ሠለሞን አየለ 

በዚህ ጽሑፍ የገለፅኩትን ጉዳይ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ የሚከታተሉ ወገኖች ጋር ለመጋራት ከአንድ ወር በላይ ከራሴ ጋር ሙግት ገጥሜአለሁ። አንድነት ፓርቲንም ቀረብ ብዬ ለማጥናት ሞክሬያለሁ።

 

የወያኔ “የቤት ልጅ” የነበረው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ በጋዜጠኛው ማስታወሻ መጽሐፋ “ክንፈ የሁሉ ወዳጅ የሚሉት አይነት ሰው ነበር። ፕሮፌሠር አሥራትን ከርቸሌ ከላከ በኋላ ከተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ከቀኝ አዝማች ነቃጥበብ በቀለ ጋር ወዳጆች ሆነው ነበር። …” (ገጽ 207)

 

“… ቀኛዝማች ብዙ ጊዜ ወደ ክንፈ እየደወሉ ‘ይህን ይህን አታድርጉ ለስማችሁም በጎ አይደለም’ እያሉ እንደ አባት ይመክሩትና ይቆጡት የነበረ ሲሆን፤ ክንፈ ደግሞ መአህድ ተዳክሞ እንዲቆይ ቀኛዝማችን ከሥልጣን የሚገለብጥ ሁኔታ እንዳይመጣ በምስጢር ያስጠብቃቸው ነበር። …” (ገጽ 207) በማለት የገለፀውን በወቅቲ ሐሜት የነበረውን ጉዳይ ያረጋገጠና ዛሬ ማንም ሊያስተባብለው የማይቻል እውነት መሆኑ የተረጋገጠውን ሳነብ ይህችን ሃሳቤን ለማጋራት ወሰንሁ። ከዚህ በላይ መዘግየት ትርፉ ፀፀት መሆኑም ተሰማኝ።

 

አፈሩ ይቅለላቸውና የመአህድ ተ/ም/ፕሬዝዳንት የነበሩት ቀኛዝማች ነቃጥበብ በቀለም ሆኑ የደህንነቱ መ/ቤት ኃላፊ ክንፈ ገ/መድህን ይህችን ምድር ጥለዋት ሄደዋል። ክንፈ ቀድሞ እሳቸው ደግሞ ተከትለው ሄደዋል። ድርጊታቸው ግን በመጥፎም ቢሆን ሲታወስ ይኖራል። ታሪክ መዝግቦታልና።

 

ፕ/ር አሥራት የወያኔ ሥጋት

መአህድ (የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት) ከመመስረቱ ሠፊ ህዝባዊ ተቀባይነት የማግኘቱ አንድ ምክንያት የፕ/ር አሥራት ቀደም ታሪክና የወቅቱም ድፍረት መሆኑን የተገነዘበው ወያኔ መአህድን ለማዳከም ፕ/ር አሥራት ላይ ማነጣጠር ዕቅዱ አደረገና ሰበብ እየፈጠረ ይከሳቸው ጀመር።

 

ፖሊስ ጣቢያ እየተመላለሱ መጠየቅ፣ ፍ/ቤት እየቀረቡ በዋስ መለቀቅ የዘወትር ተግባራቸው ሆነ። “ከእንግዲህ የዋስ ክምችት በባንክ ማስቀመጥ ሊኖርብኝ ነው” በማለት የተናገሩትም በዚህ ወቅት ነው። ፕ/ር አሥራት ክሱ፣ ወከባው፣ ማስፈራራቱ፣ ክትትሉ፣ ቦርሳ መነጠቁ (ተስፋዬ እንደነገረን፤ በወቅቱም የነፃው ፕሬስ ጋዜጦች እንደዘገቡት) ሁሉ ሲፈፅምባቸው ከዕምነታቸው ዘነፍ፣ ከአቋማቸው ሸብረክ፣ ከይዞታቸው ለስለስ ቢሉና ርምጃቸውን ገታ አድርገው ቢንበረከኩ ለእስራት አይበቁም እንደነበረ ለማወቅ “ጠንቋይ ቀላቢ” መሆን አይጠበቅም። አሥራት ግን በዕምነታቸው ፀኑ፣ በአቋማቸው ጠነከሩ፣ በትግሉ ገፉበት ወያኔም ሕግን በፖለቲካ መሣሪያነት ተጠቅሞ ወህኒ አወረዳቸው። ለሞትም በቁ።

