Dr. Abiy Ahmed

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

በቀለ ደገፋ

ዶ/ር ዐቢይ ጠ/ሚ ሆኖ ከተመረጠ በኋላ በበጎ የሚነሱና አንዳንዴም በዚህ ፍጥነት ይሆናሉ ተብሎ የማይጠበቁ ነገሮችን አድርጓል፤ የለማና የገዱ ከእሱ ያልተናነስ አስተዋፆ ሳይዘነጋ። ከእነዚህም ውስጥ ጎልተው የሚወጡት ስለኢትዮጵያዊነት መናገር እንደ ወንጀል መቆጠሩ ቀርቶ ሊኮራበት የሚገባና ብዙ ዋጋ የተከፈለበት መሆኑን ማሳየቱ፤ በኦሮሞ ወገኖቻችን ዘንድ የነበረውን አንዳንድ ጥርጣሬ አስውግዶ ኦሮሞ ከሌላው ሕዝብ እኩል መሥዋዕትነት ከፍሎ ባቆያት አገር ውስጥ ሆኖ የፍትሕና የእኩልነት ጥያቄውን ማስመለስ እንደሚችል ማሳየቱ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉ ወገኖቻችንን ከእስር እንዲፈቱ ማድረግ፤ ለዚህም አንዳርጋቸው ፅጌን ከመፍታት የበለጠ ምንም ዐይነት ማስረጃ አያስፈልግም። አንዳርጋቸው ምንም እንኳን ምርጥ የፍትሕና የእኩልነት ታጋይ ቢሆንም፤ ከመረጠው የትግል መንገድ አንጻር እንዲፈታ መደረጉ በቀላሉ ሊታይ አይገባውም። ለለውጥ ያለውን ቁርጠኝነት ያመላክታል። ቂመኞቹ አሁንም ከአገር አንጋግተው ሊያባርሩት ሲያሴሩ ዶ/ር ዐቢይ በክብር ቤተመንግሥት ጠርቶ በማናገሩ ያልተደመመ ያለ አይመስለኝም። የታሰሩትን ከመፍታት በተጨማሪ በተፈበረከ የአሸባሪነት ክስ ለስደት የተዳረጉ ምርጥ ኢትዮጵያዊያንን ክስ ማንሳትና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረቡ ሌላው ወሳኝ እርምጃ ነው።

በዚች ሁለት ወር ውስጥ ከአደረጋቸው ንግግሮችና ተግባራት ዶ/ር ዐቢይ እንደ ግለሰብ ቅን አሳቢ ኢትዮጵያዊና ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው መረዳት ይቻላል። የኢሕአዴግ ቡራኬ የማያስፈልጋቸውና አስተዳደራዊ የሆኑ አንድ ጠ/ሚ በራሱ ሊያደርጋቸው በሚችላቸው ነገሮች ላይ እያሳየ ያለው ይህንኑ ነው። ከፍላጎት ከቅን አሳቢነትና አስተዳደራዊ የጥገና ለውጥ ከማድረግ በዘለለ የሚመራውን ድርጅት አሳምኖ የፖሊሲና የሕግ ለውጥ የማድረግ ሙሉ ሥልጣን አለው ወይንስ የለውም የሚለው በእስከ አሁን አካሄዱ በተደሰቱ በርካታ (እኔን ጨምሮ) ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

የዚህ ጥያቄ መልስ በሂደት የሚታይ ቢሆንም፤ አሁን እየተደረጉ ያሉ ነገሮች ከሞላ ጎደል (በንግግር ደረጃ እንኳን የፖሊሲ ለውጥ ሃሳብ አለመቅረብ) ጥገናዊ የአስተዳደር ለውጥ መሆናቸው ሲታይ ሥልጣኑን ለመጠቅለል ያላለቀ ውስጣዊ ትግል እንደሚጠብቀው መረዳት ይቻላል። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥልጣን ከመጣበት መንገድ አንጻር ከበቂ በላይ እንቅስቃሴ ማድረጉን ግን መካድ አይቻልም። በአሁኑ ሰዓት ዋናው ቀም ነገር መሆን ያለበት ያለውን ሥልጣንስ በአግባቡ እየተጠቀመው ነው አይደለም የሚለው ነው። የእሱን ወደ ሥልጣን መምጣት የተቃወሙ አካልትን ብዙም ሳያስከፋ የራሱን የድጋፍ መሰረት ለማስፋትና ለማጠናከር እየተጠቀመበት ይመስላል። ከዚም አንጻር ድጋፍ የሚጨምሩለትን ኃይለማርያም ደሳለኝ ለዓመታት ያላደረጋቸውን ነገሮች በሁለት ወር ውስጥ አድርጓል። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በሕዝብ ኃይል ወደ ሥልጣን የመጣና አሁንም ከፍተኛ ድጋፍ ያለውን ሰው መሉ ሥልጣን አይኖርህም የሚል ሥርዓት ሊኖር አይችልም። አብዛኛው ሕዝብም የለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠል ጊዜና ድጋፍ ሊሰጠው እንደሚገባ ይስማማል።

