Yegazetegnaw Mastawesha የጋዜጠኛው ማስታወሻያያ አባ ቦር - ከሂዩስተን

ባለፉት 48 ወራት ውስጥ ያነበብኳቸውን የአማርኛ መጻሕፍት ሳስብ ሦስት መጻሕፍት በውስጤ ያኖሩት ደስ እስከወዲያኛውም ባይደበዝዝ ደስ ይለኛል። ዘነበ ፈለቀ (የብዕር ስሙ ነው) የፃፈውን ”ነበር”፤ የፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያምን ”የውድቀት ቁልቁለት” እና አንዳርጋቸው ፅጌ የፃፈውን ”ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ” የተሰኙት መጻሕፍትን መጥቀሴ ነው።

 

እነሆ አራተኛው መጽሐፍ ደግሞ በዚህ ባሳለፍነው ወር ለመነበብ በቅቶ ነፍሴ አድናቆት የቸረቻቸውን መጻሕፍት ቁጥር ወደ አራት ከፍ አደረገው። በተስፋዬ ገብረአብ የተፃፈው ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ”።

 

እነዚህ አራት መጻሕፍት ልብወለድ ወይንም የሕይወት ታሪክ ትረካዎች አይደሉም። ይልቁንስ የቁርጥራጭ ማስታወሻዎች ጥርቅም ናቸው እንጂ። ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ወይንም ግፊት የፈጠረብኝ የተስፋዬ ገብረአብ ”ማስታወሻ” ነው።

 

Yegazetegnaw Mastawesha የጋዜጠኛው ማስታወሻይህ መጽሐፍ ገና ገበያ ላይ ከመዋሉ በፊት ጀምሮ (ሶፍት ኮቲው በኢ-ሜይል) ተሰራጭቷል። በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ (ዳያስፖራው) ኢትዮጵያዊያን ”ጉዳያችን ነው” ብለው በድረ-ገጽና በየሻይ ቡናው መቅመሻ ቤት ተነጋግረውበታል። ተደብረውበታል።

 

አብዛኞቹን ”ዋው!” ያሰኘው ጉዳይ ፀሐፊው የወያኔን ወይም የኢህአዲግን ገመና አጋለጠው፤ ወያኔን ገልቦ ነውሯን ፀሐይ አስሞቀው ዓይነት ነገር ነው።

 

ይህን ጽሑፍ ከማዘጋጀቴ በፊት ”ኢትዮጵያን ሪቪው” እና ”ኢትዮ ሚዲያ” በተባሉ ድረ-ገጾች ላይ የወጡትን ሁለት ጽሑፎች ናሙና ይሆኑኝ ዘንድ ይሁነኝ ብዬ አነበብኳቸው።

 

ፕሮፌሠር ጌታቸው ኃይሌ ”የመጽሐፍ ግምገማ” መሠል ነገር በኢትዮጵያ ሪቪው ላይ ጽፈዋል። ፕሮፌሠሩ ጽሑፉን የፃፉት በእርግጥ መጽሐፉን ለግምገማ ይሁን፤ ፀሐፊውን ለማድነቅ ይሁን ወይንም መጽሐፉ ሰበብ ሆኗቸው የልባቸውን ለመተንፈስ አልመው ይሁን አላወኩም።

 

ፕሮፌሠር ጌታቸው ኃይሌ፦ በተስፋዬ ገብረአብ ከዓመታት በፊት የተደረሰውን አነጋጋሪ መጽሐፍ አስመልክተው በሰነዘሩት በዚህ ሃሳባቸው ”ቆሻሻና ኃይማኖተ ቢስ ህዝብ” ያሉት የትኛውን ህዝብ እንደሆነ ምናልባት አንድ ቀን ሲለይላቸው ይነግሩን ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ወረቀት ላይ መትፋት ነውር ነው።

 

ሌላው ፀሐፊ ”ኢትዮጵያ ይንጋልሽ” በሚል (የብዕር ሥም መሆን አለበት) ሥም በኢትዮ-ሚዲያ ላይ ስድስት ገፅ አስተያየት የፃፉት ናቸው። የእኒህኛው ፀሐፊ ብዕር የተሞላው ቀለም የኢህአዲግ ጠበል የተቀላቀለበት ይመስላል። የቃል አጠቃቀማቸውም ወያኔያዊ ነው። ፅሑፋቸው በርካታ ቃሎችን ቢዘራም አብይ ጭብጡ ”በተስፋዬ መጽሐፍ ላይ እየተንጫጫችሁ ዋናውን የፀረ-ወያኔ ትግላችሁን አትዘንጉ ...” የሚል መካሪ፤ ጥሪ አቅራቢ ብሎም የአዛኝ ቅቤ አንጓች ይመስላል።

