S3457 እና HR2003 በተመለከተ - መስተዋል ያለበት የጋራ የዲፕሎማሲ ሥራ

ከአማኑኤል ዘሰላም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በቅድሚያ በሀገር ቤትና ከሀገር ውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ እንኳና ለአዲሱ ዓመት በሠላምና በጤና እግዚአብሔር አደረሳችሁ! አደረሰን! እላለሁ። «መጪው ዓመትም በታሪካችን አዲስ ምዕራፍ የሚጀመረበትና በአዲስ አመለካከት በጋራ ሀገራችን ኢትዮጵያ ካለችበት የድህነት አዘቅት ውስጥ የምናወጣበት ዓመት ያድርግልን!» እያልኩ ለአንባብያን ለማካፈል የፈለኳቸውንና ከውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ሥራ ጋራ የተገናኙ አንዳንድ ሃሳቦችን በትህትና ለማቅረብ እሞክራለሁ።

 

ሴናተር ራስ ፋይንጎልድ S3457 ተብሎ የተጠራውን በኢትዮጵያ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቀውን ረቂቅ ሕግ አቅርበዋል። ሕጉ በብዙ መልኩ በአሜሪካ ህዝብ ምክር ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ካለፈው HR2003 ተብሎ ከሚታወቀው ረቂቅ ሕግ እምብዛም ባይለያይም መሰረታዊ የሆኑ ጥቂት ልዩነቶች አሉት።

 

S3457 በአጭሩ

 

S3457 ሰባት አንቀጾች ሲኖሩት የመጀመሪያው አንቀጽ የረቂቅ ሕጉ ስያሜን የያዘ ነው። በስያሜው “ተጠያቂነት” የሚለው ቃል አይጠቀስም። የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብትን በኢትዮጵያ ለመደገፍ የሚል ብቻ እንጂ።

 

አንቀጽ ሁለት - የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት መስሪያ ቤት ያወጣውን ዘጋባና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ያቀረቡትን መረጃዎች በማሰባሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ገጽታና ከዚህ በፊት የተከሰቱ አሳዛኝ ክስተቶችን በሰፊው የሚዘግብ ነው። እነዚህም አብዛኞቻችን የምናውቃቸውና የምንመሰክራቸው ብዙም የማያከራክሩ ጉዳዮች ናቸው።

 

አንቀጽ ሦስት - አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን ፖሊሲ አስታውሶ አምስት ቁልፍ ነጥቦች ይጠቅሳል። እነርሱም

 

• ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ለመገንባትና ፀረ-ሽብረተኝነት ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት መደገፍ፣

 

• በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ የሕግ የበላይነትና፣ ልማት፣ … እንዲሰፍን፣

 

• የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ፣

 

• ሰብዓዊ መብትን ለሚረግጡና ግፍን ለሚሠሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት ክፍሎችና የደህንነት ኃይላት የሚሰጡ ማናቸውንም እርዳታ ማገድ (መንግሥት ወንጀለኞችን ለፍርድ እስካላቀረበ ድረስ)፣

 

• የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮ-ኤርትራን ቦርደር ኮሚሽን የወሰነውን ውሳኔ መቀበል እንዳለበት ናቸው።

 

እነዚህ ነጥቦች በአሜሪካ አምባሣደርና በውጭ ግንኙነት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች በኩል ሁልጊዜ ስንሰማቸው የነበሩ በሥራ አስፈጻሚውም አካል ዘንድም ተቀባይነት ያላቸው ብዙም በአሜሪካ ባለሥልጣናት ዘንድ የማያወዛግቡ ናቸው ብዬ አስባለሁ።

 

አንቀጽ አራት - ሴኔቱ ሊያስተላልፍ የሚፈልጋቸውን ስድስት አቋሞችን ይዘረዝራል። እነርሱም በአጭሩ የሚከተሉት ናቸው፦

 

• የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱን በአዎንታዊነት በመመልከት በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚን በመጠቀም የተሻለ ክንዋኔዎችን ወደፊት ማድረግ እንዲቻል፣

