ህዝባዊ ውይይቱ ምን ይመስል ነበር?

ያሬድ ክንፈ ከስዊድን

ሠላምና ጤናውን ከነቤተሰብህ ያበዛልህ ዘንድ የዘወትር ምኞቴ ነው። ለእመቤትህና ለልጃችሁ የከበረ ሠላምታዬን አቅርብልኝ። ዛሬ የማወጋህ “ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ” የተሰኘውና በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው አዲስ ንቅናቄ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ከተማ ከህዝብ ጋር ያደረገውን ውይይት ነው። ውይይቱ ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ስላወቅሁ ከስቶክሆልም 220 ኪሎ ሜትር ርቄ ከምኖርበት ሳንድቪከን ከተማ ወደዚያው አመራሁ። ንቅናቄውን በመወከል ዶ/ር ብርሃኑ እና አቶ ቸኮል ጌታሁን ነበር የተገኙት። አቶ ቸኮል የቀድሞው ቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት አባል የነበረ ሲሆን፣ አሁን በስዊድን ስደተኛ ነው።

 

አሁን አሁን በአዕምሮዬ ምን እንደሚመላለስብኝ ታውቃለህ? “ይህች ኢትዮጵያችን ካለአቅሟ ትቀፈቅፈንና ማሳደግ ሲያቅታት፣ ከቤትዋ አሽቀንጥራ የምታባርረን ለምንድን ነው? ሊያውም በወጉ እንኳን ለጉዲፈቻ አትሰጠንም። እኛው ልጆችዋ ጉዲፈቻ የሚቀበለንን ፍለጋ በዓለም እንንከራተታለን። … ግን ለምን?” … የኔ ነገር እንግዲህ አንዱን ጥሎ ወደ ሌላ ሳይሆን በፊት ወደ ግንቦት ሰባት ልመለስ። 

 

Ginbot 7 public meeting in Stockholm 20080621

 

በስብሰባው ላይ ከ210 ሰዎች በላይ ተገኝተዋል። ስብሰባውን ያዘጋጀው በስዊድን የኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ማኅበርና በስዊድን የኢትዮጵያ ራዲዮ ናቸው። “ኦሽታ” በተሰኘው ክፍለ ከተማ የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ስብሰባው ከቀኑ በ8 ሰዓት እንደሚጀመር በራዲዮና በድረ ገጾች ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር። ዶ/ር ብርሃኑ ከምርጫ 97 ጀምሮ በውጭ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጋቸውን አብዛኞቹን ውይይቶች ተከታትያቸዋለሁ፤ በቀጥታ ስርጭቶች፣ በራዲዮ፣ በኢንተርኔት። “ለምንድን ነው ሰዓት የማናከብረው?” ብሎ ያልጠየቀበት ስብሰባ ትዝ አይለኝም። ታዲያ እሱ የሰዓቱን ነገር ባነሳ ቁጥር ተሰብሳቢው ሁሉ ይስቃል። ሞቅ ደመቅ ያለ ሳቅ። እስቲ አሁን በሞቴ ምኑ ያስቃል? በቅርቡ አውሮጳ ውስጥ በተደረገ ውይይት ላይ በስደት ያለን ኢትዮጵያውያንን ልክ ልካችንን ሲነግረን ፈረንጅ ሲቀጥረን ብቻ ለምን ሰዓት እንደምናከብር ሲጠይቅ ተሰብሳቢው ሳቀ። ግልፍጥፍጥ ብሎ ሳቀ። … በቦታው ላይ ባልኖርም ብርሃኑም አንጀቱ እየተቃጠለ ፈገግ እንዳለ እገምታለሁ።

 

እኔና ጓደኞቼ ለስምንት አስር ጉዳይ ላይ ደረስን፤ ሠልጥነን። ለማንኛውም ስብሰባው 25 ዕፁብ ድንቅ ደቂቃዎች አሳልፎ በአዘጋጁ ማኅበር ሊቀመንበርና ራዲዮ ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ አሕመድ ዓሊ የመክፈቻ ንግግር ነበር የተጀመረው። ከዚያ በመቀጠል (8፡33 ሰዓት) አቶ ቸኮል የዕለቱን የግዜ ሰሌዳ አስረዳ። ለተሰብሳቢው “ማንም ሰው የፈለገውን ሃሳብና ጥያቄ ሊሰነዝር ይችላል። ልታስቆሙትና ልትቃወሙት አይገባም!” በማለት ተሰብሳቢውን አስጠነቀቀ።

 

