ያሬድ ክንፈ ከስዊድን

በዕለተ ቅዳሜ ኅዳር 6 ቀን 2001 ዓ.ም. ከምኖርባት ከተማ 200 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው የስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ያቀናሁት በመኺና ነበር። በዕለቱ የጉዞዬ ዋና ዓላማ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እና አቶ አክሉ ግርግሬ (የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ አባልና የዕቅድና የስትራቴጂ ኃላፊ) ከኢትዮጵያውያን ጋር ከቀኑ በ7 ሰዓት ሊያደርጉ ያቀዱትን ውይይት መሳተፍ ነበር።

 

በቀጥታ ያቀናሁት ነዋሪነቱ ስቶክሆልም ወደሆነ አንድ ባለትዳር ወዳጄ ጋር ነበር። ከጠዋት ጀምሬ ከወዳጄ ጋር በየመሃሉ እየተደዋወልን ነበር። እነሱ ቤት ገብቼ ምሳ በልተን አንድ ላይ እንድንወጣ ወዳጄም ባለቤቱም ወተወቱኝ። መኪና ውስጥ መንገድ ጠቋሚ (ናቪጌተር) ስለነበረች እቤታቸው የምደርስበትን ሰዓት ስለምትናገር፤ ”ጊዜ አይኖረንም” የሚል ስጋቴን ገለጥኩላቸውና እነሱ ምሳቸውን በልተው እንዲጠብቁኝ፤ ባይሆን እኔ በቁሜም ይሁን መኪና ውስጥ እየበላሁ እሄዳለሁ በሚለው ተስማማን። እነሱ ግን ”7 ሰዓት ተብሎ 8 ሰዓት ነው የሚጀመረው” እያሉ ሲወተውቱኝና እንዳልጣደፍ ሲመክሩኝ ነበር።

 

እነሱ ጋር ስደርስ 6 ሰዓት ነበር። አንድ ሰዓት ቀሪ ጊዜ እንዳለን ስረዳ፤ ምን የመሰለ ጥብስና ክትፎ በልቼ፤ ተያይዘን ወደ ስብሰባው በመኺና አመራን። ለ7 ሰዓት 10 ጉዳይ አካባቢ ደረስን። በጣም በሚገርም ሁኔታ በጣት የምንቆጠር ሰዎች ብቻ ነበርን በዚያን ሰዓት የደረስነው። ሰዉ ሁሉ እየተንጠባጠበ ብቅ ብቅ ይል ጀመር። ወደ 8 ሰዓት ተኩል አካባቢ አዳራሹ በሰው ተሞላ። ስብሰባው ይጀመራል ከተባለበት የአንድ ሰዓት ተኩል ጊዜ በኋላም ቢሆን ሰዉ መምጣቱን አላቆመም። በመጨረሻም እንግዶቹ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ አርፍደው 9 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ ወደ አዳራሹ ገቡ። ለነገሩ በሰዓቱ ቢገኙ ኑሮ ምን ያደርጉ ነበር? …

 

9፡20 ሰዓት፦ መድረክ ላይ ከሁለቱ እንግዶች በተጨማሪ ተሰይመው የነበሩት በስዊድን የአንድነት ድጋፍ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ታምራት አዳሙ እና ፀሐፊው አቶ ስሜነህ ታምራት ነበሩ። አቶ ስሜነህ የልዑካን ቡድኑ መምጣቱን አስመልክቶ የተሰማቸውን ደስታ ገልጠው፤ በዕለቱ የተያዘውን ፕሮግራም አስተዋውቀው፤ አቶ ታምራትን ወደ መድረኩ ጋበዙ።

 

9፡26 ሰዓት፦ አቶ ታምራት የ10 ደቂቃ ንግግር አድርገዋል። ሁላችንም በያለንበት ለሀገራችን የምንመኝላት ሠላም፣ ዲሞክራሲ፣ አንድነት፣ … ገና እንዳልደረስንበት አስረድተው፤ ”ወቅቱ ተስፋ ቆርጠን ራሳችንን ለባርነት የምናዘጋጅበት ሳይሆን፤ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከስህተቶቻችን ተምረን፣ ዛሬም እንደገና ለትግል ታጥቀን መነሳት ይኖርብናል። … የራሳችንን የቀድሞ የትግል አስተዋጽዖ መመርመር ይገባናል” ሲሉ ተናግረዋል።

 

”እርስ በእርሳችን ለመደማመጥ ተዘጋጅተናል ወይ? … ስለአንድነት ስናወራ ራሳችንን ከዘረኝነት አላቀናል ወይ? … የምንለውና የምንሠራው አንድ ነው ወይ? …” ሲሉ ጠይቀዋል። የሁለት ሴቶች ልጆች አባት መሆናቸውን ገልጠው፤ ”… የወለላዬን ”የኔ ሽበት” የሚል ግጥም ሳነብ የኮረኮሩኝን ያህል ስስቅ፤ ”ሽበቴን በሀገሬ ላይ ቢያደርግልኝ” የሚል ምኞት አለኝ። ከልጆቼ ጋር በማደርገው ውይይት ”ወሳኝ እኔ ነኝ” ብዬ ስላቸው፤ እሳት የበሉ ተከራካሪዎች ናቸው። ያሸንፉኛል። ምርር ብዬ ስከራከር፤ አንዷ ”አሁንስ የታሊባንን አስተሳሰብ አመጣህ” ብላኛለች” ብለው ካሉ በኋላ፤ ”እኔ ብቻ ልሰማ፣ እኔ ብቻ ልወስን” ከሚለው አስተሳሰባችን መላቀቅ አለብን ብለዋል። በመቀጠልም ወ/ት ብርቱካንን ወደ መድረኩ ጋበዙ።

 