 

ተስፋዬ ገብረአብ በመጽሐፉ ውስጥ በተለይም ከገፅ 291 እስከ 294 ላይ የኢትዮ-ሚዲያ ድረ-ገጽ አዘጋጅ (ባለቤት) መሆኑ የሚነገርለትን ግለሰብ ስብዕና ኩስ ቀብቶታል። ለዚህም ነው መሰል የኢትዮ-ሚዲያ ድረ-ገጽ በተስፋዬ መጽሐፍ ላይ የሚያቀርበው አስተያየት አሉታዊ ድምፀት ያለው ነው።

 

”ኢትዮጵያን ሪቪው” ተብሎ የሚታወቀው ድረ-ገጽ ደግሞ የተስፋዬ መጽሐፍን በተመለከተ የሚያቀርበው አስተያየት አዎንታዊነቱ ይበረታል። ሰዎች መጽሐፉን ገዝተው እንዲያነቡትም ማስታወቂያ እየሠራለት ይገኛል።

 

እኔ እንደሚመስለኝ ተስፋዬ ገብረአብም፤ ኤልያስ ክፍሌም ሆነ አብርሃ በላይ ይራገጡ እንጂ ጥርስ የሚሳበሩ ዓይነቶች አይደሉም። ለእኔ በሦስቱ መሀከል ያለው እውነተኛ ልዩነት ሊከሰትልኝ የሚችለው በመለስና በኢሳያስ መሀከል ያለው ልዩነት ግልፅ ሲሆንልኝ ብቻ ይመስለኛል። ”የዘመድ ጥል ... የሥጋ ትል” እንዲሉ ዓይነት።

 

ተስፋዬ ገብረአብ መጽሐፉን ካሳተመው በኋላ በድምፅ ቃለምልልስ ያደረገው ከአንድ የአዲሶቹ የኢትዮጵያ ነፃ አውጪዎች ሬድዮ ጣቢያ ጋር ነው። በአፍላ ነፃ አውጪዎች ጉያ ስር መጣበቅ ዕጣ ክፍሉ የሆነው ተስፋዬ፤ ነገ ከእነማን ጋር በድል አድራጊነት አዲስ አበባ መግባት እንዳለበት ከወዲሁ አስልቶ የጨረሰም ይመስላል።

 

በአንድ ፓልቶክ ላይ ቀርቦ ሰሞኑን እንደተናገረውም ከደቡብ አፍሪካ አስመራ ደርሶ ተመልሷል። ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ክፍል ሁለትንም አሥመራ ሆኖ እንደሚፅፈው ገልጧል። የእነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ነፃ አውጪ ድርጅት አምባሳደር ሆኖ መሄድ ስላለመሄዱ ግን በይፋ የተናገረው ነገር የለም።

 

የተስፋዬ መጽሐፍ ልብወለድ አይደለም። ስለሆነም ስለጭብጥ፤ ስለሴራ፤ ስለገፀ-ባሕሪይ አሳሳል፤ ስለ ታሪክ አወቃቀር፤ ስለመቼት፤ ስለቋንቋ ... እየተባለ የግምገማ ብልት የሚወጣለት ወይም የትችት ብዕር የሚቀሰርበት አይደለም። ”ቁርጥራጭ” ያላቸውን ማስታወሻዎች አሰካክቶና አሰናስሎ ተነባቢ፤ ትኩረት ሳቢ መጽሐፍ ለማድረግ የተጠቀመበት የአፃፃፍ ስልትና የቋንቋ አጠቃቀሙ አበቅ የለሽ ነው።

 

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ፤ የማትሪክ ቆሌ ስለጠመመበት በደብረዘይት ውስጥ ”ሀብታም” የሚባሉ ሰዎችን ልጆች እያስጠና በሚያገኘው ሳንቲም ኑሮውን መደጎም ባለመቻሉ ወታደርነት መቀጠሩን የሚያውቁ ሰዎች ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሥነ-ጽሑፍ ያጠና መሆኑን ሲናገሩ ሂዩስተን ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ሰምቻለሁ።

 

”ዩኒቨርሲቲ” የሚባለው ነገር የሥነ-ጽሑፍ ሕግ መማሪያ እንጂ የሥነ-ጽሑፍ መገብያ አለመሆኑን ልነግራቸው ዳድቶኝ ”ምን አገባኝ” ብዬ ተውኩኝ። ኢትዮጵያዊ መሆን ለዚህ-ለዚህ ካልጠቀመኝ ለመቼ ሊሆነኝ ነው?

