Prof. Tesfatsion  Medhanie ፕ/ር ተስፋጽዮን መድኅኔ"የኢትዮጵያንና የኤርትራን ወንድማማች ህዝቦች ሊቀራርብ የሚችለው የኮንፌዴሬሽን ሥርዓት ነው" ፕ/ር ተስፋጽዮን መድኅኔ

ባለፈው ግንቦት 7 ቀን 2001 ዓ.ም. በካሊፎርኒያ ሳን ዮሴ በተካሄደው የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን የወዳጅነት ኮንፈረንስ ላይ ፕ/ር ተስፋጽዮን መድኅኔ እና ፕ/ር ዳንኤል ክንዴ ተናጋሪዎች ነበሩ። ፕ/ር ተስፋጽዮን ”ኢትዮጵያና ኤርትራ ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ወንድማማች ህዝቦች ሊቀራርብ የሚችለው የኮንፌዴሬሽን ሥርዓት ነው ይላሉ። ፕ/ር ዳንኤል ክንዴ ደግሞ በፌዴሬሽን ነው ሲሉ በኮንፈረንሱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል። ለዛሬ የፕ/ር ተስፋጽዮንን ሙሉ ንግግርና ጽሑፍ እንደሚከተለው ቀርቧል።

 

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከየት ወዴት?

 

ፕሮፌሠር ተስፋጽዮን መድኅኔ (ብረመን ዩኒቨርሲቲ፣ ጀርመን)

 

የተከበራችሁ የስብሰባው ተካፋዮች!

 

አስቀድሜ ይህንን የውይይት ስብሰባ ላዘጋጁት እህቶችና ወንድሞች ጥልቅ ምስጋናየን ማቅርብ እወዳለሁ። ይህን በመሰለ የሰሜን አሜሪካ ስብሰባ ስለኤርትራና ኢትዮጵያ ጉዳይ ለመወያየት ስሳተፍ አሁን የመጀመሪያ ጊዜየ ነው። ይህ ውይይት በጣም አስፈላጊ በመሆኑ በመሀሉ ተገኝቼ ሃሳብ በማቅረብ እንድሳተፍ ለተሰጠኝ ዕድል ከልብ አመሰግናለሁ።

 

ከዚሁ ጋር በማያያዝ ሌላው ተናጋሪ ፕሮፈሠር ዳንኤል ክንዴ ኢትዮጵያንና ኤርትራን እንዲያውም የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራትን በተመለከተ ብዙ ምሁራዊ ሥራዎች ያበረከተ ሊቅ በመሆኑ መድረኩን ከርሱ ጋር መጋራቴን ትልቅ ዕድል አድርጌ የምቆጥረው መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ።

 

 

ዛሬ የምንወያይበት አርዕስት በአፍሪቃ ቀንድ ሠላም የሚሰፍንበትን ጉዳይ የሚመለከት ሲሆን፣ በተጨባጭ ግን በኢትዮጵያና ኤርትራ መጪ ዝምድና ላይ ያተኮረ ነው። የኢትዮጵያና ኤርትራ ዝምድና ምን ይሁን የሚል አርዕስት አዲስ ባይሆንም በአዲስ መንፈስ መታየት ያለበት ነው።

 

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ እኔም የደመቀ ባይሆን መጠነኛ እንዲያውም ትሁት የሆነ ታሪክ አለኝና ያንን ታሪክ ባጭሩ በማስታወስ ልጀምር። ለኤርትራ ነፃነት የትጥቅ ትግል ይካሄድ በነበረበት ጊዜ፣ ማለት በ80ዎቹ፣ የኤርትራ ጉዳይ በፌዴሬሽን መልክ እንዲፈታ በጽሑፍ አስስተያየቴን ገልጨ ነበር፣ ነገሩ እኔ በተመኘሁት መንገድ አልተሳካም። ሂዶ ሂዶም በ1991 የደርግ ሥርዓት ወደቀና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ሉዓላዊት ሀገር ሆነች። በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ወይም ዝምድና እንዴት ይሁን የሚል ጥያቄ አዲስ ዕይታ የሚጠይቅ ሆነ። ኤርትራ በሕግ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ሁኔታ የቀረበ የመፍትሄ ሃሳብ፣ ኤርትራ ተለይታ ሉዓላዊት ሀገር ከሆነች በኋላ ከተከሰተ ዕውነታ ጋር ሊጣጣም አልቻለም። ስለዚህ በዚህ አዲስ ሁኔታ ሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ሊያቀራርብ የሚችል የኮንፌዴሬሽን ሥርዓት ነው የሚለውን አቋም ወስጄ በተለያዩ መድረኮች፣ በጽሑፍ መልክም አራመድኩ።

 

ባለፉት 18 ዓመታት - ማለትም ከ1991 አንስቶ፣ በሀገሮቻችን ወይም በአጠቃላይ በአፍሪቃ ቀንድ የተከሰቱት ሁኔታዎች፣ የ1998 - 2000 ጦርነትን እና አሁን ያለውን አደገኛ ሁኔታ ጨምሮ በወስድኩት የኮንፌዴሬሽን አቋም በመሰረቱ እንድጸና አደፋፍሮኛል። ይህ ሲባል ግን አቋሜን ባንዳንድ ረገድ እንዳበለጽገው ወይም እንዳሳድገው የተከሰቱት ሁኔታዎች የገፋፉኝ መሆናቸውን መግለጽ እወዳለሁ።

 

ምንም እንኳ ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆነች ሉዓላዊት ሀገር ብትሆንም፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት በይዘቱም በመልኩም ገና ፈጽሞ አልተደመደመም ማለት ይቻላል። እንድያውም የሁለቱን ሀገሮች ዝምድና የሚመለከት ጥያቄ አንገብጋቢ ወደ መሆን እየተቃረበ ነው ለማለት ሁኔታው ያስደፍራል።

 

ይህንን በመገንዝብ በሁለቱ ሀገሮች፣ ማለትም በኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ዝምድና ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ ደረጃ ለወደፊት የሚዘረጋ የኮንፌዴሬሽን ጉዳይ በተመለከተ ካንድ ዓመት በፊት አንዲት አነስ ያለች መጽሀፍ በማሳተም አስተያየቴን ገልጫለሁ።

 

አሁንም የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝምድና ወደየት? የሚለውን ጥያቄ የምመልሰው የኮንፌዴሬሽንን ሃሳብ በመንተራስ ነው። ካሁን በፊት የኮንፌዴሬሽን ሃሳብ ሳቀርብ ብዙም ባይባሉ ቁጥራቸው የማይናቅ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን የተቀበሉኝ ነበሩ፤ አንዳንድ ኢርትራውያን በልዩ ልዩ ምክንያት ያልተቀበሉት ነበሩ፣ አንዳንድ የማከብራቸው ኢትዮጵያውያን ምሁራን ደግም፣ ወንድሜን ፕሮፈሠር ዳንኤል ክንዴን ጨምሮ፣ ኤርትራና ኢትዮጵያ በሽግግር ጊዜ አልፈው በፌዴሬሽን ይተሳሰሩ የሚል ሃሳብ አራመዱ። ይህ አቋም ከበጎ መንፈሥ የተነሳ፣ ማለት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ በጎ ያሰበ ለመሆኑ ጥርጥር ባይኖረኝም፣ በዚህ ጊዜ ካለው ሁኔታ፣ ከቅርብ ታሪካችን፣ ካለው ህዝባዊ ስነልቦናና ስሜት ጋር ሙሉ ለሙሉ የሚጣጣም አይደለም፣ የሚል አቋም አለኝ። ዛሬ የማቀርበው ለውይይት ማስጀመሪያ የሚሆን አጭር ንግግር በዚሁ ነጥብ ላይ ያተኮረ ነው።

