የአባኪያ ማስታወሻ፤ አባኪያ ተመልሷል**

ትናንት ለጠበቆቻችን፣ ዛሬ ደግሞ ለዳኞቻችን

“ፍትህን ፍለጋ፣ ፍትህን አሰሳ”

“ፍትህን ፍለጋ፣ ፍትህን አሰሳ” የሚቀጥለው የቴዲ አፍሮ ዘፈን አልበም መጠሪያ ይመስለኛል። “ቃሊቲ ቃሊቲ” ሊለውም ይችላል። መቼም ዶ/ር ብርሃኑ ወይም ኢንጂነር ኃይሉ ወይንም ብርቱካን ሚደቅሳ ቢዘፍኑ አያምርባቸውም። ነገር ሁሉ ለበጎ ነው የሚለውን የሐዋርያውን ቃል ካመንበት፤ ምናልባትም የቴዲ አፍሮ መታሰር ለበጎ ነው። ከዚህ ቀደም ጽሑፌን ያቆምኩበትን አልዘነጋሁም። ወደዚያ እመለሳለሁ። ለጊዜው ግን ፈተና ላይ ከርሜ ጠፋሁኝ። ኢትዮጵያ የተውኩትን/ያቋረጥኩትን ትምህርት እዚህ ቀጥያለሁ። ይሄ የጀመርኩትን ትምህርት ምዕራብና ምስራቅ ጫፍ ካላቸው፣ ከምዕራብ ጫፍ ምስራቅ ጫፍ የመሄድ ያህል ዞሬ ነው የጀመርኩት። መቶ ሰማኒያ ዲግሪ መዞር የሚሉት አይነት ነገር። ቀድሞ እማር የነበረው የcivil law ሥርዓትን መሰረት ያደረገውን የኢትዮጵያን ሕግ ነበር። አሁን ወደ common law ዞሬያለሁ። ሕግን - ሕግ ከሚከበርበት ሀገር ስትማሩት እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ። አሁን የምማረው በተለይ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ አሜሪካና ካናዳ የሚከተሉት የሕግ ሥርዓት ቀደም ሲል ምናልባትም ከአንድ ሺህ ዓመታትም በፊት ጀምሮ የተወሰኑ ውሳኔዎችን መሰረት ያደረጉ፣ መርሆዎችና ሕግጋት በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚፈጠርና ለሚገኝ ጉዳይ በተመሳሳይ መልኩ የሚወሰኑበት የሕግ ሥርዓት ነው።

 

ካናዳ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነበረች። ማለቴ ካናዳን የሠራቻት እንግሊዝ ነች። በግልጽ በሕግ እስካልተቀየሩ ድረስ እንግሊዝ የምትከተላቸው የcommon law ሕግጋት በሙሉ ካናዳ ውስጥ ይሰራሉ። ያ ማለትም ካናዳ ራሷን ችላ መንግሥት የሆነችው ገና በቅርቡ ቢሆንም፤ ከእንግሊዝ ጋር ባላት ትስስር የተነሳ የካናዳ የሕግ ሥርዓት ብዙ መቶ ዓመታትን ወደኋላ ይጓዛል። የሆነ ሆኖ ለዛሬው ጽሑፌ ያንን ሁሉ በማተት ጊዜ ሳላባክንባችሁና ገና አንደኛ ዓመቴን መጨረሴ መሆኑን እየጠቆምኳችሁ ብዙ ዝርዝር ሳትጠብቁ ወደ አንድ ከካናዳ የሕግ ሥርዓት ያደነቅኩትና የቀናሁበት ሕግ ትምህርት ቤትም ሳትገቡ የምትረዱት ነገር እነሆ። የካናዳዊያን የፍትህ ሥርዓት ህዝቡም በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ያለው እምነት የካናዳዊያን የዳኝነትን ነፃነት ትንሽ አጋንኜው በሰማይ ብቻ ያለ ዳኝነት ይመስላል። ባለፈው ሰሞን እኛ አካባቢ የመጣውን ያንዱን ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጨምሮ፣ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ባለሟሎች በተለያየ አጋጣሚ ወደ ውጭ አገር እየወጡ ያደጉት አገራትን የዳኝነት ሥርዓት ለመመልከት ዕድል አግኝተው ሳለ፤ ለምን በመንፈሳዊ ቅናት የአገራቸው ዳኝነት እንደነዚያ ያደጉ አገሮች ባይሆንም፤ በትንሽ በትንሹ እንኩዋን ነፃ እንዲሆን እንደማይጥሩ አይገለጥልኝም። እነሆ ዝርዝር ለኢትዮጵያና ለኢህአዴግ ዳኞች።

 

