አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ ፕ/ር መረራ ጉዲናና ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ ፕ/ር መረራ ጉዲናና ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (ከግራ ወደቀኝ)

ነፃነት ዘለቀ (ከአዲስ አበባ)
በሰው የሚጠሉት ወይም እንደሚጠሉት የሚናገሩትን ራስ ሲያደርጉት የማያስጠላ ከሆነ የተሳከረ ስብዕና (MPD) ባለቤት የመሆን ችግር አለ ማለት ነውና፤ በቶሎ መታከም ያስፈልጋል። እኔ ለምሣሌ በወንድሜ ወይ በጓደኛዬ ላይ የማየውንና የምቃወመውን መጥፎ የመሰለኝን ምግባር እኔ ራሴ ባደርግና እንደነውር ባልቆጥር ትክክል አይደለሁም። ጨለማና ብርሃን ሕብረት እንደሌላቸው ሁሉ በአንድ ሰውነት ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ ተቃራኒ ሰውነቶች ሊኖሩ አይችልም። እንደዚያ ያለ ችግር በፖለቲካው መስክ በጉልኅ እያስተዋልን ነው። ይህ አንቀጽ መግቢያዬ መሆኑ ነው። 
ትናንት የአገራችን የፖለቲካ ተፎካካሪዎች (በአዲሱ አጠራር) በጠ/ሚኒስትሩ ተጠርተው ውይይትና የምሣም ግብዣ ማድረጋቸውን በመገናኛ ብዙኃን ተከታትለናል። እጅግ በጎ ጅምር ነው። በአገራችን ለዘመናት ስንመኘው የነበረና በነዚህ ባሳለፍናቸው ጥቂት የለውጥ እንቅስቃሴ ጎልቶ በታየባቸው ወራት ውስጥ እናያለን ብለን ያልገመትነው ነገር ነው። ፖለቲከኞቹ ከዚህ መልካም ጅማሮ ብዙ ነገር እንደተማሩ መገመት ይቻላል - ለመማር ፈቃደኛ ከሆኑ። በባሕላችን እንካ ያሉት ዳቦ ርካሽ እንደሆነ መኖሩ አውኮን እንጂ፤ በቀደምት አምባገነን ገዢዎች ዘንድ እንደዜጋና እንደሰውም መቆጠር ብርቅ እየሆነባቸው በየማጎሪያ ቤቶች እየታጨቁ ስንትና ስንት ግፍና በደል ይደርስባቸው የነበሩ ተቃዋሚዎች፤ ይህንን የመሰለ ክብር ሲያገኙ ቢያንስ የጌቶች ጌታ የሆነውን ኅያው እግዚአብሔርን (የሚያምኑ ከሆነ ነው እሱም)፤ ቢበዛ ደግሞ ለዚህ ማዕረግ ያበቃቸውን የሕዝብ ትግልና የወጣቶች መሥዋዕትነት ክብር ሊሰጡት በተገባ ነበር። 
ይቺ እድል እንዲህ በቀላሉ አልተገኘችም። እንኳንስ ተቃዋሚዎች ጠ/ሚ ዐቢይ ራሱ የንጹሓን ዜጎች ደምና አጥንት ነው ወደላይ አሽቀንጥሮ ለዚህ የታሪክ ኃላፊነት ያበቃው - ኃላፊነቱ ባለው እቶናዊ የሚጋረፍ ሙቀት የተነሣ የሚቀናበት ባይሆንም። ነገር ግን በአገራችን የተለመደው ነገር ሌላ ሆነና ተቸገርን። 
አንድ ያገሬ የኔ ቢጤ (“ለማኝ” ላለማለት ነው) እንዲህ አለ ይባላል፤ “ስንቅ ያለቀበት ጌታ ‹ደጅህ ላይ ቆሟል› ብለህ ለጌታህ ንገረው!”። መግደርደርና መኮፈስ በመንደር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በላይኛው እርከንም መታየቱ እየጎዳን ነው። … እንጂ አሁን “በምድርህና በሕዝብህ መሐል በሰላም ታገል” ተብሎ ተጠርቶ ሲያበቃ፤ ሕዝብን ማመስና ትጥቅ አልፈታም ማለትን ምን ያመጣው ነበር? ለማንኛውም የነፃነትን አየር ገና በጨረፍታው ከመተንፈሳችን ያን ለዘመናት ያንገፈገፈንን የቆሪጥ አገዛዝ እንዳታመጡብን ተቃዋሚዎች/ተፎካካሪዎች አቅል ግዙልን፤ ከራሳችሁም፣ ከመንግሥትም ጋር በቀናነት ተግባቡ። እናንተስ ሾልካችሁ ብትሄዱ መውጫ መግቢያውን ታውቁታላችሁና ምንም አትሆኑም። ለኛ ለተገፋነው አስቡልን። …
የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን ስብሰባ በቲቪ ስመለከት ብዙ የተደበላለቀ ስሜት አደረብኝ። ጎላ ብሎ የተሰማኝ ግን አገራችን በሁሉም ረገድ ዕድለኛ አለመሆኗ ነው። በርካታዎቹ ፖለቲከኞች ዕድሜያቸው ከመግፋቱ የተነሣ ራሳቸውን ችለው ስለመራመዳቸውም ተጠራጠርኩ። እንዲህም አልኩና ራሴን ጠየቅሁ “ይሄ ፖለቲካ የሚሉት ነገር ጡረታ የለውም ማለት ነው?” ጥያቄዬ ሳላስበው ቀጠለ፤ “እነዚህ ሀፍረትና ይሉኝታ የሚባሉ ነገሮች ከትግራይ - ከወያኔ ትግሬዎች መፈልፈያ ዋሻ - ብቻ ሣይሆን ከመላው ፖለቲከኞቻችን ጭንቅላት ውስጥም ሙልጭ ብለው ወጥተው ይሆን?” አልኩ። ነገር በሦስት ሲሆን ይጸናልና እንዲህ ስል ጥያቄዬን ሰለስኩ፤ “በዚህ ሁኔታ የዚህች አገር የመኖር ዋስትና ምንድን ነው?” አዎ፣ ከ“ታላላቆች” እንዲህ ያለ ስሜት-አልባነት (insensitivity) ከተስተዋለ’ ከተራው ዜጋማ ምን ሊጠበቅ? “የዓሣ ግማት ከአናቱ” መባሉ ትክክል ነው። ሁላችን ተያይዘን የዝቅጠት ቁልቁለቱን የምንነጉደው አለምክንያት አልነበረም። ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሲሆን?
አንዱ አንዱን ሲያማ ጀምበር ልትጠልቅ ነው። ተፎካካሪዎች በመንግሥት ወንበር ላይ ያሉትን “ሥልጣን ርስተ ጉልት መሰላቸው እንዴ? የሥልጣን ገደብ ተበጅቶለት መሪዎቻችንን በዙር ለምን አንመርጥም?” ለማለት የሚቀድሙት ተፎካካሪዎች ናቸው። ይህን የሚሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፤ ራሳቸው በድርጅታቸው በሚገኙ የሥልጣን ወንበሮች አንዳንዶቹ ከ25 ዓመታት በላይ መጎለታቸውንና፤ በፈረንጅኛው አነጋገር እዚያው ወንበር ላይ vegetate ማድረጋቸውን (መብቀላቸውን) ሳስበው አፈርኩ። በአገሬ እድልም አዘንኩ። ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ በጣም ጥቂት ጎልማሦችን ብቻ ነው ያየሁት። አብዛኛው ያረጀው ያፈጀው የኢሕአፓውና በኋሊዮሽ አቆጣጠር ከዚያም የሚያልፈው ትውልድ ነው - አንዳንዶቹ እንዲያውም ከዐቢይ ጋር መግባባት ሊሣናቸው የሚችሉ ጎምቱዎች ናቸው። ደግነቱ የመድረኩ መሪ - ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ - ወጣት መሆኑ ትንሽ ተስፋ አጫረብኝ እንጂ፤ ዱሮ ወጣት ሳለሁ የፖለቲካ ቡድን መሪ የነበሩ የያኔዎቹ አንጋፋዎች አሁንም በ80 እና በ90ዎቹ ዕድሜያቸው እዚያው ሙጭጭ ብለው ስመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ ንግግርና ተግባር እጅግ የተለያዩ መሆናቸውን አስታወስኩ - አውሮፓ ውስጥ ብሆን ኖሮ - ብቻዬንም ብሆን ሠልፍ ወጥቼ “shame on you dear octogenarians and nonagenarians!” እል ነበር። ዕድሜ ፀጋ መሆኑንና በአግባቡ ከተጠቀሙበት የሚያስከብር መሆኑን አውቃለሁና፤ ትችቴን ከዐውድ ውጪ በሌላ መልክ እንዳትተረጉሙብኝ አደራ። ይህ ራስን የማምለክና ሌሎችም እንዲያመልኩብን የማስገደድ አባዜ ቤተ መንግሥቱን አልፎ ወደ ተቃዋሚዎች/ተፎካካሪዎች መውረድ ነገንም ከዛሬው በበለጠ እንድንፈራው ቢያስገድደን አይፈረድብንም። ክፉ ዐመል። 