 

• የኢትዮጵያ መንግሥት ለዕርቅ ፍላጎት ካላቸው የተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ለውይይት እንዲቀርብ ማበረታታት፣

 

• የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲያከብር መማጸን፣

 

• የሰብዓዊና የሰብዓዊ ድርጅቶች የመንቀሳቀስ መብት እንዲጠበቅና ጋዜጠኞች ያለተጽዕኖና እንግልት በየክልሉ መሥራት እንዲችሉ ማበረታታት፣

 

• በሰዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ግፍ የፈጸሙትን ግለሰቦችና ድርጅቶች ተጠያቂ ለማድረግ እንዲረዳ፣ የተባበሩት መንግሥታም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መረጃ ለማሰባሰብ የሚያደርጉትን ጥረቶች የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲደግፍና እንቅፋት እንዳይፈጥር፣

 

• በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዕርቅ እንዲሰፈን፣ ኢትዮጵያም የድንበር ኮሚሽኑ ያቀረበውን ውሳኔ እንድትቀበል (ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ተቀበለች ማለት ባድመ ለኤርትራ ተሰጠች ማለት ነው)

 

አንቀጽ አምስት - የሴኔቱን አቋም ተግባራዊ ለማድረግ የሥራ አስፈጻሚው አካል ሊወስዳቸው የሚገቡትን ድርጊቶች ዘርዝሮ ለሥራውም እንዲረዳ 20 ሚሊዮን ዶላር ባጀት ይመድባል።

 

አንቀጽ ስድስት - ሃያ ሚሊዮን ዶላሩ ለናሳ (የአሜሪካ የጠፈር ምርመራ መሥሪያ ቤት) ተመድቦ ከነበረ ወጪ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ሲሆን፣

 

አንቀጽ ሰባት - ደግሞ በረቂቅ ሕጉ ላሉ አንዳንድ አባባሎች ትርጓሜ ይሰጣል።

 

S3457 እና HR2003 ይለያያሉን?

 

በመሰረቱ ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች ከላይ በግርድፉ ይለያያሉ እንጂ በውስጣቸው ብዙም ልዩነቶች ያላቸው አይመስለኝም። ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች ጥርስ ያላቸውና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቀጥተኛ ተጽኖ የሚያመጡ አይደሉም።

 

እርግጥ HR2003 እንደ ቪዛ መከልከል አይነት ጥርስ እንዳለ የሚያስመስሉ አንዳንድ እገዳዎችን ይዘረዝራል። ነገር ግን እነዚህ እገዳዎች ቢዘረዘሩም ቅሉ ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉና በቀላሉ በሌላ አማራጭ መንገዶች የሚጣሱ ናቸው ብዬ አስባለሁ።

 

አንዳንድ የዚህን ሕግ ጥቅም ከመጠን በላይ የለጠጡ ቡድኖች HR2003 ጥርስ እንዳለው አድርገው በማቅረብ ህዝባችንን ሲያወናብዱት እንደነበረ የምናስታውሰው ነው። ነገር ግን HR2003 የፕላስቲክ ጥርስ አድርጎ ስለነበረ ጥርስ እንዳለው ተደርጎ በስህተት ተወሰደ እንጂ ጥርስ አልነበረውም። (“HR2003’ን በተመለከተ ያሉ ግራ መጋባቶች” በሚል ርዕስ ያቀረብኩት ጽሑፍ እንዴት HR2003 ጥርስ እንደሌለው በግልጽ ለማሳየት ሞክሬአለሁ።) 

 

ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች ሃያ ሚሊዮን ዶላር ለዲሞክራሲ ግንባታ ለኢትዮጵያ ይመድባሉ። ሁለቱም በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ግንባታው ሂደት ሃዲዱን ስቶ እያሽቆለቆለ እንዳለ በግልጽ አስቀምጠዋል። ሁለቱም በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት በጣም ቁልፍ እንደሆነና የበለጠ መጠናከር እንዳለበት አስምረውበታል።

