ልጅ ተክሌ-ከካናዳ

የትችት ብድር፤

ጋሽ ገዳሙ መኳንንት እና አያ ነአምን ዘለቀ

የጀርመኑ ጋሽ ገዳሙ መኳንንት የምወደው፣ የማከብረው፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ እለት እለት የሚያቃጥለው፣ የወያኔ ስራ የሚፈጀው፣ ወደዚህ ወደሀገረ ካናዳ ከመጣሁበትና እሱን ካወቅኩበት እለት አንስቶ ስለኢትዮጵያ ያለው ስሜት የማይዋዥቅ፣ አገር ወዳድ፣ ታላቅ ትሁት፣ የሩቅ የሀሳብ ወዳጄና መምህሬ ነው። ጋሽ ገዳሙ ሲናገር፣ ሲጣራ፣ ሲመሰክር እንዴት ደስ ይላል?። አያውቀኝም። ግን ያውቀኛል። ሲጣራ፡ “ተክልዬ፡ የናቴ ልጅ” ሲል ሆዴ ሽብር ይላል። ለማውገዝና ለመሳደብ አይቸኩልም። ተስፋዬን ግን ጠላብኝ። ኢትዮጵያዊውን ተስፋዬ ገብረአብን ጨከነበት።

 

“ጋሽ ገዳሙ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ግትር የማለት ጠባይ አለህ። ምናለ ይሄን ሰው ብንተወው። ተስፋዬ ትናንት የጻፈውን ጻፈ። ዛሬ የጻፈውን ስራ በትናንቱ መለኪያ መመዘን አለብን ወይ?” ስለው፡ እኔን ግልፍ ብሎኝ መናገሬ እስኪቆጨኝ ድረስ በትህትናና በመልካም አንደበት ከመናገር አልሰነፈም። የምወደው ጋሽ ገዳሙን ተግሳጽ መቋቋም ቢያቅተኝም፣ ሌላው የምወደው ነአምን ዘለቀ አስቀድሞ ስለተስፋዬ የጻፈው ገንቢ አስተያየት ግን የጋሽ ወንድሙንም ይሁን የሌሎች የተስፋዬን ስራ ሲያዩ ደማቸው የሚፈላ ተቺዎች ትችት እንድቋቋም ስንቅ ሆነኝ። ይሄ ጽሁፍ ስለተስፋዬ መጽሀፍ፣ ስለተነሳበት የትችት ማእበል፣ ስለኔ ምልከታ፣ ስለቡርቃ ዝምታ፣ ስለመሰል ጉዳዮች ነው። የማይመቻችሁ ከዚሁ ተመለሱ። ዋናው መልእክቴም ይሄ የተስፋዬን ያለፈ ስራና ዘር/ወላጆች መሰረት ያደረገ ትችት ብዙም አይጥምም የሚል ነው። አይመችም። አልተመቸኝም ብቻ አይደለም ብዙ አያስኬድምም። ምክንያቱም ይሄ ወላጆችን መሰረት ያደረገ ትችት ሁላችንንም ይነካናልና። እነሆ ምሳሌ።

 

አባቴ ከሸዋ እናቴ ከወሎ፤ እኔስ?

 

አባቴ ከሸዋ ነው። እናቴ ከወሎ። ለልደቱ አያሌው ያለኝን ቁጭትና ፍቅር የሚያውቁ “ያገሬ”፡ የቫንኩቨር ሰዎች፡ “እህ፡ ለካ ይቺ ሰውዬ ልደቱ ልደቱ የምትለው ወዳ አይደለም፣ የናቷ ደም ስቧት ነው” እንደሚሉ አልገምትም። እንዳማይሉ አውቃለሁና። ቢሉም የባሰ ሊመጣ እንደሆነ ነው የምነግራችሁ። በቅርቡ አባቴ ኦሮሞ ሳይሆን እነዳልቀረ የሚጠቁም ትልቅ ማስረጃ እንደወጣ ስነግራችሁ ደግሞ በታላቅ ደስታና መፈንደቅ ባይሆንም፡ ከዚህ በፊት “በሴት አያቶቻችን ደጃፍ ማን እንዳለፈ ስለማናውቅ እኔ ኦሮሞ ነኝ እኔ አማራ ነኝ ማለት አንችልም” ያለውን ሰለሞን ደሬሳ ያጠናከረውን እምነቴን ምንም እንዳላናጋው በመጠቆም ነው። ዝብርቅርቅ አለ? ትንሽ ታገሱ ይጠራል። አባቴ የሚጠራው ባሳደጉት አባት ስም ነው። ሀኪም ሳህለማሪያም። አባቴ በ12 ዓመቱ አካባቢ በጣሊያን ተሰርቆ ተወሰደና የሀኪም ሳህለማሪያምን በቅሎ እየጎተተ አደገ። አባቴ። ወላጅ አባቴ። የአባቴ እርግጠኛ አባት ስም ግን መርጊያ ወይም መርጋ ነው። መርጊያ ከሆነ ያው አማራ እንደሆንኩ እቀራለሁ። ይሁን መቼም ምን ይደረግ። መርጋ ከሆነም ኦሮሞ እሆናለሁ ማለት ነው። ምናለ ኦሮሞ ቢያደርገኝ? ዞሮ ዞሮ እናቴ አማራ እንደሆነች ስለምትቀር ባባቴ ኦሮሞ መሆን የምትሰጉ ልትኖሩ አይገባም። ከምንም በላይ ግን እኔ ዞሮ ዞሮ እኔ ነኝ። እኔ አባቴን አይደለሁም። እኔ እናቴንም አይደለሁም። እኔ አያቴንም አይደለሁም። እኔ እኔን፡ እኔ ዘመኔን ነኝ። በናቴና ባባቴ የሆንኩትን የሆንኩት ወድጄ አይደለም። የሆንኩትን እንድሆን ሆኜ እንጂ።

 

