ዳንዴው ሰርቤሎ

ከአንድ ተቋም ግቢ ውጪ ለብዙ ህዝብ በጽሑፍ ወይም በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ አማካይነት ለህዝብ እንዲደርስ የሚፈለገው መረጃ የሚተላለፍበትን መሣሪያ ”መገናኛ ብዙኀን” ብለን እንቀበል። አጠር ባለ መልኩ የውጭውን ቃል ተውሰን፣ ”ሚዲያ” ብንለው ደግሞ የሚያግባባን ይመስለኛል። ሚዲያው ህዝብን ለማስተማሪያ፣ ለማሳወቂያ፣ ለመቀስቀሻና ለማዝናኛ ዓላማ እንደሚያገለግል ይታወቃል። በዚህ ጽሑፍ ማተኮር የፈለግሁት በፖለቲካ ረገድ በሚጫወተው ሚና ላይ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ከታዘብኳቸው ሁኔታዎች በመነሣት ነው።

 

ከዛሬ 50 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚተላለፍ ”መወያየት መልካም” በሚል ርዕስ በጋዜጠኛ አሳምነው ገ/ወልድ የሚዘጋጅ የውይይት ፕሮግራምና ”መምህር አብራራው” በሚል ርዕስ አቶ መኰንን በተባሉ አንጋፋ ጋዜጠኛ የሚቀርቡ የሬድዮ ፕሮግራሞች እንደነበሩ አስታውሳለሁ። እነዚህ ፕሮግራሞች የሚያተኩሩት፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮችና ፓርላማውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በመስጠት፣ በአመዛኙ ህዝብን ለማስተማር የታለሙ ይሁኑ እንጂ ለምን ተዘለሉ ከሚል አንፃር ብዙዎቹ ጥያቄዎች ህዝብን የሚያነጋግሩና የሚያከራክሩ ነበሩ።

 

በአዲስ ዘመን፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በሰንደቅ ዓላማችን፣ በኢትዮጵያን ሄራልድና በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጦች ዓምዶች ላይ ምሁራን የሚያቀርቧቸው ነፃ አስተያየቶች ይነበቡ ነበር። የጽሑፍም ሆነ የሬዲዮ መገናኛ ሚና የጎላው ግን ከ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ጋር በተያያዘ ነበር።

 

ከታህሳስ 3 ቀን 1953 ዓ.ም. ጀምሮ ”ቀፎው የተነካበት ንብና መሪ የሌለው ህዝብ አንድ ናቸው” በሚል የመቀስቀሻ ጽሑፍ፣ በአልጋ ወራሽ ልዑል አስፋ ወሠን ኃ/ሥላሴ የተነበበው ዲስኩር ተደጋግሞ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሲተላለፍ ለመስማት የነበረው የህዝብ ፍላጎት በግልጽ ይታይ ነበር። የመንግሥቱ ነዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተበላና በዚያው ሬዲዮ ጣቢያ ወዲያውኑ ትችት ይቀርብ ጀመር። ጋዜጠኞቹም ከሥራ ገበታቸው ተባረሩ። ጥቂቶቹም (እንደነ ጌታቸው ጋረደው ይመስሉኛል ካልተሳሳትኩ) ወደ ሞቃዲሾ ኰብልለው በአማርኛ ቋንቋ ፀረ-ኃይለሥላሴ ቅስቀሳ ማካሄድ ጀመሩ።

 

በልዑሉ ዲስኩር ውስጥ ”እኔ እንደ አንድ ሰው በደምወዝ አገለግላለሁ …፣ ኢትዮጵያ በሪፐብሊክ መንግሥትነት ትተዳደራለች …” የሚሉት ሃሳቦች መወያያ ሆኑ። መፈንቅለ መንግሥቱ ቢከሽፍም ዓይን-ገላጭነቱ አሌ አይባልም። የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት ቅድመ-ዝግጅቶች እንደሚያስፈልጉ አስተምሮ አለፈ። ከ13 ዓመት በኋላ የተነቃነቁ ጥርሶች መወላለቅ ጀመሩ። ህዝቡ ለለውጥ ተነሳሳ። የ10 ሣንቲም የቤንዚን ጭማሪ ተቃውሞ አስነሳ። ታክሲዎች ሥራ አቆሙ። የአንበሣ አውቶቡሶች በድንጋይ እሩምታ ተደበደቡ።

 