ብዙ ስብሰባዎች ላይ የተለየ ሃሳብ፣ ወይንም ተቃውሞ ብጤ ያለው ሰው ንግግር ማድረግ ሲጀምር ተናጋሪውን በጩኸት፣ በተቃውሞ ድምፅ፣ … ማስቆምና መረበሽ እዚህ በሠለጠነው ዓለም በስደት የምንኖር ወገኖችህ መታወቂያችን ነው። አንተ ከምታስበው ትንሽ ፈቀቅ ያለ አስተሳሰብ ካለው ሰው ጋር በጠላትነት መተያየት የሥልጣኔና የአዋቂነት ልዩ መለያው ነው። “ሰው እንዴት ከጠላቱ ሊያውም የሀገሩ ልጅ ጋር ሊወያይና ሊደማመጥ ይቻለዋል?” በዚህ የማታምን ከሆነ ምኑ ላይ ነው ኢትዮጵያዊነትህ። በተቻለህ መጠን እንኳን ሃሳቡን አይደለም የዓይኑ ቀለም ያላማረህን ኢትዮጵያዊ ሙልጭ አድርገህ መስደብ ነው። ታዲያ ተቃዋሚ መሆንህን የምታሳውቀው በምን ይመስልሃል? … አቶ ቸኮል አሁን በቅርቡም አይደል የተሰደደው? በዚህች አጭር ጊዜ ገብተነዋል መሰል፣ ኮስተር ብሎ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ የሁሉም መብት መሆኑን ነገረን። ዕድሜ ለእሱ ማስጠንቀቂያ፣ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ሥርዓታችንን ጠብቀን ነበር። - ጌታ ይባርክህ አቶ ቸኮል!

 

በዚህ በያዝነው ዓመት በተደረገው የማሟያ ምርጫ ኢህአዴግ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ከእንግዲህ በሀገሪቱ ሊሞከር እንደማይችል አሳይቶናል፣ ሠላማዊ ትግልን ረግጦታል፤ ረገጣውን ደግሞ መከላከል ያስፈልጋል ሲል አቶ ቸኮል ተናግሯል። አክሎም ይህንን ረገጣ ለመከላከል የሚያስችል ስልት ተጠንቶ፣ ጥናቱን በሥራ ላይ ለማዋል ግንቦት 7 ንቅናቄ መቋቋሙን ለተሰብሳቢው ገልጿል። የንቅናቄውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሁሉም ወገኖች (በተለይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች) መቻቻል፣ መተሳሰብና መደራደር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው፤ ድርድሩ ቀላልና አልጋ በአልጋ እንደማይሆን አስረድቷል። ፓርቲዎችም በሽርፍራፊና በማይረቡ ነገሮች መፏከታቸውን ማቆም አለባቸው ብሏል።

 

9፡15 (15:15) ሰዓት፦ ላይ መናገር የጀመረው ዶ/ር ብርሃኑ ነበር። ከያዝኳቸው ማስታወሻዎች ቀነጫጭቤ ላካፍልህማ! … ከሁሉም በላይ የሃሳብ ትግል እንደሚያስፈልግና በዚህ ውይይት ላይ በደማቁ ሊያሰምርበት የሚፈልገው ቁልፉ ነጥብ የሃሳብ ትግል መሆኑን ገልጿል። ትግሉ በብሔር ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን በዜግነት፣ በግለሰብ እኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት፤ ምክንያቱም እውነተኛ ዴሞክራሲ መሠረቱ ዜግነት ነው ብሏል። ለዚህም ጠንካራና እውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች መፈጠርና መጠናከር እንዳለባቸው፤ ዴሞክራሲያዊነትን የሚሸከሙ ብሔራዊ ኃይሎች፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሙሉ ጊዜያቸውን የሰጡ ኃይሎች መጠናከር እንዳለባቸው ጠለቅ ብሎ አብራርቷል።

 

ዴሞክራሲያዊነትን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚሸከመው ድርጅታዊ ኃይል በባህሪው፣ በአመለካከቱና በቋንቋው ሁሉንም የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያንፀባርቅ እንዲሆን እስከመጨረሻው መጣር አለበት። ለማሟላት ተብሎ ሳይሆን፤ ለዚህ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሙሉ ጊዜያቸውን የሰጡ ኃይሎች መፈላለግና መሰባሰብ ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው ብሎ ግንቦት 7 ንቅናቄ እንደሚያምን ዶ/ር ብርሃኑ አስረድቷል።

 

Ato Chekol & Dr Berhanu 080621 Stockholm

 