ተስፋዬ ተስፋዬ ነው። ወዶ አይደለም ከአቶ ገብረአብ የተወለደው። የእናቱን ስም አላውቅም። ያንን ፍለጋም መጽሀፉን አልበረብርም። ምናልባት ሀዳስ? አዳነች? ጽዮን? ትብለጽ? ልጅ አባኪያ አበበ ሳህለማሪያም ወይንም ልጅ አባኪያ አበበ መርጋ/መርጊያ ከሸዋና ወሎ፡ ከአበበና ከሰብለ ለመወለዱ ምንም ካላዋጣ፤ ተስፋዬ ገብረአብ ከምድረ ኤርትራ ከሆኑ ወገኖች ለመወለዱ ምንም ያዋጣው ነገር የለም። ከማንም መወለዱ የሱ ችሎታ የሱም ጥፋት አይደለም። ተስፋዬ ራሱን ተስፋዬን ነው። ስለኢትዮጵያዊነት ከተነሳ የሁላችንም ኢትዮጵያዊነት አጠያያቂ ነው። እኛ ኢትዮጵያ ለመሆናችን ምን ያዋጣነው ነገር አለ? እንደው በድንገት ኢትዮጵያዊ ሆንን እንጂ። ማለቴ፡ እንደ ደረጄ ዳዲ ገብረ ጉራቻ ወይንም እንደ ዴንዝል ዋሽንግተን መወለድ አጋጣሚ ነው። ችሎታ አይደለም። ተስፋዬም ሌላ ነኝ ቢል እንኩዋን ኢትዮጵያነቱን ሊክደው አይችልም። እኛ ጋር ያለ እሱ ጋር የሌለ ምን አለ። ክፋት ከሆን የኛ ተስፋዬን በኤርትራዊነት የምንከስ ሰዎች ደም ከክፋት የጠራ አይደለም። በተለይ እዚህ እውጭ ዘመናችንን የፈጀንና መመለሻችን የማይታወቅ፡ ኢትዮጵያዊነታችን እየተሸረሸረ ሌላነታችን እየጎለበተ የመጣ ሰዎች የተስፋዬን ኢትዮጵያዊነት ለመጠየቅ ከቶም ግብረገባዊ መደገፊያ የለንም። መቆሚያችን ከድቶናል። አገሬ ቫንኩቨር ስል ወድጄም አይደለም። ሰው ከቆየ ከሚስቱ ከወለደ፤ ሰው በሰው አገር ከቆየ የሰውን አገር አገሩ ማድረጉ አይቀርም። ስለዚህ እኛ የሰውን አገር አገራችን ያደረግን ሰዎች ተስፋዬን ኢትዮጵያዊ አይደለም ለማለት ከቶ እንደምን ይቻለናል?

  

የትችት ብድር፤ ይሄ ሰው ምን ይሁን? ስቅሎ ስቅሎ !!

 

ብዙዎቹ በተስፋዬ ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች የሚመነጩት በመጸሀፉ ላይ ከሰፈሩ ህጸጾች ሳይሆን፤ ደራሲው ከዚህ ቀደም ካሳተማቸው መጻህፍትና ከኤርትራዊ ደሙ ጋር በተያያዘ ነው። ተስፋዬ ነኝ ያለውን ላይሆን ይችላል። ግን ደግሞ እኛ ነህ ያልነውንም አይደለም። ይልቅስ የሆነውን ነው። ወይም የሚለውን ይቀርባል። አትዮጵያዊ ነኝ ካለ ኢትዮጵያዊነቱም ከምን እንደመነጨ ካሳየን፤ የለም አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ያባትህ አጎት ነውና ኤርትራዊ ነህ ብሎ መደምደም አግባብም በጎም አይደለም። ተስፋዬ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብቻ አይደለም ያለው፡ ኢትዮጵያዊነቱ እንዴት እንደተገነባ፤ ምናልባትም ብዙዎቻችን ልንገልጸው ከምንችለው በተለየ መልኩ ዜግነቱ የተገነባበትን አፈር፣ ዜግነቱ ያበጀውን አፈር ሰርቶታል። እንደተስፋዬ አገላለጽ ተስፋዬ ሌላ ነገር መሆን አይችልም። ልጥቀስ ከመጽሀፉ? ውረዱ ገጽ 408 ላይ። “እኔ የአድአ ጥቁር አፈር ነኝ” ይለናል ተስፋዬ። ተስፋዬ ሌላ ሊሆን አይችልም። በመሰረቱ ኤርትራዊያንስ ሌላ ሊሆኑ ይቻላቸዋልን? ተስፋዬ ኤርትራዊ ነኝ ቢለን እንኩዋን ኢትዮጵያዊነቱ አያበቃም። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊነት ምርጫ አይደለም ብያቻኋለሁ። “የእያንዳንዱ ሰው ማንነቱ በአካባቢው፣ በልጅነት ሕይወቱና በቤተሰቦቹ የተገነባ ነው” ይለናል ተሰፋዬ። “ማንነት ደምና ነፍስ ነው።” በቃ ከዚህ በላይ ምን ይምጣ? ያለአማርኛ ቋንቋ እኔ ህይወት የለኝም ያለው ተስፋዬ በርግጥም ያለአማርኛ ቋንቋ ህይወት እንደሌለው አየን። ልብ አድርጉ ተስፋዬ የጻፈው ጥፋትን፣ ተስፋዬ የሰበከው ደም መፋሰስን፣ ተስፋዬ ያስተማረው የህዝብን ርስ በርስ መባላት ሊሆን ይችላል። ግን ያ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊያደርገው የሚችለውን ነው። ኤርትራዊ ከመሆን ካለመሆን ጋር አይገናኝም። ደም መፋስስን የሰበኩ ሌሎች ኢትዮጵያንም አሉን።

 