ትናንት ለጠበቆቻችን፣ ዛሬ ደግሞ ለዳኞቻችን

ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች በነቂስ ጽፌ ነበር። አሁን ደግሞ ትንሽ ጠበብ አድርጌ ለኢትዮጵያ ዳኞች መጻፍ ሻትኩ። ማለቴ ተገደድኩ። እንደችግር መጻፍ የሚቀል ነገር እንደሌለ ተናግሬ ነበር ባለፈው። እንደፍትህ ማጣት የሚያቃጥል ነገር ደግሞ የለም። ፍትህ ከፍትህ መቅደስ ወጥታ ከግለሰቦች ጡንቻ ላይ ስትኮፈስ፣ ከግለሰቦች ኪስ ውስጥ ስትዝናናና፣ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እየመነዘሩ ሲከብሩባት፣ ከፊታችን ሲፈጠፍጧት እንደማየት የሚያቃጥል ነገር የለም። ሰው ካንተ የበለጠ ኃይልና ጠብመንጃ ስላለው ብቻ ያሻውን ሲያደርግ፣ የፈለገውን ሲናገርና ሲተፋብህ፣ መለስ ብለህ ፍትህና ፍርድ የምትጠይቅበት ስታጣ፣ ይባስ ብሎም ፍትህን ይሰጡ፤ ፍትህንም ያሰፉ ዘንድ የታጩ ዳኞች፣ ፍትህን ሲያሽመደምዱ እንደማየት የሚያስለቅስ ምን ነገር አለ? ለነገሩ ያሳሰበኝ ያቃጠለኝም ይሄ ግለሰቦች ወይም አምባገነኖች ድንገት በየመንገዱ ፍትህን ወደራሳቸው እጅ ወስደው የሚተረክኩት ነገር አይደለም። ይሄ ፍትህ ይገኝበታል ተብሎ፣ ተለፍቶ ተንከራቶ የሚታጣው የሚዛባው ፍትህ ነው። ፍትህን በትንሽ በትንሹ ከካናዳ እስከ አራዳ እንዳስሳለን። ማለቴ እስከልደታ፤ ከስዬ አብርሃ እስከ ቴዲ አፍሮ መሆኑ ነው።

 

የቴዎድሮስ ጉዳይ በራሱ ላያስደንቅ፣ ላይበርድ ላይሞቅ ይችላል። ነገር ግን በቴዎድሮስ የደረሰ በሌሎች ፍትህ አጥተው በሚጉላሉ ሰዎች የሚደርሰው ፍትህ እጦት ምሳሌ ነው። ባለፈው ሣምንት እዚህ እከተማችን ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ንግግር እንዲያደርግ ጋብዘነው፣ ስለቴዲ አፍሮ መታሰር ተጠይቆ፣ እስሩ ፍትሃዊ አለመሆኑንና ገና ጥፋተኛ ይሁን አይሁን ባልታወቀበትና ባልተረጋገጠበት ሁኔታ እንዲሁም፣ ቢሆንም እንኩዋን በአደጋ እንጂ ሆን ብሎ የሰው ሕይወት ባላጠፋበት ሁኔታ ይሄ ዕድሜ ልኩን ስለፍቅርና ስለአገር በመዝፈን የሚታወቅ ዘፋኝ፣ ነፃነቱን መገፈፉ፣ የዋስ መብት መከልከሉም አግባብ እንዳልሆነ ተናግሯል። የቴዲ አፍሮ ጠበቃና ቤተሰቦች፣ እሰሩ ፖለቲካዊ ትርጓሜ እንዳይሰጠው ይማጸናሉ። የሆነ ሆኖ እነሱ ወደዱም ጠሉም፣ ሁላችንም ግን እስራትና የዋስ መብት መነፈግ እንደፍትህ ሥርዓቱ አንድ መለኪያ ምሳሌ አድርገን ከመውሰድ እንመለስም። በየወረዳው በየቀበሌው ተመሳሳይ ዕጣ የሚደርሳቸውን እየተዘዋወርን መመዝገብ በማንችልበት በዚህ ዝግ ሥርዓት ውስጥ፣ ቴዲና ቤተሰበቹ ተቀበሉትም አልተቀበሉትም፤ የእሱን ጉዳይ ተንተርሰን የፍትህ ስርዓታችንን ከመገምገምና ከመተንተን አንመለስም።

 

እንደመነሻ - መነሻን ማወቅ ጥሩ ነውና

ሁለት መነሻዎች አሉኝ። አንዱ በቴዲ አፍሮ እየደረሰ ያለው፣ ወይንም ካለፈውና ካየነው ተነስተን ሊደርስበት ይችላል ብለን የገመትነው። ሌላው በዶ/ር ያዕቆብ የተጻፈ ቁጭት። ዶ/ር ያዕቆብ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ፣ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለፍትህና ሕግ የነበረው ክብር ከፍተኛ ሲሆን የዳኝነት ሥራ ደግሞ በጣም የተለየና እጅግ በጣም የተከበረ ከመሆኑ የተነሳ፣ ለዳኞች የነበረው አመለካከትም የተለየና እነሱን ከፍጡራን ከፍ የሚያደርግ ነበር ብለዋል። ቀጥለውም በጽሑፋቸው፣ የዳኝነት ሥራ እንደ መንፈሣዊ ተግባር ተቆጥሮ ከዳኛው ነፍስ ጋር ትስስር እንደነበረው ከመታመኑ የተነሳ፣ ፍርደ ገምድል ዳኛ በቀጥታ ወደ ገሃነም እንደሚወርድም ይታመን ነበር። ያሁሉ ግን ጥንት ነው። ዛሬ ዛሬ ግን ይላሉ ዶ/ር ያዕቆብ፣ “በአገራችን የፍትህ ሥርዓቱ ተሰብሯል ማለት ይቻላል። ለሕግ የነበረው ከበሬታ እየተሸረሸረ፣ ሕጉ ነፃነቱን ተገፍፎ፣ በፖለቲካ ተቀፍድዶ ህዝቡ ለፍትህ ያለው እምነት እየተሟጠጠ ነው።” እነሆ የሰው ልጅ በፍትህ ላይ ያለው እምነት የተሸረሸረ ዕለት እናንተ በዳኝነት ምግባር ላይ የተቀመጣችሁ ሰዎች ሁሉ ተጠንቀቁ። እንደ ፍትህ ሥርዓት መሰበር የሰውን ልጅ ቅስም የሚሰብር ነገር የለም። የፍትህ ሥርዓት ከተሰበረ፣ ምርጫው ምርጫ አይሆንም፣ ንግዱ ንግድ አይሆንም፣ ፍርዱ ፍርድ አይደለም፣ ሥልጣኔው ሥልጣኔ አይሆንም፣ እምነቱ ሁሉ እምነት አይደለም።

 