 

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ረቂቅ ሕጎቹ የሚያመሳስላቸው ብዙ ነጥቦች ቢኖሯቸውም በቁጥር የማይናቁ ልዩነቶችም አሏቸው። ከነዚህም ልዩነቶች ውስጥ ስድስቱን ብቻ እንደ ክብደታቸው ደረጃ ለመጠቆም እሞክራለሁ።

 

• HR2003 ስለ ኤርትራ ብዙም አልጠቀሰም። S3457 የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ኮሚሽን የወሰነውን ውሳኔ ኢትዮጵያ እንድትቀበል ይጠይቃል። በሌላ አባባል የብዙ ወጣቶቻችን ደም መፍሰስ ምክንያት የሆነችው ባድመ ለኤርትራ እንድትሰጥ ነው ረቂቅ ሕጉ የሚጠይቀው።

 

ይህ መሰረታዊ ችግርን የሚፈጥር፣ እንዳለ ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት እንዲያጣና የተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንዳይደግፉት ሊያደርግ የሚችል በጠቃሚ አንቀጾች ውስጥ የተተከለ መርዝ አድርጌ አየዋለሁ።

 

የድንበር ኮሚሽኑን የአልጀርሱ ስምምነት ነው የወለደው። የአልጀርሱ ስምምነት ደግሞ ያለህዝብ ፍቃድ ኢህአዲግ የወሰነው ፀረ-ኢትዮጵያ ውሳኔ ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር ባድመ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ግዛት መሆኗ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። (እንደውም እራሷ ኤርትራ የኢትዮጵያ ናት በታሪክና በሕግ አኳያ ከተወሰደ።)

 

• HR2003 የኢትዮጵያን መንግሥት በበለጠ የተጫነ የሚመስልና ላይ ላዩን ኃይለኛ እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠር ረቂቅ ሕግ ነው። S3453 በአንጻሩ በውስጣዊ ተግባራዊ ይዘቱ እምብዛም ከHR2003 ባይለይም የኢትዮጵያ መንግሥት የበለጠ ወደ ቀናው መንገድና እርቅ እንዲመጣ መምከሩና ማበረታታቱ ላይ ያተኮረ ይመስላል። ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች ዓላማቸውና ይዘታቸው አንድ ሆኖ እያለም አቀራረባቸውና ቶናቸው የተለያየ እንደሆነ እናያለን።

 

ለዚህም ነው በሴኔቱ ረቂቅ ሕግ ላይ በርካታ ጊዜ “እናበረታታለን” የሚል ቃል የምናነበው። ለዚህም ነው በHR2003 እንደምናየው “ይህን ካላደረጋችሁ ይሄ ይከተላል” የሚሉ የማስፈራሪያ ሃረጎች በS3453 ውስጥ የማናነበው።

 

• S3457 በተለየ መልኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሀገሪቱን ሕግ ይጋፋል ተብሎ በማያስፈርጅ መልኩ የቀረበ ነው። ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው የኢህአዲግ ባለሥልጣናት HR2003’ን እንደ ውጫሌ ውል ቆጥረው፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገባች እንደሆነ ሲናገሩ ነበር።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዴት ኢትዮጵያ የራሷ ሕግ አውጪ አካል እያላት የሌላ ሀገር ሕግ አውጪ አካል በኢትዮጵያ ላይ ሕግ ያወጣል ብለው በፓርላማ ንግግራቸው HR2003 ለማጣጣል የተናገሩትን አስታውሳለሁ። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተረዱት ወይንም አማካሪዎቻቸው በደንብ ያላስረዷቸው ነገር ቢኖር HR2003 በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ የሚጠይቅ ረቂቅ ሕግ ሳይሆን አሜሪካኖች በራሳቸው ገንዘብና በራሳቸው ሀገር ጉዳይ ላይ የወሰኑት ውሳኔ ነው። (ስለኢትዮጵያ ሕጉ ቢናገርም አሜሪካ ለኢትዮጵያ ስለምትሰጠው የራሷ ገንዘብና ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ ሲመጡ ማን ቪዛ ይሰጠው የሚለውን ነው ሕጉ የዳሰሰው።)