አብዛኞቹ የተስፋዬን መጽሀፍ ሳይሆን ተስፋዬን የሚተቹ ሰዎች ለትችታቸው ጉልበትና ብርቱ መቀመጫ የሚያደርጉት የተስፋዬን ስራ ሳይሆን የተስፋዬን እናትና አባት ነው። ኤርትራዊ ነው። ግፋ ካለ ደግሞ ትችታቸው የሚዘለው ወደ ቡርቃ ዝምታ ነው። የጋዜጠኛው ማስታወሻን የሚተቹት ከቡርቃ ዝምታ ተበድረው ነው። የትችት ብድር። እንደው ይህ ሰው ከንስሀ በላይ ምን ይበል? ምንስ ያድርግ? ይሰቀል? ይሙት? ይፈንዳ? ይህ ሰው እኛ የምንፈልገውን ማለት የለበትም። ነው ወይስ እንደ ስዬ “ሉአላዊነታችን በሻእቢያ ተደፍሮ” እያለ ማላዘንና “ደርግን በመጣል ሂደት በሰራሁት ከዚያም በኋላ የህዝቦችን የብሄር ብሄረሰቦችን መብት በማስከበሩ ሂደት ባደረግኩት አልቆጭም ሉአላዊነታችንን ባስደፈረ ቡድን በመረታታችን እንጂ” ማለት ነበረበት?  በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካና ሁኔታ ከተጻፉ መጻህፍት ውስጥ ቀደም ሲል ከእስር ቤት ሾልኮ የወጣው የዶ/ር ብርሀኑ መጽሀፍ አሁን ደግሞ የተስፋዬ ገ/አብ የጋዜጠኛው ማስታወሻ እጅግ ማርከውኛል። ማርከውኛል ብቻ አይደለም፤ ለምናደርገው ፖለቲካዊ ትግል ፋይዳቸው ጎልቶ ይታየኛል። የዶ/ር ብርሀኑ መጽሀፍ ታትሞ ሲወጣ በዚህ ባካባቢያችን በተዘጋጀ ምሽት ላይ፡ ስለዶ/ር ብርሀኑ መጽሀፍ ስናገር እንዲህ ብዬ ነበር። “ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ማስተማሪያነት የሚያገለግል ታላቅ መጻህፍት።” አንተ አልክ አላልክ እኛ ምን ቸገረን ትሉ ይሆናል። የማትሉም ትኖራላችሁ። ስለተስፋዬም ይሄንን ማለት እችላለሁ። የቋንቋ ሊቃውንት ምን እንደሚሉ አላውቅም፡፡ እንደው ከሊቃውንት ባነሰ ምልከታ ግን የተስፋዬም መጽሀፍ እንደዚያው ለኢትዮጵያ የቋንቋና ወግ ተማሪዎች በሆነ መልኩ ሊያገለግል የሚችል ታላቅ ስራ ነው ብየ አምናለሁ። ከምንም በላይ ግን ፖለቲካዊ ፋይዳው። የመሰከረው እውነታ። የተነተነው ትንታኔ።

 

ተስፋዬ ምስክር ነው፡ ህያው ምስክር

 

አንዳንድ ሰዎች ተስፋዬ የማናውቀው አዲስ ነገር አልነገረንም ይላሉ። መልካም፡ እነዚህ ሰዎች በርግጥም ስለሕወሀት ሁሉን ያውቁ ይሆናል። ለኛ ለማናውቀው ግን አናውቀውምና ያላወቅነውን ነው የገለጠልን። ብናውቀውም እንኩዋን፡ በስማ በለውና በግምት የምናውቀውን በማስረጃና በአመንክዮ አስጨበጠን። ይሄንን ደራሲው ምንም የማናውቀው ነገር አልነገረንም የሚሉ ተቺዎች አስተያየት ሲተች ወዳጄ ነአምን ዘለቀ የተስፋዬ ገብረአብ መጽሀፍ እይታ፣ መረጃና እውነታ እጅግ ጠቃሚና ወቅታዊ ነው ይለናል። ትክክል ነው። የተስፋዬ መጽሀፍ እንደ ብአዴንና ኦህዴድ ያሉ ስብስቦችን መሳቂያና መሳለቂያ አድርጎ ራሳቸውን እንዲመረምሩና ቁጭት በውስጣቸው እንዲገባ ሊያደርግ ይችላል። ተስፋዬ ምስክር ነው። ሰው ሲገደል ያየና ሲመከር የሰማ ምስክር። ተስፋዬ የወያኔን አሻጥር እንደኛ ሳይሆን እንደነሱ ያየ፣ የተመለከተ፣ የሰማ፣ የመከረ፣ ያማከረ ምስክር ነው። እንዲህ ያለውን ምስክር ሲሆን ሲሆን በል ግፋ ተናገር መስክር ነው፡ እንጂ የታባህ ምናባክ፣ ሻእቢያ ምናምን ማለት ደካማነትና ፈሪነት ብልሀት ማጣትም ነው። ላንዳንዶቹ ግን፣ በተለይ ይሄንን ኤርትራዊ ነው መዝሙር ለሚዘምሩ ሰዎች ከዚያም አልፎ ወገን ይዞ ማፋጠጥ፡ ራስን ማጋለጥ ነው። ወያኔን የተጸየፍነው በስራው ነው። ከተስፋዬና ተስፋዬን ከምንጠረጥርበት ሻእቢያዊም ንግግር በፊት ወያኔን ጠልተነዋል። ተስፋዬ ይሄንን መጽሀፍ የጻፈው ኢትዮጵያዊ ተልእኮ ይዞ ነው። ተስፋዬና መጽሀፉ ወያኔን በመጥላታችን ላይ የሚጨምሩት ምንም አይነት ኤርትራዊ ግብአት የለም። ምናልባት ለጥላቻችን መሰረትና ተጨማሪ ማስረጃ ያስጨብጡን ይሆናል። ያንን አድርጓልም። ቀድሞ በግምት የቆመውን እምነታችንን ዛሬ በማስረጃ ላይ አኖረንል። እነሆ ምሳሌ።

 

