Dr. Berhanu Nega and Mr. Andargachew Tsege

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ

ስሜነህ ታምራት (ከስዊድን)

ዛሬ ኢትዮጵያችን በሰላማዊ ሽግግርና "በየአብሮነት ልዩነት" መርኅ በዴሞክራሲያዊ ግንባታ ላይ ትገኛለች። ስለሆነም ከዚህ ቀደም ያልተጠቀምንባቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ በትምህርትነት ወስደን፤ ዛሬ የተፈጠረው ሁኔታ እንደትናንቱ እንዳያመልጠን ብዙ እጅግ በጣም ብዙ የሆነ ትዕግሥትና ብሔራዊ ትኩረት የምናደርግበት የለውጥ ነጋሪት እየተጎሰመ ያለበት ጊዜ ነው።

በተለይም ዛሬ የተፈጠረው ሁኔታ ኢትዮጵያን ወደፊት አራምዶ መጭውን ብሩህ ዘመን ከወዲሁ ለማሳየት ያለው ተስፋ እጅግ አበረታች ነው። ለምን ቢባል ያሁኑ ለውጥ በሰላምና በፍቅር፣ በልዩነት አንድነት፣ በመደመርና በአብሮነት ላይ የተመሠረተ ነው። ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ኢትዮጵያዊ ፍቅር የወለደው የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አመራር ትናትና በጠላትና በአፍራሽነት ተፈርጀው የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ አገራቸው ገብተው ከሕዝቡ ጋር በሰላም እንዲታገሉ ብሔራዊ ጥሪ አቅርቦላቸዋል። በእራሱ በጠ/ሚ/ሩ አሰባሳቢ ቃልም ከእንግዲህ እነዚህ ድርጅቶች አጋዥና ተፎካካሪ እንጅ፤ በተለምዶ እንደሚጠሩት ”ተቃዋሚና ሽብርተኛ” ድርጅቶች አይሆኑም።

ወደ አገር ቤት እንዲገቡና አጋዥነታቸውን በተግባር እንዲያውሉ ብሔራዊ ጥሪ ከቀረበላቸው መካከልም አንዱ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌና በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በ2008 የተመሠረተው የአርበኞች ግንቦት 7 ነው። ”ግምባር” ያላልኩት ወደፊት ተግባሩን ሲቀይር መጠሪያ ስሙንም ሊቀር ይችላል በሚል እሳቤ ነው። የድርጅቱ ቀዳማይ አላማ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለብዙ ዓመታት በመገንጠል መርከብ ተሣፍረው የነበሩ ኃይሎችን ወደ አብሮነት ትግል ለመለወጥ ያደረገውን ጥረት በበጎ ጎኑ ይዘን፤ በቀጣይነት በሚያካሂደው ትግል ውስጥ የሚከተሉትን በኩረ ሐሳቦች በውል እንዲያሰምርባቸው ላሳስበውም ላስጠነቅቀውም እፈልጋለሁ።

አንድ - የኢትዮጵያን ብሔራዊ አንድነት የትግሉ ቀዳማይ ጥያቄ ማድረግ

በእኔ እይታና በእኔ ፍተሻ፤ አሁን ባለው የአገራችን ጭብጥ ሁኔታ ጎልቶና ደምቆ የሚታይ ሕዝብን በብዛት አሰባስቦ የያዘ ሕብረ-ብሔር የፖለቲካ ድርጅት የለም። አሉ ቢባልም እንኳን ከመሪዎቻቸው በስተቀር በጉልህ የሉም። ለዛውም በውስጥ ሽኩቻና ታውቆ እንዲበታተኑ በሚደረግ ሥውር ሤራና እነሱም ለዚህ ሁኔታ የተመቻቹ በመሆናቸው ደምቀውና ጎልተው የትግሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኃይል ለመሆን አልቻሉም። ባለመቻላቸውም፤ ዛሬ ኢትዮጵያ በዚህ ወርድና ስፋቷ እንዳለችው ነገም እንደምትቆይ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር በሕዝቦቹ መካከል መሠራት የነበረበት የአንድነት የፍቅርና ተከባብሮ በጋራ የመኖር ባህል በእጅጉ ተሸርሽሯል። ስለዚህ የዶ/ር ዐቢይንና የቲም ለማን የኢትዮጵያዊነት ሱስና የመደመር ፖሊሲ በስፋት ሊያስተጋባና ሊተገበር የሚችል ጠንካራ ሕብረ-ብሔር ፓርቲ እንደ ግንቦት 7 ዐይነት ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አቅጥነው፤ ለአንድ አገር ለአንድ ሕዝብ ቀዳማይ ዓላማና ተግባር እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ግንቦት 7 ከሌሎች መሰል ዓላማ ካላቸው ድርጅቶች ጋር ድርና ማግ ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል።