9፡37 ሰዓት፦ ወ/ት ብርቱካን ንግግራቸውን የጀመሩት ተሰብሳቢውንና በስዊድን ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በማመስገን ነበር። በተለይም የቅንጅት አመራሮች ከእስር እንዲፈቱ ላደረጉት ጥረት አመስግነዋል። የፓርቲውን የአውሮፓ የጉዞውን ዓላማ በተመለከተ፤ የፓርቲውን ማንነት ይበልጥ ለማብራራት፣ ፓርቲው ምን ሊሠራ አቅዷል? ደጋፊዎቹስ ምን እንዲሠራ ይፈልጋሉ፣ ምንስ ይመክራሉ? ... በሚሉ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት መሆኑን ገልፀዋል።

W/t Birtukan

ቅንጅት በምርጫ 97 ዓለምንም ሆነ መላውን ኢትዮጵያውያንን ያስደነቀ ፓርቲ እንዲሆን ያደረገው፤ ኅብረተሰቡ ውስጥ የነበረ የነፃነት ናፍቆት እንደነበርና ፓርቲውም የኅብረተሰቡን ሃሳብ በማስተጋባቱ እንደሆነ ገልፀው፤ ፓርቲው አቅም ነበረው ወይ? አጥንት ነበረው ወይ? ሥጋ ነበረው ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ፓርቲያቸው መጠየቁንና ምላሹ ”አልነበረውም” የሚል እንደሆነ ገልፀዋል። ”... ከእኛም አልፎ ተርፎ እናንተንም ያሳፈረ፣ ያስደነገጠ፣ በተወሰነ ደረጃ ለመከፋፈል የተገዳደረ ችግር መሃከላችን ተፈጥሮ አይታችኋል። ያንን ውጤት ያመጣ ቅንጅት፤ ያለመለትን ሃሳብ፣ የተሸከመውን ያንን መንፈስ፣ ... ወደ እውነት መለወጥ የሚችልበት አቅም ያልነበረው በመሆኑ ነው። ... አንድነት ወደፊት እየገሰገሰ ነው ስንል፤ ዛሬ የአንድነት እንቅስቃሴዎች የቅንጅትን መንፈስ ሥጋ ለማልበስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ናቸው። እያንዳንዱ የሚሄድባቸው መንገዶችና የሚፈጽማቸው ተግባራት ይሄንን የሚያደርጉ ናቸው። ከዚህ በኋላ ለሰው ተስፋ ሰጥተን የምናቆም ኃይሎች አንሆንም። ተስፋን እውን ለማድረግ አቅም ያዳበርንና የገነባን ፓርቲ ነው የምንሆነው” በማለት ወ/ት ብርቱካን ተናግረዋል።

 

አንድነት ፓርቲ እንደህዝብና እንደፓርቲ ሁለተኛ ዕድልን ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት ወ/ት ብርቱካን፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ወገኖች በተደጋጋሚ የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎችና ክርክሮች ጠቅሰዋል። ”97 የሆነው እውን ይደገማል? እውን ኢህአዲግ በሠላማዊ ትግል ይሄዳል? እውን ሠላማዊ ትግል አሁንም ይቻላል? ...” እነዚህንና የመሳሰሉት ጥያቄዎች የሚደጋገሙት መዛል መኖሩን ያሳያሉ ብለዋል። ይህንን መዛል በቦክስ ተጋጣሚዎች አድርገው በምሳሌ አስረድተዋል። ተመትቶ ተዘርሮ ከወደቀ በኋላ ከወደቀበት የማይነሳ ቦክሰኛ እንዳለ ሁሉ፤ ሌላው ደግሞ ወድቆ ቀርቷል ተብሎ መቆጠር ከመጀመረበት በኋላ ቀስ ብሎ የሚነሳና፤ እንዲያውም የግጥሚያውን ውጤት በሚገርም ሁኔታ ቀይሮ ለማሸነፍ የሚበቃ መኖሩን ገልጸው፤ እንደመጀመሪያው ዓይነት ቦክሰኛ ተዘርረን በዛው ወድቀን መቅረት የለብንም፤ ያንን ካደረግን እኛን ብቻ ሳይሆን ሀገራችንንም ነው የምንጎዳት በማለት አስረድተዋል።

 

”ዛሬ ትግላችንን ካቆምነው እንደቦክሰኛው ሽንፈት ነው። እንደህዝብ፣ እንደፖለቲከኛ/ፓርቲ ሁለተኛ ዕድል ለራሳችን ልንሠጥ ይገባል … አሁንም የ97 ተዓምርን የፈጠረ ኃይል ዛሬም በቦታው አለ። ለራሳችን ሁለተኛ ዕድል መሥጠት ከቻልን ታሪክ እንሠራለን። ”አይሆንም!”፣ ”እንዴት ይቻላል?” … የሚለውን ትተን አንዴ ዕድል እንሥጥ፤ ያኔ የወደቅነውን ሣይሆን የሠራነውን ታሪክ እናስታውሰው … እንደገና ታሪክ እንሥራ!፣ እንደገና ለራሳችን ዕድል እንስጥ! እንደገና ለሀገራችን ዕድል እንስጥ! ...” ብለዋል ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ።

 

Ato Akelu15፡49 ሰዓት፦ አቶ አክሉ ግርግሬ ማርፈዳቸውን አስመልክተው ይቅርታ በመጠየቅ ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት። እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ በፈረንጅ ሀገር የምንኖረው ሐበሾች ላይ ማሸሞራቸው (በዘወርዋራ መወረፋቸው) ነበር። እኛ በጊዜ ብንሰበሰብ ኑሮ፤ እነሱም በጊዜ ይመጡ እንደነበር እናውቃለንና። አቶ አክሉ የእኛን ጥፋት ወደእራሳቸው የወሰዱ ደግ ሰው ናቸው።