 

የሁለቱ ሀገሮቻችን ግንኙነት ምን ይሁን ብዬ ከገለጽኩ በኋላ፣ የሚመረጠው ግንኙነት በተግባር እንዲረጋገጥ ወይም ወደተፈለገው ግብ ለመድረስ መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ ወይ? እነዚያ ነገሮች እንዲሟሉስ ከእኛ የሚጠበቀው ምንና ምን ነው? የሚሉትንና ከእነርሱ ጋር የተያያዙትን ጥያቄዎች በመዳሰስ ለውይይት መነሾ የሚሆኑ ነጥቦችን መግለጽ እወዳለሁ። አስቀድሜ ግን ይህንን ጉዳይ የሚመለከቱ አንዳንድ መሠረታዊ ጽንሰ-ሃሳቦች መግለጽ ይኖርብኛል።

 

 

የውይይታችን ጉዳይን የሚመለከቱ አንዳንድ ጽንሰ-ሃሳቦች አሉ። ዋና ዋናዎቹ ፌዴራሊዝም፣ ፌዴሬሽን እና ኮንፌዴሬሽን ናቸው። እነዚህ ሦስት ጽንሰ-ሃሳቦች ምን ማለት እንደሆኑና እንዴት እንደሚለያዩ ማወቅ ያስፈልጋል። ስለዚህም አጠር አድርጌ ላብራራቸው እሞክራለሁ።

 

ሀ) አብዛኛውን ጊዜ፣ ወይም ሁልጊዜም ማለት ይቻላል ፈዴራሊዝም (ፌዴራላዊነት) የሚለውን ቃል እንደ ፌዴሬሽን ወይም የፌዴሬሽን ንድፈ-ሃሳብ (ቴዎሪ) አድርገን ነው የምንረዳው፤ እኔ ትክክል እምለው አገላለጽ ግን ፈዴራሊዝም ወይም ፌዴራላዊነት የኮንፌዴሬሽንንና የፌዴሬሽን ዝምድናዎችን በጠቅላላ የሚመለከት ጽንሰ-ሃሳብ ነው የሚለውን ነው።

 

ባጭሩ ፈዴራሊዝም ወይም ፌዴራላዊነት ማለት በራስ-ገዝነትና በጋራ አገዛዝነት (Self-rule & Shared-rule) ድምር የቆመ ሥርዓት ወይም ሁኔታ ማለት ነው። እንዲህ የመሰለ ሥርዓት ወይም ሁኔታ የተለያዩ

 

ሀገሮችን ወይም ደግሞ በአንድ ሀገር ውስጥ በአንዳንድ ረገድ የሚለያዩ ክፍሎችን ያገናኛል ወይም ያስተሳሥራል።

 

ለምሳሌ እዚህ ሀገር ፈዴራሊዝም ስንል በሃሳባችን የሚመጡት የፈዴራሉ መንግሥት ፍርድ ቤቶች እና ኮንግሬስ ነው። ፈዴራሊዝም ወይም ፌዴራላዊነት ሲባል በሃሳባችን አስቀድሞ የሚመጣ ነገር ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑት አውቶኖሚ ያላቸው አካላትን ያስተሣሰሩ መዋቅሮች ናቸው። ይህ ግን ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም። ፈዴራሊዝም ሲባል መዋቅሮች ብቻ አይደለም፤ ፈዴራሊዝም ሲባል ሂደት፣ ማለትም የግንኙነት ወይም የዝምድና ሂደት ማለትም ነው።

 

የዚህ ሂደት ዋነኛው መሠረት በተዛመዱት አካላት (ሀገሮች ወይም ክፍሎች) መካከል ያለው የመቀራረብና የጋራ መንፈስ ነው። ይህ መንፈስ ነው አካሎቹ በተለያዩ ጉዳዮችና ጥያቄዎች ላይ እየተወያዩ እየተስማሙና አስታራቂ መንገዶችን እያገኙ ዝምድናቸውን እንዲጠብቁና እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው። ይህ መንፈስ ነው ፈዴራሊዝምን ከሚከሰተው የሁኔታ ለውጥ ጋር እንዲስተካከልና እንዲጣጣም የሚያስችለው፤ አዲስ ነገር ወይም ለውጥ ሲመዘገብ የፈዴራሊዝም ይዘት ያለችግር ይስተካከላል።

 

ፈዴራሊዝም ወይም ፌዴራላዊነት በራስ-ገዝነትና በጋራ አገዛዝነት የቆመ ሁኔታን የሚመለከት ጠቅላላ ጽንሰ-ሃሳብ ነው ብለናል። ይህ እንግዲህ ፈዴራሊዝም የተለያዩ ዓይነቶች (መልኮች) እንዳሉት ይጠቁማል። በእርግጥ የተለያዩ የፈዴራሊዝም ዓይነቶች አሉ፤ ዋናዎቹ ግን ሁለት ናቸው፤ እነርሱም ኮንፌዴሬሽን እና ፌዴሬሽን ይባላሉ።

 

(ለ) ኮንፌዴሬሽን ማለት ሁለት ወይም በቁጥር ከዚያ በላይ የሆኑ ሀገሮች አብዛኛው ሉዓላዊነታቸውን ጠብቀው ለተወሰኑ ጉዳዮች በሕግ መሠረት ተሣስረው የጋራ መንግሥት የሚያቆሙበት ዝምድና ነው። በቀላል አነጋገር ኮንፌዴሬሽን ሉዓላዊ ሀገሮች ሉዓላዊነታቸውን ጠብቀው የሚያበጁት የአገዛዝ ትብብር ወይም የጋራ መንግሥት ነው።

 

አንድ ነጥብ እዚህ ላይ ማስመር እወዳለሁ፤ ኮንፌዴሬሽን ሲባል በይዘቱ ሁሉ አንድ አይደለም፤ ኮንፈዴራላዊ ግንኙነቱ ምን ያህል የጠበቀ ወይም የላላ መሆኑን የሚወስነው የተዛመዱት ሀገሮች ታሪክና ሁኔታ ነው።

 