 

የፕ/ር አሥራት መታሰር የመአህድ መንበርከክ

ፕ/ር አሥራት እንደታሰሩ ሁለተኛው ተ/ም/ሊቀመንበር የነበሩት ኢ/ር ኃይሉ ሻውል “ሀገር ጥለው ቁርበት ጠቅለለው” ኑሮአቸውን ባህር ማዶ አደረጉ። ሌሎቹ ምክትል ሊቀመናብርትም በተለያየ መንገድና ምክንያት ከፓርቲው መልቀቃቸው ሳያንስ በጋዜጠኛ ይወነጃጀሉ ገቡ።

 

በዚህ ወቅት አንደኛው ተ/ም/ሊቀመንበር ቀኛዝማች ነቃጥበብ በቀለ መአህድን በብቸኝነት ተቆጣጠሩት፤ ቀኛዝማችን ደግሞ የደህንነቱ ሹም ክንፈ ገ/መድህን ተቆጣጠራቸው። በዚህም መአህድ የማይስፋፋም የማይጠፋም ፓርቲ ሆነና ለተነሳለት ሳይሆን ለወያኔ ዲሞክራሲ በመሣያነት የሚሠራ ሆነ።

 

የዚህ ጽሑፍ አቅሪቢ እንደሚያስታውሰው “ፕ/ር አሥራት የመአህድ መሥራች” እየተባለ ሲነገር ቀኛዝማች ምቾት አይሰጣቸውም ነበር። እንደውም አንድ ዝግጅት ላይ ቃሉ ተደጋግሞ መነገሩ አበሳጭቷቸው “ታሪክ አታበላሹ የመአህድ መሥራች እኛ ነን” በማለት እንደተናገሩ ያስታውሳል።

 

በአንድ በኩል በአሥራት የእስር መስዋዕትነት እየተነገደና አውሮፓና አሜሪካ ገንዘብ እየተሰበሰበ፤ በሌላ በኩል ትግሉ ቀዘቀዘ ሲባል “አሥራት የለኮሱት ሻማ እንዳይጠፋ በሩ እንዳይዘጋ” የሚል ማደናቆሪያ እየተነገረ ትግሉ ተረስቶ “አሥራት ይፈቱ!” የሚል አንድ ጠንካራ ሥራ እንኳን ሳይሠራ ወህኒ ቤት ማቀው ሞቱ። አስክሬናቸውን ከቦሌ አጅቦ ቤት ለማድረስ የወጣው ሰው በዱላ ሲደበደብ በቀብረኛው ዕለት አንድ ወጣት ቆስሎ፣ አንድ ሲሞት “ቀኛዝማች መአህድን አይመለከተውም” አሉ።

 

ቀኛዝማችን በሥልጣን ለማቆየት ሌሎችን መምታት

ብዙዎች በወቅቱ ይጠረጥሩት የነበረውን ጋዜጠኛ ተስፋዬ በውስጥ ዐዋቂ ብዕሩ እንዳረጋገጠው፤ ቀኛዝማች በደህንነት መ/ቤት እየተጠበቁ ፓርቲው ደከሟል፣ ቀኛዝማች እየመሩ አይደለም፣ መሪውን አሳስሮ ፓርቲው ተኝቷል፣ … ወዘተ የሚል ጥያቄ የሚያነሱትን የተለያየ ስም እየሰጡ ይመቱዋቸው ነበር። ከዚህም ውስጥ “የአሥራትን ስም እየጠሩ ተቆርቋሪ መስለው ፓርቲ የሚያፈርሱ ናቸውና የወያኔ ሠርጐ ገቦች ናቸው” ከማለት አልፎ ከየት እንዳመጡት የማይታወቅ የሸዋ አርበኞች ግንባር አባል የሚልም ይገኝበት ነበር። በተለይ ይህኛው ዓቃቤ ሕግ በፕ/ር አሥራት ላይ ምስክር በሚያሰማበት ወቅት መባሉ በዚህም ስም ሰዎች መባረራቸው የእነ አቶ ክንፈ ሥራና ሴራ በመሆኑ ባያስገርምም፤ ለዚህ እኩይ ተግባር ቀደም ተዋናይ ሆነው የተሰለፉት ቀኛዝማች እና በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች ሁኔታ ግን አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው።

