ከጠላቶቿ የበለጠች፤ ያኮራችን ምስኪን ሴት

 

የነውር ጥግ፡ ሴት ደብዳቢ፤ አረጋዊ ረጋጭ

ይሄ የአንድነትም ብቻ አይደለም። ይሄ የኢህአዴጎችም ጭምር ነው። ይሄ የሴቶች ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ ልጆች ያላቸው ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ የእናቶች ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ የክርስቲያኖች ብቻ አይደለም። ይሄ የእስላሞችም ብቻ አይደለም። ይሄ የኦሮሞዎች ብቻም አይደለም። ይሄ ኢትዮጵያዊያን ብቻም አይደለም። ይሄ የሂላሪ ክሊንተንም ነው። አልልላት ብሎ እንጂ ይሄ የአዜብ ጎላም ጭምር ነው።

 

ብርቱካን ታሰረች። እስራት ዜና ባልሆነበት አገር የብርቱካን መታሰር ዜና አይደለም። ግን የተሰጠው ምክንያት፡ የአስተሳሰሩ ሂደት እና የአረጋዊው ሰብአዊ መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ መመታት እጅግ ያስገርማል። በዚህ ተግባራቸው የተበሳጨው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም በሰላው ቋንቋና ቃና አዋቂ ብእሩ እንዲህ ብሎ ጀመረ፤ “በሞቃዲሾ ያሉትን ጀግኖች ማሸነፍ ካቃተህ፡ በአዲስ አበባ የምትገኘውን ምስኪን ሴትና አረጋዊ ወንድ ደብድብ።” ይሄ ያበሳጫል። ይሄ ያሳፍራልም። ይሄ ሰዎቹ ምንኛ ወደ ደማቸው ጥላቻና በቀል፤ ንቀትና እብሪት ዘልቆ እንደገባም ያሳያል። በእውኑ ይሄ ነውር አይደለምን?

 

ሴት ማሰር፡ የሰባ ስምንት ዓመት አዛውንት በመሳሪያ ሰደፍ የኋልዮሽስ ይሁን የፊትዮሽ፡ እንኩዋንስ መደብደብ፤ መሰንዘርስ አግባብ ነውን? ይሄ ከትግራይ ነው? ይሄ ከጎንደር ነው? ይሄስ ከዮሐንስ ነውን? ይሄስ ከምንሊክ ነውን? አረ ይሄ ከኢትዮጵያስ ነውን?

 

ዛሬ ብቻም አይደለም። በፕሮፌሰርም ብቻ አይደለም። የዛሬ ዓመት ከምናምን አካባቢ ወደዚህ ወደ ሰሜን አሜሪካ መጥተው ሲጎበኙን እንዳጫወቱን ወደ እስር ቤት እያዳፉ ሲወስዷቸው ዶ/ር ሀይሉ አርአያንም ያጋጠማቸው ይኸው ነው። ጸያፍና ቀፋፊ ስድቦችን እየሰደበ የሚወስዳቸው የህወሀት ወታደር፡ ሙልጭ አድርጎ እያዋረዳቸው፡፡ ራሱን አዋረደ። “ከሀዲ፡ የራስህን ህዝብ ልታሰጨርስ የምትዋዋል ከሀዲ ነህ” እያለ እየገፈተረ ወሰደኝ አሉ ዶ/ር ሀይሉ አርአያ። ሊያስረዱት ሞከሩ። መጀመሪያ ከልደታ አካባቢ ሊወስደኝ ሲመጣ አይኑ ደም ለብሶ፡ ቀልቶ ነበር። ደም። ጥላቻው በአይኑ ውስጥ ይንቀለቀላል። ደም እንደ ነበልባል ይነዳል። ይንቦገቦጋል። ላስረዳው ሞከርኩ። ትንሽ መለስ አለለት አሉ። ስንለያይ የቀላው አይኑ ትንሽ መለስ ነጣ ብሏል።

 