ንቅናቄው መኖር አለበት ብሎ ለሚያምነው ዴሞክራሲ መሠረት የሆነው የዜግነት እምነት፣ የዜግነት ማንነት የበላይነትን ሲያገኝ ብቻ ነው። እሱ የበላይነትን ካላገኘ ሁልጊዜ አሁን የምናየው ትንቅንቅ ሰለባ ነው የምንሆነው። ዶ/ር ብርሃኑ “አሁን የምናየው ትንቅንቅ” ብሎ ያለውን ሲያብራራ “ኢህአዴግ በፈጠረው የብሔር ነገር ከባቢው አየር ስለተሞላ፣ አንዳንድ ግዜ ሳታስቡትና ሳታውቁት ሰውን በማየት ‘ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ … ነው’ በማለት መጠራጠር ...” ሲል አስቀምጦታል። ይሄ አመለካከት አውቀንም ይሁን ሳናውቅ በውስጣችን የመስረጹ ችግር የሚያመላክተው ባላንጣችን (ኢህአዴግ) እንደበለጠን ነው። ኢህአዴግ በአስተሳሰብ በልጦናል፣ አሸንፎናል ማለት ነው። ራሳችንን ከዚህ የአስተሳሰብ ሽንፈት ማጽዳት እንዳለብን ዶ/ር ብርሃኑ አስጠንቅቋል። አክሎም "ቀላል አይደለም ከባድ ነው" በማለት የችግሩን ክብደት ገልጦታል።

 

“በግለሰብ ደረጃ ልናደርግ የሚገባው፤ ‘ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለእኛ ይገባናል’ ብለን በግለሰብ ደረጃ ማመን ግድ ይላል። ‘እውነተኛ ቃልኪዳን አለን ወይ?’ ብለን በመጠየቅ ራሳችንን ከዚያ ጋር ማዋሀድ ይገባናል።

 

“… የሌላውን ሰው ሰብዓዊ መብት የማክበር ግዴታ አለብን። መለስ ዜናዊ ከእኔ በቅንጣት የሚበልጥበት ምንም መብት የለውም።

 

ዶ/ር ብርሃኑ “ዴሞክራሲ ጥሩ ሰው (መሪ) ልትመርጥ ዋስትና (ጋራንቲ) አይሰጥህም። ዴሞክራሲ ጥሩ ሰው ቢመርጥ ኖሮ ቡሽ አይመረጥም ነበር። የጨዋታው ሕግ የምንፈልገውን ለመምረጥ ብቻ ሳይሆን የማንፈልገውንም መስማት መቻል እንዳለብን ያስገድደናል …” በማለት ገልጾታል።

 

በተጨማሪም "ነፃነትን የመሻት እልህ ነው የሚያስፈልገው" ብሏል ዶ/ር ብርሃኑ። ነፃነትን የመሻት እልህ እንደሚያስፈልግ አጠንክሮ ተናግሯል። እግዚአብሔር በአምሳሉ ሲፈጥረን ሙሉ ነፃነታችንን ሰጥቶን ፈጥሮናል፤ ነፃነት መሰረታዊ የሆነ የሰውነት ባህሪ ነው። አንድ ጥጋበኛ ነፃነቴን ሊወስድብኝ ሲል እንዴት ነው “ምናባክንስና ነው የምትወስድብኝ?” ብዬ የማልታገለው? ታዲያ ከዚያ በላይ ምን ቢወስድብኝ ነው የምናደደው? የማልታገለውስ? … እነመለስ ሰው የሚያደርገንን ነገር ነው የወሰዱብን። እንዴት ለእሱ እልህ የማይዘን? እንዴት ዝም ብለን ዞረን ገብተን እንተኛለን? ማን ሆኖ ነው እሱ (አቶ መለስ) ይሄን የሚያደርገው? አንዳንድ ጊዜ አንዳርጋቸው "እሱ ሲፀዳዳ ኬክ ነገር ይወጣዋል እንዴ?" ይላል … እንዴት ነው ይሄንን ተቀብለን የምንኖረው?” ሲል ዶ/ር ብርሃኑ ተሰብሳቢውን እያዋዛ ሃሳቡን ገልጿል።

 

10፡00 (16:00) ሰዓት፦ የ30 ደቂቃ እረፍት ተደረገ። ሻይ ቡና ብጤ ነበር። ዶ/ር ብርሃኑን በአካል ያገኘሁት ከስድስት ዓመት በኋላ ነበር። እዚህ ስዊድን ነጮች የበዙበት ሀገር የምኖር ስለሆነ ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም፣ ቢሆንም ግን ከበፊቱ ጠቆር ብሎብኛል። ምናልባት ፀሐዩ ሊሆን ይችላል። በእኔ ግምት ለክፉ የማይሰጥ ትንሽዬ ኪሎ ሳይጨምር አይቀርም። የማስተማርና ሰው የማሳመን ችሎታው ጨምሯል እንጂ አልቀነሰም፤ ባለበትም አልረገጠም። ጥንቆላ ባይሆንልኝም፣ እልህ እንደተጋባ ቅንጣት ታህል አልጠራጠርም። የዚህች ሀገር ጉዳይ ጨጓራቸውን ከመለጣቸው፣ ጉበታቸውን ከጠበሳቸው፣ ቆሽታቸውን ካደበናቸው፣ ... ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው። ያስታውቃል።