በዚህች የበሬ ግምባር በማታህል አገር እንደሚባለው 70 እና 80 የፖለቲካ ኩይሣ ካለ፤ የበሽታ እንጂ የጤና ሊሆን አይችልም። ከ310 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አሜሪካ እንኳን ሁለት ታላላቅ ፓርቲዎች ናቸው ያሏት፤ ከዚህ አንጻር የኛ በርግጥም አለመታደል ብቻ ሣይሆን ትልቅ እርግማን ነው። ይሄ ሁሉ ፓርቲ ደግሞ በጎሣ ፖለቲካ ላይ የተመሠረተ ነው ማለት አንችልም። ለይምሰል ያህልም ቢሆን የሐሳብና የአመለካከት ልዩነትም አለበት። ስለዚህ ችግሩ የጎሣና የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን፤ እነሱን ሽፋን አድርጎ በሐሳብና በአመለካከት የተለያዩ በማስመሰል የጥቅምና የሥልጣን ፍትጊያ እንደሆነ መገመት አይከብድም። ከ“ፍቅር እስከመቃብር” የሚቀጥል “የሥልጣን ጥም እስከ መቃብር” በሚል መጽሐፍ ቢጻፍ ጥሩ ነው።
አንዲት ትል ከመሐል ሸዋ በጠዋት ተነስታ እየገሠገሠች ስትሄድ፤ እዚያው መሐል ሸዋ አንድ ሰው ያያታል አሉ። “አንች ትል ወዴት ትሄጃለሽ?” ብሎ ይጠይቃታል። እርሷም “መተማ!” ብላ ትመልስለታለች። እሱም ይቀጥልና “ትደርሻለሽ?” ይላታል። እርሷም “ልብማ!” ትለውና መንገዷን ትቀጥላለች። እኛም በነዚህ ጎምቱ የፖለቲካ አበጋዞች የዴሞክራሲ ጥማታችን ሊረካ ጫፍ ላይ ደርሰናል። …
የኛም ነገር እንደትሊቱ መሆኑ ነው። በ1983 እና ከዚያ ወዲህ እንደአሸን የፈላው ይሄ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅት ጉዞው ወደ አራት ኪሎ ነው። ግን የትም ሳይደርስ ዕድሜውን ብቻ በመቁጠር አብዛኛው የድርጅት መሪ አራት ኪሎን በልቡ እንደሰነቀ አረጃና፤ አሁን ጠማማ ጣሳ መስሎ በሕልሙ ብቻ ጠ/ሚኒስትርና ፕሬዝዳንት እንደሆነ ቀረ - ላልተለመደ ግልጽነቴ ይቅርታ። እንደሚመስለኝ እንደኛ እንደ ኢትዮጵያውያን ሥልጣንና ሀብት ወዳድ በዓለም ያለ አይመስለኝም። ለሥልጣን በተለይ ጉጉ ነን። ለዚያም ስንል አይደለም አገርና ሕዝብ ልጃችንንም ቢሆን ሳንሸጥ የማንቀር ብዙዎች ነን። መጥፎ ተፈጥሮ። ለዚህ ይመስላል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትንንሽ ዘውዶችን አናቱ ላይ ጭኖ እንደሚንቀሳቀስ አንዳንድ የፖለቲካና የማኅበረሰብ ሥነ ልቦና ተንታኞች የሚናገሩት። የሥልጣን ሱሳችንን በስያሜዎች ሳይቀር መገንዘብ እንችላለን። “የኢዴፓ ፕሬዝዳንት፣ የመዐሕድ ፕሬዝዳንት፣ የኢመማ ፕሬዝዳንት፣ የኢ.ቤ.መ ፕሬዝዳንት፣ የአኢወማ ፕሬዝዳንት፣ የኢሠማ ፕሬዝዳንት፣ የ‹መኢጠማ› ፕሬዝዳንት፣ …” የብዙ ተቋማትን ኃላፊዎች ወይም ሊቃነ መናብርት ስያሜ ስንመለከት “ፕሬዝዳንት” ነው የሚለው። ... እንዲህ ከሆነ እኔም የስድስቱ ቤተሰቤ ፕሬዝዳንት ሆኜ ራሴን በራሴ መሾሜን በዚህ አጋጣሚ ሳልገልጽ ባልፍ ይቆጨኛል። ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ተሰይማ የቤት እመቤትነት ሥራዋን እንድትቀጥል ዛሬ ማታ የሹመት ደብዳቤዋን እሰጣታለሁ - በልጆቻችን ፊት። ከጊዜው የሴቶች አገራዊ የሥልጣን ክፍፍል አኳያ ግን፤ ይህ ሹመት መመርመር ሳይኖርበት አይቀርም። ቢሆንም እኔ ግን ሞቼ እገኛታለሁ እንጂ የፕሬዝዳንትነቷን ሥልጣን አልለቅም። … ይሁን። ፈገግታም የሕይወት ቅመም ናት። 
እባካችሁ እናንት አረጋውያን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች!