በቀድሞው መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የደረሰውን እንመልከት። የዛሬ ስንት ዓመት አካባቢ፣ አስር ዓመት ከታሰሩ በኋላ ነፃ ናችሁ ተብለው የተለቀቁ ባለሥልጣናትን በሬድዮ ሰምቻለሁ። ከተፈረደባቸው ዓመታት በላይም የታሰሩ ሰዎችን ጉዳይ ሰምቻለሁ። ሰው ያለፍትህ አስራ አምስት ዓመት ሲታሰር፣ ካስራ አምስት በኋላ ነፃ ነህ ሲባል፣ በእውኑ ነፃ ነውን? የኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓት እንደዚህ ነው። ስለዚህስ ማን ያውቃል፣ ቴዎድሮስም አምስት ስድስት ዓመት ታስሮ ነፃ ነህ ተብሎ ቢለቀቅ፣ በእውኑ ነፃ ነውን። ይሄ የዳኝነትን ነፃነት የሚፈትሽ ጽሁፍ ያተኮረው፣ በተለይ በፖለቲካዊ ምክንያቶች በሚታሰሩና ከፍርድ ቤቶች ፍትህን በተነፈጉ፣ ጉዳዮችና ባለጉዳዮች ላይ ነው። ቴዎድሮስ ካሳሁን ለምን ታሰረ? ሳይሆን፤ በዚህ ጉዳይ ከተከሰሰበት ከዛሬ ዓመት ከምናምን ገደማ ጀምሮ፣ በሃምሳ ሺህ ብር ዋስ ተለቆ ሲገባ ሲወጣ እየተመለከትነውና፣ የፍትህ ሥርዓቱን ጥሎ፣ አምልጦ ሊሄድ እንደሚችል ዓቃቤ ሕጉ ባላስረዳበት፣ ፍርድ ቤቱም ዓቃቤ ሕጉን ባላፋጠጠበት ሁኔታ፣ ለምን የዋስትና መብት ተከለከለ ነው? ተከትሎም፣ ሌሎች ደሃ ኢትዮጵያዊያንም ተመሳሳይ ዕጣ ይደርሳቸው ይሆንን? የሚለው ጥያቄ መጣብኝ።

 

ፍትህ በካናዳ እና ፍትህ በኢትዮጵያ - ስለሰው መብት መጠበቅ

ማንኛውም በካናዳ የሚኖር ሰው መብቱ በሕግ የተጠበቀና፣ ያለሕግ መብቱ ሊገፈፍ የማይችል መሆኑን ያረጋግጣል፤ የካናዳ ሕገ መንግሥት አንድ አካል የሆነው የካናዳ መብቶችና ነፃነቶች ሰነድ፣ አንቀጽ አንድ። ሆን ብሎ የተደረገ ይሁን አጋጣሚ፣ ካናዳም ኢትዮጵያም/ኢህአዴግም አሁን በሚመሩበት ሕገ መንግሥታቸው ውስጥ፤ የሰውን ልጅ መብቶች የሚያስጠብቁ ተመሳሳይ አንቀጾች አላቸው። ከሕጋዊ ነፃነት ጋር በተያያዘ፣ ሰው ነፃነቱ ቀድሞውንም በሰውነቱ ብቻ የተረጋገጠ ነውና ነፃነቱን ሊያረጋግጥ እስር ቤት ሊከርም አይገባም ነው ነገሩ። የኢህአዴግ ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ ኢህአዴግ ሕገ መንግሥቱን የቀዳባቸው አገራት ድንጋጌ እንደዚያ ነው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ያላልኩት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ስለመሆኑ ስላለመሆኑ አስቤ አይደለም። የራሱን የኢህአዴግን ቋንቋ ለመጠቀም ነው። የደርግ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ካልሆነ፣ የኢህአዴግን ሕገ መንግሥት የኢህአዴግ ብንለው ኢህአዴግን ራሱን አይከፋውም ብዬ አስቤ እንጂ። የሰውን ልጅ መብት ስለመጠበቅ ሳስብ፣ በሕይወቴ ሁሌም ከማይረሱኝና አሁንም ድረስ ተፎካካሪ ያላገኘሁላቸው ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ስለ ሞት ቅጣት ካስተማሩኝ ነገሮች ውስጥ ትዝ የሚለኝ፣ የሞት ቅጣት ተከራካሪዎች/ተቃዋሚዎች ከሚያቀርቡት ተቃውሞ ውስጥ ዋነኛው ተቃውሟቸው፣ የሞት ፍርድ irreversible መሆን ነው። በሞት የተቀጣን ሰው፣ ጥፋቱ ሐሰት ሆኖ ቢገኝ በምን እንመልሰዋል? አስራ አምስት ዓመት ታስሮ ምንም ጥፋት ያልተገኘበትን ሰውስ በምን እንክሰዋለን? ለዚያውም በኢትዮጵያ።

 

