ገሞራው - ዘስዊድን

ጦማር ቁጥር 2 (የመጀመሪያው ቁጥር ተከታይ)

ግባዊ ዓላማው እኔን ከምወዳት ሀገሬ ምድር ነቅሎ ለማስወጣት በሆነ ዕቅድ የትውልድ ቦታዬን ዘራቸው ለሆነ ሰው መስጠታቸውን ባለፈው መቅድማዊ መልዕክቴ ላይ መግለጼን ታስታውሱልኛላችሁ። የተፈፀመብኝ በደል እጅግ ቅጥ ያጣ መሆኑን ያነበበው ወገን ሁሉ እንደተረዳልኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

 

በእኔ ላይ የደረሰውን በደል አስቀድሜ ጻፍኩ እንጅ፤ ተመሳሳይ የአፅመ-ርስት ዘረፋ የፈፀሙበት የሀገሬ ሰው ቁጥር ሥፍር ቁጥር የለውም። በየቤቱ ዕንባውን አፍስሶ ቁጭ ብሏል። የአሁለበት ሁኔታ የማያፈናፍን በመሆኑ ብቻ ነው ዝም ጭጭ ብለው የተቀመጡት። እንደዚያም በመሆኑ ይህ የእኔ እሪታ ለእነሱም ጭምር መሆኑን አንባብያን ሁሉ ሊያውቁልኝ እፈልጋለሁ። ነርቭ የሚያቃጥል ከፍተኛ በደል ነው። ይህን ሁለተኛ ጦማሬን የምጽፈው ያ ትንግርተኛ ቦታ በቅርቡ ያሳየውን ልዩ ተዓምር በተቀዳሚ በመግለጽ ነው። ከታማኝ ያካባቢው ምንጮች በደረሰኝ ዜና መሠረት በርስትነት የተረከበው ዘረኛ ሰው፣ ለሚክበው የድንጋይ ካቡ መሠረት ለመጣል አስቦ መሬቱን ሲቆፍር ከዚህ መጣ ተብሎ ታሪኩ ሊነገር ያልቻለ፣ አንዳች ግዙፍ ቋጥኝ ድንጋይ ከውስጡ ብቅ በማለት ለቁፈራው የቀረቡትን ቡልዶዘሮች ሁሉ እየሰባበረ እንደጣላቸው በመሰማቱ ዜናው ለአካባቢው ሰው ሁሉ ተረት ማውጫዎች ሆነዋል አሉ።

 

”የመምሬ መሬት፣

የተገኘ ከጥንት፣

ልቆፍርህ ብሎ፣

ቢደርስ ተንከባሎ

ታንከ ቡልዶዘር

በጥርስ አልባ ነገር!

ከውስጡ በወጣ

በቋጥኝ ባላንጣ!” ... እያሉ የመንደሩ ሰው ሁሉ ይዘይበርታል አሉ። ድንቅሣ!

 

በአዲስ አበባው የመስቀል አደባባይ አካባቢ ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ላይ የሚገኘው ይህ ቦታ በየትኛውም ምክንያታዊ መንስዔ ቢሆን ከባለንብረቶቹ ሕጋዊ ባለቤትነት በስተቀር ሌላ ሰው ሊወስደው የሚያስችለው በቂ ማስረጃ ከሰማይ በታች ሊኖር አይችልም። በዚህም ሰበብ ይመስላል በተከታዩ ሥዕል ላይ እንደሚታየው ለጥ ብሎ በተዝናናው ደልዳላ መሬት ላይ መሠረት መጣሊያ የሚሆን ጉድጓድ ሲቆፍሩ ከየት መጣ የማይሉት ታላቅ ቋጥኝ ድንጋይ ብቅ ብሎ የካባቸውን ስር ያሰናከለባቸው።

 

 

በብዙኀን እንደታመነበት ይህን ዓለመ-ምድር በስተመጨረሻ ላይ ሁላችንም ጥለነው እንደምንሄድ የኃይማኖትም የሣይንስም የፍልስፍናም ሐቆች አስረድተውናል። የሣይንሱ ”Matter is destructive” የሚለው ሐቅ ዓለማችን ዘላለማዊነት (Infinite) እንደሌለው የሚያስረዳ ነው። ይህን ሣይንሳዊ ሐቅ፣ ኃይማኖቶች ሁሉ በየበኩላቸው ሲያስተምሩ ኖረዋል። ታዲያ ያንን ሁላችንም ጥለነው ለምንሄደው ይህ ግብዝ ዓለም ሰዎች ለምን እርስበርስ እንናጭበታለን የሚለው እሳቤ እኔን ሲጎሻሽመኝ ኖሯል። የኋላ ኋላ ሁለት ካሬ ሜትር የመቃብር ቦታ ላይ የምጠናቀቀው ሰው ለምን ለተባለው ሠፊ ቦታ ባለቤትነት እጨቃጨቃለሁ? በማለት ነገሩን እስከጭራሹ ለመተው የዳዳኝም ወቅት ነበር። እንዲያም በማሰብ ጉዳዩን ለመተው በማውጠንጠን ላይ እንዳለሁ የዚህ ቦታ ጉዳይ ሌላ መልክ ይዞ የቀረበ በመሆኑ አቤቱታ ማቅረቡን የመሰረዝ ጉዳይ የደካማነት ስሜት ያሳደረብኝ ተፅዕኖ እንጅ ተፈጥሯዊም ሆነ የሰብዓዊ ሕግ የደነገገውን ሥርዓት መጣስ እንዳይደለ ተገንዝቤ በአቤቱታው ልቀጥልበት ወሰንኩ። እንዴት ዘረኞች በጠራራ ፀኃይ ይውሰዱት?

