ሙሉነህ እዩኤል

ኢትዮጵያና አሜሪካ ምን አገናኛቸው ትሉኝ ይሆናል። ነገሩ እንዲህ ነው፦ ባለፈው ሳምንት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም የሰባት አገሮች ዜጎች ወደ አሜሪካን አገር እንዳይገቡ እግድ ጥለው ነበር። ፕሬዝደንቱን ለዚህ ያነሳሳቸው እግዱ ከተጣለባቸው አገሮች የሚመጡ ዜጎች ለአሜሪካን ደህንነት የሚያሰጉ ሆነው ስላገኟቸው እንደሆነ ይናገራሉ፤ ብዙዎች ይህን ስጋት ባለመጋራት እገዳውን ቢቃወሙም። እገዳው ውሎ ሳያድር የዋሽንግተን ክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የተከበሩ ጀምስ ሮበርት በሰባቱ አገሮች ዜጎች ላይ የተጣለው የጉዞ እግድ በዋሽንግተን ክልል ብቻ ሳይሆን በአሜሪካን በሙሉ እንዳይተገበር የሚል ብይን ይሰጣሉ። የእግድ እግድ መሆኑ ነው።

የዚህች ጥሁፍ አላማ ስለ ፕሬዝደንቱና ስለተከበሩት ጀስቲስ ውሳኔዎች ለመተንተን ሳይሆን በአሜሪካን ታላቅነት መደመሜንና በተቃራኒው ደግሞ በኢትዮጵያ አገዛዝ የበታችነት ማፈሬን ለመግለጥ ነው። በተለይ ያሳዘነኝ በሀገራችን ያሉ ዳኞች ለፍትህ ቀናኢ፥ ለህሊና አዳሪ መሆን ሳይፈልጉ ቀርተው ሳይሆን ለህሊና ማደር፥ ለፍትህ መስፈን እና ለህግ የበላይነት መቆም የሚያስከብር ሳይሆን ውድ ዋጋ የሚያስከፍል እዳ ስለሚሆን ነው። ለዚህ ብዙ ምሳሌዎች መስጠት ይቻላል፤ እኔ ግን አንድ ሁለቱ ላይ ብቻ እንዳተኩር ፍቀዱልኝ።

አንድ ሰሞን ህወሓት "ከአናቴ ጀምሮ በስብሼአለሁ፤ በክቼአለሁ፤እንደ አሳ ግማቴ ከአናቴ" ብላ ነበር። በዚያን ጊዜ አንደኛው ቡድን ሌላኛውን ቡድን ለአገሪቷ እድገት ደንቃራ፥ ለዴሞክራሲ እጦት ዋነኛ ተጠያቂ፥ ወዘተ እያለ ክስ አቀረበ። በመጨረሻም የአቶ መለስ ቡድን የበላይነት አግኝቶ በሀሳብ በተለዩ ጓዶቹ ላይ ተመጣጣኝ ያለውን እርምጃ ይወስድ ጀመር። ከጠላት ወገን ቀንደኛ ተብለው የተፈረጁት አቶ ስዬ አብርሃ ነበሩ። አቶ ስዬም ተከሰው አራዳ ፍርድ ቤት ዳኛ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ፊት ቀረቡ። ዳኛዋም የከሳሽንና የተከሳሽን ክርክር ካዳመጠች በኋላ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥታ አሰናበተች። በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ወ/ሪት ብርቱካን ከምርጫ 97 ማግስት የእነ እንጂነር ሀይሉ ሻውል መዝገብ የሚል ተውኔት ውስጥ ሆነን ቃል በቃል ባይሆንም እንደሚከተለው ያጫወቱኝ ይመስለኛል፦

"የተከሳሽ የዋስትና መብት ጥያቄ ከቀረበ በኋላ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቼ ከወጣሁ ከጥቂት ሰአት በኋላ አቶ መንበረ ጸሃይ ስልክ ደውሎ፦'ቅድም ስዬ ተተረተረ አይደል? በጣም ተዳፈረሽ። አገሪቷ ላይ ያደረሰው ጥፋት እድሜ ልኩን ዘብ ጥያ የሚያወርደው እንደሆነ ያልታወቀበት ይመስል ራሱን እንደ ጻድቅ ቆጥሮ እንደዚያ መዘባነኑ በጣም የሚያናድድ ነው። እኔ አንችን ብሆን ኖሮ አፉን ነበር የምዘጋው•••” አላት። ከክብርት ዳኛዋ የሰማሁትን ምን ማለት እንደሆነ ትግርኛ የሚችሉ ጓደኞቼን ጠይቄ እንደተረዳሁት ከሆነ "ስዬ እንዲከላከል እድል ልትሰጭው አይገባም፤ የፍርድ ውሳኔው ደግሞ እድሜ ልክ እንደሆነ እወቂ" ማለት ነው ብለውኛል። አቶ መንበረ ጠሃይ ማናቸው የሚለኝ ከተገኘ ሰውዬው በጊዜው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት በሚል ማዕረግ በአገሪቷ ለነበሩ ዳኞች ሁሉ ዋና አዛዥ እንደነበሩ ማስታወስ ጥሩ ይሆናል።