አንዳንዱ ኮንፌዴሬሽን ላላ ያለ ሲሆን አንዳንዱ ደግሞ በብዙ ዘርፎች ትሥሥር ያለው የጠበቀ ኅብረት ይሆናል። ለምሳሌ በአንዳንዱ ኮንፌዴሬሽን ግንኙነቱ በተወሰኑ መስኮች ብቻ፤ ለምሳሌ በንግድና በመከላከያ ጉዳዮች፣ ሲሆን ባንዳንዱ ግን በብዙ እንዲያውም ሁለገብ ለመሆን የተቃረበ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የጋራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ የጋራ የመከላከያ ፖሊሲ፣ የጋራ የፀጥታ ፖሊሲ(የጋራ ሠራዊት) የጋራ ፍርድ ቤት፣ የጋራ ገንዘብ እንዲሁም የጋራ ተቋማት፤ ለምሳሌ የጋራ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ወዘተ ሊኖረው ይችላል። የአውሮፓ ኅብረት ይህንን የሚመስል የጠበቀ ኅብረት ነው። ቆየት ብዬ እንደምገልጸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ኮንፌዴሬሽን በብዙ ዘርፎች ዝምድና የቆመ፣ ጠበቅ ያለ ኅበረት ሊሆን የሚችል ነው።

 

በታሪክ ደጋግሞ እንደታየው በአንዳንድ ሁኔታዎች የኮንፌዴሬሽን ሂደት እየበሰለ ሄዶ ወደፌዴሬሽን ሊያድግ ይችላል። በዚህ በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በስዊዘርላንድ መዠመሪያ ኮንፌዴሬሽን ነው የነበረው፤ በጊዜ ኅብረቱ እየሰፋና እየጠነከረ መጥቶ ወደ ፌዴሬሽን አደገ።

 

በአሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም ውጤታማ የሆነ ኮንፌዴሬሽን የአውሮፓ ኅብረት ነው። ይህ ትብብር የአውሮፓ ማኅበረሰብ ተብሎ ሲጀመር ዋና ዓላማው ንግድና ኢክኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን ነበር። በሂደት ግን ዓላማው እያደገ መጥቶ አሁን ፀጥታን ሁሉአቀፍ ፖለቲካንና ሰብአዊ መብቶችን የጨመረ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚና ፍርድ ቤት እንዲሁም ብዙ መዋቅሮች ያሉት የጠበቀ ኅብረት ሆነዋል። እንዲያውም ኅብረቱ አሁን ከኮንፌዴሬሽን ወደ ፌዴሬሽን እያደገ ነው።

 

 

የኮንፌዴሬሽን ዋና መለዮዎች ምንድን ናቸው?

 

ጀራልድ ቦድዋን የተባሉ ካናዳዊ ፕሮፌሰር፣ ቬኒስ ኮሚሽን ለሚባል ዲሞክራሲ በህጋዊ ሥርዓት በኩል እንዲዳብር የሚያጠና አካል በ1994 ባደረገው ስብሰባ ካቀረቡት ጽሑፍ የተውጣጡ ዋና ዋና መለያዎች እጠቅሳለሁ።

 

1. የኮንፌዴሬሽን ሕጋዊ መሠረት በአገሮቹ መሃከል የሚፈጸመው ውል ወይም ቃል ኪዳን ነው። በሌላ አነጋገር ኮንፌዴሬሽን በዓለም አቀፋዊ ሕግ የተመሠረተ ትሥሥር ነው ማለት ነው።

 

2. በትልልቅ ወይም መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰዱት ውሳኔዎች በሙሉ አባል ሀገሮች የተደገፉ መሆን አለባቸው። በአነስተኛ ጉዳዮች ግን በአብላጫ ድምፅ ውሳኔዎች ያልፋሉ።

 

3. ማዕከላዊ ወይም የኅብረቱ መንግሥት የሚወስዳቸው ውሳኔዎች በአባል ሀገሮች ውስጥ በተግባር የሚውሉት በራሱ በመሃከለኛ መንግሥት ሳይሆን በየአባል አገሩ መንግሥት ነው።

 

4. ማዕከላዊ መንግሥት በአባል አገሮቹ ህዝቦች ላይ ቀጥተኛ ሥልጣን የለውም፤ ሕዝቦቹን የሚነካ እርምጃ የሚወስደው በሚመለከታቸው አባል ሀገሮች መንግሥታት በኩል ነው።

 

5. ይህ ሲባል ግን ማዕከላዊ ወይም ኮንፈዴራላዊው መንግሥት እንደማንኛውም ዓለማቀፋዊ ድርጅት የራሱ እርምጃ ለመውሰድ ሥልጣን ጨርሶ የሌለው ሃሳብ በማቅረብ ብቻ የተወሰነ አካል ነው ማለት አይደለም። በአንዳንድ ጉዳዮች በራሱ ኃላፊነት አንዳንድ እርምጃዎች ሊወስድ ይችላል። ለምሳሌ አባል አገሮቹ የኮንፈዴራሉ መንግሥት ሕጎችን ወይም መመሪያዎችን ተግባር ላይ ሲያውሉ ማዕከላዊ መንግሥቱ የቁጥጥር ሚና ይኖረዋል። በተጨማሪም ማዕከላዊ መንግሥት ኮንፈዴራላዊ ኅብረቱን የመጠበቅ ኃላፊነት አለው፤ ለኅብረቱ አደጋ በተነሣ ጊዜ ማዕከላዊ መንግሥት ይህንን አደጋ ለማክሸፍ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፤ በሌላ አነጋገር ኅብረቱ ራሱን የመከላከል መብት አለው ማለት ነው።

 

እንዲሁም የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ የኅብረቱ መንግሥት ሥልጣን አለው፤ የኅብረቱ ተቋማት ከሌሎች ጋር ወይም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አባል ሀገሮችን የሚገዛ ውል ሊገቡ ወይም ውሳኔ ሊወስዱ ይችላሉ።

 

6. ማዕከላዊ መንግሥት ስራዎቹን ለማካሄድ ገንዘብ የሚያገኘው ከአባል አገሮቹ በተውጣጣ ነው። የጋራ መከላከያ ካለም ወታደሮቹ ከአባል አገሮቹ የተውጣጡ ናቸው።

 

7. አብዛኛውን ጊዜ ኮንፈዴራሲዮኑን በሚያቆመው ውል ወይም ስምምነት አባል አገሮቹ በመሃከላቸው አለመግባባት ወይም ማንኛውም ችግር ቢመጣ እርስ በርሳቸው እንዳይዋጉ ቃል ይገባሉ፣ እንዲህም ይደነገጋል። ችግሩ ወይም አለመግባባቱ በሽምግልናና በፍርድ ሂደት እንዲፈታ ይስማማሉ።

 

ኮንፌዴሬሽን የሚቋቋመው በማንኛውም ሁኔታ አይደለም፤ የኮንፌዴሬሽን ኅብረት እንዲመሰረት መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ። መሠረታዊ የሆኑትን ለመጥቀስ፦

 

ሀ) አገሮቹ ወይም ህዝቦቹ በተለያየ ረገድ የሚመሳሰሉና የሚጣጣሙ መሆን አለባቸው፤ በተለይ በፖለቲካ እምነቶቻቸውና እሴቶቻቸው የሚጣጣሙ መሆን አለባቸው። ይህ መጣጣም ከሌለ ኮንፌዴሬሽኑ ሊቀና አይችልም።

 

