Meles Zenawi መለስ ዜናዊ ተስፋዬ ገብረአብ

“መለስ ታመመ” የሚለውን ወሬ ተከትሎ፣ ኮማ ውስጥ መግባቱና መሞቱ እየተነገረ ሰንብቶአል። የወያኔ መንግስት ግን ወሬውን አፍኖ ለመቆየት ተጨናነቀ። መለስ ጀርመን ሃገር ላይ ቀዶ ጥገና ህክምና ማድረጉ በአንድ ወገን ሲገለፅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቤልጅየም 10 ቀናት አልጋ ይዞ መሰንበቱ ተሰምቶአል። “አዲሳባ ገባ” የሚለው ተሰምቶ ሳያበቃ፣ “ብራስልስ ላይ መሆኑ ተረጋገጠ” ተባለ። ወሬዎቹ መልከ ብዙና ውል አልባ ነበሩ። ዞረም ቀረ መለስ ታሞአል። ከመለስ መታመም ጋር በተያያዘ እንዲሞትም ሆነ እንዲፈወስ የሚፀልዩ ተደምጠዋል።

 

 

ከህይወት ልምድ እንደተረዳሁት ከሆነ፣ አምላክ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እጁን ስለማያስገባ የሁለቱንም ወገን ፀሎት የሚሰማ አይመስለኝም። መፍትሄው አበበ ገላው እንዳደረገው፣ እያንዳንዱ ለአላማው መሳካት አንድ ነገር ማድረግ ብቻ ነው።

 

እርግጥ ነው፣ መለስ በደም ካንሰር እና በአንጎል እጢ ህመም በመሰቃየት ላይ መሆኑ ተረጋግጦአል። በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ከዚህ በሁዋላ እንደቀድሞው ወደ ቢሮው ገብቶ ስራውን መስራት ይቸገር ይሆናል። እንደሚሰማው ከማንበብና ከመፃፍ እንዲገለል በሃኪም የተመከረው ከስድስት ወራት በፊት ነበር። ዞሮ ዞሮ መለስ በህይወት አለ። እንዲህ በአጭር ጊዜ ለህይወቱ የሚያሰጋው አለመሆኑም ይሰማል። እንደተነገረው ቀዶ ህክምናም አላደረገም። የአንጎል እጢውን በጨረር ሊያክሙት ሲሞክሩ ነበር የከረሙት። ቀዶ ህክምና ለመሞከር ጊዜው ገና መሆኑን ዶክተሮቹ ለመለስ ነግረውታል። ይህን መረጃ እንደ ጥሬ እውነታ በመያዝ ግን ስለ አጠቃላዩ የአካባቢያችን ፖለቲካ አንዳንድ ነጥቦችን ማንሳት ይቻል ይሆናል።

 

የመለስን መታመም ተከትሎ በኢህአዴግ የአመራር አባላትና በጄኔራል መኮንኖች መካከል የተፈጠረው መቧደን በጣም አሳሳቢና ለውይይት የሚጋብዝ ሆኖ ሰንብቶአል። አመራር አባላቱ የመለስ እድሜ አጭር መሆኑን በመገመታቸው ለህልውናቸው ሲሉ አይኖቻቸውን ወደ ምኒልክ ቤተመንግስት ልከው ከረሙ። አሁንም በሰራዊትና በሲቪል ባለስልጣናት መካከል የስልጣን ሽኩቻ ስለመኖሩ እየተፃፈ ነው። ኢህአዴግ ቀድሞውንም አንድነት አልነበረውምና ከመለስ መታመም ጋር ድርጅቱ በየአቅጣጫው ሲፈነዳዳ ታይቶአል። የመለስ አልጋ ወራሽ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ስሞችም በየሚዲያው እየተገለፀ ቆይቷል። ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ አዜብ መስፍን እና ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ቀዳሚ እጩዎች ሆነዋል።

 

የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ የፃፈውን አይቻለሁ። የግምት ወይም የመረጃ ስህተት አለባቸው። ለአብነት በረከት ስምኦንና አዜብ መስፍን በአንድ ቡድን ውስጥ ሊሰሩ አይችሉም። በሁለቱ መካከል ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ጦርነት ተነስቶ ሰንብቶአል። አዜብ በሚዲያ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብታ በረከትን ለማዘዝ ሞክራ ነበር። በረከት በጣም በመበሳጨቱ፣

 

“አንቺን በዚህ ጉዳይ ውስጥ ምን ያገባሻል? ሚስት ብቻ መሆንሽን ለምን ትረሽዋለሽ?” ይላታል።

 