አንጀቴ እያረረ በራሴ እስከመቀለድ የበቃሁት በናንተ ሁኔታ ስለተበሳጨሁ ነው። አላስፈላጊ ብዛታችሁን በተመለከተ እንደተመከራችሁት ቢቻል ወደ ሁለት፤ አለበለዚያም ወደ ሦስትና አራት ውረዱ። ሰባና ሰማንያ ፓርቲ ሕዝብን ያወናብዳል፣ የሀብት ምንጭንም ያራቁታል እንጂ ለአገር አይጠቅምም። አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሊይዝ የሚችለው የጠ/ሚኒስትር ብዛትም አንድ ብቻ ነው። በመቶና ሁለት መቶ ሥፍራ ተቧድኖ ለአንድ ቦታ መወዳደር ደግሞ አላዋቂነት ነው፤ ሕዝብ ይታዘባችኋል። ስለዚህ የዚህ ሁሉ ጎራ ዋናው ልዩነት የሥልጣን ጉዳይ እንጂ ሌላ ባለመሆኑ በቶሎ ንቁና ተሰባሰቡ። በዘርና በሃይማኖት ፓርቲ መመሥረት ደግሞ የስብዕና ክስረት ነው። ይህን ከሌላው ዓለም ተማሩ። በተለይ በዚህ በሠለጠነ ዘመን በጎሣና በሃይማኖት መሰባሰብ ከእንስሳም መውረድ ነው። ለአንዲት ቦታ አትራኮቱ። ሕዝቡን አድምጡት። ሕዝቡ ከእናንተ በላይ የነቃ ነው። የዝንብ ልጃገረድንና የቁንጫ ጠንጋራን የሚለየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ማታለል በፍጹም አይቻልም። በበቀደሙ ስብሰባችሁ ለምሣሌ ብዙ ሰው ሆዱን ይዞ ሲስቅባችሁ ተመልክቻለሁ። እኔም ፍርፍር ብዬ ስቄያለሁ። ከልጅነት እስከ እውቀት ካሙዙ ባንዳንና ሮበርት ሙጋቤን በተቃውሞው ጎራ ተጎልተው እንደማየት ምን እሚያስቅ ነገር አለ?