ይህ ሲባል ግን አሠራራቸውና ሥርዓቶቻቸው ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት መሆን አለባቸው ማለት አይደለም። ሉዓላዊ በመሆናቸው: አባል አገሮቹ በሁሉም ረገድ አንድ ሊሆኑ አይችሉም፤ መጣጣም አለባቸው ብቻ ነው የሚባለው ያለው።

 

ለ) የኮንፌዴሬሽን ዝምድና በዓለም አቀፋዊ ውል ብቻ ሳይሆን በመተማመንም ላይ የተመሠረተ ነው። እንዲያውም የፈዴራሲዮን መሠረት መተማመን ነው። ፌዴራላዊነት (ፈዴራሊዝም) የሚለው ቃል ራሱ “Fidere” ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ነው። Fidere ማለት መተማመን ማለት ነው። መተማመን ደግሞ የሚመነጨው እኛ: ማለት በኮንፌዴሬሽን የተወሃድነው ሀገሮች: ተመሳሳይ ነን ወይም በብዙ ረገድ እንገናኛለን፤ ብዙ የጋራ ነገሮች አሉን፤ ወ.ዘ.ተ. ከሚሉ አመለካከቶች ነው። መተማመኑ መሠረታዊ አስፈላጊነት አለው። መተማመኑ ከቀረ: እንዲያውም ከተዳከመ ብቻ እንኳን: ኮንፈዴራላዊ ኅብረቱ ችግር ላይ ይወድቃል።

 

ኮንፌዴሬሽኑን የሚያካሂዱ ወይም የሚያስተዳድሩ አካላት አሉ፤ አባል ሀገሮቹ የሚወከሉበት አንድ ፓርላማ መሳይ ተቋም፣ መሪዎቹ ወይም ከየመንግሥታቱ ባለሥልጣኖች የሚወከሉበት ሸንጎ ወይም ምክር ቤት፣ ሕግ የሚተረጉምና በአከራካሪ ጉዳዮች ብይን የሚሰጥ ተቋም፣ እንደዚሁም ሥራ አስፈጻሚ ወይም ኤክስኩቲቭ መሳይ አካል ይኖራሉ። የአውሮፓ፤ ሕብረት ለምሳሌ ፓርላማ፣ የመሪዎች ሸንጎ ወይም ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤት፣ እና ሕግና ፖሊሲ አስፈፃሚ የሆነ ኮሚሽን አሉት።

 

ኮንፌዴሬሽን ምን እንደሆነ ባጭሩ አየን፤ ፌዴሬሽንስ ምንድነው? ከኮንፌዴሬሽን በምን ይለያል?

 

 

ፌዴሬሽን ማለት ሁለት ወይም በቁጥር ከዚያ በላይ የሆኑ ህዝቦች ወይም አካላት በሕገ መንግሥት መሠረት አንድ ሀገር በመሆን ተዋሕደው የሚኖሩበት፣ የራስ ገዝ መንግሥትና ማዕከላዊ መንግሥት ያሉት ሥርዓት ነው። በፌዴሬሽን የሚተሳሰሩት አካላት (ክፍለ ሀገሮች) የየራሳቸው ግዛት፣ ህዝብ፣ ፖለቲካዊ ድርጅት ወይም መንግሥታዊ ተቋማት አሏቸው፤ ሉዓላዊነት ግን የላቸውም። ሁሉም ተዛምደው የሚያቆሙት አንድ ሀገር ነው፤ ሉዓላዊው ደግሞ ያ የሚያቆሙት ሀገር ብቻ ነው።

 

የፌዴሬሽን መሠረታዊ መለዮዎች ምንድናቸው?

 

አሁንም ጀራልድ ቦድዋን ከአቀረቡት ጽሑፍ የተውጣጡ ዋና መለዮዎችን እገልፃለሁ፤

 

1. በፌዴሬሽን ሁለት ዓይነት መንግሥታት ይኖራሉ፤ አንዱ የማዕከላዊው ወይም የፈዴራሉ መንሥት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የክፍለ ሀገሩ መንግሥት ነው። እነዚህ ሁለት ዓይነት መንግሥታት ለህዝቡ በቀጥታ የሚመለከቱ ድርጊቶች ይፈጽማሉ፤ ማለት ሕጎች ያረቃሉ፣ ያውጃሉ፣ ያስፈጽማሉ፣ ተርጉመው ይፈርዳሉ፣ ሌሎች እርምጃዎችም ይወስዳሉ።

 

2. የማዕከላዊው (የፈዴራላዊው) መንግሥት ባለሥልጣናት የሚመረጡት በቀጥታ በመላው የአገሩ ህዝብ ነው። ይህ መንግሥት ህዝቡን በቀጥታ የሚመለከትና የሚገዛ ሕግ ያወጣል፤ ቀረጥም ያስከፍላል።

 

3. የክፍለ ሀገሩ መንግሥትም ወይም ባለስልጣናትም በክፍለ ሀገሩ ህዝብ ይመረጣሉ፤ ይህንን ህዝብ ብቻ በቀጥታ የሚመለከትና የሚገዛ ሕግ ያወጣሉ፤ ቀረጥ ያስከፍላሉ።

 

4. በፈዴራላዊ ሥርዓት፣ ማለት በማዕከላዊ መንግሥትና በክፍለ ሀገሩ መንግሥታት የሥልጣንና የገንዘብ ምንጭ መከፋፈል አለ። ከዚህ ጋር በተያያዘ አለመግባባት ወይም ክርክር ሊነሣ ይችላል፤ ይህንና ሌላ አለመግባባትን በሕግ መሠረት የሚፈታ ነፃ የሆነ የፍርድ አካል ይኖራል።

 

5. ከሁሉም በላይ መሠረታዊ የሆነ የፌዴሬሽን መለዮ እና ከኮንፌዴሬሽን የሚለየው የክፍለ ሀገሮች ዝምድና በብሔራዊ ሕገ መንግሥት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው። ክፍለ ሀገሮች የየራሳቸው ከአገሩ ሕገ-መንግሥት ጋር የማይጋጭ ሕግጋት አሏቸው። የሃገሩ፣ ማለት የፌዴሬሽኑ ጠቅላይ ሕገ-መንግሥት ግን አንድ ነው። የፌዴሬሽኑ ሕጋዊ መሠረትም ያ ሕገ-መንግሥት ነው።

 

የፌዴሬሽን ሥርዓት ከዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት ጋር በቅርብ የተዛመደ ነው። ፈዴራላዊ መንግሥቱ አምባገነናዊ ከሆነ ፌዴሬሽን በሚል ስያሜ የተተከለው ሥርዓት ሽፋን ብቻ ነው። የፌዴሬሽኑ መዋቅሮች እና ሥርዓቱ የዲሞክራሲ ዕድገት በማስጀመር ሚና ሊኖራቸው ይችላል። ፌዴሬሽን እውነተኛ የሚሆነው እና ትርጉም የሚኖረው ግን ዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት በሚያስተማምን መጠን ሲኖር ብቻ ነው። ስለዚህ ሕገ-መንግሥት መሠረታዊ የሆነ ሚና አለው። በፈዴራላዊ ሥርዓት ሕገ-መንግሥቱ በአንድ ሠነድ የተዘጋጀ እና የተጻፈ ሆኖ በቀላሉ የማይለወጥ ነው።