 

አቶ አክሉን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ያየኋቸው በዚህ ስብሰባ ላይ ነው። ባደረጉት የ40 ደቂቃ ንግግር የዳሰሱት የፓርቲውን አወቃቀርና የሥልጣን ተዋረድ፣ የሥራ ዕቅዶች፣ ራዕዩን፣ የአጭር ጊዜ ተልዕኮውን፣ የረዥም ጊዜ ዓላማዎቹን፣ ለ2001 ያለውን ፕሮግራም፣ ስልቱን፣ ፓርቲው ለዓላማዎቹ እውን መሆን በታሳቢነት ያስፈልጋሉ ስለሚላቸው ነገሮች፣ የፓርቲውን እንቅስቃሴዎች፣ በጀቱን፣ የገቢ ምንጩን፣ ጽሕፈት ቤቶች ስለመክፈት፣ ስለምርጫ 2002 ዓ.ም. (2010 እ.ኤ.አ.)፣ ስለማኒፌስቶው፣ ... እጅግ አጭር በሆነ፣ ባልተንዛዛ ሁኔታ፣ አሰልቺ ባልሆነ መንገድ ለተሰብሳቢው በግልጽ ቋንቋ አስረድተዋል።

 

እንደ አቶ አክሉ ገለጻ ከሆነ ፓርቲያቸው በሥራ ተፈትኖ የታረመ ቀልጣፋ ሥርዓት እንደሚገነባ ገልጸው፤ ፓርቲው እገነባዋለሁ ብሎ ያለመውን በተለይም አመራሩ ማንኛቸውንም መንቀጥቀጥና ችግሮችን ሊቋቋም የሚችል (ሾክ አብዞርቨር)፣ ከስሜታዊ ነገር ተላቅቆ ውሳኔ መስጠት የሚችል፣ ግራ ቀኙን መገምገምና መመርመር የሚችል ይሆን ዘንድ የደጋፊዎቹም አስተዋጽዖና ተሳትፎን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

 

በምርጫ 97 አንዲት የአሜሪካ ዲፕሎማት ”ይህቺን ታክል ዲሞክራሲ ትበቃችኋለች” ማለቷን አውስተው፤ በምዕራባውያን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዲፕሎማሲው ረገድ ትልቅ ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል። ”ምዕራባውያን ዘላለማዊ ጥገኛ ሊያደርጉን ካልፈለጉ ሊረዱን ይገባል ... ሚዛናዊ በመሆን ሊረዱን ይችላሉ” በማለት ሁሉም ወገን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።

 

”ቃል መግባት አልወድም” ያሉት አቶ አክሉ፤ የሁሉም ድጋፍ ከታከለበት፣ በፓርቲው ዕቅድ መሠረት ሁሉም በያለበት ከተደራጀ፤ ምንም እንኳን ችግሮች ሊኖሩ ቢችሉም፤ ፓርቲያቸው እስከ ነኀሴ 2002 ዓ.ም. (2010) ያቀደው ላይ ለመድረስ እንደሚችል ቃል ገብተዋል።

 

Welelaye (Ato Matias)

16፡33 ሰዓት፦ ወለላዬ በሚለው የብዕር ስም የሚታወቀው አቶ ማትያስ ከተማ ”እኔም አለኝ ሕልም” እና ”የኔ ሽበት” የሚሉትን ግጥሞቹን አንብቧል። በተለይም ”የኔ ሽበት” የሚለው ግጥሙ ተሰብሳቢውን በተደጋጋሚ ሲያስቅና ሲያስጨበጭብ የነበረ ሲሆን፣ በየመሃሉም በኀዘን ከንፈር ያስመጠጠ ነበር።

 

The public while Welelaye reading

16፡42 ሰዓት፦ ጥያቄና መልስ ተጀመረ።

 

ጠያቂ - አቶ እንዳለ፦ ሀገር ቤት ሆናችሁ ትግል ማካሄዳችሁ የሚያስመሰግን ነው። 1ኛው ሠላማዊ ትግልን መርጣችኋል፣ በምርጫ ለማሸነፍ ምኞታችሁ - ጥሩ ምኞት ነው - እግዜር ከእናንተ ጋር ይሁን! … ያለው መንግሥት ምን ፍንጭ እያሳየ ነው (ለሠላማዊ ትግል) - ምርጫ ቦርድን በመቀየር በኩል፣ ነፃ ሚዲያውን በመቀየር በኩል ምን እያደረገ ነው? … ይህንን ሁሉ ተስፋ ስታደርጉ፣ ይህ መንግሥት ይለወጣል ብላችሁ ታስባላችሁ ወይ? ከመንግሥት አቅጣጫ ምን የታዘባችሁት አለ?

 

ጠያቂ - አቶ በላይ፦ … ሠላማዊ ትግል የትም አያደርስም! … በዚህ የትግል መስመር የትም እንደማትደርሱ አምናለሁ። በአንድ ዓመት ውስጥ ትፈርሳላችሁ። … ከኢህአዲግ ጋር የሚደረግ ትግል ፀረ-አረመኔ፣ ፀረ-ባንዳ፣ ፀረ-ፈረንጅ፣ ... መሆን አለበት። መጀመሪያ መደረግ ያለበት ትግል ይሄ ነው። ካለዚህ ትግል በስተቀር ምንም ብታደርጉ በአንድም በሁለትም ዓመት ምንም ውጤት ሳታሳዩ እንደምትፈራርሱ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ...

