ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም (ታኅሳስ 2001 ዓ.ም.)

የካርል ማርክስ የፖለቲካ ፍልስፍና ሞተ ተብሎ፣ ወደ መቃብር ከገባ ሃያ ዓመት ሊሆነው ነው። ስለካርል ማርክስ በጻፍሁት ያልታተመ ጽሑፍ “በይሁዲነት ተወልዶ፣ በክርስቲያንነት አድጎ፣ በከሀዲነት የሞተ” በማለት የተገነባበትን ሁኔታ ለመግለጽ ሞክሬ ነበር።

 

ብዙዎች በደንብ የተረዱት ሰዎች ስለምዕራባውያን የካፒታሊስት ሥርዓት፣ (ወይም በደርግ ዘመን የሰው በላው ሥርዓት ሲባል የነበረው) ያደረገውን ትንታኔ ያደንቁታል፤ በማርክስ ላይ ከባድ ነቀፌታ የሚሰነዘርበት በመተንበዩ ላይ ነው። ዋናው ትንቢት የካፒታሊስት ሥርዓት እያደገና እየሰፋ ሲሄድ፣ በውስጡ በሚፈጠሩት ቅራኔዎች የተነሳ ብጥብጥ ወይም በደርግ ቋንቋ አብዮት የሚባለው ይከሰትና ወደ ሶሻሊስት ሥርዓት ይለወጣል፤ የሶሻሊስት ሥርዓትም ወደ ኮሚዩኒስት ሥርዓት ይለወጣል የሚል ነው።

 

በእርግጥ ማርክስ እንዳሰበው የካፒታሊስቱ ሥርዓት ደረቅና እስቲሰበር የሚጠብቅ አልሆነም፤ በአዳዲስ ሁኔታዎች አዳዲስ መፍትሔዎችን እየፈጠረ ራሱን ሲያራምድ ቆይቷል። ባህርዩን ባይለውጥም መልኩን እየለዋወጠ፣ ማርክስ በገመተው ፍጥነት ወደ አስከፊ ውስጣዊ ቅራኔዎች አልገባም፤ ምልክቶች ግን ነበሩ።

 

ለምሳሌ የአሜሪካ ፋብሪካዎች እየተዘጉ፣ የአሜሪካ ባለሀብቶች ወደ እስያና ወደ ላቲን አሜሪካ ሀገሮች እየሄዱ ፋብሪካዎችን ሲያቋቁሙ፣ ማርክስ ካፒታል (ሀብት) ሀገር የለውም ያለውን እያረጋገጡ ነበሩ። የእስያና የላቲን አሜሪካ ሀገሮች፣ በምዕራባዊያን የእውቀት ጥበብና ገንዘብ እንዲለሙና እንዲከበሩ ለማድረግ ሲረባረቡ፣ አትኩሮታቸው ወደነሱ ኪስ የሚገባው ገንዘብ ላይ እንጂ በየሀገሩም ሆነ በዓለም አቀፍ ገበያ ብለውም፣ የሦስተኛውን ዓለም አምባገነኖች እያሰለፉ ሲያባብሉና ሲያስገድዱ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ የምዕራብ ሀገሮች በብዙ ሸቀጦች በተለይ በልብስ፣ በጫማ፣ ቀጥሎም በራዲዮን፣ በተለያዩ ቁሳቁሶች፣ በልጆች መጫወቻዎች፣ … እያለ፣ በመኪናና በኮምፒዩተሮችም ከአምራችነት ወደ ሸማችነት ተሸጋገሩ።

 

በሦስተኛው ዓለም ህዝብ ርካሽ ጉልበት እያተረፉ የተንደላቀቀ ኑሮ ለመዱ፤ እርስ በርሳቸው ባለው ፉክክር ወዳጅና ጠላትን መለየት አቃታቸው። እነሱን ለከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ያበቃቸውን የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የፍትህና የሕግ የበላይነት ረሱት፤ በሥልጣን መባለግ፣ ማጭበርበር፣ ከማጅራት መችነት ያላነሰ ወንበዴነትና ዝርፊያ ባህላቸው ሆነ። ዋጋ ያላቸው ማዕድናት ያላቸውን ሀገሮች ሁሉ በግድም ይሁን በውድ በቁጥጥራቸው ስር አዋሉ፤ በብድር የኑሮ ዘዴ የውሸት መንደላቀቅ አስኮራቸው። ቀስ በቀስም ሌሎች ደሀ ህዝቦች የነሱን ጦርነቶች እንዲዋጉላቸውና እነሱን እሳቱ እንዳይነካቸው ሁኔታዎችን አመቻቹ።

 

በዚህ ዓመት ጉድ ፈላባቸው፤ የገንዘብ ንግዳቸው ተንገዳግዶ ወደቀ ወይም እነሱ እንደሚሉት ቀልጦ ተንጠባጠበ። ብዙ ሀብታሞች የተባሉ ሞላጮች በአውሮፓም በአሜሪካም ተያዙ፤ በዚህ ሰሞን እንኳን አንድ ሞላጫ ሀብታም ከሃምሳ ቢልዮን (ሚሊዮን አይደለም ቢሊዮን) ዶላር በላይ ማጭበርበሩ ታወቀ። ሃምሳ ቢሊዮን ዶላር ማለት በግርድፉ አምስት መቶ ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ይሆናል። አሥር ጊዜ ግድም የኢትዮጵያን የዘንድሮ ዓመት በጀት ያህላል ማለት ነው!

