስ ለመሰረታዊ ለውጥ የሚያመራ ሂደት አለ ብሎ ለማመን ያስቸግራል።

ጥላቻ መንዛት ወንጀል ነው፣ መከፋፈልና ማጋደል ወንጀል ነው። አንዱን መጉዳትና ሌላውን መጥቀም ወንጀል ነው። አገር መናድ ወንጀል ነው። ሕዝብን ማሳደድና ማፈናቀል ወንጀል ነው። የአገርን ሀብት መዝረፍና ማዘረፍ ወንጀል ነው። ያገሩን ባለቤት እያፈናቀሉ መሬቱን ለባዕዳን መሸጥና አሳልፎ መስጠት ወንጀል ነው። እነዚህን ሁሉ በሕግ ሽፋን የሚፈጽም መንግሥትም ይሁን ቡድን ወንጀለኛ ነው። ዘረኞች በዚህ ”ሕገ መንግሥት” ድጋፍ አገር አፍርሰው ሌላ አገር ለመፍጠር ሲሞክሩ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ ዜጎች ደግሞ አገር ለማፈራረስ የተሰናዳውን ”ሕገ መንግሥት” በመቃወምና ባለመቀበል ነባሯን ኢትዮጵያን፣ ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያን በተሻለ መልክ ለማስቀጠል የሚረዳ፣ ሕዝብ የመከረበትና የተቀበለው ሕገ መንግሥት እንዲኖር ይጥራሉ። የነሱ ኢትዮጵያ በጎሠኝነት ካስማ ላይ የተገነባች ሳትሆን፣ በሕዝብ ጥረትና ሕብረት፣ በመስዋዕትነት ዋጋ የተገነባች አገር ነች።

ዘረኞች የደቀቀችና የደከመች ብሎም የተበታተነች፤ ለወራሪ ጠላት የተመቸች ኢትዮጵያን ማየት፣ እነሱም የደከመ፣ ቁርጥራጭ ክልል ይዘው በውጭ እርዳታና በልመና እናድጋለን ብለው ሲመኙ፤ አገር ወዳድና በራሳቸው የሚተማመኑ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ታፍረውና ተከብረው የሚኖሩባትን፣ ይበልጥ የተባበረችና ጠንካራ አገር ለመጭው ትውልድ ማስረከብን ይመርጣሉ። ይህንን ምርጫቸውን ለማደናቀፍ የሚወጠነው ሴራ ግን ቀላል አይደለም። በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ ዜጎች ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ የግዴታ የራሳቸውን ዓላማ በቅጡ ተረድተው በአንድ ጣራ ስር መሰባሰብ ይኖርባቸዋል። ከጠላት ወረዳ ምህረት፣ ከአፍራሽ ጎራ ጥንካሬ ይገኛል ብለው መጠበቅና መዘናጋት አይኖርባቸውም። ወይም በአንዳንድ ሽርፍራፊ ጥቅም ትጥቃቸውን ሊፈቱ አይገባም። ትጥቃቸውን ባጠበቁ ቁጥር የሚያገኙት ድል ይበዛል፤ ትጥቃቸውን ካላሉና ከፈቱ ግን ያገኙትንም ያጣሉ። የአንዳንድ የታወቁ እስረኞች መፈታት በጎ ገጽ ቢኖረውም፤ አሁንም በሽህ የሚቆጠሩ ዜጎች በየቦታው እስር ቤት ውስጥ እየማቀቁ ነው፤ አገር ራሷ በጎሠኞች ገመድ ተተብትባለች። አሁንም ማፈናቀሉ፣ ማሳደዱ ግድያው እየተፈጸመ ነው። ይህ ሁሉ ግፍ በሚፈጸምበት ወቅት ላይ ሆኖ ”ጉሮ ወሸባዬ!” ብሎ መጨፈር ጨለምተኝነት ነው። የትግሉንም ዓላማ ማሳነስ ይሆናል። አሁን ትግሉ ከወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል። ጎሠኞች ሥርዓቱን ለማዳን እየተሰባሰቡ ናቸው። በተቃዋሚው በተለይም ዲያስፖራ በሚባለው ጎራ ውስጥ ያለው ወገን እገሌ ወጣ! እገሌ ወረደ! ዶ/ር ዐቢይ ይህንን አለ! እያለ በትዝብት ከማየትና በጆሮው የሚሰማውን ከማድነቅ የተለየ እራሱን ሲያጠናክር አይታይም። የተገኘው መለስተኛ ውጤትና የጠላቶቹ መፍረክረክ ብዙ ኢትዮጵያውያን በከፈሉት የሕይወት ዋጋና የእስራት ስቃይ የተዋቀረ የትግል ውጤት መሆኑን ዘንግቶ የተወሰኑ ሰዎች ፍላጎትና ስጦታ አድርጎ ቆጥሮ ያጨበጭባል። በሌላም በኩል የአንድ ድርጅት የትግል ውጤት አድርጎ የመቁጠር ወገንተኝነት ሲሰነዘርና ለግለሰቦች የሥልጣን ጎዳና ጠራጊ የመሆኑ ጭፍን ጀሌነት ሲያንጸባረቅ ይታያል።