 

ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር በቅርብ የተዋወቅሁት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1981 ጀምሮ በመሆኑ መጽሐፉ በቀረበበት የቋንቋ ብስለት መደነቅ አልቻልኩም። ለአጫጭር ልብወለድ ፅሑፎቹና ለአንዳንድ ግጥሞቹ አድናቆት የሰጠሁት ገና ድሮ ነውና። ”የቡርቃ ዝምታ” የተሰኘውን መጽሐፉን ያነበበ ሰው ደግሞ ለሰውዬው ሥነ-ፅሑፋዊ የቋንቋ ውበት ቢደነቅ ነው የሚገርመኝ።

 

ፀሐፊው ከላይ ባነሳነው የራዲዮ ቃለ-ምልልስ ላይ ወዳነሳቸው ጉዳዮች እንመለስ። ከያሬድ ጥበቡ ጋር ባደረገው በዚህ ቃለ-መጠይቅ ላይ ዓይነተኛ ትኩረት የነበረው፦ ለኢህአዲግ ይሠራ በነበረበት ወቅት የሚያምንበትን ለመፃፍ ነፃነት እንዳልነበረውና ነፃነቱን ደቡብ አፍሪካ ከገባ በኋላ መጎናፀፉን ነው።

 

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበርን ሰዎች እስከምናውቀው ድረስ ይኽ ሰው ከማንም የኢህአዲግ ግልገል ካድሬዎች በላይ የሚያምንበትን ሲፅፍ ኖሯል። የህዝብ አለኝታ በሆኑ ምሁራንና የህዝብ አንደበት በሆኑ የነፃው ፕሬስ ውጤቶች ላይ ያለአንዳች ገደብ ተሳልቆባቸዋል። በሥልጣንና በካድሬነት ሥራ ዘመኑ ከ”ይበልታ” በስተቀር ማንም በክፉ ዓይን ያየው የመንግሥት ሹም አልነበረም። እርሱ በመጽሐፉ ውስጥ ባይጠቅሰውም በአንድ ወቅት ”የፕሬስ ሕግን በመተላለፍ” ተብሎ ክስ ተመስርቶበት ከእኛ ከነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች ጋር ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ሳጥን ውስጥ ቆሞ ተመልክቼዋለሁ። በእርሱም ቢሆን ምንም የደረሰበት ቅጣት አልነበረም። ቀድሞውኑም ”እፎይታም ይከሰሳል” የሚል ድራማ በእኛ ላይ ለመሥራት ነበርና።

 

”ኢትዮጵያ ውስጥ እያለሁ በነፃ ኅሊና የመፃፍ ወኔ አልነበረኝም” ብሎናል ተስፋዬ አባ ደፋሩ በሬድዮ ምልልሱ። በመጀመሪያ ደረጃ ተስፋዬ ወኔ ያለው ሰው አይደለም። አስፈላጊ ከሆነ ለወደፊቱ የምንነቃቅሳቸው እውነታዎች ሞልተዋል።

 

በሌላ በኩል፦ ትልቁና እውነተኛው ጀግንነት (የወኔ መፈተኛ) የሚገለፀው በነፃነት ነሺዎች መሀከል በመሆን (የግንባር ሥጋ ሆነው) በነፃ ሳቢና ያዩትንና የሰሙትን ግፍና ተግባር ማጋለጥ፤ የህዝብን ነፃ ስሜት ማንጸባረቅ፤ ለዚህም ሲባል ማንኛውንም ዋጋ መክፈልና ቆራጥ መሆን መቻል ነው እንጂ ፕሪቶሪያ ተቀምጦ ስለ አዲስ አበባ መፃፍ የምን የኅሊና ነፃነት፤ የምን ወኔ ይጠይቃል? ከተቻለ ጫት፤ ካልተቻለም ጥሩ አረቄ መቼ አነሰ?

 

ማስታወሻዎቹን ለማቀነባበበርና መጽሐፍ አድርጎ ለማውጣት ስምንት ወሮችን እንደተጠቀመ የተናገረው ይኽ ሰው ”መጽሐፉን ፅፌ ስጨርስ ነፃ ሆንኩኝ!” አለ። ”እንኳን ደስ አለህ! እንኳንም ለነፃ መሬት በቃህ!” ከማለት ወዲያ እንዲህ ያለውን ግብዝነት ስለምን ይከራከሩታል?