”ወታደሩ የራሱን ደምወዝ አስጨምሮ፣ ህዝቡን ሜዳ ላይ ጥሎ ወደ ካምፑ መመለሱ ነው ወይ?” የሚል የሚዲያ ቅስቀሳ በረከተ። ማን ምን ማድረግ እንዳለበት መላው ቀጠነ። አንዳንድ ምሁራን አስተያየታቸውን በጽሑፍ ይሰጡ ነበር። እነአጥናፉ አባተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በማታ ይከታተሉ ስለነበር ከጓደኞቻቸው ምክር ያገኙ ነበር። ለስድስት ወር ዕድሜ የነበረው የፕሬስ ነፃነት ወደር አልነበረውም። ቀጥሎ የ”ፋታ ስጡኝ” መንግሥት በእንዳልካቸው መኰንን ጠቅላይ ሚንስትርነት ተቋቋመ። ህዝቡ ግን ”ጉልቻ ቢቀየር ወጥ አያጣፍጥም” እያለ ተቃውሞውን ቀጠለ። ”ህዝባዊ መንግሥት ይቋቋም” ሲል በሠላማዊ ሠልፍና በተገኘው ሚዲያ ጠየቀ።

 

”የወሎው ረሃብ ተጠያቂዎች ለፍርድ ይቅረቡ” የሚል ጥያቄ በረከተ። አጣሪ ኮሚሽን ተመሠረተ። ከምሁራን የተውጣጣ የመንግሥት አማካሪ ሸንጐም ለማቋቋም ተመከረ። ደርግ የሥነ ጽሑፍ ዝሆኖችን አሰባስቦ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚተላለፉ፣ በመንግሥት ጋዜጦች የሚታተሙ እጅግ ቀስቃሽ የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ይዘት ያላቸው ሥራዎች ይቀርቡ ጀመር። ይህ በእንዲህ እንዳለ በምሥራቁና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የጦርነት ጥቃት ተጀመረ። የሁሉም ትኩረት በተባበረ ክንድ የሀገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ፣ ዳር ድምበር የማስከበር፣ የእናት ሀገር ጥሪ ለህዝብ ቀረበ፤ ምርጫ አልነበረም።

 

በዚያም የዘመቻ ጥሪ የሚዲያው ሚና ወሳኝ ነበር። ጋዜጠኞች እስከ ጦር ግምባር ድረስ ዘመቱ። ዜናውን እግር በእግር እየተከታተሉ ያሳውቁ ነበር። መዋጮው እንደ መዓት ይጎርፍ ጀመር። ህዝቡ ከዳር እስከዳር ለእናት ሀገሩ መከበር ያደረገው መረባረብ፣ ታሪካዊ ነበር ማለት ይቻላል።

 

የደርግንም አገዛዝ ለመጣል ሚዲያው የተጫወተው ሚና ጠንካራ ነበር። ከበረሃ ይተላለፍ የነበረው የሬዲዮ ፋና መልዕክት ሠፊ ሚና ተጫውቷል። የደርግ ሥርዓት ወድቆ ኢህአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን እንደተቆጣጠረ፣ ከወሰዳቸው ተገቢ እርምጃዎች መካከል አንዱ የፕሬስ ነፃነት ዐዋጅ ማወጁ እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ። በተለይ በፖለቲካው ረገድ የዲሞክራሲ ባህልን በህዝብ ዘንድ ለማስረጽ ይልቁንም ለ1997 ዓ.ም. የግንቦት ምርጫ ሚዲያው ያደረገው አስተዋጽዖ ቀላል አልነበረም።

 

ምርጫው ከመድረሱ በፊት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋምና ችግሮችን ለመፍታት ያቀዱትን የፖሊሲ እርምጃ እንዲያስረዱና እንዲከራከሩ ነፃ መድረክ ተፈጥሮላቸው እንደነበር አይዘነጋም። እነ አቶ በረከት ስምዖን፣ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ እነ ዶ/ር ያዕቆብ፣ … ያደርጉት የነበረውን ክርክር፣ የመንግሥትና የግል ጋዜጦች ይጽፏቸው የነበሩት አስተያየቶች ሁሉ ተደማምረው፣ ህዝቡን ለግንቦቱ ምርጫ አዘጋጅተውት ስለነበር፤ በምርጫው ዕለት ከንጋት እስከ እኩለ-ሌሊት ድረስ ተሠልፎ ድምፁን ሲሰጥ ቆይቷል። ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የምርጫ ተሳትፎ ነበር ማለት ይቻላል።

 

በጋዜጦች ላይ ይወጡ የነበሩ የነፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያም፣ የነዶ/ር ሽመልስ ተ/ጻድቅ፣ የነዶ/ር በፈቃዱ ደግፌ፣ የነዶ/ር ያዕቆብ፣ … ማብራሪያዎች ወጣቱን በመቀስቀስ ረገድ የማይረሳ ታሪክ ሠርተዋል። ጋዜጦችም እንደ ትኩስ ኬክ የተቸበቸቡ ሲሆን፤ እነ እውነቱ ዘለቀ፣ አብርሃም ኤልያድ፣ እነታንጉት በሚል የብዕር ስም ይወጡ የነበሩ ጽሑፎችም የአንድ ወቅት መነጋገሪያ ጉዳዮች ነበሩ።

