ግርማ ካሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  ጥቅምት 11 ቀን 2001 ዓ.ም. (October 21, 2008)

ከኢያሪኮ ወደ እየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዘ የነበረ አንድ ሰው፣ በመንገድ ላይ ወንበዴዎች አግኝተውት በሞትና በሕይወት መካከል እስኪሆን ድረስ ደብድበውና ዘርፈውት መንገድ ዳር ጥለውት ሄዱ። ይህ ሰው ባለዕቅድና ባለራዕይ ከቤቱ ሲወጣ ደግሞ ጤነኛ ሰው ነበር። ነገር ግን ያላሰበው ነገር በመንገዱ ላይ አጋጠመው። ቆሞ ይሄድ የነበር ሰው ወደቀ። ጠንካራ የነበረ ሰው ደከመ። በራሱ ይንቀሳቀስና ኪሎ ሜትሮችን ያቋረጥ የነበረ ሰው አንድ እርምጃ መሄድ አቃተው።

 

ይህ ሰው በመንገድ ላይ ወድቆና በሞትና በሕይወት መካከል ሆኖ እያቃሰተ በነበረበት ወቅት፣ አንድ ዲያቆን በመንገድ ሲያልፉ ቁስለኛውን አይተው እንዳላዩ ሆነው መንገዳቸውን ቀይረው ሄዱ።

 

ትንሽ ቆየት ብሎም አንድ ቄስ ጥምጥማቸውን ጠምጥመው መጡ። እርሳቸውም እንደ ዲያቆኑ እጃቸውን ለወደቀውና ለቆሰለው ሰው ሳይዘረጉ አይተው እንዳላዩ ሆነው መንገዳቸውን ቀጠሉ።

 

በዘመኑ በነበሩና እግዚአብሔርን እናወቃለን በሚሉ ሰዎች ዘንድ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ፣ አኅዛብና ሐጢያተኛ እንደሆኑ ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል የሆኑ፣ አንድ ሣምራዊ ሰው፣ ቁስለኛው ወደቆ በሚታይበት መንገድ ላይ፣ በአህያ ላይ ሆነው ሲጓዙ በወንበዴዎች ተደብድቦ ደሙ መሬቱን ሲያርስ የነበረውን ሰው ወድቆ አዩት።

 

የእኝህ የሣምራዊ ሰው ልብ በጣም አዘነ። መሄድ ወደነበረባቸው ጉዟቸውን ከመቀጠል ይልቅ “የኔ ጉዳይ ለጊዜው ይቁም። ምንም እንኳን ከዚህ በፊት የማውቀውና እንደ እኔ ሣምራዊ የሆነ ባይሆንም እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ልረዳውና ላድነው ይገባል” ብለው ከአህያቸው ላይ ወረዱ።

 

እጃቸውንም ዘርግተው የወደቀውን ሰው ቀና አደረጉት። ለመንገዳቸው ይዘውት የነበረውን ወይን ጠጅና ዘይት በተደበደበው ሰው ቁስሎች ላይ ፈውስ ይመጣ ዘንድ አፈሰሱ። ልብሳቸውን ቀደው በጨርቅ ቁስሎቹን ካሸጉ በኋላ በአህያቸው ላይ ቁስለኛውን ጭነው፣ እርሳቸው በእግር እየሄዱ ወደ ሆቴል ቤት አመሩ።

 

በሆቴል ቤቱ እንደደረሱም ያላቸውን ገንዘብ ሁሉ ለሆቴሉ ባለቤት ሰጥተው “እባክህን ይህን ሰው እስኪያገግም ድረስ በደንብ ተንከባከብልኝ። ይኸው ያለኝን ገንዘብ ሁሉ ውሰድ። ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ካስፈለገ ስመለስ እከፍልሃለሁ” ብለው መንገዳችውን ቀጠሉ።

 

