በአሉ ግርማ Bealu Girmaተስፋዬ ገብረአብ

በኛ ዘመን የብእር ሰው ሆኖ መፈጠር መረገም ሆኖ ይሰማኛል። ከቡቃያው የሚነጋገር፣ በሁዳዱ ላይ ሽምጥ ፈረስ የሚጋልብ፣ ውሎው ከዋልካው፣ ማምሻው ከመልካው የሆነ ገበሬ እንዴት እድለኛ ነው? የኛ ዘመን ብእረኛ ህይወቱ በሰላዮች የተከበበ ነው። ተፈጥሮው ነውና አለመፃፍ አይችልም። መፃፍ ደግሞ አደጋ ነው። በአሉ ግርማ እንዲህ ባለ ችግር ውስጥ አልፎ፣ በከንቱ ያለፈ ደራሲ ነበር። ደርግ ብዙ ሰላዮች መድቦበት ነበር።

 

በአሉ ግርማ ምንም እንኳ ከደርግ ሰዎች ጋር በቅርብ ይሰራ የነበረ ሰው ቢሆንም ህሊናው ግን ነፃ ነበር። የደርግ የፀጥታው መስሪያ ቤት የበአሉን ነፃ መንፈስ በማወቁ፣ ነፃ ለቆት አያውቅም። በሰላዮቻቸው ከበውት ኖረዋል። በአሉ ግርማን እንዲሰልሉ ከተመደቡት አንዱ አይነስውር ለማኝ ሆኖ ነበር የሚተውነው። በአሉ ግርማ መኪናውን ውቤ በረሃ አቁሞ፣ እዚያው መኪና ውስጥ ሆኖ ሲቀመቅም፣ አይነስውር መሳዩ ለማኝ ወደ በአሉ መኪና ጠጋ ብሎ ይለምናል፣

 

“ስለ መድሃኒያለም፣ በቀን ጨለመብኝ። ሌትና ቀኑ ተደባለቀብኝ። በኔ የደረሰ በዘርማንዘራችሁ አይድረስባችሁ። ስለመድሃኒያለም ስትሉ እርዱኝ እባካችሁ።”

 

ይህ ለማኝ ሰላይ መሆኑን ግን በአሉ ግርማ ገና ድሮ አውቆ ነበር። ሆኖም ያላወቀ መስሎ በመጣ ቁጥር አስር ሳንቲም ይሰጠዋል። ሰላዩም አይኖቹን እንደ ፀደይ የቢራቢሮ ክንፍ ብልጭ ድርግም እያደረገ አስር ሳንቲሟን ተቀብሎ፣ በአሉ ግርማ ከማን ጋር እንዳመሸ ተመልክቶ ሲያበቃ፣ በነጋታው በማያዩት አይኖቹ ያየውን ለተስፋዬ ወልደስላሴ ቢሮ ሪፖርት ያደርጋል። ይህ ድብብቆሽም ለረጅም ጊዜ ቀጠለ።

 

ከእለታት አንድ ቀን በአሉ ግርማ እና ስብሃት ገብረእግዚአብሄር የበአሉ መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው እያወጉና እየቀመቀሙ ነበር። ስብሃት እንዳጫወተኝ በመካከሉ የበአሉ ደምበኛ የሆነው አይነስውር ለማኝ መጣ፣

 

“ስለ ጊዮርጊስ … በቀን የጨለመብኝ …”

 

አስር ሳንቲሙን ከተቀበለ በሁዋላ የሚያየውን አይቶ ተመልሶ ሄደ። በዚህ ጊዜ በአሉ ግርማ ለስብሃት እንዲህ አለው፣

 

“ለማኝ አይደለም። ሰላይ ነው …”

 

“እንዴት አወቅህ?”

 

በአሉ ግርማ እንዴት እንዳወቀ ለስብሃት አጫወተው። በዚህ ጊዜ ስብሃት በጣም ተበሳጨና እንዲህ አለው፣

 

“እንደነቃህበት ነግረህ ለምን ቆሌውን ገፈህ አታባርረውም? ለምንድነው በየቀኑ አስር ሳንቲም የምትገብረው?”

 

በአሉ እየሳቀ እንዲህ መለሰ፣

 

“የማውቀውን ሰላይ ካባረርኩማ የማላውቀውን ይተክሉብኛል”

ተስፋዬ ገብረአብ

www.tgindex.blogspot.com

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