ከጊዜው ይታየው

"ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክህነቱ ያገኘውን ቦታ፣ ያቀፋቸው አባላት ያላቸውን ሁሉን ዐቀፍ ዕውቀት፣ ያሰባሰበውን ብሔራዊ ተዋጽኦ፣ የዘረጋውን ዓለም አቀፋዊ መዋቅር ያህል በምሣሌነት ከላይ እንዳነሣናቸው ማኅበራት የጎላ ሀገራዊ አስተዋጽዖ አይታይበትም። ከኃይማኖት ክርክሮች፣ ከመጻሕፍት እና መዝሙሮች፣ ከጉባዔያት እና ስብሰባዎች ባለፈ ለሀገር ዕድገት እና ለህዝቡ ማኅበራዊ አገልግሎት መስፋፋት ብሎም ኅብረተሰቡን ለዕድገት በማነሣሣት ረገድ ዘገምተኛነት አስተውላለሁ።"

ከላይ ያለው "የመንፈሣውያን ማኅበራት ሀገራዊ አስተዋፅዖ" በሚል ርዕስ ጊዜው ይታየው ከፃፉት አስተያየት የተቀነጨበ ነው።

 


መንፈሣውያን ማኅበራት በመላው ዓለም ልዩ ልዩ የእምነት ተቋማት ዘንድ የተለመዱ ናቸው። በዋናነት የሚለዩበት ጠባያቸውም እምነታቸውን ጠብቀው በልዩ ልዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች መሳተፋቸው እና ሁለት ተግባራትን ማከናወናቸው ነው። በአንድ በኩል ሰማያዊ ዋጋ እናገኝበታለን ብለው የሚያምኑትን ኃይማኖታቸውን መሠረተ እምነቱ፣ ሥርዓቱ እና ትውፊቱ ተጠብቆ ይኖር ዘንድ ይተጋሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ለመጠበቅ መሠረቱ ሰው ነውና የሰው ማኅበራዊ ኑሮ የሚደገፍበትን፣ መብቱ ተከብሮ የሠላም ሕይወት የሚገፋበትን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ይሰጣሉ።

 

እነዚህ መንፈሣውያን ማኅበራት ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ያደረጓቸው ሦስት መሠረታዊ ጠባዕያት ስላሏቸው ነው። የመጀመሪያው በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡ መሆናቸው ሲሆን፣ ይህም የተቀጣሪነትን ስሜት በማጥፋት ሰዎች ያለማንም አስገዳጅነት ወይም ቆስቋሽነት ላመኑበት ዓላማ ግብ መምታት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል። ሁለተኛው ደግሞ ለአገልግሎታቸው ዋጋን ከፈጣሪያቸው የሚጠብቁ እና እርሱንም የሚፈሩ በመሆናቸው ታማኝነትን፣ ለሙስና እና ለራስ ወዳድነት ሳይጋለጡ መሥራትን እንዲሁም የሚደርስባቸውን ማንኛውንም ተጽዕኖ መቋቋምን አጎናጽፏቸዋል። ሦስተኛው ጠቃሚ ጠባያቸው ደግሞ የኃላፊነት ቦታዎቻቸው መስዋዕትነትን የሚጠይቁ በመሆናቸው ለሥልጣን በሚደረግ አጓጉል ሽኩቻ ውስጥ ያን ያህል ጠልቀው እንዳይገቡ ማድረጉ ነው።

 

በእርግጥ እነዚህ የመንፈሣውያን ማኅበራቱ ጠባዕያት ሁልጊዜም ተጠብቀው ይገኛሉ ማለት አይደለም። ከእነዚህ አንዱ እንኳን ተሸርሽሮ በሚገኝበት ጊዜ ማኅበራቱ የሚገጥማቸውን ድቀት በዓለም ታሪክ በተለያዩ ዘመናት ታይቷል። እንኳንስ እምነትን መሠረት አድርገው የሚጓዙት ማኅበራት ቀርቶ ራሳቸው የእምነት ተቋማቱ እንኳን ከላይ የተገለጡት ጠባዮቻቸው ሲጠፉ ምን እየመሰሉ እንደ መጡ በአሜሪካ ያለችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የገባችበት ሕፃናትን የተመለከተ ውድቀት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አንዳንድ መነኮሳት እና ጳጳሳት ያሉበት የሥልጣን፣ የዘር እና የጥቅማ ጥቅም ሩጫ ማሣያ ይሆነናል።

