የችግሩ ጥልቀት ካሳሰባቸው የኢሮብ ተወላጆች

እ.ኤ.አ. Dec. 22 ቀን 2008 “Tiny tribe Ethnic group claim Ethiopian allegiance in border row with Eritrea” በሚል ኤ.ኤፍ.ፒ. (AFP) ያወጣውን ዘገባ በአንክሮ ተመልክተነዋል። ኤ.ኤፍ.ፒ. የራሴ በሚለው መንግሥት ለተረሳው የኢሮብ ህዝብ ድምፅ ለመሆን በመብቃቱ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

 

የኢትዮጵያ ሪፖርተር ጋዜጣም፣ በጋዜጠኛ የማነ ናግሽ አማካኝነት የኤ.ኤፍ.ፒ. ዘገባን ተርጕሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረቡ ምስጋናችንን ሳንቸረው አናልፍም። የህዝብ ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ነውና፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ለወደፊቱ ለአካባቢው ይበልጥ ትኩረት በመስጠት፣ ሁኔታውን እየተከታተለ በቀጣይነት እንዲዘግብም የተማጽኖ ጥሪያችንን በዚህ አጋጣሚ ልናቀርብ እንወዳለን። (የኤ.ኤፍ.ፒን ዘገባ አስነብበኝ)

 

ከዚህ ቀጥለን ዘገባውን በመንተራስ መስተካከል አለባቸው ብለን በምናምንባቸው ጉዳዮች ላይ አጠር ያለ አስተያየት እናቀርባለን። ቀጥሎም የኢሮብ ህዝብ ብሶትን አስመልክቶ ለናሙና ያህል ከባሕሩ በትንሹ ጨልፈን ለወገኖቻችን ለማቅረብ እንሞክራለን።

 

ዘገባውን በሚመለከት

 

የኤ.ኤፍ.ፒ. ዘገባ “ጦርነቱን ለማስቆም ይረዳ ዘንድ የኋላ ኋላ ድንበሩ በተባበሩ መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እውቅና በተቸረው ኮሚሽን ሲሰመር፣ ግዙፉን የኢሮብ መሬት ለኤርትራ እንዲሰጥ አድርጓል” (ትርጉም የኛ) ሲል፣ ሪፖርተር ጋዜጣ ደግሞ፡ “ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውና ለኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት እልባት እንዲያስገኝ በተመድ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የሰጠው የድንበር ውሳኔ አብዛኛውን የኢሮብ ህዝብ ግዛት ለኤርትራ የሚሰጥ ነው” ይላል። እዚህ ላይ ሁለቱም ዘጋቢዎች ሁኔታውን በትክክል በነበረው መልኩ ባያስቀምጡትም፣ በተለይ ሪፖርተር “… በተመድ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን …” ያለው ትክክል አይደለም።

 

ምክንያቱም፣ የድንበር ኮሚሽኑን ያቋቋሙት የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ወደው፣ ተሰማምተው፣ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዳኞችን ከመረጡ በኋላ አምስተኛ (የማኸል) ዳኛ በተመድ ተጠቁሞ እንዲቀርብና ሁለቱ ከተስማሙበት ብቻ ፀድቆ እንዲሰየም ተደረገ እንጂ ኮሚሽኑ በተመድ አልተቋቋመም። ይህም የተደረገው፣ በመሠረት-አልባው የኢትዮጵያን ጥንታዊ ግዛቶች ለኤርትራ በወርቅ ሳህን ያቀረበው፣ ሁለቱ መንግሥታት አምነው ፈቅደው በፈረሙት የአልጀርስ ስምምነት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። በተመድ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የሚለው አገላለጽ ተራ የቃላት ጨዋታ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ግን በሕግ አንጻር ሲታይ ኮሚሽኑን ያቋቋመው ተመድ ነው የሚለው ድምዳሜ ላይ ከቆምን፣ የራሳችንን ችግር ለመፍታት የማንችልበት አዘቅት ውስጥ የሚከተን ይሆናል።

 

የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት፣ የድንበር ኮሚሽኑ ብይኑን ይፋ ባደረገበት ማግስት፣ ሉዓላዊ የኢትዮጵያ ግዛት የሆነውን የኢሮብ መሬትና ህዝብ ለኤርትራ አሳልፎ እንዲሰጥ በካድሬዎቹ አማካኝነት ሰፊ ሰበካ አካሂዷል። የስብከቱና የፕሮፓጋንዳው ይዘት፤ የሔግ ፍርድ ቤት ስለወሰነብን፣ የተባበሩት መንግሥታት ስለወሰነብን፣ … ወዘተ በሚሉና ከተጨባጩ እውነት ጋር ግንኙነት በሌላቸው ራስን ከደሙ ንፁኅ ለማስመሰል በተቀመሩ ድራማዎች፣ ችግሩ የተመድ እንደሆነ አስመስሎ ለማቅረብ ሞክረዋል። እውነት እንነጋገር ከተባለ ግን፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶችን ለኤርትራ አሳልፎ የሰጠው፣ የተባበሩት መንግሥታት ወይም የሔግ ውሳኔ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

 

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ውሳኔዎች እንዲወሰኑ መንገድ የጠረገው በሁለቱ መንግሥታት ፍላጎትና ፈቃደኝነት የተፈረመው መሠረት-አልባው የአልጀርስ ውል ነው። ለዚህም ነበር ከህወሓት/ኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ውጭ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ገና ከጅምሩ የአልጀርሱ ሰነድ ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በጥልቀት በመገንዘብ፤ ሰነዱ ውድቅ እንዲደረግ በአመክንዮ የተደገፈ ጥሪያቸውንና ተቃውሞአቸውን ሲያስተጋቡ የቆዩት። የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ግን ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን የህዝባችንን ጥቅምና ሀገራዊ ሉዓላዊነትን አሳልፎ ለጠላት አስረክበዋል።

 

የኤ.ኤፍ.ፒ. ዘጋቢ ኢማኑኤል ጉጆን “… ኢትዮጵያ የኢሮብ ህዝብን ሁኔታ እንደ አንድ ምሳሌ በመጥቀስ በያንዳንዱ ተጨባጭ ጉዳይ ድርድር እንዲካሄድ ትጠይቃለች” (ትርጉም የኛ) ይላል።

 

በመሠረቱ በበኩላችን መሠረት-አልባው የአልጀርስ ስምምነት እስካልተሻረ ድረስ ለኤርትራ የተቸሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ተገቢ እልባት ስለማያገኙ በዘላቂ ሠላምና የጋራ ዕድገት ፋንታ፣ የማያቋርጥ የመናቆርና የጦርነት ምንጭ ሆነው እንደሚቀጥሉ የሚያጠራጥር አይደለም ብለን እናምናለን። የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝም፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች እንደተከበሩ እንደሚኖሩና ምንም መሸበር እንደማያስፈልገን ውስጥ ውስጡን ሲሰብክ ሰምተናል፣ የሚሉ ግለሰቦች መኖራቸው ቢታወቅም በይፋ መድረክ ላይ ወጥቶ ዳር ድንበራችን እንደተከበረ ይኖራል የሚል የአገዛዙ ባለሥልጣን እስካሁን አልተደመጠም። ይህንን በሚመለከት በኢትዮጵያ መንግሥት የወጡ ሰነዶችንም ሆነ መግለጫዎችም አላነበብንም፤ አልሰማንም። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ባለ አምስት ነጥብ መደራደርያ ሃሳብም ቢሆን ስለ ኢሮብ መሬት የሚያነሳው ነገር የለም። ይባስ ብሎ ጠ/ሚ/ሩ የሰጡዋቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች የሚሉት አንድ ቤት ከሁለት እንዳይከፈል ድርድር እናድርግ ነው።

 

ለኤርትራ ስለተሰጠው የኢሮብ መሬት ስናወራ የኤ.ኤፍ.ፒ. ዘጋቢ በትክክል እንዳሰፈረው ስለ አንድ ቤት ለሁለት መከፈል ሳይሆን፣ ስለብሔረሰቡ ለሁለት መከፈል ነው። የአንድ ቤትና የአንድ ማሳ ጉዳይ ቢሆን ባንወደውም ይህን ያህል የሚገደን ባልሆነ ነበር። ለኤርትራ ስለተሰጠው የኢትዮጵያ (የኢሮብ) መሬት ስናወሳ ስለአንድ ቤት ሳይሆን ተጨንቀን የምናወራው፣ ስለግዙፉ የሰሜንና የምዕራብ ኢሮብ መሬታችንና በዛው ስለሚኖረው ህዝባችን ነው። የግማሽ ያህሉ የኢሮብ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ተገፎ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቶች ለባዕድ በተሰጡበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን እያለን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አንድም ቀን ስለኢሮብ መሬትና ስለኢሮብ ዜጎች አለማንሳቱ እጅጉን ይከነክነናል። ይህንን አርዕስት ለማንሳት ለምን እንደሚያፍርና እንደሚፈራ ፈጽሞ ሊገባን የሚችል ጉዳይ አይደለም። ስለሆነም፣ ያስጨንቀናል፣ ያሰጋናልም።

