Ustaz Ahmedin Jebel

ኡስታዝ አህመዲን ጀበል

* ፍትሕ ለኡስታዝ አህመዲን ጀበል!

* በግፍ አስሮም ሕክምና መንፈግ ለምን?

* ሐሳብን የደፈረው ጀግና ...!

ነቢዩ ሲራክ

የወንድም ኡስታዝ አህመዲን ጀበልን በእስር ላይ ሕክምና መነፈጉን ከተለያዩ ምንጮች ለማረጋገጥ ችያለሁ። በእስር ላይ ያሉ ወገኖችን በሕገ መንግሥትና በዓለም አቀፍ ሕግ የተደነገገ እየተጣሰባቸው ነው። በሕግ ስር ባለው ኡስታዝ አህመዲንና በብዙ ታሳሪዎች መንግሥት የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈጸመባቸው ተደጋግሞ ተመልክተናል። ዛሬ አደባባይ በአህመዲን ያየነውም ይህንኑ ነው። በኡስታዝ አህመዲን ሰውነት ላይ የሚታየውን ጉዳትና መጎሳቆል ስመለከት የተሰማኝ ስሜት ደስ አይልም።

አሳሪው መንግሥት ደጋግሞ "ኡስታዝ አህመዲንና ጓደኞቹ የታሰሩት በሕግ ጥሰት ነው!" ቢልም፤ የታሰረበት በመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴነቱ ብቻ እንደሆነ አምናሁ። ከታሰሩት በርካታ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መካከል፤ ኡስታዝ አህመዲንን ጨምሮ ጥቂቶች ተለይተው ሲቀሩ፤ ዋና ዋና የተባሉት ተከሳሾች በነጻ ተፈትተዋል። ዛሬ ጎልማሳው ወንድም አህመዲን እንደቀሩት ወንድሞቹ እኩል ከወህኒ እንዲወጣ ባይፈቀድለት እንኳ ሕክምና የማግኘት መብቱ ሊከበርለት ይገባል እላለሁ!

በእስር ላይ ሆኖ ሕክምና አለማግኘት ቀርቶ ሕክምና እያገኙ ኑሮን መግፋት እጅግ የከፋ መከራ ስለመሆኑ ከ4 ዓመት በፊት በሳውዲ የወራት ወህኒ ሕይወቴ አውቀዋለሁ። "ከዐረብ አገራት በተሻለ መልኩ የሰብአዊ መብት ይዞታ ተከብሯል" በምትባለው ኢትዮጵያ አገራችን መሳሪያ ያላነሳ ታሳሪን ሕክምና ነፍጎ ማሰቃየትን የመሰለ የከፋ ግፍ ሲፈጸም ደጋግመን ተመልክተናል። ይህ መራራ እውነት እጅግ በጣም ያሳዝናል። ልብን በኀዘን ይሰብራል። ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በአስቸኳይ ሕክምና ይደረግለት ዘንድ የዜጋ ድምጼን አሰማለሁ!

Ustaz Ahmedin Jebel
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል

ሐሳብን የደፈረውን ጀግና ፍቱት ...!

ወንድም ኡስታዝ አህመዲን ጀበልን ሳስታውስ ብዙ ነገሩ ትዝ ይለኛል። ኡስታዝ አህመዲን ለቆመበት ዓላማ ጽኑ ነው። የሕዝብ ከበሬታ ያሰጠው አስተምህሮት መሆኑንም ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም። ኡስታዝ አህመዲን በሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ተመርጦ በወቅቱ ለነበረው ሁከት መፍትሔ አመንጭ ከነበሩት መካከል አንዱ ነበር። ዳሩ ግን ለመፍትሔ የተወከሉት ”ወንጀለኛ” ተብለው ዘብጥያ ሲወርዱ፤ አህመዲን ክራሞቱ ወህኒ ሆነ። በእሱና በቀሩት ወንድሞች እስር አዘንን።

ኡስታዝ አህመዲን የአገሬ ሰው ለማንሳትና በአደባባይ ለመሞገት ይፈራቸው የነበሩ የሙስሊም ጉዳዮችን በሥራዎቹ እያነሳ የማይደፈር ሐሳብን የደፈረ በመሆኑ አደንቀዋለሁ። በጋዜጦችና በየአደባባዩ ሐሳብን ሲያቀርብና ሲሞግት፣ ከዚያም የታሪክ ድርሳናትን ፈታትሾ ለንባብ ሲያቀርብ ተመልክቻለሁ። አህመዲን ማኅበረሰቡ ውስጥ ይንሸራሸር የነበረውን ሐሳብ በአደባባይ ማውጣቱና መነጋገሪያ ማድረጉን አደንቃለሁ!

ኡስታዝ አህመዲን የጻፋቸውን መጻሕፍት ደጋግሜ ካነበብኳቸው ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው። "ስለ ሙስሊሙ ጉዳት ያገባኛል" ማለቱንና ሐሳቡን በነጻነት መግለጹን አከብርለታለሁ። በመጻሕፍቱ ከሰነጋቸው ሐሳቦችና ምልከታዎቻ ጋር ግን ብዙም አልስማማም። በሐሳብ ልዩነት አምናለሁ፣ የሐሳብ ልዩነት አለን ማለት ሰብአዊ መብቱ ሲጣስ ዝም እላለሁ ማለት አይደለም።

ጎልማሳው ኡስታዝ አህመዲን የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል ሆኖ እያለ ሲጀመር መንግሥት ሆደ ሰፊ በመሆን መፍትሔ አብሮ እንደመፈለግ ማሰሩ ምን ጠቀመ? በግፍ አስሮም ሕክምና መንፈግስ ለምን? ብዬ ደጋግሜ ራሴን ጠይቄያለሁ። አጥጋቢ መልስ ግን የለኝም። በሕግና ሥርዓት እስር ላይ ያለን ፍርደኛ ሕክምና ነፍጎ ማንገላታትና እንዲህ እንዳየነው ከሰው ተራ ማውጣት፤ ግለሰብን ብቻ ሳይሆን ዜጋን መናቅ ማለት ነው። እናም የታሳሪውን ስቃይ ስሰማ ከተናቁት ዜጎች መካከል መሆኔ ተሰምቶኛል። ለኡስታዝ አህመዲን ጀበል ሕክምና ከማድረግ በላይ በሕዝብ ውክልና በመውሰዱ ለወህኒ የተዳረገ ወጣት ነውና፤ በአስቸኳት ትፈቱት ዘንድ የዜጋ ድምፄን አሰማለሁ! ፍትሕ ለኡስታዝ አህመዲንና በግፍ ለሚሰቃዩት ታሳሪዎች!

ወዳጄ ኡስታዝ አህመዲን ሆይ ምሕረቱን ይላክልህ!

እስኪ ቸር ያሰማን!


ነቢዩ ሲራክ

ኅዳር ፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