ያሬድ ክንፈ ከስዊድን

ሠላምና ጤናህ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ባለቤትህና ልጅህሳ? ... እኔ አያልቅበት የተመሰገነ ይሁን አማን ነኝ። ሀገር እንዴት ነች? ... (‘ሀገር’ ስልህ የድሮ ፍቅረኛህን አይደለም፤ ኢትዮጵያን እንጂ) ... በእኔ በኩል ስደትና ስዊድን ሃሪፍ ናቸው፤ ለክፉ አይሰጡም።

 

የዛሬው ጦማሬ የሚያተኩረው ከሰሞኑ ትኩስ ዜና ጋር በተያያዘ በተለይ በስደት የምንገኝ ዘሮችህ (ኢትዮጵያውያን) ከምንሳተፍባቸው በኢንተርኔት የመወያያ መድረኮች አንዱ በሆነውና “ዋርካ” በተሰኘው ላይ ነው። እንደሰማኸው ተስፋ አለኝ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ‘ግንቦት ሰባት ንቅናቄ’ የተሰኘ ፓርቲ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ሊያቋቁሙ መሆኑ ተዘግቦ ነበር። ዜናው በኢንተርኔት እንደተሰራጨ ሁሉም ያሻውንና የበኩሉን በዋርካ ድረ ገጽ ላይ ጣጥፏል። ድረ ገጹን ስጎበኝ ያገኘሁትን ቀነጫጭቤና እንደሚሆን አድርጌ ጫጭሬልሃለሁና ተቀበለኝ። (በዚህን ወቅት ግንቦት ሰባት ስለመቋቋሙ በኦፊሴል የተሰጠ መግለጫ አልነበረም)

 

በመጀመሪያ ዋርካን የማታውቀው ከሆነ ትንሽ ላስተዋውቅህ። መቼም አንተና ኮምፒዩተር ብዙም የማትገናኙ መሆኑን አውቃለሁ። አንተ በጊዜ አውቅህበታል ልበል!? ‘ንጂ ሞኖፖሊስቶቹ የሀገር ቤቶቹ የኢንተርኔት፣ የስልክና የመብራት ድርጅቶች እየተጋገዙ በዓመት አንዴ እንደመስቀል ወፍ ከኢንተርኔት ያገናኙህ ነበር። በዋርካ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ያሻህን ትጥፋለህ። በነፃነት ሀገር መኖር አንዱ ጥቅሙ ይኼ ነው። በዋርካ “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” የሚባል ነገር አይሠራም። የሆድህን ለመጻፍ መጠጣት አያስፈልግህም፤ ከኢንተርኔት የተሰካ ኮምፒዩተር ‘ንጂ። ይቺን ታህል ስለዋርካ ከነገርኩህ ዘንዳ፤ ቀጥዬ ደግሞ ከዋርካ ደንበኞች ጋር በመንፈስ ላስተዋውቅህ።

 

(ማስታወሻ፦ አብዛኛው ታዳሚ በብዕር ስም (ኒክ ኔም) ነው የሚሳተፈው። ስለሆነም እኔም የብዕር ስማቸውን ወይንም የዋርካ ስማቸውን እጠቀማለሁ። ጦማሬን ለማንበብ ይቀል ዘንድ ስሞቻቸው ላይ አስምሬባቸዋለሁ፣ በጽሑፋቸው መሃል እኔ የጨመርኳቸውን በቅንፍ ውስጥ አስቀምጫቸዋለሁ። የመሳቅ፣ የማዘን፣ የማልቀስ፣ የማሽሟጠጥ፣ … የተለያዩ ምልክቶች አሉ፤ እነሱን በቃላት በቅንፍ ውስጥ አስገብቼልሃለሁ)

 

አሁን በቅርቡ ራሳቸውን ከቀድሞው ቅንጅትና ከአሁኑ አንድነት ፓርቲ ያገለሉት እነ ዶ/ር ብርሃኑ የመሠረቱት ግንቦት ሰባት ንቅናቄን በሚመለከት በመጀመሪያ በድረ ገጽ ላይ የተነበበውን ዜና በመጥቀስ ‘ማይ ኔም’ የተሰኘው/ችው “አዲሱ ግንቦት ሰባት ፓርቲ …” በሚል ርዕስ አዲስ ርዕሰ ጉዳይ ይከፍታል/ትከፍታለች።

 

ጉግል፦ በጣም ደስ የሚል ዜና ነው ። እሳቸውንም ሆነ ጓደኞቻቸውን እንኳን ለዚህ ታሪካዊ ቀን ግንቦት ሰባት አደረሳችሁ እላለሁ። እግዜአብሔር ይህንን የተቀደሰ ዓላማቸውን አይቶ እስከመጨረሻው በጽናት እንደሚያዘልቃቸው መሀል ላይ ደከመኝ እንደማይሉ ምንም ጥርጥር የለኝም። መንገዱን ስጋጃ ያድርግላቸው።

