ነብዩ ግዛው

በእንቢልታ ጋዜጣ ቅጽ 1 ቁጥር 49 እትም ”የፖለቲካ ውዝግቡና የሽማግሌዎች ሚና” በሚል ርዕስ የቀረበውን ዘገባ አንብቤዋለሁ። ጹሑፉ በጣም ጥሩና ሊነበብ የሚገባው ሲሆን፣ በውስጡ ቢካተት የበለጠ ጥሩ ይኾን ነበር ያልኩትን፤ ይችን ጽሑፌን ለአንባቢ እንድታደርሱልኝ እጠይቃለሁ።

 

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ሊባል የሚችል ሕገ-መንግሥት በ1995 እ.ኤ.አ. ፀድቆ ”ተግባራዊ” ሆኖአል። በተመሳሳይ ዓመት የመጀመሪያው እንዲሁም በ2000 እ.ኤ.አ. ደግሞ ሁለተኛው ሀገር አቀፍ እና ብሔራዊ ምርጫ ተደርጓል። ሦስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ግን ከቀደሙት ሁለት ምርጫዎች በእጅጉ የተለየ ከመሆኑም በላይ፣ በወቅቱ ምርጫውን እንዲታዘቡ የተጋበዙ የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ታዛቢዎችም ቅድመ ምርጫው (Pre election period) ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ነበር ሲሉ ዘግበዋል። ("የፖለቲካ ውዝግቡና የሽማግሌዎች ሚና" በሚል የቀረበውን ጽሑፍ አስነብበኝ)

 

እዚህ ጋር እንደማሳያነት እንዲጠቅመን ጥቂቶቹን ለማንሳት እፈልጋለሁ። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሕገ-መንግሥቱን ”አክብረው” ለሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሁሉ በምርጫው እንዲሳተፉ ከመጋበዙም በላይ፣ ለፓርቲው አባላት የምርጫ ሕግ አውጥቷል። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሕጉ ላይ ማሻሻያ አድርጎ፣ በመራጭነት ለተመዘገበው ከ26 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ለማስተናገድ እንዲቻል 32 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች በመላው ሀገሪቱ ተዘጋጅተው ጠብቀዋል። በነገራችን ላይ ለዚህ ምርጫ ከተመዘገበው ውስጥ 90 በመቶ ድምፅ መስጠቱም ሌላው አዲስ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።

 

ድኅረ ምርጫው (Post election period) እንደታሰበው ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም። በምርጫው ዙሪያ የተለያዩ ቅሬታዎች መደመጥ የጀመሩት ገና በምርጫው ዕለት (ግንቦት 7) ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ማንኛውንም ዓይነት ሠላማዊ ሠልፍ ለአንድ ወር መከልከላቸውን ተከትሎ ነበር። ይህንን ተከትሎም በምርጫው ዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲ የነበረው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ፣ በ299 የምርጫ ጣቢያዎች መጭበርበር እንደነበር በመግለጽ፣ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበለው አስታውቆ፣ የተለያዩ የሠላም ትግል ጥሪዎችን ማድረግ ጀምሯል። በመንግሥትና በቅንጅት መካከል የነበረው ልዩነት እና ግጭቶች እየሰፉ ሄደው፣ ገዢው ፓርቲ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን በቂ ድምፅ ማግኘቱን ሲገልጽ፣ ዋነኛው ተቀዋሚ ፓርቲ ቅንጅት በጥቅምት 1998 ዓ.ም. በጠራው ህዝባዊ ትግል፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በወሰደው የኃይል እርምጃ የ199 ንፁኀን ወገኖቻችን ሕይወት ከማለፉም በላይ ከ18 ሺህ ሰዎች በላይ ለእስር ተዳርገዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በ131 የቅንጅት ከፍተኛ አመራሮች እና የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢትዮጵያ ፊዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) (ለ)፤ 38-34 27 (1) እና 238 (2) 258 የተደነገገውን በመተላለፍ ለሕገ-መንግሥትና በሕገ-መንግሥት ሥርዓቱ እንዲሁም በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ እንዲመሠረትባቸው ምክንያት ሆኖአል።

 

ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ በተለያዩ ጊዜያት ስለ ቅንጅት ከፍተኛ አመራሮች ከእስር መፈታት፣ በሀገራችን የሽምግልና ባህል መሆኑ ይነገራል። ለእኔ ግን እውነታው ሌላ ነው ባይ ነኝ። ይህንን ከዚህ በታች በተቀመጡ የሽምግልና መመዘኛዎች ለማሳየት እሞክራለሁ።

 

ሽምግልና

 

“Indigenous Institutions for Resolving Conflict outside the choired Legal system” በሚል በአቶ ዮሐንስ ብርሀኑ ጽሑፍ ውስጥ፣ ሽምግልና ማለት የሦስተኛ ወገን በሁለት ባላጋራ (ባላንጣዎች) ወገኖች መሀል በመግባት፣ ግጭቶችን አስወግደው ሁለቱ ወገኖች በሠላም ችግሩን ፈተው ወደ ሠላም የማምጣት ሂደት መሆኑን ይገልፃሉ። የሀገራችን የሽምግልና ሥርዓቶች እንደየአካባቢያቸው ቢለያዩም፣ በመሠረታዊ ደረጃ ሁሉም አንድ የሚያደርጋቸውን እና የሚወራረሱት መገለጫዎቻቸውን ብንመለከት፣ ዳሰሳችንን በተወሰነ መልኩ ሙሉ እንዲሆን ያግዛል።

 

ሽማግሌ Shemagelle /elders/

 

እንደሚታወቀው የቃሉ ትርጉም የሚወክለው ወንድ፤ ዕድሜው ከ50 ዓመት በላይ ለሆነ ሰው የምንሰጠው መጠሪያ ቃል ነው። በሃሳብ ደረጃ እዚህ ዕድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች ጥሩ የመረዳት ችሎታ እና ነገሮችን አገናዝበው ፍርድ መስጠት ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል። ይሄ ሽማግሌን ለመምረጥ እንደ አንድ መሥፈርት ከመቀመጡም ባሻገር፣ የግለሰቡ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ሁኔታ (Economic & Social Status) የራሳቸው አስተዋጽዖ አላቸው። ከዚህ አንፃር ደግሞ በቅንጅት ከፍተኛ አመራሮች ዙሪያ የነበሩት የሽምግልና አባላት በአብዛኛው ያላቸው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተሰሚነት የጐላ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ እንዳለ ሆኖ በሽማግሌዎቹ ውስጥ የሴቶች አባላት መኖር ከቃሉ ትርጉም ብቻ ሳይሆን ከሀገራችን የሽምግልና ሥርዓት ጋር ተቃራኒ እንዲሆን ያስገድደዋል።

 

የሽማግሌዎቹ አመራረጥ /Selection of Shemagelle/

 

በሀገራችን ባህል መሠረት ሽማግሌዎቹን የመምረጥ ሥልጣን ያላቸው ሁለቱ ባላንጣ ወገኖች ሲሆኑ፣ ይህም ሽማግሌዎቹ የሚያሳልፉትን ውሳኔ ገለልተኛ እና ተፈፃሚ እንዲሆን ያደርገዋል ከሚል እሳቤ ነው። እዚህ ላይ እንድናይ የምፈልገው ነገር በቅርቡ በተደረገው የዕርቅ ሂደት ላይ ከነበሩ የሽማግሌ አባላት ውስጥ፣ ማንኛቸውም በገዢው ወይም በተቃዋሚው ፓርቲ እንዳልተመረጡ እና ሁለቱ ባላጋራ ወገኖችም በሽማግሌዎቹ ምርጫ ላይ ምንም ዓይነት አስተዋጽዖ (Role) እንዳልነበራቸው ይታወቃል። ይሄም ከሀገራችን የባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት ጋር ተፃራሪ ሆኖ እንዲቀመጥ ሌላው ምክንያት ይሆናል። ከነብሂሉስ ”በቆረጥከው ዱላ ብትመታ፣ በመረጥከው ዳኛ ብትረታ አይቆጭም” ነው ነገሩ።

 

የእምነት አባት /Religious father/

 

