Administrative Mapበካሊፎርኒያ ሳን ዮሴ ባለፈው ግንቦት 7 ቀን 2001 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን የወዳጅነት ኮንፈረንስ ላይ ፕ/ር ተስፋጽዮን መድኅኔ እና ፕ/ር ዳንኤል ክንዴ ተናጋሪዎች እንደነበሩ መዘገባችን አይዘነጋም። “የኢትዮጵያንና የኤርትራን ወንድማማች ህዝቦች ሊቀራርብ የሚችለው የኮንፌዴሬሽን ሥርዓት ነው” በማለት ፕ/ር ተስፋጽዮን መድኅኔ ”ኢትዮጵያና ኤርትራ ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ባቀረቡትን ጽሑፍ አስነብበን የፕ/ር ዳንኤል ክንዴን ጽሑፍ ለማቅረብ ቃል ገብተን ነበር። ፕ/ር ዳንኤል ክንዴ “የኢትዮጵያና ኤርትራ ፌዴሬሽን አስፈላጊነት” በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ጽሑፍ ታነቡ ዘንድ እንጋብዛለን። መልካም ንባብ!

 

“የኢትዮጵያና ኤርትራ ፌዴሬሽን አስፈላጊነት” ፕ/ር ዳንኤል ክንዴ

 

የተከበራችሁ እንግዶች!

ከሁሉ አስቀድሜ ይህን ስብሰባ በማዘጋጀት ረገድ በጣም የደከሙትን ሁሉ ከልብ እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ።

 

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የጋራ ጉዳያቸውን የሚወያዩበት መድረክ ለብዙ ጊዜ አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝም፤ የወቅቱ የሥነ-ልቦናና የፖለቲካ ሁናቴ አመች ስላልነበረ እንዲሁ በጎሪጥ እየተያዩ መተላለፍ እንጂ ሰላምታ እንኳ ለመለዋወጥ ያልቻሉበት ጊዜ ነበር። ሁለቱ ሀገሮች ከተለያዩ እነሆ 16 ዓመታት አልፈዋል። እነዚህ ዓመታት ራስን በጥሞና የመፈተሻና የመመርመሪያ፣ እንዲሁም ጠላትና ወዳጅን የማወቂያ ዓመታት ሆነው መቆጠር ይኖርባቸዋል።

 

የፖለቲካ ታሪክን ቅመራ አተኩረን ብንመረምር፣ በመድረኩ ላይ ልዩ ልዩ የሆኑ ታሪክ ሰሪና የለውጥ ጎኅ ቀዳጅ የሆኑ መሪዎችን እናገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ ያሉት ሰኞ ላይ ሆነው ቅዳሜና እሑድን ለማየት ችሎታ ያላቸውና የህዝብን ሕልም መፍታት ብቻ ሳይሆን ችግሮችንም መርምረው በማጥናት አመርቂ የሆነ መፍትሔ የሚያቀርቡ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ያሉት፤ ያለውን የህዝብ የችግር ምንጭ ከቀረበው መፍትሔ ጋር በማጣመር ለህዝብ በሚገባ ቋንቋ የሚያስረዱና ህዝቡን አንቅተው የሚያደራጁ፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ያሉት የቀረበውን መፍትሔ በሥራ ለመተርጎምና በግብር ለማሳየት ብቃትና ችሎታ ያላቸው፣ በአራተኛ ደረጃ ያሉት የሚሠራው ሥራ ሁሉ ለህዝብ የሚሰጠውን ጠቀሜታ የሚከታተሉና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ዘገባ የሚያቀርቡ ያጋጥሙናል። እንደዚህ ባለ የሥራ መከፋፈል በሰፈነበት የትግል መድረክ ጤናማ የሆነ ትብብር በመኖሩ ውጤቱም ብዙውን ጊዜ አመርቂ ሆኖ ይገኛል።

 

ታሪክ እንደሚያስተምረን ሁሉ አንድ ህዝብ ከአንድ የዕድገት ደረጃ ወደ ሌላ ከፍ ወዳለ የኑሮ ደረጃ በዘፈቀደ ወይንም በራሱ ምኞት አይሸጋገርም። ለሽግግሩ መፈጠርና መከሰት አመች ሁኔታዎች መኖር ይኖርባቸዋል። በዚህ እረገድ እላይ የተዘረዘሩት ዓይነት መሪዎች የሚጫወቱት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሁኔታዎች ተሟልተው ካልተገኙ ግን የተባለው ሀገር ህዝብ ባለበት ይዳክራል፤ ወይንም ተገነጣጥሎ ይጠፋል ማለት ነው።

 

ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ከዚህ የታሪክ ሰለባ ለመዳን ይችላሉ። ምሑሮቻቸው ያካበቱትን ትምህርትና ዕውቀት እርስ በርስ ለመጠፋፋት ከማቀድ፣ ወይንም በግል ቅራኔዎች ተውጠው እየተጠላለፉ ከመውደቅ ይልቅ አድማሳቸውን ሰፋ አድርገው እውነትን ተመርኩዘው መታገል ይኖርባቸዋል። ትምህርታቸውና ዕውቀታቸው የህዝቡን የኑሮ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ካልዋለ፤ የጋን መብራት ይሆናሉ፣ ወይንም ትምህርታቸውና እውቀታቸው የግል ጥቅም ማስፋፊያ ብቻ ሆኖ ይቀራል። አንድ ሰው ከመጠን በላይ የሆነ ሀብት ቢያካብትም የሚተኛው በአንድ አልጋ ላይ ሲሆን፤ የሚበላው ደግሞ በቀን ሦስት ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል። ይህንን ለተነፈጉት ማሰቡ የትልቅነት ምልክት ነው።

 

ከወንድሜ ከፕሮፌሠር ተስፋጽዮን መድኃኔ ጋር ያለን ጓደኝነት ቆየት ያለ ነው። ብዙ ጽሑፎችንም እንለዋወጣለን፤ በብዙ ስብሰባዎችም አብረን ተካፍለናል። ሁለታችንም በሃሳብ ግጭት እናምናለን። የሃሳብ ግጭት የዕድገት ምንጭ መሆኑን አጥብቀን ስለምናምን የአንድ ወገን ሃሳብ እንዲገን፤ ተጻራሪው አሳብ ግን እንዲጨቆንና እንዲኮላሽ የሚያደርጉትን ደካማ ቡድኖች አጥብቀን እንቃወማለን። ሃሳብ በተሻለ ሃሳብ ይተካል እንጂ፤ ተፃራሪ አሳብ ያፈለቁትን ግለሰቦች በመግደል ወይም እሥር ቤት አስገብቶ በማሰቃየት ሃሳቡን ለመግደል አይቻልም። ስለዚህ ሁለታችንም በአእምሮ ነፃነት፣ በንግግርና በጽሑፍ ነፃነት አጥብቀን እናምናለን።

 

ክቡራንና ክቡራት!

ታሪክ አይዋሽም!