 

“እባክህ ለአንድ ሣምንት አስረህ ልቀቀኝ” በማለት የደህንነት ሹሙን ክንፈን እስከ መማጠን ደርሰው እንደነበር በጋዜጠኛ ተስፋዬ የተነገረን ቀኛዝማች መአህድን እንዴት እና በምን ሁኔታ እንዳቆዩት በስፋት የሚታወቅ በመሆኑ ለማስታወስ እና ከአንድነት ፓርቲ ጋር ለሚኖረው ንፅፅር ይህን ያህል ከጠቀስኩ በቂ ይመስለኛል።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለወያኔ ስጋት ሆኖ መታየት

ከ21 ወራት የእስር ቆይታ በኋላ በሽማግሌዎች ድርድር የተፈቱት የቅንጅት መሪዎች ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ በፈጠሩት መከፋፈል ተበታትነው እንዲቀሩ ወያኔ ይመኝ ነበር ብቻ ሳይሆን ለዚህ ይሠራ ነበር ማለት ስህተት አይሆንም።

 

አንድነት በርካታዎችን የቀድሞ ቅንጅት አባላትና አመራሮች ይዞ ሲመሠረት የወያኔ ምት ከሸፈ። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ መሪ መመረጥዋ ደግሞም ትልቅ ስጋት ሆነበት። የወያኔ ሰዎች ዳኛ ብርቱካንን በሚገባ ያውቋታል። ለአቶ ስዬ አብርሃ የዋስትና መብት በመፍቀድ የማይደፈረውን የደፈረች ቆራጥ ሴት ወደ ፖለቲካ ፓርቲ መሪነት መምጣት ለወያኔዎች ራስ ምታት ቢሆንባቸው አይገርምም።

 

ብርቱካን የመረጣትን አንድነት ለማጠናከር ሙሉ ጊዜዋን ብቻ ሳይሆን ሕይወቷንም ሰጠች። የቤተሰብ በሙሉ ለማሰባሰብ በትዕግስት፣ በሆደ ሰፊነት እና በቆራጥነት ተንቀሳቀሰች። አውሮፓና አሜሪካ የሚኖረውና በቅንጅት መሪዎች መለያየት ተስፋ የቆረጠው ኢትዮጵያዊ ተስፋቸው እንዲንሰራራ ለማድረግ ተጣጣረች። ሆኖም ወያኔዎች “ይህች ባቄላ ከአደረች አትቆረጠምም” አሉ።

 

መአህድን ለማዳከም አስራት ላይ ወጥነው እንደሠሩት ሁሉ አንድነትንም ለማዳከም ብርቱካን ላይ አነጣጠሩ። አውሮፓ በጉብኝት ላይ እያለችም “አትመለስም” የሚል ወሬ በስፋት አሰራጩ። ብርቱካን ግን ምን ሆኜ ለምንስ ብዬ ሀገሬን ጥዬ እቀራለሁ አለች። ሕገወጥ ንግግር አድርጋለች፣ መንግሥት ዝም ብሎ ማየት የለበትም ቢያስራት ይሻላል የሚል ወሬ ደግሞ በስፋት አናፈሱ በሐሰተኛም ፃፉ። ማስፈራሪያ ቢጤ መሆኑ ነው። ብርቱካን ግን ሁሉንም ወደ ጐን ጥላ ወደ ሀገሯ ተመለሰች። ሕጉን ሁሉ ትተው የጉልበት ሥራ ጀመሩ።

 

ሕግ ሥልጣን የማይሰጣቸው የፖሊስ ኮሚሽነር ጠርተው ማስፈራሪያም ማስጠንቀቂያም ሰጧት። “በምን ሥልጣናችሁ ነው እንዲህ የምትሉኝ?” ስትላቸው ተከታታይ መድበው በሄደችበት እየተከታተሉ እያስፈራሩ እንዲያንበረክኳት ለማድረግ ሞከሩ። የብርቱካን ፅናት ይበልጡንም ንዴት ውስጥ ጨመራቸውና “ሦስት ቀን ሰጥተንሻል” አሉ። ይህንንና በመገናኛ ብዙኀን ገለፁ። ይህ ሁሉ ወ/ሪት ብርቱካንን አንበርክኮ አንድነትን ለማዳከም ነበር። ብርቱካን ግን በእምነቷ ፀናች፤ ቃሏን አከበረች፤ ለዓላማዋ እስከ ሞት የተሰለፈች በሕግ የበላይነት ላይ የማትደራደር መሆኗን አሳየች። በዚህም በማስፈራሪያ ሁሉ ሳትበገር እስራትን በጀግንነት ተቀበለች።