 

”... የህወሓት አባልና ካድሬ ሆኜ ከአሥር ዓመታት በላይ እንደመሥራቴ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካና የህወሓት / ኢህአዲግ ጉዳይ በቀጥታ ይመለከተኛል።” (ገፅ 6) ሲል በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ካድሬነቱን የሚያውጀው ታጋይ ተስፋዬ፤ በዚሁ መግቢያ ጽሑፉ በገፅ 7 (ሰባት) ላይ ደግሞ፦

 

”... በጋዜጠኝነት ሙያ ከኢህአዲግ ጋር በሠራሁበት ወቅት ያወቅኋቸውን ሚስጥሮች ሁሉ ግን እዚህ አላካተትኩም።” ይለናል። ”ለምን?” ቢሉ የጋዜጠኝነትን ሥነ ምግባር ለመጠበቅ። ”ለመሆኑ ሰውዬው ታጋይ ካድሬ ወይም የፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ሠራተኛ ነበር ወይስ ጋዜጠኛ?” የሚለውን ጥያቄ እናቆየውና እርሱ ”ሚስጥሮች” ብሎ ገለባ ሊያለብሳቸው ስላሰበው ነገር አንድ እንበል።

 

በመጀመሪያ ደረጃ ተስፋዬ በመጽሐፉ ውስጥ የጠቀሳቸው የኢህአዲግ ባለንብረቶች ጉዳይ ለእኔና እኔን ለመሰሉ ኢትዮጵያውያን አዲስ አይደሉም። ያላየና ያልሰማ ቢደነቅበትም አይፈረድበትም።

 

አብዛኞቹ ጉዳዮች በአንዱ ወይንም በሌላው መንገድ የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ አባላት በይፋ ሲፅፉበትና በሹክሹክታም ሲሳለቁበት የቆዩት የአደባባይ ሚስጥሮች ናቸው። በርካታ የነፃው ፕሬስ አባላትም እነዚያን የወያኔ እርኩስ ተግባራትና የሹማምንት ቅሌት በማጋለጣቸው ሲታሰሩ፣ ሲገረፉ፣ ሲገደሉ፣ በገንዘብ ሲቀጡ፣ ሲሰደዱ ... ”አበጀህ” ብለው የኢህአዲግን ”መንግሥት” ሲያንቆለጳጵሱት ከነበሩት ካድሬዎች መሐከል አንዱ ተስፋዬ ገብረአብ ነው። በየትራፊኩ መብራት ላይ መኪናውን አቁሞ አንገቱን በመስታወት አውጥቶ የሚዝትብን ”ወያኔም” አልነበረምን?

 

በሌላ በኩል ተስፋዬ ሚስጥር ሊጠብቅለት አሳሩን የሚያየው ሥርዓት ከቶውንም ከህዝብ የተደበቀ ሚስጥር ኖሮት አያውቅም። ”ሚስጥሩ ነው” ቢባል እንኳን የዘረፋ፣ የግድያ፣ የአፈና፣ የማሰቃያ፣ የውንብድና፣ የውስልትና ... ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ወንጀሎች ደግሞ በሀገርና በህዝብ ላይ የተፈፀሙ መሆናቸው እየታወቀ የተስፋዬ ገብረአብ የጋዜጠኝነት ሥነምግባር ሊሸፋፍናቸው ይንደፋደፋል። ይኽ ደግሞ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ሳይሆን ”የታጋይነት ሥነ ምግባር” ነው መባል የሚኖርበት፤ ቢባልም የሚያምርበት።

 

ተስፋዬ በእርግጥ ጋዜጠኛ የመሆን ሕልም ነበረው። ወደ ጋዜጠኝነት የሚወስደውን መንገድም መጓዝ ጀምሯል። ሆኖም ግን ካድሬነት ከመንገድ ላይ ጠልፎት መጀመሪያ ሐረር ወደሚገኘው የደርግ ወታደራዊ ፖለቲካ ትምህርት ቤት ውስጥ ወርውሮ ጣለው። ከዚያም ከደብረታቦር አሽቀንጥሮ ተከዜ ሸለቆ ውስጥ ወተፈውና ጋዜጠኝነትን እንደተመኘው ቀረ።

 

የኢህአዲግ አገዛዝ የመጀመሪያውን የፕሬስ ሕግ ሲያወጣ ከደነገጋቸው አንቀፆች መሐከል አንዱ ”ማንኛውም የፕሬስ ውጤት የዋና አዘጋጁን እና የምክትል ዋና አዘጋጁን ስም የመፃፍ ግዴታ አለበት” (አንቀጹ ቃል በቃል አልተገለፀም) የሚል ነው። ከዚህም አልፎ የአንድ የፕሬስ ውጤት አዘጋጅና ምክትል ዋና አዘጋጅ ከሚኖሩበት ቀበሌ ሠላማዊ ዜጋ ስለመሆናቸው የሚገልጽ ደብዳቤ አፅፈው (ከቀበሌ መታወቂያ በተጨማሪ) በማስታወቂያ ሚኒስቴር በፕሬስ ሥራ ፈቃድ ምዝገባና ቁጥጥር መምሪያ ፋይል የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

