Horn of Africa

የአፍሪካ ቀንድ

ኪዳኔ ዓለማየሁ

ክቡር ሆይ፤

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ምክር ቤት ያስተላለፉት መልእክት፤ እንደዚሁም በቅርቡ ሶማሊያ ያከናወኑት ታሪካዊ ጉብኝት፤ አሁን ደግሞ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ስለ አልጀርሱ ስምምነት መተግበር የሰጡት ቀና መልስ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም፤ ሕብረትና ልማት ያለኝን ከአሥር ዓመት በላይ የታገልኩበትን ዓላማና ተስፋ የሚያጠናክር ስለ መሰለኝ በትሕትና ላመሰግንዎ እወዳለሁ።

ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲና ሶማሊያ አሁን ካሉበት ከመከፋፈል፣ ከመናቆር፣ እርስ በርስ ከመጋጨት፣ ከመጠራጠርና ከመነታረክ አባዜ ተላቅቀው፤ ወደ ሰላም፣ ወደ መተባበር፣ ብሎም ወደ አንድነት፣ ወደ መደጋገፍ፣ ወደ መጠቃቀም ቢሸጋገሩ፤ በክፍለ-አሕጉሩ ባለው በአመራር ችግር መንስኤ፣ በድህነት፣ በዴሞክራሲ እጦት ምክንያት በሰብአዊ መብት ጥሰት ፍዳውን እያየ የሚገኘው 125 ሚሊዮን ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ እፎይ የሚልበት ወቅት እንዲከሰት ማድረግ እንደሚቻል ጥርጥር የለኝም። በተጨማሪም፤ በተከሰተው የመከፋፈል አዝማሚያ ለመጠቀም ጦሮቻቸውን በአፍሪካ ቀንድ ካሰፈሩት ከቱርክ፣ ከኢራን፣ ከሳውዲ ዐረቢያ፣ ከዩናይትድ ዐረብ ኤሚሬትስ፣ ወዘተ ... ለመገላገል እንደሚያስችል የታወቀ ነው።

ለዚህም ዓላማ በክቡርነትዎ አማካኝነት የሚከናወነው ከፍተኛ ጥረት እንዲሳካልዎ፤ ተግባርዎ ሁሉ በዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት መከበር ላይ የተመረኮዘ እንደሚሆን ያለኝን ከፍተኛ ተስፋ እገልጻለሁ። በዚህም መሰረት ለሚፈጸመው ትግል ሁላችንም ያልተቆጠበ ድጋፍ ማበርከት እንዳለብን የምገነዘብ መሆኑንም አረገግጣለሁ።

ስለ አፍሪካ ቀንድ ሰላምና ሕብረት ጉዳይ ከዚህ ቀደም ስለ ተከናወነው ጥረት ለመገንዘብ በ(www.hafrica.com) ላይ ያለውን መመልከት ይቻላል። እንደዚሁም ስለ አካባቢው ጉዳይ ቀደም ብዬ የጻፍኩትን እንዲመለከቱልኝ ከዚህ በታች በትሕትና አቀርባለሁ፤

"Horn of Africa: from Glory to Misery, and Hope?" በሚል ርዕስ ያቀረብኹትን ጽሑፍ እዚህ በመጫን ያንብቡ!

ክቡርነትዎ፤ ዱባይና ሌሎችም ያስገኙትን ፈጣን ልማት ኢትዮጵያም ማስገኘት እንደምትችል የገለጹት የሚደገፍ ሐሳብ ነው። በተለይ ዱባይን በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት የማዘጋጃ ቤቱ አማካሪ በመሆን 15 ዓመት አገልግዬ ስለ ነበር የዓይን ምስክር ነኝ። ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር ቸርነት እጅግ ከፍ ያለ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ስለ ሆነች፤ በጥሩ አመራር እጅግ ከፍ ያለ የልማት ውጤት ማስገኘት እንደምትችል የማይጠረጠር ነው።

በተጨማሪም፤ ቀይ ባሕር የምዕራብና የምሥራቅ አገሮች የንግድ መተላለፊያ ብቻ ሆኖ ባካባቢው ያሉ የዐረብና የአፍሪካ አገሮች፤ እንደዚሁም እስራኤል ተፋጥጠው የሚኖሩበት አካባቢ ከመሆን ፈንታ የሕብረት ማዕከል በማቋቋም ለሰላም፤ ለልማትና ለመደጋገፍ የሚያመቻች፤ (Red Sea Cooperative Council) የተሰኘ ድርጅት እንዲመሰርቱ በማክበር አሳስባለሁ። ስለዚሁ ጉዳይና ስለ ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች “My Journey with the United Nations, the Horn of Africa’s Unity and Justice for Ethiopia” በተሰኘው መጽሐፌ ሐሳቤን በሰፊው ገልጫለሁ።

ከፍ ካለ የአክብሮት ሰላምታ ጋር፤

አፍሪካ ቀንድ ሰላም፤ ሕብረት፤ ልማትና ዲሞክራሲ የሰፈነበት አካባቢ እንዲሆን ቸሩ አምላካችን ይርዳን።

ኪዳኔ ዓለማየሁ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