 

እውነተኛው ፌዴሬሽን አንዴ ከተቋቋመ በቀላሉ የሚፈርስ አይደለም፤ እንዲያውም አንድ ጸሐፊ እንደሚለው ከሆነ፣ ፈዴራላዊ ሥርዓት በነበረባት ሀገር ሁኔታው ተለውጦ ፌዴሬሽኑ ቀርቶ ክፍለ ሀገሮቹ ሙሉ በሙሉ ተቀላቅለው አሃዳዊ ሀገር የመሠረቱበት ጊዜ የለም።

 

 

ኮንፌዴሬሽንና ፌዴሬሽን ምን ማለት መሆናቸውን አየን፤ አሁን እንግዲህ በአሁኑ ጊዜ ኤርትራንና ኢትዮጵያን በተመለከተ በተግባር ሊውል የሚችለው፣ ስለዚህም የሚመረጠው የትኛው ነው? ወደሚለው ጥያቄ እንሂድ።

 

በመጀመሪያ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ። መተባበር በተለይም በአሁኑ ወቅት አለማችን በሙሉ በኢኮኖሚ በተሳሰረበት ጊዜ በየትኛውም አህጉር የሚፈለግ ነው፤ ይህንን የማይቀበሉ የሀገር መሪዎች ወይም የፖለቲካ ጠቢባን ቢኖሩ በጣም ጥቂት ናቸው።

 

የአፍሪቃ ቀንድ ሀገሮች በኮንፌዴሬሽን እንዲተሳሰሩ የሚረዱ ነገሮች አሉ፤ ስለአፍሪቃ ቀንድ የተመራመሩ እነ ዳንኤል ክንዴ፣ ንጉሴ አየለ፣ መስፍን አርአያ፣ ገላውዲዎስ አርአያ፣ አሰፋ ምህረቱ፣ ጳውሎስ ሚልኪያስ፣ ሲሳይ አሰፋ እና ሌሎች የአካባቢው ሙህራን ከአሳተሟቸው ጽሁፎች የተውጣጡ የሚከተሉትን ዋና ዋናዎቹን እጠቅሳለሁ።

 

1. የአፍሪቃ ቀንድ ሀገሮች በጅኦግራፊ አቀማመጣቸው ሆነ ባላቸው የተፈጥሮ ፀጋ የተዛመዱና እርስ በርሳቸው ሊረዳዱ የሚችሉና መረዳዳትም ያለባቸው ናቸው።

 

2. በአፍሪቃ ቀንድ ሀገሮች መሃከል ክሎኒያሊዝም የደነገገውና ያቆመው እንጂ የተፈጥሮ ድንበር እንደ ወንዞች ወይም ተራሮች፣ በአንዳንድ ቦታ በከፊል ካልሆነ በስተቀር የለም። እነዚህ ሀገሮች የባህል ይሁን የዘር ክልሎች አይደሉም።

 

3. እነዚህ ሀገሮች (ወይም ህዝቦቻቸው) በዘርና በባሕል የተሳሰሩ ናቸው፤ ባሕሎቻቸው እጅግ ተመሳሳይ ሆነው አብዛኛዎቹ በክርስትናና በእስልምና እምነት ወይም በኃይማኖትና በግብረ-ገብነት የዳበሩ ናቸው።

 

4. የእነዚህ ሀገሮች ህዝቦች እርስ በርሳቸው ይተዋወቃሉ፣ ይተዋወቃሉ ብቻ አይደለም፤ ይግባባሉም፤ ለብዙ ዘመናት አብረው ኖረዋልና።

 

እነዚህና ሌሎች ነገሮች በአፍሪቃ ቀንድ ሀገሮች ኮንፈዴራላዊ ዝምድና እንዲኖር ይረዳሉ።

 

በሌላው በኩል ደግሞ እንዲህ የመሰለውን መተሳሰር ለማበጀት አስቸጋሪ የሚያደርጉ ነገሮች አሉ። እንደገና ከላይ የጠቀስኳቸው ሙህራን ያበረከቷቸውን ጥናቶች በመመርኮዝ የሚከተሉትን እጠቅሳለሁ።

 

1. በቀጠና ደረጃ አገሮቹን ለማስትባበር ራዕይና ዝግጁነት ያለው መንግሥታዊ ሥልጣንና በቂ ኃይል የታጠቀ አካል የለም።

 

2. በአፍሪቃ ቀንድ ልሂቃን መሃከል ይህንን ራዕይ ለመቀበልና ለማራመድ እስከአሁን አጠቃላይ ስምምነት የለም።

 

3. ኮንፌዴሬሽን የሚጠቅመው ማንን ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ አለመግባባት አለ።

 

4. አንዳንዱ ሀገር ደግሞ፤ ለምሳሌ ኤርትራ፣ በሉዓላዊነቱ እምብዛም ቀናተኛ በመሆኑ ሉዓላዊነትን በሚነካ ትብብር ውስጥ ለመካፈል ይሰጋል። (የኤርትራን ህዝብ በተመለከተ ግን ስጋቱ እየቀነሰ መጥቷል)።

 

5. አንዳንዱ ሀገር (ለምሳሌ ሶማሊያ) መረጋጋት ገና የለውም፤ በአንዳንዱ ሀገር ደግሞ ያለው መንግሥት ሕዝባዊ ድጋፍ ወይም ተቀባይነት የለውም።

 

ከአፍሪቃ ቀንድ ሀገሮች ሁሉ አስቀድመው በፌዴራላዊነት ሊተሳሰሩ የሚችሉ ኢትዮጵያና ኤርትራ ናቸው። አስቀድሜ የጠቀስኳቸው የአፍሪቃ ቀንድ ሀገሮችን የሚያገናኙ ነገሮች ኤርትራንና ኢትዮጵያን በተመለከተ እጅግ በጎላ መጠን ይገኛሉ፤ ሁለቱ ሀገሮች በብዙ ረገድ ይዛመዳሉ፤ በታሪክ፣ በባሕል፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በጅኦግራፊ አቀማመጥ ወ.ዘ.ተ.። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ ሀገር ስለነበሩም በኢኮኖሚም ይሁን በኅብረተሰባዊ ደረጃ በጣም ተሳስረዋል። ተጋብተዋል፣ ተዋልደዋል።

 

ይህ ምንም ጥያቄ የለውም። በኔ አመለካከት (በመጽሐፌም እንደጠቀስኩት) ሁለቱ ሀገሮች በይፋ ቢፋቱም በተግባር በእውነት አልተለያዩም። ኢትዮጵያና ኤርትራ በመፋታታቸው የሁለቱ ሀገሮች ህዝቦች እየተጎዱ መሆናቸው ግልፅ ነው። ኢትዮጵያ በኤርትራ ወደቦች ስለማትገለገል በንግድ ረገድ ሁኔታዋ አስቸጋሪ ሆኗል፤ ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ይፋዊ የኢኮኖሚና ሌላ ግንኙነት ስለሌላት በኃይል ተጎድታለች፤ እንዲያውም፣ ሁኔታው ተባብሶ ኤርትራውያን ወጣቶች ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው።

