Ethiopian Airlines for sale

ይሸጣሉ ከተባሉት የሕዝብ ንብረቶች አንዱ የኾነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ዮፍታሔ

ትሕነግ (የትግራይ ሕዝብ ነጻአውጭ ግንባር / ሕወሓት/ወያኔ) እብሪተኛ፣ ስግብግብ፣ ሕዝብን የምትጠላና ችግር ለመፍታት እውቀት የሌላት ድርጅት በመሆኗ እንጂ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ችግር አስከፊነት ከፖለቲካው የማይተናነስ መሆኑን በመግለጽ መፍትሔውንም የጠቆሙ በርካቶች ናቸው።

የቅርቡን እንኳን ብንመለከት ለአገሮች ዓመታዊ የኢኮኖሚ ሪፖርት ካርድ በመስጠት የሚታወቀው Fitch የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ባለፈው ዓመት June 8, 2017 ስለኢትዮጵያ ባወጣው ዘገባ በውጭ ንግድ፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በዕዳ ጫና፣ በመንግሥት በተያዙት ድርጅቶች ሙስናና ምዝበራ ... ወዘተ ያለውን ችግር አሳሳቢነት ጠቅሶ፤ እነዚህ ችግሮች ካልተስተካከሉና አሁን ያለው በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ኢኮኖሚ በፍጥነት በሌላ ሴክተር (ኢንዱስትሪ) ካልተተካ በስተቀር የከፋ ችግር እንደሚከተል አስጠንቅቆ ነበር።

እጅግ ከፍተኛ የአገር ጥሪትና በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ብድር የፈሰሰበትን የባቡሩን ሥራ በሚመለከት ደግሞ፤ ሁለት የታወቁ የውጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ኢትዮጵያ ድረስ በመሄድ ከመረመሩ በኋላ፣ የባቡሩ ሥራ በዕዳ የተተበተበ ብቻ ሳይሆን ወለዱን እንኳን መክፈል ባለመቻሉ የመሸጥ አደጋ እንዳንዣበበበት ሁለት ክፍል ያለው ዘገባ እ.ኤ.አ. February 13 እና 22, 2018 አስነብበው ነበር።

ትሕነግ ግን ይህንን ሁሉ ደብቃ በመጭዎቹ ዓመታትም ሁለት አኀዝ ኢኮኖሚ እድገቱን እናስቀጥላለን በሚል ፕሮፖጋንዳ ተሰማርታ ቆይታለች።

አሁን ግን ትሕነግ ዶ/ር ዐቢይን በማስደንገጥ የአገር ምልክትና ሀብት የሆኑትን ቴሌን፣ አየር መንገድንና መብራት ኃይልን የመሳሰሉትን ድርጅቶች በአክሲዮን መልክ በቁጥጥሯ ሥር ለማድረግ ሲባል የአገሪቱን የኢኮኖሚ ገበና አደባባይ ላይ አውጥታዋለች። በመጋረጃ ጀርባ ከሚደረገው በተጨማሪ በዚህ ሳምንት ሪፖርት ያቀረበው የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ ኢኮኖሚው ያለበትን ችግር ከመቼውም ጊዜ በላይ አጉልቶ በማውሳት ሲወተውትና የውጭ ዕዳን ለመክፈል ዋናው መፍትሔ ከሕዝቡ ላይ ግብር በስፋት መሰብሰብ እንደሆነ የ“መፍትሔ” ሐሳብ ሲያቀርብ እንደነበር የሚታወስ ነው። ከዚያ በፊት ጠቅላይ ኦዲተሩ በመንግሥት ድርጅቶች እየተመዘበረና እየባከነ ስላለው ገንዘብ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፤ የችግሩን አሳሳቢነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንከር ባለ ቋንቋ “ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተመሳሳይ ሪፖርት እያቀረብኩ ስለሆነ እንድትሰሙኝ እፈልጋለሁ” በማለት መግለጹ የሚታወስ ነው። ይህን ለመናገር ለምን 9ኛ ሪፖርት ላይ እስኪደርስ መጠበቅ እንደነበረበትና አሁን ለምን መናገር እንዳስፈለገው ግን አልገለጸም።

የትሕነግ ስሌት በአንድ በኩል ባላት የኢኮኖሚ መረብ በሕዝብና በመንግሥት ላይ አሻጥር (sabotage) መፈጸም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት በኢኮኖሚው ላይ መወጠርና ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ ኢኮኖሚያዊ ርምጃዎችን እንዲወስድ መገፋፋት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ትሕነግ በግልም ሆነ በድርጅት መልክ አሁን ያላትን የኢኮኖሚ የበላይነት ተጠቅማ እነዚህን ድርጅቶች በሙሉና በከፊል በመቆጣጠር እንደ ደቡብ አፍሪካ ነጮች ኢኮኖሚውን የፖለቲካ የበላይነት ማስቀጠያ ማድረግ ነው።

