የወያኔ ጎምቱ አመራሮች

የወያኔ/ሕወሓት ጎምቱና በዕድሜና በአስተሳሰብ ያረጁ መሪዎች

ክንፉ አሰፋ

የሕወሓት መግለጫ በመስመሮች መካከል ሲነበብ በተቀማ ጩኸት ሊመስል ይችላል። ከመቀሌው ዱለታ በስተጀርባ የነበሩ እውነታዎችን ለመዳሰስ የፖለቲካ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም። ሕወሓቶች አብረው ወስነው ያስተላለፉትን ጉዳይ እንደመጋዣ አኝከው ሲያበቁ፤ ከብዙ ገጽ የክስ ቻርጅ ጋር ብቅ ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩን ለማስጠቆር የሄዱበት ርቀት ግልጽና መሳጭ ነው። ሰማይ ወጥተው ቁልቁል ቢወርዱም ግን፤ ከቶውንም የሕዝብ ቀልብ ሊስቡ አይችሉም። እኛ ከሌለን አገር ትጠፋለች ይሉት የነበረው ቁንጽል እሳቤ፤ እነሆ ፉርሽ ሲሆንባቸው፤ አዲስ ካርታ መዘዙ። የአዲሱ ትውልድ መሪዎች፤ ሕዝብን በኃይል ሳይሆን በፍቅር መምራት እንደሚቻል ሲያሳዩዋቸው፣ ወደ ኦሪት ዞር ብለው ከዘፍጥረት መጀመራቸው ይሆን? በአዲሱ ዜማቸው፤ ኢትዮጵያን ትተው ስለ ትግራይ መጮህ የያዙ ይመስላል።

"ለነባር አመራሮቻችን እውቅና ይሰጥ" የምትለዋ ሐረግ ግን ብዙዎችን አስደምማለች። እውቅናውስ ይሰጥ። ግን ማን ነው ሰጭው? ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወይንስ የአሜሪካ መንግሥት?

እውቅና ሲሉስ ምን ማለታቸው ይሆን? ሰዎቹ ያካበቱት እና የተካኑበት ነገር ቢኖር ሱስና ዝርፊያ ነው። ለሌብነት የሚሰጥ የሥራ ፍቃድ ማለታቸው ይሆን? የቃሉ ሰምና ወርቅ ፍቺ ይህ ከሆነ፤ ጥያቄው በአግባቡ መታየት አለበት። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አግባብ።

ሰጭው እና ከልካዩ ዶ/ር ዐቢይ ከሆኑ ግን ለ27 ዓመታት ሳይታክቱ አገር በመዝረፍና ዜጋን በመግደል፤ ላደረጉት አስተዋጽዖ ከዝምታ ይልቅ እውቅናውን ቢሰጡ ይመረጣል። ጥያቄውን ተቀብለው በአቃቤ ሕግ በኩል ቢያሳውቁ፤ ከእንደዚህ ዐይነት ክስ ይድኑ ይሆናል።

እጃቸው ላይ በከንቱ የፈሰሰ የንጹኀን ደም እና የሕዝብ ሀብት መያዛቸውን ለአፍታ እንኳ ዘንግተው፤ ለወንጀላቸው እውቅና ሲጠይቁ እፍረት እንኳ አይታይባቸውም። ክብር ለሚገባው ክብር ይሰጠዋል። የዘረፈ እና የገደለ ደግሞ ለፍርድ ይቀርባል። “ዘመኑ የይቅርታ እና የፍቅር ነው” በሚል እሳቤ ቅሊንጦና ዝዋይ የሚገባቸውን ሌቦች፤ በማክበር በጡረታ ስለሸኙዋቸው ብቻ መቀለድ ጀመሩ። ግዜውን ሳይዋጁ መቀለድ ደግሞ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ሕጻን ልጅም መገመት አያቅተውም።