 

በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ጠባዕያት ጠብቀው በነበሩበት ጊዜ እና በዘለቁበት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የካቶሊክ መንፈሣውያን ማኅበራት፣ የፍልስጥኤም ሙስሊሞች መንፈሣውያን ማኅበራት የፈጸሟቸው በጎ አገልግሎቶች ምሳሌዎቻችን ይሆናሉ።

 

በልዩ ልዩ ምንኩስናዊ ሥርዓቶች መሠረትነት የተቋቋሙት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መንፈሣውያን ማኅበራት ሌላው ቀርቶ በአሜሪካን ሀገር እንኳን ደረጃውን እና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እና የጤና አገልግሎት እንዲኖር አስችለዋል። ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎችን እና ሆስፒታሎችን በመገንባት፣ አባሎቻቸው ሙያዊ በሆነውና የሰው ልጅን መሠረታዊ ችግር ሊፈታ በሚችለው መስክ እንዲሰማሩ በማድረግ ለማኅበረሰቡ ቅርብ የሆኑ አገልግሎቶችን ሰጥተዋል።

 

በአሜሪካን ሀገር የጤና አገልግሎቶች የካቶሊክ እና የካቶሊክ ያልሆኑ ተብለው እስከ መመደብ የደረሱት እነዚህ መንፈሣውያን ማኅበራት ይከተሏቸው የነበሩትን መንፈሣውያን/ማኅበራውያት ዕሴቶችን በተቋማቱ በማንጸባረቃቸው ነው። ጽንስ ማስወረድን በመሰሉ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋራ ጥብቅ ግንኙነት ባላቸው እና የእምነት ተቋማትን የኃይማኖት ድንጋጌ በሚጠይቁ ጉዳዮች የአሜሪካ የካቶሊክ ሆስፒታሎች ያላቸው የተቃውሞ ድምፅ ከፍተኛም ኃይለኛም ነው። በዩኒቨርሲቲዎቻቸው በሚከተሉት የሥነምግባር እና የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤ ጠበቅ ያለ መሆን፣ በልቅነት ከሚጓዙት ሊበራል የትምህርት ተቋማት ተለይተው እንዲታወቁም አድርጓቸዋል።

 

ይህም ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ እና በአውሮፓ ከሚገኘው ገንዘብ የመክፈል ዐቅም ካለው ኅብረተሰብ በሚሰባሰብ የአገልግሎት ክፍያ፣ አቅም የሌለው የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካ እና የእስያ ህዝብ እንዲረዳ በማድረግም አስቸጋሪ የሆነውን የሀብት ሽግሽግ ለማከናወን ሞክረዋል። በሕንድ እና በላቲን አሜሪካ ድኾች ዘንድ የካቶሊክ መንፈሣውያን ማኅበራት ያከናወኑት ትምህርትን ጤናን፣ ንጹኅ ውኃ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን የማስፋፋት እንቅስቃሴ የብዙዎችን ሕይወት ለውጧል። የማኅበራቱ አባላት በበጎ ፈቃደኛነት ምዕራባውያን ተቋማት በሚፈሯቸው፣ ግጭት እና ተፈጥሯዊ ችግር በሞላባቸው አካባቢዎች በመዝለቅ ያበረከቱት አስተዋፅዖ የሚደነቅ ነው።

 

ከላይ በሁለተኛ ምሣሌነት ያነሣናቸው የፍልስጥኤማውያን መንፈሣውያን ማኅበራት፤ በፍልስጥኤም እስራኤል ግጭት የሚታመሰውን ህዝባቸውን ለመታደግ ከራሳቸው እና ድጋፍ ከሚያደርጉ አካላት የሚያገኙትን አቅም በማስተባበር፣ ጠንካራ መንግሥታዊ ተቋማት የሌሉት የፍልስጥኤም መንግሥት ያልሠራውን ሥራ ሠርተዋል። የውኃ ጉድጓዶች በማስቆፈር፣ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው በበጎ ፈቃደኛነት በማስተማር፣ በተማሩት የሕክምና ትምህርት የነፃ አገልግሎት በመስጠት፣ ሌላው ቀርቶ በፍልስጥኤም አንጃዎች መካከል የሚፈጠረውን ደም ማፍሰስ ለማቆም እንኳን በሽምግልና በመግባት የማይናቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል።