ወቅቱ ፈታኝ ነው፤ በፖለቲካው መስክ በውዥንብር የደፈረሰ የሃሳብ ጎርፍ ይወርዳል፤ ጎርፉ ደካማውን እያግበሰበሰ በመስገር ላይ ነው። እዚያ ውስጥ ላለመስጠም ብርታትና ብስለትን ይጠይቃል። ጎርፉ እየተመመ ከሚገባበት አደገኛ ውቅያኖስ ለመዳን አቅጣጫ አመላካች (compass) ያለው የራስን ታንኳ ወይም ጀልባ ሠርቶ መቅዘፍ ያዋጣል። በሰው ጀልባ ላይ መሳፈር ዋስትና የለውም፤ ከጀልባው ባለቤት ጋር ካልተስማሙ መሃል መንገድ ላይ ጥልቀት ካለው ውሃ ውስጥ ተወርውረው ሊሰጥሙ እንደሚችሉ ማሰብ መልካም ነው። ኮምፓስ ያለው ጀልባ ማለትም ኢትዮጵያዊነት ራዕይና የፖሊሲ መመሪያ ያለው ድርጅት ማለት ነው። ዘሎ በሌላው ድንኳን ውስጥ ገብቶ አጫፋሪ መሆንን እንደ ባህል አድርገው የያዙ ድርጅቶች ካለፈው ውድቀታቸው ሊማሩ ይገባል። በአሁኑ መልክ ተበታትኖ መነሻና መድረሻውን ሳያውቁ መንጎድ ለተደራጀ ጥቃት ያጋልጣል። አሁን በመሽመድመድ ላይ ያለው የጎሠኝነት አከርካሪ እስከነጭራሹ በኢትዮጵያዊነት ክንድ ካልተሰበረ፤ ሰላምና አንድነት አይኖርም። ዜጋ ተነጥሎ የሚጠቃበትና የሚፈናቀልበት ሕግና ሥርዓት እስካለ ድረስ፤ ለውጥ አለ ብሎ ማጨብጨብጨብ ሞኝነት ነው። ለውጡም የጌታ እንጂ የሥርዓት ለውጥ አይሆንም። በልዩነት ክር የተሰፋው ባንዲራም ተወግዶ የደም ዋጋ ተከፍሎበት፣ ለሌሎች አገሮች ሳይቀር የነጻነት አርማ የሆነው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ከዳር እስከዳር እስኪውለበለብና መሰረታዊ ለውጥ እስኪመጣ ድረስ ትግሉ መቀጠል ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!

አገሬ አዲስ

ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. (04-06-2018 እ.ኤ.አ.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