Dr. Abiy Ahmed

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

በቀለ ደገፋ፣ ኅዳር ፳፻፲፩ ዓ.ም.

በጠ/ሚ ዐቢይ የሚመራው የለውጥ ሥርዓት ወደሥልጣን ከመጣበት ዕለት አንስቶ እጅግ የሚያስደንቁና አንዳንዴም ለማመን የሚቸግሩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በጥቂቱ ለማስታወስ - በወያኔ የማሰቃያ ቤቶች ተወርውረው የነበሩ ንጹሕንን ነፃ ማውጣት፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ ከአገር የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውድ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ አሸባሪ ሲባሉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደ አገር ገብተው በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ፣ መቀመጫቸውን በውጭ ያደረጉ የመገናኛ ብዙኀን ሕዝብን በቀላሉ እንዲደርሱ እድል መስጠት፣ ትርጉም-አልባ የነበረውን የኢትዮ ኤርትራ ፀብ በእርቅ መፍታትና ብሎም በአፍሪካ ቀንድ የሰላም አየር እንዲነፍስ ማድረግ፣ ተለያይተው የነበሩ የቤተክርስቲያን አባቶችን በማስማማት የቅዱስ ሲኖዶሱን አንድነት መመለስ፤ እንዲሁም በባዕድ አገራት ለእስር ተዳርገው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን አስፈትቶ ወደአገራቸው ማምጣት የሚሉት ይጠቀሳሉ።

እነዚህንና ሌሎችንም አስደማሚ ተግባራት እያከናወነ ያለው የለውጥ ኃይል በአንፃሩ ሕልውናውን የሚፈታተኑና የአገርንና የሕዝብን ሰላምና አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ከዚህ ቀደም ባልተስተዋለ መልኩ በተደጋጋሚ ሲከሰቱ፤ ’በቂ እርምጃ አልወሰደም’ የሚሉ ምክንያታዊ ጥያቄዎች፣ ተቃውሞዎችና ቅሬታዎች እየቀረቡበት ይገኛል። ወቅቱ የለውጥ እንደመሆኑ መንግሥት መቀመጫውን እስኪያደላድል እዚህም እዚያም መንገጫገጮች መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፤ አካልን የሚሰባብሩ፣ የሰውነት ክፍልን የሚያጎድሉና ለሕይወት የሚያሰጉ መንገጫገጮችን በዋዛ ማለፍ ግን፤ የኋላ ኋላ የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አይሆንም። ከዚህ አንፃር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በንጹሕን ላይ የደረሱ ጭፍጨፋዎችና መፈናቀሎች በአብዛኛው በዝምታ የመታለፋቸው ጉዳይና፤ አገሪቱን ሲያደሙ የኖሩና አሁንም ከማድማት ወደኋላ ያላሉ ወያኔያውያንና ተባባሪዎቻቸው ከፍትሕ ዕይታ ተሰውረው መቅረታቸው የማያቋርጥ እሮሮ ከሚቀርብባቸው ችግሮች ቀዳሚ ናቸው። መንግሥት የሕዝብ መፈናቀልን ሲያወግዝ ቢሰማም፤ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ለማድረግ ሲሞክር አለመታየቱ ሌላው የቅሬታ ምንጭ ነው። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚወጡ ያልተማከሉ መረጃዎችና ውሳኔዎች መበራከት፣ በቅርቡ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ሴራ መድበስበስ፣ እንዲሁም ’የለውጡ ባለቤት እኛ ነን’ በሚል እብሪት በየአካባቢያቸው አዛዥ ለመሆን የሚቃጣቸው ጉልበተኞች እንደአሸን መፍላት ከዚሁ ጋር ይጠቀሳሉ።