 

አሜሪካኖች የራሳቸውን ገንዘብ በፈለጉት መልኩ የማደላደልና ማን ሀገራቸው መግባት እንዳለብት የመወሰን ሙሉ መብት እንዳላቸውም የኢህአዲግ ባለሥልጣናት ያጡታል ብዬ አላስብም።

 

የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በማይታሰብና በማይዛመድ መልኩ ለጥጠውት በመተርጎም HR2003ን እንዳጠቁ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይመስለኛል፣ በአንቀጽ አምስት መጀመሪያ ዐረፍተ ነገር ላይ፣ የዲሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት መከበርና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ ይሰፋ ዘንድ፣ በረቂት ሕጉ የተዘረዘሩት ነጥቦች በኢትዮጵያ ያለውን ሕገ-መንግሥት በጠበቀ መልኩ ለማስፈጸም እንዲሞከር S3457 በግልጽ ያስቀመጠው።

 

S3457 የኢትዮጵያን ሕገ-መንግሥት ሆነ የሀገር ሉዓላዊነት የሚጻረር ሕግ አይደለም። ነገር ግን ኢትዮጵያ አንድ እርምጃ እንድትራመድ ለመርዳት የሚሞክር በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ለማገዝ የተረቀቀ ሕግ ነው።

 

• HR2003 ከመንግሥት ውጭ በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች የተሠሩ ግፎችን አላቀረበም። S3452 ግን ሚዛናዊነት ይታይበታል። የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር በሠላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸመውንና እየፈጸመ ያለውን ሽብር የሴኔቱ ረቂቅ ሕግ ዘግቦታል። የውጭ ግንኙነት መሥሪያ ቤትን በመጥቀስ በS3453 በአንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ 10 ኦብነግ በሠላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳደረገ ነው የምናነበው።

 

• HR2003 እንዲሁም S3457 ሃያ ሚሊዮን ዶላር ለዲሞክራሲ ግንባታ በጀት የመደቡ ሲሆን፣ HR2003 በግልጽ ሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኙ ጠቅሷል። S3457 ብዙም የገንዘቡ አጠቃቀም ሁኔታ ላይ የሰጠው ትንታኔ የለም።

 

ከአሁን በኋላ ወዴት?

 

S3457 በሴኔት ውስጥ ብዙ ተቃውሞ የሚገጥመው አይመስለኝም። ብዙ አከራካሪና አወዛጋቢ ነጥቦች የሉበትም። ድንገት 20 ሚሊዮን ዶላር ከናሳ በጀት መውጣቱን የሚቃወሙ ሴናተሮች ካሉ በገንዘቡ ምክንያት ችግር ካልተፈጠረ በቀር የአሜሪካን ሴኔትን በቀላሉ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊያልፍ የሚችል ነው ብዬ አስባለሁ።

 

በዚህ አጋጣሚ ብዙ እንደሰይጣን ሲደበደቡ የነበሩትና ከሁለት ወር በኋላ በሚደረገው ምርጫ ተቀናቃኛቸውን ከ20 ነጥብ በላይ በህዝብ አስተያየት እየመሩ ያሉ የኦክላሆማው ሴናተር ኢንሆፍም ሊደግፉት የሚችሉት ረቂቅ ሕግ እንደሆነ እገምታለሁ።

 

የግጭት ፖለቲካን ከማራገብ በአክብሮት እኝህንና ሌሎች ሊቃወሙ ይችላሉ የሚባሉትን ሴናተሮች በማስተዋል መቅረብና ማነጋገር ከቻልን ብዙ ልንደነቅ እንችላለን።

 