በተለይ እንደኢትዮጵያ ባለች ጠንካራ የፍትህ ሥርዓትና የወንጀል ምርመራ ልምድ በሌለባት አገር፣ ፍትህን በጊዜና ባግባቡ አለማግኘት ውጤቱ ልክ የለውም። ቤተሰብ ይበተናል፣ ልጆች ይበተናሉ፣ አስራ አምስት ዓመቱ ብቻ ሳይሆን መጪው ሕይወትም ይበላሻል። ወደ እስር ቤት መመለሱ ሳይቀል አይቀርም። ሦስት ዓመት በሶርያ እስር ቤት የማቀቀው ካናዳዊ ማሀር አራርም ያለው ይኸንኑ ነው። ከመስከረም አንዱ የኒውዮርክ መንታ ህንፃዎች ውድመት በኋላ የአሜሪካ መንግሥት የተጠራጠራቸውን ዐረብ ሙስሊሞች ሁሉ በገፍ ያስር ነበርና፣ ይሄ የሶርያ ተወላጅ የሆነ በዜግነቱ ግን ካናዳዊው ኢንጂነር ማሀር አራር ኒው ዮርክ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ከካናዳ መንግሥት ፖሊስ ኃይል በደረሳቸው ጥቆማ ይታሰርና፣ መርምረው ምንም ሲያጠቡት፣ ወደ ካናዳ ከመመለስ ይልቅ ወደ ሶሪያ ይሰዱታል። በሱዳኖች በኢህአዴግ የሚፈለግን ግለሰብ አንገት ይዞ ወደ አዲስ አበባ እንደመወርወር ቁጠሩት። ከስንት ትግል በኋላ ከሶሪያ ተለቆ ሲመጣ፣ በብዙ ጉትጎታ መርማሪ ኮሚሽን ይቋቋምና የካናዳ ፖሊስ ባለሥልጣናት የተሳሳተ መረጃ ለኤፍ.ቢ.አይ. አሳልፈው በመስጠታቸው፣ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፣ የጠበቆቹን ዋጋ ሳይጨምር፣ አስር ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ይወሰናል። ያ ጥሩ ቢዝነስ የነበረው ኢንጂነር ማሀር አራር ግን ያጣሁትን ነፃነትና መልካም ዝና ምንም ገንዘብ አይተካውም ነው ያለው። በነገራችን ላይ ይሄንኑ ተከትሎ የካናዳው ፖሊስ ኮሚሽነር ሥልጣኑን ለቋልም። የመርማሪውን ኮሚሽን የመሩት የቀድሞ ዳኞችና ጠበቆች ናቸው። ከምርጫ 97 በኋላ በኢትዮጵያ የደረሰውን አፈናና ግድያ እንዲመረምር እንደተቋቋመው ኮሚሽን መሆኑ ነው። ይሄ እዚህ የተለመደ አሰራር ነው። እዚህ ግን የምር ነው። የኮሚሽኑ ምርመራ ውጤት ያለአንዳች ማሻሻያ ተቀባይነት ያገኛል። ዳኛ እዚህ አገር፣ የቀድሞውም ያሁኑም፣ የፍትህ ቋት ናቸው ተብሎ በሰፊው ይታመናል።

 

ወደ ፍርድ ቤት ስንመለስ፣ ዳኞችም ይቁረጡ፣ ልክ እንደካናዳ

የፍርድ ቤቶች ዋነኛ ሚና ሕግን መተርጎምና የመንግሥትን ቅጥ ያጣ ያልተገደበ ሥራ መቆጣጠር/መገደብ ነው። ሥልጣን ካልተገደበ ያባልጋል። አሁን ባለጌዎቹንና ባለጊዜዎቹን እንደሚያባልገው ማለት ነው። የሆኖ ሆኖ ትኩረቴን የማደርገው በእኩያና አንጋፋ ዳኞች ላይ ነው። መቼም ሰው እያወቀ ሲመጣ፣ በአካባቢው ተሸንፎ፣ አንድም ስጋው ያለዚያም ውጪያዊ ጫና አስጨንቆት ፍትህን ሊያዛባ ይችል እንደሆን እንጂ፣ ማንም ከመነሻው መልካም ዳኝነትን አይወድም ብለን ለመናገር አንደፍርም። ገንዘብና ፍትወት ወይንም የግል ስሜት አንበርክኮት ፍትህን የሚያዛባ፣ እሱ ከዚህ ጽሑፍ ወሰን ውጪ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ከመንግሥት ሊመጣ በሚችለው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት አንድም ፈርቶ፣ አልያም ሥልጣን ፈልጎ ወይንም በጥቅም ተደልሎ ፍትህን ሊያዛባ ስለሚችለው ስጋ ለበስ ዳኛ ነው። ፍትህን ስለማጣት የሚጠየቀው ወይንም ፍትህን ሊያመጣ የሚችለው መንግሥት ብቻ አይደለም። ግለሰብ ዳኞችም ቆራጥ መሆን አለባቸው። ዳኝነት አለአድልዎና ያለወገንተኝነት፣ ፍትህን ለማገልገል ምለንና ተገዝተን የምንገባበት ሙያ እንደመሆኑ መጠን፣ ምንም እንኩዋን ገዢው ፓርቲ በራሱ ርዕዮተ ዓለም የተጠረበ የዳኝነት ፍልስፍና ሊጭንብን ቢጥርም፣ እኛ ግን ዘወትር ያመንበትንና የማልንበትን ፍትህ ከመስጠት ወደ ኋላ ማለት የለብንም።

 

ፍትህ በካናዳ እንደዚያ ነው። በተለይ ሰው ነፃነቱንና ሰብዕናውን የሰውነት ክብሩን የሚነካ ቅጣት የሚያስከትሉ ክሶች ላይ ሁሉ መንግሥት የተከሳሾችን መብት እንዲያስጠብቅ ሕግም ፍርድ ቤቱም ያዛል። ጠበቃ ማቆም ብቻ አይደለም። ዓቃቤ ሕግ ክሱን ፍጹም እንዲያረጋግጥ ይገደዳል። እንዲህ ዝም ብሎ ያለአግባብ አግበስብሶ ፍርድ ቤት ማጎር የለም። በዚህ ረገድ የካናዳም የኢህአዴግም/የኢትዮጵያም ሕገ መንግሥታት የሚሉት አንድ ነው። ለምሳሌ ስለተከሰሱ ሰዎች መብት የሚናገረው የኢህአዴግ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20፣ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ባፋጣኝ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፣ እስኪፈረድባቸውም ድረስ ንጹኅ እንደሆኑ እንዲታሰብ፣ አግባብ ባለው ፍርድ ቤት ጉዳያቸው እንዲታይ፣ እንዲሁም ራሳቸውን እንዲከላከሉ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንም አገላብጠው እንዲፈትሹ፣ በማናቸውም ሕጋዊ መንገድ ራሳቸውን ሊከላከሉ የሚችሉበት ዕድል ካለ፣ ያን ዕድል እንዲጠቀሙ ስለማስቻል ይደነግጋል። ካናዳም ከዚህ የተለየ ወይም የበለጠ መብት በሕገ መንግሥቷ አላስቀመጠችም።