 

ጥያቄና መልስ

10፡30 (16:30) ሰዓት፦ ከእረፍት መልስ፣ ጥያቄና መልስ። የመጀመሪያው ጠያቂ አቶ በላይ ይባላል። በሀገራችን ከ430 በላይ መያዶች፣ ወርልድ ባንክ፣ … ወዘተ አሉ። ከበጎ ሥራቸው ይልቅ ሀገሪቱን የሚጎዳ ሥራ እየሠሩ ስለሆነ፣ ከሀገር ሊወጡ ይገባል፤ በዚህ ትስማማላችሁ ወይ? (እኔን በጣም የገረመኝ አስተያየት/ጥያቄ ቢኖር ይሄ ነበር። እንግዲህ ይታይህ በሰው ሀገር እየኖርክ፣ የሰው ሀገር ሰዎች ከሀገሬ ይውጡ ብሎ ነገር እንዴት እንደሆነ አልገባኝም፤ አንተም ባይገባህ እመርጣለሁ። አቶ ቸኮል እዚህ ጋር ስለሌለ ያሻኝ ብል ማን ይከለክለኛል?!) አቶ በላይ ያነሳው ሌላው ጥያቄ የትግሬ መንግሥት ነው የሚባለውን ትጋራላችሁ? የሚል ነበር።

 

2ኛ ጠያቂ ሄለን (ወጣት)፦ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ትጥቅ ትግል ያዋጣ ነበር፣ አሁን ግን ቀዝቃዛው ጦርነት አብቅቷል። ግንቦት 7 እንዴትና ከማን ጋር ነው የሚሠራውና ያሰበው ውጤት ላይ የሚደርሰው?

 

3ኛ ጠያቂ፦ ግንቦት 7 የትኛውን የትግል ስልት ነው የሚከተለው?

 

መልስ

ዶ/ር ብርሃኑ፦ ከብልህነትና ከሚዛናዊነት አኳያ በጥቅሉ ሁሉም ፈረንጆች ይውጡ ማለት ተቀባይነት የለውም። በብስጭት ይውጡ ሊባል ይችላል፤ ከዚህ በኋላ በጩኸት፣ በአካኪዘራፍ፣ … ለውጥ የምናመጣ ይመስለናል። ከዚህ መውጣት አለብን …

 

አሁን ያለውን መንግሥት የሚያሽከረክሩት የተወሰኑ ጥቂት ሰዎች ናቸው። የመለስ፣ የበረከትና የስብሃት መንግሥት ነው። … በእኔ እምነት በእነዚህ ሰዎች የትግራይ ህዝብ የተጠቀመ አይመስለኝም። … ለእኔ ጥቂት ሰዎች በሥልጣን እንዲቆዩ የሚያደርግ መንግሥት ነው ያለው …

 

የእኔ እህት ግንቦት 7 ትጥቅ ትግል ያልሸው፣ ጦራችን የቱ ጋር እንዳለ አላውቅም። ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት በኋላ የሚደረግ የትጥቅ ትግል የማሸነፍ አቅሙ ደካማ ነው ለሚባለው ነገር፣ አሜሪካንን በአፍጋኒስታን፣ ኢህአዴግን በሶማሊያ ማየቱ ጥያቄው ያለው ቃልኪዳን ላይ መሆኑን ያሳየናል። ምን ያህል እኛ ለዓላማው ልንቆምለት ዝግጁ ነን የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ ሊሆን የሚገባው።

 

“ጠብመንጃ ይዞ የመጣ ዴሞክራሲ አይገነባም” የሚባለው ውሸት ነው። የገነቡ አሉ። የቅርብ ጊዜ ኒካራጓን ማየት ይቻላል። መንግሥት ገልብጦ፣ ሥልጣን ከያዘና በምርጫ ከተሸነፈ በኋላ ሥልጣኑን አስረክቦ በተቃዋሚነት ቀጥሎ ሲያበቃ፣ ከረዥም ዓመታት በኋላ በምርጫ አሸንፎ ወደ ሥልጣን መጥቷል። ጋናንም በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ዋናው ምርጫ ያለው ዝም ብሎ መገዛት እና ዴሞክራሲን መምረጥ ላይ ነው። ዝም ብዬ አልገዛም። … እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ይበጃታል ብሎ መሪ ሊመርጥልን ካሰበ፣ ከአሁን በኋላ በህዝብ ምርጫ ሊያደርግልን ይገባል እንጂ፣ በሌላ ሊያደርግልን አይገባም።

 