 

የመአህድ ታሪክ በአንድነት ተደገመ

የፕ/ር አሥራት ወልደየስን መታሰር ተከትሎ በመአህድ ውስጥ የተከሰተው ድርጊት ተመሳሳይነት ባለው መልኩ በአንድነትም ውስጥ እየተፈፀመ ነው። ጥቂቱን እንመልከት።

 

ወ/ት ብርቱካን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽኑ ጠርተው ባነጋገሯት ሰሞን የፓርቲው ሦስተኛ ሰው ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብቻለሁ በማለት በጋዜጦች አማካኝነት ነገሩን። አንዳንድ የአመራር አባላት ደግሞ “ይህ ጉዳይ የብርቱካን የግሏ ጉዳይም ነው” ማለታቸውን ጋዜጦች ዘገቡ። ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው የፓርቲው ም/ቤት አባላት ፊርማ አሰባስበው ስብሰባ መጥራታቸውና የሥራ አስፈፃሚው አካሄድ አላማረንም ማለታቸው፣ ም/ቤቱም በወ/ሪት ብርቱካን ላይ የተፈጸመው ድርጊት ሕገወጥ እና ፓርቲውን ለማደከም ታልሞ የተከናወነ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ የፓርቲው ጉዳይ እንደሆነ በመግለፅ ለሥራ አስፈፃሚው ማሳሰቢያ መስጠቱ እንዲሁ ከጋዜጣ ተነበበ።

 

አንድነት እንደ መአህድ እየተንበረከከ ይሆን!?

በመሪው በፕ/ር አሥራት ወልደየስ መታሰር እና በቀኛዝማች ነቃጥበብ በቀለ በደህንነቱ መ/ቤት መማረክ ምክንያት መአህድ ለወያኔ የተንበረከከ ፓርቲ ሆኖ እንደነበር በተለይ ዛሬ አሌ የሚል አይኖርም። “ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ” ነውና ጋዜጠኛ ተስፋዬ በማያሻማ፣ በማያጠራጥር፣ በግልጽና በሚገባ ገልጾታል። አንድነትስ ከወ/ሪት ብርቱካን መታሰር በኋላ ምን እየሠራ ነው? ወደየትስ እየሄደ ነው?

 

ወ/ት ብርቱካን በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ የተጠየቁ ሰሞን መልቀቂያ አስገብቻለሁ ብለው በጋዜጦች አማካኝነት የገለፁት ምክትል ሊቀመንበሩ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም የመልቀቅ ሃሳባቸውንም ሆን መሰረዛቸውን በተመሳሳይ ሁኔታ በጋዜጦች ዐወጁ። “ብርቱካን መብቷ በሕግ የተገፈፈ እስረኛ ስለሆነች የፓርቲው ሊቀመንበር ናት ማለት አይቻልም።” የሚል ሃሳብ ከአንዳንድ የአመራር አባላት መሰንዘሩም ተሰማ። አባባሉ ቁጣ በማስነሳቱ ግን ሳይገፉበት እንደቀረ የፓርቲውን የዕለት ተዕለት ክንውን በአወንታዊም በአሉታዊም ሆኔታ በሚፅፉ ጋዜጦች ተነበበ።

 

የወቅቱን ሁኔታ ሲያስታውሱ የነበሩ ሁሉ በጣም አሳዛኝ ነበር የሚሉት፤ “አንድ የም/ቤት አባል ታህሳስ 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ የመጀመሪያም የመጨረሻም የሆነው የአቋም መግለጫ በወጣበት ወቅት ከተቃወሙት ሁለት ሰዎች አንዱ የፓርቲው ሁለተኛ ሰው መሆናቸው አስገራሚ ነበር።” ይላሉ። የመአህድንና የቀኛዘማችን ሁኔታ በቅርብ እናውቅ ነበር የሚሉ ወገኖችም ወ/ት ብርቱካን ወህኒ ከገባች ጊዜ ጀምሮ ፓርቲው አከናወናቸው ተብለው የሚጠቀሱ የጐሉ ተግባራት ያለመኖራቸውን በማንሳት ሂደቱን ለማመሳሰል ይሞክራሉ።