 

የወ/ት ብርቱካን ምላሽ

የአቶ በላይ ጥያቄም አስተያየት የተቀላቀለባቸው ናቸው። የቀድሞው ቅንጅትም ሆነ የአሁኑ አንድነት እንዲህ የሁሉም ጠላት (ፀረ-ሁሉም ጠላት) የሆነ ትግል ውስጥ ራሴን አልከትም። ሁሉን ለማጥፋትና ከሁለም ጋር በመጣላት ማን ሊቀር/ሊተርፍ ነው?

 

ለአቶ እንዳለ ምላሽ፦ ሕግ የሚባሉ፤ ነገር ግን መሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶችን የማያከብሩ ሕጎች እየወጡ እንደሆነ ይታወቃል። ለተቃውሞ ያለውን ቦታ እያጠበበው እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ባለንበት ሁኔታ በመንግሥት በኩል ፈቃደኝነት እንደሌለ ግለጽ ነው። ደጋግሞ እያሳየው ነው የሚገኘው። ነገር ግን በዋናነት ሀገሪቷ የኢህአዲግ ብቻ አይደለችም። ሀገሪቷ በዋናነት የዜጎችዋ ሀብት ነች። የሀገሪቷን ዕጣ ፈንታ የኢህአዲግ ፈቃድ ብቻ የሚወስነው አይደለም። (ጭብጨባ) የእኛም ፈቃድ፣ የእኛም እንቅስቃሴ፤ በፈቃዱ፣ ያለፈቃዱ የዚህችን ሀገር ዕጣ ይወስናል ብለን ነው የምንንቀሳቀሰው። ዛሬ እንዲህ ያለ አዝማሚያ እየታየ ነው። እኛም ጋር፣ ህዝቡም ጋር ይህንን ለማስቀየር የሚችል አቅም አለ። እንደገና እንደህዝብ የምንያያዝበትን፣ እንደገና ተፅዕኖ ማሳደር የምንችልበትን፣ እንደገና አስፈሪ ሆነን የምንመጣበትን፣ … በየቀኑ እየሠራን ነው ያለነው። እኛ ብቻ አይደለንም በዚህ የፖለቲካ መድረክ ላይ ያለነው፣ ሌሎችም ባለጉዳዮች አሉ። … አንድነት መሬት የረገጠ ፓርቲ መሆኑን፤ እንደበፊቱ ሲነኩት የማይፈርስ፤ ሲገፉት መልሶ የሚገፋ ፓርቲ መሆኑን ሲያውቁ ሁሉም ወገኖች ያግዙታል፤ የአቶ መለስን መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያሟላ ያስገድዱታል፣ ይጫኑታል፣ ሃሳቡን እንዲቀይር ያደርጉታል፣ …። ሜዳውን ለኢህአዲግ ብቻ አንለቅም፤ ሜዳው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ...

 

እስር ቤት በነበርኩ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ተገርፈዋል፣ ተንገላትተዋል፣ በጣም ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። በተለይ ሴቶቹ ላይ የደረሰውን ስሰማ አስብ የነበረው ምንድን ነው፣ … ይሄን ያህል ገራፊና አንገላቺ ኢትዮጵያውያን አሉ ማለት ነው? ... እነዚህን ገራፊዎች ቦታ ለማሳጣትና፣ መግረፍ ቢፈልጉም እንዳይገርፉ ማድረግ ነው የእኛ ፍላጎት። የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በህዝቡ ውስጥ እንዲሰርጹ (እንደምዕራባውያን) ማድረግ ነው። ቅንጅት ሥራውን ጀምሮ፤ አልጨረሳቸውም። ገና ያልተነኩ፣ ያልተሠሩ፣ ያልተገበርናቸው፣ … ብዙ ሥራዎች ይቀሩናል። እኛ እነዚያን እውን ለማድረግ ነው የምንሠራው። እንደወለላዬ ሕልም - ሕልሜ ፍንትው ብሎኛል እንዳለው፤ ይሄም የማይሆንበት ምክንያት የለም - አጭር ጊዜ ነው …

 

የአቶ አክሉ ግርግሬ ምላሽ፦ ... ፕሮግራሙ በሙሉ ቅስቀሳን፣ ህዝብን ማነሳሳት፣ … የሚሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ያልናቸውን ነገሮች፣ ዲሞክራሲን ለመገንባት መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ናቸውና። … ነባራዊ ሁኔታዎች አስገድዶት፣ … ውስጡ፣ የድርጅት ይዘቱ፣ … ወደ ውስጥ ገብታችሁ ብትመለከቱት ሁለት ቅንጅት ነበር ማለት ይቻላል። አራትም ልታደርጉት ትችላላችሁ። ከቅንጅት መሠረታዊ ከሆኑ ችግሮቹ ተነስተን ነው፤ አንድነትን የመሰረትነው። ... ህዝባዊ ተነሳሽነት ብዙ ሥራ ይቀረዋል። (የታሰሩት ፍ/ቤት ይቀርቡ የነበረው 6 ኪሎ ነበር፤ ችሎቱን ለመከታተል ግን ይሄድ የነበረው ሰው ጥቂት ነበር፤ እኔ እጠብቅ የነበረው ሰልፍ እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ድረስ ነበር) … ጠንካራ ድርጅት ቢኖረን ኖሮ ህዝቡን ለሠላማዊ ትግል ማነሳሳት ይቻል ነበር፤ እስረኞቹም ወዲያው ሊፈቱ ይችላሉ ነበር። ሠላማዊ ትግልን ሰፋ አድርገን መመልከት አለብን። የትኛው ገጠር፣ የትኛው ገበሬ ማኅበር፣ ... ተገብቶ ነው ሥራ የተሠራው? ... እነዚህ እነዚህ ነገሮች መታየት አለባቸው። ”ይቻላል ወይ? እነዚህን ነገሮች ለማድረግ?” - ”አዎ ይቻላል!” ... ሠላማዊ ትግል ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ክፍተት አለው። ያ ክፍተት ሊሞላ ይገባል።