በበረከት ልቅ ንግግር እብደት ውስጥ የገባችው አዜብ በሃይለማርያም ደሳለኝ በኩል በረከት ላይ ተፅእኖ ለማድረግ ሞከረች። እዚህ ላይ ግን በረከት ችግር ውስጥ ገባ። ወደደም ጠላ ሃይለማርያም የበላይ አለቃው ነው። መንበርከክ ግን አልቻለም። የብአዴን ምንጮች እንደሚገልፁት፣ በረከት ስምኦን አኩርፎ ወደ እናት ክልሉ ዋና ከተማ ወደ ባህርዳር ኮበለለ። ስራውን ትቶ ባህርዳር አንድ ሳምንት እንደቆየ በአዲሱ ለገሰ ልመና እና ማግባባት ወደ አዲስአበባ ሊመለስ ችሎአል። የመለስን መታመም ተከትሎ በረከት ወላጅ አልባ ልጅ መስሎ ታየ። መለስ ከስራው ገለል ከማለቱ የተፈጠረ ቁጥር አንድ ሽኩቻ ነበር። አዜብ ሃይለማርያም ደሳለኝን መጋለብ መጀመሯ እውነት ነው። እዚህ ላይ ሃይለማርያም ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሳበበትን ዋና አላማም ለመረዳት ያሰችላል። ነባር ሚኒስትሮችና ትግሬ ያልሆኑ ታጋዮችን በዚህ መንገድ ከቤተመንግስቱ ለማራቅ ሃይለማርያም መልካም መንገድ ሆኖ ሊያገለግል ይቻለዋል።

 

የህወሃት ነባር የአመራር አባላት በዚህ ወቅት ይከፋፈላሉ ማለት ግን ለእውነት የቀረበ አይደለም። ከተከፋፈሉ ቤተመንግስት ውስጥ ማን እንደሚገባ ያውቃሉ። የምኒልክን ቤተመንግስት አንድ ጊዜ ከለቀቁ፣ ዳግም እንደማይመለሱባትም ይረዳሉ። ስለዚህ ህወሃት ለአራት ወይም ለሶስት ተከፋፍሎ ትርምስ ውስጥ እንደሚገባ መጠበቅ የዋህነት ነው።

 

ከተመስገን ትንታኔ የምስማማበት የብአዴን ተፎካካሪነት ጉዳይ ነው። በዚህ ወቅት አዲሱ ለገሰ እንደሚገመተው በጡረታ የተገለለ አይደለም። እንደ ጆርጅ ኦርዌል ውሾች ሸሽጎ ያኖራቸው ከፍተኛ መኮንኖች ካሉት ብልህነቱን ማድነቅ ይቻላል። ብአዴን ተሸፋፍኖና ተጠጋግኖ ያደፈጠ ድርጅት ነው። አብዛኞቹ የብአዴን ካድሬዎች ቁጭት ይሰማቸዋል። ህወሃትን የሚገለብጡበት አጋጣሚ ከተገኘ፣ ከመጠቀም አይመለሱም ተብሎ ይታሰባል። በርግጥ ከህወሃት የተሻለ ስርአት መገንባት ይችላሉ ተብሎ ተስፋ አይደረግም። ህላዌና ካሳ ሸሪፎ ከኢህአፓ መንፈስ ጋር አብረው ያሉ እንደመሆናቸው፣ ኢህአፓን ወደ ጓዳቸው ለመጋበዝ ይሞክሩ ይሆናል። መለስ ዜናዊ ዘግይቶም ሆነ ፈጥኖ በሞት የሚሰናበት ከሆነ የብአዴን አመራር አባላት ከባድ ፈተና ውስጥ ይገባሉ። ምክንያቱም የመለስ ዜናዊ መንግስታዊ ወንበር በሌላ የህወሃት ሰው የሚወረስ ከሆነ፣ ለብአዴን ታሪካዊ ውርደት ይሆንበታል። ብአዴን ለ23 አመታት የኢህአዴግ ምክትልነትን ወንበር ይዞ ቆይቶአል። ከ23 አመታት በሁዋላ ሊቀመንበሩ “በሞት” ቦታውን ሲለቅ፣ ብአዴን ሊቀመንበርነቱን መተካት ካልቻለ ለዘመናት የሚወነጀሉበትን አሽከርነት በማፅደቅ እነርሱም ወደ መቃብራቸው ያመራሉ። በግብፅ የቀበሌ አስተዳደር ውስጥ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ምንጊዜም ምክትልነት ቋሚ ቦታቸው እንደሆነው ሁሉ፣ ብአዴንም ምክትልነትን አምኖ ሳይቀበል አልቀረም። ከዚህ ውርደት ለመዳን ብአዴን ሁለት አማራጮች አሉት። የመጀመሪያው መለስ እንዳይሞት መፀለይ ሲሆን፣ ሁለተኛው የመለስን ወንበር ለመያዝ ሽምጥ መጋለብ ናቸው።

 

መለስ የሰራዊቱን ትግርኛ ተናጋሪ አመራር ለሁለት ከፍሎ ሲያስተዳድረው ነበር። በቀጥታ ሳሞራ የኑስ የሰራዊቱ አዛዥ ቢሆንም፣ በጎን ደግሞ ሌላ መዋቅር ዘርግቶ ቆይቶአል። ታደሰ ወረደ እና ወዲ አሸብር የሚባሉት ጄኔራሎች ከሳሞራ እዝ ውጭ ከመለስ ጋር ግንኙነት ነበራቸው። ታደሰ ወረደ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ድፍረቱም ብቃቱም ሊኖረው ይችላል። ወዲ አሸብር እብድ ነው። ምን ሊያደርግ እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይቻልም። የመለስን ልጅ ክርስትና ያነሳው ጄኔራል ወዲ መድህን፣ አቅሙ ባይኖረውም የታዘዘውን የመፈፀም ችግር የለበትም። እነዚህ ሶስት ጄኔራሎች አዜብና ቴዎድሮስ ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋ ካለ ለመመከት ተወርዋሪ ሃይል ይዘው የሚጠብቁ ሊሆኑ ይችላሉ። በተቀረ የህወሃት ጥቅምና ስልጣን እስካልተነካ ድረስ ሰራዊቱ ወደ ቤተመንግስት ታንክ ለማንቀሳቀስ አይገደድም።