የአቶ መንበረ ጠሃይን ትእዛዝ ከቁብ ያልቆጠረችው ዳኛ ተከሳሹ ዋስ ጠርቶ በውጭ ሆኖ እንዲከራከር ወሰነች። ከዚያ በኋላ የሆነውና ያየችው ነገር እነመለስ ፍትህ፥ የህግ የበላይነት፥ ህገ መንግስት የሚባሉ ሀሳቦችን መረዳት የሚችል አእምሮ ያላቸው የሰው ልጆች ሳይሆኑ ከእነ ተኩላ ተርታ የሚቀመጡ ከጫካ የወጡ አውሬዎች እንደሆኑ እንድትገነዘብና እንዲያውም በፖለቲካ ውስጥ ገብታ አገዛዙን እንድትፋለም ሁነኛ ምክንያት የሆናት ይመስለኛል።

ሁለተኛው አብነት ደግሞ የ1993 የአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍና ሰልፉን ተከትሎ በአገዛዙ የተወሰደው እርምጃ ነው። ሰልፉን አነሳስተዋል በሚል በርካታ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን በጊዜው የኢዴፓ አመራር አባላት ከነበሩት ደግሞ አቶ ልደቱ አያሌውና አቶ ታምራት ታረቀኝን ከማስታውሳቸው መካከል ነበሩ። ምንም እንኳን የጥሁፌ አላማ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ለመተረክ ባይሆንም በጊዜው አስገርሞኝ የነበረውን አንድ የአገዛዙን ምላሽ ሳልጠቅስ ማለፍ ግን አልፈልግም። በጊዜው የበርካታ ንጹሃን ሰዎች ህይወት ተቀጥፎ ነበር። የሟቾችን ቁጥር በሚምለከት በነጻው ፕሬስ በኩል ሪፖርት የተደረገውና በአገዛዙ በኩል የሚቀርበው ቁጥር በጣም የተራራቀ ነበር። አገዛዙ ጥቂት ህገወጥ ሰዎች እንደሞቱና አንደኛው ሟች የመአህድ አባል እንደሆነ ገልጾ የመአህድ አባሉን አሟሟት በሚመለከት በኢቲቪ የተገለጸበት መንገድ “ምን ታካብዳላችሁ? የሞተው እኮ የመአህድ አባል ነው” የሚል እንድምታ ስለነበረው “መአህድ መሆን መብት ሳይሆን በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው እንዴ?” ብዬ እንድገረም አድርጎኝ እንደነበር አልዘነጋውም።

ታዲያ በዚህ ጊዜ ታሳሪዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ሸዋ ሮቢት ተወስደው እየተጉላሉ ስለነበር የፖለቲካ መሪዎቹ ጠበቆች ክስ በመመስረታቸውና አሳሪው አካልም ፍርድ ቤት ሊያቀርባቸው ባለመቻሉ የፍትህ ምኒስትሩ አቶ ወረደ ወልዱ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ዳኞቹ አቶ አለም አቶ ወንድወሰንና አቶ ነጻነት ትእዛዝ ይሰጣሉ። የዳኞቹ ውሳኔ አቶ መለስ ሊኮሩበት የሚገባ ሆኖ ሳለ እሳቸው ግን እንደትልቅ ድፍረት እንዳዩትና “ይህች ባቄላ ካደረች•••” የሚለውን የትግራይ ተረት ተርተው ፍርድ ቤቶችን በመከላከያ ሰራዊት እጅ እንዳለ ጠብመንጃ ሁሉ ጠላቶቻቸውን መግደያ መሳሪያ አድርገው እንዲያወቅሩ ትምህርት የሰጣቸው አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