ሁለት - አንደበተ ርዕቱ ካድሬዎች ማዘጋጀትና ትግሉን በንቃት የመምራት ሚና

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ የደረሰበት መብትን በእምቢተኝነት የማስከበር የላቀ አመለካከት ራቅ አድርጎ የሚያይ ካድሬ እንጅ፤ እሱ የሚለውን የሚያስተጋባ የገደል ማሚቶ አይደለም። የሚፈልገው ብሔራዊ ችግሮችን የሚደርትለት ሳይሆን፤ ችግሩን ለመፍታት አቅጣጫና ዘዴ የሚያሳየውን ነው። ይህን ብሔራዊ ድርሻ ለመወጣት ደግሞ በደረቀ ብሔራዊ ስሜት የሚመራ ቀስቃሽ ሠራዊት ሣይሆን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ድርጅታዊ ተግባር ከዋኝ ኃይል በአገር ቤትም በውጭም መኮልኮል ግድ ይላል። የድርጅትህ የኢኮኖሚ መመሪያ ምንድን ነው? ሲባል ይህን ዶ/ር ብርሃኑ ነው የሚያውቀው የሚል ካድሬ ይዞ ሕዝብን የሚስብና የሚያሳትፍ ተግባር መከወን በእጅጉ ይከብዳል። ስለሆነም ድርጅቱ፤

* የሕዝቡን ንቃተ-ሕሊና አስረግጦ የተረዳ

* የመፍትሔ አቅጣጫ አመንጭ ትኩስ ኃይል

* በጥቅሉ ክልላዊና ብሔራዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት አቅሙና ልምዱ ያለው ሳቢና አሰባሳቢ ኃይል ማዘጋጀት ይኖርበታል።

* የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንዲሉ፤ የግንቦት 7 ቀስቃሽና አደራጅ፤ አብዛኛው ከእዛው ከአገር ቤት የተፈተኑቱ ላይ ቢያተኩር፤ ሊመዘን የሚችል ብሔራዊ ፋይዳ ያለው ተግባር ሊከውን ይችላል የሚል እምነት አለኝ።

ሦስት - የዲፕሎማሲያዊ ተግባርና የፋይናንስ ምንጭ ትኩረት

ድርጅቱ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የሕዝቡን አኗኗርና የፍትሕ ጥማት፣ የኢኮኖሚና ባህላዊ እሴቶቹን በሚገባ የሚረዱና ወደ ጊዜያዊ ለውጥ ሣይሆን፤ ወደ መፍትሔ ወሳጅ መዋቅራዊ ለውጦችም ሊመሩት አቅሙ ያላቸው ብቁ መሪዎች አሉት።

ይሁን እንጅ ውስብስብ ብሔራዊ ተግባርን በሚገባ ለመወጣት፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የውጭ መንግሥታት ጋር ጅምር ዲፕሎማሲያዊ ተግባሮቹን አጠናክሮ መቀጠል የሚጠበቅ ቀጣይ ተግባሩ ሊሆን ይገባል። ከዚህ ባላነሰ ሁኔታ ሌላው ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጉዳይ የፋይናንስ አቅም ነው። የገቢ ምንጭን ከአባላትና ደጋፊዎች የመሰብሰቡ ተግባር እንዳለ ሆኖ፤ እንደነ ኤፈርት ያለ የድርጅት ኢኮኖሚያዊ አቅምን በአንድ ጊዜ መፍጠር ባይቻልም፤ ድርጅቱ ገቢውን የሚያዳብሩለት የገንዘብ ምንጮች (income generators) መፍጠርና በርካታ ወጪዎቹን ለመሸፈን እንዲችል ከአሁኑ ሊያስብበት ይገባል።

እንደ ማጠቃለያ

* አርበኞች ግንቦት 7 የተነሳሳበትን ብሔራዊ ተግባር በብቃት ለመወጣት በአፋጣኝ ድርጅቱ አጠቃላይና ዝርዝር የውስጥና የውጭ ፖሊሲዎቹን በማናቸውም የመገናኛ ዘዴዎች በይፋ ማሳወቅ፤ ለነገ የማይባል ሥራው ሊሆን ይገባል። በተለይም ድርጅቱ የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብዙኀኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለለውጥ እንዲነሳሳ የሚያስችል ትልቅ ብሔራዊ ጉዳይ ስለሆነ፤ በአንክሮ ሊተኮርበት የሚገባ በድርጅቱ ሕይወት ላይ ታላቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ዘርፍ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

* የቅራኔ አፈታት ቅደም ተከተል የማውጣት ሚና፤ ድርጅቱ በወል ብሔራዊ ድርሻውን፣ በግል ደግሞ ድርጅታዊ ተልዕኮውን በአግባቡ ይወጣ ዘንድ እጅግ ይጠቅመዋል። በቅራኔ አፈታት ሂደት ነገ መሠራት የሚኖርበትን ድርጅታዊ ተግባር አንዳንድ ግልብና ችኩል ካድሬዎች ዛሬ እንሥራው በማለት ከፈረሱ ጋሪውን እንዳያስቀድሙ ችኩሎቹን እያረገቡ በትክክለኛው ሐዲድ መጓዝ ትናንት ታይተው ከጠፉ የፖለቲካ ድርጅቶች ውድቀት መማር ይሆናል።

* አርበኞች ግንቦት 7 መሠረታቸው ሕብረ-ብሔር ከሆኑ እንደነ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አንድነት ፓርቲ፣ ኢዴፖና የመሳሰሉ ድርጅቶች ጋር ፕሮግራሙን አቀራርቦ በጋራ ለመሥራት ቢሞክር፤ ሊመዘን የሚችል ፋይዳ ያለው ብሔራዊ ድርሻውን በብቃት ሊወጣ ይችላል በማለት ግላዊ መልእክቴን አስተላልፋለሁ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

ለተከባበረ ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ፣ ስሜነህን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ያገኙታል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!