 

በርግጥ በብሔራዊ ክብሩ የሚኮራ የኢትዮጵያ ህዝብ ወጊድ ባይል ኖሮ፣ መንግሥት ሰጥተን እንገላገላቸው የሚል ሰበካ ከማካሄድ ባሻገር ለማተግበር መንቀሳቀሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ዛሬም ቢሆን ህዝብ እምብየው፣ ለማንነቴ መስዋዕትነቱን ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ባለበት ወቅት፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ከህዝቡ ጎን ለመቆም አለመዘጋጀቱ እጅጉን ያስጨንቀናል። ለዚህም ነው የዳር ድንበራችንና እንደ ብሔረሰቡ ተወላጆች የኢሮብ ህዝብ ሁኔታ የሚያሳስበን፣ የሚያስጨንቀን።

 

ኤ.ኤፍ.ፒ.፣ ወረድ ብሎ “ኤርትራ እ.ኤ.አ. በ1993፣ ነፃነቷን ከተጎናፀፈች በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢሮብ ህዝብ ልብን ለማሸነፍ ከባድ ሥራ ሠርቷል” (ትርጉም የኛ) በማለት በአካባቢው ስለተከናወኑ የልማት ሥራዎች ይዘረዝራል። በመሠረቱ በመንግሥት የተከናወኑ ትርጉም ያላቸው የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል ለማለት ያስቸግራል። ቢሆንም ግን የኢሮብን ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ጥርጣሬ ውስጥ በማስገባት ልቡን ለማሸነፍ ተብሎ የሚደረግ ልማት ከሆነ አገባብነት የለውም እንላለን። ምክንያቱም የኢሮብ ህዝብ ከጥንት ከጥዋቱ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ህዝብ ነውና። በመሆኑም የሚደረግለት ልማት ሊደረግለት የሚገባው ከዜግነት መብቱ አንፃር መታየት ይኖርበታል እንላለን።

 

ለመሆኑ የተከናወኑት የልማት ሥራዎች ምንድናቸው? የኢሮብ ህዝብ ቢቃወመውም፣ የህወሓት አመራር ዳውሀንን የኢሮብ ወረዳ ርዕሰ-ከተማ እንድትሆን እንደመረጣት የሚታወስ ነው። በዚህችው ዳውሀን (የወረዳው ርዕሰ-ከተማ) በዋናነት ከቢሮክራሲው አገልግሎት ጋር በቀጥታ የሚተሳሰሩ እንደ እስር ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያና የአስተዳደር ቢሮዎች የመሳሰሉ ተሠርተዋል። እንዲሁም ባንዳንድ ቦታዎች ጥቂት ትምህርት ቤቶችና ባለሙያና መድኃኒት የማይገኝባቸው በህዝብ ጉልበት የተሠሩ የሕክምና ጣቢያ ተብለው የሚጠሩ ቤቶች መኖራቸውም ይታወቃል። በዋናነት ፖሊስ፣ አስተዳደርና፣ የስለላ መዋቅሮችን ለማገናኘት የሚያስችል አንድ የስልክ መስመርም ተዘርግቷል። ከዚህ ሌላ የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ሊያሻሽል የሚችል እንዲህ የሚባል ፕሮጀክት አለ ብለን የምንጠቅሰው ነገር የለም። እኛ ልማት የምንለው ቢሮክራሲውን ማገልገል እንደ ዓላማ አርገው የሚከናወኑ ሥራዎችን ሳይሆን፣ ለህዝባዊ አገልግሎት ቅድሚያ ሰጥተው የሚሠሩትን ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ “ድምጺ ወያኔ” የሚዘግበውን እንመን ካላልን በስተቀር፣ በኢሮብ ወረዳ ውስጥ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ያከናወናቸው የልማት ሥራዎች የሉም። ያም ሆነ ይህ፣ የተባለውን ያህል የልማት ተግባር ተከናውኖ ቢሆን ኖሮም እንኳ፣ እንደ የአንድ ህዝብ ዜግነታዊ መብት እንጂ፣ የአንድ ፓርቲ የልማት ክንዋኔ መመጻደቂያ ሊሆን አይገባም እንላለን።

 