የመጨረሻው ምሳሌዬ ወደ ምርጫ 97 ይወስደኛል። የወያኔን የድምጽ ዘረፋ ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ወገኖቻችን በመቶዎች የሚቆጠሩ በግፍ ሲገደሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ወደ ግዞት ተወስደው ነበር። በጊዜው ብዙዎቹ ታሳሪዎች ወደ ጦር ካምፖች ተግዘዋል። በተለይ ጦላይ ዋና ማጎሪያ ሆኖ ነበር። በዚህ ጊዜ የተጋዙት ሰዎች ቁጥር በውል ባይታወቅም በሂደት ብዙዎቹ ተፈትተው በመጨረሻ የቀሩትና የአጣሪ ኮሚሽን አባላት የመዘግቧቸው ሰዎች 20 ሺ ይሆናሉ።

በጊዜው አለም በቃኝ በሚገኘው ጨለማ ቤት ለብቻዬ በታሰርኩበት ወቅት በትንሳኤ ራድዮ አንድ ቃለ መጠይቅ ማዳመጤን አስታውሳለሁ። ቃለ መጠይቁን የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕረዝዳንት ኦቶ ተሻለ አበራ ነበሩ። አቶ ተሻለ በቃለ ምልልሳቸው በጊዜው የነበረውን ሁኔታ በተለይም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት አቶ መንበረ ጸሃይ ስልክ ደውለው የተናገሯቸውን በሚመለከት የሚከተለውን ያሉ ይመስለኛል፦ “እንግዲህ አማሮቹን ልኬልሃለሁ። ምን እንደምታደርጋቸው የምታጣ አይመስለኝም። እንደምውቀው በስንት መስዋእትነት የተገኘውን የብሄር ብሄረሰቦች መብት ሊቀለብሱ የመጡ ደመኞቻችን ናቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አንድ ሁለት የሚባል አይሆንም። የብሄር ብሄረሰብ መብት በተከበረበት ስርአት ኦሮሞ የተጎናጸፈውን መብት ላንተ አልነግርህም ...” አቶ ተሻለ ይህን ትእዛዝ ባለማስፈጸሙ ለትልቅ ሹመት ሊታጭ ሲገባው ህይወቱ አደጋ ላይ እንደወደቀ በመገንዘቡ ከአገር ጥሎ ወጥቷል። የአጣሪ ኮሚቴ ሊቀመናብርትና አባላት ምን እንደደረሰባቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ከላይ የገለጽኳቸው ለህሊናቸው ያደሩ፥ ፍትህና የህግ የበላይነት ምን እንደሆኑ የተረዱ፥ አገዛዙ የሚፈልገውን ሳይሆን ህጉ የሚደነግገውን ለመተግበር የቆረጡ ዳኞች ከአንዱ በስተቀር ሁላቸውም ለህይወታቸው በመስጋት አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። በአገር ውስጥ የቀረው ወንድማችንም ቢሆን ዳኝነትን ደህና ሰንብት ብሎ በሙያው በሌላ መስሪያ ቤት ይሰራ እንደነበር አስታውሳለሁ።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቱንም ያህል የዳኛው ውሳኔ ቆሽጣቸውን ቢያሳርራቸውም ይግባኝ ይሉ እንደሁ እንጂ ውሳኔያቸውን ተጻርሮ ወደቆመው ዳኛ ስልክ ደውለው ማስፈራሪያ ለመስጠት አይሞክሯትም። እንዲህ አይነት ሙከራ እምፒችመንት የሚባል አውሎነፋስ ቀስቅሶ ጠራርጎ ሊወስዳቸው እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። በእኛ ሁኔታ ግን ስልክ የደወለው አቶ መንበረ አራት ሺ በሚደርስ ደመዎዝ ትንግርታዊ በሆነ ሁኔታ የሰራውን ባለ ፔንት ሃውስ ቪላ በወር አምስት ሺ ዶላር አከራይቶ መንግስት ኪራይ በሚከፍለው ውብ ቤት ውስጥ ተንደላቅቆ ሲኖር ለሙያቸው ክብር፥ ለህሊናቸውና ለፍትህ የቆሙትን የአገሬ ልጆች ግን ስደት የሚባል አውሎነፋስ ጠራርጎ ወስዷቸዋል።

አሜሪካንን ታላቅ ያደረጋት የቆረቆሩት አባቶች የማይናወጥ መሰረት ላይ ያኖሯት አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን ተቋሞቿ ከሚገጥማቸው ፈተናዎች ይልቅ ጥንካሬ ያላቸው መሆናቸው ነው። ኢትዮጵያን ያኮሰመናት በአሸዋ ላይ የተገነባች መኖኗ ብቻ ሳይሆን ለ21ኛ ክፍለዘመን በማይመጥኑ ኋላ ቀር ድኩማን እጅ የወደቀች ምስኪን አገር መኖኗም ጭምር ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!