ባለፉት ስምንትና ዘጠኝ ወራት ሶማሌን፣ ቤኒሻንጉልን፣ ሐዋሳን፣ ወላይታን፣ ባሌ ጎባን፣ ቡራዩንና ራያን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በንጹሓን ዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ የሆኑ ጭፍጨፋዎችና ማፈናቀሎች ሲፈፀሙ ቆይተዋል፤ አሁንም እየተፈፀሙ ነው። መንግሥት እነዚህ ወንጀሎች የተቀነባበሩ መሆናቸውን አስረግጦ ቢናገርም፤ ከሶማሌ ክልል አመራር በስተቀር ወንጀሎቹን በፈፀሙ አካላት ላይ እርምጃ ሲወስድ አልታየም (የሶማሌውም ቢሆን ችግሩ ከተደጋገመ በኋላ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ልብ ይሏል)። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሻሸመኔ ላይ ሰው ዘቅዝቀው የገደሉ ወንጀለኞች አንዳች ቅጣት ባልተቀበሉበት አገር፤ ‘ባንዲራ አወረዳችሁ’ በሚል ሰበብ በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶች ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ ግርምትንና ግራ መጋባትን የፈጠረ ነው። ለዘመናት በአገሪቱና በሕዝቧ ላይ ግፍና በደል እንዲሁም ዘረፋ ሲፈጽሙ የኖሩ ሰዎች ለፍትሕ ያለመቅረባቸው ጉዳይ ሌላው ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት የሜቴክ አመራሮች መታሰራቸው ተነግሯል። ይህም ሆኖ ፍትሕ እጇን ዘርግታ በጉጉት የምትጠብቃቸው እጅግ ብዙ ነፍሰ-በላዎችና ዘራፊዎች አሁንም ትግራይ ውስጥ እንደተጠለሉ ነው። አለምአቀፍ እውቅና አይሰጣት እንጂ የቀን ጅቦቹ የመሸጉባት ትግራይም ራሷን የቻለች አገር መስላ ቁጭ ብላለች። የመንግሥት እንቅስቃሴ ከማይሰማበት ከዚያ አካባቢ የሚወጡት የድርጅት መግለጫዎች ትግራይን የኢትዮጵያ ባላንጣ የሆነች ጎረቤት አገር እንጂ፤ መሐል አገር በተቀመጠ መንግሥት የምትመራ ክልል አያስመስሏትም። ትግራይ የመሸጉት ዘራፊዎች የእስር ትዕዛዝ የወጣበትን የቀድሞ የደህንነት ቁንጮ የድርጅታቸው አመራር አባል አድርገው ሲመርጡ፤ አልታዘዝም ባይነታቸው ምን ያህል ጥግ እንደደረሰ የሚያሳይ ይመስለኛል። በቅርቡ ራያ ላይ ለተፈጠረው ችግር ከትግራይ ልዩ ኃይል ውጭ በአካባቢው ድርሽ ያለ የፌደራል መንግሥት ኃይል አለመኖሩስ የሚያሳብቀው ምን ይሆን? በዚህም በኩል ‘የዐቢይ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ከወያኔ ታጋችነት ለማስለቀቅ እየሠራ ያለው ሥራ ምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ሆኗል።

ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ችግሮችና ሕገ-ወጥነቶች በለውጥ ጎዳና ላይ ባለችው አገራችን በተከታታይና በፍጥነት እንዲከሰቱ ካስቻሉት ምክኛቶች ዋነኛው አገሪቱ የተረጋጋ መንግሥት እንዳይኖራት ጠንክሮ እየሠራ ያለው ወያኔ መሆኑ አያጠያይቅም። አገርንና ሕዝብን ሲዘርፉ የኖሩ የወያኔ ኃይሎች ያጡትን ሥልጣን መልሰው ማግኘት ባይችሉም ራሳቸውን ከሕግ ተጠያቂነት ለማሸሽ አቅምና ልምዳቸውን ተጠቅመው አገርን ለመበጥነጥና ለማተራመስ በትጋት እየሠሩ ነው። ለዚህ ደግሞ በሥልጣን ዘመናቸው በየቦታው የቀበሯቸውን የEthnic federalism ፈንጂዎች በፈለጉት ግዜና መንገድ በማፈንዳት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። ከወያኔ በተጨማሪ ‘ለውጡን ያመጣነው እኛ ነን’ የሚሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መጠቀሚያ በማድረግ አገሪቱ ሁለት መንግሥት እንዳላት በአደባባይ እየደሰኮሩ፤ እኩይ አላማቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መኖራቸውንም ልብ ይሏል። እነዚህ ኃይሎች በራሳቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ፤ በገንዘብ አቅሙ ጠንከር ካለውና አገር አበጣብጦ ራሱን ለማዳን ያገኘውን ሁሉ ከሚፈነቅለው ወያኔ ድጋፍ እንደሚያገኙ አጠያያቂ አይሆንም። የሥርዓቱን በአፍላ ዕድሜ ላይ መሆንና አለመጠንከር ተረድቶ፤ ችግርና አለመረጋጋትን በመፍጠር ዕድሜውን ለማሳጠር አልያም መሰናክሎቹን ለማብዛትና ከዚያም ለማትረፍ ያለመታከት የሚሠሩ ሌሎች ቡድኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት የሚያስተች አይሆንም። ከዚህ በተጨማሪ በአገር ውስጥ ለነበሩና ከውጭ ለተመለሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግን ተከትለው የሚንቀሳቀሱበት የጠራ አቅጣጫ አለመቀመጡ፤ ፓርቲዎቹ በፈለጉት መልኩ ሕዝብን እንዲቀሰቅሱና እንዲያነሳሱ እድል ስለፈጠረላቸው፤ ይህ አገሪቱ እየገጠማት ላለው ችግር ያበረከተው ድርሻ ቀላል አይደለም።