 

እርስ በእርሳቸው ሊጠፋፉ በሚፈልጉ በልዩ ልዩ አንጃዎች በተሞላችው ፍልስጥኤም ውስጥ አንዱን ደግፈው ሌላውን እንዲቃወሙ፣ የአንደኛው ደጋፊ ለሆኑ አካላት አገልግሎት እንዳይሰጡ፣ ከተነሱበት እምነት ተኮር አገልግሎት ወጥተው ፖለቲካዊ አዝማሚያ እንዲይዙ የሚደረግባቸውን ተጽዕኖ መሥዋዕት በመኾን ሊቋቋሙ የታገሉት የፍልስጥኤም መንፈሣውያን ማኅበራት ለሌሎች አርኣያ የሚሆን ገድል አላቸው።

 

“ማኅበራተ ክርስቶስ” (Societies of Christ) በሚል ርዕስ በ1998 እ.ኤ.አ. መጽሐፍ ያሳተሙት እስጢፋኖስ ዲ. አባዲ የተባሉ የካቶሊክ መነኩሴ “እነዚህ መንፈሣውያን ማኅበራት ለረዥም ዘመን የዘለቀ፣ ኅብረተሰቡን ሊጠቅም የሚችል እና ውጤታማ ሥራ ሊሠሩ የሚችሉት ስድስት ነገሮችን ገንዘብ ካደረጉ ብቻ ነው” ይላሉ።

 

እርሳቸው የሚያነሱት የመጀመሪያው ነገር፣ አሳታፊ የሆነና ግልጽ አሠራር ነው፤ በበጎ ፈቃድ የሚሰባሰብ ኃይል ጉልበቱን፣ ጊዜውን እና ገንዘቡን ሠውቶ ዋጋ ያለው አገልግሎት ሊሰጥበት የሚችል፣ ያለአድልዎ የሚለገስ ሥፍራ ይፈልጋል። የተወሰኑ ሰዎች ሠሪ ሌላው ተመልካች፣ የተወሰኑ ሰዎች ሁሉን ዐዋቂ ሌላው አጨብጫቢ የማይሆንበት፣ ሁሉ ያለውን የሚሰነዝርበት የአገልግሎት ሥፍራ ሊከፈት ከቻለ በጎ ፈቃደኞች የሚሰጡትን ልግስና ይጨምራሉ።

 

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ግልጽ የሆነ አሠራር ነው። ”የኃላፊዎችን አመራረጥ ወይም አወካከል፣ የአሠራር ሂደቱን፣ የገንዘብ አያያዝ እና አሠራሩን፣ የአባላት አመላመል እና አወጋገዱን፣ … ወዘተ በተመለከተ ማንኛውም ሰው ሊረዳው የሚችል ግልጽ ነገር ያስፈልጋል” ይላሉ። ይህም እነዚህ ማኅበራት መታወቂያቸው የሆነውን ታማኝነትን እንዳያጡ ያደርጋቸዋል። በአንዳንድ የፖለቲካ ተቋማት እንደሚታየው ”በአመራር ውስጥ ያለ ስውር አመራር” በእነዚህ የበጎ ፈቃድ ተቋማት ውስጥ እንዳይፈጠር፣ ያልተመረጡ እና ያልተሰየሙ አካላት የሚመሩት አመራር እንዳይኖር ጥንቃቄ መወሰድ አለበት።

 