ኦነግን ለሚደግፉ የኦሮሞ ወዳጆቻቸውን የምንላቸው “በታሪክ ለተፈጠሩ ችግሮችና ወንጀሎች አባቶቻችን/የፈፀሙት ግለሰቦች ሊጠየቁ ይገባል እንጂ፤ እኛ ልንጠየቅ አይገባም። መጪውን ትውልድ ማሰብ ነው ያለብን። አጤ ምኒልክ ለምን ዴሞክራት አልነበሩም ብሎ መጠየቅ ተገቢ አይደለም። … ለደላችሁ ኀዘናችን ጥልቅ ነው፣ እናዝናለን። ከዚህ በኋላ እንዳይደገም እንሠራለን፤ መሥራት አለብን” ብለን ነው መቅረብ ያለብን … በዚህም ምክንያት ልባችንን ከፍተን ነው ሁሉንም የምንቀርብ። በዚህም ምክንያት ቢያንስ የመቀራረብ፣ የመነጋገር፣ የመደማመጥ፣ … ሁኔታዎች ይዳብራሉ። የአዲስ አበባው፣ የኦጋዴው፣ ፍትህ በማጣት በየእስር ቤቱ የሚንገላቱ ኦሮሞዎች፣ … ሁሉም ሲነኩ ተያይዘን መጮህ አለብን። ለሁሉም እኩል መጮህ አለብን።

 

የትግል ስልት የተባለው ምን ያካትታል ለሚባለው፣ ሁሉንም ያካትታል። የትግል ትንሽና ትልቅ የለውም። ይሄ ሥርዓት ሁሉንም ያዋረደ ሥርዓት ነው። ይህንን ሥርዓት መታገልና መጣል የሁላችንም የዜግነት ግዴታ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ አድጓል፤ ሁሉም መሪ መሆን ይፈልጋል። በገንዘብ፣ በፀሎት (ገንዘብ ማዋጣት የማይወድና ጸሎት የሚወድ ከሆነ በፀሎቱ)፣ መለገም ጎበዝ የሆኑ ሰዎች በመለገም፣ … ከአሁን በኋላ የትግላችንን መስመር እኛ ነን የምንወስነው እንጂ፤ መለስ ዜናዊ አይደለም።

 

ሁለተኛ ዙር ጥያቄ

ጠያቂ አቶ ስሜነህ፦ ፕ/ር ኤፍሬም እንዳይቀየሙኝ እንጂ፣ ለእናንተ መፈታት ዳያስፖራውም የበኩሉን ጥረት አድርጎ ከእስር ተፈትታችኋል። ሠላማዊ ትግልን በተመለከተ የዛሬን አያድርገውና አስተማሪያችን ነህ። የትግል ስልታችሁን ለመቀየር ስታስቡ ቅንጅትን ለማነጋገርና ለማሳመን ውይይት አደርጋችኋል ወይ?

 

ጠያቂ ወጣት ፋሲል፦ ”ተኝታችሁ አስቡበት” ላልከው ”እኔን ተኝቼ እንቅልፍ የሚነሳኝ ነገር አለ” ስዊድን ያለው ኢትዮጵያዊ ግንቦት 7ን መርዳት አይደለም የረባ የመረዳጃ ዕድር እንኳን የመመስረት ሕብረት የለውም፤ በሌሎች ሀገሮችም ይኸው ችግር አለ። ለዚህ ምን ጥናት አላችሁ?

 

ጠያቂ ፍሰሀ፦ ከተነሱት ፊሎሶፊዎች ብሔረሰቦችን የሚያናቁር፣ የተጋቡትን የሚያፋታ ሥራ ነው የተሠራው። ስለዚህ ከብሔር ወደ ዜግነቱ ማተኮር ይሻላል እያላችሁ ነው፤ ሕብረብሔራዊ ናችሁ ወይ?

 

መልስ

ዶ/ር ብርሃኑ፦ እነ ፕ/ር ኤፍሬም የሀገራችንን የሽምግልና ባህል ያዋረዱ ሰዎች ናቸው። ቢቀየሙኝ ግድ የለኝም።

 

ለአቶ ስሜነህ - መልሱ አይቻልም ነው። 1ኛው ምክንያት ቅንጅት እነመለስ ያሉትን የማይቀበል ከሆነ ሰዎቹ ፊዚካሊ (በአካል) ችግር ውስጥ የሚገቡበት ነው። 60ዎቹን ሰዎች ሰብስቦ የትግል ስልት እንለውጥ በሚለው ላይ ለመወያየት፣ … የኢትዮጵያ ሠላዮች በቀላሉ ሊያገኙት በሚችሉበት ሁኔታ፣ ከኖርማሉ (ከመደበኛው) ሰው ሰላዩ በበዛበት ሀገር፣ ከዚያ ማዕቀፍ ውጭ ነው መወያየት እንኳ የሚቻለው። … በየቀኑ መለስና በረከት ሕግ በሚያወጡበት ሀገር እንዲህ አይነት ውይይት ማድረግ አይቻልም። አይታሰብም።