 

እንግዲህ የሁለቱ ህዝቦች ሁኔታ መተሳሰርን የሚጠይቅ እያለ አገሮቹ መፋታት ብቻ ሳይሆን ጦርነትም ሲዋጉ እጅግ የምያሳፍር ቅራኔ ነው።

 

ስለዚህ ኢትዮጵያና ኤርትራ በፈዴራሊዝም (ፌዴራላዊነት) መተሳሰር አለባቸው። ዋናው ጥያቄ ምን ዓይነት ፌዴራላዊነት፣ ኮንፌዴሬሽን ወይስ ፌዴሬሽን የሚለው ነው።

 

 

በንግግሬ መክፈቻ እንደጠቀስኩት ሁለቱ ሀገሮች በሽግግር ወቅት አልፈው ፌዴሬሽን ማቋቋም አለባቸው የሚል አመለካከት ያላቸው ምሁራን አሉ፤ አስቀድሜ እንዳልኩት እኔ በዚህ አልስማማም፤ አመለካከቱና መንፈሱ በጎ መሆኑ ባምንም። ለምን?

 

በመዥመሪያ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ፤ ወንድሜ ፕሮፌሰር ዳንኤልና ራሴ የምናከብረው ከ126 ዓመታት በፊት ሕይወቱ ያለፈው አንድ ፈላስፋና የታሪክ ጠቢብ እንዳመለከተው “ታሪክን የምንሠራው እነደፈለግነው አይደለም”። ይህ ሰፊ ትርጉም ያለው ጥልቅ አባባል ነው። የውይይታችንን ጉዳይ በሚመለከት ግን ታሪክን ስንሠራ አሁን ያለው እውነታ፣ ወይም በጊዜያችን የተከሰተው ታሪክ ያወረሰን ሁኔታ በሚያስችለው መንገድና መጠን ነው ማለት ነው።

 

ስለዚህ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በተመለከተ አሁን የቅርብ የፖለቲካ ታሪካችን የሚፈቅደውና የሚያስችለው ምንድ ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።

 

በኢትዮጵያና ኤርትራ ሁኔታ ለፌዴራላዊነት የሚረዱ ነገሮች እንዳሉ አይተናል፤ እነዚህ ነገሮች ግን ፈዴራላዊነቱ በአሁኑ ጊዜ የፌዴሬሽን ዓይነት እንዲሆን የሚያስችሉ አይደሉም። ለምንድ ነው አሁን ፌዴሬሽን የማይቻለው? በፌዴሬሽን እንቋቋም ማለት እኮ አሁን በአንድ ሕገ-መንግሥት ሥር የምንተዳደር አንድ ሀገር እንሁን ማለት ነው! ኤርትራውያን መገንጠሉ ስህተት ነው ብለው ሉዓላዊ ሀገር መሆናችን ቀርቶ ከኢትዮጵያ ጋር አንድ አካል እንሁን ይበሉ ማለት እኮ ነው፤ ከብዙ የትግል ዓመታት በኋላ የተገኘው ሉዓላዊነት ቀርቶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሙሉ በሙሉ ትቀላቀል የሚለውን ሃሳብ መቀበል ለኤርትራዊ ሥነ-ልቦና በዚህ ጊዜ አዳጋች ነው፤ መገንጠል የሚቆጨው ኤርትራዊም ቢሆን ሌላውስ ይቅርና ህፍረት የሚባል፣ ክብር መጠበቅ የሚባል ነገር ስላለ ብቻ እንኳን ይህንን ሃሳብ ሊቀበል ይቸገራል።

 

በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሁኔታ የፈዴራላዊነቱ ዓይነት ኮንፌዴሬሽን ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ለምንድነው ኮንፌዴሬሽን ተስማማሚና የሚቻል የሚሆነው?

 

1. ኮንፌዴሬሽን በሁለት ሉዓላዊ ሀገሮች መሃከል የሚቋቋም ኅብረት ስለሆነ ለኤርትራዊ ሥነ-ልቦና ችግር አይፈጥርም፤ ሁለቱ ሀገሮች ሉዓላዊነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ መንግሥት ያቋቁማሉ፤ ሉዓላዊነታችን አደጋ ላይ ይወድቃል ብለው ኤርትራውያን ሆነ ኢትዮጵያውያን አይሰጉም።

 

2. ኮንፌዴሬሽን ሁለቱን ሀገሮች የሚጠቅም መሆኑን በቀላሉ ማሳየት ይቻላል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ በምን መንገድ እንደምትጠቀም ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በመተሳሰርዋ እንዴት እንደምትጠቀም ማስረዳት አያስቸግርም።

 

3. ሁለቱ ሀገሮች ኮንፌዴሬሽን ለማበጀት አስፈላጊው ግንኝነቶችና እርስ በርስ የሚጠቃቀሙ የተፈጥሮ ፀጋዎች እንዳሏቸው አስቀድሜ ጠቅሻለሁ፤ በተጨማሪም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአንድ ሀገር ዜጎች የነበሩ ህዝቦች ስለሆኑ በሁሉም ረገድ ተዋህደዋል። እንዲያውም መለያየቱ ያስቸግራል፤ ስለዚህ ኮንፌዴሬሽን አስፈላጊው ነገር ሁሉ የተሟላለት በቀላሉ ሊተገበር የሚችል አጀንዳ ነው።

 

 

አስቀድሜ እንደገለጽኩት ፌዴራላዊነት ሂደት ነው፤ ኮንፌዴሬሽንም አንድ የፈዴራሊዝም ዓይነት እንደመሆኑ መጠን ሂደት ነው። ይህ ምን ማለት ነው? ይህ ማለት ኮንፌዴሬሽኑ ገንቢና ፍትሓዊ በሆነ መንገድ ተግባር ላይ ከዋለ የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ወደተለያዩ ዘርፎች ያሸጋገራል፤ ወይም ይዘረጋል፤ ኅብረተሰቦቹም በበለጠና ብብዙ ረገድ ይገናኛሉ፣ ይዛመዳሉ። ይህም ማለት መተማመን ይጠነክራል ማለት ነው። በኮንፌዴሬሽን ጊዜ እንግዲህ የመቀራረብ መንፈሱ አድጎ የሁለቱ ሀገሮች ህዝቦች ለጠበቀ ግንኙነት፤ እስከ ፌዴሬሽን ድረስ፣ በሥነ ልቦና ደረጃ ዝግጁ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በሌላ አነጋገር ኮንፌዴሬሽኑ ወደ ፌዴሬሽን የሚመራ የሽግግር ጊዜ ሊሆን ይችላል።

 