መተካካት ሌላው የዲ. አባዲ ሦስተኛ ነጥብ ነው። ”በእርግጥ መንፈሣዊ አገልግሎት በዕድሜ የሚወሰን ባለመሆኑ ረዥም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ከሚገኙባቸው ተቋማት አንዱ እነዚህ ማኅበራት ናቸው” ይላሉ። ነገር ግን ይህም ቢሆን በበጎ ፈቃድ የተሰበሰበን አካል ያለተሳትፎ ይዞ መዝለቅ አይቻልምና ቀደምቶቹ ለተተኪዎች በተገቢው ጊዜ ኃላፊነትን የሚያወርሱበት ቅብብል ያስፈልጋል። አለበለዚያ ግን ”ከተሣታፊነት ይልቅ የተመልካችነት አባዜ እየጨመረ ይመጣል” ባይ ናቸው። መተካካት ማለት ነባሩ አመራር ሌሎች አዲስ ፊቶችን ለማሳደግ ሲችል ነው። በአንዳንድ ማኅበራት እንደሚታየው ለተወሰኑ ዓመታት ገለል ብለው የነበሩ አመራሮች ተመልሰው ቦታውን ሲይዙ አይደለም ወይም ደግሞ ”ሂዱና ቤታችሁን ሠርታችሁ፣ ልጆቻችሁን አሣድጋችሁ ስትጨርሱ ኑ” የተባሉ ይመስል ዐረፍ ብለው የመጡ አመራሮች ወደ ቀደመ ርስታቸው ሲመለሱም አይደለም።

 

ተጽዕኖን መቋቋም። እነዚህ በበጎ ፈቃድ አምላካቸውን ፈርተው የተሰባሰቡ መንፈሣውያን የየራሳቸው ርዕዮተ ዓለም ወይም አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይችላል። ይህም ቢሆን ግን ማኅበራቱ ከተነሱበት ዓላማ ውጭ ሊወስዳቸው ወይም ደግሞ ሊያግዳቸው በሚችል ፖለቲካዊም ሆነ ፍልስፍናዊ ተጽዕኖ ውስጥ መግባት የለባቸውም። ህዝቡን ለማገልገል እስከተነሱ ድረስ እንደ ፍልስጥኤም ማኅበራት ከልዩ ልዩ አንጃዎች የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ መቋቋም አለባቸው። የደጋፊነትም ሆነ የተቃዋሚነታቸው መሠረት አንድን ፓርቲ፣ አንጃ ወይም ድርጅት መሠረት ያደረገ ከሆነ ማኅበራቱ የመሰነጣጠቅ አደጋ ያጋጥማቸዋል።

 

ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው አስፈላጊ ነገሮች አንዱ የሆነው አምስተኛው ነገር ደግሞ የግጭት አፈታት ዘዴ ነው። ሰዎች በበጎ ፈቃድ ሲያገለግሉ እና በሙሉ ኃይል ሲሠሩ ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እነዚህ ግጭቶች ግልጽ፣ አስተማሪ እና ችግር ፈች በሆነ መንገድ የሚፈቱበት የታወቀ እና የዳበረ ባህል እና አሠራር በእነዚህ ማኅበራት ውስጥ ከሌለ አኩራፊው እና ራሱን በየምክንያቱ የሚያገልለው እየበዛ ይመጣል። ይህ ደግሞ አዲሶችን ያርቃል፤ ማኅበራቱን ማዳከም ብቻ ሳይሆን ይከፋፍላል። ”እንደ ገባ ይውጣ፤እንደ ወጣ ይቅር” የሚለው አሠራር እያንዳንዱን ቦታ ሰጥቶ በመስማት እና በመቻቻል ብሎም ለሁሉም እኩል ዋጋ በመስጠት ብሂል ሊተካ ይገባዋል።

 

የመጨረሻው ደግሞ ከድርጅታዊ ሥራ መውጣት ነው። አምላክን ፈርተው፣ እርሱ ይረዳናል ብለው የተሰባሰቡ ሰዎች ግልጽ በሆነ መርኅ እና ንጹኅ በሆነ አሠራር እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ እያወቁ በሚሠሩበት የስለላ ተቋማት አሠራር መመራት የለባቸውም። ”ሌላው አይገባውም፤ ገና ወጣኒ ነው፤ እኛ የበለጠ እናውቃለን፤ ስለሚያምነን ምንም አይልም” በሚል ዓይነት ድርጅታዊ ሥራ የሚሠሩ ከሆነ ለሐሜት፣ ለሃሳብ መለያየት እና ለታማኝነት መጉደል ከመጋለጣቸውም በላይ የተነሱበትን እምነትን መሠረት ያደረገ አሠራር ይሸረሽሩታል።

 