እንደ ፕሮፌሰር አገላለጽ እውነትም ባንድ ደብዳቤ፤ ባንድ ፖሊስ ለዚያውም እንኩዋንስ መሳሪያ ቆመጥም ባልታጠቀ፤ በሱፍ ባጌጠ በክራቫትም በተሸመቀቀ ባለሟል እባክዎትን እመቤት ከፖሊስ ጽ/ቤት ይፈለጋሉና ይከተሉኝ ማለትና ራሱንም ማስከበር ሲችል እነዚህ ሲዋጉ እንደ ደደቢት፤ ሲገዙም በደደቢት መንፈስ የሚገዙ ሰዎች ስለምን ይህቺን ሴት በዚህ መልኩ እኚህንም አረጋዊ በዚያ መልኩ ሊያስተናግዷቸው ፈቀዱ? ሀ- ሞራል መንካት። ለ- ማዋረድ። ሐ- ማስፈራራት። መ- ምን ታመጣለህ። ሰ- ማለቂያ የለውም። የምናደርገውን እናደርጋለን። የምንፈልገውንም እንሰራለን። እንግዲህ ምን ይውጣችኋል አይነት ነገር።

 

አለማየሁ፤ ፕሮፌሰር ተበሳጨ። አዘነ። እሱ ብእር ነው ያለው። እሱ ከተቀዳበት የህግ ወንዝ ሰዎች የሚፋለሙት በአመንክዮ ነውና እንዲህም አለ። “በሞቃዲሾ ያሉትን ጀግኖች ማሸነፍ ካቃተህ፡ በአዲስ አበባ የምትገኘውን ምስኪን ሴትና አረጋዊ ወንድ ደብድብ።”

 

አንገት ማስደፋት፡ መሪን ማዋረድ

 

መሳይ ከበደ መጣ። ሌላ ፕሮፌሰር፡ ሌላ ትሁት ሀሳብ። ብርቱካን ቀድሞውንስ ቢሆን የተናገረችውን መልሳ መዋጥ ነበረባትን? የሚል ክርክር ተነሳ። ገና ሰሞኑን ነው ያኔ በ1985 ዓ.ም. ከአ.አ.ዩ. ባንድ ደብዳቤ ያለአግባብ ከተባረሩት አርባ ሁለት መምህራን መካከል መሆኑን ያወቅኩት። ሰዎችን ማወቅ ቆንጆ ነው። ዋጋቸውንና ሀሳባቸውን ያሳድገዋል። Survival and Modernization, Ethiopia's Enigmatic Present: A Philosophical Discourse የተሰኘ እነ መለስ እንዲህ እንደ ዋዛ፤ መቶ ሁለት መቶ እያሉ የሚያቦኩትን የኢትዮጵያን ታሪክ አሳምሮ የሚፈትሽና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለሆነው መሆን ላልሆነው አለመሆን ምክንያት ለመፈልሰፍ የሚጥር ሸጋ መጽሀፍ የጻፈ ትልቅ ሰው ነው። የለም የለም፡ ብርቱካን ያለችውን ኢህአዴግ በፈለገው መልኩ ብትውጥ፡ ወይንም ኢህአዴግ አድርጊ ያላትን ብታደርግ ፈጽሞ ጎጂ ነበር አለ። ምክንያት፡ አንደኛ የቀድሞውን ቅንጅትን የአሁኑን አንድነትን ተነሳሽነትና የትግል መንፈስ ሽባ ያደርገዋል። ሁለተኛ ራሷ ብርቱካን በህዝቡ ዘንድ እያገኘች የመጣችውን ታዋቂነትና ተቀባይነት ይጎምደዋል። ሶስተኛ ኢህአዴግ ፍጹም ጌታ ሆኖ እንዲቆም በማድረግ የህዝቡን ሽንፈትና ተንበርካኪነት ያጎላዋል። የብርቱካን ቃሏን ማጠፍ ለኢህአዴግ አንጸባራቂ ድል ነው። ስለዚህ ብርቱካን ያለችውን ብቻ ማለቷ ከትክክልም በላይ ነው።

 

የኢህአዴግ ዋና ዓላማ መሪዎቹን በሚመሩት ወይንም እንመራሃለን፡ ይወዳናል ይከተለናልም በሚሉት ህዝብ ፊት ማዋረድ ነው። በህዝብ ፊት የተዋረደ መሪ ደግሞ ያን በፊቱ የተዋረደውን ሕዝብ ሊመራ አይችልም። ፕሮፌሰር መሳይ ቀደም ሲል የቅንጅት መሪዎች ከእስር ሲፈቱ ሰሞን በጻፉት ጽሁፍም ኢህአዴግ የተቃዋሚ መሪዎች በማሰር በፍርድ ቤት መሰል ሂደት ውስጥ ያንገላታበት ምክንያት እነሱን በህዝባቸው ፊት ለማዋረድ ነው። ይሄ የማዋረድ ምኞት ደግሞ ዓላማው በቀል ብቻ ሳይሆን መሪዎችንና ሕዝብን የማለያየት ፖለቲካዊ ዓላማ ነው። ማለት፤ መናገር መገመት ይከብድ ይሆናል። ግን ፕሮፌሰር መሳይ ያለው ትክክል ነው። እጠቅሳለሁ “ምቾቱን፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ሕይወቱን ለመሰዋት ያልተዘጋጀ መሪ ደግሞ መሪ ሊሆን አይችልም።” እነሆ ብርቱካን ግን በጎ ነገርን፤ መሪ መሆን ፈለገች። ሆነችም።