ተስፋዬ ምስክር ነው። አሁን የብረሀነ ገብረክርስቶስና ሚስቱ ታሪክ ሰምቼው አላውቅም። እነዚህ ሰዎች ይሰርቃሉ? በሚገባ። እነዚህ ሰዎች ይገድላሉ? እንክት አድርገው። ዋናው ሰይጣንና የታሪኩ ብልት ያለው ግን ከዝርዝሩ ነው። ከገጽ 388 ላይ የተዘረዘረው የመለስ ቀኝ እጅ፤ የብርሀነ ገብረመስቀል ሙስና ዝርዝር ግን ለኔ እንግዳ ነው። የተስፋዬ ማስረጃ የመጨረሻ አይደለም። የመጀመሪያም አይደለም። ግን የተስፋዬ ማስረጃ በክሳችን ላይ ሌላ አንድ ተጨማሪ ዋጋ ያክልልናል። ልጨምር? ለምሳሌ፡ ብዙዎቻችን ስለትግራይ መልማትና መበልጸግ እየበሸቅን ስንናገር ይሰማል። ምናልባት የትግራይ  መበልጸግና የትግራያዊያን እውነት ባይሆን እንኩዋን አንድ ነግር ግን እርግጥ ነው። ሰዎቹ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ያቺን ክልል ብልጽግናን እስኪያስታውካት ድረስ፤ በላይ በላይ ሊያጎርሷት ቀን ተሌት ይለፉ እንደነበር በማስረጃ ያሳየናል። ትግራይ የባቡር ሀዲድ ሊዘረጋ እንደታሰብ ያኔም ጀምሮ እሰማ ነበር። እንደውም ባቡሩ አዲስ አበባ ድረስ የሚዘልቅ ቢሆንም ለአማራው ካላቸው ጥላቻ የተነሳ የባቡር መስመሩ በአማራው ክልል እንዳያልፍ ወዲያ በአፋር አዙረው እንደው በምድርም ቆፍረው አዲስ አበባ ሊያስገቡት ነው የሚል የተሸራረፈ ወሬ ነበር። ተስፋዬ ግን ወሬውን ወደ እውነቱ በሚያቀርብ መልኩ በማስረጃ አስደግፎ ሰዎቹ ያንን አላማቸውን ለማሳካት ምን ያህል እንደ ተጓዙም ጭምር አሳየን። የመገናኛ ምክትል ሚኒስትሩን አቶ አየነውን ልብ ይሏል። እኔ ወደ ደቡድ አፍሪካ ለስራ ጉዳይ ሄጄ በነበረበት ወቅት አቶ አየነውም ትግራይ ላይ ባቡር የመዘርጋትን እቅድ ለመነጋገር ደቡብ አፍሪካ መጥቶ ነበር ይለናል። በቃ አበቃ። ያ ጫፍ ጫፍ እናውቅ የነበረውን ነገር በማስረጃ አስደግፎ ነገረን።

 

ተስፋዬን እንዴት እናምነዋለን የምንል እንኖራለን። ሁለት መልስ አለኝ። አንዱ የብስጭት መልስ ነው። መልአክ እስኪገልጽላችሁ ጠብቁ ነው። ሁለተኛው እውነተኛ መልስ ነው። ተስፋዬ ያነሳቸው ነገሮች እኛም በምናውቃቸውና ከዚህ በፊት በሰማናቸው ነገሮች የሚጠናከሩ ናቸው። ለዚህም እነሆ ምሳሌ። ለምሳሌ፡ በ2000 ዓ.ም. አካባቢ ወጋጎዳ በሚባልና አራት ቋንቋዎችን ማለትም ወላይትኛ፣ ጋሙ፣ ዳውሮኛና ሌላኛውን ዘነጋሁት ቋንቋወች የተውጣጣ የመማሪያ መጻህፍት ታትመው ያንን በመቃወም በወላይታ አካባቢ አመጽ ተፈጥሮ ብዙ ሰው ተገድሎ ነበር። ከፍተኛ አመጽ። በዚያን ዘመን እንደ ኢህአዴግ አቀንቃኝ የምናየው እፎይታ መጽሄት እጅግ ያስደነቀኝንና ተስፋዬ መጽሀፉን ሳይጽፍም በፊት ለሰዎች ሁልጊዜም አነሳው የነበረውን ዘገባ ይዞ ወጣ። ያ መጽሄት ከአገሬ እስክወጣ ድረስ እጄ ላይ ነበር። እኚ ተስፋዬ መጽሀፉ ላይ ያነሳቸው የአርባምንጩ አቶ ወንድሙ የተናገሩትን ያኔም ጽፎት፤ ይሄ በወያኔነት የምናውቀው ሰው በወያኔ ልሳንነት በምናውቀው መጽሄት እንዴት እንደዚያ ያለ ቃለ ምልልስ አቀረበ ብዬ ተደንቄ ነበር። ተስፋዬ ዛሬ ብቻ ሳይሆን በዚያም ዘመን ውስጥ ከኢህአዴግነትም ባሻገር የሚታገለው እውነት እንደነበር ይጠቁማል።

 

ተስፋዬና አብርሀ፤ አበበና አብርሀ፡-

 

በኛ መካከል መደጋገፍ እንጂ መነቃቀፍ በጎ እንዳልሆነ አምናለሁ። ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት ይሆናልና። አንዳንድ ጊዜ ግን መተቻቸት ይጠቅመናል እንጂ አይቆምጠንም። አበበ በለው ሌላው የማደንቀው የማከብረውም ጎበዝ ባለሙያ ነው። አንዳንድ ጊዜ ከትግራይ ተወላጆች ጋር የተያያዘ ነገር ሲነሳ ቱር ብላ የምታመልጠው ጥብቅና ነገር አለችው። ለነገሩ እንዳበበ አይነት ሰዎች ያስፈልጉናል። ካላበዙት በስተቀር ሚዛን ይፈጥራሉ። አቤ ብዙውን ጊዜም ምክንያታዊ ነው። አንዳንድ ግዜ ሚዛኑ ጎዶሎና ጋዳላ ቢሆንም ቅሉ። ለምሳሌ ከተስፋዬ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ የመጽሀፉን አጠቃላይ ፋይዳ ረስቶ ወይ አሸንፎ ላያሸንፈው ነገር የተስፋዬን ድካም ከግምት ሳያስገባ በትችት ተኮር ጥያቄና መለስ ተስፋዬን ጠምዶት ነበር። አቤ አንዳንዴ ጥብቅናው ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለግለሰቦች ይመስላል። ዘወትር የትግራይ ተወላጆችን ጥያቄ ውስጥ የሚፈጥር ነገር ሲነሳ ቀድሞ ድምጽ ማጉያ ይዞ ዘራፍ ማለቱ መልካም ቢሆንም መደገፍ የሚፈልገውን ወገን ለመደገፍ ሲል ብቻ የሚጸየፈውን ወገን የሚያፋጥጥበትን ነገር አልወደድኩለትም። በተለይ ተስፋዬን አንድ ሰዓት ሙሉ ሲያናግረው አንድም የመጽሀፉን ጠንካራ ጎን አልጠቀሰም። አንድ በተለይ ከትግራይና ሕወሀት ጋር የተገናኘ የአበበን አቀራረብ የማይወድ ወዳጄ አበበ በተመሳሳይ መልኩ የትግራይ አካባቢን ሰዎች ቃለ ምልልስ ሲያደርግ ተቃራኒ ወገን ጥያቄ እንዲጠይቃቸው እድል ካለመስጠቱም በላይ፡ ያንን በኩል የሚሞግተውን ሀሳብ አያቀርብም። የአበበን ሬድዮ ፕሮግራሞች ስለማልከታተል ስለጠቅላላው ዝግጅቱ አስተያየት መስጠት አልፈልግም። አልችልምም። ከተስፋዬ ጋር በተያያዘ የቀረበው ግን ተስፋዬን ለመፋለም ቆርጦ የተነሳ አስመስሎበታል። ይሄ አንድ ነገር አስታወሰኝ።