በሀገራችን እምነትን መሠረት ያደረጉ አያሌ ማኅበራት መኖራቸው ይሰማል፤ ይታያልም። በርግጥ እነዚህን ማኅበራት በሁለት መልኩ ማለትም በፍትሕ ሚኒስቴር እና በየእምነት ተቋማቱ በኩል ምዝገባው ስለሚካሄድ በትክክል ቁጥራቸውን እና አሠራራቸውን ለማወቅ ያስቸግራል። አንዳንድ ጊዜም በማኅበረሰቡ ዘንድ በሥራቸው ከመታወቃቸው ባለፈ መዝጋቢም ፈቃጅም ያለ የማይመስልበት ሁኔታም ይታያል።

 

እንደማኅበረ ቅዱሳን ያሉ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ሰፋ ያለ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራት በድረ-ገጻቸው በለቀቁት ደንባቸው እና አሠራራቸው፣ በኅትመቶቻቸውም ሆነ በየጊዜው በሚያቀርቡት ፕሮግራም በሚገልጡት ማንነታቸው ሥራቸውን ይገልጣሉ። ሰፊ እና ግዙፍ መዋቅር ዘርግተው ይሠራሉ። እነዚህን መሰል ግዙፍ እና ብዙዎችን ያሳተፉ ማኅበራት ዕድሜያቸው ዘላቂ፣ አገልግሎታቸው ታዋቂ፣ አሠራራቸው ግልጽ ሆኖ ከላይ በምሣሌነት እንዳነሳናቸው የካቶሊክ እና የፍልስጥኤም ሙስሊሞች ማኅበራት ኅብረተሰብ ጠቀም የሆነ አገልግሎት ይጠበቅባቸዋል።

 

የማኅበሩን አገልግሎት በየጊዜው እከታተላለሁ፤ አደንቃለሁም፤ አስተያየትም እሰጣለሁ። በሀገሪቱ ከሚገኙ መንፈሣውያን ማኅበራት አንጋፋው መሆኑን ማሳያዎች አሉኝ። 210 ኮሌጆች ውስጥ ያስተምራል፤ ሠላሳ ሺ አባላትን አቅፏል፤ በሀገር ውስጥ 38 በውጭ ደግሞ ስድስት ቅርንጫፎች አሉት። ስለዚህም በምሣሌነት እንድናነሣው ግድ ይለናል። ውድቀቱ ውድቀታችን፣ ዕድገቱም ዕድገታችን ነው። በገዳማት እና አድባራት እንደጀመረው ሁሉ በሀገሪቱ ማኅበራዊ እና ልማታዊ ጉዞም በቂ ሚና እንዲኖረው እንሻለን።

 

ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክህነቱ ያገኘውን ቦታ፣ ያቀፋቸው አባላት ያላቸውን ሁሉን ዐቀፍ ዕውቀት፣ ያሰባሰበውን ብሔራዊ ተዋጽኦ፣ የዘረጋውን ዓለም አቀፋዊ መዋቅር ያህል በምሣሌነት ከላይ እንዳነሣናቸው ማኅበራት የጎላ ሀገራዊ አስተዋጽዖ አይታይበትም። ከኃይማኖት ክርክሮች፣ ከመጻሕፍት እና መዝሙሮች፣ ከጉባዔያት እና ስብሰባዎች ባለፈ ለሀገር ዕድገት እና ለህዝቡ ማኅበራዊ አገልግሎት መስፋፋት ብሎም ኅብረተሰቡን ለዕድገት በማነሣሣት ረገድ ዘገምተኛነት አስተውላለሁ።

 