 

ጥያቄ የሚያነሱ አባላትን የመምታት ተመሳሳይ ሂደት

በቀኛዝማች ነቃጥበብ የሥልጣን ዘመን ጥያቄ ያነሱ የነበሩ ወገኖች ምን ስም እየተሰጣቸው እርምጃ ይወሰድ እንደነበር ከላይ በመጠኑ አሳይቻለሁ። የእርምጃው አቀናባሪ ደግሞ የደህንነቱ ቁንጮ አቶ ክንፈ ገ/መድህን እንደነበሩ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ነግሮናል። የዛሬውን የአንድነት የሚያቀናብረው ማን እንደሆነ ለጊዜው ባይታወቅም ተመሳሳይ የሆነ ሥራ ግን ተጀምሯል። የሊቀመንበሯ እስራት ትኩረት አልተሰጠውም፣ የፓርቲው እንቅስቃሴ አይታይም፣ የፓርቲው አመራር የመሪነት ድርሻውን እየተወጣ አይደለም፣ … የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ወገኖች የተለያየ ስም እየተሰጣቸው በተለያየ ሁኔታም እየተፈረጁ መሆኑን ለማወቅ በሀገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦችን ማየቱ ብቻ በቂ ነው። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት

 

የወ/ት ብርቱካንን ምስል እያስቀደሙ ፓርቲ የሚያፈርሱ፦

ይህ አባባል ውስጥ ለውስጥ ከመባል አልፎ ፓርቲው በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በይፋ መነገሩን የሚገልፁት ሰዎች ድርጊቱን “የፕ/ር አሥራትን ስም እየጠሩ መአህድን ለማፍረስ የሚጥሩ” ከሚለው አባባል ጋር ያዛምዱታል። ይህ ፍረጃ በስፋት በአባላቱ ውስጥ እንዲሠራም በመደረጉም በአንድነት ውስጥ ስለብርቱካን ማንሳት ሰዎችን እያሸማቀቀ መጥቷል ይላሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚገልፁ አባላት።

 

የወያኔ ሠርጐ ገቦች

ይህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በሃሳብ የተለየን ወይንም ጠንክሮ የታየን ለማንበርከክ አልያም ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውል ዘመን ያልለወጠው ሥልጣኔ ያልረሳው ፍረጃ ነው። በአንድነትም ውስጥ በሃሳብ የሚለዩ፣ ጥያቄ የሚያነሱ፣ ፓርቲው መሥራት ያለበትን እየሠራ አይደለም፣ የሚሉ አመራሩን የሚተቹ፣ … ወዘተ ይሄው ስም እየተሰጣቸውና አሉባልታ እየተወራባቸው እንደሆኑ ፓርቲውን ቀረብ ብሎ ለማየት የሞከረ ለመረዳት ጊዜ አይፈጅበትም።

 

ቀኛዝማች ነቃጥበብ በቀለ በደህንነት ሹሙ ክንፈ ገ/መደህን እየታገዙ ጠንካራ የመአህድን አባላት በወያኔ ሠርጐ ገብነት እየወነጀሉ ሲያሳስሩ እንደነበር የሚያስታውሱ ወገኖች የዛሬውን በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የተጀመረ ፍረጃ በጥርጣሬ እንደሚያዩት ይናገራሉ።

 

ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ያላቸው

ይህኛው በጣም አደገኛው እና በቀኛዝማች ጊዜ ከነበረው “የሰሜን ሸዋ አርበኞች ግንባር አባል” ከሚለው ፍረጃ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። ወያኔ ብለው ቢፈረጁ ተቀባይነት ላያገኙ የሚችሉበትን ሰው ከፓርቲው ለማባረሪያ፤ ወይንም ግለሰቡን አስደንግጦ ለማንበርከክ ሌላው ሰበብ እንደማይሠራላቸው ሲገነዘቡ ነው ወደዚህኛው አደገኛ ፍረጃ የሚሄዱት።

 

ይህ ፍረጃ ለወያኔ አሳልፎ የመስጠት ስለሆነ በጣም አጠያያቂ አፈራረጅ ነው። በዚህ እኩይ ተግባር የተሠማሩ ሁሉ በአስቸኳይ ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ ታሪክ ይቅር የማይለው ትውልድም በይቅርታ ሊያልፈው የማይቻል ወንጀል እየፈፀሙ መሆኑን እንዲገነዘቡት የዚህ ጽሑፍ አቀራቢ ይጠይቃል።

 

የአንድነቱ ቀኛዝማች ማን ይሆን?