 

መታሰሯን የምታውቅ፤ መስቀላችንን የምትሸከም ሴት

 

ብርቱካን ገና ከበለስ ዛፍ ስር ሆና እስራቷን አይታው ነበር። ገና ሳትታሰር መታሰሯን አውቃው ነበር። “ እኛ እንታሰር፡ እንገደል፡ እንታፈን ይሆናል። ትግላችን ግን ግቡን እስኪመታ ይቀጥላል።”

 

ኢህአዴግ ያ ታሪክ አበቃለት ብሎ እንደጻፈው አሜሪካዊ ጀግንነት ተጋድሎ መስዋእትነት የኢትዮጵያ ታሪክ አበቃ ያለ ይመስላል። ፈራንሲስ ፉኩያማ ፍጻሜ ታሪክ ብሎ የጻፈው ያኔ የጀርመን ግንብ ፈርሶ ኮሚኒዝም ለካፒታሊዝም መንገድ ሲለቅ ነበር። ኢህአዴግም የዚያ ዘመን ባለድል ነውና የዚያን አሜሪካዊ ድርሰት ተውሶ ታሪክ አበቃለት ያለ ይመስላል። ታሪክ ማለት ለፉኩያማ የኮሚኒዝምና የካፒታሊዝም ፍልሚያ ትንቅንቅ ቀውስ ውጤት ነበር። ለኢህአዴግም ታሪክ የደርግና የሕወሀት ፍልሚያ ብቻ ነበር። የኢትዮጵያዊያን ብሄርተኞችና የትግራይ ተገንጣዮች ፍልሚያ። ስለዚህ ታሪክ አበቃ። ስለዚህ ባህል አበቃ። ስለዚህ፡ ይሉኝታ አከተመለት። ስለዚህ ሴት እደፍራለሁ። ሽማግሌም እገጫለሁ። አቶ መለስ ያለፈውን ለኢትዮጵያውያን ያው የሆነ ለሳቸው ግን ከትቢያ ላይ አንስቶ ላነገሳቸው ሚሌኒየም መሸጋገሪያ እሳቸውና ሌላ የሙስና አጋራቸው አቶ አላሙዲን (አላሙዲን በኔ አስተያየት ሼህ አይደለም) ባሰሩት የፌሽታ አዳራሽ ውስጥ ሲናገሩም ያሉት ይሄንኑ ነው። ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ይሄ ይሆናል። ይሄ ግን አይደረግም። ይሄ አይደገምም። አራት ኪሎ ገብተናል፤ አንወጣም። እነሆ ቃላቸውን ለመፈጸም አንዲት ምስኪን ሴት አሰሩ።

 

ምእራባዊያን አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ጠቀሰ፤ ነካ፤ ጎሸመ ብለው sexual assault, sexual harassment, sexual abuse sexual ምንትሴ እያሉ እንደ ትልቅ ዜና እንደ አቢይ ነገር የሚጮሁበት ነገር እነሆ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስትና በመንግስት ወታደሮች ተፈጸመ። አቶ መለስ ባለትዳር የልጆች አባት ሆነው ሳለ፤ አስራ ምናምን ወታደሮች ልከው አንዲት ጠላቴን ኢህዴግን ሳይሆን፤ ወገኖቻችንን ኢህአዴጎችን በሰላማዊ ትግልና በፍቅር ብቻ ነው የምናሸንፋቸው ብላ በሰላማዊ ትግል ተጠምቃ፣ በሰላማዊ ትግል አድጋ ፣ በሰላማዊ ትግል የቆረበችን ምስኪን ሴት እያዳፉና እያካለቡ ወሰዷት። አጎሳቆሏት። አገራቸው ተፈጽሞ ቢሆን መገናኛ ብዙሀኑን ሁሉ የሚያጣብቡት የአሜሪካው ኤምባሲ ቃል አቀባይ የብርቱካን መታሰር አሳስቦኛል ብቻ አለ።