ራሱን ግልጽ አድርጎ በዙሪያው ያሉትን አካላት እንኳን በዓላማው ዙሪያ በሚገባ ማሳመን የቻለ አይመስለኝም። በዚህም ምክንያት ደጋፊዎቹ ሊሆኑ ይገቡ የነበሩ ብዙ አካላትን አጥቷል። አሠራሩ ግልጽ ነው ብዬም አላምንም። የአባላት አመላመሉን፣ ከቤተክህነት ጋራ ያለውን ግንኙነት፣ የአመራር አሰያየሙን፣ … ወዘተ በተመለከተ ኅብረተሰቡ ሊረዳው የሚችል አሠራር የዘረጋ አይመስለኝም። በቅርቡ (ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ከነኀሴ 23 እስከ 25 ቀን 2000 ዓ.ም.) ባከናወነው 8ኛው ጠቅላላ ጉባዔው የተስተዋለውም ይሄው ነው። አባላቱ አመራራቸውን እንዲመርጡ ከማድረግ ይልቅ ለድርጅታዊ አሠራር በተጋለጠ መልኩ አስቀድመው የተመለመሉ ሰዎችን አቅርቦ በአስመራጭ ኮሚቴ በኩል ማስመረጥ በቀጣዩ ጥሩ ልምድ የሚሰጥ አይመስለኝም። በግልጽነት መምረጥ፣ መመረጥን ካላስተማረን ይህንን ከማን እንማር? ሌላው ቀርቶ በዕጣ እና በፀሎት ተደርጓል የተባለው ምርጫ እንኳን ለ17 አመራር 20 ዕጩ አቅርቦ ዕጣ ማውጣት ”የፕሮባብሊቲ ቲዮሪ” ተምረው ላደጉ አባላቱ ምን ማለት እንደሆነ ይጠፋቸው አይመስለኝም።

 

”የሚደግፉንን እንጂ የሚነቅፉንን እና የሚያርሙንን አንቀበልም” የሚለው አካሄድም ትርጉም ያለው የማኅበራዊ ዕድገት ሚና እንድትጫወት ለምንጠብቃት ቤተክርስቲያን ይተርፋል ከምንለው ማኅበር የሚጠበቅ አልነበረም። ”በጉባዔው መግባት የለበትም” ተብሎ የተገመተ ነባር አባልን ለማባረር የነበረው ሩጫ፣ ሁኔታውን ”በመንፈሣዊ ምክር እና ጨዋነት በተሞላበት አኳኋን ለምን አናስወጣውም” ብለው በመጠየቃቸው ምክንያት፣ ከአመራር ዕጩነት እንዲወገዱ የተደረጉትን በሕክምና ሙያ የተሠማሩ ልሂቅ እና ነባር አባል ጉዳይ ስናይ ተስፋችንን ያጨልምብናል። ከመንፈሣዊ ማኅበራት ግልጽ፣ አስተማሪ እና ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል አሠራርን እንጂ በፌዴሬሽኖች እና በአንዳንድ ድርጅቶች የምናየውን ዓይነት ሕጋዊ እና ሕገ ወጥነትን የሚያጣቅስ አሠራርን አንጠብቅም። ማኅበሩ ቤተክህነትን ወደ ተሻለ አሠራር እንዲወስደው እንጂ ”እንግሊዝኛ ተናጋሪ ቤተክህነት” እንዲሆን አንጠብቅም።

 

የግጭት አፈታት ዘዴውንም ቢሆን ለሀገሪቱ ፓርቲዎች፣ ተቋማት እና መሠል ማኅበራት ትምህርት ሊሆን በሚችል መልኩ ማዳበሩን እጠራጠራለሁ። ማኅበሩን ሲመሩ እና ስለማኅበሩ ሽንጣቸውን ገትረው፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሲሟገቱ የነበሩ አንዳንድ ቱባ ቱባ አባላቱ፣ ከማኅበሩ አሠራር ጋር ባለመጣጣማቸው ራሳቸውን ማግለላቸውን ወደ ጽ/ቤቱ ጎራ በማለት ብቻ መረዳት ይቻላል። ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ክፍሉ በሪፖርቱ ቢዘነጋውም ከ50 በላይ አገልጋዮቹ በ2000 ዓ.ም. ብቻ ጥለውት ሄደዋል። አባላቱን በማራቅ ብቻ ችግር ለመፍታት የሚያስብ ማኅበር እና ታግለው ከማሸነፍ ይልቅ ራሳቸውን በማግለል ብቻ ከችግር የሚሸሹ አባላት ይህችን ሀገር የት ይወስዷት ይሆን?