 

በአጋጣሚ ከግንቦት ወር ጋር የሚያያዙ ክስተቶች፦

 

ግንቦት 1 - ልደታ፣

 

ግንቦት 7 -የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ ቅንጅትን የመረጠበት፣

 

ግንቦት 7 - የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው

 

ግንቦት 7 - ፓርቲ የሚቋቋምበት፣

 

ግንቦት 8 - ተሞክሮ የከሸፈው መፍንቅለ መንግሥት፣

 

ግንቦት 13 - ፈሪው መንግሥቱ ፈርቶ የፈረጠጠበት፣

 

ግንቦት 16 - የኤርትራ ነፃ አውጪ አስመራ የገባበት፣

 

ግንቦት 20 - የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ አዲስ አበባ የገባበት፣

 

ግንቦት 27/28 - የትግራይ ነፃ አውጪ አዲስ አበባን በፍንዳታ ያናወጠበት

 

እናዳይለየን … እንዳይለየን … እንዳይለየን … (የቪዲዮ ግብዣ፣ ወ/ት ብርቱኳን፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ እና የአቶ ብሩክ ከበደ ከእስር ከተፈቱ በኋላ የቅንጅት የሰሜን አሜሪካው የልዑካን ቡድን ሆነው በተዘዋወሩ ጊዜ በላስ ቬጋስ ከተማ በሀገርኛ ዘፈን እስክስታ ሲወርዱ - መስከረም 22 ቀን 2000 ዓ.ም.)

 

 

 

ሐመሩ፦ አምጬ … አምጬ … አምጬ … አንጀቴ ቆስሎ ቆስሎ ተወለደ ይሉሀል ይሄ ነው!!

 

ሌኒን(ከላይ ያለውን የሐመሩን አስተያየት ይጠቅስና) ምኑ????

 

ሌኒን(ከላይ ጉግል “በጣም ደስ የሚል ዜና …” ብሎ ያስቀመጠውን የመጀመሪያ አንቀጽ ይጠቅስና) በቃ ዝም ብለህ በነፈሰበት አብረህ ትነፍሳለህ አይደል!!!

 

ጉግል፦ አይደል?! (ሳቅ) እየቆየ ይገባሻል - ሽው ሽው ... (በማሽሟጠጥ)

 

ስልኪ(የጉግልን “ግንቦት 7 የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ግንቦት 7 ፓርቲ የሚቋቋምበት” የሚለውን በመጥቀስ …) እርማት:- "የኒውዮርክ - ኒውስኩል ተራራ የወራት ሱባዔ የወለደው ግንቦት 7 ፓርቲ" ተብሎ ቢስተካከል። ዓላማውም የዲያፖራው ላሜ ቦራ እያለቡ ለልጅ ልጅ የሚሆን ገንዘብ መሰብሰብ ነው!!! (ዶ/ር ብርሃኑ በኒውዮርክ - ኒውስኩል ፒ.ኤች.ዲውን ማግኘቱንና ወደ አሜሪካ ተጉዞ ከነበረው የልዑካን ቡድን ጋር ተለይቶ አሜሪካ ሲቀር በዚሁ ት/ቤት ስኮላር አግኝቶ እንደቀረ መነገሩን ልብ በልልኝ)

 

ሐመሩ፦ ስልኪ ገና ጉሮሮህ ተይዞ ህዝብ ፊት ትቀርባለህ! አንተ ነፍስ በላ … ቀጥል ድሮ ቀረ ከእናተ ጋር በዚህ ወጣ ወደዚህ ሄደ መባባሉ ቀረ። አሁን እስኪገባህ ድረስ በዱላ ማድቀቅ ይሆናል ነገሩ …!!

 

ይከአሎ፦ ስልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥ አለ ያገሬ ሰው

 

ሐመሩ፦ ይከአሎ … ስልቻው ውስጥ ትገባለህ አንተ ነፍሰ በላ ሁላ

 

ቆራጥ፦ ቂቂቂቂቂ አይ ተረት … 'ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል' ... ወደ ቁምነገሩ ስንመለስ። በኔ አመለካከት ከብዛት ጥራት ሊመጣ ይችል ይሆናልና እስቲ እንየው። ለምንም ድል ከማይበቃ ስብስብ እንደዚህ በተናጠል ቢታይ ማን ማንን ይጎትት እንደነበረም የመታዘቢያ ዕድል ነው። እስቲ የፈጣሪ ችሮታም ሀገራችንን አይለያት (ይከአሎን “ስልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥ አለ ያገሬ ሰው” በማለት ይጠቅሳል)

 

ማይ ኔም፦ ይሁን ብለናል። በርቱ ነው የምለው። እነ ብርሃኑን ባለን ሁሉ እንረዳለን … በሁሉም! ብቻ የተስተካከለ አመራር የሚሰጥ ስርዓት ያለው የዘመኑ ፖለቲካ የገባቸው ቆራጥ … ሰዎች ያስፈልጋሉ። ያለጊዜው ሊሆን ይችላል እንጂ … የኔ ጥያቄ - ይሄ ፓርቲ በየትኛው ሀገር ሕግ መሰረት ነው የሚቋቋመው?