 

ከመለስ መታመም ጋር ተያይዞ በኢህአዴግ ውስጥ ከብአዴንና ከህወሃት ነባር አመራር አባላት በቀር ለሽኩቻው ብቃት ያለው ሃይል ማየት አይቻልም።

 

ለመሆኑ በዚህ ወቅት የተቃዋሚ ሃይላት ቦታ የት ነው?

 

አንዳንድ ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ከምርጫ ውጭ በማድረግ፣ “አዜብ ትተካለች፣ የለም ሃይለማርያም ነው” ሲባባሉ ስሰማ ጠጉሬን ማከኬ አልቀረም። በትግርኛ ተናጋሪዎች ቁጥጥር ስር የወደቀው መድረክ ራሱን እንደ አማራጭ በማየት ፈንታ፣ “የሚተካ የተዘጋጀ ሃይል የለም። መጥፎም ቢሆን መንግስት ያስፈልጋል” አይነት ህወሃትን የማዳን አዝማሚያ ያላቸው ይመስላል። “የአንድነት” መሪ ዶክተር ነጋሶ የሚሰማቸው ጠፋ እንጂ እሳቸውም እንደ መለስ ታመዋል። እግዜር ይማራቸው። “ኢህአፓ ምን እያሉ ይሆን?” በሚል ወደ ድረገፃቸው ገብቼ ነበር። “ኢህአፓ በአዲስ አበባ ወረቀት በተነ” የሚል ዜና ለጥፈዋል። ከ30 አመታት በሁዋላም የትግል ስልት አልቀየሩም። ፌስቡክ እና ኢሜይል በተስፋፋበት ዘመን ወረቀት መበተን ለምን ያስፈልጋል? በጥንት ዘመን ወረቀት መበተን ያስፈለገው ሌላ አማራጭ ስላልነበረ ነው። የዶክተር ፍስሃ እሸቱ የሽግግር ምክርቤት፣ “መለስ ሞቶአል፣ አረጋግጠናል” ብለው አውጀዋል። ፊሽ መቼም ችኩል ነው። አዲስ ናቸውና ከልምድ እየተማሩ ይሄዱ ይሆናል። የፖለቲካ ድርጅቶች ለዜና መሽቀዳደም የለባቸውም። ዜና መቅደም የጋዜጠኞች ስራ ነው። እንደ ሽግግር ምክርቤት አቅጣጫ ማሳየት ነው የሚጠበቅባቸው። በመሰረቱ የመለስ መሞት የችግሮች መፍትሄ አይሆንም። ከመለስ መወገድ በሁዋላ ስልጣኑን ህዝብ እንዲቆጣጠር ታክቲክና ስትራቴጂ መንደፍ ያስፈልጋል። በመጨረሻ የተስፋ አይኖች የሚያርፉት በታጠቁት ሃይሎች ላይ ነው። ኦነግ፣ ግንቦት 7 እና ሌሎችም ሃይሎች ተቀናጅተው አንድ የታጠቀ የጋራ ሃይል ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። አለመረጋጋት ቢፈጠር የሚያረጋጋ ሃይል ያስፈልጋልና ይህ ለነገ ሊባል የማይገባ ተግባር ይመስለኛል። አንዲህም ሆኖ የሃይል ሚዛኑን ስመረምረው በአስፈሪ ጭጋግ ውስጥ ያለን መስሎ ይሰማኛል። ህወሃት ደክሞታል። የሚገፈትረው ግን አጣ። ተቃዋሚዎችም አልተደራጁም። መንገዱ ወዴት ያደርስ ይሆን? እንደ ፕሮፌሰር መስፍን፣ “እግዜር ያውቃል” ማለት ብቻ ይሆን የቀረን?

 

በጥንት ዘመን አንድ ጋዜጣ፣ “ማርክ ትዌይን ሞተ” የሚል ዜና አትሞ ነበር። ማርክ ትዌይን ለጋዜጣው በላከው የማስተባበያ ደብዳቤ፣ “ስለኔ መሞት የፃፋችሁትን ዜና አንብቤዋለሁ። ተጋንኖአል።” ብሎ ነበር። ምናልባት መለስ በቴሌቭዥን ብቅ ብሎ፣ ተመሳሳይ ነገር ይነግረን ይሆናል። የሚበጀው ህወሃት እንደ ስርአት ይሞት ዘንድ፣ ታክቲክና ስትራቴጂ ነድፎ መትጋት ብቻ ይመስለኛል።


ተስፋዬ ገብረአብ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!