 

በእርግጥም ሊገፋፋኝ የቻለው ዋነኛው ምክንያት ጉዳይ የሰውን መሠረታዊ የእኩልነት መብት የሚያናጋ መሆኑ ነው። ”አንዱ ሰው ከሌላው ሰው ይበልጣል” የሚል ከበስተጀርባው ያለው ስሑት ሃሳብ ስላለው ውሳኔውን ዝም ብሎ ለመቀበል ጭራሽ አያስችልም። በሀገሩ ላይ ላልጠፋ ቦታ፣ በተለይ ያንን መርጦ ለዘመዱ ለመዳረግ ምን መንፈስ አሳሰበው? ሊሰጠው ቢፈልግ ነፃ የሆነ ሰው የሌለበት ስንት የተንጣለለ መሬት ሞልቶለት የለምን? የፈለገውን ያህል ሰፊ መሬት አይሰጠውም? ...

 

የዓለመ-ምድር ፈጣሪዋ አዶናይ እያንዳንዱን ሰው ሲፈጥረው የሚኖርበት ቦታ አዘጋጅቶለት እንደሆነ ይታወቃል። እያንዳንዱ የሰው ፍጡር የምድሪቱን ሀብት እኩል ተካፍሎ የግሉ ድርሻ እንዲኖረው ተፈጥሯዊ መብቱ ነው። የኔም ጥያቄ ከዚህ መሠረተ-ሃሳብ ላይ ይመነጫል። የሌላ ሰው መሬት ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ የለኝም። የግሌን ማስከበር ግን መብቴ እንደሆነ አውቃለሁ። ”አንዱ ሰው ከሌላው ሰው ይበልጣል” ብለው የእኔን ግላዊ ድርሻ ለዘመዳቸው ቢሰጡ የብሔራዊ ሕግም ሆነ የሰብዓዊ ሞራል ሊደግፋቸው አይችልም። ለትውልድ ርስት መታገል ክብር እንጅ ውርደት አይደለም።

 

ከዚያ ሁሉ ይልቅ እኔን እጅግ ያሳሰበኝ ”በአሁኑ ጊዜ ብሔራውያን ችግሮች አለቅጥ አግጠው፣ አብዛኛውን ዜጋ ቁምስቅሉን በሞት ደረጃ እያሳዩት ባለበት ወቅት እንዴት ለግላዊ ርስት ሽንጤን ገትሬ ልታገል?” የሚለው ወጣሪ ጥያቄ ነው። ወገኖች በሀገር ማዳን ጉዳይ ላይ ባጭር ታጥቀው በሚታገሉበት ጊዜ እኔ እንዴት ለዚያች ቦታ ልንፈራፈር የሚለው ሃሳብ ብዙም ቢከነክነኝም፤ የዚያች መሬት ነገር በስተኋላዋ ያዘለችው ጉዳይ የዜጋዊ መብት ጥያቄ የያዘ በመሆኑ በዓይነቱ ይለይ እንጅ በነገሩ ከፍተኛነት አንፃር የዘረኞችን እብሪታዊ ሥልጣን አከርካሪ አጥንቱን ለመስበር የሚደረግ አንዱ የትግል አካል በመሆኑ ልተወው አልፈለግሁም።

 