ሀገራችን ካሏት ጥሩ ጐኖች መካከል፣ የተለያዩ ኃይማኖት ተከታዮች ተቻችለው እና ተከባብረው መኖራቸው ነው። ማኅበረሰባችን ለኃይማኖት አባቶች ካለው አክብሮት የተነሳ የኃይማኖት አባቶች በሽምግልና ሥራ ሂደት ውስጥ አባል እና የራሳቸው የሆነ ኃላፊነትም አላቸው። ነገር ግን አሁንም ላነሳው የፈለኩት ጉዳይ ቢኖር፣ በእዚህኛው የሽምግልና ሂደት ውስጥ ከየትኛውም የኃይማኖት ተቋም ተወክሎ አባል የነበሩ የኃይማኖት አባቶች አለመኖራቸው ሌላው ልዩነት እና ይህንን ሂደት ሽምግልና ብሎ ለመናገር እንደማያስችል ያመለክተናል።

 

የሽምግልና ሂደት /Process of Shemgellena/

 

የሽምግልና ሥርዓታችን አንዱ መለያው በመደበኛነት ያለ ተቋም አለመሆኑ እና ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተለይ ጊዜ እና ገንዘብ መቆጠቡ ነው። ከዚህ በላይ በሁለቱም ወገኖች መሀከል የጠላትነት የአሸናፊ እና ተሸናፊነት (Win-Lose) ዓይነት ግንኙነት በመቅረፍ፣ በመቻቻል የሁለቱንም ፍላጐት በተወሰነ መልኩ አሟልቶ ማለቁ ሊጠቀስ ይችላል።

 

አሁን በቅርቡ ለቅንጅት አመራሮች መፈታት ምክንያት የሆነውን ስንመለከት ግን፣ ከባህላዊው መንገድ ያፈነገጠ ሆኖ የምናገኘው፣ በሽምግልና የተያዘ ጉዳይ አብሮ በተመሳሳይ ጊዜ በፍርድ ቤት ሊታይ አይችልም፤ እናም ከሁለት አንዱ መቋረጥ ነበረበት። ሆኖም ግን በእዚህኛው ጉዳይ የታሰሩት ከፍተኛ አመራሮች በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ከተበየነባቸው ቅጣት ምህረት ያገኙት፣ በመንግሥት ሚዲያዎች እንደተዘገበው በድርጊታቸው ተጸጽተው ይቅርታ እንዲደረግላቸው በመጠየቃቸው፣ በዐዋጅ ቁጥር 395/96 አንቀፅ 11 መሠረት ይቅርታ ተደርጐላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስፈፃሚው አካል (executive body) በሕግ ተርጓሚው (Judicial Body) ሥራ ውስጥ መግባት እንደማይችሉ፣ ጉዳዩም በሕግ የተያዘ መሆኑ መናገራቸው የሚታወስ ይሆናል።

 

ከላይ ልጠቃቅስ የሞከርኳቸው ጉዳዮች፣ በጥቂቱም ቢሆን ያለንን ግንዛቤ ሊያሰፉ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። ካለኝ ጊዜ አንፃር እነዚህን አነሳሁ እንጂ፣ ሌሎች ብዙ ጉዳዮችን አንስቼ ወደፊት ለመፃፍ እሞክራለሁ። ይህ በዚህ እንዳለ አንድ ነገር በመናገር ጽሑፌን አጠናቅቃለሁ፤ ላለፉት ሁለት እና ሦስት አስርት ዓመታት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ መገለጫው በሥልጣን ላይ ያለው የበታቹን በጠመንጃ ወይም በኃይል ችግሮችን ሲፈታ ነበር። ከዚህ አንፃር ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም እንደ ይቅርታ ሰጪነቱ፣ የቅንጅት ከፍተኛ አመራሮችም በይቅርታ አምነው መጠየቃቸው እና ከሁሉም ይህንን ጉዳይ እላይ እና ታች በማለት ደከመን፣ ሰለቸን ሳይሉ ገንዘባቸውንና አሁንም የገዢውንና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም የህዝቡን የልብ ትርታ አዳምጠው፣ ሁሌም ለችግሮቻችን ሠላማዊ መፍትሔ እንዲሰጡን እግዚአብሔር ልብ ይስጣቸው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!