Addis Ababa

አዲስ አበባ

ወለላዬ ከስዊድን

ኢትዮጵያ ልሄድ ነው። ይኼን እያሰብኩ እያለሁ እንባዬ ፊቴን ሞላው። እንደደረስኩ እቤት አልገባም። ተቀባዮቼን አስከትዬ ደብረ ሊባኖስ እሄዳለሁ። በናቴ መቃብር ላይ ሻማ ማብራትና አበባ ማስቀመጥ አለብኝ። በቦታው ላይ የማፈሰው እንባ ታየኝ። ከፊሉን አሁኑኑ ዘረገፍኩት። እናቴ ይኸው መጣሁ እናቴ ተቀበይኝ ... ያልቀበርኳት እናቴን ኀዘን በዛ ብቻ አልወጣውም፤ ግርግር ሳይኖር፣ ተው ባይ ሳይከተል፣ ብቻዬን ሌላ ቀን እመጣለሁ። ለናቴ የምነግራት ብዙ ነገር አለኝ። ሠንዬ እመለሳለሁ።

እኔ ውጪ ከወጣሁ ጀምሮ አያሌ ዘመዶቼ በሞት ተለይተውኛል። አባዬ ጀማነሽ አንዷ ናት። ራሷን የሞላው ሽበቷና ወጣ ወጣ ያሉት ጥርሶቿ አይረሳኝም። አያ እንደምን ሰነበትክ ትለኝ ነበር። ጋሼ ሚሊዮንም እዚሁ ካረፈ ቆየ። ምናምን ግዛባት ብሎ የሚያስጨብጠኝ ሳንቲሞች ትዝታዎቼ ናቸው። ጋሼ አሰፋም እዚሁ አለ። ረጅም ቁመናው ቀጥ ብሎ የወረደ አፍንጫው መለያው ነው። መልኩ ጄነራል መንግሥቱ ነዋይን ይመስለኛል። ጋሼ አሰፋ ሥርዓት አክባሪ ነው። እያንዳንዷ ነገር ዝንፍ እንድትል አይፈልግም። ጋሼ አሰፋን እጁን የሚያስታጥብ የፈረደበት ነው። ውሃው አልቆ እንደገና መጨመር ግድ ነው። ከስር ማስታጠቢያው እየሞላ በጉልበቴ ደግፌ ያስታጠኩበትም ቀን አለ። ሌላው የማይረሳኝ፤ ተለቅ ያለች አሻንጉሊት ከፔዦ መኪናው ውስጥ ምንግዜም አትለየውም ነበር። እንደሰው ክብር ይሰጣታል። እቤትም ይዟት የሚገባበት ቀን አለ። የሷ አሻንጉሊት ነገር ምንግዜም እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ ይኖራል።

ሌሎችም ከዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ተፈናቅለው የመጡ ዘመዶች አሉኝ። አስከሬናቸው ነው የተፈናቀለው። አሰግድና መዝሙረ። አሰግድን ዮሴፍ ቆሜ ቀብሬው ነበር። በኋላ እዚህ መዛወሩን ሰማሁ። በሕይወቱ ሲንከራተት ከርሞ፤ ሙት አካሉም መንከራተቱ ኀዘኔን ድርብ ማድረጉ አይቀርሬ ነው። መዝሙረም እዚሁ ነው። መዓዛ፣ ውብሸት ሁሉም የደብረ ሊባኖስን አፈር ነው የለበሱት። መዝሙረ በሕይወት ኖሮ ቢሆን ኖሮ እንዲህ አርጅቼ ስመጣ ቢያየኝ፤ «አባ ጆሊማን መሰልክ» ወይም አንድ ነገር ሳይል አያልፈኝም ነበር። ዳንኤል፣ ጋሽ ፍቅሩ ነፍሳችሁን ይማር! ጋሽ ፍቅሩን ባሰብኩ ቁጥር በወታደር ልብስ ቆሞና ቁጭ ብሎ የተነሳው የኮርያ ፎቶ አይረሳኝም። «እማማ ትሙት!» የሚላት መለያው ናት። በሁሉም መቃብር ላይ ሻማ አበራለሁ፣ አበባም አስቀምጣለሁ። እያንዳንዳቸውን እያሰብኩም እንባዬን አፈሳለሁ።

ከደብረ ሊባኖስ ስወጣ የምሄደው ቀራንዮ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ነው። ጋሼ አበራ አለ። ዶ/ር አበራ ጀምበሬ በጃንሆይ ዘመን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ነበር። ከአያሌ መጽሐፎቹ በተጨማሪ «ድርሳነ ሕይወቴ» በሚል ርዕስ የሕይወት ታሪኩን በተገቢው ሁኔታ ጽፏል። ለአገሩ ጉልበቱን፣ እውቀቱን፣ ሳይሰስት እንዳገለገለ የራሱን ሕይወት በወግ ሳይኖር ያረፈ ሰው ነው። ስምንት ዓመት በደርግ እስር ቤትም አሳልፏል። ለሱም ሻማ አበራለሁ፣ አበባም አስቀምጣለሁ። እንባዬን መቃብሩ ላይ ማንጠባጠቤም የማይቀር ነው።