 

2ኛው ግንቦት 7፣ ዳያስፖራ (ስደተኛ) አይደለም። የምንደራጀው ሀገር ውስጥ ነው። በኅቡህ ነው መደራጀት ያለብን። እየተደራጀን ያለነውም በዚያ መልክ ነው። ከምንም በላይ የምንደራጀው በጨዋታ ሕጉ ነው። የጨዋታ ሕጉ በህዝብ የተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መገንባት የሚለው ነው።

 

መናቆር ለተባለው፦ ማኅበረሰባችን አንድ ሰው ቢሆን ሳይካተሪስት ጋር (የአዕምሮ ሐኪም/አማኑዔል ሆስፒታል) መሄድ ነበረበት። ጥላቻ እንደሚመርዘን እያወቅን ውስጡ እንገባለን … ሽማግሌዎችም እያጣን ነው፣ ሽማግሌዎቹም እየቀለሉ ናቸው፣ … ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ … አሰቃቂ ነው። ባለፉት አምባገነን ሥርዓቶች በጥልቀት ተጎድተናል። አንድ ሰው ሲያድግ፣ ለምንድን ነው የምንቀናው? የምንበሳጨው? በመውደቁ ምንድን ነው የምናገኘው? ከወደቀ ምናልባት ከእኔ ይፈልግ ይሆናል ብለን ነው? … የሞራል መሰረት የሆነው ቤተ-ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉ አባቶች ከማንም በላይ ሲቧጨቁ፣ ሲናከሱ፣ … ነው እያየናቸው ያሉት። ይሄ ጤናማ አይደለም። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በዚህ መልኩ አይገነባም። … ከእምነታችን ጋር የረገጠ አስተሳሰብ/መሰረት የሌለን ለምንድነው? ፖለቲካው ራሱ ወሬ ሆኗል። ጊዜ ማሳለፊያ/መደበሪያ ሆኗል። የእኛ ፖለቲካ እንዲያ መሆን የለበትም።

 

ግንቦት 7 ”ሕብረብሔራዊ” ነው። በሃሳብ የምናሸንፍበት ጠንካራ ድርጅት ያስፈልጋል፤ ያ ደግሞ ግንቦት 7 ነው።

 

ሦስተኛ ዙር ጥያቄ

ጠያቂ አህመድ፦ እኛ 99% እንስማማና በቀረችውና ባልተስማማንባት ላይ ተንጠልጥለን እንፋጫለን። ለምንድን እንደሆነ አይገባኝም። ከሰላማዊ ትግል ወጥተህ እዚህ ውስጥ የገባኸው ለምንድን ነው? አቶ መለስ ስለሸወዷችሁ ነው ወይ? ኅቡህ ነው ብላችኋል፤ ፕሮግራማችሁ ምንድን ነው?

 

ወጣት ሴት ጠያቂ፦ ስለንቅናቄው የሚያውቁ ሰዎች ትንሽ ናቸው። ዲያስፖራው ካላወቀ፣ ሀገር ቤት ያለው እንዴት ያውቃል? ስለሚዲያው ምን አስባችኋል?

 

ሌላ ጠያቂ፦ ወኔ ያለው መምጣቱ ደስ ይለኛል፣ 1) "የሠላማዊ ትግሉ ተጀመረ እንጂ መች አለቀ" በማለት በሾርኔ እየተናገሩ ያሉ አሉ። ወደዚህ እንድትመጡ ያደረጋችሁ በቂ መረጃ አለ ወይ? 2) በብሔር ላይ የተደራጁና የሞከሩ አሉ … ምንድን ነው መተማመኛው? የኔን ጥያቄ ይመልስልኛል ወይ ብሎ የሚል 3) መቻቻል የሚለው ተነስቷል። እኛ አናውቅበትም። ከእናንተ መሪዎች ይጠበቅ ነበር። በእናንተ በቅንጅት መሪዎች ውስጥም አልነበረም። እናንተ ውስጥ የሰረፀ ነው ወይ?