ይህ ታሪክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ለሰው የማያስብና ለባልንጀራው ፍቅር ከሌለው፣ ሌሎች የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ጸያፍና ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ለማስተማር የተናገረው ታሪክ ነበር።

 

የዚህን የደጉ ሣምራዊ ሰው ታሪክ ስንመለከት አራት የተለያዩ ሰዎችን እናያለን። በሀገራችን ኢትዮጵያም ያለነው ሁላችንም ከነዚህ ከአራት ቡድኖች ውስጥ በአንዱ የምንመደብ ነን።

 

የመጀመሪያው ቡድን ከኢያሪኮ ወደ እየሩሳሌም ሲጓዝ አግኝተውት ደብደውና ዘርፈው እንደጣሉት እንደ ወንበዴዎቹ አይነት ሰዎችን የሚያቅፍ ቡድን ነው።

 

በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች፣ የጥፋት መልዕከተኞች ሆነው የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ፣ መንደሮችን ለጥቅማቸው ሲሉ የሚያቃጥሉ፣ ጉቦ እየበሉ የድሃውን ኢትዮጵያዊው ደም የሚመጡ፣ ሠላማዊ ዜጎችን አልሞ በሚተኩስ መሣሪያ በግፍና በጭካኔ የሚገድሉ፣ ያላጠፋን አጠፋ ብለው ለዓመታት እስር ቤት የሚያንገላቱ፣ ነጩን ጥቁር ጥቁርን ነጭ እያሉ ፍርድን የሚያዛቡ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ቆማ እንዳትሄድ ያደረጉና በተለያዩ መልኮች በሌሎች ጉዳት እነርሱ የሚበለጽጉ ሰዎች ናቸው።

 

እነዚህ ሰዎች ድንገት ሁለት ስሙኒ ለማግኘት ብለው ይሆናል የሰው ደም የሚያፈሱት። ድንገት የቀበሌ ሹመት እንዳይቀርባቸው ይሆናል ሕሊናቸውን ሽጠው ግፍ የሚሠሩት። የሰው ነፍስ ሳያጠፉ፣ ንጹኅ ዜጋን ሳይበድሉ የሚቆረጥሟት ባቄላ፣ ሼራተን ተቀምጦ በሰው ደም የተጠበሰ ብስቴካ ከመብላት የተሻለ እንደሆነ የረሱ በአስተሳሰባቸውና በመንፈሳቸው ደሃ የሆኑ ሰዎች ናቸው።

 

ሁለተኛው ቡድን የተደብዳቢዎችና የተጠቂዎች ቡድን ነው። ዕቅድና ዓላማ የነበራቸው፣ ማናችንም የደረስንበት ደረጃ መድረስ ይችሉ የነበሩ፣ ዕቅዳቸውንና ዓላማቸው ከግብ ለማድረስ በጀመሩት ጉዞ መንገድ ላይ ወንበዴዎች አግኝተዋቸው የደበደቧቸውና የወደቁ፣ ጠዋትና ማታ እየሠሩና ወዛቸውን እንደጎርፍ እያፈሰሱ ሥርዓቱ ተጠያቂነት የሌለውና በጉቦኛና በደመኛ የተሞላ ከመሆኑ የተነሳ ኑሩዋቸውን ማሻሻል ያልቻሉ፣ በምግብ እጦት በረሃብና በችጋር እየተቃጠሉና እንደቅጥል እየረገፉ ያሉ፣ በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ቤቶች አንዳንዶች ሲሠሩ መንገድ ዳር ወድቀው የበረንዳ አዳሪ የሆኑ፣ ጥቂቶች ከውሃ አልፈው በዊስኪ ሲራጩ ከንፈራቸው ላይ ወሃ ጠብ የሚያደርግላቸው ያጡ፣ ፍርፋሪ ለቀማ የሆቴል ቤቶችን ጀርባ የሚያጣብቡ፣ ነፍሰ ገዳዮችና ወሮበሎች በአደባባይ ሲንጎራደዱ ባላጠፉት ጥፋት ተከሰው በእስር ቤት የሚማቅቁ፣ መንደራቸው በእሳት የተቃጠለና ጥቂቶች ባላቸው ዝምድና አባል በሆኑበት ድርጅት ምክንያት የሥራና የቢዝነስ ዕድሎች ሲከፈትላቸው፤ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ሆነውም እንኳን ሥራ አጥተው የሚንገላቱ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያያን ያቀፈ ቡድን ነው።

