ዩሱፍ ከዲ

AA traffic police. በደመነፍስ የሚነዱ ትራፊክ ፖሊሶችና የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር

የቅዳሜ ሚያዝያ 1 2008 አጭር ገጠመኝ

ከሜክሲኮ በባልቻ አድርጎ በአብነት ወደ አውቶቡስ ተራ የሚወስደውን በተለምዶ ዶልፊን የሚባለውን ታክሲ ስሳፈር፣ ሰዓቱ ገና አንድ ሰዓት ከሃያ አካባቢ ነበር። ታክሲውም አንድ ወይም ሁለት ሰው ቀርቶት ባልሞላበት ሁኔታም ነበር መንቀሳቀስ የጀመረው። ይህ ድርጊቱ የሾፌሩን "ለሰዓት/ለጊዜ እንዲሁም ለጫናቸው ተሳፋሪዎቹ ያለውን አክብሮት" ያሳየኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁና እንዳከበርከን ክበር እያልኩኝ በውስጤ መልካም እየተመኘሁለት ነው የተጓዝኩት።

ጉዞው ተጀምሮ የባልቻ ሆስፒታል አካባቢ ስንደርስ፣ አንዲት እናት፣ ከአለባበሳቸውና ከጠቅላላ አኳኋናቸው የልደታ ቤተክርስቲያን ሊሳለሙ ይመስላሉ፣ "ወራጅ" ይሉና ታክሲያችን ጥግ ይዞ ይቆምላቸዋል። እርሳቸውና ሌላ ሰው እየወርዱ ሳለ፣ ከኋላችን የመጣ ረዥሙ ባለተሳቢው የከተማ አውቶቡስ፣ "ሰለሜ" እንዲሁም "ክፍለ ከተማ" ይሉታል አንዳንድ ሰዎች፣ በስተግራችን በኩል ሊያልፈን ሞክሮ፤ ነገር ግን ከፊት ለፊቱ ባለው የእግረኞች ማቋረጫ (ዜብራ ክሮስ) በሚያልፉ በርከት ያሉ ልደታን ተሳላሚ ምዕመናን ምክንያት መቆም ይገደድና ይቆማል። አቋቋሙ ግን ተጠማዝዞና እኛ ያለንበትን ታክሲ በጣም ተጠግቶት ነበርና፤ ሾፌሩ እንደውም የኋላ ማሳያ መስታወቱን አጥፎና መሪውን ወደቀኝ በጣም ጠምዝዞት ከዚሁ አንበሳ አውቶቡስ ታክሲውን ሲያሸሽ ነበር።

ልክ የከተማው አውቶቡስ ከጎንና ከፊታችን ተጣማዝዞ ቆሞ እንቅስቃሴያችንን ከገታበት ሁኔታ ተንቀሳቅሶ ሲርቅ፣ የእኛው ታክሲ ደግሞ ፍሬቻ እያበራ ሊወጣ ሲል ሞተር ሳይክል ላይ የተቀመጠ የትራፊክ ፖሊስ ይመጣና እንዲቆም ይጠይቀዋል። እንዳተባለውም አድርጎ ቆሞ ጠበቀው።

ትራፊክ ፖሊሱ ከሞተሩ ወርዶ በሹፌሩ መስኮት በኩል ቆሞ እይታውን ንቀት በተሞላበት ሁኔታ አልፎት ወደመጣው መንገድ እያደረገ ፍጹም ትህትና በሌለውና በሚጎረብጥ ቁጣ ተሞልቶ "መንጃ ፍቃድህን!?" ሲል ትዕዛዝ ሰጠ!

አርባዎቹን ያጋመሰ የሚመስል የፊት ገጽታ አለው ፖሊሱ። ሾፌሩም ተረጋግቶ የከተማው አውቶቡስ ታጥፎ የቆመበት ሁኔታ ከእንቅስቃሴው እንደገታው ሊያስረዳ ሞክሮ ነበር። ፖሊሱ ግን ከመስማት ይልቅ በዛው በሚያቅለሸልሽና በሚጎረብጥ ቁጣው እንደተሞላ "መንጃ ፍቃድህን?" ሲል መጮኹን ቀጠለ፤ ሾፌሩም መጀመሪያ አንዲት መነኩሴ ለማውረድ ቦታ እንደያዘ፣ ሊወጣ ባለበት ሰዓት ግን፣ የከተማ አውቶቡሱ ተጠማዝዞ ቆሞ እንደውም እንዳይገጨው ሲሸሽ እንደነበር ለመናገር ሞከረ። ሰሚ ግን አላገኘም። እንደውም ፖሊሱ ይበልጥ መናደድ ጀመረ።

"ስትጭን አይቼሃለሁ" ሲል ቅዠቱን ገሃድ አወጣው። እኔ በሩ አካባቢ ተቀምጬ ነበር። መነኩሴዋ ሲወርዱም ልረዳቸው ሞክሬያለሁ፤ አንዲት ወጣትም ከእርሳቸው በኋላ ወርዳለች እንጂ የገባ ተሳፋሪ አልነበረም። ሾፌሩም ያንኑ ነገር ምንም ውሸት በሌለበት ሁኔታ አስረዳ።