ኢትዮጵያና ኤርትራ በፖለቲካ ፈዴሬሽን ሥርዓት ለምን መዋቀር አለባቸው ብዬ ሃሳቤን በዝርዝር ከማቅረቤ በፊት አንዳንድ የተረሱ የሚመስሉ ሆኖም በታሪክ ገጾች ላይ ሰፍረው የሚገኙ እውነታዎችን ለማቅረብ እፈልጋለሁ።

 

እ.ኤ.አ. ከ1941 - 1948 ዓ.ም. ድረስ ኤርትራ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ይሠራ የነበረ G.N.K. Trevaskis የሚባል እንግሊዝ Eritrea: A Colony in Transition (1960) በሚል ርዕስ ላይ የጻፈውን ልጥቀስ፣ “Italy created Eritrea by an act of surgery by severing its different peoples from those with whom their past had been linked and by grafting the amputated remnants to each other under the title of Eritrea. Eritrea had never enjoyed any form of unity, had never had a government of its own, and had never even had a name ….”.

 

ይህም ማለት አንድ የነበረው ህዝብ ለሁለት ተከፍሎ ግማሹ ኤርትራ ውስጥ ሲቀር ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀረ ማለት ነው። ይህም አፋርን፣ አሳውርታን፣ ከበሳ ውስጥ ያለውን የሃማሴን፣ ሠራየና አኮሎ ጉዛይ ትግርኛ ተናጋሪውን፣ ከረን አካባቢ የሚኖረውን ብሌን(አገው)፣ ኩናማንና ሌሎችንም ይመለከታል።

 

ይህም ማለት ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ከሞላ ጎደል ታሪካቸው፣ ዘራቸው፣ ቋንቋቸው፣ ሃይማኖታቸውና ባሕላቸው አንድ ዓይነት የሆነ ወይንም በጣም የተቀራረበ ነው ለማለት ይቻላል። ለኢትዮጵያውያን ከኤርትራውያኖች የበለጠ ወንድምና እህት እንደሌላቸው ሁሉ፤ ለኤርትራውያንም እንደዚሁ ከኢትዮጵያውያን የበለጠ የሚቀርባቸው በዓለም ውስጥ ማንም እንደሌለ ማወቅ ይኖርብናል። እንኳንስ ህዝቡ ከብቱ እንኳ ሳይቀር አገሩን በትክክል ያውቀዋል። ለምሳሌ ያህል ከሃዘሞ (አከለጉዛይ) ተነስቶ ወሎ ድረስ ለግጦሽ በየዓመቱ ይመጣ የነበረው ከብት ውሃና ሳሩ ሁሉ የት እንዳለ በትክክል ያውቀዋል። እንደዚሁም ከሠራየና ጋሽ ሰቲት ተነስቶ በየዓመቱ ጐንደር ድረስ የሚመጣው ከብት የግጦሽ ሰፈሩን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ለምሳሌ ያህል ሰቲት ሑመራ፣ ባናት፣ ባሕረ ሰላም፣ ንጉዲ፣ አርማጭሆ፣ ኮረደም ሊጠቀሱ ይችላሉ።

 

በ1941 ዓ.ም. የተቋቋመው የአንድነት ፓርቲ (Unionist Party) ዓላማው ከኢትዮጵያ ጋር ሙሉ በሙሉ ለመቀላቀል ነበር። ይህም ማለት ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽን የሚባሉት የአስተዳደር ስልቶች ለውይይት እንኳ አልቀረቡም ነበር ማለት ነው።

 

እነ ሎሬንሶ ታዕዛዝና ብላታ ኤፍሬም ተወልደ መድኅን ኢትዮጵያን ወክለው በሚገኙበት በ1946 ዓ.ም. በተካሄደው የፓሪስ የሰላም ጉባዔ ፊታ/ ገብረ መስቀል ወልዱ የአንድነት ፓርቲ የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ የሚከተለውን ቴሌግራም ለስብሰባው አስተላልፈው ነበር፤

 

“Our country Eritrea is historically, ethnically, and geographically an integral part of Ethiopia. The unanimous and sole desire of our people is to be unconditionally united to our Motherland Ethiopia.”

 

ቀጥሎም፣ ከስድስት ዓመት በኋላ በተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር፣ የአንድነት ፓርቲ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ፓርላማ ውስጥ ከነበረው 67 የውክልና ወንበር ውስጥ 47ቱን አሸንፈው ሲይዙ፣ ኤርትራን ነፃ እናወጣለን ብለው ይታገሉ የነበሩት ፓርቲዎች 18 ወንበሮች ብቻ ነው ያገኙት። የቀረውን ሁለት ትናንሽ ፓርቲዎች ወሰዱ።

 

ሁናቴው ይህ ከሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያንና ኤርትራን በፌዴሬሽን ለምን ለማዋቀር አሰበ? ብለን ብንጠይቅ ተቃዋሚውን የቆላ ክፍል ህዝብ በተለይም እስላሙን ለማግባብት ሲል ነበር።

 

በእኔ አስተያየት የፌዴሬሽኑ ሥርዓት ጥሩም ቢሆን ከጊዜው ጋር የማይሔድ ገጽታ ነበረበት። ቢቆይ ኖሮ የኢትዮጵያንና ቀጥሎም ሌሎችን የአፍሪካን ቀንድ ሀገሮች በማስተሳሰር እረገድ ለምናደርገው ጥረት ዓይነተኛ መነሻ ይሆነን ነበር። ብዙ ትምህርትና ዕውቀት እናካብትበት ነበር። ስለሆነም ከጊዜው ጋር የማይሄድ ነበር። የፈላጭ ቆራጭ የሆነውን የዘውድ ሥርዓት መዋቅር ሳይለወጥ ዴሞክራቲክ በሆነ ሥርዓት ለመለወጥ መሞከሩ ነበር። ታሪክ እንደሚያስተምረው ሁሉ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ ሥርዓቶች አብዮታዊ በሆነ በህዝብ አመፅ ከተገረሰሱ በኋላ ነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚቻለው።

 

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተቋቋመ የተባለው የስም ፌዴሬሽን በእውነቱ ፌዴሬሽን አልነበረም። የተባለውም “ፌዴሬሽን” ሊሠራም አልቻለም፤ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ነበሩ፤

 

1. ከፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር ይዘት ልዩነቶች ሌላ ኤርትራና ኢትዮጵያ በህዝብ ቁጥር ብዛት፣ በመሬት ስፋትና በምጣኔ ሀብት ተመጣጣኝነት አልነበራቸውም። በእንዲህ ያለ አጋጣሚ የሚሠፍነው የእኩልነትና የትብብር መንፈስ ሳይሆን ትልቁ ትንሹን በቁጥጥሩ ሥር የሚያደርግበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው። ፌዴሬሽን የሚሠራው አባል ክፍለ ሀገራት በመሬት ስፋትና በህዝብ ብዛት ተመጣጣኝ ሲሆኑ ነው። ለዚህም ብዙ ሀገሮችን ለመጥቀስ ይቻላል። አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ሕንድ … ወ.ዘ.ተ

 