 

በካናዳ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ያላቸው መብቶች በኢህአዴግ ሕገ መንግሥት ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ልዩነቱ በካናዳ ፍርድ ቤቶቹና ዳኞቹ እነዚህን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ነፍስ ሲዘሩባቸው፣ በየዕለቱ ሊያስጠብቁ ሲተጉ ስናይ፣ በኢትዮጵያ ግን መብቶቹ ባብዛኛው ገና ጥሬና በትላልቅ ፖለተካዊ ክሶች እንዳየነው ዳኞቻችን በቁርጥ የሚያልፏቸው ናቸው። መቼም ይሄንን ለማለት ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት የተፈረዱ ፍርዶችን ሁሉ አገላብጬ ማየት አይገባኝም። አንድ ሰው በፖለቲካዊ ክስ ምክንያት ታስሮ ለአስራ አምስት ዓመት ፍርድ ካላገኘ፣ ያ የፍትህ ሥርዓት ዶ/ር ያዕቆብ እንዳሉት ሰባራ ነው። የፍርድ ሥርዓት ደግሞ የሚሰበረው በመንግሥት ብቻ ሳይሆን መንግሥትን በሚያግዙት ዳኞችም ነው። በነፕሮፌሰር መስፍን በነዶ/ር ብርሃኑ የደረሰውን ስንመለከት፣ በቴዎድሮስም ይሄ እንደማይደርስ ምንም ዋስትና የለም።

 

ወደ ቴዲ ስንመለስ፣ ገንዘቡን ማሰር ሲቻል እሱን ለምን?

ቴዎድሮስ ካሳሁን ታዋቂ ዘፋኝ ስለሆነ ለሱ ሲባል የሚቀለበስ ሕግ አይኖርም። ግን ደግሞ እስኪፈረድበት ድረስም ንጹኅ ስለሆነ በተቀነባበረ ክስ ወህኒ መውረድና መታጎር የለበትም። ነፃነት በገንዘብ ሁሉ አይተካም። የቴዎድሮስ ነፃነት በቴዎድሮስ ገንዘብ ሁሉ አይተካም። ነፃነቱን ካጣ ገንዘቡንም ራሱንም ያጣል። ገንዘቡን ቢያጣ ግን ራሱን ካላጣ ይተካዋል። ዳኞች ሆይ! በተለይ እንደኢትዮጵያ ባለች፣ የዳኝነት ሥርዓቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ጫና ነፃ ስለመሆኑ አከራካሪ (በግሌ አከራካሪ ሳይሆን ዳኝነቱ በሙሉ ከኢህአዴግ ቁጥጥር የወጣ ነው ብዬ አላምንም) በሆነበት አገር፣ ዳኞች ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በርግጥም ትልቁና ዋነኛው የፍትህ መሰረትም በመሆኑ ጭምር፣ ዓቃቤ ሕግ ላይ ማነቆውን ጠበቅ ማድረግ አለባችሁ። ልብ እንበል ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያስፈለገበት ምክንያት መንግሥት ወይም የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሻቸው ብድግ እያሉ ኢ-ፍትሃዊ የሆነና ጥንቃቄ የጎደለው እርምጃ እንዳይወስዱ፤ ይሄ ቢከሰት ግን የፍርድ ቤቱም ሚና የነሱን እርምጃ መግራት ነው። ያልተገራ መንግሥትና ያልተገራ ፈረስ አንድ ናቸው። ሁለቱም ይረጋግጣሉ። ገደል ይከታሉ።

 

ዳኞች ሁልግዜም በተለይም ከሰው ልጅ መሰረታዊ መብትና ነፃነት ጋር በተያያዘ፣ የመንግሥትን እርምጃ በጥርጣሬና በጥንቃቄ ማየት አለባቸው። መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት እሱ ራሱ ነው። እንጂ ዳኞች የመንግሥት እርምጃ ትክክል ነው፣ የሚቃወም ካለ እሱ ያረጋግጥ ብለው መነሳት የለባቸውም። ለምሳሌ የቴዎድሮስ መታሰርን አስፈላጊነት ማረጋገጥ፣ በእስር ካልቆየም ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ማሳየት ያለበት ራሱ ዓቃቤ ሕግ እንጂ፣ ገና ለገና ዋስትና ሊያስከለክል የሚችል አንቀጽ ስለጠቀሰ ብቻ አንቀጹን እንደወረደ መተግበር ትክክል አይደለም። ለዚያ ለዚያማ ፍርድ ቤትም ባላስፈለገ ነበር።

 

የዛሬ ስንት ዓመት አካባቢ አቶ መለስ ዳኞችን ሰብስበው ስለሕግ አተረጓጎም ማብራሪያ ሰጡ የሚል ዜና አንብቤ ነበር። በዚህ በካናዳ ሕገ መንግሥትና ዳኝነት ታሪክ ውስጥ ግን፤ በመሰረቱ ዳኞችና ሥራ አስፈጻሚው ወይንም ሕግ አውጪው፣ ሊነጋገሩ የሚችሉት በአዋጅ ብቻ ነው። ሕግ አውጪው ሕግ አውጥቶ ሕጉን በዳኞች ዘንድ እንዲደርስ ካደረገ በኋላ፣ ስለአተረጓጎም ሌላ ስብሰባና ሌክቸር መስጠት ጣልቃ የመግባት ያህል ነው። ዳኞች ሕጉን እንዴት መተርጎም እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይንም ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ፣ መመሪያ ወይንም መግለጫ ከሰጣቸውማ መጀመሪያውንም ዳኝነቱን የፍትህ ሚኒስቴር ቅርንጫፍ ማድረግ ነው እንጂ፣ ነፃ ፍርድ ቤት ማቋቋም የሚባል ነገርም ባላስፈለገ። በመሰረቱ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና የካናዳ ሕገ መንግሥት የሰውን ልጅ መብት ከማስጠበቅ አንጻር ያላቸው፣ አቀራረብ ብዙ የተራራቀ እንዳልሆነ ከላይ ጠቅሻለሁ።