ኮንፌዴሬሽኑ ወደ ፌዴሬሽን የሚያድገው “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት” በሚለው መሪ ሃሳብ መሣሪያነት ነው። ይህ መብት በኤርትራ ሕገ መንግሥት ይሁን ኮንፌዴሬሽኑን በሚያቆመው ውል ወይም ቻርተር እንደ ዋነኛ መሪ ሃሳብ መስፈር፣ ማለት መደንገግ አለበት። እስካሁን ድረስ ይህ መሪ ሃሳብ ወይም ፕሪንስፕል ኤርትራን በተመለከተ ከመገንጠል አጀንዳ ጋር በተያያዘ ነው የሚታወቀው። አሁን ግን፣ ማለት በኮንፌዴሬሽን ጊዜ ይህንን መሪ ሃሳብ የምናወሳው ከአንድነት ጋር በተያያዘም ነው። የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚለው መሪ ሃሳብ ህዝቡ የመገንጠል ብቻ ሳይሆን ከሌላ ሀገር ጋር በማንኛውም መልክ፣ በፌዴሬሽን ይሁን በሌላ ለመተሳሰር ወይም ለመቀላቀል ያለውን መብትም ያመለክታል። በህዝቡ ሙሉና ነፃ ፈቃድ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ ማንኛውም የዝምድና ለውጥ ማድረግ ይቻላል።

 

እንግዲህ ኮንፌዴሬሽን ወደ ፌደሬሽን ሊያድግ ይችላል ስንል ይህንን መሪ ሃሳብ፣ ማለት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ሳንረሳ ነው። ህዝቡ ወይም ሕዝቦቹ (ማለት የኢትዮጵያና የኤርትራ) ከፈለጉና በሙሉ ነፃነት ከወሰኑ ኮንፌዴሬሽኑን ወደ ፌዴሬሽን ሊያሳድጉ ይችላሉ።

 

ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ በአጽንኦት መጠቀስ ያለበት ነጥብ አለ፤ ኮንፌዴሬሽኑ ወደ ፌዴሬሽን ሊያድግ የሚችለው ሕዝቦቹ በኮንፌዴሬሽኑ ሂደት የተጠቀሙና የረኩ እንደሆነ ብቻ ነው። በኮንፌዴሬሽኑ ጊዜ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ፍሪያማ ከሆነ፤ ማለት ዕድገት ከተገኘ ሰላምና ፍትሕ ከሰፈነ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከተጠበቁና ከጠነከሩ፣ የህዝብ ኑሮ ከተሻሻለ መተማመኑ ይጠነክራል። የጠነከረና ያደገ መተማመን ደግሞ ለሁለቱ ሀገሮች የጠበቀ ግንኙነት መሠረት ይሆናል። በሌላ አነጋገር መተማመኑ ሲጠነክር በፌዴሬሽን አብሮ የመኖር ዝንባሌም እያደገ ይመጣል ማለት ነው።

 

ይህ ካልሆነ ግን፣ ማለትም በኮንፌዴሬሽን ጊዜ ሰላም ካልተገኘ ኑሮ ካልተሻሻለ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ካልተጠበቁና ካልጠነከሩ፣ የዝምድናው ጠቃሚነት ግልፅ አይሆንም፤ ስለዚህም ኮንፌዴሬሽኑ ወደፌዴሬሽን አያድግም፤ እንዲያውም በተቃራኒው ኮንፌዴሬሽኑ ራሱ ሊፈርስ ይችላል።

 

 

ስለዚህ ጉዳይ ንግግር በማደርግበት ጊዜ የሚያጋጥመኝ አንድ ጥያቄ አለ፤ አሁን ወደዚያው ጥያቄ ልሂድ፤ ጥያቄው የኮንፌዴሬሽን ሃሳብ ገንቢ ቢሆንም አሁን ያሉት የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ሊሳካ ይችላል ወይ? እነዚህ መንግሥታት ሁለቱን ሀገሮች በኮንፌዴሬሽን ማስተሳሰር ይችላሉ ወይ? የሚል ነው። ይህ ዘለን ልናልፈው የማይገባ መሠረታዊ ጥያቄ ነው።

 

በዚህ ጥያቄ ላይ አስተያየቴ ባለፉት ዓመታት ትንሽ እየተለወጠ መጥቷል ማለት ይቻላል፣ በተለይ ኢትዮጵያን በተመለከተ። የኤርትራ ሁኔታ ግን የማያያሳስት ነበር፣ አሁንም ፈጽሞ አያያስትም፤ የኔም አስተያየት አልተለወጠም። አሥመራ ያለው ሥርዓት ሊያሳስተን ያልሞከረ፣ ለይስሙላ እንኳን መድብለ ፓርቲ ያልፈቀደ፣ ዲሞክራሲን ያልተቀበለ፣ ሕገ-መንግሥትም የሌለው የወጣለት አምባገነናዊ ሥርዓት ነው። የኤርትራ ህዝብን ባርያ አድርጎ እያሰቃየ ያለው በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ሥርዓት ነው። ከዚህም በላይ ሁላችሁም እንደምታውቁት ከሁሉ ጎረቤት ሀገር ጋር ጦርነት ገጥሞ ኤርትራን ከዓለም

 

እንድትነጠል ያደረገ ነው። ይህ መንግሥት እንግዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ይሁን ከማንም ሌላ ጎረቤት ሀገር ጋር በኮንፌዴሬሽን ሊዛመድ ብቃት የለውም።

 

ስለዚህ በሁለቱ ሀገሮቻችን መሃከል የኮንፌዴሬሽን ሂደት እንዲጀመር ኤርትራ ያለው መንግሥት መነሳት አለበት። የዚሁ መንግሥት መውደቅና በአንድ በህዝቡ ተቀባይነት ያለው ሥርዓት መተካት፣ የሚፈለገው ኮንፌዴሬሽን እንዲጀመር መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ ነው።

 

ኢትዮጵያስ? በ90ዎቹ የዲሞክራሲን ጥያቄ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሁኔታ አከራካሪ ነበር፤ የኢህአዲግ መንግሥት አሥመራ ካለው መንግሥት የበለጠ ዘዴኛ ነው፤ በጠቅላላ አነጋገር እስከ 2005 ምርጫ ድረስ በብዙ ረገድ ለዲሞክራሲ መንቀሳቀስ የሚያስችል ቀዳዳ፣ ለዘዴም ቢሆን ከፍቶ ነበር። ከ2005 ምርጫ በኋላ ግን ተከፍቶ የነበረው ቀዳዳ እየጠበበ፣ በአንዳንድ ረገድም እየተዘጋ ነው። ስለዚህ አሁን በኢትዮጵያ ያለው “ዲሞክራሲ” በአብዛኛው ለአንድ ፓርቲ የሥልጣን ቁጥጥር መሸፈኛ እየሆነ መጥቷል፤ የኢህአዲግ መንግሥት በዲሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ሥልጣን ለሌላ ፓርቲ ሊያስረክብ ዝግጁ ነው ለማለት ያስቸግራል።

 

ስለዚህ ሁለቱ ሀገሮች በኮንፌዴሬሽን እንዲተሳሰሩ ኢትዮጵያ ውስጥም ለውጥ ሊያስፈልግ ነው። በኢትዮጵያም አሁን ያለው አገዛዝ በህዝቡ ሙሉ ተቀባይነት ባለው መንግሥት መተካት አለበት። የሚመረጠው ዓይነት ሥርዓት ደግሞ ሁሉን ያቀፈ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ነው።

 

በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣው በትግል ነው፤ በሁለቱም ሀገሮች ለውጥ ሲመጣ ለሁለቱም ህዝቦች ጥቅም ነው። ስለዚህ ይህንን ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ትግል ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን መተባበር ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

 

የኮንፌዴሬሽን ሂደት እንዲጀመር መወገድ ያለባቸው ሌሎች እንቅፋቶችም አሉ፤ ይህም አስተሳሰብን ወይም በአንዳንድ ጥያቄዎች ላይ የሚወሰዱትን አቋሞች የሚመለከት ነው። ትክክል ያልሆኑና ለኮንፌዴሬሽን ዕንቅፋት የሚሆኑ አመለካከቶች በኤርትራውያንና በኢትዮጵያውያን በኩል አሉ፤ ለምሳሌ አንዳንድ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ጋር መዛመድ በሚለው ሃሳብ ይሰጋሉ፤ ይጠራጠራሉ፤ በኮንፌዴሬሽንና በፌዴሬሽን መሃከል ያለውን ልዩነት አያውቁትም፤ አንዳንዱማ ኢትዮጵያን ገና እንዳባላንጣ ያያታል፤ ስለታሪክ ፈጽሞ የተሳሳተ አመለካከት አላቸው፤ የሁለቱ ሀገሮች ታሪክ ምን ያህል የተዛመደ፣ እንዲያውም በብዙ ረገድ አንድ መሆኑን አያውቁም፣ በባሕል ረገድም እንደዚሁ።

 

እነዚህ እንቅፋቶች እያነሱና እየተዳከሙ መሆናቸውን እታዘባለሁ። ይህንን ስገልጽ በደስታ ነው። በሂደት ጨርሰው ባይሆንም በመሰረቱ እንደሚጠፉ አምናለሁ።

 

በኢትዮጵያውያን በኩልም እንደዚሁ ዕንቅፋቶች አሉ። ኤርትራውያን አንፈልጋችሁም ብለውናልና በኮንፌዴሬሽን ይሁን በፌዴሬሽን ከነርሱ ጋር ዝምድና አንፈልግም፣ ኤርትራ ድሀ ሀገር ናት፣ እንዲያውም መንግስቷ የተኮላሸ ሆኗል፣ እርሷን ማዳን አንሻም፣ ኮንፌዴሬሽን የሚባለው ኤርትራን ብቻ ነው የሚጠቅመው፤ ስለዚህ አያስፈልገንም፣ ከኤርትራውያን ጋር ለሁለታችን የሚበጅ ግንኙነት ማድረግ እንደማይቻል እስከ እ.ኤ.አ. 1998 የነበረው ሁኔታ አስተምሮናል፤ ያኔ የሻዕቢያ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደልቡ እየዘረፈ ኢፍትሃዊ የሆነ ተግባራት ፈጽመዋል ወዘተ። ከነዚህ አባባሎች የአንዳንዶቹ አነሳስ ይገባኛል፣ አብዛኛዎቹ ግን ትክክል አይደሉም። ኮንፈረደረሽን ለሁላችን ነው የሚጠቅመው፤ የኤርትራ መገንጠል ታሪካዊ መግለጫ አለው። የአለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታትም የሚጠየቁበት ጉዳይ ነው። አሁን ያለው የሻዕቢያ መንግሥት ኢፍትሃዊ ነገሮች እንደፈጸመ ዕውነት ቢሆንም የሚፈለገው ያለው ኮንፌዴሬሽን የሚቋቋመው የሻዕቢያ መንግሥት ከተጣለ በኋላ፣ የሻዕቢያ አሰራር የሚመስል ሁሉ ከተከለከለና ከቀረ በኃላ ነው። ስለዚህ ሻዕቢያ የፈጸመው ሌብነት አይደገምም።

 

እነዚህ የተሳሳቱ አመለካከቶች በሂደት እየተስተካከሉ ይመጣሉ፣ የሚል እምነት አለኝ፤ እንዲያውም እየተስተካከሉ ናቸው ለማለት የሚያስደፍሩኝ ምክንያቶች አሉ። ያሁኑ ስብሰባችን ለራሱ ትልቅ ትርጉም ያለው አንድ ምልክት ነው ማለት ይቻላል።

 

 

አሁን ኃላፊነታችን ምንድን ነው? ወደሚለው ጥያቄ ልሻገርና ንግግሬን ልጨርስ። የኛ ኃላፊነት በሁለቱ ሀገሮችና በሁለቱ ህዝቦች በኩል ያሉትን አስቀድሜ የጠቀስኳቸውን ዕንቅፋቶች ንዲወገዱ መታገል ነው። የፌዴራላዊነት ትርጉምና ጥቅም ማስረዳት፣ የኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወንድማማችነት፣ የታሪካቸውን አንድነትና የባህሎቻቸውን ግንኙነት ሁሉ ለማስተማርና ለማስረዳት መጣር አለብን።

 

በመሰረቱ ደግሞ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ስለ እርስ በርሳችን በጎ ማሰብ ያስፈልገናል። ኤርትራውያን የኢትዮጵያውያንን ችግርና ስሜት እንዲረዱ ያስፈልጋል። እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የኤርትራውያንን ችግርና ስጋት እንዲረዱ ያስፈልጋል። መለያየቱ ወይም መገንጠሉ እንዴት እንደመጣና ከምን እንደተነሳ ያለአድልዎ መመራመርና ማወቅ ያስፈልጋል።

 

በተጨማሪም፣ ስለዚህ ጉዳይ ስናስብ ዓላማችን አርቆ የተመለከተ መሆን አለበት። ለወደፊቱ ጠንካራና አስተማማኝ የሆነ መሰረት ያለው ዝምድና እንዲኖር በሚል ሃሳብ መመራት አለብን፣ ቶሎ ብለን ውህደት ካላደረግን ብሎ የችኮላ እርምጃ መውሰድ ፍሬ አይሰጥም። በሌላ አነጋገር ታሪካዊው ውርሻና የወቅቱ ሁኔታ የሚቻል የሚያደርጉት ምንድነው ብሎ ተመራምሮ በጥንቃቄ ግንኙነቱን መጀመር፣ ማጠንከርና ማሳደግ ነው የሚሻለው።

 

የኢትዮጵያና የኤርትራ ልሂቃን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። ለመቀራረብ መንገድ እንዲከፈትና እንዲሰፋ የህብረት መንፈስ፣ ማለት ፈረንጆች animus integrandi የሚሉት የመግባባትና የመተሳሰር ህሊና እንዲዳብርና እንዲሰርጽ መጣር አለባቸው።

 

የዛሬ ስብሰባችንና ውይይት ይህንን ህሊና ለማስፋፋት ይረዳል ወይም ሊረዳ ይችላል ብዬ አምናለሁ።

 

ስላዳመጣችሁኝ በጣም አመስግናለሁ!

 

እግዜር ይስጥልኝ!!


 

የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን ወዳጅነት ኮንፈረንስ አዘጋጅ ኮሚቴ አድራሻ፦ 

 Ethio-Eritrean Friendship Conference Committee

PO BOX 1482

SAN JOSE, CA 95102

PHONE: 40864695102

E-MAIL: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!