የኢኮኖሚውን ችግር ከመሥሪያ ቤቶች ብክነትና ከጉዞ ወጪዎች ቁጠባ ጀምሮ መቋቋም እንደሚገባ በማስገንዘብ የተነሣው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባድመን አሳልፎ ለኤርትራ የመስጠቱ ውሳኔ በሙሉም ባይሆን በከፊል ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ይመስላል። ዶ/ር ዐቢይ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት "ሞት አልባ ጦርነት" መባል ነው ያለበት በማለት የገለጸው ከሰላም ማጣቱ ባሻገር በዚያ መስመር ለወታደራዊ ዝግጅት፣ ሥልጠናና ስለላ የሚፈሰውን የአገር ሀብት ለመጠቆም እንደሆነ አያጠራጥርም። ከዚህም በተጨማሪ አገራችንን ካጋጠማት እጅግ አንገብጋቢ የወደብ ችግር በመነሣት የሚፈጠረው ሰላም በሂደት አሰብን ለመጠቀም ዕድል ሊያስገኝ ይችላል ከሚል ሊሆን ይችላል። የምሥራቅ አፍሪካ ተንታኙ ፕሮፌሰር መድኃኔ የባድመን ውሳኔ በሚመለከት በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ በተደጋጋሚ የገለጸው ነገር ቢኖር ከሰላም ባሻገር “ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር” የውሳኔው ዋና ዓላማ እንደሆነ ነው። ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ፈጽሞ ሊኖሩ አይችሉም ባይባልም፤ እንደጅቡቲና ሶማሊያ ሁሉ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሚኖር ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር በዋናነት አሰብን ከመጠቀም የተለየ ሊሆን አይችልም። ለውሳኔው ከነዚህ የተሻለ ሌላ አገራዊ ምክንያቶች ለማሰብ አስቸጋሪ ነው። ውሳኔው ለምን አሁን? ለሚለው ግን እነዚህም በቂ ምክንያቶች አይደሉም። ምክንያቱም ሁለቱም ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የኤርትራን መንግሥት መልካም ምላሽ እስካላገኙ ድረስ ተፈጻሚነት አይኖራቸውምና። አሁን እንደተደረገው በጥድፊያ ሳይሆን ሕዝብ መክሮበትና ለጉዳዩ ጊዜ ተሰጥቶት በድርድር ከተካሄደ ግን የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ የሚችልበት ዕድል ይኖራል።

ዶ/ር ዐቢይ ጠንካራና ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ያስፈልጉታል። ኢኮኖሚ ሳይንስ ነው። ለየችግሩ መፍትሔው ሁሌም ተመሳሳይ ካለመሆኑም በላይ እንደችግሩ ሁኔታና እንደየአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። ድርጅቶች ነፃ (liberalize) እና በገበያ ኢኮኖሚው የሚመሩ መደረጋቸው ጠቃሚ ነው። ሆኖም ይህ ከመከናወኑ በፊት በአገራችን የሚገኘው የገበያ፣ የውድድርና የቢሮክራሲ ሥርዓት አሁን ከሚገኝበት እጅግ ወገናዊ ድብቅና የተጭበረበረ መንገድ ወጥቶ ፍትሐዊ፣ ሁሉን ተደራሽ፣ ሁሉን አሳታፊ፣ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መዋቀር ይኖርበታል። ከዚያም እነዚህ ድርጅቶች ገለልተኛ በሆነ ዓለም አቀፋዊ/ አገራዊ አካል በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ ወደግል የሚዞሩበት ሁኔታ ቢመቻች አገርና ወገን ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህም በኢኮኖሚው፣ በሕዝቡ ፍላጎትና፣ በየድርጅቶቹ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ሕይወት ላይ የጎላ ቀውስ ሳይፈጠር ሽግግሩን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲከናወን ያደርገዋል። መታወቅ ያለበት እንዲህም ሆኖ ከፍተኛ የአገር ሀብት የሆኑትን ትላልቅ ድርጅቶች በከፊልና በሙሉ መሸጥ አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የዕዳ ጫና ላያቃልለው የሚችል መሆኑ ነው።

አሁን የተፈጠረውን አንገብጋቢ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ሆነ የዕዳ ክፍያ በሚመለከት ፈጣን መፍትሔ ከሆኑት መካከል በባለሥልጣናት አማካኝነት በውጭ ባንኮች ተቀምጦ የሚገኘውን ገንዘብ ማስመለስ የአንድ ሰሞን ብቻ ርዕስ ሆኖ መቅረት አይኖርበትም። እውነተኛ ጥረት ተደርጎ ይህ ከአገር የኮበለለ በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ መመለስ ይኖርበታል።