 

ብርቱካን ሰላማዊ ትግልን አጥብቃ ከመያዟ የተነሳ፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንኩዋን እሷ ለራሷ፤ እሷን እየጎዳት፤ ትክክል እንዳልሆነ ህግም እንዳልሆነ እያወቀች እንኳን “በህጉ እንሂድ” ነው የምትለው አሉ። እነሆ ሕግ እኛ ነን ያሏት ሰዎች ሲወስዷት እንኳን አላንገራገረችም። ተከተለቻቸው። ታሰረችም። እንደሚሸለትና በጌቶቹ ፊት እንደሚያልፍ በግ ያቺ የትህትና እመቤት ታዘዘቸቻወ።

 

ብርቱካን ውስጣችን ነች፤ ብንረሳት ቀኛችን ትርሳን

 

አሁን “ብርቱካን በሁላችንም ውስጥ” ነች አለ ፕሮፌሰር መሳይ። እሷ እስር ቤት ገባች እኛም የተለመደ ህይወታችንን እንቀጥል ይሆናል። ነገር ግን በምንም መልኩ ያሳየችውን አኩሪና አርአያነቱ የሚጠቀስ ጀግንነት ልንረሳው አይቻለንም። ሁላችንንም የምትኮሮኩር፡ በአፏ ሳይሆን በስራዋ፤ በጪኸቷ ሳይሆን በኩራቷ፤ የምትናገር የማትፈራ ግን የምታኮራ መሪ ነች። ትሆናለችም።

 

ፕሮፌሰር አለማየሁ ቀጠለ እስኪ የኢህአዴግ ብርቱካን ይቅርታ መጠየቋን ካደች የሚለው ክስ እውነት ነው ብለን እንነሳ። የቱ ጋር ነው ወንጀልነቱ? በእውኑ ይሄስ በራሱ በኢህአዴግ ወንጀለኛ መቅጫ ህግስ ቢሆን ወንጀል ነው ተብሎ ተደንግጓልን? ቀድሞ ስለታሰረበት ሁኔታ ወይንም ቅጣት ወይንም ይቅርታ የሚያብራራ ሰው ወንጀለኛ ነው ተብሎ ተደንገጓልን? ሰው በመሀላና የሀሰት ምስክርነት በመስጠት በሚያስቀጣ ወንጀል ካልሆነ በስተቀር የሚናገረው ማናቸውም ንግግር ወንጀል እንዳልሆነ የአንደኛ ዓመት የህግ ተማሪ የሚያውቀው የቀለለ ህግ ነው። በትክክል እኔም እመሰክራለሁ። እሺ ይሄም ይሁን። ብርቱካንን ካደች። ኢህአዴግም ከሰሰ። ለመሆኑ ፖሊስ በሶስት ቀን ቃልሽን አርሚ ያለበለዚያ ትገቢያታለሽ ብሎ እንዲያስፈራራ የሚያዝ ስልጣን ማን ሰጠው? ብርቱካን ግን ፍቅር ነች። እርግጠኞች ነን በዚያም በዚህም ቅጽበት “አባት ሆይ እነዚህ ሰዎች የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ነው የምትል።

 

በርግጥም የሚሰሩትን የሚያውቁ አይመስሉም። እንኩዋንስ የትግሬ ዘር፡ ዝራርም ባልጠፋበት አገር፤ እንዲያውም የተገደለ የሞተ የተቃዋሚ ደጋፊ ሆኖ ሳለ የዘር ማጥፋት ክስ ብለው ስንት ወራት ከተጓዙ በኋል ባለፈው ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት፤ ፕሮፌሰር አለማየሁም እንዳከለበት አረ ተዉ መሳቂያ አታድረጉን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ አልተፈጸመም። በዘር ማጥፋት ወንጀል አታላግጡ ተብለው ተመክረው እሺ ሙከራ እናድርገው አሉ። እውነቱም የሚሰሩትን አያውቁትም። ለነገሩ ያውቃሉ። ባያውቁም ያውቃሉ። ብርቱካን ግን በፍቅር ስለምታምን የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው የምትል መሰለኝ። ለነገሩ የሕወሀት መስራችና የእድሜ ልክ አባል አቶ ስዬ አብርሀ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ ባደረጉት ንግግር ችግራቸውን ቁልጭ አድርገው አስቀምጠውታል።

 