በመአህድ ተ/ም/ፕሬዝዳንት ቀኛዝማች ነቃጥበብ በቀለ እና በደህንነት ሹሙ ክንፈ ገ/መድህን መካከል የነበረውን ግንኙነት ምንም በማያጠያይቅ መልኩ “የቤት ልጅ” የነበረው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ዛሬ ይንገረን እንጅ፤ በወቅቱ ይወራ የነበረ ስለመሆኑ የዚህ ጽሑፍ አቀራቢ ያስታውሳል። ያኔ ሽንጣቸውን ገትረው ለቀኛዝማች ይሟገቱ የነበሩ እና ሌላውን በአፍራሽነት ይፈርጁ እና ያወግዙ የነበሩ ወገኖች ዛሬ ምን ይሉ ይሆን?

 

የወ/ሪት ብርቱካን ጥንካሬ የአንድነትም ጅምር ያሰጋው፣ አስግቶትም ብርቱካንን በሕግ መሣሪያነት በሰበብ ያሰረው ወያኔ አንድነትንም እንደ መአህድ የማይጋፋም የማይጠፋም ፓርቲ አድርጎ ለማቆየት ተመሳሳይ ተግባር ከመፈፀም ይቦዝናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል።

 

ለዕቅዱ ተፈፃሚነት ደግሞ እንደ ቀኛዝማች ከኃላፊነቱ ወንበር ላይ ተቀምጦ የሚሰጠውን ገፀ-ባህርይ ተላብሶ የሚጫወተው ሰው ማን ነው? የሚለውን ለመመለስ ቀርቶ ማን ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት አሁን የሚቻል አለመሆኑን ለዚህ ጽሑፍ ግብዐት ያነጋገርኳቸው የፓርቲው አባላትም ሆኑ የአመራር አባላት ገልፀውታል።

 

ጊዜ መስተዋቱ ሁሉን ፍንትው አድርጐ ያሳየናል፤ የአንድነቱ ቀኛዘማች ተደብቆ እንደማይቀር ቢታመንም እስከዛሬው ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ብዙ ጠንካራ ሰዎች ከፓርቲው ሊያርቅም፣ ሊያባርርም፣ አልፎ ተርፎም በወይኔ ሠይፍ ሊያስቀላም ይችላልና የአንድነት ፓርቲ ጉዳይ በተናጠል የሀገራችን ጉዳይ በጥቅል የሚያሳስበን እና የወ/ሪት ብርቱካን ሕገ-ወጥ እስራት የሚያስቆጨን ወገኖች ሁሉ ጉዳዩን በንቃት ልንከታተል እና የአንድነቱን ቀኛዝማች ፈጥነን ልንደርስበት ይገባል መልዕክቴ ነው።

 

የብርቱካንን የድል አክሊል መግፈፍ አይቻልም

ወ/ት ብርቱካን የዕምነት ፅናቱን አሳይታለች። ለቃሏ ታማኝ ለዓላማዋ ሟች መሆኗን አስመስክራለች። ለትግሉ ቆራጥነቷን አረጋግጣለች። ተንበርክኮ ከመኖር መሞትን መርጣለች። በዚህም አኩሪ ተግባሯ አሳሪዎቿንም ተፎካካሪዎቿንም አሸንፋ የድል አክሊል ደፍታለች። ይህን በግንባር የተገኘ የክብር አክሊሏን ማንም ሊገፍፋት ፈፅሞ አይቻለውም። ታሪክ መዝግቦታል አይፋቅም። ትውልድ ይቀባበለዋልና አይዘነጋም። ምን አልባት አንድነትን ማዳከም ከተቻለም የማይሞትም የማይሞግትም አድርጐ ማቆየት ይቻል ይሆናል፤ የብርቱካንን የድል አክሊል መግፈፍ ግን አይቻልም። ለሁሉም ጊዜ አለው። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ብርቱካንም ነፃ ትወጣለች፣ አንድነትም ይጠነክራል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!