ከዚህም በተጨማሪ ለዳያስፖራው ወዳገሩ እንዲገባና በአገሩ ጉዳይ እንዲሳተፍ በቴሌቪዥን በኩል በስማ በለው ከሚደረግ ጥሪ ባለፈ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ራሳቸው በአካል በአሜሪካ (ዋሽንግተን ዲሲ)፣ ካናዳ (ቶሮንቶ) እና እንግሊዝ (ለንደን) ተገኝተው ስለችግሩ ዳያስፖራውን በግልጽ በማነጋገር ከጎናቸው እንዲቆም ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በሕዝብ ላይ በፈጸሙት ክፉ ሥራና ከትሕነግ ጋራ ባላቸው የሴራ ግንኙነት የተጠሉትን ካሣ ተከለብርሃንን፣ የለንደኑንም ሆነ የኦታዋ አምባሳደሮች ወደዳያስፖራው በመላክና እነዚያኑ ተመሳሳይ “የቤት ልጅ ዳያስፖራዎች” ሰብስቦ ዘገባ በመሥራት ሳይሆን፤ እውነተኛውንና ከጥቅም ባለፈ ለአገር የሚቆረቆረውን መላውን ዳያስፖራ ማሰለፍ የሚቻለው ርስዎ ራስዎ ለጊዜው በነዚህ ሦስት ከተሞች (ዲሲ፣ ቶሮንቶና ለንደን) ተገኝተው ችግሩን በሚገባ አፍረጥርጠው በግልጽ ሲጋብዙ ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተጉዘው በየከተሞቹ መድረስ እንዲችሉ አስቀድመው ቀናቱ ታውቀው ቅስቀሳ መደረጉ ይጠቅማል። ይህን ካደረጉ በዳያስፖራው በኩል በፍጹም ያልጠበቁት ትብብር እንደሚያገኙና ያም ለጊዜው ያጋጠመውን ችግር የሚቀርፍ ብቻ ሳይሆን፤ ለዘላቂ ዕቅድዎና የአገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ቅንጣት ታክል ሊጠራጠሩ አይገባም። ወያኔ 27 ዓመት ሙሉ ዳያስፖራውን በጅምላ ለማስጠላትና ከሕዝብ ለመነጠል ሲል እንደአገር ጠላት፣ እንደሽብርተኞች ተባባሪ፣ ለአገሩ ግድ እንደሌለው፣ ወገኑን እንደሚንቅ፣ እንደ ጥቅመኛ፣ እንደ ሥራፈት፣ በመንግሥት ርዳታ እንደሚተዳደር፣ በሱስ እንደተተበተበ ወዘተ በማድረግ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ያስተጋባውን ርካሽና አንዳችም ጥናታዊ መሠረት የሌለው ፕሮፖጋንዳ ከሕዝቡም ሆነ ከርስዎ አእምሮ ማውጣት እጅግ አስፈላጊ ነው። በየኤምባሲው በኩል ስለዳያስፖራው የሚደርስዎትንም ሪፖርት በጥንቃቄ ማየትና ከዳያስፖራው ጋር የሚደረገው ግንኙነት በጠላትነት፣ በስለላና በጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ቀርቶ፤ በወገናዊነት፣ በመግባባትና በመደጋገፍ ላይ መመሥረት ይኖርበታል። ዳያስፖራው በሚኖርበት አገር የሰፈነው ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና በትውልድ አገሩ የሌለ በመሆኑ ቁጭት የሚያንገበግበውና በየዓመቱ ለቤተዘመዶቹ በሚልከው 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ቤተሰቦቹንና አገርን የሚደግፍ ነው። ከዚህ የመጨመርና የሚቀነስ ነገር የለውም። ለቤተሰቦቹ ብቻ በሚልከው ይህን ማድረግ ከቻለ በአገሩ ልማት ላይ ቀጥታ ተሳታፊ ቢሆን ምን ሊያበረክት እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።

በሌላ በኩል ዕዳውን በሚመለከት በሌሎችም አገሮች እንደተለመደው አገራችን የምትገኝበትን የሽግግርና የዕዳ ክምችት ግምት ውስጥ በማስገባት ብድር እንዲሰረዝላት ጥረት መደረግ ይኖርበታል። አንዳንድ ከፍተኛ ወለድ ያላቸውን ብድሮች ደግሞ የተሻለ ወለድ ባላቸው ብድሮች መተካት ወይም የተለያዩ ብድሮችን አከፋፈል ወደአንድ በማጠቃለልና ብድሩ የሚከፈልበትን ጊዜ በማራዘም እፎይታ ለማግኘት ይቻላል። በመሠረተ ልማት ግንባታዎች የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በኢንዱስትሪ ግንባታም ሆነ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ መስኮች በኩል ለመረከብ አስተማማኝ ሁኔታ ሳይፈጠር በየቦታው የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ ማስቆም ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳያመዝን የተጀመሩት አልቀው ወደአገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ የተሻለ ሊሆን ይችላል።

ይኸው ነው!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!