እስከ አሁን የተደረጉ በጎ ጅማሬዎች እውነተኛ ፈተና የሚጠብቃቸው በቀጣዩ ምርጫ ነው። ከሁለት ዓመት በኋላ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ ዶ/ር ዐቢይና የለውጥ ኃይሉ የሚፈተኑበት የመጀመሪያ መድረክ ይሆናል። ከምርጫው ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን እናያለን፤

ሀ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚስተናገዱበት ሁኔታ

የመጀመሪያው ፈተና የሚሆነው፤ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁኔታዎችን እናመቻቻለን ተብሎ የተገባውን ቃል ማክበር አለማክበር ሲሆን፤ ለዚህ እንደጥሩ ምልክት ሊታዩ የሚችሉ ነገሮች ተደርገዋል። ከእነዚህም መካከል ፖለቲከኞችን ከእስር መፍታት፤ የፖለቲካ መሪዎችን ቤተመንግሥት ድረስ ጋብዞ ማናገር፤ ለዓመታት አሸባሪ ተብለው በስደት ሲኖሩ የነበሩ የፖለቲካ መሪዎች ወደ አገር እንዲመለሱ መፍቀድ።

እነዚህ በሙሉ እንደ መልካም ጅማሬ የሚታዩ ሲሆን፣ ዋናው ፈተና ግን፤ በዴሞክራሲያው ለውጥ ተስፋ ቆርጠውና ተገደው መሣሪያ ያነሱትንና ሌሎችም በስደት ያሉ ፖለቲከኞችን በአገር ውስጥ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ። ለዚህም በተናጠል ከእያንዳንዱ ቡድን ጋር ድርድር ማድረግ ሳያስፈልግ፤ የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ማንኛውም አካላት በነጻነት የመንቀሳቀስ ዋስትና መስጠትና ምርጫ ቦርድን ገለልተኛ እንዲሆን ማድረግ። ይሄ ካልተደረገ ዞረን ዞረን እዚያው ነው የሚሆነው።

ለ፤ ምርጫው መቼ መካሄድ አለበት?

እውነተኛ የውድድር መድረክ የሚፈጠር ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው ምርጫው ቀድሞ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መካሄድ አለበት ወይንስ ቢራዘም ይሻላል የሚለው ይሆናል። ሁለት ዓመት ብቻ የቀረው ምርጫ ለአዲሱ አስተዳደርም ይሁን ለዓመታት ተገፈተው ለኖሩ ተፈካካሪ ፓርቲዎች በቂ የመዘጋጃ ጊዜ አይሰጥም ብለው የሚከራከሩ አሉ። አገሪቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት ካሳለፈችው ቀውስ አንጻር በቂ የማረጋጋት ሥራ ተሠርቶ ሙሉ ፊትን ወደ ምርጫ ማዞር ቀላል አይሆንም። ከሁሉም ወገን በኩል በደንብ ካልተያዘ ለሌላ ቀውስም ሊጋብዝ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ያደፈጡ ወያኔዎች በምርጫ ሰበብ ገና ኦሕዴድና ብአዴን የጠነከረ ድጋፍ ከመፍጠራቸው በፊት አዳክሞ ከጨዋታ ውጭ የማድረግ ስጋት አለ። በሌላ በኩል ደግሞ የለማና የደጉ ቡድን አሁን እያገኙ ካለው ድጋፍ አንጻር የምርጫ ጊዜው ማጠር እንዲያውም እነሱን የበለጠ ይጠቀማሉ የሚሉ አሉ። ምርጫው ከሚካሄድበት ሁኔታ ባልተናነሰ መቼ የሚለውም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ሐ፤ የለማ ቡድን ተወዳጅነትና ሕዝቡ ለሚመሩት ድርጅት ያለው ጥላቻ

ምርጭው ተራዘመም አልተራዘመም በፓርላሜንታዊ ሥርዓት መሪዎችን በምትመርጥ አገር ውስጥ የግለሰቦች ተወዳጅነት የራሳቸውን የመመረጥ ዕድል ከማስፋት ባለፈ የሚመሩትን ፓርቲ ለውጤት ማብቃታቸው አስተማማኝ አይደለም። በኢሕአዴግ የ27 ዓመት የሥልጣን ጊዜ ተራውን እየተጠበቀ በደል ያልደረሰበት የሕብረተሰብ ክፍል አይኖርም። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ መጠነኛ የሆነ ነጻነት ቢሰጠው ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ከመምረጥ ወደ ኋላ አይልም። ለዚህም ጥሪ ምሳሌ የሚሆነው በ97ቱ ምርጫ የአርከበ ተወዳጅነት ኢሕአዴግን ከቅንጅት ማዕበል ሊያድነው አለመቻሉ ነው።

ቀጣዩ ምርጫ አዲሱን አስተዳደር መጀመሪያ የሚጠበቀው መሰናከል ሲሆን፣ ምርጫው የሚካሄድበት ሁኔታና ጊዜ በከፍተኛ የሕዝብ መሥዋዕትነት የተገኘን የተስፋ ብልጭታ እንዳያጨልም ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአጭር ጊዜ የሥልጣን ሽሚያ ሳይሆን፤ ዘለቄታዊ ለሆነ ዴሞክሪያሲያዊ ሥርዓት ግንባት ሊጠቀሙበት ይገባል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!