 

ሦስተኛው ቡድን የቄሱና የዲያቆኑ ቡድን ነው። ከከናፍርቶቻቸው የሚወጡት ቃላት እጅግ የጣፈጠጡ ናቸው። ማውራት ይችሉበታል። ግርግር ይወዳሉ። ዝግጅትና ግብዣ ሲኖር “አለሁ! አለሁ!” የሚሉና ቀዳሚ ሆነው ጉድ ጉድ የሚሉ እነርሱ ናቸው። ነገሮችን አቀነባብረው ማቅረቡ ላይ የሚወዳደራቸው የለም። ከላይ ሲታዩ ጻድቃን ናቸው።

 

ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ውስጣቸው ከውጫቸው የተለየ የሸበተና የበሰበሰ ነው። ግብዞች ናቸው። ጽድቅን ይሰብካሉ ግን ጽድቅድን አያደርጓትም። ሌላውን ለማውገዝና በሌላው ላይ ለመፍራድ ይቸኩላሉ። ነገር ግን በዓይናቸው ያለው ትልቁ ምሰሶ አይታያቸውም። በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለው ችግር ተጠያቂ ከነርሱ በስተቀር ሁሉንም ሰው ያደርጋሉ። ሁሉም ሰው ጥፋተኛ ነው ከእነርሱ በስተቀር።

 

እነዚህ ሰዎች፣ እነርሱ እስካልተነኩ ድረስ ሌላው ቢጎዳ፣ ቢሞት፣ ቢያልቅ፣ ቢደኸይ ግድ አይላቸውም። የሚያስቡትና የሚቃዡት ሥልጣን እንዴት እንደሚያገኙ፣ ገንዘብ እንዴት እንደሚያካብቱ ብቻ ነው። ለጊዜው ሥልጣን ከያዘው ጋር የሚያጎበድዱ፣ ማዕበሉን አይተው ደግሞ በትልቅ ጅምናስቲክ የሚገለባበጡ አስመሳዮችና ግብዞች ናቸው። ዛሬ አንዱ ጋር ነገ ደግሞ ሌላው ጋር የሚታዩ፣ አቋምና መርኅ የሌላቸውና እምነት የማይጣልባቸው ሰዎች ናቸው።

 

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ግን ከኢትዮጵያ እንደመጡ ይረሳሉ። በኢኮኖሚ ተምችቷቸዋል፤ ግን ትላንትና የነበሩበትን ችግር አያስታወሱም። ወገናቸው እየተቸግረ፣ እየተራበ፤ ልባቸው አይራራም። አይተው እንዳላዩ ይሆናሉ። “ከኢትዮጵያ የሚሰማው ችግር ብቻ ነው፤ ችግር አታንሱብኝ!” ብለው በድሃው ሀገራቸው ላይ በሩን ይዘጋሉ።

 

አራተኛውና የመጨረሻው ቡድን ሰውን ለመርዳት መንገዳቸውን አቋርጠው የሚመጡ፣ እንደ ደጉ ሣምራዊው አይነት ሰዎች ያሉበት ቡድን ነው። በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉ በኑሮ የተሻለ ደረጃም ቢሆኑ የመጡበትን አይረሱም።

 