 

ይኽ ”ለሁሉም እኩል ይሠራል” የተባለው ሕግ ባለበት ወይም በነበረበት ሁኔታ ውስጥ ነው ተስፋዬ ገብረአብ የእፎይታ መጽሔትና ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሠራ ከነምክትል አዘጋጁ በብዕር ሥም ሲጠቀም ማንም ጠይቆት የማያውቀው።

 

ተስፋዬ ገብረአብ የዋና አዘጋጅነት ስሙ ”ዋለልኝ ብርሃነ” (ለዋለልኝ መኮንንና ለብርሃነ መስቀል ረዳ መታሰቢያ እንዲሆን የተዘየደ ይመስላል) ሲሆን፤ ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበረው ሻለቃ መኩሪያ መካሻ ደግሞ ”ሡልጣን አባዋሪ” በሚል ሥም ይጠቀም ነበር።

 

የህወሓትን ክፍፍል ተከትሎ የበረከት ስምዖን መብረቅ ወርዶባቸው እፎይታም ተዘግቶ ተስፋዬም በድንጋጤ እስከ ፕሪቶሪያ እስከፈረጠጠበት ጊዜ ድረስ እንዲህ ዓይነት የውንብድና ሥራ ሲሰራ እንደነበር እናውቃለን።

 

ይኼ ሰው ነው እንግዲህ ”ጋዜጠኛ ነኝ” ብሎ የጋዜጠኝነትን ሥነምግባር ለመጠበቅ በሥራ አጋጣሚ ያወቃቸውን የኢህአዲግ ባለሥልጣናት የሚስጥር ፍርፋሪ ስለመደበቁ የሚነግረን።

 

ከያሬድ ጥበቡ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ”እኔ የአደአ ጥቁር አፈር ነኝ” ያለው ተስፋዬ ገብረአብ ጋዜጠኛ ሳይሆን የህወሓት / ኢህአዲግ ፕሮፓጋንዳ ታጋይ ካድሬ ነው። የሚያምርበትም ቃጭል ይኼኛው ነው።

 

ደቡብ አፍሪካ ገብቶ ንግድ ከጀመረ በኋላ የጋዜጠኝነቱን አክሊል ደፍቶም ቢሆን ለወደፊቱ ይሠራበት እንደሁ እንጂ ላለፈው ማንነቱ መግለጫ ሊሆን ከቶውንም አይችልም።

 

ከዚህም በመነሳት ነው ”የጋዜጠኛው ማስታወሻ” የተባለው መጽሐፉ እንደገና የሥም ዳቦ ሊቆረስለት ይገባል እምለው። እኔ በበኩሌ ”የታጋዩ ማስታወሻ” ወይም ”የካድሬው ማስታወሻ” ተብሎ ይሰየም ዘንድ ምኞቴ ነው። ተስማሚውን ለምርጫ አቅርቤአለሁ።


 

ከኢትዮጵያ ዛሬ ይህ ጽሑፍ በሰሜን አሜሪካ ቺካጎ ውስጥ በሚታተመው ”ናፍቆት ኢትዮጵያ” የተሰኘ መጽሔት ላይ ያያ አባቦር የተሰኙ ፀሐፊ ”የአደአው ጥቁር አፈር ጋዜጠኛ ወይስ የፓርቲ ካድሬ?” በሚል ርዕስ ጽፈውት የታተመ ነው። የያያ አባቦርን ይህንን ጽሑፍ ተከትሎ የ”ጦማር” ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ በፈቃዱ ሞረዳ ”እኔም ማስታወሻ አለኝ” በሚል ርዕስ በ”ናፍቆት ኢትዮጵያ” መጽሔት ላይ የበኩሉን ብሏል። ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ደግሞ በኢትዮ ሚዲያ ፎረም ላይ በቅርቡ ”የግንቦት ማስታወሻ” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አስነብቧል። ሦስቱም ፀሐፊዎች ያስነበቧቸው ጽሑፎቻቸው ተያያዥነት ያላቸው ሆነው ስላገኘናቸው የሦስቱንም ፀሐፊዎች ዕይታና አስተያየት አቅርበናቸዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