 

እኛና እነሱ እንደገና፤ ልዩነታችን የትየለሌ

የሰውን ልጅ መብት ከማስከበር አንጻር የኛን አይነቱን ሥርዓት የሚከተሉ ሀገሮችም ይሁኑ የእንግሊዝና አሜሪካንን ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች ያላቸው ልዩነት ብዙ አይደለም። ሁለቱም ሥርዓቶች ለምሳሌ የሰው ልጅ ያለአግባብ መታሰር እንደሌለበትና ነፃ ፍርድ ቤት ጥፋተኝነቱን እስኪወስን ድረስ ንጽኅናው የተረጋገጠ እንደሆነ ያምናሉ። ልዩነቱ እኛ ይሄንን ሕግ የሚያስፈጽም ነፃ ፍርድ ቤት የለንም፣ እነሱ ነፃ ፍርድ ቤትና በጭንቅላታቸው የሚመሩ ዳኞች አሏቸው። ዋናው ነጥቤ መንግሥት ነፃ ፍርድ ቤት እንዳይኖር የቻለውን ሁሉ ቢያደርግም፣ የግለሰብ ዳኞች ሚናም ወሳኝነት አለው ለማለት ነው። ግለሰብ ዳኞች በሕሊናዬ ተመርቼ ይሄንን ብወስን ከሥራዬ እባረራለሁ ብለው ከፈሩና የግለሰቦችን መብት ለማስከበር ብቻ ሳይሆን የዳኝነትንም ቅድስና ለማስጠበቅ ደፋር ካልሆኑ፣ ከፈሩና ከተንጰረጰሩ፣ መንግሥት ከሚያሳድርባቸው ጫናም ባሻገር የነሱም ፍርሀትና አድርባይነት ሚና አለው ባይ ነኝ።

 

ለምሳሌ እነፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ1993 ዓ.ም. በተከሰሱበት ክስ የተከሰተው ጉዳይ የተወሳሰበና የተደበቀ አይደለም። ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ በምኑም በምኑም ክስ እያጓተተ የግለሰቦችን ነፃነት የሚያውክ ጉዞ ሲጓዝ ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩን በጊዜ እንዲጨርስ ጫና ማሳደርና መገሰጽ አለበት። አለበለዚያ ዓቃቤ ሕግ ያሻውን ጊዜ ወስዶና ተዝናንቶ ሥራውን የሚሠራ ከሆነ በፖለቲካዊ ምክንያትና በአድልዎ የሚከሰሱ ሰዎች ሕጋዊ ላልሆነ የክስ ሂደትና ውጥንቅጥ ይጋለጣሉ። የዘር ማጥፋት ፈጽማችኋል የተባሉ የቀድሞ መንግሥት ባላሥልጣናት ፍትህ ከተባለ ፍትህ ለማግኘት አስራ ምናምን ዓመታት ፈጀባቸው። የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሚያዚያ ወር 1993 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የሐሰት "የማወናበጃ" ወሬ በመንዛት ለአመፅ አነሳስተዋል በሚል የከሰሳቸው ፕሮፌሰር መስፍንም ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ ሰባት ዓመት ፈጀባቸው። በሰባት ባስራ አራት ዓመታት የሚለካ ፍትህ ፍትህ አይደለም። በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ የቀረበ የሪፖረተር ዘገባ ፕ/ር መስፍን ከቀረበባቸው ክስ በነፃ ተሰናበቱ ይላል። መጀመሪያ የትኛው ክስ ነው ብዬ ግር ብሎኝ ነበር። የዛሬ ሰባት ዓመት እኛን ያሰደደው ክስተት መሆኑን ስገነዘብ እጅግ በጣም አልገረመኝም። በዚህ እንኩዋንስ ሰባት ዓመት በማንኛውም መለኪያ ቢመዘን ሰባት ወርም በማይፈጅና ቅንነትና የፍርድ ቤቱ ሀቀኝነት ቢታከልበት ወዲያውኑ መፈታት በሚችል ጉዳይ ተከሳሹ ሰባት ዓመት ሙሉ ፍትህ ሳያገኙ መቆየታቸው የፍርድ ቤቶቻችንና የፍትህ ሥርዓታችንን ሁኔታ የሚጠቁም ነው።

 