የዚህችን አገር ፖለቲካ እያበለሻሸ ያለው ትውልድ እንደሚመስለኝ ከ60 እስ 90 አካባቢ ያለው የቀደመው ትውልድ ነው። እናንተ ቢቻል ዕረፉ፤ ባይቻላችሁና የመታየትና የመወደስ እንዲሁም የዝነኝነትና የታዋቂነት አባዜ ናላችሁን እያዞረ የሚያስቸግራችሁ ከሆነ፤ በወጣቶች ጀርባ አማካሪ ሆናችሁ ለሕዝቡ ታዩት። በእናንተ ቦታ ግን የተማሩ ወጣቶችን ተኩና ከድካማችሁ ዐረፍ በሉ። ይሄ “ያለ እኔ አገር ትጠፋለች” የሚለው የምትክ-የለሽነት አስተሳሰብ (sense of indispensability - which is, to me, a psychopathic problem) አሳውሯችሁ እንዳይቀር ወደ ሕሊናችሁ ተመለሱና ከእናንተ የተሻሉ ወጣት ዜጎችን በመተካት ሕዝቡን ካሱት። አሪስቶትል ይሁን ፕሌቶ እንዲህ ብሏል አሉ “ተማሪ ከመምህሩ ካልበለጠ፤ መምህሩ ደከመ እንጂ ዘር አልተካም።” ግሩም አባባል ነው። እኛ ግን የፈዘዘ ቅጂ (ኮፒ) እየተውንና ራሳችንን እሰማየ ሰማያት እየሰቅልን መሥራት የሚገባንን ሣንሠራ፤ አገሪቱን ሰው-አልባ አድርገን አስቀረናት። ዶ/ር ዐቢይን ተመልከቱ። ይህ ብላቴና ትናንት ማንም የማያውቀው ፈጣሪ ከሰማይ ዱብ ያደረገው የሚመስል የአገር አለኝታ ነው። እግዜር ቢፈልግ ኖሮ ብዙ የደከሙትን ኢንጂኔር ግዛቸውን ወይም ፕሮፌስር በየነን ያስነሳ ነበር። ያ አቅቶት አይመስለኝም። ግን የሁሉንም ልብና ኩላሊት የሚመረምር ፈጣሪ እነጎልያድን ትቶ ትንሹን ዳዊት አስነሳ፤ ምናልባት ጎልያዶችን በጎልያዶች ማጥፋት አልፈለገ ይሆናል - የፈጣሪ ሥራ እንደዚህ ነው። ከዚህ እንኳን ብዙ መማር በተገባ። 
በመሠረቱ በዚህች ዓለም ሁላችንም ነቁጥ ነን። ምንም ያህል እንማር፣ ምንም ያህል ሀብትና ገንዘብ ይኑረን፣ ምንም ያህል ዝነኞችና ታዋቂዎች እንሁን፣ በሕይወት ዘመናችን ምንም ዐይነት ተዓምር እንሥራ … ዕድሜያችን ግን ውሱን ናት - ይህን ሌጣ እውነት ከተፎካካሪ ፖለቲከኞች ስብሰባ በጣም ተገንዝቤያለሁ። በሽታ ባያውቀን፣ ማጣት ባይደፍረን፣ ፍቅር ሞልቶ ቢፈሰን … እርጅናን ግን ልናስቀራት አንችልም። ታዲያ ለዚህች ዕድሜ ብለን ለምን በሥልጣንና በሀብት ሱስ እንጠመዳለን? ለዚህች ከንቱ ዓለም ለምን የወገኖቻችንን ቁስል እያነፈረቅን በፖለቲካ ቁርቋሶ ሰበብ የሕዝብን እንባ በከንቱ እናፈሳለን? መንግሥቱና መለስ ኢትዮጵያን ልክ እንደእጅ ሥራ ዳንቴላቸው ቆጥረው ሲጫወቱብን፣ “እኔ ከሌለሁ ሁሉም የለም” ከሚል ዕብሪትና ትምክህት ያለነሱ ኢትዮጵያ አንድም መሪ ሊሆን የሚችል ዜጋ እንደማታፈራ አስበው ብዙ ተጫወቱብን። መጨረሻቸውን ስለምናውቀው አናነሳውም። ከንቱ ሰው መጨረሻውም ከንቱ ነው።
ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም። አይሳካልንም እንጂ የወላድ መካን ልናደርጋት የምንፋጭረው እኛው ነን - በተለይ ትልልቆቹ። ሰውን እንንቃለን፤ ወጣቱን በተለይ አናስጠጋውም - ልክ እንደዝንጀሮ አባት፤ (ዐቢይ አህመድ ከዝንጀሮ አባቶች እንዴት እንዳመለጠ ይገርመኛል፤ ለነገሩ እንዴት እንዳመለጠ እርሱ ራሱ በአንድ ወቅት ተናግሮታል)፤ ክፋታችን እኮ ወደር የለውም። ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ከአገራችን ይልቅ ለሥልጣናችን ቀናኢ መሆናችን ነው፤ ለሀብትና ለገንዘብ ሱሰኞች ነን፤ እንጂ ብዙ የተማሩ ሰዎች አሉ። እነሱን እየመከርንና እያቃናን ወደ ኃላፊነት ብናስገባቸው፤ በአዲስ አስተሳሰብ አዲስና ለሁሉም የምትመች አገር መሥራት በተቻለን። አሮጌ ምን ጊዜም አሮጌ ነው። በ1983 የፖለቲካ ቅኝት 2011ን ልንመራው አንችልም። ዝንታለማችንን ዳውድ ኢብሳ ወይም በየነ ጴጥሮስ ወይም አረጋዊ በርሄ ወይም መርሻ ዮሴፍ እያልን መኖር አልነበረብንም። አሜሪካኖች የአንድን ሰው ፊት ከስምንት ዓመታት በላይ እንዳያዩ በሕጋቸው የወሰኑት ወደው አይደለም። የመንግሥት ጥርስ ጠብመንጃ ስላለው - ታንክና መትረየስ ስላለው - ይሁን ግዴለም፤ የአንድን የፖለቲካ ተፎካካሪ መሪ ማለቴ “ፕሬዝዳንት”፤ ግን እንዴት ለ30 ዓመታት እንድመለከት ዕድሜ ይፍታህ ይበየንብኛል? ይችም እድል ሆና? 