 

ስሙ ይናገር፦ ወንድሜ ጉግል - ይሄ ነው ኢትዮጵያዊነት። ወያኔን በየአቅጣጫው ማስጨነቅ ነው እንጂ። አየህ አሁን ጠላትንና ወዳጅን እንለይበታለን። ወያኔ መሃላችን ገብታ ስታባላን ከረመች። አሁን ግን አስተያየትህን ሳነበው ወያኔን ከህዝባችን ጫንቃ ላይ አሽቀንጥረን የምንጥልበት ጊዜ እንደተቃረበ ለመገመት ችያለሁ። በርታ ወንድሜ ትግላችን ረዥምና መራራ ነው። በአስተያየትህ በጣም ደስ ብሎኝ ነው። እንግዲህ በሁሉም አቅጣጫ የሚታገሉትን እንዳንገድላቸው ሁላችንም እንጠንቀቅ በርታልኝ።

 

… እነዚህ ከላይ ያሰፈርኩልህ እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ ‘ማይ ኔም’ በጀመረው/ችው ርዕስ ላይ ተንተርሰው የተጣፉ ናቸው። በተመሳሳይ ጉዳዮች የተለያዩ አርዕስቶች ሰጥተው የየበኩላቸውን የሚሉ በርካቶች ናቸው። የዋርካ ታዳሚዎች የየራሳቸውን አመለካከትና አስተሳሰብ እንዳሻቸው ይጥፋሉ። ብዙ ጊዜ ሳንሱር አይደረግም፤ ለሁሉም ክፍት ነው። አንተም የራስህን ቅጽል ስም እና የምስጢር ቁልፍ ፈጥረህ በጽሑፍ መሳተፍ ትችላለህ። ድረ ገጹ እናንተ ሀገር ይዘጋ አይዘጋ በትክክል አላውቅም ‘ንጂ ቢያንስ ገብተህ ብትጎበኘው ደስ ይለኝ ነበር። ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ባህልና ስነጽሑፍ፣ ስፖርት፣ ፍቅር፣ ጠቅላላ እና ዜና በሚሉ ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ ስለሆነ ካንዱ ወደሌላው እየዘለልህ እኛ ስደተኛ ወገኖችህ የሰው ሀገር አዘጋጅቶ የጠበቀንን የመናገርና የመፃፍ ነፃነት እንዴት እንደምንጠቀምበት ትቃኘው ዘንድ እጋብዝሃለሁ።

 

ከሺህ ቃላት አንድ ስዕል ወይንም ፎቶ ይናገራል እንዲሉ፤ እኔ ብዙ ለማስረዳት ከምጥር ለዛሬ ሦስት ፎቶግራፎችን ወይንም ፖስተሮችን መርጬልሃለሁ። ዶ/ር ብርሃኑ ባሳለፍነው እሁድ በሲያትል ከህዝብ ጋር ተወያይቶ ነበር። ያንን አስመልክቶ በተላለፈ ጥሪ የተሰራጨውን ፖስተር ተመርኩዘው የዋርካ ታዳሚዎች “የፈጠራ ችሎታቸውን” እና የመናገር፣ የመፃፍ፣ የማሾፍ፣ የማላገጥ፣ የመቦጨቅ፣ የመፈተል፣ … መብቶቻቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ ፖስተሮቹ ይገልጡልሃል ብዬ አምናለሁ። ፖስተር አንድን የለጠፈው መረዋ ሲሆን፣ ፖስተር ሁለትንና ሦስትን ደግሞ ‘ቀንዱ’ የተሰኘው ባለቅጽል ስም ነው። በፖስተሮቹ ላይ ያሉትን የጽሑፍና የምሎቹን ልዩነቶች በደንብ ልብ ብለህ እያቸውና ልዩነታቸውን ፈልግ። (ፖስተሮቹ የወጡበትን ገጽ እዚህ ስትጫን ታገኘዋለህ) ለማንኛውም ሄይዶ! (ሠላም ሁን! - በስዊድን አፍ) የሣምንት ሰዎች ይበለን! - አሜን!!!

 

ፖስተር አንድ - በመረዋ

 

ፖስተር ሁለት - በቀንዱ

 

ፖስተር ሦስት - በቀንዱ

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!