 

መልስ

ዶ/ር ብርሃኑDr. Berhanu

የመደባበቅ ሁኔታ ያለ ይመስላል ለሚለው - አሁን ጅምሩ ላይ ስላለን የተወሰነውን ነገር ነው ለህዝብ ይፋ የምናወጣው። ወደፊት ግን ህዝብ የሚጠይቅበትንና እኛም በተግባር የምንተረጉምበትንና የምንጠየቅበትን እናሳያለን። ለዚያ ጊዜ ያስፈልጋል። መጠበቅ ነው።

 

ለአህመድ ጥያቄ፦ የሃሳብ ለውጥ ያደረግኸው መቼ ነው? ለሚለው፤ የትግል ስልት ቀኖና አይደለም፤ መቀየር ይችላል። እስር ቤት ሆኜ ነው እዚህ ላይ የደረስኩት። … ከወሮበላ መንግሥት ጋር፣ በምታምንባቸው መሠረታዊ እሴቶችን በማይቀበል፣ አዋርጄ ልግዛህ ከሚል ኃይል ጋር በሠላማዊ ትግል መዝለቅ አይቻልም።

 

ፕሮግራም ከሌላችሁ ለሚለው፦ ግልፅ የሆነ አለን። በኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ሥልጣን ላይ የሚወጣው በህዝብ የተመረጠ ብቻ ነው። … ለኢትዮጵያ የሚጠቅም የምንለው የኢኮኖሚ፣ የመከላከያ፣ … ፖሊሲዎች መቅረጽ ጠፍቶን አይደለም። መጀመሪያ የምንፈልገው በህዝብ የተመረጠ መንግሥት መመስረት ነው።

 

ስለሚድያ ለተጠየቀው፦ ድርጅታችን ከምንጠብቀው በላይ ምላሽ እያገኘን ነው። የድረ ገጽ ጋዜጣችንን በሀገር ቤት ውስጥ በ8 ሺህ የኢ-ሜይል አድራሻዎች ይሰራጫል፤ ሀገር ቤት ያሉ ጋዜጦች መሸጫ አድርገውናል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገር ቤት የሚገባ ራዲዮ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነን፣ … በዚህና በመሳሰሉት ላይ እየሠራን ነው።

 

እንዲህ ደፋር መፈጠሩ ስለተባለው - “ጀግንነት ማለት እንዴት ፍርሃትን እንደምትቋቋመው ማወቅ ነው” ይላሉ ፈረንጆች። እኛ የተለየን አይደለንም፤ ይሄ እናንተም ውስጥ አለ።

 

ሠላማዊ ትግል ካልተጀመረ እነሱ ይጀምሩት ነው የምንለው። ሙሉ ለሙሉ አብቅቶለታል አላልንም። ፋሲሊቲው (የትግሉ መጠቀሚያዎች) ተዘግተዋል፤ መድረሻችን አንድ ከሆነ ምንም አያጣላንም። ሁላችንም በየመስመራችን ሄደን እዚያ ላይ እንገናኛለን። ለሌሎች … እንደነሱ ”የትጥቁ ትግል መቼ ተጀመረና” ብንል ይቀለናል። ወደን አይደለም እዚህ ውስጥ የገባነው። … በነመለስ … የተሰጠን ምርጫ ባርነትን መቀበል ነው።

 

የትግል ስልቱ የተደበቀ ነው ለተባለው - ወታደራዊ ጫማ ገዝተናል እንድንል ነው ወይ የተፈለገው? የሳይኮሎጂ ዲፓርቸር (የስነልቦና መለየት) … ዋናው እሱ ላይ ነው ያለው። … በምን መንገድ? እነማን? … ተራውን ህዝብ እማይጎዳ እስከሆነ ድረስ ሁሉንም ነገር እናደርጋለን። … ብርሃኑ አርፒጂ፣ ክላሺንኮቭ፣ … ነው የሚይዘው የሚለውን አሁን አንነጋገርም። ዋናው የትግል ስልቱ ያዋጣል የሚለውን መስመር ይከተላል።

 

እናንተ ውስጥ መቻቻል አለ? ለሚለው - በቅንጅት ውስጥ የመቻቻል ችግር አልነበረም። ያልገባው ሰው ነበር። ከድርጅት ሕግና ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ውጭ … ልሂድ የሚል ሰው ነበር። … እሱን ብቀበል የቅንጅትን መንፈስ መግደል ነው የሚሆንብኝ።

 

መቻቻል በመሪዎቹ ውስጥ አለ? ለሚለው - እኔ መንፈሱ ሰርጾብኛል።

 

ያለውን እያፈረሱ መሄድ ለተባለው - እኛ አላፈረስነውም። የድርጅት ሕግና ዴሞክራሲያዊነት ይከበር ነው ያልነው።

 

ስብሰባው ከቀኑ ስምንት ሰዓት እስከ ምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ታስቦ የነበረ ቢሆንም በመሃል ላይ አንድ ሰዓት መጨመሩንና እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት እንደሚዘልቅ ለተሰብሳቢውና ለእነአቶ ቸኮል ተነግሮ ነበር። ዶ/ር ብርሃኑ ንግግሩን ሲያቋርጥ ከወዳጄ የተዋስኳት ላብቶፕ ኮምፒዩተር ላይ ያለው ሰዓት አናቱ ላይ 19፡00 (ከምሽቱ አንድ ሰዓት) ትል ነበር። ለራሴ ሳቅሁ። ከጎኔ ለተቀመጠው ወዳጄ ሰዓቷን በእጄ አሳየሁት። ዶ/ር ብርሃኑ ብዙ ጊዜ የእጅ ሰዓቱን አውልቆ ጠረጴዛ ላይ ያስቀምጣል። በዚህ ላይ የማስተማር ልምድ አለው። ስለዚህ እንደእኔና አንተ በሰዓት አጠቃቀም ላይ አይታማም።