በሌላ አነጋገር ስለልማት ስናወራ ከላይ የተጠቀሱት አገልግሎቶች ተጠቃሚ የሆነው ህዝብ ምን ያህል ነው? አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚችል አቅም ያለው የአካባቢው ተወላጅ ምን ያህል ነው? አቅም እንዲኖረው ለማድረግ የተነደፉና ብዙኃኑን ለማሳተፍ የሚችሉ ፕሮጀክቶች አሉ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ይመስለናል። የኢሮብ ህዝብ በሻዕቢያ በተሰነዘረበት የጥፋት ጦርነት የነበረውን ሁሉ እንዳልነበረ ተደርጎ የወደመበት መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ግን “በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም” ከሚለው መርኅ ተጠቃሚ አልሆነም።

 

በነገራችን ላይ ህዝቡ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ቀድሞ ሻዕቢያ ሊወረን እየተዘጋጀ ነው፣ በማለት አቤቱታውን ለመንግሥት ቢያቀርብም፣ በወቅቱ ሰሚ ጆሮ ለማግኘት ባለመቻሉ፣ በድንበር ጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በየዋሻውና በየጥሻው ሲንከራተት ከሁለት ዓመት በላይ ማስቆጠሩ ይታወቃል። ጦርነቱ በተወው ጠባሳ ምክንያት እስካሁን ድረስ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ያልቻሉ ዜጎች መኖራቸውም ገሃድ ነው።

 

በወቅቱ ከሻዕቢያ ዓይነቱ ሀገር አጥፊ ጦረኛ የሚከላከልለት መንግሥት ባለማግኘቱ ህዝቡ ክላሽንኮቭን ይዞ የሻዕቢያን ታንክና ከባድ መሣሪያዎችን በዓይጋ ምድር ላይ ገትሮ በመያዝ እንደተዋደቀም ይታወቃል። በዚህ ጊዜ “ዕጡቓት ሰንበት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጀግናው የኢሮብ ሚሊሺያ በወራሪው ኃይል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ የቀረውን ወደመጣበት መልሶ የነበረ ቢሆንም፣ ደጀን የሚሆነው መንግሥት ባለመኖሩ በሕይወት መስዋዕትነት ያስመዘገበውን ድል እንዲነጠቅ ተደርጓል። ደጀን የሚሆንለት መንግሥት ኖሮት ቢሆንና ረዳትና ስንቅ በወቅቱ ደርሶለት ቢሆን ኖሮ፣ ያ መስዋዕትነት እንዳሁኑ ዋጋ ባላጣ ነበር። ሻዕቢያም ከጥቂት ቀናት በኋላ ተዝናንቶ በመመለስ ሀገርና ህዝብ ላይ ያንን ያህል ጥፋት ለማድረስ የተመቻቸ ዕድል አይገጥመውም ነበር።

 

ያንን ዓይነት መስዋዕትነት ከፍሎ አለሁልህ የሚል መንግሥት በማጣት ድሉን የተነጠቀው የኢሮብ ህዝብ ከቀዬው ተፈናቅሎ በየዋሻውና ጥሻው ቢንከራተትም መልሶ እንዲቋቋም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ በመንግሥት በኩል የተደረገለት አንዳችም ድጋፍ የለም። ጠቅለል ባለመልኩ ስለልማት ስናወራ በ18 ዓመት የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዕድሜ ውስጥ የኢሮብ ህዝብ መሠረታዊ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል የሚያስችል የተቀየሰ ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የሚችል የልማት ተግባር የለም።

 

ለኢሮብ ህዝብ ስለተደረገው ልማት፣ ስለፍትህ መጓደል፣ ስለየሕግ የበላይነት፣ ስለድንበር መካለልና በዙሪያው ስላጋጠሙት ችግሮች፣ ህዝቡ ላይ ስለደረሱ የተለያዩ ወከባዎች፣ ስለሥራ አጥነት መስፋፋት፣ ስለአካባቢው አሉታዊ የባህል ለውጥና የሚያስከትለው ውድቀት፣ የብሔረሰቡን አባላት እርስ በርስ ለማጋጨት እየተሠ ያለው አሻጥር፣ በምርጫ ’97 በገዢው ፓርቲ ያላገባብ ስለተሰረቀው ህዝባዊ ድምፅ … ወዘተ ዝርዝር ማቅረብ የዚህ መግለጫ ዓላማ አይደለም። ባጭሩ ለማስቀመጥ ግን፣ የኢሮብ ህዝብ ተደራራቢ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮዓዊ ችግሮች ቀፍድደው ይዘውታል። በተለይ ባሁኑ ጊዜ ደግሞ በህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ የብሔረሰቡ ሕልውና ከምን ጊዜም በላይ ለአደጋ ተጋልጧል።