 

አንድ የኛ የቫንኩቨር አካባቢ ዳኛ ስለጎበዝ ጥብቅናና ጠበቃ ያጫወቱንን አሸናፊ ሆነው የወጡበትን ገጠመኝ አስታወሰኝ። ዳኝነት ሳይሾሙ የዛሬ ሀያ ምናምን ዓመት በፊት ነው። አንድ የፍቺ ጉዳይ ይዘው ፍርድ ቤት ሲከራከሩ የከሳሽ ወገን ያቀረበችው የቤተሰብና ሕጻናት ጉዳይ አማካሪ ስለተከሳሽ የጻፈው ዘገባ ተከሳሽን/ባልን አንድም ሳያስቀር የሚወነጅል፤ የተከሳሽን ምንም በጎ ጎን የማይናገር ምስክርነት ነው። ለተከሳሽ ጥብቅና የቆሙት እኚህ ሰው ያንን ምስክርነት ሊያስተባብሩ የሚችሉበት ምንም መንገድ አልታይ አላቸው። ግን ተነሱ። ይሄ ደምበኛዬ ከዚህ ቀደም ለልጆቹ እንዲህ አላደረገላቸውም? አድርጓል። ልብስ አልገዛላቸውም? ገዝቷል። ወስዶ አላጫወታቸውም፤ አላዝናናቸውም? አጫውቷል አዝናንቷል። እንዲህስ ያለ መልካም ነገር አላደረገም? አድረጓል። ታዲያ ምን ገዶህ ነው ስለ ደምበኛዬ ባቀረብከው የምስክርነት ዘገባህ ውስጥ ከነዚህ መልካም ስራዎች ውስጥ አንድም እንኩዋን ያልጠቀስከው? ያቀረብከው ሪፖርት ሙሉ በሙሉ መጥፎ መጥፎውን ብቻ ነው። የዚህ ምስክር ምስክርነት ሚዛናዊነት የጎደለውና አንድን ወገን ብቻ ለመጥቀም የተሰጠ በመሆኑ ውድቅ ተደረገ። አበበ በቃለ ምልልሱ ላይ ተስፋዬን ለማሸነፍና አፍ ለማዘጋት ቆርጦ የተነሳ ይመስል ነበር። እሺ አለማለቱ እንጂ ራሱ መለስ እንኩዋን ፈቃደኛ ሆኖ ቢመጣ በዚያ መልኩ መጠየቅ የለበትም። ዞሮ ዞሮ ተስፋዬም አልተረታም። አብርሀን ለመከላከል ተስፋዬን ማፋጠጥ ወይም ማራወጥ የለብንም። ትንሽ ስለአብርሀ ልጨምር።

 

አብር በላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ መከራና እጣ ፈንታ የሚያስጨንቀው፤ ለረጅም ጊዜ በሙያው በትጋት ኢትዮጵያን ያገለገለና የሚያገለግል ጥሩና ትጉህ ኢትዮጵያዊ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ ከህወሀት ራስ አውርዶ ሻእቢያ ላይ የሚያላክከውን ነገር አልወደድኩለትም። አሁን ኢትዮጵያና ኤርትራ ተለያይተዋል። የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ አብቅቷል ማለት አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር ግን ኤርትራ አይደለም። የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር የሚተበትቡት ከትግራይ የበቀሉ የሕወሀት ልጆች ናቸው። ይሄ የሚያስጨንቀው መሰለኝ አብርሀን። ስለዚህ ሕወሀት ምንም ነገር ሲያደርግ ወስዶ በሻእቢያ ተወላጆች ላይ የሚያላክከከው ነገር አይዋጥም። ስለዚህ የኢትዮጵያን ችግር ድንበር አሻግሮ ኤርትራ ይወስደዋል። ይሄንን እታች እሄድበታለሁ። ተስፋዬ ሲጽፍ ነው የሚያምርበት ሲናገር አይመጣለትም። የአብርሀን ጉዳይ እንደዋዛ መጽሀፉ ውስጥ ስላካተተው አምሮበት ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ከአብርሀ ጋር በተያያዘ የሰጣቸው ማብራሪያዎች እምብዛም ሚዛን አልደፉም። ይልቅስ በበቀል የተነሳሳበት ይመስላል። ተስፋዬ ገብረአብ በምንም መልኩ ስሙን ያንሳው አብርሀ ራሱን በሚገባና በሚያሳምን መልኩ ተከላክሏል። አብርሀ ላንድ ወዳጁ የጻፈውና በኋላም በተለያዩ ድረ-ገጾች ላይ የተሰቀለለት ጽሁፉ እኔን ራሴን አስደምሞኛል። አሳምኖኛልም። በወቅቱ፡ እነዚህ ሰዎች አገሪቱን ይለውጣሉ ብዬ እንደማንኛመውም ኢትዮጵያዊ በማሰብ ደግፌያቸው ነበር ይለናል አብርሀ። የኋላ ኋላ ግን ስራቸው ክፉ መሆኑን ሳይ መቃወም ጀመርኩ ይላል። የአብርሀ መልስ ጠንካራ ነው። ጠንካራ ብቻም አይደለም፡ ሀቀኛም ይመስላል። አጥጋቢ።