2. የአዲስ አበባ ህዝብ የኤርትራ ዓይነት ፓርላማ ለምን የለም? ሲል፤ የደሴ ህዝብ ደግሞ ለምን የኤርትራ ዓይነት ጋዜጦች የሉም? የድሬዳዋ ህዝብ ደግሞ ኤርትራ ያለው ዓይነት የሠራተኛ ማኅበር ለምን አይቋቋምም? የጐንደር ህዝብ ደግሞ ለምንድን ነው የጐንደር ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪዎች ከሽዋ የሚመጡት? ክፍለ ሀገሩን ለማስተዳደር የሚችሉ የጎንደር ሰዎች ጠፍተው ነው ወይ? እያሉ መጠየቅ ጀመሩ።

 

3. የመካከለኛው መንግሥት በየዓመቱ ለኤርትራ 100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር የሚያደርገውን የባጀት ድጎማ፤ እንዲሁም ለትግራይ በየዓመቱ የሚሰጠውን 38 ሚሊዮን ብር ድጎማ የአንዳንድ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪዎች ገንዘቡ ከሚያስተዳድሯቸው ክፍላተ ሀገራት ተወስዶ ስለሚታደል ይቃወሙ ነበር።

 

እላይ የዘረዘርኳቸው ጥያቄዎች በጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች ከመሆናቸው በፊት የቀ.ኃ.ሥ. መንግሥት ፌዴሬሽኑን እንዲፈርስ አደረገ።

 

የኤርትራ “የቅኝ” ግዛትነት ጥያቄ፣

 

ኮሎኒያሊዝም አንድ ነፃ የነበረውን ህዝብ በቁጥጥር ሥር በማስገባት ህዝቡንና የአገሩን የተፈጥሮ ሀብት የሚበዘብዝ ሥርዓት ነው። በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ግንኙነት ግን እንደዚህ ዓይነት አልነበረም። ኢትዮጵያውያን የኤርትራን ህዝብ መሬቱን ቀምተውና የኤርትራን የተፈጥሮ ሀብት የተቆጣጠሩበት ጊዜ በጭራሽ አልነበረም።

 

እንዲያውም ኤርትራኖች የኢትዮጵያ ዜጎች ስለነበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ዕድል ተጠቅመው እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ በነፃ ይማሩ ነበር። በልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችም ያላንዳች መሰናክል ሠርተው እንዲኖሩና እንዲበለጽጉ፣ በልዩ ልዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የጦር ኃይሎች በማገልገል ርዕሰ ብሔር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮች፣ ጀኔራሎች፣ አምባሳደሮች፣ የክፍለ ሀገር አስተዳዳሪዎች ደረጃ… ወ.ዘ.ተ. የደረሱበት ወቅትም ነበር። ኮሎንያሊስም እንዲህ ያለ ዕድል አይሰጥም።

 

ጭቆና አንገፍግፎን ነው ለመታገል ቆርጠን የተነሣነው ቢሉ ኖሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው ቆሞ አብሮ ይታገል ነበር። ስለሆነም፣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለማስገንጠል ይረዷቸው ዘንድ ከሞቃድሾ መንግሥት ጋር ሳይቀር ቢተባበሩም የኢትዮጵያን ጦር ኃይሎች ማምበርከክ ፈጽሞ ስላልቻሉ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች እና በተማሪዎች ንቅናቄ በመጠቀም ጦርነቱን ወደ መሃል ሀገር ለማስገባት አቀዱ። Amrit Wilson, Women and the Eritrean Revolution (1991) በሚባል መጽሐፍ ጴጥሮስ ጊዮርጊስ የሚባለውን የሻዕቢያ ወኪል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል ገብቶ የመገንጠሉን ሴራ የሚያሰራጭ የነበረውን ካድሬ እና ወርቁ ዘርዓይን ቃል በቃል በመጥቀስ ደራሲዋ ያቀረበችውን ሪፖርት በትንሹም ቢሆን እንመልከት፤

 

“Ethiopian students took a long time to recognize the Eritrean question as a colonial question. In student demonstrations those who would bear the brunt of any attack were Eritreans. Ethiopian security agents were trying to appeal to the Ethiopian students that they were being used by Eritrean secessionists. Then the Eritreans decided at a secret meeting to support the student union but not be at the forefront of the leadership. The right to self-determination continued to be discussed by Ethiopian students. An Ethiopian student leader Waliling [Walleligne] discussed it openly in front of 2,000 students. Members of the EPRP were sent to the Sahel (Eritrea) to get training. Waliling and some others including an EPLF cadre tried to hijack a plane, but they were caught and murdered by security men. Martha Mebratu is one of the martyrs of the Eritrean struggle…”

 

የሻዕቢያ መሪዎች በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ስላላቸው፤ መርዘኛ የሆነ የሀገር ማጥፊያ ዘመቻ ሲያካሂዱ ኖረዋል። ኢትዮጵያን ታሪክ የሌላት ሀገር ለማስመሰል “የተፈጠረችው” በአፄ ምኒልክ ዘመን ነው ይላሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት ጎጃም ከመከፈታቸው በፊት ጎሙ ጎፋ፣ ባሌና ሲዳሞ እንዳልተከፈቱ ሁሉ፣ የደቡብ ክፍል የኢትዮጵያ አካል የሆነው በቅርብ ዓመታት ውስጥ ነው ይላሉ፣ ከ400 ዓመታት በፊት ኦጋዴን የኢትዮጵያ አካል እንዳልነበረ፣ ኦጋዴን ለኢትዮጵያ የተሰጠው በ1948 ዓ.ም. በእንግሊዞች ደባ ነው ይላሉ፣ የኤርትራ ህዝብ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ብሎ ታግሎ በራሱ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ጋር እንዳልተቀላቀለ ሁሉ፣ “ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነች” እያሉ ሲያማቱ ኖረዋል። ራሳቸው ለፈጠሩት ችግር ያቀረቡትም መፍትሔ ደግሞ የብሔረ ሰቦች እራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ድረስ ነው። ሥልጣን ሲጨብጡ ግን “ኤርትራ አንድ እና የማትገነጣጠል ሀገር ነች” ማለት ብቻ ሳይሆን አፋሩን፣ ኩናማውን፣ ቤን አምሩን፣ እና ሌላውን የምንታገልለት የሚሉትን መብት ነፍገው እንዴት አድርገው እንደሚረግጡት የአደባባይ ምሥጢር ነው።

 

ይህ መሠሪ ፕሮፓጋንዳ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ዕድገትን የሚያመጣ መስሏቸው የዋህ የሆኑት የኢትዮጵያ ተማሪዎች የሻቢያን የትግል ዓርማ አንግበው ለኢትዮጵያ መጥፊያ ዋና መሣሪያ በመሆን ትግሉን ማህል ሀገር ድረስ አስገብተው ይዋጉ ጀመር።

 