በኢሊኖይ ዊተን በምትባል ከተማ የሚኖሩ አንድ ኢትዮጵያዊ በአካባቢያቸው የሚኖሩ የውጭ ሀገር ተወላጆችን በማስተባበር ከ80 ሺህ ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ አሰባስበው፣ በተሰበሰበው ገንዘብ ከመቀሌ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ “አይናለም” ተብላ በምትታወቅ ትንሽ መንደር የሶላር (የፀኃይ ብርሃን) ቴክሎሎጂ ዕቃዎች ከጃፓን አስገብተው፣ መብራት ያልነበረውን የአይናለምን ነዋሪ መብራት እንዲያገኝ አድርገዋል። እኝህ ሰው ከዚህ ከደጉ ሣምራዊው ቡድን የሚመደቡ ሰው ናቸው።

 

“ቡክስ ፎር አፍሪካ” ከሚባለው ድርጅት ጋር በመተባበር የወገናችን የዕውቀት አድማስ እንዲሰፋ በየዓመቱ ሁለት ኮንቴነር መጻሕፍት በደሴ፣ በአዋሳና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እንዲደርስ ያስደረጉና አሁንም እያስደረጉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ከደጉ ሣምራዊ ቡድን ውስጥ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

 

የተወለዱባትን የአርሲ መንደር ሲጎበኙ ምንኛ ወገናቸው መጎሳቆላቸውን ያዩ በካሊፎርኒያ የሚኖሩ አንድ ኢትዮጵያዊ ሰው የሚኖሩበትን ቤት ሽጠው በልጅነታቸው ባደጉባት በአራሲ በምትገኝ መንደር ትምህርት ቤትን አቋቁመዋል። እኝህ የአርሲ ተወላጅ የሆኑት ኢትዮጵያዊ ከደጉ ሣምራዊ ቡድን ጋር የሚመደቡ ኢትዮጵያዊ ናቸው።

 

በአዲስ አበባ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የስዕል አስተማሪ የሆነች አንዲት ወጣት የእርሷ ቢጤዎች በየመንገዱ ልጆቻቸውን ይዘው ሲንከራተቱ ማየቷ እንቅልፍ አሳጥቷት “የእነዚህ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች የእኔ ልጆች ቢሆኑ ዝም እላቸዋለሁን?” በሚል በተቀደሰ ሃሳብ ሕፃናትን አሰባስባ ለማስተማርና ለመመገብ ያደረገችውን ጥረት እግዚአብሔር ባርኮለት አሁን በሽሮ ሜዳ፣ በፒያሳና በቦሌ መጠነኛ ሕፃነ-መዋያዎችን መስርታ ከመቶ በላይ ለሚሆኑ ሕፃናት ተስፋ ሆናለች። ይህች ወጣት ከደጉ ሣምራዊ ቡድን ጋር የምትመደብ ወጣት ኢትዮጵያዊት ናት።

 

በአሜሪካን ሀገር በኢኮኖሚ የተሻለ ኑሮ መኖር ሲችሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱና ለነፃነቱ የሚያደርገውን ትግል ለማገዝ የሥጋ ምቾት ያለበትን ሀገር ጥለው የመንፈሥ ምቾትና ነፃነት ወዳለበት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ፣ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የሀገርን ጥቅም ያስጠበቁ፤ እንዲሁም ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ በተለያዩ መስክ ሳይታክቱና ሳይደክሙ ህዝባቸውንና ሀገራቸው እየረዱ ያሉ ከሣማራዊው ቡድን የሚመደቡ ብዙ ኢትዮጵያን አሉ።

 

እነዚህ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ይልቅ ለወገናቸው የቆሙ፣ እነርሱ በእግራቸው እየሄዱ አህያቸው ላይ ወገናቸውን የጫኑ፣ ገንዘባቸውን ከስረው የወደቀውንና የተጎዳውን ወገናቸውን ቀና ለማድረግ የተሰማሩ ሰዎች ናቸው።

 

የእነዚህ በአራተኛው ቡድን ውስጥ የሚመደቡት ሰዎች ጭንቀት እንዴት ገንዘብ እንደሚያገኙ፣ እንዴት ሥልጣን እንደሚይዙና እንዴት የሚያተርፉበትንና የሚሻሻሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አይደለም።