 

በረብሻው ጊዜ ከፖሊሶች ዘጠኝ ያህል፣ ከህዝብም 56 (በኋላ የመርማሪ ኮሚቴ ኦፊሲያል ያልሆነ አኀዝ ወደ 199 ከፍ ያደርጋቸዋል) እንደተገደሉ፣ ብዙዎች እንደቆሰሉ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ፣ ብዙዎች ሀገር ጥለው እንደኰበለሉ ተጽፈው ነበር።

 

በሚዲያ እንደምንከታተለው በቅርቡ በኬንያና በዚምባቡዌ የተካሄዱትም ምርጫዎች፣ ተመሣሣይ ይዘት እንደነበራቸው እንገነዘባለን።

 

ይህ በእንዲህ እያለ ካለፉት 20 ወራት ጀምሮ፣ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት በዴሞክራቶችና በሪፐብሊካን መካከል የተደረገውን የምርጫ እሽቅድምድም፣ በሚዲያ አማካይነት ስንከታተል ቆይተን፣ በሴናተር ባራክ ኦባማ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተረዳን። የአፍሪካ ሀገር መሪዎችን ምርጫና የአሜሪካኑን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማወዳደር አንችልም። ይሁንና አንዳንድ ግንዛቤዎችን ማግኘታችን አልቀረም። ዋናው ግንዛቤ ፉክክሩን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያሽከረክር የነበረው ሚዲያው ነበር።

 

ይህንኑም በመገንዘብ ሴናተር ማኬን እና ሴናተር ኦባማ ለሚዲያው ያወጡት ገንዘብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው። ተፎካካሪዎቹ በሥልጣን ላይ የሚገኙትን የጆርጅ ቡሽን የከሸፈ ፖሊሲ መነሻ በማድረግ፣ ”ለውጥ” እንደሚያመጡና ለለውጥም የሚያበቃቸውን የፖሊሲ እርምጃ በነፃነት ተናግረዋል። ሚዲያው የያንዳንዳቸውን የጀርባ ታሪክ እየጎለጎለ ለህዝብ ገልጧል። በኢኮኖሚ፣ በአካባቢ ጉዳይ፣ በሠላምና ደህንነት ጉዳይ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በነዳጅ፣ በቀረጥ፣ ሥራ-አጥነትን ለመቀነስ ባላቸው ዕቅድ፣ … ወዘተ ጠይቆ መልሳቸውን ለህዝብ ግልጽ አድርጓል።

 

ህዝቡ መልሱን በድምፁ ሰጠ። ያመነበትን ሰው መረጠ። ያሸነፈው አሸነፈ፣ የተሸነፈም ተሸነፈ።

 

ተወዳዳሪዎች በመጨረሻ ተጨባበጡ። ሁለቱም ከነደጋፊዎቻቸው ለአንዲት ለሚያፈቅሯት ሀገራቸው ተባብረው እንደሚሠሩ ቃል ገቡ። ዲሞክራሲ ይህ ይመስለኛል። ከዚህ ብዙ መማር ይቻላል። የሚዲያው ሚና ማስተማር፣ ማሳወቅ፣ ማዝናናት እንጂ ከፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መወገን አይመስለኝም። ጋዜጠኞች በየግላቸው የራሳቸው የሆነ አቋም ሊኖራቸው ይችላል። እንደ ህዝብ አገልጋይነታቸው ግን ሚዛናዊ ሊሆኑ ይገባል። የመንግሥት ዓላማና ፖሊሲ ለህዝብ ለማስተዋወቅ ሊጠቀሙባቸው ይገባል። ራሳቸውን ለሁሉም እኩል ክፍት ማድረግ አለባቸው። የጐሪጥ ከመተያየት ይልቅ ለአንድ ህዝብ በጋራ ቆመው የመሥራት ኃላፊነት ያለባቸው ይመስለኛል።

 

ስለሚዲያ ስናወራ ስለጋዜጠኞች አስተዋጽዖ ልንዘነጋ አይገባም። ህዝብን ለማሳወቅ፣ ለማስተማርና ለማስረዳት በየጊዜው ተገፍተዋል፣ ታስረዋል፣ ተገድለዋል፣ ከሀገርም ተባርረዋል። የሙያ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲሉ ያልከፈሉት መሥዋዕትነት የለም። በአንፃሩ ደግሞ በስመ-ጋዜጠኝነት ለዕለት ጥቅማቸው ብቻ ሲሯሯጡ፣ ብዙዎችን ያሳሳቱና ወደአልሆነ አቅጣጫ የመሩ፣ ሙያቸው በቅንፍ ውስጥ የሚጠቀስም “ጋዜጠኛ” ተብዬዎችም እንዳሉ አይዘነጋም። ህዝብ ያውቃል፣ ህዝብ ይፈርዳል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!