በዚህ መርዝ የተለከፉት ወያኔዎች አንጎላቸው ሙልጭ ብሎ ስለታጠበ የመመራመርና የማመዛዘን ችሎታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ እስካሁን ድረስ ከበሽታቸው ለመዳን አልቻሉም። ከጳጳሱ በላይ የሆንን ክርስቲያን ነን ብለው ትግሉን ቀጥለውበታል። የወያኔን ካድሬዎች አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት፣ መለስ ዜናዊ ከኢትዮጵያ ጥላቻ በስተቀር ሌላ የሚያስተምረው ነገር አልነበረም። የፈጠራ ወሬውን የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች የማይቀበሉት መሆኑን ሻዕቢያ ሲረዳ፣ ወያኔን ኮትኩቶ አሳድጎ “የኮሎኒያል” ጥያቄ መሆኑን አጥብቀን እናምንበታለን ስላለ አሰልጥኖና አስታጥቆ ከጎኑ በማሰለፍ 15 ዓመት ሙሉ ለኤርትራ መገንጠል ጠበቃ ሆኖ እንዲዋጋለትና ከሃያ ሽህ በላይ የትግራይ ልጆች እንዲያልቁ አደረገ። የትም ሀገር ያልሠራ የብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል ድረስ የሚባለው ለራሻ ብቻ የታቀደው የስታሊን ፖለቲካ ፕሮግራም Marxism ነው ብለው አሰራጭተው ህዝባችንን እርስ በርስ ሲያፋጁት ኖሩ።

 

ቀጥሎም ወያኔን አጅበው አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ማስገባት ብቻ ሳይሆን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስፈላጊውን ደብዳቤ ወያኔ እንዲጽፍ አደረጉ። የሁለቱ ድርጅቶች ግንኙነት በሐቅ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ጀርባዬን እከክልኝ እኔም የአንተን ጀርባ አካለሁ በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነበር። ሻብያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያስቀመጡትን አሻንጉሊት መንግሥት ሊያምኑት ስላልቻሉ፣ ሌላ የውስጥ መንግሥት አቋቋሙ። አህያ ጭነቱ ሲከብዳት እንደምትፈራገጥ ሁሉ ወያኔ የታዘዘውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ የሚሰጠው ትእዛዝ ከአቅሙ በላይ ስለሆነበት ሁለቱ በከፈቱት ጦርነት ተዋጉ። በከፈቱትም ጦርነት ምክንያት 100,000 የሚሆን ድሃ ገበሬ እና ወዝአደር በከንቱ ደሙን አፈሰሰ። በዚህም ጦርነት በኢትዮጵያ በኩል በአብዛኛው ያለቁት አማራዎች፣ ኦሮሞዎችና አፋሮች ነበሩ።

 

ከመሪዎቹ ጋር በቅርብ በሠራው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ አነጋገር “የወያኔ መሪዎች ዕውቀት የሌላቸው፣ ነገሮችን ግራና ቀኝ የማየት ችሎታ ፈጽሞ የሌላቸው፣ በጥቅም የተደለሉና ሀገራቸውን በማውደም ተግባር ላይ የተሠማሩ፣ በህልም የታያቸውን በነገታው አዋጅ የሚያደርጉ፣ የሹመት መለኪያቸው ዕወቅት፣ ችሎታ፣ ሥነምግባርና ሰብእና ሳይሆን ግለሰቦች ለመሪዎቹ ያላቸውን ታማኝነት ብቻ መመዘኛ ያደረጉ ናቸው። “መለስ ያሉ ሙያ ነክ የሆኑ መሥሪያ ቤቶች እንኳ ለባለሙያተኞች አልተተውም። የሚሠሩት ሁሉ ለአገሪቱ የወደፊት ኅልውና የማይበጅ መሆኑን እንኳ መገንዘብ አልቻሉም።”

 

አርባ ሁለት የዩኒቨርስቲ አስተማሪዎችን አባረው ከናይጀሪያ አስተማሪ የሚለምኑ፣ የኢትዮጵያ ሃኪሞች ደመወዝ ጨምሩልን በኑሮ ውድነት ምክንያት ብለው ሲጠይቁ ኢትዮጵያ ሃኪም አያስፈልጋትም፣ ወደፈለጋችሁበት ሀገር ለመሄድ ትችላላችሁ ብለው ህዝቡን ሆነ ብለው በበሽታና በሕመም እንዲያልቅ የሚያደርጉ ናቸው። ደርግ እየፎከረ ይገድል ነበር፤ ወያኔ ግን ይገድልና አብሮ ያለቅሳል፤ ብሎም ለሟች ሃውልት ይሠራና በበነገታው ያፈርሰዋል።

 

ከሻቢያ ባገኙት የጦር መሣሪያ በመመካት፣ የወያኔ መሪዎች ሑመራን፣ ወልቃይትና ጠገዴን ከጐንደር ወስደው፣ ራያ አዘቦንና አላማጣን ከወሎ ከነጠቁ በኋላ የሚያሥሩትን አሥረው፣ የሚገድሉትን ገድለው ኗሪውን ህዝብ በማባረር 650,000 የሚሆነውን የትግራይ ገበሬና ወታደር በእነዚህ መሬቶች ላይ አሥፍረው ይገኛሉ። የኢትዮጵያን መሬትና ኢኮኖሚ በ75 ኩባንያዎች አማካኝነት እነሆ ከተቆጣጠሩ በኋላ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት አድርገው በመበዝበዝና በመርገጥ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያም አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ለምና ታሪካዊ መሬት በማን አለብኝነት መንፈስ በመነሣሣት ለሱዳን መንግሥት አስረክበዋል። ይህ ድርጊት የታላቋ ትግራይ ሪፓብሊክን መቋቋም ሲያውጁና ሲገነጠሉ፣ ሱዳን ከጎናቸው እንዲቆም የተሰጠ ጉቦ ነው።

 

ሻዕቢያ የኮሎኒያል ጥያቄ የሚለውን የልብ ወለድ ታሪክ እንተወውና፣ ጦርነቱ ለምን 30 ዓመት እንደወሰደ የደረስኩበትን መደምደሚያ ላካፍላችሁ፤

 

1. ኤርትራ ውስጥ በቆለኛውና በደገኛው፣ በእስላምና በክርስቲያኑ፣ በጀብሃና በሻዕቢያ መካከል የተደረገው ጦርነት፤

2. ከአዲስ አበባ መንግሥት ጋር በተደረገው ፍልሚያ፤

3. ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ በወንዞችና ሃይቆች ላይ ግድቦችን እንዳትሠራ ለማደናቀፍ ሲሉ ጀብሓን እና ሻብያን አሰልጥነውና አስታጥቀው በኢትዮጵያ ላይ የማዝመታቸው ጉዳይ፤

4. ዓረቦች በብጥብጡ ተሳታፊ በመሆናቸው፣ እስራኤልን መላወሻ ለማሳጣትና ኤርትራን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው የቀይ ባሕርን የዓረቦች ባሕር ለማድረግ በነበራቸው ዕቅድ፤

5. አሜሪካና ሶቭየት ኅብረት ጥቅማቸውን ለማስፋፋት ሲሉ በአካባቢው ያራምዱት በነበረው የጥቅም ግጭት የተነሣ ጦርነቱ በጠቅላላ 30 ዓመት ወሰደ።

 