ደርሰን ካናዳን አንሆንም፣ ቢሆንም ቢሆንም

በዚህ በካናዳ እንደዚህ አይደለም ነገሩ። እኔም የካናዳን ተሞክሮ ሳነሳ ደርሰን እንደካናዳ እንዲያደርገን ሳይሆን፣ ዞሮ ዞሮ ሕጎቻችንና ዲሞክራሲያችንን ከምዕራቡ ዓለም ስንቀዳ ለመድረስ የምንጠረው የሥልጣኔ ጫፍ እነሱን ስለሆነና ምናልባትም የካናዳ የፍትህ አተያይ ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነ ለመጠቆም ነው። በካናዳ ምክንያታዊ በሆነ ግዜ ውስጥ የመዳኘት መብት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው። የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ በወሰናቸው ውሳኔዎች እንደጠቆመው፣ አንድ ክስ ለፍርድ ሳይቀርበ ከስድስት እስከ ስምንት ወራት በላይ ከዘገየ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት እንደተጣሰ ተቆጥሮ ክሱ እንዲወገድ ወይም ወደጎን እንዲደረግ ያዛል። ይሄ ባንድ በኩል ምን ያህል ፍርድ ቤቶች ለዚህ መብት ቦታ እንደሚሰጡ ሲጠቁም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ሥራውን ባግባቡ እንዲወጣ ያለበትን ከፍተኛ ጫና ያመለክታል። እንጂ እንደኛ ልቅ አይደለም። አንዳንዴ የኛ አገር ፍርድ ቤቶችና ዳኞች የፍትህ ሚኒስቴር ቅርንጫፎች ይመስሉኛል። ወይንም ሥራ አስፈጻሚውን ወይንም ዓቃቤ ሕግን ለማረቅ የተቋቋሙ ሳይሆን፣ ዓቃቤ ሕጉን ለመርዳት የተቋቋሙ አካላት ይመስሉኛል።

 

አንድ በሲያትል የሚገኝ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ የሕግ ባለሙያ በዚህ ጉዳይ ላይ ስንጫወት የዓቃቤ ሕግ ሥራው እውነትን መፈለግ ነው እንጂ ሰዎችን እንደምንም ተሟሙቶ ማስቀጣት አይደለም። በቂም በቀልና እልህ ተነሳስቶ ጥፋተኝነታቸው ያልተረጋገጠባቸውን ሰዎች እስር ቤት በማጎር አይደለም የዓቃቤ ሕግ ውጤታማነት የሚለካው። ከተከላካይ ጠበቆች ጋር ተባብሮ በመሥራት እውነትን በመፈለግ እንጂ። እኔ የኢትዮጵያ ዓቃብያነ ሕግ እውነትን ለመፈለግ ሳይሆን እንደምንም ተጋግጠው ሰዎችን ለማስቀጣት ሲጥሩ ብመለከት አይደንቀኝም። ፍርድ ቤቶች ወይም ዳኞች ግን፣ የሰውን መብትና ነፃነት በማስጠበቅ ፋንታና ዓቃቤ ሕግ ጉዳዮቹን አሳማኝ በሆነ መልኩ እንዲያረጋግጥ ከማስረዳት ፋንታ፣ ዓቃቤ ሕግ የሚለውን ሁሉ እንደ ወረደ ተቀብለው ጥፋተኝነቱ ያልተረጋገጠበትን ወይም ከእስር መልስ በሌላ መልኩ ለምሳሌ በከፍተኛ ዋስ አስገድዶ ከፍርድ ቤት ማቅረብ የሚቻልን ሰው እስር ቤት ሲያጉሩ፣ እርግጥም እነኝህ ሰዎች የቆሙት፣ ዓቃቤ ሕግን ለመርዳት ነው ያሰኛል።

 

ከእስር መልስ፣ ከነፃነት ወዲያ

ሰውን ማሰር exception ነው። ሁልጊዜ አይከሰትም። ባለፈው ሰሞን ብዙ አሜሪካኖች ሚስቱን ገድሏል ብለው የሚያምኑትና ነገር ግን አስራ ሁለት ሰዎች በሚገኙበት ጁሪ፣ ነፃ የወጣው ኦ ጄ ሲምፕሰን በመሳሪያ አስገድዶ ንብረት ሊዘርፍ ሲል ተያዘ። ነገር ግን በገንዘብ ዋስ ተለቀቀ እንጂ፣ አገኘንህ ብለው ነጭ ዳኞች የዋስ መብት አልነፈጉትም። በቅንጅት አመራር የደረሰውን ታስታውሳላችሁ። ለወራት በየምርጫው ዘመቻ በየቴሌቪዥኑ ጣቢያና በየሬዲዮ ጣቢያው ሲናገሩ በነበሩት ነገር ነው ታስረው የነበረው። በሰዓቱ ከዋስ መብት መንፈግ ጀምሮ በማስረጃ አቀራረብ ሂደት ላይ እንዲሁም በመከላከያ ሂደት ውስጥ፣ ዳኞቹ ከዓቃቤ ሕግ ጎን ቆመው፣ ሲከራከሩና ተከሳሾቹን ሲሞግቱ ለነበረ፣ እንደውም በፍርድ ወንበር ከመሰየማቸው በፊት ፍትህ ሚኒስቴር ተገናኝተው የተመካከሩ ያስመስልባቸው ነበር። በየትኛውም ዘመናዊና ዲሞክራሲያዊ ሀገር ፍርድ ሂደት ውስጥ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያለአንዳች ምክንያታዊ ጥርጣሬ ማረጋገጥ ሲገባው ወይም ሲጠበቅበት፣ ተከሳሽ ወይም ተከላካይ ጠበቆች ግን የሚጠበቅባቸው ትንሽ ጥርጣሬን ብቻ መፍጠር ነው። ቅንጣት ታህልም ጥርጣሬ ባለበት ሁሉ፣ በተለይም የሰው ልጅ ነፃነትና ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ቅጽበት ሁሉ፣ ተከሳሾች በነፃ መለቀቅ አለባቸው። በካናዳ እንደዚያ ነው። በኢትዮጵያ ግን ተገላቢጦሹ ይመስላል እውነቱ።

 