መንጌ በአንድ ወቅት ካቢኔውን ሰብስቦ፡ "ወደዳችሁም-ጠላችሁ፣ ይህ ሕዝብ የምትነዱትን መኪና፣ የምትኖሩትን ሕይወት፣ የምትኖሩበትን ቤት ... ጠንቅቆ ያውቃል” ብሏቸው ነበር። አንዳንዶች ዝቅ ብለው ሌሎች ደግሞ ከፍ ብለው ይብረሩ እንጂ፤ ከሕዝብ ራዳር ውጭ ያለመሆናቸውን ገና የባነኑ አይመስልም።

ዛሬ ደርሰው ይህን ሲሉ፤ ይህ ግዜ የሚሉት ተረኛ በማማው ላይ ከፍ አርጎ ስላስቀመጣቸው ብቻ ሕዝብን በጅምላ ናቁት። ወገንም እያየ እንዳላየ፤ እየሰማ እንዳላዳመጠ እንጂ የጠጡትን ውስኪ፣የዘረፉትን ዶላር፤ ምን ያህል እንደዘረፉ፣ ዶላሩን ያስቀመመጡበት አገር ጭምር ያውቃል። ይህ ሕዝብ ግዜ ይሰጠው ቅል ዐይነት እንዲያው ዝም ይበል እንጂ፤ በነሱ የተገደለን ዜጋ ሁሉ፤ የተሰቃየና በግፍ የታሰረውን ሁሉ በቁጥርም ያውቀዋል።

እንደ ሞዴል አርሶ አደር “እውቅና ይሰጠን” አሉ። ጥሩ ጥያቄ ነው። ግን ምን አስቸኮላቸው። ግዜው ሲደርስ፤ ሪከርዳቸሁ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ከፍሪደም ሃውስ ዳታቤዝ ውስጥ እየወጣ እውቅናውን ያከናንባቸው የለ?

ጥቂቶች ብቻ ይዘውሩት የነበረ መልኅቅ አልባ መርከብ፤ በባሕር ሞገዶችና ከጎን በሚነፍሱ ወጀቦች ክፉኛ ሲወዘወዝ በግልጽ ይታያል። መርኅ አልባ ያሉት ጉድኝት፤ ራሳቸውን ቆላልፎ ፍጹም ከማይወጡበት ማጥ ቢዶላቸውም፤ ካሁን በኋላ የኋሊዮሽ ሊመለስ ከቶም እንደማይሻ ግን ገና የተረዱት አይመስልም።

እርግጥ ነው። ሕወሓቶች ተከፋፍለዋል። ስለዚህም ከሕዝብ ጋር በጀመሩት ሌባና ፖሊስ ጨዋታ ብዙ ሊገፉበት አልቻሉም።

“አውሬውን አቁስለነዋል!” ብለው ነበር ኦቦ ለማ መገርሳ። አውሬው ቲም ለማን መልሶ ለማጥቃት ቁስሉ እስኪሽርለት እንኳን አልጠበቀም።

የዘረፋ ቡድን መቀሌ ላይ መሽጎ ሲዶልት የነበረውን ሁሉ አደባባይ አውጥቶታል። በመቀሌው የግንቦት 20 የፓናል ውይይት ላይ ሕላዌ ዮሴፍ፣ ጌታቸው ረዳና ስዩም መስፍን የተናገሩት አስደምሞን ሳያበቃ፤ እነሆ “ያሁኑ ይባስ” የሚያስብል መግለጫ ጀባ ብለውናል። አስቀድሞ በነ ሕላዌ ዮሴፍ፤ በነ ስዩም መስፍን ማማሟቂያ ተለቀቀ። ሕላዌ ዮሴፍ ቋንቋችንን ተቀማን፤ “ጽንፈኛ፣ ሽብርተኛ፣ አክራሪ፤ ወዘተ” ብለን ለመሳደብ የምንሳቀቅበት ዘመን ደረስን ሲል ነበር ያማረረው። ኢትዮጵያ ብለው ለመጥራት የሚጸየፏትን አገር ለሃያ ሰባት ዓመታት መግዛታቸው ሳያንስ፤ ሕዝቧ ላይ ለምን አልተሳለቅንም ሲሉ ቀለዱብን።

