Yegazetegnaw Mastaweshaቦጋለ ዳኜ - ከካሊፎርኒያ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

“… የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ማሪዋናን መጥነው በመጠቀም በቅዳሴ ወቅት ጥቅም ላይ ያውሉታል። ዝቋላና አክሱም ላይ ይህን እንደሚያደረጉ እኔ በግሌ አውቃለሁ። …” ይህ የተወሰደው “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ከተባለውና በቅርቡ ከታተመው ከጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ መጽሐፍ ገጽ 378 ላይ ነው።

 

የተባለው መጽሐፍ በእጄ ገብቶ ያነበብኩትf በቅርቡ ሲሆን፤ ለደራሲው በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ጥያቄ በቀረበላቸው ወቅት ማሪዋና በምን መልክና እንዴት በቅዳሴ ወቅት በጥቅም ላይ እንደሚውል ጠይቄ በተረዳሁ ነበር። ያ ሁሉ ጥያቄ ሲነሳ ቤተክርስቲያንን ከሚወክሉ ሰዎች ካንዳቸውም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ተነስቶ ለተነዛው ሐሰተኛ ወሬ መልስ ተሰጥቶ አንባቢዎቹን ከተሳሳተ ግንዛቤና ትዝብት መመለስ አለመቻሉ የሚደንቅ ነገር ነው። መጽሐፉ በልብወለድ መልክ እንዳይታይ በመግቢያው ላይ ፀሐፊው የጻፉት እውነተኛ ገጠመኞቻቸውን መሆኑን ገልጸውልናል።

 

ቤተክርስቲያኗን ባልወክልም በቤተክርስቲያን ስላደግሁ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ ተራ ምዕመን መልስ ልሰጥበት እወዳለሁ። ደራሲው በቅዳሴ ወቅት እጣን ሲጤስ አይተው ማሪዋና መስሏቸው ነው እንዳልል የእጣንና የማሪዋና ሽታ አይለዩም ለማለት አልደፍርም። ስለ ኃየሎም ገዳይ በጻፉበት ምዕራፍም ማሪዋና ማጨሳቸውን ስለነገሩንና እጣንም ቡና ሲፈላ በየቤቱ ስለሚጨስ የእጣንና የማሪዋና ሽታ ለይተው አያውቁም አልልም። ዕጹንም ባጨሱ ጊዜ የተሰማቸውን ቅብዥርዥር ሁኔታ ነግረውናልና።

 

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የሰውን ጤናማ ስሜት የሚቀያይሩና የሚያዛቡ ዕፅዋትን እንኳን በቅዳሴ ጊዜ ልትጠቀም በሌላውም ጊዜ፤ ምዕመናኗ እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንዳይጠቀሙ አጥብቃ ታስተምራለች። በተለይ እንደ ትንባሆ (ሲጋራ) ያለውን ስሙን ጭምር ጥንባሆ እያሉ በማክፋፋት፣ የበቀለውም በአርዮስ ፈርስ ላይ ነው እያሉ በማጥላላት አንዳንድ ቄሶች በተለይ ለሕፃናት ይነግሩ እንደነበር ትዝ ይለኛል። እንደ ፈረንጅ ቄስ ሲጋራ የሚያጨስ አንድም የኦርቶዶክስ ቄስ የለም። ጫትም የሚያመነዥግ ቄስ የለም። በተለይ ጫት እንዲህ እንደዛሬ ለጥናት ይጠቅማል በሚል ፈሊጥ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሳይቀር እየተሸፋፈነ ሾልኮ ከመግባቱ በፊት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ብዙም አይታወቅም ነበር።

 

ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኃይማኖት ሳይሆን በሥልጣንና በአስተዳደር ተከፋፍላ በከፍተኛ ችግርና ስደት ላይ ነች። እንደ ፖለቲካው ሁሉ የቤተክርስቲያን አባቶች በሥልጣን ሽኩቻ ላይ ናቸው። ይህን በወንበር የመገፈታተር ሁኔታ ሳይ የታወቁት የቅኔ መምህር የስሬው መድኃኒዓለሙ አለቃ ጥበቡ ገሜ ይታወሱኛል። ንጉሡ በ40ዎቹ ዓመተ ምህረት ወደ አዲስ አበባ ጠርተዋቸው ለሲመተ ሊቀ ጵጵስና መታጨታቸውን ሲነግሯቸው “የማስተምራቸውን ልጆቼን በትኜ ተሸፋፍኜ አልቀመጥም” ብለው ወደዘረጉት ወንበር ጠፍተው መሄዳቸው ይነገራል።

 

ቤተክርስቲያኗ ችግር ሲደርስባት ሥርዓቷን ጠብቃ መጓዝ ይሳናታል። በግራኝ ወረራ ወቅት ንጉሡ ዐፄ ልብነ ድንግል ከፍተኛ መከራና ስደት በደረሰባቸው ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ባሕረ ሃሳብ አውጥታ አበቅቴ ቆጥራ ትክክለኛውን ቀኑን ማወቅ እንኳን አቅቷት የትንሣኤን በዓል በተለያየ ቀን ያከበረችበት ዓመት እንደነበር ፕሮፌሠር ጌታቸው ኃይሌ ከተረጎሙት የባሕረ ሃሳብ መጽሐፍ ተረድተናል።

 

በኢህአዲግ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሳይቀር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የነፍጠኞች ምሽግ ነች እየተባለ ስለተዘመተባትና ኃይማኖቱም የነፍጠኞች ኃይማኖት ነው እየተባለ አባባሉ ስለተራገበ ሊሆን ይችላል፤ በዚህም ሆነ በሌላ የምዕመናኖቿ ቅማሬ-አኀዝ (rate) በማደግ ፈንታ ቁልቁል መሄዱን ባለፈው ይፋ ከሆነው የህዝብ ቆጠራ ተረድተናል።

 

ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና ማሪዋና የተባለው ዕፅ፤ ዕፀፋርስ (አጠፋሪስ/እጠፋሪስ) ይመስለኛል። ዕፀ ፋርሱን አብሾም የሚሉት አሉ። ከስያሜው መረዳት እንደሚቻለው ይህ ዕፅ በመጀመሪያ ከፋርስ የመጣ ሳይሆን አይቀርም። አቶ ተስፋዬ በተለይ በታወቁት አድባራት፤ በዝቋላና በአክሱም በቅዳሴ ጊዜ አብሾ በጥቅም ላይ መዋሉን ካዩ፤ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የማይኖርበት ምክንያት አይኖርም። እኔ እንዳየሁት በአንዳንድ ዜማ ቤትና ቅኔ ቤት አንዳንድ የዋሆች (ደራሲው በዚሁ መጽሐፋቸው በገጽ 399 በተማሪነት ዕድሜያቸው “ዝቋላ ጫካ ውስጥ አንጎልን የሚከፍት አንድ ቀይ ዛፍ አለ” በሚል ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዝቋላ ሄደው ዛፉን ለማግኘት እንደሞከሩት) ትምህርት ይገልጻል በሚል በራስ አነሳሽነት ይህን ዕፅ በዕድሜያቸው አንድ ወይም ሁለት ጊዜ የሚጠቀሙ አሉ። አጠቃቀሙም ማታ ጸጥ ሲል ዕፁን በገል፤ ፍም ላይ ያጨሱና ሁለት ሦስት ሆነው በደበሎ ወይም በቁርበት ተጀቡነው ይታጠኑታል። ከዚያም ህሊናቸውን በመሳት ለተወሰነ ጊዜ ግማሹ ይለፈልፋል፤ ግማሹ ይደብተዋል።

 