 

ጥያቄዎች

ጠያቂ አቶ ፍስሃ፦ በመጀመሪያ ለተከፈለው መስዋዕትነትና ወደፊት ሊሠሩ ለታቀዱት ሥራዎች ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ። ጥያቄ የለኝም፣ አስተያየት ነው። በሀገር ቤት የተጀመሩትንና የሚሠሩትን ሥራዎች የማሳወቅና መረጃ የመስጠት ሥራ ከእናንተ ይጠበቃል። በውጭ ላለውም ጭምር። ... ስደተኛው ዜግነቱን ኤርትራዊ፣ ሶማሌ፣ … ነኝ እያለና ኢትዮጵያዊነቱን እየሸሸ ነው ያለው። በዚህ ላይ ብትሠሩ መልካም ነው።

 

መሰዳደቡ መቆም አለበት። ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ አየር መንገድ የመምረጥ መብት አለኝ። ”ሌላውን አየር መንገድ መጠቀም የለብህም” ብሎ ማስቆም አይቻልም። አንድነትን አትደግፉ መባል የለበትም።

 

በየቀበሌውና በየገበሬ ማኅበሩ አልሠሩም የተባለው ቅር አሰኝቶኛል። እኔ ራሴም ግርድዳ የሌለበት ቦታ ነው የታሰርኩትና የተሰቃየሁት። እስካሁንም ፍትህ አጥተው (እንዳንቺ ትክክለኛና ጥሩ ዳኛ አጥተው) የታሰሩ ሰዎች አሉ። እናንተ በከተማ አልሠራችሁ ይሆናል እንጂ፤ እኛ በገጠር ሠርተናል።

 

አጋንንት የሚባለውን ስሎ ማሳየት አይቻልም። ነገር ግን ነፃ ምርጫ ከተደረገ አጋንንትም ኢህአዲግን ያሸንፈዋል። - እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!

 

ጠያቂ አቶ ደረጀ፦ እነ ወ/ት ብርቱካን እዚህ ስለመጣችሁ ላመሰግን እወዳለሁ። ታስራችሁ የተፈታችሁት ይቅርታ በመጠየቅ ነው? ወይንስ በምንድነው? ምንስ ማስረጃ አላችሁ - በይቅርታ ካልተፈታችሁ?

 

በአውሮፓና በአሜሪካ ስትዞሩ ነው የምትታዩት። በአፍሪካ አልሄዳችሁም፤ … ለምን?

 

ጠያቂ አቶ ዳንኤል፦ የፈራረሳችሁትን አሰባስባችሁ ድርጅታችሁን እያጠናከራችሁ ነው ያላችሁት። ድጋፌንና አድናቆቴን ልገልጽ እወዳለሁ። ”አንድነት ኃይል ነው!”። ለብሔራዊ እርቅ ከሌሎች ጋር አንድነት ለመፍጠር የምታደርጉት ነገር የለም? በዚህ ልባችን ደምቷል፤ ከሌሎች ጋር የመተባበራችሁን ነገር ምን ልታደርጉት አስባችኋል?

 

ፓርላማ ውስጥ ከገቡት ድርጅቶች ምን ተምራችኋል? … የእነዚያን ውድቀትና መኮርኮም እያየን እንዴት እናንተ ፓርላማ ለመግባት …

 

ዕረፍት - 11፡58 - 12፡40

 

የወ/ት ብርቱካን ምላሽ፦ ለአቶ ፍሰሃ አስተያየት- በገጠር ምርጫውን ለመቆጣጠር፣ የምርጫ ታዛቢዎችን አላሰልፍንም ነበር። ድርጅታዊ ሥራ አልተሠራም። … የመወራረፉ ነገር መኖር የለበትም፤ እያንዳንዱ ፓርቲ በራሱ መንገድ ተከትሎና ተከባብሮ መሄድ ይችላል። አንተ በአየር መንገዶች ምሳሌ አቅልለህ ነው ያቀረብከው። እንደዛ ቀላል አይደለም፤ … አዲስ አበባ ላይ (ዲሞክራሲያ) ላይ አልደረስንም። ኢህአዲግን (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራዊያዊ ግንባር) ውሰዱ፤ ዲሞክራሲያዊ የሚለውን አስምሩበት። የታገሉት ሰዎች ዲሞክራሲን ለማምጣት ነበር፤ ነገር ግን የመጣውን አይተናል። … በመጠቃቃትና በኃይል የሚመጣ ለውጥ የለም። የሂደቱ ድምር ነው ውጤቱ። … ቅድም እንዳልኳችሁ ገራፊ የሚታጠበትን … በሕግና በሕግ ብቻ (በሠላማዊ ትግል) … ነው ዲሞክራሲ የሚገነባው። ... እንዳለመታደል ሆኖ ዲሞክራሲ አጭር መንገድ የለውም።

 

በጎረቤት ሀገር ለተባለው ነገር - ሶማሊያ መንግሥት የላትም፣ በኬንያም ዲሞክራሲ ገና አልተገነባም፣ … በእርግጥ ከሌሎች መማርና ልምድ መውሰድ ይቻላል። ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ግን ገና ናቸው … ደቡብ አፍሪካና ቦትስዋና ካልሆኑ በስተቀር …

 

መሥራት እየቻልን ያልሠራናቸው ነገሮች ነበሩ። … ቅንጅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሊኖረው የሚገባውን ጥንካሬ ነበረው ወይ? አሳይቷል ወይ? … መስከረም 14 የቅንጅት ም/ሊቀመንበር ሆኜ ስመረጥ፤ እነኝህን ልንሠራቸው አቅደን፤ ነገር ግን በጊዜያዊ ሥራዎች ላይ ተጠምደን ስለነበር፤ አልሠራናቸውም።