ፌዴሬሽን ተቃዋሚዎች

 

የተወሰኑ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ በመነሣሣት ህዝቡን እናቀራርብ ብለው ቢነሡ አራት ዓይነት መደበኛ ተቃውሞዎች ይገጥሟቸዋል፤

 

1. በሰው ልጅ ስሜታዊና ዝቅተኛ ባሕርይ የሚነግዱ ግለሰቦች፣ ሰነፎች፣ ተንኮለኞች፣ በአንድ ሰው ላይ የሚያዩትን ድክመት ሁሉ ሌሎችንም እንደዚሁ ናቸው ብለው የሚያምኑ፤ ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያውያንም ኤርትራውያንም ይገኛሉ፤

2. በሁለተኛ ደረጃ የሚቃወሙ፣ የህዝብ ድጋፍ የሌላቸው፣ የህዝብ አንድነት የሚያስፈራቸው፣ ከፋፍለህ ግዛን መመሪያ አድርገው ህዝብን ከህዝብ ጋር እያጋጩ የሥልጣን ዕድሜያቸውን የሚያራዝሙት የወያኔ መሪዎችና በግል ጥቅም የተያዙ ኅሊና ቢስ አገልጋዮቻቸው ይገኛሉ። የኢትዮጵያን እና የኤርትራን መቀራረብ የሚቃወሙበት ምክንያት የታላቋ ትግራይን እቅዳቸውን ስለሚያበላሽባቸው ነው።

 

ታላቋ ትግራይ ዓረና (ጀግናዋ) ትግራይ

 

አዶልፍ ሒትለር የጀርመን ቋንቋ የሚናገር ህዝብ ሁሉ የጀርመን ሪፓብሊክ አካል መሆን አለበት ብሎ ጀርመንን እንዳጠፋት ታሪክ የሚያነብ ሰው ሁሉ ለመገንዘብ ይችላል። የሒትለር ግልገል ደቀ መዛሙርት የሆኑት ፋሽስት ወያኔዎችም ደግሞ በልዩ ልዩ ምክንያት ትግርኛ ለመናገር የሚችለውን ሰው ሁሉ የታላቋ ትግራይ አካል መሆን አለበት ብለው ያምናሉ።

 

ቋንቋ የመገናኛ፣ የጥናትና ምርምር መሣሪያ ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ የጣሊያንኛ ቋንቋ ቢመናገሩ ብቻ ጣሊያን ነው ማለት አይደለም። ወለጋ ውስጥ የሚኖሩ ትግርኛ ተናጋሪ ኦርሞዎች ቢኖሩ ትግራይ ክልል ውስጥ መግባት አለባቸው ብሎ የሚያስብ ሰው ቢኖር በትክክል የማሰቡ ጉዳይ አጠያያቂ ነው። የታላቋ ትግራይን ፍልሥፍና አስተናጋጆች አስተሳሰብ ብንሄድ ኩናማው፣ ሳሆ፣ አፋር፣ ጥልጣል፣ አገው፣ የጠገዴ ጠለምትና ወልቃይት ጐንደሬዎች፤ የወሎ አካል የሆኑት አላማጣ፣ አሸንጌ፣ እና ቆቦ ሁሉ ትግሬዎች ናቸው ተብለው የታላቋ ትግራይ አካል እንዲሆኑ በወታደር ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ። የወያኔ መሪዎች የታላቋ ትግራይ ሪፓብሊክን መሥርተው ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ሽር ጉድ በማለት ላይ ናቸው።

 

“የጀግናዋ ትግራይ/የታላቋ ትግራይ” ሪፓብሊክ አራማጆች ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡- ዓረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘርዓጽዮን፣ ስብሐት ነጋ፣ አባይ ፀሐየ፣ ሥዩም መስፍን፣ መለሰ ዜናዊ፣ አለቃ ፀጋየ፣ ስየ አብርሃ እና የወልቃይትን ህዝብ ባርኖስ(ትል) ብሎ የሚጠራው ገብሩ አሥራት ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በሥልጣን ላይ ባይኖሩም “የታላቋ ትግራይን” ዕቅድ እንቃወማለን ብለው የተናገሩት ምንም ነገር የለም።

 

የትግራይ ሪፓብሊክን ነፃነት ሲያውጁ ዕርዳታ ለማግኘት ሲሉ ታሪካዊ የሆነውን የኢትዮጵያን መሬት ቆርጠው ለሱዳን አስረክበዋል። መቀሌ፣ አኩስምና ሑመራ ዓለም አቅፍ የሆኑ የአይሮፕላን ማረፊያዎች ሠርተዋል፤ መቀሌንና ገዳሪፍን የሚያገናኝ መንገድ በመሠራት ላይ ነው። የኢትዮጵያን አየር ኃይል በሙሉ ወደ ትግራይ አዛውረው የትግራይ አየር ኃይል ብለው ለመጥራት ዕቅድ አላቸው። ትልልቅ ግድቦች፣ ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች፣ ፋብሪካዎች፣ መኖሪያ ቤቶች … ወ.ዘ.ተ. ለነፃይቱ ትግራይ ድጋፍ እንዲሆኑ በመቋቋም ላይ ናቸው።

 

መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ምኒስትርነቱን ለቆ ጊዜውን ለትግራይ ሪፓብሊክ ምሥረታ ክዝይ ብቻ ሙሉ በሙሉ ቢያውል አያስገርምም። ወያኔዎች የኢትዮጵያንና የኤርትራን በፌዴሬሽን መደራጀት ይቃወማሉ፤ ምክንያቱም “የታላቋ ትግራይን” ህልም የሚጻረር ስለሆነ ነው። በእነርሱ ዕቅድ ከሄድን ኤርትራ የሚባለው ሀገር ይጠፋል። ትግርኛ የማይናገረው ቤንአምር፣ አፋር፣ ብሌን … ወ.ዘ.ተ. የት ሊገባ ነው? ትግርኛ ተናጋሪ ነው ተብሎ ከሚረገጠው የጐንደር ህዝብ ውስጥ ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ትግርኛ ተናጋሪው 5% ብቻ ነው። 95% አማርኛ ተናጋሪ ነው። ትግርኛውንም የተማረው ከኤርትራኖች ነው። ከትግራይ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ስለዚህ ይህን ህዝብ በግድ ትግሬ ለማድረግ ማመልከቻ በትግርኛ ማስገባት አለብህ፣ የሥራ ፍለጋ ደብዳቤ በትግርኛ መጻፍ አለብህ፣ ትምህርት ቤት ለመግባት ትግርኛ መማር አለብህ እየተባለ ሲረገጥ ይገኛል። ሁለት ሰዎች ተካስሰው ፖሊስ ጣቢያ ወይንም ፍርድ ቤት ቢሄዱ አጥፊው የትግራይ ሰውም ቢሆን ወልቃይቴው ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ይቀጣል።

 