የጠ/ሚ ዐቢይ አስተዳደር ለነዚህ ችግሮች አፋጣኝ እርምጃ ላለመውሰዱ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጥቂት ነጥቦችን ማስቀመጥ ይቻላል። ወያኔን ለ27 ዓመታት ከተንጠለጠለበት የሥልጣን ማማ ላይ አሽቀንጥሮ የጣለው ቡድን፤ የለውጡን ሂደትና የአገሪቱን ሕልውና እየተፈታተኑ ያሉ ኃይሎች ላይ ለዘብ ማለትን መምረጡ የሚፈራው ወይም በጥንቃቄ ሊይዘው የፈለገው ኃይል እንዳለ ያስጠረጥራል። ከላይ ከተጠቀሱት ጎላ ጎላ ያሉ የነውጥ ዘዋሪዎች በተጨማሪ በለውጡ ኃይል ውስጥ ወይም ዙሪያ የተሰገሰጉ ስጋት ፈጣሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚህ አንፃር ፊት ለፊት የምናያቸው ሰዎች ሲናገሩ ከምንሰማው ውጭ፤ በለውጡ ኃይል ውስጥ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ምን ያህል ተቀባይነትና ድጋፍ እንዳለውና በዚህም የተከፉ ቡድኖች ላለመኖራቸው በእርግጠኝነት ለመናገር አዳጋች ነው። ለዐቢይ ፈራ ተባ ማለት የአቅም ማነስ ሌላው ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል - በተለይ ከአደረጃጀት አኳያ ያለ የአቅም ማነስ። ለዚህ ደግሞ ጠ/ሚሩ በቅርቡ በፓርላማ ‘የintention ችግር የለብንም’ ሲሉ የተናገሩት፤ ችግሩ ከአቅም ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ‘ዐቢይ መለሳለሳቸው ጠላት ላለማብዛት ብለው ነው’ የሚሉም አይጠፉም። ይህ ደግሞ ከላይ እንደጠቆምኩት አብሯቸው የተሰለፈውን ኃይል አስተሳሰብ በእርግጠኝነት ያለማወቅ ችግር ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል። ጠ/ሚሩ የፍልስፍና ተፅእኖም ያለባቸው ይመስላል - የቀደመውን ዐይነት እርምጃ መውሰድ አይጠቅምም፣ መግደል መሸነፍ ነው፣ ሁሉን ነገር በይቅርታ ሲሉ በተደጋጋሚ እንደሚደመጡት።

ሳጠቃልል፤ በበኩሌ አገራችን ካለችበት ወቅታዊ እውነታ አንጻር ይህ የለውጥ ወቅት ወደሚፈለገው አቅጣጫ እንዲጓዝ ለማድረግ የዐቢይ መንግሥት አሉ ከሚባሉት አማራጮች ሁሉ በብዙ ርቀት የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህንን ስል የዐቢይ መንግሥት ፍጹም ነው ከሚል አስተሳሰብ ተነስቼ ሳይሆን (ፍጹም ቢሆን ይህን ጽሑፍ መጻፍ ባላስፈለገኝ ነበር)፤ በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት፣ በአንፃራዊ መልኩ የያዘውን የተሻለ የኃይል ሚዛንና በዘር ጉዳይ በአገሪቱ የሰፈነውን ትኩሳት ለማስታገስ ያለውን የስብስብ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት በተደላደለ መሰረት የቆመ አገራዊ ራዕይ ያለው ድርጅት ለመኖሩ እርግጠኛ አለመሆኔ፤ የዐቢይን መንግሥት በተሻለ አማራጭነት እንድወስድ ያስገድደኛል። ነገር ግን ከዚህ የለውጥ ቡድንም ሆነ ለአገራችን የሚችሉትን አስተዋፆ ለማበርከት ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የምንጠብቀውን ለማግኘት ይህንን ፈታኝ ወቅት በጥንቃቄ ማለፍ ያስፈልጋል። ለዚህም ስንዴውን ከእንክርዳዱ ለመለየት እንዲቻል፤ በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግን ተከትለው የሚንቀሳቀሱበት ፍኖተ-ካርታ (roadmap) መነደፍ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ በፍንደቃ የተቀበልነው ለውጥ የመቀልበስ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ የብዙዎች ስጋት ነው። በብሔር ፖለቲካ የአገርን አንድነት ማስጠበቅ የሚቸግር መሆኑ አይቀሬ ነውና፤ የለውጡ መሪዎች ይህን ጉዳይ ከአሁኑ የጠራ መልክ ሊያሲዙት ይገባል። ከዚህ አንፃር አገሪቱ አሁን ላለችበት መመሰቃቀል ያበቃትን ሕገመንግሥት መቀየር ቀዳሚ ሥራ ይሆናል። ይህ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ሕዝብ በመረጠው መንግሥት አስፈፃሚነት እንደመሆኑ፤ የለውጡ ኃይል በቅርቡ በፍትሕና በሌሎች ተቋማት ላይ እየወሰደ ያለው አመርቂ እርምጃ በስፋት ቀጥሎ ቀጣዩ ምርጫ ነፃና ፍትሓዊ እንዲሆን መሥራት ይኖርበታል። ሥርዓቱ ለመግደል የሚንቀዠቀዥ አለመሆኑ የሚያስመሰግነው ቢሆንም፤ የሕዝብን ሰላምና የአገርን አንድነት የሚፈታተኑ አደጋዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ፤ አገርን የሚመራ ኃይል ቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑን ማስታወስ ደግሞ የግድ ይሆናል። ‘ነገሮች የሚሆኑት ለምክንያት ነው’ እንዲሉ፤ መሆናቸው የማይቀር ችግሮች ከአሁኑ መከሰታቸው እድሉን ለተጠቀመበት በግዜ መፍትሔ ለመፈለግና ችግሮቹም ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ ይረዳል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!