 

ከምርጫው በኋላ ግማሾቻችን ፓርላማ፣ እስር ቤት፣ … የገባነው በኢህአዲግ ዲክቴት የተደረገ ነው። በዚያ አይነት ሁኔታና መንገድ አሁንም አንሄድለትም። ተቀናቃኛችን በቀደደልን ቦይ አንሄድም።

 

ሽምግልና ለተባለው - እኛ ከታሰርን በኋላ ነው የይቅርታ ቦርድ የተቋቋመው። በሽምግልና በባህላዊ መንገድ ነው የጨረስነው። ይቅርታ አልጠየቅንም። ኢህአዲግ እንደፈለገው ሊተረጉመውና ሊያስተረጉመው፤ ሊጠቀምበት ይችላል።

 

በሠላማዊ ሁኔታ ሊገለጹ የሚችሉ ሰብዓዊ መብቶቻችንን በመጠቀም፤ የሚደረግብንን እመቃ በመቋቋም የምንወጣው ትግል ነው የምናካሂደው። እንደዚህ አይነት ሠራዊት ነው የምንገነባው። … ኅዳር 28 የመንገድ/አደባባይ ላይ ስብሰባ ለማካሄድ አቅደናል፤ … መብታችንን ተጠቅመን ትግላችንን እንቀጥላለን። … የግጥም ምሽቱን ከለከሉን፣ በትኚ አሉኝ - አልበትንም አልኳቸው፣ … ግጥም ትከለክሉናላችሁ? ብለን አንበተንም አልን፤ … በመጨረሻ እነሱ እሺ አሉ። ... ነገ ጠዋት መሰብሰብ አትችሉም፤ ቢባል በተገቢው መንገድ እንታገላለን፤ ስብሰባውን እናካሂዳለን። ”መሰብሰብ አትችሉም” የሚል ሕግ ቢያወጡ … በተገቢው መንገድ ማድረግ የሚገባንን እናደርጋለን። ሠላማዊ ትግል ማለት ይሄ ካልሆነ ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም …

 

ጥያቄዎች

ጠያቂ ያሬድ፦ በፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉት እነ አቶ አስራት ጣሴን፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያን፣ ኢንጂንየር ግዛቸውንና የመሳሰሉትን ብንወስድ የፓር-ታይም (የትርፍ ጊዜ) ፖለቲከኞች ናቸው። ፓር-ታይም ፖለቲከኞች አመራሩ ላይ በበዙበት ሁኔታ ምን ዓይነት የተሻለና ውጤታማ የፖለቲካ ሥራ መሥራት ትችላላችሁ? ወደፊትስ የፓር-ታይም ፖለቲከኞቻችሁን ጉዳይ ምን ልታደርጉ አስባችኋል?

 

ጠያቂ አቶ ድንበሩ፦ ሠላማዊ ትግል ሰው ሁሉ የሚፈልገው ነው። በምዕራቡ ዓለም ልምድ አላቸው። ሰዎች በሚገደሉበት ሀገር ስለሠላማዊ ትግል መዘመር ለእኔ ትንሽ ይከብደኛል። 200/300 የሚሆኑ ወንድም እህቶቻችን ሲገደሉ ዓለም ያውቃል፤ ጠብመንጃ እንዳላነሳችሁ ዓለም ያውቃል። ምንም ምላሽ አልሰጠም። ነገም እንደትናንቱ ምላሽ አይሰጣችሁም። እነአሜሪካና አውሮፓ ተባብረው ነው የሚሠሩት። … ነገ ሰዎች ቢገደሉ፤ እንዴት ነው ልታቆሙት የምትችሉት? ምን መመከቻ አላችሁ? … እንደአለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያዊ የሆነ ጠንካራ ድርጅት የለም። በስሜት የሚደራጁ በየጊዘው ብቅ ብቅ ይላሉ፤ ነፋስ በመጣ ቁጥር ይረግፋሉ። በኢትዮጵያ ላይ እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት ከፈለግን መጀመሪያ ድርጅቱን መሥራት፣ ማጠናከር ያስፈልጋል።

 

ምላሾች

የአቶ አክሉ ምላሽ፦ … ሰፊው ልዩነት ያለው በኢህአዲግና በተቃዋሚዎች መካከል ነው። ኢህአዲግ ”ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት አጥቼ ነው” ይላል፤ ለዚህ አባባሉ ቅንጅት ምላሽ ሰጥቶታል። እንዲህ ያለ ጠንካራ ፓርቲ አይፈልግም። … ከተቃዋሚዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለን፤ ለምሳሌ ከመድረክ ጋር …

 

ምላሽ ለያሬድ፦ የፓርታይም ፖለቲካኞች። ካላቸው ጊዜ 30 እና 40 በመቶ ጊዜያቸውን እየሰጡ መሥራት አይችሉም ብለን በማለታችን … ወጪ ተድቦ ሙሉ ጊዜያቸውን እንዲሠሩ የተደረጉ አሉ። … በተቻለን ያህል ቁልፍ የሆኑ ቦታዎች ላይ ሙሉ ጊዜያቸውን እንዲሰዉ ለማድረግ ሞክረናል።

 

አቶ ድንበሩ ላነሱት - ለሠላማዊ ትግል ሰፊ ክፍተት አለ። ወደምዕራቡ ሄደን ጽ/ቤት ልንከፍት ስንሄድ፣ ቁሙ ተባልን፣ … ሂዱ ሲሉን፣ አንሄድም፤ … ነን ቫዮለንት የሆኑ ነገሮችን አናደርግም። ድንጋይ አንወረውርም። … በኢትዮጵያ ውስጥ ከነጭራሹ ለሠላማዊ ትግል መንገድ/ክፍተት የለም የሚባለውን ነገር አልስማማበትም። መንገድ አለ። … በጠብመንጃ እኮ ዲሞክራሲ አይገነባም።