የህወሀት መሰረታዊ ችግሩ አሉ አቶ ስዬ ጫካ እያለን እንደወታደርም እንደ ፖለቲካ መሪም ነበር የምንንቀሳቀሰው። ከድል በኋላም፡ ወደ ከተማ ስንገባም ይሄ የወታደር ባህሪያችንን ይዘን የፖለቲካ ስልጣኑን ጨበጥን። ስለዚህ ተደበላለቀብን። በሌላ አነጋገር ኮንጎ ጫማችንና ቁምጣችን ቢቀየርም፤ ሱፍና ክራቫት ያመጣልን ለውጥ የለም። አለባበሳችንና አኗኗራችን እንጂ አገዛዛችንና ባህርያችን አልተለወጠም።

 

ሽንፈትን ለመሸፈን፤ የሶማሊያውን ኪሳራ

 

ማዋረድ ብቻም አይደለም የዚህ ምክንያት የለሽ እስራት ዋና ዓላማ። ፕሮፌሰር አለማየሁ በፕሮፌሰር መሳይ ምክንያት ላይ አከለበት። የሶማሊያውን ሽንፈት ለመደበቅ። ማስቀየሻ መሆኑ ነው። እነ መለስ ተግዚናቸውን ወጥረው፤ በርጫቸውን እያደቀቁ የወጠኑት የሽንፈት መሸፈኛና ትኩረት ማስቀየሻ ዘዴ መሆኗ ነው። አንዲት ምስኪን ሴት ማሰር። እኛ ኢትዮጵያዊያን በሶማሊያ ስለገጠመው አሳፋሪ ሽንፈትና ኪሳራ ሳይሆን ስለብርቱካን መታሰር እንድናወራ ነው የሚፈለገው። እንጂ ብርቱካን ፕሮፌሰር መስፍን ከተናገሩት፣ ዶ/ር ሀይሉ ካከሉበት፣ አቶ ሀይሉ ካሉት፣ ዶ/ር ያእቆብም ከመሰከሩት የተለየ ምንም አልተናገረችም። “ይቅርታ ጠይቄያለሁ” ያንን ልክደውም አልችልም። አከተመ።

 

ከዚህ በላይ ምን ትበል ይህቺ ልጅ። እንደው ጸብ ያለሽ በዳቦ ወይንም አያ ጅቦ ሳታመሀኝ ብላኝ እንጂ፡ ፕሮፌሰር እንደመሰከሩት የተናገረችው አንድም የሚጣል ነገር የለበትም።

 

ብርቱካን እንዲህ ነው ያለችው፤ “በሽምግልናው በኩል ተኬዶ ይቅርታ ጠየቅን ነው ያለችው። በሕጋዊ ሥርዓት ግን ሌላ አይነት መንገድ ነው ያለው። አንደኛ መጀመሪያ ውሳኔ መስጠት አለበት። ፍርድ መፈረድ አለበት። ይቅርታ ለመጠየቅ። እና ይሄ የተጀመረው ገና ገና ውሳኔ ብይንም ሳይሰጥ ነው። ፍርድ ከተፈረደ በኋላ እስረኞቹ ምንድን ነው የሚያደርጉት ቃሊቲ እንዳየነው? ፎርም አለ። ይቅርታ መጠየቅ ሲፈልጉ ፎርም ይሰጣቸዋል። የይቀርታ ኮሚቴ እስር ቤት ውስጥ አለ። ፍሮም ይሰጣቸዋል። አንድ አሥር ገጽ ይሆናል። ያንን ይሞላሉ። ያንን ሞልተው ይመልሳሉ። ሲመልሱ ለየቀበሌው ከጎረቤቶች ከሰዎች ከሚያወቋቸው ሰዎች አጣርቶ አስተያየት ሰብስቦ እንደገና መልስ ለእስር ቤቱ ይላካል።

 

