PM. Dr. Abiy Ahmed addressing the parliament

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ንግግር ባደረጉ ጊዜ

ነፃነት ዘለቀ

“ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” ይባላል። ይሁንና እንዳለመታደል ሆኖ በኔ ዕድሜ ይህ አባባል እውን ሲሆን ማየት አልቻልኩም። ከአሁን በኋላ ግን ተስፋ ያለኝ ይመስለኛል። ዕድሜ ለዕንባ አባሹ አንድዬ!

ወያኔ ከየሥርቻው ለቃቅሞ አራት ኪሎ ፓርላማ ያስገባቸውን ዜጎች ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩር ብዬ ያየኋቸው ገና ትናንት ነበር - ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም። ቁም ነገር አገኛለሁ ብዬ ኢቲቪን መቼም ቢሆን አልመለከትም። ውሸትና ግነት በልቦለድ ዓለም እንጂ በእውነተኛው ሕይወት እንዲህ እንደኢቲቪ በዝቶ ሲገኝ ያስጠላልና በኢቲቪ ቱሪናፋ አንጎሌን ማዞር አልፈልግም ብዬ ትቸው ነበር። ትናንት ግን አንድ ጓደኛየ ስልክ ደውሎ የዶ/ር ዐቢይን የፓርላማ ንግግር እንዳዳምጥ ጎተጎተኝ። እያየሁት የነበረውን የእንግሊዝንና የቱኒዝያን የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ ትቼ ወዲያው ወደ ኢቲቪ ዞርሁ። የሚገርመው ነገር ቲቪውን ስከፍት እየተነገረ የነበረው ጓደኛየ የነገረኝ የአንዲት ወያኔ የፓርላማ አባል ጥያቄና የጠ/ሚኒስትሩ መልስ ነበር። ከዚያን በፊት የነበረው አምልጦኛል። ከዚያ በኋላ የነበረውን ግን ተከታትየዋለሁ። በጣም አስደሳች ነበር። በማግሥቱም ደገምኩት - እንደሚወዱት ሙዚቃ እየተደጋገመ ቢደመጥ የማይሰለች ገለጻና ማብራሪያ ነው፤ መሪ ማለት እንደዚህ ነው።

የፓርላማ አባላቱን ለቅጽበት ቃኘኋቸው። እኛን የሚወክሉ እንደመሆናቸው በነሱ ውስጥ እኛን አየሁ። እስከዚህን ድረስ መጎሰቆላችንን አላውቅም ነበር። በአእምሮየ የመጣልኝ ነገር ቢኖር ውድቀታችን ሊሸፈን ወይ ሊስተባበል የማይችል ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ ነው።

የፓርላማ አባላቱ ወያኔ ኢትዮጵያን የመዝረፍና የማፈራረስ ሤራውን ለማሳካት እንዲያመቸው ብሎ ከትምህርትም ከዕውቀትም ከግንዛቤም ከምንም ከምንም የፀዱ ማይማንን መርጦ የጎለታቸው ናቸው። ዋነኛ ሥራቸውም እንደሚታወቀው ማጨብጨብ ነው። ነቃ ያሉት ደግሞ ከነገሩ ጦም እደሩ ብለው በጦፈ የጭብጭባ ወቅት ሳይቀር ዕንቅልፋቸውን የሚደቁ ናቸው። የአውሮፓንና የአሜሪካንን ፓርላማ የሚያውቅ ሰው በነዚህ የፓርላማ ተብዬ አባላት ምን ያህል እንደሚያፍር ግልጽ ነው። እኔ እጅግ አፍራለሁ፤ በወያኔ መናቄም እየታየኝ እነሱን ባሰብኩ ቁጥር እሳቀቃለሁ።

ከሰው መርጦ ለሹመት ዛሬ የለም። ከእንጨት መርጦ ለታቦትም ዛሬ የለም። ፖለቲካውም ሃይማኖቱም በማይረቡ ወሮበላ ሰዎች ተጠልፎ እንዳይሆን ሆኗል። ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራልና የመንደር አውደልዳይ የፓርላማ አባል ይሆናል። ባዶ ጭንቅላት የያዘች የሠፈር ተርቲበኛ የፓርላማ አባል ትሆናለች። ወይራና ዝግባ ተንቀው እምባጮና ብሣና ታቦት ሆነዋል። ምሥጢረ መለኮት በአልባሌ ሰዎች ይዋረዳል። በዘሟቾችና ንስሃን በማያውቁ ኃጢኣተኞች ሥጋ ወደሙ ይፈተታል። ዘመነ ግርምቢጥ። በዚህ መሀል ሀገርና ሕዝብ ለባዕድ አምልኮና ለአጋንንታዊ ኃይል ይጋለጣል። ሀገራችንን ዲያብሎስ የሚጋልባትና ወያኔያዊ የጭራቅ ሠራዊት የሚጨፍርባት እንግዲህ በዚህ ሂደት ነው። ከጠፋንበት ሊታደገን ፈጣሪ ፊቱን ካልመለሰልን አካሄዳችን እጅግ አደገኛ ነው። አሁን አሁን የፈጣሪ ፊት ወደኛ የዞረ ይመስለኛል። እውነት ያድርግልን። ቅዠት አይሁንብን። የምናየውና የምንሰማው ከምር ይሁን። “እንዲህ ነበርን” ለማለት ያብቃን። ስቃያችን ታሪክ ይሁን።