ኩናማውም፣ ሳሆም፣ አፋሩም፣ ጥልጣሉም፣ አገውም በምንም መንገድ ትግሬ ሊሆን አይችልም። የአላማጣ፣ አሸንጌ፣ ቆቦ ህዝብ የትግራይ አካል የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራው የትግራይ ህዝብ፣ ለኢትዮጵያ ነፃነት ደሙን ሲያፈስና አጥንቱን ሲከሰክስ የኖረው የወያኔዎችን የልጆች ቁማር በምንም መንገድ አይደግፍም።

 

3. በሦስተኛ ደረጃ የሚቃወሙ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ አንድነት ጥቅማቸውን የሚያበላሽባቸው የሩቅና የቅርብ ኃይሎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል ዓረቦችን ብንወስድ ታሪካቸው እንደሚያሳየው ሁሉ ሃይማኖታቸውን የመስፋፊያ መሣሪያ አድርገው ብዙውን ሀገር ዓረብ አድርገውት ይገኛል። የእኛን አካባቢ ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ በመጣር ላይ ናቸው። እስካሁን ድረስ ሊያንበረክኩን ያልቻሉበት ምክንያት በህዝባችን አንድነትና ብርታት ነው።

 

አሁንም ቢሆን የእኛን ቀዝቃዛ ዓየር፣ ውሃና ለም መሬት በጣም ይፈልጋሉ፤ ግብፅና ሱዳን በወንዞቻችን ላይ እንዳንጠቀም ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። አሁን ግን ለሥልጣን ያበቁት ቅጥረኛ መንግሥት ስላለ ችግራቸው ተቀንሶ ይገኛል። አባቶቻችንና መሪዎቻችን መከራቸውን አይተው ያቆዩትን ከሱዳን ኩታ-ገጠም ሆኖ የሚገኘውን ታሪካዊ መሬት መለሰ ዜናዊ በራሱ ፈቃድና አነሳሽነት ለሱዳን አስረክቦ ይገኛል። ይህን ደን እና የዱር አራዊት የሞላበት ለም መሬት ለማስመለስ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ መሰዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርበታል። ለዓለም ፍርድ ቤት ክስ ማቅረብም ጦርነትም አማራጭ ሆነው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

 

በአሁኑ ወቅት በተለይም የምዕራቡ ዓለም ከዓረቦች የቤንዚን ብዝበዛ ነፃ ለመውጣት ቆርጦ ስለተነሣ ዓረቦቹ የአፍሪካን አህጉር አተኩረው ማየት ጀምረዋል። ሶማሊያ የእነርሱ የመተላለፊያ በር ብቻ ነች። ዓላማቸው ኤርትራና ኢትዮጵያ ነው። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ከተባበረ ግን የዓረቦች የመስፋፋት ህልም ቅዠት ሆኖ ይቀራል።

 

ኢትዮጵያን እንደ ቅኝ ግዛት አድርጎ የሚበዘብዛት የወያኔ ጥርቅም ቡድን ህዝቡን በቋንቋ ከፋፍሎ ማፋጀቱ አልበቃው ስላለ፤ አሁን ደግሞ እስላሙንና ክርስቲያኑን ለማጫረስ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል። ይህም ድርጊት የኤርትራን ሰላምና ፀጥታ የመጠበቁ ተግባር አሳሳቢ ሁናቴ ላይ ስለሚጥል ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የመተባበሩን ጥያቄ በጥብቅ ማሰብ ይኖርባቸዋል።

 

የወደቦች ጉዳይ፣

 

አንዳንድ በአስተሳሰባቸው ውስን የሆኑ ኢትዮጵያውያን ከኤርትራ ጋር ያሉትን ታሪካዊ ሰንሰለቶች ሁሉ በጥሰው፤ ስለአሰብ ወደብ ብቻ የተቆረቆሩ ይመስላል። ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ችግሩን በትክክል ካለመገንዘብ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። የኢትዮጵያ ሰላም፣ ዕድገትና ነፃነት ከጠቅላላው የመካከለኛው ምሥራቅና በቀይ ባሕር ላይ ከሚነሡ ግፊቶች ተነጥሎ አይታይም። በዚህ ሁናቴ ላይ ስለ ዓሰብ ወደብ ብቻ ማውራቱ ትርጉም የለውም።

 

የዚህ ዓይነት የአስተሳሰብ ድህነት በብዙ ኤርትራውያንም ላይ ነግሦ ይታያል። አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ ከኤርትራ የምትፈልገው “ወደብ” ብቻ ነው ሲሉ እነሆ 16 ዓመት አለፈ። ስለሆነም በዚሁ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በአሰብና ምፅዋ ወደቦች አልተጠቀመችም። በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚዋ አልወደቀም። ፖርትሱዳን፣ ጅቡቲ፣ በርበራ፣ ሞምባሳ፣ ሶማሊያ ደግሞ ሰላም ስታገኝ ኢትዮጵያ በሞቃድሾ፣ በቦሶሶ እና በኪስማዮ ወደቦች መጠቀም ትጀምራለች።

 

ሌሎች ኤርትራውያን ደግሞ ኢትዮጵያ በምፅዋና በአሰብ እንድትጠቀም ይፈልጋሉ። በኋላ ግን በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የቀረጥ ተፅእኖ በማምጣት አገሪቱ ከአላት የመክፈል አቅም በላይ የሆነ ታሪፍ በማውጣት ኢትዮጵያን ለማምበርከክ ህልም ነበራቸው። ይኸ ሁሉ ጤናማ የሆኑ ሰዎች አስተሳሰብ ሊሆን አይችልም። ወደፊት ቀርቶ ግራና ቀኝ እንኳ የማየት ችሎታ የላቸውም።

 

የሚገርመው ነገር፤ ጣሊያኖችና እንግሊዞች ኤርትራን ጥለው ከመሔዳቸው በፊት ያቀረቡት ሪፖርት አለ። ይኸውም፣ “ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ካልሆነች ዕድሏ ውስን ነው” ብለው ያቀረቡትን ሪፖርት በጥሞና ቢመረምሩት ኖሮ እንዲህ ካለ የተሳሳተ አስተሳሰብ ውስጥ አይወድቁም ነበር። የሲዳሞን ቡና ለምሳሌ ኢትዮጵያ በምፅዋ በኩል ለዓለም ገበያ ላቅርብ ብትል፣ ቡናዋ ዋጋ ያጣል። ለምን ቢባል ምፅዋ ቡናውን ለማድረስ የሚከፈለው የትራንስፖርት ወጭ ብዙ ስለሚሆንና ከቡናው ዋጋ ላይ መጨመር ስላለበት የቡናውን ዋጋ በጣም ከፍ ስለሚያደርገው ገዥ ያጣል። በጅቡቲ፣ በበርበራ፣ በሞቃድሾ እና በሞምባሳ መጠቀም ያዋጣል።

 

የኮንፌዴሬሽን ግንኙነት

 

የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት በኮንፌዴሬሽን ይጀመር የተባለውን እኔ በበኩሌ አጥብቄ ነው የምቃወመው። ኮንፌኢዴሬሽን የመንግሥታት ልል የሆነ የማኅበር ክለብ ነው። ሀገሮቹ አባልነቱን ካልፈለጉ ጥለው ለመውጣት ይችላሉ። ታሪክ እንደሚያሳየው ሁሉ በኮንፌዴሬሽን ግንኙነት አመርቂ ውጤት ያለው ሥራ አይሠራም። በአሜሪካ ተሞክሮ አልሠራ ስላለ ወደ ፌዴሬሽን የሄዱበት ዋናው ምክንያት ይኸው ነበር።