”እኛ ከሌላው እንበልጣለን” በሚል ገሐዳዊ ዓይን ያወጣ የትምክህተኞች እብሪት ከነሰንኮፉ ተነቅሎ ከተገቢ ጎልጎታው እስኪቀበር ድረስ፤ በየመልኩ የኢትዮጵያውያን ትግል ያለፋታ መቀጠል ይኖርበታል። ዘረኞቹን በየመስኩ ማዋከቡ ግድ ይላል! ገና ከበረሃ ዋሻዋ እንደወጣች ወያኔ/ኢህአዴግ ”እኔ ወርቅ ነኝ፣ ሌላው ግን ጨርቅ ነው!” ማለቷ የሰው ልጆችን ተፈጥሯዊ እኩልነት ለማስተሐቀር የተሰነዘረ ቃለ-እብሪት ነው። አብዛኛው ”ጨርቅ” የተባለው ወገኔ ”ወርቅ ነኝ” ባዩን ዘረኛ ቅስሙን ሰብሮ እስካላጠፋ ድረስ ሚስቱን ከመንጠቅ፣ ርስቱን ከመውረስ፣ ቤት ንብረቱን ከማፍረስ፣ ከማሰርና ከመግደል ወደ ኋላ አይልም። እንደ መቶ ዓመት ያህል ያስቆጠረው ሁለት ሱባዔ ዓመታት የወያኔ/ኢህአዴግ ዘመን እያንዳንዱን ዜጋ የሕይወት ትርጉምን መላ እንዳሳጣበትና ምድራዊ ኑሮውንም እንዳመሳቀለበት እናውቃለን። ”ወግድ ይሁዳ!” ካላሉት፤ ”... በዱሹ ገብቶ ይፈተፍታል” እንደሚባለው ብሂል የፈለገውን ኢ-ሕጋዊ ነገር ሁሉ ከመተግበር አይመለስም።

 

የዚያች ቦታ አቤቱታዬ በተለየ መልኩ ያንን ሃሳብ ያመላክታል። ምድሪቱን የፈጠረ አዶናይ በእኩልነት ለፈጠረን ልጆቹ ተመጣጣኝ የሆነ ንብረት በእኩልነት እንድንጠቀምበት አደላድሎ ሲሰጠን፤ ጥቂት ድምባዥ የዞረባቸው ወለወልዳዎች፤ ”እኛ ከሌላው እንበልጣለን” በሚል የመታበይ ስሜት ሀገርንና ዜጎችን ሲያወናብዱ ይኖራሉ። ለእነዚህ መሰል አወናባጆች ተገቢውን ምግታር አለመስጠት በራሱ ስህተትም ደካማነትም ይሆናል። ነውም! እኔ ካንተ እበልጣለሁና እኔ ርስትህን ልውሰድ ለሚል አወናባጅ ትንታግ ያለምንም ክርክርና ጥያቄ ቦታውን አሳልፈህ ብትሰጥ፣ ”አንዱ ሰው ሌላውን ሰው ይበልጣል!” የሚለውን ስሑት አስተሳሰብ የመቀበልና የመደገፍ ያህል ሊያስቆጥርና ሊያስገምት ይችላል። ከዚያ ቦታ በስተጀርባ ባለው ቁም ነገር አንፃር በደካማነት ስሜት ያለ ምግታር አሳልፎ መስጠት ከባድ የሆነ የተፈጥሯዊ ሕግ ተቃርኖ ያዘለ በመሆኑ ዝም ብሎ ማስረከብ ሽንፈት ሊሆን ይችላል።

 

በተራ ትይታና ባልባሌ አመለካከት ”ዘላለም ለማልኖርበት ምድር ምን አነታረከኝ ብሎ ጉዳዩን መረን መልቀቅ በስተኋላ ላይ ማምሻም ዕድሜ ነውና ሊያፀፅት ይችላል። እንደዚያ ዓይነቱም ኅሊናዊ ስሌት የገዛ ራስ ሰብዓዊ ድክመትና የግድየለሽነት ባህርይም ነፀብራቅ ሆኖ፣ ያስወቅሳል። የእኔ አቤቱታም ጉዳይ በዚህኛው አቅጣጫም እንዲታይልኝ እፈልጋለሁ። በቀል ሲፈፀም ዝም ብሎ ማየት የፍትህና የሕይወትን መሠረታዊ ሕልውናና ዓምዳዊ ኩነት ያናጋል። ኢ-ርቱዕ በሆነ መንገድም ሕጋዊ የሆነ የግልን ይዞታ አሳልፎ መስጠት የራስን ድቀት መኮድኮድ ይሆናል። ሊያጠፋ የተነሳ ኃይልን በፀጋ መቀበል የተዘራን ውድ የሆነ አዝመራ የአንበጣ፣ የፌንጣና የተምች መንጋ ከዳር እስከዳር ወርሮ ሲያጠፋው ዝም ብሎ እንደማየት ያስቆጥራል። ቆርቆሮ ቢንያኳኩበት እንኳ ሸሽቶ ለሚጠፋ የአንበሳ መንጋ ዝም ብሎ ሲያጠፋ ማየት ሰብዓዊነት አይደለም።

 