 

አንዳንድ ተስፋየ ራሱ በአብርሀ ላይ ያነሳቸው ክሶች ብዙም አሳማኝ እነዳልሆኑ ከክሱ መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ስለአብርሀ የሚናገረውን ክፍል ቀንሶ በድረገጽ እንዲሰራጭ ያደረገው ራሱ አብርሀ ነው የሚለው ክስ ብዙ የማያስኬድ ነው። ግን ጥርጣሬ ብቻም ነው። አብርሀ የሚሰራውን የሚያውቅ ብልህ ጋዜጠኛ ነው። እሱ ጋር ብቻ ያለ ቅጂ ቢሆን መልካም። ነገር ግን እሱ ጋር ብቻ ሳይሆን ደራሲውን ጨምሮ ሌላም ቦታ ብዙ ቅጂዎች እንዳሉ እያወቀ እንዲያ ያለ ስራ ይሰራል ብለን አንገምትም። በርግጥም ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ ሁላችንም/አብዛኞቻችን ብንሆን እንደ ደርግ ይሆናሉ ከዚያም ይብሳሉ ብለን አልጠበቅንም ነበር። ስለዚህም በዚያን ወቅት እንኩዋንስ ትውልዱና/ደሙ ከነሱ የሆነው አብርሀ፡ “ጠላትህን አማራን አጥፋ” እየተባለ የተፎከረበትና የተቀሰቀሰበት የአማራ ተወላጆችም ከኢህአዴግ ጉያ ገብተዋል ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግን እቅድ በከፍተኛ ደረጃ አስፈጽመዋል። ስለዚህ አብርሀ በላይ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን አመታት ከህወሀት ጎን ተሰልፎ ቢያገለግል ብዙም አያስደንቅም። ዋናው ነገር ግን እሱ አይደለም። ዋናው ነገር ልክ እንደተስፋዬ ሁሉ ይሄ ሰው አሁን የት ነው ያለው ነው። አብርሀንም ይሁን ተስፋዬን የሚያድናቸው ያሁን አቋማቸውና ስራቸው ነው። ተስፋዬ አቋሙን ጻፈ። ኢትዮጵያዊነቱን ተናገረ። እሱም እንዳለው፡ እሱ የሆነውን ነኝም ያለውን ልንነሳው አይቻለንም። ምክንያቱም እኛስ ምን መሆናችንን ማን አረጋገጠልን? የአብርሀ አገር ወዳድነት ምንም ጥየቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ይልቅስ ከዚህ ከኤርትራዊነት ጋር በተያያዘ የማይጥመኝ የነአብርሀስ አካሄድ የሚከተለው ነው።

 

ይልቅስ፤ ስለኤርትራዊነትና ትግሬነት

 

እነ አብርሀና እነስዬ የኖርንበትንና የሚያንከራትተንን የህወሀትን ችግር የሻእቢያ ስራ አድርገው የሚያስቀምጡት ነገር አይጥመኝም። ሕወሀት እዚህ እንዲደርስ ሻእቢያ ሚና ተጫውቶ ሊሆን ይችላል። የህወሀት ስራ ግን የሕወሀት ነው። የትግራይ ልጆች ስራ። ተስፋዬ ገብረአብንም ይሁን እነመለስን ኢትዮጵያዊ እንዳልሆኑ የማስቀመጡ ዘመቻ የትም የማያደርሰን የምንቀሰቅስበት ሳይሆን እንዲያውም አንገት የሚያስደፋን ስልት ነው። መለስም ተስፋዬም ኢትዮጵያዊያን ናቸው። የመለስና የተስፋዬ ኢትዮጵያዊነት አሳስቦኝ አይደለም። ግን ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው እየገዛኝ ከሆነ ምን ያህል አሳፋሪነቱ ታስቦኝ እንጂ። እነዚህ ተስፋዬ ኤርትራዊ ነው ከኢትዮጵያ የወጣውም ከኤርትራዊነቱ ጋር በተያያዘ የሻእቢያ ሰላይ ሆኖ ነው የሚሉ ሰዎች የሚያቀርቡት ሎጂክ ርስ በርሱ የሚጣረስ ነው። ባንድ በኩል እነስዬና እነመለስ የተለያዩት የነስዬ ወገን ኢትዮጵያዊነቱ በልጦበት ሻእቢያን ስለጠላ ሲሆን እነ መለስ ደግሞ የሻእቢያን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ሂደት ነው የሚለው ክስ አለ። በሌላ በኩል ግን ከሕወሀት መከፋፈል አሸናፊ ሆነው የወጡት እነዚህ በኤርትራዊነትና በሻእቢያነት የሚጠረጠሩት ሰዎች ናቸው። ስለዚህ ተስፋዬ ሻእቢያ ጋር ንክኪ ካለውና አሸናፊዎቹም ልባቸው ለሻእቢያ የራራ ወጎኖች ከሆኑ ተስፋዬን የሚያሸሸው ነገር አልነበረም። ምክንያቱም እሱም የሻእቢያ ወይንም ያሸናፊው ወገን ነውና። ከዚህ ይልቅ ተስፋዬ የሚያቀርበው መላ ምት የበለጠ ያስኬዳል።

 