 

የወ/ት ብርቱካን ምላሽ፦ ... ስዊድን ውስጥ ንፁኅ የፖለቲካ ፉክክር ነው የሚካሄደው፤ ሠላማዊ ትግል አይደለም የሚደረገው። ፖሊሲዎች፣ ሕጎች፣ ... እንዲሻሻሉ ነው ትግሉ። … ዲሞክራሲያቸው በተገነባበት ሜዳ ላይ የፖለቲካ ፉክክር ነው ያለው። … ሠላማዊ ትግሉን እናቁመው? … ምንም መስዋዕትነት የማያስከፍለው ትግሉን ማቆም ነው። … ሰው ሊሞት ነው ተብሎ ሠላማዊ ትግሉ እንዲተው ነው የሚፈለገው? ሌላኛው መንገድ ጋር ሞት የለም እንዴ? እዛኛው ጋር እንዲያውም መገዳደል ነው ያለው። ሥርዓትና ሕግ የሌለበት ነው። … በዚህ (ሠላማዊ) ትግል ላይ ከነጋሬጣው፣ ከነችግሩ፣ … ተቀብለነው ነው የምንሄደው።

 

ጥንካሬን በተመለከተ - እያንዳንዱ በዕቅዳችን መሠረት፤ … ለመጠንከር እየሠራን ነው ያለነው። እንደጀማሪ … ድርጅታዊ ጥንካሬና … የቅንጅትን መንፈስ ሥጋ በማልበስ ላይ ነው ሥራችን ያተኮረው።

 

የሠርግ ዘፈኖቻችን እንኳን ሳይቀሩ በለው! ምታው! ... የሚባልባቸው ናቸው። … ስለዲሞክራሲ፣ ለሕግ መገዛት፣ … ብለን ቅንጅት ጋር ሲመጣ ግን መገዛት ያልቻልን ሰዎች ነን። በማኅበረሰብ ደረጃ እንዳቃተን በቅንጅት ላይ አይተነዋል። … መግደል ቢፈልግ የሚገድልለትን፣ ማንገላታት ቢፈልግ የሚያንገላታለትን፣ መግረፍ ቢፈልግ የሚገርፍለትን፣ … ማሳጣት ነው የምንፈልገው። ... ለውጡ ከራሳችን ነው የሚጀምረው፤ አንዳንዶቹ እኛ ውስጥ የነበሩት ጠብመንጃ ቢኖራቸው ኑሮ ምን ሊሠሩ እንደሚችሉ ሳስበው ይዘገንነኛል። … ጋዜጣ ላይ ወጥተው ”ይታገዱ! ሲያንሳቸው ነው!” ያሉ ሰዎች አሉ። … ሠላማዊ ትግል ፈጣን አዳሽና ፈጣን መድኃኒት የለውም።

 

ጥያቄዎች

 

ጠያቂ አቶ አበበ፦ … የኃይል አሰላለፍ የተቀየረው አሜሪካ የበርበራውን፣ ራሽያ የአስመራውን ቤዝ የያዙ ጊዜ ነው። የኃይል አሰላለፍ ይቀያየራል። እነስዊድን ወያኔን ረድተዋል። … እኛ ግን እስከመጨረሻው መቀጠልና መታገል ነው ያለብን። ... የማወግዘው ዳያስፖራውን ነው፤ በዚያ ጠባብ ዕድል ውስጥ የምታደርጉትን አደንቃለሁ።

 

ጠያቂ ሐመሩ (ከፓልቶክ)፦ ... በአውሮፓ ያለው የቀድሞ ቅንጅት ድጋፍ ቆሽታችንን እያቆሰለን ስላለ፤ መላ ብላችሁ ብትሄዱ ጥሩ ነው፤ አሁንም ቆሽታችንን እንዳያደብኑን።

 

ጠያቂ አሕመድ፦ በተደጋጋሚ ስትናገሩ የሰማሁት፣ የቅንጅትን ደካማ ጎን አጠንክራችሁ፤ እናንተ ብታልፉ እንኳን ጠንካራ ድርጅት ፈጥራችሁ ለማለፍ እንደምትፈልጉ ነው። ይህንን ብታብራሩት …

 

ጠያቂ አቶ ምትኩ፦ ”ሥነስርዓት - እርማት ያስፈልገዋል። ለኢትዮጵያ ሠላማዊ ትግል ሕይወታቸውን የሰዉ ሰዎች አሉ። ለሞቱትና ለተሰዉት ተነሱና የኅሊና ፀሎት እናድርግ …” በማለት ነበር ንግግራቸውን የጀመሩትና የኅሊና ፀሎት ያስደረጉት። በመቀጠልም ...