 

ዘገባውን በሚመለከት ከዚህ በላይ ቆንጠር አድርገን እንዳቀረብነው ሆኖ አሁን በአካባቢው ያንጃበበው አደጋ ሥጋታችንን ከነበረው በላይ በእጥፍ እንዲጨምር አድርጎታል።

 

ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደገና ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚሉ አስተያየቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲሰነዘሩ ይሰማል። የኤ.ኤፍ.ፒ. ዘጋቢም የሚጠቁመው ይህንኑ ነው። የአፍሪቃ ቀንድ ያለመረጋጋት ሁኔታም አካባቢው የሠላም ቀጠና ሊሆን የሚችልባቸው ፍንጮችን በማሳየት ፈንታ የሠላም ፍላጎታችንንና ተስፋችንን የሚያጨልም ደመና እያንጃበበበት ይገኛል። የኤርትራ መንግሥትም የጠብ ተንኳሽነቱን የሚያቆም መስሎ አይታይም። የመለስ ዜናዊ አገዛዝም የአገዛዝ ዕድሜን ይጨምርልኛል ብሎ ካመነ፣ ሁኔታውን ሊጠቀምበት እንደምችል ጥርጥር የለውም። እነ ግብፅና ሱዳን ጥቁር ዓባይን አስመልክቶ የራሳቸው የረጅምና አጭር ጊዜ ዕቅድ አላቸው። የሀገር ውስጥ ሠላማችንም ባስተማማኝ መሠረት ላይ የቆመ አይደለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁነን አሁን ጦርነት ቢጀመር ዛሬም እንደገና ከ80 ሺ በላይ የዜጎች ሕይወት የሚቀጥፍ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። ይህንን ሁሉ ደማምረን ስንገመግም የኢሮብ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ያሉ ዜጎቻችን የሚከፍሉት መስዋዕትነት ከፍተኛ እንደሚሆን ግምት ውስጥ እናስገባለን።

 

እንደ ከዚህ በፊቱ፣ ዛሬም “ሳናውቀው” ልንወረር እንደምንችል መጠርጠሩ አይከፋም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢሮብ ህዝብ ከማንም በላይ ተጎጂ ሊሆን እንደሚችል የማያጠራጥር ሐቅ ነው። ከዚህ በፊት በሻዕቢያ ተጠልፈው የተወሰዱት ከመቶ በላይ የኢሮብ ዜጎችን የት ደረሱ ብሎ የጠየቀ የመንግሥት አካል የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዳሎል ተጠልፈው የተወሰዱት የፈረንሣይና የእንግሊዝ ዜጎች (ቱሪስቶች) ለማስፈታት ሲል ያካሄደው ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ የሚደነቅ ከመሆኑም በላይ ውጤትም አስመዝግቦ ቱሪስቶቹ መፈታታቸው ይታወሳል። ከ10 ዓመት በፊት በሻዕቢያ ስለተጠለፉትና እስካሁን ድረስ መዳረሻቸው የማይታወቅ ከ100 በላይ ኢትዮጵያዊ የኢሮብ ተወላጆች ግን ዲፕሎማሲያዊ ግፊቱ ይቅርና የውግዘት መግለጫም በመንግሥት በኩል አለመሰጠቱ እጅጉን አሳዝኖናል።

 

በመሆኑም ህዝባችን ቁርጥ ቀን ሲመጣ ከራሱ ውጭ ሌላ ድጋፍ እንደሌለው ቆጥሮ መንቀሳቀስ የሕልውናው ብቸኛ ዋስትና መሆኑን ተገንዝቦ ራሱን ለመከላከል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል። በበኩላችን ህዝቡ በራሱ ተደራጅቶ በሚወስደው ማነኛውም እርምጃ ላይ ከጎኑ እንደማንለይ ልናረጋግጥለት እንወዳለን። ከዚህም በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች፤ እንዲሁም ለሀገር መከላከሊያ ሠራዊት የኢሮብ ብሔረሰብን የገጠመው አሳሳቢ የመኖርና ያለመኖር ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት ደህንነቱና ሕልውናው የሚጠበቅበት ሁኔታን እንዲከታተሉና ባስፈለገ ጊዜ ሁሉ እንደ ከዚህ በፊቱ አሁንም ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

 

ኢትዮጵያና ህዝቧ ለዘላለም ይኖራሉ!!!

የኢሮብ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት በማንም ኃይል አይገሰስም!!!

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!