 

ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተራቆቱ፤ በብድር የተሠሩና የተገዙ ቤቶች ሁሉ፣ ከፋይ በማጣታቸው በአበዳሪው ባንክ ተያዙ፤ ባንኮቹም ራሳቸው እየከሰሩ የመንግሥትን ዕርዳታ የሚጠይቁ ሆኑ፤ የመኪና ፋብሪካዎች ወደ ኪሳራ በመጠጋታቸው የመንግሥትን ድጋፍ ጠየቁ፤ አሜሪካ የቻይና ባለዕዳ ሆነ። ቻይናን ጨምሮ ብዙ የሦስተኛ ዓለም ሀገሮች፣ ዓለም አቀፍ ገበያ በተባለው ላይ ተስፋቸውን መስርተው የገነቧቸውን ፋብሪካዎች መዝጋት ተገደዱ።

 

በያለበት ብዙ ሠራተኞች ከሥራቸው እየተፈናቀሉ፣ በቤታቸው እንዲቀመጡ ግዴታ ሆነ። የህዝብ ቁጣ በአስከፊ መልኩ እየተገለጸ ነው። በብዙ የበለጸጉ ሀገሮች የንግዱና ፋብሪካው ፊታውራሪዎች፣ በግፍና በገፍ ሲዘርፉ ኖረው ዛሬ በዓመት አንድ ዶላር ደምወዝ ብቻ እያገኙ፣ ለመሥራት ፈቃደኞች መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው።

 

ይህ ሁሉ የሚያሳየው ማርክስ እንዳለው፣ የካፒታሊስት ሥርዓት በውስጡ ብዙ ቅራኔዎችን የያዘ መሆኑን ነው፤ ዛሬ በአውሮፓና በአሜሪካ መንግሥት የህዝብን ገንዘብ እያወጣ የግል የንግድና የፋብሪካ ድርጅቶችን በተለያየ መንገድ መደጎሙ፣ የውስጥ ቅራኔዎቹ የመጨረሻ መግለጫ ነው። ለምን ተብሎ ነው ሲበዘበዝ የኖረ ህዝብ አሁን በዝባዡ ሲጨነቅ፣ ለዕርዳታ የራሱን ኑሮ እየጎዳ እንዲደጉመው የሚደረገው? ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል፤ ትክክለኛ መመሪያ የሚሆነው አሁን ነበር።

 

ምዕራባዊያን የስድ ገበያ እምነታቸውን ለመጠበቅ፣ ድንጋዩን ጨው ለማድረግ እየጣሩ ይመስላሉ፤ ከአሁን በኋላ ግን መሪዎቹ ለማታለል ቢፈልጉም ህዝቡ የሚታለል አይመስልም። እውነቱ ፍጥጥ ብሎ ሲታይ እንኳን ሌላው ሲ.አይ.ኤም ይጨክናል፤ መጨካከን እየመጣ ነው። ኋላቀር የነዳጅ ዘይት አምራቾች ነገሩ ገና አልገባቸውም፤ ዓለምን በቤንዚን ብር ለመንዳት የነበራቸው ሕልም እያከተመ ነው። ዓለም እየተለወጠ ነው። ቤንዚን ከጥቂት ወራት በፊት በበርሚል ወደ መቶ ሃምሳ ዶላር ደርሶ ነበር፤ ዛሬ አሽቆልቁሎ ወደ ሠላሳ አምስት ብር እንዘጭ ብሏል።

 

ለሀብታም ሀገሮችም ቢሆን ከአሁን ወዲያ በቀኝ እጅ እየዘረፉ፣ በግራ እጅ እየቆነጠሩ፣ የሦስተኛው ዓለም አሽከሮቻቸውን የሚደጉሙበትና የህዝብን ቁጣ ማስታገሻ የሚሆን የብስኩት ዕርዳታ የሚሰጡበት አቅም እያነሰ ወይም ጭራሹኑ እየጠፋ ሊሄድ ወደሚችልበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስላል። ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ፣ በሰለሉ የገዛ እግሮች ላይ መቆም ግዴታ ሊሆን ነው፤ ምናልባት ግዴታው ያቀራርበንና ያፋቅረን፣ ያሳድገንም ይሆናል፤ ካወቅንበት።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!