አሁን ኢትዮጵያ ትመራበታለች የሚባለው የኢህአዴግ ሕገ መንግሥት በመግቢያው ላይ እንዲህ የሚሉ ወርቃማ ሕግጋትን አስቀምጧል። በሕጋዊ አገዛዝ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት በመቁረጥ፣ ይህም የሚሳካው የግለሰቦችና የቡድኖች መሰረታዊ ነፃነትና መብት ሲጠበቅ መሆኑን አምነን፣ (አሁንም ይሄ መሰረታዊ መብትና ነፃነቶች የሚለው ቃል ተደግሟል) ይህንን ሕገ መንግሥት አጸደቅን ይላል። የካናዳ ሕገ መንግሥት ራሱ እንደዚህ ያለ ወርቃማ መግቢያ የለውም። በዚህ ብቻ አልተገታም። የካናዳ የነፃነትና መብቶች ቻርተር (ሰነድ) ባካተታቸው ሰላሳ አራት አንቀጾች፣ በካናዳ የሚኖሩትን ማናቸውንም ሰዎች መብት የሚያስጠብቅና ከመጣስ የሚከላከሉ መብቶችን አስቀምጧል። የኢህአዴግ ሕገ መንግሥትም ከዚያ ባልተናነሰ እንዲያውም በሰፋ መልኩ፣ የግለሰቦችን መብትና ነፃነቶች የሚቀበሉና የሚከላከሉ ሕግጋትን አስቀምጧል። ስለዚህ በካናዳ እነዚህ መብቶች ለመከበራቸው፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ላለመከበራቸውና ወረቀት ላይ ለመቅረታቸው ምክንያቱ ምንድነው ብለን ስንጠይቅ፣ ልዩነቱ ያለው ነፃና ፍትሃዊ ፍርድ ቤቶች ወይም የፍርድ ሥርዓት የመኖሩ ላይ ነው። የካናዳ ፍርድ ቤቶች፣ ዕድሜ ልካቸውን፣ የካናዳው የመብትና ነፃነቶች ሰነድ ከወጣም በኋላ ይሁን ከዚያ በፊት፣ የግለሰቦችን መብት ሲከላከሉ፣ መንግሥት ወይንም የመንግሥት አካላት የግለሰቦችን መብት የሚጥስ ድርጊት ሲፈጽሙ ወይንም ሕግ ሲያወጡ፣ የለም አይሆንም እያሉ ከሥራ አስፈጻሚውና ሕግ አውጪው ጋር እየተፋለሙ ነው እዚህ የደረሱት። ይሄ የሆነው ዳኞች በሕግ ነፃነት ስለተሰጣቸው ብቻ ሳይሆን፣ የተሰጣቸውን መብት ለማስጠበቅም ቁርጠኛና ዝግጁ ስለሆኑ ነው።

 

እንደመዝጊያ፣ እንደምክርም

መቼም ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው ብላችሁ አትተርቱብኝም እንጂ፣ በዳኝነት ሙያ ላይ የተሰማራችሁ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊም ዕጣ ፈንታና መጪ ዕድል መወሰን የምትችሉት እናንተ ናችሁ። ከዚህ ቀደም በጻፍኳቸው ጽሑፎች ላይ፣ እዚህ ውጭ አገር ቁጭ ብዬ ይሄን አድርጉ ይሄን ብትፈጥሩ ማለት እንደማይገባና ያንን ብዬ ብገኝ ግን በቅን ልቡና እንዲታይልኝና፣ እንደየተጨባጩ ሁኔታ እንዲተረጎምልኝ ተማጽኜ ነበር። አሁንም ያ ከግምት ይግባልኝ። በፍርሃት የማይኖርና ነፃ የሆነ፣ ወገናዊ ግን ያልሆነ የፍርድ ሥርዓት ከመሰረትን፣ ምርጫችን ምርጫ፣ ንግዳችን ንግድ፣ ግንኙነታችን ግንኙነት፣ ፍትሃችን ፍትህ፣ ሥልጣኔያችንም ሥልጣኔ ይሆናል። ይሄንን ደግሞ ለማድረግ ኢህአዴግ ተሳስቶም ይሁን አውቆ፣ ካወጣው ሕገ መንግሥት ላይ አስቀምጦታል። በየትኛውም ዓለም ባሉ ዴሞክራሲ አለባቸው በምንላቸውም ፍርድ ቤቶች ሳይቀር እንደተደረገው፣ በተለይም የካናዳ ሕገ መንግሥታዊ ታሪክ እንደሚያሳየው መንግሥት ዘወትርም የራሱን ሥልጣን ለማብዛት፣ ሕጉም እንደፈለገው እንዲተረጎምለት ለማድረግ ከመጣር ወደኋላ አይልም። በተለይ እንደኢህአዴግ ባለ በጠብመንጃ ሥልጣን በያዘና ሕገ መንግሥትንና ፍርድ ቤቶችን፣ ፍትህንና ሕጋዊ አገዛዝን ከማስፈኛ መሣሪያነት ይልቅ የራሱን ሥልጣን ለማራዘሚያና የዓለም መንግሥታትን ለማታለያ መሣሪያነት ከሚጠቀም መንግሥት፣ ፍርድ ቤቶች በተለይ በፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ የምር ነፃ እንዲሆኑ ይፈልጋል ብሎ መመኘት የዋህነት ነው። ስለዚህ ቀሪው እዳ ያለው፣ በማናቸውም መንገድ ፍርድ ቤት ገብተው ከሚሠሩ ዳኞች ላይ ይሆናል ማለት ነው። ደፋር፣ ቆራጥ፣ የሾማቸውን መንግሥት ለመሞገት የማይፈሩ ዳኞች ካላፈራንና፣ ነፃ ፍርድ ቤት የማቋቋሙ ሂደት ካልተሳካልን፣ ዲሞክራሲ እንደሸወደን፣ ሰብዓዊ መብትም እንደራበን እንኖራለን።

አባኪያ ነኝ፣ ከካናዳ

 

** (ይሄ ጽሑፍ የተጻፈው ኢትዮጵያ ለሚታተመው እንቢልታ ጋዜጣ ነውና በዚያ ማዕቀፍ አንብቡት)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!