 

የእነዚህ ሰዎች ጭንቀት “በግፍ የተደበደበው ሰው ሕመሙና ስቃዩ መለስ አለለት ወይ? በረሃብ የተጎዳው ወገናችን በልቶ አደረ ወይ? በልቶ ካላደረስ እንዴት አድርገን ነው ምግብ እንዲደርሰው የምናደርገው? በግፍ የታሰሩት እስከመቼ በግፍ ይታሰራሉ? የወይኑ መዝጊያዎች መቼ ነው የሚሰበሩት? እንደ ሽብሬ ደሳለኝ ያሉ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እንደተገደሉበትና በኦጋዴን መንደራቸው በግፍ እንደተቃጠለው አይነት ግፍ መቼ ነው የሚያቆመው? እንዲህ አይነቱ ግፍና ወንድም ወንድምን የመግደል ባህል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሠላም እንድታርፍ ምንድን ነው ማድረግ ያለብን? የእኛ ድርሻ ምንድን ነው? …” የሚሉ ናቸው።

 

እያንዳንዳችን ያለንበትን ሁኔታና በውስጣችን የምናስበውን የምናወቀው እኛው እራሳችን ብቻ ነን።

 

ማንም የማይክደው ሐቅ ግን አለ። ሀገራችን ኢትዮጵያና ህዝቧ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። የበሰበሰው እንዳልበሰበሰ፣ የሞተው እንዳልሞተ፣ የተሰበረው እንዳልተሰበረ አድርገው ከውጭ የሚያሳዩ ብዙ የሚያንጸባርቁ ነገሮች አሉ። ነገር ግን በምድራችን በሞትና በሕይወት መካከል ያሉ፣ የወደቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙና እየተባዙ ነው።

 

ጥያቄው “ችግር አለ ወይ?” የሚል አይደለም። በሀገራችን ያለውን ችግር ስንተርክና ስናወራ ብንከርም ይሄ ነው የሚባል የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።

 

ጥያቄው የኢህአዴግ ወይንም የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባል መሆናችንና አለመሆናችን አይደለም። ጥያቄው የምንይዘው የፓርቲ አባልነት ካርድ አይደለም። ጥያቄው አማራ ነን ወይስ ትግሬ ወይስ ከንባታ ወይስ ኦሮሞ የሚል ዘራችንንና ጎሣችንን የሚያነሳ ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው ከየት ነው የመጣነው? የተወለድንበት ክልል የት ነው? … የሚል አይደለም።

 

ጥያቄው አንድና አንድ ብቻ ነው። እርሱም “በሀገራችን ያለውን ችግርና እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ እያየን መልሳችን ምንድን ነው? ከላይ ከተዘረዘሩት አራት ቡድኖች ውስጥ የትኛው ቡድን ውስጥ ነን?” የሚል ነው።

 

ከወንበዴዎቹ ቡድን ውስጥ ካለን የለውጥና የመቀየር ዕድል እንዳለ ለመጠቆም እፈልጋለሁ። የህዝባችንን ሰቆቃ አሁን ካለው የባሰ እንዲሆን የጥፋት መልዕክተኞች ሆነን እስከ መቼ እንቀጥላለን? የሰው ደም እየጠጣን፣ ወገናችንን እያዋረድን፣ እጆቻችንን ተዘርግተው ወንድማችንን ከማንሳት ይልቅ ጦር መዘን አንገት እየቆረጥን፣ በገደልናቸው ሰዎች እሬሳ ላይ ተረማምደን በንጹኅ ዜጎች አጥንት በተሠራ ዙፋን ላይ ተቀምጠን የምንኖረው እስከመቼ ነው?