ሁሉም ማለትም መለስም፣ ተወልደም፣ ገብሩም አይተ ስዬም፣ ስለትግራይ ያላቸው ራእይ ተመሳሳይ ነው። ያጣላቸውም እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እንጂ ሌላ ምንም አይደለም። ለዚህም ነው አንዳቸው ህወሀት ሌላኛውን ህወሀት አሸንፈው የተቀረው አሸናፊውን ሕወሀት ተቀብሎ አሜን ብሎ የሚኖረው። አሁንም አንገታቸውን የደፉት እነ ስዬ አንድም ቀን አምልጧቸው የሕወሀትን ጥፋት የተናገሩበት ቀን ትዝ አይለኝም። የተወሰነ ቡድን ላይ ነው ግግም ያሉት። አሁን ባለው ሁኔታ በዋንኛነት የኢትዮጵያ ችግር ማእከል ያደረገው እዚያው እትግራይ ወይንም ከትግራይ የወጣው ሕወሀት ላይ ነው። ድንበር ተሻግሮ ሻእቢያ ላይ ማላከክ ወይንም የሌለ ሻእቢያዊ ትስስር መፍጠር የትግራይን ልሂቃን ለመታደግና ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት የተገነባውን የትግራይ የበላይነት በቀጣዮቹ አመታትም መንግስትም ተለውጦም ቢሆን ይዞ ለመጓዝ የተቀየሰ የተባረሩ ግን ያልተለወጡ የሕወሀት መስራቾች ዘዴ ነው። ወደተስፋዬ እንመለስ።

 

ከዚህ በላይ ምን ይፍጠር? እንዲያውም አሁንም ወደፊትም ይጠቀሳል

 

ተስፋዬ ቆንጆ ቆንጆ ለጥቅስ የሚበቁና የአገራችንን ችግር ቁልጭ አድርገው የሚያስቀምጡ አባባሎችም አሉት። “ባለሙያና ስራ ያልተገናኙበት አገር ዜጎች ነን” ይላል ገጽ 15 ላይ ስለራ ከስነጽሁፍና ታሪክ ንባብ ያልዘለለ እውቀትና የፕሬስ መምሪያ ሀላፊነት ሲገልጽ። ባለሙያና ስራ ብቻ አይደለም አዋቂና ተገቢ ሰዎች በተገቢው ቦታ የማይሾሙበት አገር። የህክምና ባለሙያ የመንገድ ስራ ባለስልጣን ሀላፊ ሆኖ የሚሾምበት ብቻ አይደለም፤ የሽምቅ ተዋጊ የአገር መሪ ሆኖ የሚቀመጥበት ብቻ አይደለም እንኩዋንስ ለፕሬስ መምሪያ፤ ሰው ካልጠፋ በተቀር ለአንደኛ ደረጃ ት/ቤት የአማርኛ መምህርነት የማይመጥነው ተስፋዬ እነሆ ብርሀንና ሰላም አናት ላይ ቁጢጥ አለ። ሰውየው በተቻለ መጠን በወንጀል የማያስጠይቀውን እውነት ለመናገር ሞክሯል። ለምሳሌ ገጽ 16 ላይ የፕሬስ መምሪያ ሀላፊ ሆኖ እንደተሾመ እነ ክፍሌ ሙላትና ዋካ ይርሳው በቡድን ሆነው ሲያስቸግሩት አንድ ባንድ እየለቃቀምኩ አስወገድኳቸው ይላል። ተስፋዬ ሊያስወግዳቸው እንዳልሳሳ ብቻ አይደለም የሚናገረው ለቃቀምኳቸው ብሎ ልክ አሁን እንዳደረገው አድርጎ ነው የገለጸው። አላድበሰበሰውም። አልሸፋፈነውም። ምክንያት አልደረደረም። እቅጩን ነው ያስቀመጠው። መለቃቀም ብቻ አይደለም። አማሮ ከስራ ለማስወጣት ሆን ብሎ ወደሌላ አካባቢ በክፋት ተነሳስቶ እንደላካቸውም ነው የሚናገረው። ከዚህ በላይ ምን ያድርግ? ቡርቃ? ስለቡርቃ እናውጋ።

 

ቡርቃ ያበሳጫል። ቡርቃ ሲጻፍ ጮርቃ ወጣት ነበርኩ። መልሼ አላነበብኩትም። በሰዓቱ በኢህአዴግ ላይ ባለኝ ጥላቻ ምክንያትና መጽሀፉ የኢህአዴግን ፖለቲካ የታከከና የኢህአዴግ አገዛዝ ያመጣቸውን ፖለቲካዊ አካሄዶች ነስፍ የዘራባቸውና የተለየ ህይወት ሊሰታቸው የጣረ ስለሆነ አናዶኛል። ደግሞ የጻፈው ተስፋዬ ነው። ገመቹ አይደለም። ኢብሳም አይደለም። ቢያበሳጭም ከወቅቱና ከኢትዮጵያ ደህንነት አንጻር የቡርቃ ዝምታ ያነሳቸው አንዳንድ ነገሮች የሚያስደነግጡ፣ ለጸብ የሚጋብዙ ቢሆኑም ያ ህዝብን ያጣላል ያልነው የቡርቃ ዝምታ ክፍል ግን ባብዛኛው እውነት ነው። ያ ኦሮሞ ወዳጄ ገረሱ ቱፋ ዘወትር የሚያነሳልኝ በቤተክርስቲያናችን አንዳንድ ድርሳናት የተጻፉት አንዳንድ ህዝብን የሚነኩ ጸያፍ ቃላት ብቻ አይደሉም። አያሌ ምሳሌዎች አሉ። አንድ ሌላ ወዳጅ አለኝ የፈረንጅ ዳቦ፣ የፈረንጅ ዶሮ፣ የፈረንጅ በሬ፣ ትልቅ ትልቁን ነገር ሁሉ የፈረንጅ አድርገን፤ ትልቅ ዝንብ ስናይ ግን “የእንትን ዝንብ” እንለው ነበር አለኝ። የት እንደተተረተ አላስታውስም። ግን “ለእንትን ንስሀ አባት ዲያቆን መች አነሰው” ተብሎም ተተርቷል። ያን የፈጠረው ሕብረተሰቡ ነው። ተስፋዬ አልወለደውም። ተስፋዬ ጻፈው። መጻፉ አደገኛ ነበር። ነውም። ግን ውሸት አይደለም። እውነት ነው። እውነትን ደግሞ መጋፈጥ ነው። መሸምጠጥ አይበጅም።

 

ምን አለ፤ ነአምን ምን አለ? ተስፋዬ ገብረአብ ጥሩ ጽፏል አለ

 