 

ይህን ጽሑፍ በምጽፍበት ጊዜ ያነጋገርኩት አንድ አባል፤ ”አባላቱን ውጤት ሊያመጣ በሚችል መነሣሣት እና አሠራር ይዞ ለመጓዝ መቻል ከፊታችን የተደቀነ ፈተና ይመስለኛል። አዲስ አባላትን በየጊዜው የምታየውን ያህል ነባሮችን በየጊዜው ታጣለህ። በሚሠሩት ሥራ ያለመርካት ሁኔታ ይታያል። ላሉት አባላት የተሰጣቸው አገልግሎት እና ሊሠሩት የሚችሉበት አቅም አልተጣጣመም” ብሎኛል። ይህ እውነት ከሆነ የቅርብ ትኩረት ያሻዋል ማለት ነው። በስትራቴጅያዊ ዕቅዱ ግምገማ ላይ ያነሣቸውን ደካማ ጎኖቹንም ሠፋ አድርጎ በዝርዝር ሊገመግማቸውና ሊያርማቸው የሚገባ ይመስለኛል።

 

ከላይ እስጢፋኖስ ዲ. አባዲ ያነሷቸውን ስድስት ነገሮች አባላቱም ሆኑ አዲስ የተሰየመው አመራር ሊመለከታቸው የሚገባ ይመስለኛል። ”ጀምረን መለያየት እንጂ ጀምረን መጽናት አይሆንልንም” እየተባልን ለምንታማው ኢትዮጵያውያን ማኅበሩ አንድ ሌላ ተጨማሪ ምሣሌ መሆን የለበትም። ሀገራችን ዛሬ የመንፈስ መነሣሣት፣ የዓላማ ጽናት እና ከብረት የጠነከረ ሕብረት ያላቸውን ዜጎች ትሻለች። ድህነት ታሪክ ሆኖ እንዲቀር፣ ማኅበራዊ ችግሮቻችን ተረት እንዲሆኑ እንመኛለን። ማኅበረ ቅዱሳንን የመሰሉ በመላ ሀገሪቱ አባላት ያላቸው መንፈሣውያን ማኅበራት ደግሞ እነዚህን በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው።

 

የዕድገታችን ነገር ኢኮኖሚያዊ ብቻ አይደለም፤ መንፈሣዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ዕድገት ጎን ለጎን ካልሄዱ ኢኮኖሚው ብቻውን የሰውን የአንድ ወገን ረኻብ ብቻ ነው የሚፈታው። በመሆኑም ለዚህች ሀገር ትርጉም ያለው አስተዋፅዖ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳንን የመሰሉ የሀገራችን መንፈሣውያን ማኅበራት ውጫቸውንም ውስጣቸውንም ሊፈትሹ ይገባል።

 

እዚህ ላይ ማኅበሩን በምሳሌነት የጠቀስኩት አንጋፋ እና የተወሰነ ዕድሜም ያሳለፈ፣ ብሎም ክፉም ደግም ያየ በመሆኑ ለመማማሪያ ይሆናል በሚል በጎ ሃሳብ ብቻ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ማኅበሩን የተመለከቱ ከ12 በላይ የመመረቂያ ጽሑፎች ቀርበዋል። ይህም የማኅበሩ የተግባር እንቅስቃሴ ለዕይታ የተጋለጠ መሆኑን ያሳያል። መቼም ይህ የተማረ ስብስብ ያለበት ማኅበር ”የሚተቹኝ ሁሉ ጠላቶቼ ናቸው” ብሎ ያስባል ብዬ ለማመን ይከብደኛል።

 

በማኅበሩ ላይ ያነሣኋቸው ነጥቦች በሙስሊሙም በክርስቲያኑም ወገን እምነትን መሠረት አድርገው የተቋቋሙ መንፈሣውያን ማኅበራት ሁሉ ራሳቸውን ሊያዩባቸው የሚገቡ ናቸው። እንዲያውም መንፈሣውያን ማኅበራት ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለሀገሪቱ በሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ዙሪያ ሕብረት ፈጥረው ቢሠሩ ለዕድገታችን አንድ ተስፋ ይሆናሉ። ችግሮቻቸውንም ከመተቻቸት ይልቅ በመወያየት ይፈታሉ። ”የግብጽ ቤተክርስቲያን መንፈሣውያን ማኅበራት ፌዴሬሽን” እና ”የፍልስጥኤም መንፈሣውያን ማኅበራት ሕብረት”ን የመሰለ ነገር ብናይ መቼም አንጠላም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!