እነዚህ ሰዎች ዛሬ ወይም ነገ ወደማይቀሩበት ሊሄዱ ይችላሉ። እነሱ ሄዱ ማለት ደግሞ ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ኢትዮጵያም ሄደች - እስከወዲያኛው ነጎደች ማለት ነው። ይብላኝ ለነሱ እንጂ ኢትዮጵያ ግን ትኖራለች። ዐፄዎቹ ሄዱ፤ መንግሥቱም ሄደ፤ መለስም ተጓዘ፣ “ኃይለ ማርያም”ም ከ“ሥልጣን” ወረደ - ኢትዮጵያና ሕዝቧ ግን አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። እንዲያውም ከአሁኑ በተለየ አምሮባቸውና በዓለም ላይ ደምቀው። የሆኖ ሆኖ ግን የፖለቲከኞቻችን ነገር መስተካከል ያለበት ነገር አለ። አስተሳሰባችን ካልተቀየረ የኀዘንና የልቅሶ ዘመናችን በአጭር ላይቋጭ ይችላል። 
እናም ውድ ወንድሞቼና አባቶቼ!
እባካችሁን ልቀቁን! የተሸከማችሁትን ታሪካዊ ኃላፊነት ለወጣቱ አስረክቡ። ወደ ፍቅርና መተሳሰብ ማዕድም ቅረቡ። የቆዬ ቂማችሁንና ጥላቻችሁን ትታችሁ፤ መጀመሪያ እርስ በርሳችሁ ዕርቅ አውርዱ - የጎሪጥ መተያየታችሁን ተዉት፤ ለወጣቱ ትውልድ አርኣያ ሁኑ። ብታዩት የአሁኑ ትውልድ ከእናንተ ቂምና በቀልን እንጂ ሌላ ነገርን ስላልተማረ ትቷችሁ የራሱን ኑሮ በራሱ ዓለም እየኖረ ነው። እናንተ ግን በዱሮው በሬ እያረሳችሁ በ“ማን አባት ገደል ገባ” የልጆች ጨዋታ ትቆራቆሳላቸሁ። በመሐሉ አገርን ለማፍረስ ቀን የሚጠብቁ ወገኖች የእናንተን አለመስማማት እንደወርቃማ እድል ይጠቀማሉ። 
ዕድሜ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው። ከሚጻፈው፣ ከሚነገረው፣ ከሚታየው፣ በራስ ላይ ከሚደርሰው የሕይወት ተሞክሮ መማር ካልተቻለ ከምን ይማሯል? በራስ ዓለም ብቻ በምናብ እንደተመላለሱ ማርጀት ለአወንታዊ የካርማ መዝገብ (Karmatic Record) ጠቃሚ አይመስለኝም። ከፀጉር መሸበት ጋር የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ፤ እነዚያን አለመገንዘብ ሽበትን ማስወቀስ ይሆናል፤ ድንጋይና እንጨትም ይሸብታሉና። እናም ነገ ዛሬ ሳትሉ እናንተ ታረቁና በትረ መኮንናችሁን ለወጣቱ ስጡ። ስታስረክቡም 70 እና 80 ኢትዮጵያን ሳይሆን አንዲት ኢትዮጵያን አስረክቡ። በቃ። ለመማር በጣም ዝግጁ ነኝ፤ ባጠፋሁ ይቅርታ።
 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