S3457 በሴኔት ከፀደቀ በኋላ ከሴኔትና ከህዝብ ምክር ቤት የተወጣጡ HR2003 እና S3457 ለማስታረቅ ይሞክራሉ። ከዚያም ሁለቱም የሕግ አውጪ ክፍሎች የተስማሙበት አንድ የጋራ ሕገ ረቂቅ ይዘጋጅና ድምፅ ተሰጥቶበት ለፕሬዘዳንቱ ፊርማ ይሄዳል።

 

የጋራ ረቂቅ ሕጉ በS3457 ካለው ጋር የበለጠ የሚጠጋጋ ከሆነ የአሜሪካ የሥራ አስፈጻሚ አካልም እንደሚደግፈው ነው። ስለሆነም ፕሬዝዳንቱ በቀላሉ ይፈርሙታል ብዬ አምናለሁ።

 

S3457 ከኅዳር ወር 2001 ዓ.ም. መጨረሻ በሙሉ ሴኔት ውስጥ ድምፅ ካልተሰጠበት HR2003 ይሞታል። ከጥር በኋላ እነ ኮንግረስማን ዶናልድ ፔን እንደገና ተመሳሳይ ሕግ ማውጣት ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ያኔ ፕሬዝዳንቱ ሴኔተር ኦባማ ወይንም ሴኔተር ማኬን ነው የሚሆኑት። ራስ ፋይንጎልድ በሴኔተር ማኬን በጣም ተሰሚነት ስላላቸው (በርካታ ዓበይት ሕጎች እንዲወጡ አብረው የሠሩ ናቸውና) ሴኔተር ኦባማ ደግሞ እንደ ሰኔተር ፋይንጎልድ ዲሞክራት ስለሆኑ ይህ ረቂቅ ሕግ በመጪው የአሜሪካ አስተዳደርም ችግር የሚያጋጥመው አይመስለኝም።

 

የኛ የኢትዮጵያውያን ድርሻ ምንድን ነው?

 

በመጀመሪያ ደረጃ ሁላችንም የዚህን ረቂቅ ሕግ መንፈስ መረዳት አለበን። ሕጉ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን መንግሥት ለመቅጣት የተረቀቀ አይደለም። ሕጉ አሁን ያለውን መንግሥት እንደ አጋር የሚያይ ሕግ ነው። ሕጉ የኢህአዲግ ባለሥልጣናት አላወቁትም እንጂ ኢህአዲግን እራሱ የሚጠቅም ሕግ ነው። የዚህ ሕግ ዓላማ በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ዜጋ መብቱ ተከብሮ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተጠብቆ ኢትዮጵያ ካለችበት አዘቅት እንድትወጣ የሚያግዝ ሕግ ነው። በኢትዮጵያ ዕርቀ ሠላም እንዲመጣ የሚያበረታታ ሕግ ነው።

 

በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ረቂቅ ሕግ ሲወጣ በኛ በኩል ማድረግ ያለብንን ሁሉ በጥንቃቄና በማስተዋል ማድረግ ይጠበቅብናል። ዲፕሎማሲ ወይንም የውጭ ግንኙነት ሥራ በስሜት፣ በእልህ ወይንም በመገናኛ ብዙኀን ፕሮፖጋንዳ የሚሠራ አይደለም። ከቀድሞ አባቶቻችን ከእነአምባሣደር እምሩ ዘለቀ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ የምንማራቸው ብዙ ጥበቦችና ዘዴዎች አሉ። የአሜሪካ የፖለቲካ ሣይንስ መጻሕፍትን ለጊዜው ትተን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ከስድሳ ዓመታት በፊት በአምባሳደሮቻችን በኩል ሲደረግ የነበረውን ታሪክ መለስ ብለን ብናጠና ብዙ እንማር ነበር።

 