የሕወሓቱ መግለጫ፤ በአንድ እጁ ጎራዴ በሌላ እጁ የመላእክትን ስዕል ይዞ እንደሚለምን ተመጽዋች ዐይነት ነው። በልመና ሐረጎች ታጭቋል። ኢሕአዴግ ተሰብስቦ ይምከርም ይላል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሳይሸራረፍ እንዲቀጥል በተማጽኖ ይጠይቅና እዚያው ላይ የጦርነት ጥሪ ሊያስተላልፍ ይሞክራል። "የትግራይ ሕዝብን ሰላም ለመረበሽ እየተደረጉ ያሉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሶች ሕወሓት ከሕዝቡ ጋር በመሆን በፅናት ለመታገል ወስኗል።" ይለናል። በእርግጥ ደጀን ያሉት ትግራይ ሕዝብ፤ ለነዚህ ቡድኖች የሥልጣን ሱስ ብሎ ዳግም ልጆቹን ይገብራል ብለው ማሰባቸው ሕዝቡን መናቅ አይሆንም? ይህንን ሕዝብ ከስንቱ ጋር ሊያጋጩት አቅደው ይሆን?

በብሔራዊ ቴሌቭዥን ላይ የለቀቁትን ሰበር መግለጫ፤ “አንቺው ታመጭው አንቺው ታሮጭው” ሆነና ግራ አጋባን። ለመሆኑ ሕወሓት ስንት ነው? የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ሆኖ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያስተላለፈው ሕወሓት መቸም ከማርስ አልመጣም።

ጫወታው ወዲህ ነው። እነሱ ለመግደል የሞከሩትን ኢትዮጵያዊነት፤ እነሱ ያንቋሸሹትን የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ቲም ለማ ከፍ አድርጎ ሲያነሳ እና ታሪኩን በደማቅ ቀለም ሲጽፍ፤ ፊታቸው ጠቆረ። ዐይናቸውም ደም ለበሰ። ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢ እያሉ ያሞካሹት የነበረ ሥራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የተደራጀ ሌብነት” በሚል አደባባይ ላይ ሲሰጣ አላስደሰታቸውም። “ልማታዊ መስመራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አደጋ ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል።” ማለታቸው ይህንን ያመላክታል። በአገሪቱ ብሩህ ነገር መታየቱም አስጨንቋቸዋል፤ አመራሩ ከገዢነት ወደ መሪነት መቀየሩ አስደንግጧቸዋል።

የሕወሓት መግለጫ በዶ/ር ዐቢይ ላይ ብቻ ሳይሆን በአገር ላይ የታወጀ ጦርነት ነው። ከአስር የማይበልጡ ሌቦች ያወጁት ጦርነት። የፍጻሜ ጦርነት።

መግለጫው ሲደመድም፤ "ወቅታዊ ሁኔታውን በፍጥነት ለማየት እና ለመገምገም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚና ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።" ይላል።

ከዚህ ቀደም እንዲህ ዐይነት መግልጫ እንሰማ የነበረው ከተቃዋሚዎች ነበር። እነሆ ዘመን አልፎ ይህን ለቅሶ ከሕወሓት ያሰማን ጀመር። ተመስገን ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን አንድ መልካም እድል ገጥሞታል። ሕወሓቶች ቢያውቁበት ይህ መልካም እድል እነሱንም ነጻ ያወጣቸው ነበር። ይህንን እድል በሁለት እጃቸው ከመቀበል ይልቅ ሲያጣጥሉት እና ሊያኮላሹ ሲሞክሩ ማየቱ የበለጠ ያሳምማል። አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል እንዲሉ፤ ይህንን ሕዝብ ባይፈታተኑት የሚበጃቸው ይሆናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!