ሌላው ቀርቶ ታናናሾቹ እነድመትና እነውሻ የመሳሰሉ እንስሳት እንኳ በየበኩላቸው ሊበሉት ያዘጋጁትን ሥጋ (ምግብ) ሲነኩባቸው ምን ያህል እንደሚንሰፈሰፉና ይዞታቸውንም ለማስከበር ሲሉ ምን ያህል እንደሚከላከሉ በየዕለቱ የምናየው ድርጊት ነው። ውሾና ውሮ ግላዊ ይዞታቸውን ለማስከበር ሲሉ ያን ያህል ሲታገሉ ብዙ ችሎታ ያለው የሰው ልጅማ ከዚያም የበለጠ ለማድረግ አያቅተውም።

 

ያ ቦታ በንብረትነቱ አንፃር የእኛ ግላዊ ሀብት ሆኖ ይኑር እንጅ ሊሰጠው በሚችለው ጥቅም አንፃር ቤሳ ሣንቲም ሳናገኝበት ኖረናል። ድህነት የተባለው የኢትዮጵያውያን ጠንቅ ፈትሎና አዳውሮ ባለበሰን ችግር የተነሳ በቦታው እንዳሉ ጎረቤቶች ዓይነት የሆነ ዛኒጋባ ቀልሰን መለስተኛ ገቢ ማድረግ አልቻልንም። ጎረቤቶቹም በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ሲዝቁበት ኖረዋል። ትዝብቱን ለሀገሬ ኢትዮጵያ እተወዋለሁ።

 

ኩነቶችን በየመልካቸው ሰፋ አደርጎ ለማየት የሚችል ሰው፣ ዓለማችን በከፍተኛ ጣዕር እንዳለች ይገነዘባል። ዓየር፣ ውሃ፣ አፈር፣ ፀኃይ፣ ... ጤነኞች አይደሉም። በእነሱም ሕመም የተነሳ አጠቃላዩ ምድርችን እየተመሳቀለ ነው። በአንድ በኩል ከፍተኛ ድርቀት ሲያጋያት፣ በዚያው አንፃር ደግሞ በየሀገሩ ታላላቅ ማዕበል እየተነሳ ምድሩን በማጥለቅለቅ እየተናወጠው ነው። ምድር የሚመኩባት መኖሪያ እንዳልሆነች እነዚህ ኩነቶች ከፍተኛ ማገናዘቢያ ምልክቶች ናቸው።

 

በእርግጥም የዚህ ዓለም ንብረት በጣም የሚጓጉለት አይደለም። አያስተማምንም። እንደዚያም ሆኖ ግን የማንም ድንባዣም፣ ኩታራና ጥናዣም ወለወልዳ ድንገት ከበረሃ ተነስቶ በመምጣት፤ ጠብመንጃ ቀድሞ በማንገቡ ብቻ ተወልደህ ያደግህበትን ቦታ በግድ ካልወሰድኩብህ ብሎ ቡራ ከረዩ ሲልና የእብሪት ልጋጉን ሲረጭብህ እንዴት ሁኔታው አስችሎህ ዝም ትላለህ? ይህ ነቁጣዊነት ነጥብ ነው ይህንን የአቤቱታ ደብዳቤና ለወገን ህዝብና ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከታቸው ጠላቶች ለመጻፍ ያስገድደኝ።

 

ይህ ቦታ ህዝባዊ መንግሥት ኖሮ ለህዝብ ጥቅም ልናውለው ነው ብሎ ሕጋዊ ውሳኔ ቢሰጥበት ኖሮ ቦታውን በሙሉ ፍንደቃ ለማስረከብ ምንግዜም ዝግጁ ነኝ። የሆነው ግን የማንም የፖለቲካ ጠንጋራ የዘረኛ ንክ ስሜቱ እንደው በማን አለብኝ ይሉኝታ ቢስ ስሜት ”ቦታህን ለዘመዴ ሰጥቸዋለሁ!” ቢለኝ፤ ”መተኮስ” ባያመቸኝ ”መለኮስ” አያቅተኝምና የአቤቱታዬ ስንዘራ የዛ ውጤት ነው።

 

በሌላ በኩል ደግሞ ”አንድ ኀሙስ ዕድሜ” የቀረው ወያኔ/ኢህአዴግ እየተደናበረች የምትሠራውን በደል፣ ፍዳ፣ ስቃይና መከራ በቆየ ልምዴ መሰረት ግጥምም ሆነ መጣጥፍ እያዘጋጀሁ የምጠዘጥዝበትን፤ ለአቤቱታ መጻፍያ እንዳደርገው ጊዜ ስለወሰደችብኝ እጅግ አዝናለሁ። ተከታዩን ደብዳቤ (ጦማር ቁጥር 3) ካወጣሁ በኋላ ወደ አስለመድኩት ግጥም፣ ቅኔና መጣጥፍ ስለማቀርብ እስከዛው በያላችሁበት አንባቢዎች ሁሉ ደኅና ቆዩልኝ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!