"ጭራሽ ያየሁትን ነገር ትክደኛለህ" ብሎ አምባረቀበት እንጂ ፖሊሱ፤ ምናልባትም ከቤቱ ይዞት የወጣውን ሌላ ቁጣ ሊያበርድለት የቻለ እውነት ሆኖ አላገኘውም። ሾፌሩም ሁኔታው ሳያምረው ሲቀር ክርክሩን ተወና እንደተባለው መንጃ ፍቃዱን ሰጠ። ትንሽ ራቅ ብዬ የተቀመጥኩኝ በመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ፤ ከመንጃ ፍቃድ ይልቅ የተጣጠፈች ነጭ ወረቀት ነው የሰጠውና "ምናልባት ሌላ ክስ ይኖርበት ይሆን?" ስል ለሾፌሩ ሃሳብ ገብቶኛል። ፖሊሱም ቀጠለና መታወቂያውን ተቀበለው። ጥቂት ሜትሮችን ራቅ አድርጎ ያቆመው ሞተር ላይ ካሉት ሳጥኖች ውስጥ የአንዱን ከፍቶ የሆነ ከርቀት ሲታይ ጥራዝ የሚመስል አውጥቶና ካርቦን ጨምሮበት መጻፍ ሲጀምር ሾፌሩ በሩን ከፍቶ ወጣና ያናግረው ጀመር። ረዳቱም ተከተለው። ሾፌሩና ረዳቱ እጆቻቸውን እያወነጫጨፉ ሲናገሩ የአፋቸው እንቅስቃሴ እንጂ ድምጻቸው አይሰማም ነበር። ፖሊሱ ግን ከአለት በቀዘቀዘ ስሜት አልባነት የሚጽፈውን ቀጠለ እንጂ ቀና ብሎ ሲያያቸው እንኳ አላየሁም።

ብዙም ሳይቆይ ሾፌሩ ፊቱን ግርምትና ንዴት እንደሞሉት ይመለስና ቦታው ይቀመጣል። ከኋላ ቀርቶ ሊያግባባው የሚሞክረውን ረዳቱንም ጮክ ብሎ ጠራው፤ "ባክህን ተወው! የእኛን ድምጽ ማን ይሰማናል! ና ተመለስ" ሲል አንጀቴን ያላወሰው ንግግር ተናገረ። ቁጭቱን ልቤም ተጋራው። እውነታው ሳይደመጥለት በየትኛውም ገሀድ ነገር ሊሟገቱት የማይችሉቱ፣ ከራሱ በላይ ምንም ዓይነት እውነት እንደሌለ በሚያምን ከሳሽም፣ ምስክርም፣ ፈራጅም ራሱ በሆነ ደመነፍስ እጅ ውስጥ መውደቁንና የመስዋዕት በግ መሆኑ ውስጤን ያጎደለኝ ከባድ ስሜትን አስታቀፈኝ። ረዳቱም እንደተባለው አደረገ።

ራቅ ብለው ሲነጋገሩ ምን እንደተባባሉ ባላውቅም፣ ትራፊክ ፖሊሱ አሁንም የሚጽፈውን ጽፎ ሲያበቃ ተመልሶ መጥቶ በዛው በሚያቅለሸልሽ ልቅና የራሱን ስሜት አምላኪነት ባረጋገጠበት ቁጣው ትዕግስት መፈታተኑን እንደቀጠለ በተሳፋሪው ጉምቱምታ እየተረዳሁና የራሴን የቁጣ ስሜት እያደመጥኩኝ ሳለ "ታፔላህን አምጣ!" ሲል ደግሞ ጮኸ።

ከሕጋዊነቱ ይልቅ ቂም በቀል ወይም ግልብ ስሜታዊነቱ በጎላ ሁኔታ፣ ታፔላውን መንጭቆት "አውርዳቸውና ተከተለኝ" ብሎም ሲቻኮል ሞተሩ ላይ ወጥቶ ከነፈ! በዚህን ሰዓት ተሳፋሪዎች በግልጽ ጮኸው ተናገሩ፤ "የእኛ መንገላታትስ? የእኛ ከሥራ መስተጓጎልስ? ለህዝቡስ አይታሰብም?" ቢሉም ያ ማን እንዳጎረሰው ያልታወቀን እሳት ጎርሶ የመጣንና የነጠላ ደመነፍሱን ጩኸት ከማድመጥ ውጭ በትክክል ስለሆነው እውነት ምንም ዓይነት ትዕግስት ያላሳየን፣ ሰውን እንደሰው አክብሮ ማናገር ያልቻለና ሊያገለግለው ቃል የገባለትን ህዝብ ጥቅም ከግምት ለማስገባት ያልሞከረን የትራፊክ ፖሊስ ልብ ሊያራራ የቻለ ሰው አልነበረም። በአንድ ሰው ስህተት መስሎ በታየ የቁም ቅዠት ምክንያት ከአስር በላይ ሰው መቅጣት ፍትሐዊነት ሆኖ ተገኘ፤ እናም አንድ ባንድ ገንዘባችን እየተመለሰልን ወረድንና በዛ አጉል ቦታ ላይ ወደየመድረሻችን የሚወስዱንን ታክሲዎች ጥበቃ እንደገና ጀመርን። ይህ ሲሆን በአንድ
ሰዓት ላይ 40 ደቂቃዎች ተጨምረው ነበር። ሌላ ግርግር፣ ሌላ ሰልፍ፣ ሌላ የባከነ ሰዓት፣ ሌላ ትኩረት የተነፈገው የዜጎች ጩኸት፤ ብዙዎችን ቆይ ግድ የለም በሚል ጥርስ ያስነከሰና የጥቃት ስሜትን የተወ ክስተት ነበር።