 

ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብሮ እንደተሰቀለው፣ ነፍሰ ገዳይና ወንበዴ እንደነበረው ሰው ወደ ንስኀ መመለሱ አይሻልምን? ይችን ዓለም እንደው ጥለናት መሄዳች አይቀሬ እንደመሆኑ ባለፉት ስህተቶች አምላክን ይቅርታ ጠይቀን ቀሪዋ ዘመናችን ትንሽ ብትሆንም ደግ ነገርን አድርገንና ሠርተን ማለፉ አይበጅምን?

 

ከዲያቆኑና ከቄሱ ቡድን ውስጥ ላለን ሰዎች ደግሞ ማስታወስ ያለብን መሰረታዊ ቁምነገሮች አሉ። ከንፈር መጣጮች ብቻ መሆን አይበቃም። በስብሰባዎችና በአዳራሾች ስናወራው፣ ስንለፍፈው፣ ስንሰብከው የነበረው ነገር የት አለ? “እኛ እስካልተነካን ድረስ የራሱ ጉዳይ” ብለን ከራሳችን ጥቅም አልፈን ለማየት ዓይኖቻችን ከታወሩ በርግጥ እኛ ሰዎች ነን ብለን እራሳችንን ልንጠራ እንችላለንን? ደግሞም ወንበዴ ሲገድልና ሲደበድብ እያየን ዝም ካልን ነገ ግድያው ወደኛ ወደ ልጆቻችን ሊመጣ እንደሚችል አናውቅምን?

 

በሀገራችን ኢትዮጵያ በብዛት እየተንፈላሰሱ ያሉት የወንበዴዎቹና የግብዙ ቄሱ አይነት ቡድን ውስጥ ያሉ ይመስለኛል። እነዚህ ሰዎች ቀዳሚውን ቦታ እስከያዙ ወይንም አመለካከታቸውና ሥነምግባራቸው እስካልተለወጠ ድረስ ሀገር አታድግም። ከድህነት ወደ ድህነት ከበሽታ ወደ በሽታ ከውርደት ወደ ውርደት ነው የምንሄደው።

 

ከራሳቸው አልፈው ለወገናቸው የሚቆረቆሩ፣ በሽታችን ይድንና ይፈወስ ዘንድ በቁሳልችን ላይ ዘይትና ወይን ጠጅ የሚያፈሱ፣ ወደ ማረፊያና ሆቴላችን ሄደን እናርፍና እናገግም ዘንድ እነርሱ በእግራቸው ሄደው እኛን በአህያቸው ላይ የሚጭኑ ኢትዮጵያውያን ያስፈልጋሉ።

 

እንደነዚህ አይነት ኢትዮጵያውያን ሲበዙ ተስፋ ይለመልማል። እንደነዚህ አይነት ኢትዮጵያውያን ሲበዙ የወደቀቁ ተነስተውና አገግመው ለወግ ለማዕረግ ይበቃሉ።

 

እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ በጣም የሚያስፈልጋት ነውና ከደጉ ሣምራዊ ወገን የሆንን ሰዎች ያድርገን!


 

ከግርማ ካሳ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ጥቅምት 11 ቀን 2001 ዓ.ም. (October 21, 2008)

 

አዲስ ቪዲዮ

Excavators move earth as rescuers work at the site of the landslide at the landfill.
ኤክስካቫተሮች የተደረመሰውን በማንሳት ላይ ሳሉ (ፎቶ፣ ZACHARIAS ABUBEKER/AFP/Getty Images)
...

በቆሼው አደጋ መትረፍ የ…

Discussion on the role of the diaspora
የዲያስፖራው ተሳትፎ ምን ይሁን? በቀጥታስ ሆነ በተዘዋዋሪ መሳተፍ አለበት
...

በኢሕአዴግና በተፎካካሪ …

Dr. Berhanu Mengistu on Forum 65
ዶ/ር ብርሃኑ መንግሥቱ ከፎረም ፷፭ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ
...

ዶ/ር ብርሃኑ መንግሥቱ ከፎረም ፷፭ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!