በተለይም HR2003-ኮአሊሽን እየተባለ የሚታወቀው ቡድን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ብዙም አይጥመኝም። ይህ ቡድን መግለጫዎችን በመገናኛ ብዙኀን እያወጣ፣ ኢትዮጵያውያን አላስፈላጊ ፋክሶች፣ ወረቀቶች እንዲልኩና የሴናተሮችን ሠራተኞች በባዶ የማድከም ሥራ እንዲሠራ ነው ሲያደርግ የነበረው። አንድ ወቅት ለምሳሌ ለ100 ሴናተሮች HR2003’ን እንዲደግፉ ፋክሶችና ኢ-ሜይሎች ለወራት ሲላክ እንደነበረ አስታወሳለሁ። ለፕሬዘዳንት ጆርጅ ቡሽ ከአስር ገጽ በላይ የሆነ ሰነድ ከመቶ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ፋክስ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ዘመቻ እንደነበረ አስታውሳለሁ። እግር ኳስ ለመጫወት የቴኒስ ራኬት ይዞ መምጣት! …

 

የሎቢና የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሠራው በጥንቃቄና በማስተዋል ነው። ኢትዮጵያውያን እንደ ሜክሲኮዎች ወይንም ይሁዶች ብዛትና የገንዘብ አቅም ያለን አይደለንም። የHR2003-ኮአሊሽን ዘዴ የሚሠራው ለእንደዚህ አይነቱ ማኅበረሰቦች ነው።

 

አሁን HR2003-ኮአሊሽን እንዳደረገው ሴናተሮችን በመጨቅጨቅና በመጫን ደብዳቤዎች በብዛት ፋክስ በማድረግ ወደእኛ ልናመጣቸው አንችልም። እውነታው ይሄ ነው። ስለዚህ ወደድንም ጠላንም የእነርሱን መልካም ፈቃደኝነት ማግኘት ካልቻልን የትም አንደርስም።

 

HR2003 ሕግ የሆነው እነ ኮንግረስማን ክርሲ ስሚዝ እና ዶናልድ ፔን አይነት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተቆርቋሪ ሰዎች ስላገኘን ነው። (አንድ ወቅት እንደውም ዶናልድ ፔንንም የምንሳደብ ሰዎች ነበርን።)

 

ሴናተር ፋይንጎልድ S3457’ን ሲያረቁ በውስጣቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ ስላሳሰባቸው ነው። ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን፣ በርካት ጊዜ በሴኔት ውስጥ ስለኢትዮጵያ ንግግር አድርገዋል። ያለፈው ዓመት ከአስር በላይ ሴናተሮችን በማስተባበር እስረኞች እንዲፈቱ የጋራ ጥሪ ያደርጉ ሰው ናቸው።

 

አብረዋቸው የዚህ ሕግ ስፖንሰር የሆኑት ሴናተር ፓትሪክ ሌሂም በዚያ አካባቢ ያሉ ስማቸውን የማናውቃቸው ኢትዮጵያውያን ከወዲሁ በየጊዜው የኢትዮጵያን ጉዳይ ስለሚያስረዷቸው በሥራ ኢትዮጵያም ባይሄዱም በልባቸው ኢትዮጵያን የሚያውቁና የሚወዱ የተከበሩ ሰው ናቸው።

 

በብዛት ፋክስ ስለተደረገላቸው ወደፊት እንዳይመረጡ የኢትዮጵያውያንን ድምፅ ስለፈሩ አይደለም ዶናልድ ፔን፣ ክርሲ ስሚዝም፣ ፓትሪክ ሌሂ እና ራስ ፋይንጎልድ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ረቂቅ ሕግ ያወጡት። ነገር ግን ለሰብዓዊ መብት ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡና ኢትዮጵያን ስለሚወዱ እንጂ።

 

ታዲያ ኢትዮጵያን የሚወዱትን ለማብዛት ትሁት፣ ትዕግስተኛ፣ ብልህ ዲፕሎማት፣ … መሆንን ይጠይቃል። ዛሬ እኛን ባይደግፉ ታግሰን ሁሉን በሆዳችን ይዘን ነገ ወደእኛ እንዲመጡ መጣር ነው የሚያስፈልገው። ብንሰድባቸው፣ ብናጋልጣቸው፣ ብናኮርፋቸው፣ ብናብጠለጥላቸው፣ … የትም አንደርስም። (ሴናተር ኢንሆፍን አንመለከትም - ይኸው በብዙ ድምፅ እንደገና ይመረጣሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው። እንደውም እርሱን ማጥቃቱ ላይ ከምናዘነብል በትዕግስት ወደእኛ ለማምጣት ብንሞክር ይሻል ነበር።)