የፓርላማ አባላትን በ“ሦስተኛው ዐይኔ”ና በ“ስድስተኛው” የስሜት ሕዋሤ አነበብኳቸው። ለነገሩ ማንም ቢያነባቸው እንደኔው ይረዳቸዋል። ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን ሌሎችም ቢመለከቷቸው ማንነታቸውን በቀላሉ ይረዷቸዋል - ከአዳራሹ የሚያንስ ዋጋ እንዳላቸውም ማንም ይገነዘባል። ግዑዝና ግዑዝን ማመሳሰል ደግሞ ስህተት አይደለም። መብላትና መጠጣት ብቻውን ሰው አያደርግምና።

የሰውነት አቋማቸው ራሱ ስለማንነታቸው ብዙ ያሳብቃል። አለባበሳቸውና ትክለ ሰውነታቸውም እንዲሁ ብዙ ይናገራል። ከአእምሯቸው በላይ በሆነባቸው አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አነጋገርና ገለፃ ሳቢያ ጦጣ ሆነው ሲቁለጨለጩ ማየት አንጀትን ይበላል። የዐቢይን ንግግር ስለመረዳታቸው እርግጠኛ መሆንም አይቻልም። መቁለጭለጭ ብቻ። የለመዱት ተጽፎ የተሰጣቸውን ማነብነብ በመሆኑ ይህ አዲሱ የዐቢይ አካሄድ ሊገባቸው የቻለ አይመስልም። በወረቀት ተጽፎ የሚሰጣቸውን ጥያቄ መጠየቅ የለመዱት “የፓርላማ አባላት” አሁን የፈለጉትን መጠየቅ እንደሚችሉ ሲነገራቸው ግራ ገባቸው - አልለመዱትምና። እናም ማይክራፎን ተቀብለው “በወረቀት የጻፍኩትን ነው የምጠይቀው” ማለት ጀመሩ - ያሳፍራል። ጥያቄ እንዲሁ ይጠየቃል እንጂ እንዴት ከአዳራሽ ውጭ ተጽፎ ይመጣል? ተጽፎ ይምጣ - ግዴለም። ሲጠይቁ መንተባተብን ምን አመጣው? የገዛ ጽሑፍን ማንበብ አለመቻልን የመሰለ የድንቁርና መገለጫ ደግሞ የለም። እነዚህ ናቸው እኛን በፓርላማ ውስጥ የወከሉን። እነዚህ ናቸው ህግ አውጭዎቻችን፤ እነዚህ ናቸው “በሕዝብ የተመረጡ” መሪዎቻችን። ወያኔ የተባለ ጉድ የሠራልን ሥራ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚዘነጋ አይደለም።

የሚያሳዝነኝ ዐቢይ ነው። ከነዚህን መሰል ጦጣና ዝንጀሮዎች ጋር ምን ተመካክሮ እንዴት ሥራ ላይ ሊያውል እንደሚችል አስቡት። ለቤተ ሙከራ ሠርቶ ማሳያ የተሰባሰቡ ፈቃደኛ ሰዎች ይመስላሉ እንጂ በጭራሽ የፓርላማ አባላት አይመስሉም። ቢኖሩ ባይኖሩ የማያጎድሉ ወያኔ የጠፈጠፋቸው Guinean pigs ናቸው ቢባል አሳምሮ ያስኬዳል። በአገላለጼ ክረት አዝናለሁ። ከተጎዳ ሥነ ልቦና የሚወጣ ቃል እንደሚያም ግልጽ ነውና ይቅርታ እጠይቃለሁ። …

ዶ/ር ዐቢይን እግዚአብሔር በጭንቅ ቀናችን የሰጠን የክፉ ቀን ልጃችን ነው። ይህን የክፉ ቀን ልጃችንን አለመደገፍ ማለት ነባሩን የሕወሓት ዘረኛ አገዛዝ የሙጥኝ ብሎ ወያኔን “አትሂድብኝ” እንደማለት ነው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ይህን ሰው ወፌ ቆመች ለማለት አለመፈለግ ልዩ ተልእኮ ያነገበ የሀገር ፀርነት ነው።

የዛሬው ፓርላማችን ወደፊት ጥርሳችንን ተነቅሰን እንስቅበት ዘንድ በሁሉም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተቀርጾ የሚቀመጥ የጅላንፎዎች ስብስብ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ቀጣዩ ፓርላማ ግን በምዕራቡ ዓለም እንደምናየው ዓይነት በተማሩና በበቁ ሰዎች - በሁሉም ረገድ ከተራው መንጋ በተሻለ ሁኔታ ላይ በመገኘታቸው ምክንያት በሕዝብ በሚመረጡና በሚከበሩ ዜጎች የተሞላ እንደሚሆን ተስፋዬ ብርቱ ነው።

ስለዐቢይ እግዚአብሔር በእጅጉ የተመሰገነ ይሁን። ኢትዮጵያ እንደገና ትልቅ ስትሆን ይታየኛል። የሚዲያ አካላት አፍራሽ ነገሮችን ከማቅረብ ቢጠነቀቁ፣ ጸሐፊዎችም ገምቢና አስታራቂ በሆኑ ነገሮች ላይ ቢያተኩሩ፣ ተስፋ በመቁረጥ ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩ የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤቶችም ከየተደበቁበት ጉድጓድ እየወጡ የየበኩላቸውን አስተዋፅዖ ቢያደርጉ፣ በራሳቸው ዓለም የሚኖሩ ተጋሩ ወደኅሊናቸው ተመልሰው መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ እውነት ጋር ቢስማሙ … ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይን በሚገባ ማገዝ ይቻላል። ጋን በጠጠር ይደገፋልና ከእንግዲህ “ምን አገባኝ”ን መተው አለብን።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!