 

በዚህ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስድስት የሚሆኑ የኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) ሰዎች በተቃዋሚዎችና በኢትዮጵያውያን ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በስዊድን የኦነግ ተወካይ/ኃላፊ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ። ከኦነግ ሰዎች አንዱ “ሩቅ ለሩቅ ሆኖ አጥንት የሚሰብር ነገር እየተነጋገሩ ከመናቆር፣ እንዲህ ተቀራርቦ መነጋገር ይሻላል” ሲል ተደምጧል። በተለይ እዚህ ውጭ ያለው ማኅበረሰባችን አጥብቆ የሚሠራው ለመራራቅ መሆኑን የኦነጉ ሰውዬ አባባል በግልጽ እንዳስቀመጠው በበኩሌ ላረጋግጥልህ እወዳለሁ።

 

አንዳንድ በስደት ያለን ወገኖችህ በስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ ሠላማዊ ሰልፎች ላይ መካፈል፣ ኢህአዴግን በመቃወም በሚደረጉ የሻማ ማብራቶች ላይ ወይንም ተመሳሳይ ሥነሥርዓቶች ላይ ለመገኘት አንደፍርም። ቢያንስ የምናምንበትንና የምንቃወመውን ነገር በነፃነት ለመግለጽ ምን እንደሚይዘን አላውቅም። መብታችንን እንዴት እንደምንጠቀምበት የምናውቀው ነገር የለም ማለቱ ይቀለኛል። አንዳንዶች በዚህ አይነቱ ስብሰባ ላይ ሲገኙ ፊታቸውን ለመሸፈን፣ መጠቋቆሚያ እንዲሆኑ ስለማይፈልጉ፣ ... ወይንም እኔን በማይገባኝ መንገድ (እኔን ካልገባኝ ደግሞ አንተን ሊገባህ የሚችልበት መንገድ እይታየኝም) መሸፋፈን፣ መደባበቅ፣ ካሜራ ሲደቀን ጀርባቸውን መስጠት፣ ... ያዘወትራሉ። ዶ/ር ብርሃኑ "ኢትዮጵያ ፖለቲካ መደበሪያ ሆኗል" ያለው እውነቱን ይሆን? ... ከሆነስ ምን ይሻለን ይሆን? ... እኔ በበኩሌ በዚህ ጦማሬ ምላሽ የለኝም ... ለማንኛውም ለዛሬ በዚህ ባበቃስ?! … ደክሞኛል ልተኛበት፣ ነገ ሸክም ይጠብቀኛል … ሄይዶ! (በስዊድን አፍ “ቻዎ!”)

 


 

Dr. Berhanu & Andargachew in London 20080622ለግንዛቤ

 

- ግንቦት 7 ለመጀመሪያ ጊዜ ከህዝብ ጋር ውይይት ያደረገው በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. ሲሆን፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ መስፍን አማን ንቅናቄውን ወክለው ተገኝተዋል፣

 

- 2ኛ ስብሰባውን ያካሄደው ደግሞ ስዊድን ስቶክሆልም ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. ሲሆን፣ 3ኛ ስብሰባውን እንግሊዝ ሎንዶን ውስጥ እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2000 ዓ.ም. አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እና ዶ/ር ብርሃኑ በተገኙበት ነው።

 

- 4ኛውን ደግሞ ቤልጅየም ሉቨን ውስጥ ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. ሲሆን፣ ዶ/ር ብርሃኑ ብቻ ነበር። 

 

- ዶ/ር ብርሃኑ በስዊድን ቆይታው ከፓርላማ አባላት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ ከመንግሥት አካላት ጋር መወያየቱ ታውቋል።

 

- ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን በቤልጅየም ብራስልስ ዶ/ር ብርሃኑ በአውሮጳ ፓርላማ ንግግር እንዲያደርግ የተከበሩ አና ጎሜዝ ጋብዘውት ተገኝቷል። ማክሰኞ ሰኔ 17 ደግሞ ከአውሮጳ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዣቪየር ሶላና እና ሉዊስ ሚሼል ጋር እንደተወያየተ ተዘግቧል።

 

- በአውሮጳ በተዘዋወረባቸው ሀገራት በሙሉ ከከፍተኛ የመንግሥታ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘቱ በሰፊው ተዘግቧል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!