 

በ1950-1952 ዓ.ም. በወጣው ሕገ-መንግሥት መሠረት ሁለቱ ሀገሮች በፌዴሬሽን እንዲዋቀሩ የተደረገበት ብዙ ምክንያቶች ስለቀረቡ ነበር። የጅኦግራፊ አቀማመጥ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ፀጥታ አጠባበቅ አስፈላጊነት፣ የሁለቱ ህዝቦች ባሕልና ታሪክ አንድነት፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በኢኮኖሚ የተሣሠሩ የመሆናቸው ጉዳይና ለኢትዮጵያ ወደቦች አስፈላጊነት … ወ.ዘ.ተ። የተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁሉ አሁንም እንዳሉ ናቸው። የፀጥታው ችግር እንዳውም ተባብሶ ይገኛል። ፌዴሬሽኑ ለምን እንዳልሠራ ለመነጋገር እንችላለን። የነበረውን ፌዴሬሽን አቃንቶ ለመሥራት ሲቻል ወደ ኮንፌዴሬሽን የምንሄድበት ምክንያቱ አይታየኝም።

 

ከ1991-1993 ድረስ የነበረውን ሁናቴ እንደ “ኮንፌዴሬሽን” እንኳ ብንቆጥረው ኢትዮጵያ ጠባቂ መንግሥት ስለአልነበራት ተዘረፈች። አገሩ ውስጥ የነበሩ ክሊንኮች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ፋብሪካዎች፣ ባንኮች፣ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቶች፣ የሐረር ሚሊታሪ አካዳሚ፣ የጥናትና መመርመሪያ ትልልቅ መሣሪያዎች እንኳ አልተረፉም፤ የጎነደር ከተማ ኤሌክትሪክ ጀኔረተር፣ ከተቆፈረ መሬት ውስጥ የሚቀመጡ 25 ትልልቅ የቤንዚን ማከማቻ ዲፖዎች (ጋኖች)፣ የግድብ መሥሪያ ዕቃዎች ሁሉ ተዘርፈዋል። ማታ ማታ መብራት ይጠፋና በ20-30 ትልልቅ የዕቃ መጫኛ መኪናዎች የተዘረፈው ዕቃ ሁሉ ተወስዷል። የት እንዳለ መሪዎቹ እንዲነግሩን መጠየቅ አስፈላጊ አይደለም። የተወሰደው የትግራይ ሪፓብሊክን ለማቋቋም እንዲረዳ ነው። የኢትዮጵያን ብር የሚመስል የውሸት ገንዘብ በማተምና ለገብያ በማቅረብ የተዘረፉ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ብዙ ናቸው። የኤርትራ ነጋዴዎች የኢትዮጵያን ቡና በብር እየገዙ ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ የቡና ዛፍ የማይታይባት ሀገር ለዓለም ገበያ ቡና አቅራቢ ከሆኑ ሀገሮች ውስጥ አንዷ ሆና የተቆጠረችበት ወቅትም ነበር። ስለዚህ “ኮንፌዴሬሽ” የሚባል የአስተዳደር ሥርዓት በኢትዮጵያ ህዝብ በኩል ምንም ዓይነት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

 

ኤርትራ በ1952 ዓ.ም. በነበራት ሕገ-መንግሥት መሠረት መተዳደር ስለምትችል፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን የሀገራችንን ነፃነት የሚያስጠብቅ፣ የህዝባችንን መብት የሚያስከብርና የሀገራችንን ልማት የሚያፋጥን አዲስ ሕገ መንግሥት ያስፈልገናል።

 

ፌደሬሽን፣

 

ማንም ሳይፈልገው በውጭ ኃይሎች አመራርና ድጋፍ በሥልጣን ኮረቻ ላይ የተቀመጠው ቅጥረኛ መንግሥት የጫነብንን የዘር ክልል በአዋጅ ካስወገድን በኋላ ከዚህ በፊት የነበሩትን ታሪካዊ ክፍላተ ሀገራት ማለት፤ ወለጋ፣ አሩሲ፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ትግራይ፣ ወሎ፣ ሲዳሞ፣ ባሌ፣ ከፋ …. ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉትን በፌዴሬሽን ማዋቀር ይኖርብናል።

 

ክፍላተ ሀገራቱ በመሬት ስፋት፣ በህዝብ ቁጥርና በተፈጥሮ ሃብት ስለሚመጣጠኑ አንዱ ሌላውን በቁጥጥሩ ሥር የሚያስገባበት ሁናቴ ሊኖር አይችልም። ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን የሚያስተዋውቁት ከተወለዱበት ክፍለ ሀገር ጋር እንጂ ከ”ዘር” ጋር ስላልሆነ፣ ይህ ዓይነት አደረጃጀትና አሠራር የህዝቡን ታሪክና ባሕል ስለሚያከብር ፌደሬሽኑ ቋሚነትና ጠቃሚነት ይኖረዋል።ኤርትራ የፌዴሬሽኑ አባል እንድትሆን እንጋብዛለን። ሰንደቅ ዓላማ፣ ፓርላማዋ፣ የውስጥ አስተዳደር ነፃነቷና መብቷ እንደተጠበቀ ይሆናል። በፌደራል ፓርላማውና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተገቢ ቦታዋን ትይዛለች። ሁለቱም ሀገሮች አንድ ዓይነት የመገበያያ ገንዘብ፣ የውጭ ጉዳይ ተግባርና የመከላከያ ኃይል ስለሚኖራቸው የሁለቱ ሀገሮች የመከላከያ ኃይልና ዲፕሎማሲ አገልግሎት ማዋሃድ ተገቢ ይሆናል።

 

የፌዴሬሽኑን አባላት የሚያገለግል አንድ ማዕከላዊ ባንክና ሁሉም የሚገበያዩበት አንድ ዓይነት ገንዘብ ይኖራቸዋል፤ የሁለቱም ዓየር ኃይል፣ የምድር ጦርና የባሕር ኃይል ተዋቅረው በአንድ ዕዝ ሥር ይሆናሉ ማለት ነው።

 

በውጭ የሚከተሉት ፖሊሲና የውጭ ንግድ ተዋህዶ በአንድ ማዕከል ይካሄዳል። በ1952 ዓ.ም. በወጣው ሕገ-መንግሥት መሠረት፣ አሰብና ምፅዋ በፌዴራል መንግሥት ይተዳደራሉ። ባሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በውጭ ወደቦች ስለምትጠቀም የምታወጣው ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነው ወጭ ወደ አሰብና ምፅዋ ተዘዋውሮ ወደቦችን ለማስፋፋት፣ ሥራ ለመፍጠርና ለኤርትራ መንግሥት ገቢ የሚሆን ገንዘብ ማመንጫ ሊሆን ይችላል። የሁለቱ ሀገሮች የንግድ መርከቦችና የንግድ አውሮፕላኖችም በአንድ ማዕከል ውስጥ ሆነው በቦርድ ሊተዳደሩ ይችላሉ።