የጋዜጠኛው ማስታወሻ ይላል ነአምን በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ስብእናና ኢትዮጵያዊነት እንዲሁም የኢትዮጵያዊያን ነጻነት በሁሉም ተከታታይ መንግስታት ውስጥ እንዳልተከበረ ይናገራል። አንዳንድ ሰወች የእናትና አባቱን ከኤርትራ መምጣት አይተው ጸሀፊውን ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ለማስቀመጥ ቢሞክሩም፤ ጸሀፊው ግን ከውልደቱና ልጅነቱ አንስቶ ለአገሩ ያለውን ፍቅር፤ ያም ፍቅር ምርጫ ሳይሆን መሆን እንደሆነ፤ በምንም መልኩ ማንም እሱም ራሱ ሊቆርጠው የማይችለው እንደሆነ ይናገራል። ልክ ነው። ሰውን ዜግነት መቀየሩ ሌላ ካላደረገው፡ ተስፋዬንም ምንም ድርሰት ሌላ ሊያደርገው አይችልም። ተስፋዬ የራሱን ህይወትና ማንነት አካፈለን። ያ እሱ የተረከልን የራሱ ማንነት ደግሞ ናም ማንነት ነው። እኛ ከሆነውና ካደረግነው የተለየ ምን አለና ነው ሌላ የሚያሰኘው?

 

የተስፋዬን መጽሀፍ ፖለቲካዊና ሁለገብ ፋይዳ ሲገልጽ ነአምን ዘለቀ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። በህወሀት መሪዎችና ደጋፊዎች መካከል ከፈጠረው ቁጣና ጩኸት አንጻር ከመዘነው የተስፋየ መጽሀፍ ልክ በተዘናጉ የህወሀት አመራሮች መካከል በድንገት እንደተደረገ የደፈጣ ጥቃት ይቆጠራል ብሏል። በግራም በቀኝ በውስጥም በውጭም ያሉ የህወሀት ወሮበሎችና ደጋፊዎቻቸው በዚህ መጽሀፍ ተንጨርጭረዋል።  ግን ለምን ተቆጡ። ምንስ አንጨረጨራቸው? ምክንያቱም ስላጋለጣቸውና ራቁታቸውን ስላስቀራቸው ነው ይላል ነአምን። ጭቅቅታቸውና አዳፋ ፖለቲካዊ ማንነታቸውን አደባባይ አወጣው ይለናል ነአምን ዘለቀ። የበረከት ስምኦንን ቅጥፈትና ጭካኔ፤ የአባ ዱላ ገመዳን ደራራ ከፈኔን ግድያ፡ ስናይ ተስፋዬ አበጀህ የሚባል ስራ ነው። ቀድሞ በወሬና ባሉባልታ ብቻ የምናውቃቸውንና መስረጃ ልናቀርብ የምንችላቸውን ክሶች አሁን በተስፋዬ ምስክርነት ውስጥ አገኘነው። የትግራይ ልሄቃን የት ድረስ ጠልቀው እንደገቡ እናውቅ ነበር። ተስፋዬ ግን እንዴ ያን ያህል ጠልቀው እንደገቡና አሁንም በመከላከያ በደህንነት በአስተዳደር ዘርፍ አዚያው ለመቆየት የሚያደርጉትን ሁሉ ጠቆመን። ይኸው ተስፋየ ያለውንና የተነበየውን ለማየት ጊዜ አልወሰደብንም። ከግንቦት ሰባት ጋር አብረው መንግስት ሊገለብጡ አሴሩ ብሎ የብአዴንን ሰዎች በሙሉ እየጠራረገ እያሰረ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የተደራጁ የትግራይ ብሄርተኞች ስራቸውን እንዴት አድርገው እየሰሩ እንደሆነ ከነሱ ወገን የነበረው ተስፋዬ ጨምሮ ነገረን።

 

ባይደመደምም፡ እንደመደምደሚያ፡ ባይቋጭም እንደመቋጫ፡ “ኢትዮጵያዊው ተስፋዬ፡ ካፍሪቃ ደቡብ ይጮሀል”

ይሄ ሰው ቀደም ሲል እንዲህ ያለ፣ ሰውን በሰው፤ ብሄርንም ከብሄር የሚያነሳሳ መጽሀፍ ጽፏል ብሎ ያንን መጽሀፉን ራሱን ችሎ መገምገም አንድ ነገር ነው። የጋዜጠኛውን ማስታወሻ ራሱን በቻለ መልኩ መተቸት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ትናንት ማንም ሰው ምንም ብሎ ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር ዛሬ ምን አለ? ምንስ ያምናል? ነው። ይሄ ሰው እኮ የቡርቃ ዝምታን መጻፍ አይደለም የቡርቃ ዝምታን ከሚደርስ ድርጅት ውስጥ ነበር። ይሄ ሰው ወያኔ ነበር። አልካደም። ግጥም አድርጎ ነው ያመነው። ከዚያ የጥፋት ድርጅት ወጣና ወደኛ ጎራ ተቀላቀለ። መቀበል ነው። ባንቀበለውም ተስፋዬ የሚቀርበት ነገር የለም። የሚቀርበት ነገር ካለም ጥንቱንም ቀርቶበት ወጥቶለታል። የተስፋዬን መምጣት መመኘት ያለብን እኛው ራሳችን ነን። የጠፋው ልጅ መጣ ብለን በመዝለል ፋንታ ማንገራገርና ማጉተምተም አይበጀንም። ደግነቱ ተስፋዬ የሆነውን ሆኗል። እኛ ምንም አልነው ምን እሱ የሆነውን ነው። የተስፋዬ ስራ፣ የጋዜጠኛው ማስታወሻ ንስሀ ነው። ስላለፈው ሀጢያት የሚያትት ንስሀ ነው። የተስፋዬ ስራ ትንቢት ነው። ካንዱ መለስ ተቀብለው በሌላው መለስ ኢትዮጰያን ያንድ ብሄር መፈንጪያ ሊያደርጉ ስለተዘጋጁ ሰዎች የሚያስጠነቅቅ ትንቢት ነው። የተስፋዬ መጽሀፍ ምስክርነተም ነው። ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ። ተስፋዬ በርታ። ቀጥለህ የምትጽፈውን እንጠብቃለን። ጥሩ መሳሪያ አቀብለኸናል።


ልጅ ተክሌ ከካናዳ (ግንቦት 2001 ዓ.ም.) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!