 

ለማጠቃለል

 

የወደፊት ጉዟችንን ይረዳ ዘንድ የሚከተሉትን ሃሳቦች አቅርቤ አቆማለሁ።

 

• S3457 ሕግ ከመሆኑ በፊት መስተካከል ያለባቸውን ነጥቦች (ለምሳሌ የኤርትራን ጉዳይ ከረቂቅ ሕጉ ስለማስወጣት) የሚመክርና በጥንቃቄ የሴናተር ራስ ፋይንጎልድ ጽ/ቤት ጋር ግንኙነት ፈጥሮ የሚሠራ ግብረ ኃይል በአስቿኳይ ያስፈልገናል። HR2003-ኮአሊሽን ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው ይህ ጉዳይ የመገናኛ ብዙኀን ወይንም የፕሮፖጋንዳ ጨዋታ አይደለም።

 

በርካታ በዲፕሎማሲ የተካኑ አዋቂ ኢትዮጵያውያን አሉ። አምባሣደር የነበሩ፣ የሕግ ሰዎች፣ የፖለቲካ ሣይንስ ጠበብት፣ በዋሺንግተን ዲሲ ደግሞ በካፒታል ሂል የሴኔት ሠራተኞችን የሚያውቁ ብዙ አሉ። እነዚህ ተለይተው ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ ሥራው እንዲሠራ ቢደረግ መልካም ነው። (ከመገናኛ ብዙኀኑ ፕሮፖጋንዳ ውጭ ውስጥ ለውስጥ የሚሠራ ሥራ ማለቴ ነው።)

 

የአንድነት የድጋፍ ድርጅት የዲፕሎማሲ ኮሚቴ፣ ዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያን አሜሪካን ሲቪክ አድቮከሲ ግሩፕ፣ አቶ መስፍን መኮንን የሚመሩት የመኢአድ ድጋፍ ድርጅት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ፣ HR2003-ኮአሊሽን፣ የአኝዋክ ጀስቲስ ካውንስል፣ የኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ ፎረም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጉባዔ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አይነቶቹ በአንድ ላይ ሆነው ለጅምሩ ያህል ይህ ሕግ የሚሻሻልበትን ሁኔታ ቢሠሩ እንደአንድ ጊዜያዊ አማራጭ መልካም ሊሆን ይችላል።

 

 

 

• ኢትዮጵያውያን በየስቴቱ ያሉ የሴኔተሮቻቸውን ሠራተኞች ከወዲሁ መቅረብና ያለውን ሁኔታ ማስረዳት ይጠበቅብናል። የሴኔት ረቂቅ ሕግ ስላለም ይህን ሕግ ኮስፖንሰር እንዲያደርጉ የመጠየቅ ሥራ በተቀናጀና ስሜታዊ ባልሆነ መንገድ መሠራት መጀመር አለበት።

 

• የዚህን ሕጋ ዓላማ ካለመረዳት የተነሳ S3457’ን የሚቃወሙ የኢህአዲግ ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለነዚህ ያለኝ መልዕክት S3453’ን በእርጋታ እንዲያነቡት ነው። ነገር ግን እንዲሁ በጭፍን ፖለቲካ መቆየት የወደዱ ከሆነ በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ ጥቃታቸውን ሊሰነዝሩ ይችላሉ። ስለዚህም ይህን ተረድተን በእነርሱ ዘንድ ለሴናተሮቹ ሊቀርቡ የሚችሉትን ተቃራኒ ሃሳቦች ውድቅ ለማድረግ በስሜት ላይ ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሰረቱ መከራከሪያዎች ማቅረብ ይጠበቅብናል።


 

ከአማኑኤል ዘሰላም  ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) መስከረም 2 ቀን 2001 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!