 

ኢትዮጵያ ለኤርትራ ከተሞችና ለኢንዱስትሪ የሚሆናት መብራትና ጋዝ ለማቅረብ ትችላለች። በዚህም ላይ ሁለቱ ወገኖች ተወያይተው ስምምነት ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። እንደተለመደው የኤርትራ ከብቶች ለግጦሽ ኢትዮጵያ ሊመጡ ይችላሉ፤ ኤርትራ የምትፈልጋቸውን የእርሻ ውጤቶች ከኢትዮጵያ ገዝታ በፋብሪካዎቿ ልትጠቀም ትችላለች። የኢትዮጵያም ገበያ ሰፊ ስለሆነ የፋብሪካዎችን ውጤቶች ለመሸጥ ጥሩ ዕድል ያጋጥማታል።

 

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የአንድ ሀገር ዜጎች ስለሚሆኑ ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደድሮው ለመኖርና ለመሥራት ምንም ዓይነት እንቅፋት አይኖርባቸውም። ሁለቱ ሀገሮች በትምህርት፣ በጤና ጥበቃ፣ በእርሻ፣ በመገናኛ፣ በደን ተከላና ጥበቃ ተመሳሳይ የሆነ ፖሊሲ ሊከተሉ ይችላሉ።

 

የፌደራል ፓርላማው፣ የሕግ መወሰኛ (Senate) እና የሕግ መምሪያ (House of representatives) ይኖረዋል። የህዝብ ወኪሎች በሕግ መምሪያው ውስጥ ሲሠማሩ፣ የክፍለ ሀገራት ተጠሪዎች ደግሞ በሕግ መምሪያው ውስጥ ሊቀመጡ ይችላሉ። የዓባሎቹ ዓይነትና ብዛት የሕግ አርቃቂዎች ከተወያዩበት በኋላ ለህዝብ ቀርቦ ውሳኔ ሊያገኝ ይችላል። የፌደራሉ ፓርላማ አሥመራ ወይንም አዲስ አበባ ወይንም ሌላ ተስማሚ ከተማ ውስጥ ሊሰበሰብ ይችላል። ሁለቱ ሀገሮች እየተወያዩ ጅቡቲ፣ ፑንትላንድ፣ ሶማሊላንድ እና ሶማሊያ ደረጃ በደረጃ የፌደሬሽኑ አባል የሚሆኑበትን መንገድ ለማዘጋጀት ይችላሉ።

 

አሜሪካ ትልቅ የሆነው አንድነቱን ጠብቆ በመኖሩ ነው። ምዕራብ አውሮፓና ምሥራቅ አውሮፓ ያሉ ሀገሮች እነሆ ዛሬ አንድነት እየመሠረቱ ነው። አንዳንዶቹ ታሪክ እንደሚያሳየው ሁሉ ሦስት አራት ጊዜ በከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ገብተው የተሰቃዩ ስለሆነ በመካከላቸው ሰላምና ትብብር እንዲሰፍን ከማንም የበለጠ የጦርነትን አደጋ የተገነዘቡ ይመስላል። ለዚህም ፈረንሣይንና ጀርመንን ለመጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ከእንዲህ ያለ ችግር ውስጥ ገብቶ አያውቅም።

 

ኤሽያም፣ ደቡብ አሜሪካም፣ አፍሪካም በበኩላቸው ውህደትን እያፋጠኑ ይገኛሉ። አንድ ሀገር ብቻውን ሆኖ የማደጉና የመበልጸጉ ጉዳይ አስቸጋሪ እየሆነ ስለሄደ የሀገሮች ውህደትና መቀላቀል የዘመኑ አይነተኛ የመልሚያና የማደጊያ መሣሪያ ሆኖ ተገኝቷል። አሜሪካ፣ ሶቭየት ኅብረትና ቻይና ያደጉበት ለውጭ ንግድ ዝግ የሆነ ሥርዓት (Autarchy) በራስ መተማመንን እና የውስጥ ገበያን የማስፋቱን ተግባር ያስቀድማል። በዘር ፖለቲካ እንደታወሩት የወያኔ መሪዎች አስተሳሰብ ሳይሆን ትንንሽ የመሬት ስፋት ያላቸው ሀገሮች በተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት ውስን ናቸው። በብዙ የማምረትና የመሸጥ ዕድል economies of scale ስለማይኖራቸው በሰፊው ኢንዱስትሪን የመገንባት አቅማቸው ውስን ነው። ስለዚህ ሦስት ወይንም አራት የሚሆኑ ሀገሮች መዋሃድ ይኖርባቸዋል። በአሁኑ ሰዓት ሶቭየት ኅብረት፣ ቻይናና አሜሪካ የተከተሉትን የልማት ስልት እንጠቀም ቢሉ ምናልባት ህንድና ብራዚል ይችሉ ይሆናል። ሌሎች ሀገሮች ግን ችግር ላይ ይወድቃሉ። የመሬት ስፋትና የህዝብ ብዛት ችሎታ ካላቸው መሪዎች ጋር ሲጣመሩ ዕድገትና ልማትን ለማፋጠን ይቻላል።

 

የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችን ብንመለከት ግን የምናየው ዕድገት ሳይሆን ዕልቂት ነው። ውኅደትና ልማት ሳይሆን ጦርነት፣ በሽታ፣ ዝርፊያ፣ ረሃብ፣ ስደት፣ ድርቅ፣ ጭቆና፣ ግፍ፣ በደል፣ ሞት … ወ.ዘ.ተ ሆኗል የህዝብ ዕጣ።

 

ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌዴሬሽን ከተዋቀሩ በኋላ የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ተራ በተራ የፌዴሬሽኑ ዓባል እንዲሆኑ መጋበዝ ይቻላል። ጅቡቲ፣ ሶማሊ-ላንድ፣ ፑንትላንድና ሶማሊያ ተገንጥለው ብቻቸውን ሊኖሩ አይችሉም። የኢትዮጵያንና የኤርትራን ፌዴሬሽን ጠቀሜታ ተገንዝበው የፌዴሬሽኑ ዓባል እንዲሆኑ ማሳመን ይቻላል። ስለሆነም ይህንን የተቀደሰ ተግባር በሥራ ለማዋል ይረዳ ዘንድ ሽንጣቸውን ገትረው የሚታገሉ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን አለሁ ማለት ይኖርባቸዋል። ትምህርታቸውንና ዕውቀታቸውን ለዚህ ይተቀደሰ ተግባር ቢያውሉት በዓለም ህዝብ ፊት መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን፣ ከበሬታን እናገኝ ነበር። የኤርትራና የኢትዮጵያም ህዝብ ከድህነትና ልመና ወጥቶ በሁለት እግሩ ቆሞ አንገቱን ቀና አድርጎ ለመራመድ ይችል ነበር።

Administrative Map

Tigray Administrative Wereda
 
Republic of Greater Tigray

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!