እስር ቤቱ ያንን ካየ በኋላ ወደ ይቅርታ ቦርድ የሚልከውን ይልካል። የሚያስቀረውን ያስቀራል። ይኼ ነው በይቅርታ ኮሚሽኑ የሚሄደው። እርሷ በሽምግልናው ነው የሄድነውና ይቅርታ የጠየቅነው ነው ያለችው። ይሄ ትክክል ነው። ማንም የሚክደው ነገር አይደለም። እዚህ ነው እንግዲህ “ይሄንን አንቺ በሕጋዊ መንገድ ይቅርታ አልጠየኩም ብለሻል” ያሉት። በሕጋዊው ሁለቱም ሕጋዊ ሆኗል ለነገሩ። ይሄም ሕጋዊ ነው። በይቅርታ ኮሚሽን በኩል ሄደ። ፕሬዝዳንቱ ጋር ደርሶ ነው ይቅርታው ተሰጠ የተባለው። እና ሕጉ ነጋሪት ጋዜጣ የሚያዘውን ሕጋዊ ሥርዓት አልተከተለም። የኛ በሌላ በኩል ነው የሄደው ነው እርሷ የምትለው። ደግሞ ሕጉን በሚገባ ታውቀዋለች።” አባት ሆይ የሚሰሩትን ያውቃሉ ይቅርታ ይቅርታ ነው። ስለ ሂደቱ ኢህአዴግ አንድ ነገር፤ እሷ ሌላ ነገር ብትል ዞሮ ዞሮ ይቅርታው ከታመነ ሌላ ምን ይፈልጋሉ። እነዚህ ሰዎቸ የሚሰሩትን ብቻ ሳይሆን የሚፈልጉትንም የሚያውቁት አይመስልም።

 

ከዚህ ቀደም፤ የቅንጅት መሪዎች በታሰሩ ጊዜ የምስኪኖች እሮሮና የግብዞች ፌዝ በሚል ርእስ አንድ መጣጥፍ አስነብበን ነበር። እነሆ ቀጠልን። ይሄ የቅንጅት አይደለም። ይሄ የአንድነትም ብቻ አይደለም። ይሄ የኢህአዴጎችም ጭምር ነው። ይሄ የሴቶች ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ ልጆች ያላቸው ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ የእናቶች ሁሉ ጉዳይ ነው። ይሄ የክርስቲያኖች ብቻ አይደለም። ይሄ የእስላሞችም ብቻ አይደለም። ይሄ የኦሮሞዎች ብቻም አይደለም። ይሄ ኢትዮጵያዊያን ብቻም አይደለም። ይሄ የሂላሪ ክሊንተንም ነው። አልልላት ብሎ እንጂ ይሄ የአዜብ ጎላም ጭምር ነው።

 

እንግዲህስ ይህቺ ስለኢትዮጵያዊነትና ስለፍቅር ስለእኩልነትና ስለሰብአዊነት እንደ ነቢይ ልትተነብይ፡ እንደ አዳኝም ልትሰዋ የተዘጋጀች ሴት ተስፋዋ ማነው? እኛ አይደለንምን? ስልካችሁን አንሱ፤ ወደ ኮምፒውተራችሁ ሂዱ፣ ባካባቢያችሁ ለሚገኙ የተወካዮች ምክርቤት ወይንም ሴኔት ወይንም ኮንግረስ፣ ወይንም ፓርሊያሜንት አባላት ደውሉና የሆነውን ንገሯቸው። ስለፍቅርና ሰላም የቆመች አንዲት ምስኪን ሴት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪ ታሰረች በሏቸው። ደግሞ የዚህ የጃንወሪ 14 ዓለም አቀፍ ሰልፍም አለ። እንሰለፍ። ባንድ ሌሊት ባንድ ቀን ሰልፍ ባንድ ስልክ ጥሪ የሚመጣ ለውጥ አይኖር፤ ብርቱካንም አትፈታ ይሆናል። ግን የምንፈልገው ትልቁ ለውጥ የምናደርጋቸው ትንንሽ ድርጊቶች ጥርቅምና ውጤት ነው። ባንሰለፍም፡ ዝም ብንልም ግን አንድ ነገር ርግጥ ነው። ከዚህ በኋላ ማስመሰል አንችልም።

 

ፕሮፌሰር መሳይ እንዳለው፡ “እሷም እስር ቤት ገባች፤ እኛም የተለመደ ህይወታችንን እንቀጥል ይሆናል። ነገር ግን ብርቱካን ውስጣን ነች። በምንም መልኩ ያሳየችውን አኩሪ ጀግንነት ልንረሳው፣ እንዳላየ ልናልፈው አይቻለንም። ሁላችንንም የምትኮሮኩር በአፏ ሳይሆን በስራዋ፤ በጪኸቷ ሳይሆን በኩራቷ፤ የምትናገር የምትፈታተን፣ የማትፈራ የምታኮራ መሪ ነች። ብርቱካን። ብርቱካን ሊያሳንሷት ሊያዋርዷት ከሞከሩት ጠላቶቿ በለጠች።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!