በሌላ ቀን እንደ ሁኔታው ከወራት ወይም ከዓመት በሁዋላ ቆይተው የበፊቱ አልሰመረልንም በሚል ሁለተኛ ሙከራ የሚያደርጉ አሉ። ታዲያ እንደዚህ የሚያደርጉ ሰዎች አንዳንዶቹ ትንሽ መጠጥ ሲጠጡ በቀላሉ የመስከርና የማስቸገር ጠባይ ስለሚታይባቸው አብሿም ሲሏቸው ይሰማል። እንግዲህ ይህ ዕፀ ፋርስ የመቅመስ ሁኔታ የሚሆነው ከላይ እንደጠቀስኩት በራሳቸው አነሳሽነት በትምህርት ቤታቸው ሲሆን፤ እንኳን ቤተክርስቲያኗ መምህራቸው እንኳን ብዙውን ጊዜ አያውቁም። ተማሪዎቹ ይህን ሲያደርጉም ከመታጠናቸው በፊት፤ ትምህርት እንዲገባቸውና እግዚአብሔርም ትምህርቱን እንዲገልጽላቸው ፀሎት ያደርጋሉ። ከዚያ ውጭ ሱስ ይዟቸው የሚደጋግሙም አይደለም።

 

የሚገርመው አጠቃቀሙ እንደዚህ ከመሆኑ ሌላ ለብዙ ዘመናት እንደ መቆየቱ እስካሁኑ ትውልድ፤ ማለት ከቆሎ ትምህርት ቤት ወጥቶ ወደ ውጭ እስከ ተዛመተበት ድረስ፤ እንደ ትንባሆና ጫት ለሱስ ጠቀሜታ አለመዋሉ ነው። ከዚህ ውጭ አቶ ተስፋዬ ገብረአብ እንዳሉት በተዘዋወርኩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በቅዳሴ ጊዜ በጥቅም ላይ ውሎ አላየሁም። አየሁ ያለም አላገጠመኝም። ያደግሁትም በመናገሻ ማርያም ገዳም ሲሆን፣ እንኳን በቅዳሴ ጊዜ በሌላም ጊዜ ከላይ ከጠቀስኩት ሌላ በምንም መልኩ በጥቅም ላይ ውሎ አላጋጠመኝም። ተደብቆ ሳይታወቅ የሚቀር ነገርም አይደለም። አንድ ልጅ ከእናቱ ተደብቆ ሲጋር ቢያጨስ እናቱ በጠረኑ ወይም ከቤቷ ክብሪቷ እያለቀ ሲሄድ የልጇን ሲጃራ አጫሽነት ማወቋ አይቀርም። ብዙውን ጊዜ በዚህ መልክ ትምህርት እንዲገባቸው የሚጥሩት በትምህርቱ የሚሰንፉና ተግተው ትምህርታቸውን የማያጠኑት ወይም ባቋራጭ ሊቅ ለመሆን የሚመኙ ናቸው። የሚሳካላቸው አሉ ይባላል እንጂ ከ”አሉ” ውጪ እኔ ያየሁት የለም።

f

ስለዚህ ዓላማዬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስም ማሪዋና ወይም ዕፀ ፋርስ በጥቅም ላይ እንደማይውልና ሐሰቱን ሐሰት ለማለት ስለሆነ ቤተክርስቲያኗ ለዘመናት ለአባላቷ በሥነ ምግባር አስተዳደግ መሠረት ሆና ሳለ በየአቅጣጫው ሲዘመትባት እየሰሙ ዝም ማለት አይገባም በማለት ነው። ዝም ማለት መቀበል እንዳይሆን ቤተክርስቲያኗን የሚወክሉ መልስ ቢሰጡና በጎደለ ቢሞሉበት ጥሩ ይመስለኛል። ምናልባት አቶ ተስፋዬ ከላይ ተማሪዎቹ ዕፁን ከመታጠናቸው በፊት የሚያደርጉት ፀሎት፤ ቅዳሴ መስሏቸው ይሆን?


 

ቦጋለ ዳኜ - ከካሊፎርኒያ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!