አሁንም ቤቴ አይታሰብም። ጋሽ ፀጋዬ የተቀበረበት ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ። በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ሐውልት ላይ ሁሉንም ደራሲያንና የጥበብ ሰዎች እያሰብኩ አበባ አኖራለሁ። ፈጣሪ አምላክ ነፍሳቸውን እንዲምር ጸሎቴንም አቀርባለሁ። በዛው ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያንም አቀናለሁ። እኔ ከመጣሁበት ከስዊድን አስክሬኑ መጥቶ እዚሁ ያረፈ ሌላ የሥነጥበብ ሰው አለ። ደራሲና ባለቅኔ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ስዊድን አብረን አሳልፈናል። «ገሞራውን አገኘሁት»፣ «ኑር ያለው ሰውነት» የሚሉ ስለሱ የተጻፉ ግጥሞች ጽፌ በእጁ ሰጥቸዋለሁ። ካረፈ በኋላ የተጻፈው «ዘመን ሞቷል ኃይሉ አትበሉ» የተባለ ግጥሜ በድረገጾች ሊነበብ በቅቷል። ሦስቱም ግጥሞች በቅርቡ በሚታተመው «የእኔ ሽበት» በሚለው የግጥም መጽሐፌ ላይ ተካትተዋል። መታሰቢያነታቸውም ለሱ ይሆናሉ።

ስለ ጋሼ ኃይሉ የቱን ትቼ የቱን እንደማወራ ይጠፋኛል። ብዙ ትዝታ አሉኝ። ጋሼ ኃይሉ ጨዋታ አዋቂ ነው። አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከባለቤቴ ጋር ልንጠይቀው ቤቱ ሄድን። ምሳ በልተን ቡና ጠጥተን በመሰናበት ላይ ነን፣ «ጋሼ ኃይሉ ...» አለች ባለቤቴ፤

«አቤት!»

«እንግዲህ እራስዎትን ጠብቁ»

«እንዴ ለምን እራሴን ብቻ አፌንም፣ እጄንም፣ እግሬንም እጠብቃለሁ።» ብሏት አስቆናል። ወደፊት ታሪክና ሥራውን አሰባስቤ ለመጻፍ እቅድ አለኝ።

ዛሬ ቤት መግባት የለም!። ለእኔ ወደዚህ መምጣት ሕይወታቸውን የከፈሉ የአገሬ ልጆች ያረፉበት ቦታ ሁሉ ማዳረስ አለብኝ። ሽብሬ ደሳለኝ የት ነሽ? በምርጫ 97፣ ከዛም በፊትና በኋላ በየመንገዱ ላይ በጥይት የረገፋችሁት ወንድምና እኅቶቼ የትጋ ነው የወደቃችሁት?። የናተን ደም ረግጨ ማለፍ ውለታ መካድ ነው። ነፍሳችሁ ትወቅሰኛለች። እያንዳንዳችሁ ያረፋችሁበትን ፈልጌ እስካገኝ ድረስ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ፤ ፕሮፌሰር አስራት ወ/የስን ማግኘት አለብኝ። ለአገራቸው ሕዝብ ሰላምና ነጻነት፣ ለፍትሕና ለኩልነት በሽምግልና ዕድሜያቸው እስር ቤት ማቀዋል። በመጨረሻም በዚሁ የእስር ጦስ ሕይወራቸውን አጥተዋል። ፕሮፌሰር አስራት ለሁሉም ወኪል እንዲሆኑልኝ ጉንጉን አበባ ሐውልታቸው ላይ አስቀምጣለሁ። ሁሉንም ጌታ የሰላም እረፍት እንዲሰጥ ሻማ አብርቼ ጸሎት አደርጋለሁ። የሌሎቹ የትም ይሁን የት የመቃብር ቦታቸውን አፈላልጋለሁ። ከኔ ጋር የሚንከራተቱ ዘመዶቼ ይብላኝላቸው እንጂ፤ ይህን ማድረጌ አይቀሬ ነው።

አንድ ቀን ጠዋት በቀጠሮዬ መሰረት ማንንም ሳላስከትል ደብረ ሊባኖስ እሄዳለሁ። ከናቴ ጋር ብቻችንን እንገናኛለን። የሆንኩትን ሁሉ አጫውታታለሁ። ለምን እንዳልቀበርኳት እነግራታለሁ። እስኪወጣልኝም አለቅሳለሁ። ከጎኗ እንደምቀበር እነግራታለሁ። ለዚህም የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟላለሁ። የማደርገውን ሁሉ አልደብቃትም። በሕይወት ዘመኔ እንዳሰብኳት እኖራለሁ። በመጨረሻም ከጎኗ ለዘለዓለም አርፋለሁ።

አዲስ አበባ ሆይ! ስደተኛ ልጅሽ ከብዙ ዓመታት በኋላ መጥቻለሁ ተቀበይኝ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