በዚህ ከምክንያታዊነት ፍጹም በራቀ፤ ስሜት፣ እልህና ቂም በቀል ከሕሊናና ስነምግባር በዕድሜም ተምሮ ከመብሰል በላይ ሆነው፤ ሕግንም ለዚሁ መጠቀምያ ባደረገ ክስተት ውስጥ ብዙ አሳዛኝ እውነታዎችን የምናይ ይመስለኛል። በዚህ ወቅት ባቡርና "ፐብሊክ ሰርቪስ" ሁሉ ተጨምሮበት፣ የተጠበቀውን ያህል መሻሻል ያልቻለውን የከተማችንን የትራንስፖርት ችግር፣ አንድ ምክንያቱን ማየት ይቻላል። ያለ ታፔላ መሥራት አልችልም ያለው ሾፌር ተከተለኝ ያለውን ፖሊስ ተከትሎ ባዶውን ሲሄድ፤ እንደዛ የተቆጣ ፖሊስ መኪናውን ከማሰር ይመለሳል ማለት አይቻልም።

በጣም ቀላል ሊባል የሚችል ሂሳብ ብንሠራና በዚህ ታክሲ በአንድ ጉዞ 15 ሰው ይጓጓዛል ብለን ብናስብ፣ በታፔላው መሰረትም በተመደበበት የመነሻና መድረሻ ቦታዎች መካከል በቀን ውስጥ አስር ጊዜ እንኳ ይመላለሳል ብለን ብናስብ፣ በድምሩ ከ150 ያለነሱ ሰዎችን ያስተናግድ ነበር ማለት ነው። በዚህ ታክሲ ብቻ ሊገለገሉ የሚችሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች፣ ሌላ ችግር ላይ የሚወድቁ ይሆናሉ ማለት ነው። ይህ እንግዲህ በአንድ መኪና ብቻ ነው። የሚከሰሱ፣ የሚታሰሩ ወይም የሚታገዱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በተበራከተ ቁጥር ደግሞ እንደ ከተማ በአዲስ አበባ ውስጥ የምናየውን ግራ አጋቢ የትራንስፖርት ችግር እንቆቅልሽ በትንሹም ቢሆን የሚፈታልን ይመስለኛል።

ለትንሽ ለትልቁ በታክሲ ሾፌሮች ላይ በክስ ላይ ክስ የሚጨምሩት የትራፊክ ፖሊሶች፣ ለመንግሥት የሚያስገቡት ገቢ መጨመሩና እነርሱም ያገኛሉ ተብሎ የሚነገረው ኮሚሽን ከፍ ማለቱን ልማታዊነት የሚሉት ባይጠፉም፤ በረባ ባልረባውና እንደጠቀስኩት ዓይነቱ ፍጹም ደመነፍሣዊነት በገዘፈበት ሁኔታ የሚቀጡ ሾፌሮችን ሕይወት ማበላሸት ግን ትልቁ ክፍያው እየሆነ መሆኑን መዘንጋት አይገባንም።

በዚህ የኑሮ ውድነት፣ ኢፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል፤ መቼም ላይጠብ በብርሃን ፍጥነት እየተራራቀ የመጣውን የሀብት ልዩነትና ሌሎች ፈታኝ የአዲስ አበቤዎች ተግዳሮቶች ውስጥ፤ እኒህ ሾፌሮች ደግሞ በክስ ብዛት ከሥራ ወጥተው ወደ ሕገወጥነት የማይገፉበት አስገዳጅ ምክንያት አይታየኝም። እናም ይመለከተኛል የሚል አካል ሁኔታውን መስመር ቢያስይዘውና፣ የታክሲ ሾፌሮች በደፈናው ሁሌም እንደሚያጠፉ ተደርጎ የሚወሰደው የተዛባ ዕይታ ቢስተካከል መልካም ነው እላለሁ።

ሠላም!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!