ደስታዬን ማመቅ አልቻልኩም
አንዱዓለም ተፈራ - የእስከመቼ አዘጋጅ
ያለንበትን ወቅት ማመን አስቸግሮኛል። ከጥቂት ቀናት በፊት የነበረኝ ግንዛቤ፤ ጠቅልሎ ከኔ ጠፋ። ፍጹም ያልጠበቅሁት ክንውን፤ ገሃድ ሆኖ፤ አይደረግም ያልኩት ተፈጽሞ፤ የአገራችን የፖለቲካ ሐቅ ተገለባብጦ ሳገኘው፤ ሰውነቴን ዳሰስኩ። የፈለግሁት ሆነ! ብል ስሕተት ነው። ነገር ግን፤ እየተደረገ ባለው ሂደት ያለሁበትን ማመን አቅቶኛል። ደስ ብሎኛል። ሂደቱ መቀጠል አለበት እላለሁ። ደስታዬን ግን ለራሴ አፍኜ መያዝ አልፈልግም። ለዚህም እንኳን ለዚች ቀን እላለሁ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ድፍረትና ብሩህ ገጽታ አደንቃለሁ። አገራችን አሁን ባለችበት የፖለቲካ ሁኔታ መቀመጥ ነበረባት ወይ? አለባት ወይ? በፍጹም!
አሁን ሁላችንም በያለንበት መገንዘብ ያለብን ሐቅ አለ። አገራችን አሁን ካለችበት የፖለቲካ አዘቅት ወጥታ ወደፊት መሄድ የምትችለው፤ ያለንበትን ተጨባጭ ሐቅ ተረድተን፤ ምን ሊደረግ እንደሚቻልና እንደምንፈልግ በትክክል ስናውቅ ነው። እኔ የምመጣው ከታጋዩ ወገን ነው። ከዘረኛው መንግሥት ምንም ዐይነት በጎ ተግባር አልጠበቅሁም፤ አልጠብቅም። አሁን የተገኘው ዕድል የተከፈተው፤ በሕዝቡ የአመጽ እንቅስቃሴ ነው። ሕዝቡ ከፍተኛ መሥዋዕትን ከፍሎ ነው! ለዚህ የበቃነው። መሉ ምስጋና ለሕዝቡ!
በተጨማሪ፤ እውነተኛ የሕዝብ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲከተል፤ ብዙ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ለዚህ ደግሞ፤ የሕዝቡ የትብብር ጥረት የግድ ነው። ይህ ጥረት፤ ማንንም ለመጥቀም ወይንም ለመርዳት አይደለም። ጥረቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ለመርዳት አይደለም። ራሳችንን ለመርዳት ነው። የአገራችን የፖለቲካ ሂደት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማቅናት፤ እንደ አንድ ሕዝብ ወደፊት ለመሄድ፣ እስካሁን የተበተነውን የጥላቻ ፖለቲካ ለመግራት፣ እያንዳንዱ ዜጋ ግለሰባዊ ነፃነቱ ተመልሶለት አገሩን እንዲወድ፣ ትክክለኛ ልማት እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት ሥር እንዲሰድ፣ ተስፋ እንዲነግሥ፣ ሙስና እንዲገታ፣ ዘረኝነት እንዲከስም፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ርስ በርሳችን እንድንዋደድ በር ይከፍታል።
በፖለቲካ አመለካከታችን ለመሰለፍና በዚያ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመመሥረት ገና መንገድ ላይ ነን። ከዚያ በፊት ሊጠፋ የተዘመተበት ዐማራ፤ የደረሰበት በደል መታወቅ አለበት። የተተከለው የዐማራ የጥላቻ ዘመቻ፤ ለረጅም ጊዜ በመካከላችን የሚኖር ክስተት ነው። በአገራችን ታሪክ ያልተደረገና በደንብ ተጠንቶ፤ መልሶ አንገቱን እንዳያቀና መመታት ያለበት ክንውን ነው። ለዚህ አገራችን ትኩረት ሠጥታ፤ ሙሉ ጥናት ተደርጎበት፤ መስተካከል የሚገባው ተስተካክሎ፤ ሙሉ ጥገናው ተከናውኖ፤ ወደፊት መሄድ አለብን። ወደኋላ ስንዞር አንኖርም። ወደፊት ለመሄድ ግን የነበርንበትን መፈተሽ ግዴታ ነው። ለዚህ በቅተናል። ያማረ ወደፊት እንዲኖረን ደግሞ፤ ሙሉ ኃይላችንን ማስተባበር አለብን።
አንዱዓለም ተፈራ - የእስከመቼ አዘጋጅ
ዓርብ፣ ሰኔ ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓመተ ምህረት (እ.ኤ.አ. 22/6/2018)