 

የትግራይ ነፃ አውጪ ናቸው … ሲገሉን የነበሩት እነ አቶ ስዬ ዛሬ መድረክ ብለው እየሠሩ ነው ያሉት … በቅጽበት መመታት ነው ያለባቸው። ... ገና የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ እስር ቤት ነው ያለው። የእነዚህንም ቁጥር ማወቅ አለብን። ... ”እኛና እነሱ” የሚል ነገር የለም። ሁላችንም ሁላችንም ነን። … ተመትተናል። ... እኛ ተቀናጅተን ነበር፤ ቅንጅት ነው ያልተቀናጀው … ከእንግዲህ በኋላ ማንም ቢመጣ (ኃይሉ ሻውልም) መጥተን እንጠይቃለን፣ …

 

ምላሾች

የአቶ አክሉ ምላሽ፦ ለአህመድ ጥያቄ - … ሠፊ የሆነ ህዝብ የሚያሳትፍ፣ የተደራጀ፣ ብቃት ባለው የሰው ኃይል መመራት፣ … የአንድ ጠንካራ ድርጅት መመዘኛዎች ናቸው። … አንድነትን ጠንካራ ፓርቲ ለማድረግ ነው የምንሠራው። ገና እውቅና ሳናገኝ በፊት በቅንጅት ድክመቶች ላይ ስንወያይ ነበር። … ባለፈው ከከተማ ወጥተን ተወያይተናል። እንዲህ ያለውን በዓመት አራት ጊዜ ለማድረግ ነው ዕቅዳችን ።

 

ኢንፎርሜሽን ለመሥጠት ለራሳችን ስንል እንደምንሠራው ቃል እገባላችኋለሁ። እንኳን ነፃ የሆነውን ቀርቶ የመንግሥት የሆኑትንም ቢሆን ”ኑ ግቡ!” እያልን እንጋብዛቸዋለን። በፕሬስ ኮንፈረንስ፣ በጽሑፍ፣ … ፕሬሱን የትግላችን መድረክ አድርገን ነው የምንወስደው።

 

ለአቶ ምትኩ የተሰጠ ምላሽ - ኢህአዲግን እንወቅሳለን። የምንወቅሰው ድርጊቱን ነው። ስለዚህ እኛም ምታው! በለው! የምንል ከሆነ ከእሱ በምን ተሻልን? በሕግና በአግባቡ መክሰስ እንጂ እንደነሱ መሆን የለብንም። አሸንፈን በሥራ ማሳየት ነው ያለብን። የህዝብ ነፃነት ስናከብር ኢህአዲግ እራሱንም ትምህርት እንሰጠዋለን። በስሜት ከተነሳን ግን ውጤት ልናገኝ አንችልም። በሳልነትን ማሳየት አለብን፤ ኢትዮጵያን ለመለወጥ እንደምንችልም ማሳወቅ አለብን።

 

የወ/ት ብርቱካን ምላሽ፦ ከፖለቲካ ሁኔታም አለፍ አርጌ እመለከተዋለሁ። ለመመታታት በቂ ተመታትተናል። ብዙ ኢትዮጵያን የረገፉበት ሁኔታ እያለ ሌላ መመታታት ምን አመጣው? ከመመታታት ባለፈ ተነጋግሮ ሃሳብን በሃሳብ ማሸነፍ አስቸጋሪ ሂደት ነው። ግን ጥርሳችንን ንክስ አድርገን ማለፍ አለብን። እንደአውሮፓውያኑ ለመሆን መጠፋፋትና በለው መባባል አይደለም። የማንዴላንም የጋንዲንም የምታውቁት ነው። ሌላ ያልተደጋገመ ታሪክ የኮሎምቢያ ሴት ታሪክ ልጥቀስ። ኢንግሪድ ፋርክ ትባላለች። ”ምን አደረሱብሽ ንገሪን” ሲሏት ዓይኗን ጨፈነች። ”ጫካ ውስጥ ያለውን ለጫካው እንተወው” ብላ ነው የተናገረችው። እርግጠኛ ነኝ ይህች ሴት ተደፍራለች። ቀጥሎም ”አሁን ምን ይሰማሻል? ምን ይታይሻል?” ተብላ ስትጠየቅ፤ ”እነዚህን ሰዎች ልናስረዳቸው እና ወደ ሠላም ልናመልሳቸው ይገባናል” ነው ያለችው።

 

መመታት አለበት ለተባለው፤ መለስ ቢመታ ምርጫ ቦርድ አይሆንም፤ ወይንም ሌላ ነገር ይወርዳል ማለት አይደለም። አንድነት የኢትዮጵያ ህዝብ መለማመጃ ይሁን ብሎ አያምንም። የሠላሙን ትግል ከቀን ቀን እያዳበርን መሄድ አለብን። ይህ ዓላማ ቢኖርለትም ቢሞትለትም አይቆጭም።

 

የመለስ መንግሥት ቢያናድድም፤ ያለው መንግሥት የትግራይ ነፃ አውጪ ነው እንጂ ኢህአዲግ አይባልም ብሎ ነገር ግን ስህተት አመለካከት ነው። አጣዬ ውስጥ ቢሮ ልንከፍት ሄደን፤ አንዱ … ”ሥርዓቱን ካኮረፍኩ 17 ዓመቴ ነው፤ ኢትዮጵያን ግን አላኮርፍኳትም” ብሎኛል። ስለዚህ ሙሉውን ሀገር ነው እንጂ ቀንሰን መውሰድ የለብንም። የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር ነው ያነሳነው እንጂ የተለየ ህዝብ ትግል ይዘን አልተነሳንም። የአንተ መብት የማጣት ችግር፤ የሁላችን ችግር ነው። መፍትሔውም የጋራችን ነው። ይሄ መንግሥት በሥልጣን ለመቆየት ያልመሰረተብን ክስ የለም። በዘር ማጥፋት ሁሉ ከሶናል። ያ ማለት ደግሞ ጥሩ አባባል አይደለም። ስለዚህ በሱ መልክ አንሄድም። ስትናገሩ የዘር ነገር አታልብሱት።

 

የውይይቱ ፍፃሜ፦ በውይይቱ ፍፃሜ ላይ በስዊድን የአንድነት ድጋፍ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ታምራት የመዝጊያ ንግግር አድርገው፤ ውይይቱ በአንድነት መዝሙር ተዘግቷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ከእንግዶቹ ጋር እራት እየበሉ ፎቶግራፎች በመነሳትና የግል ውይይት በማድረግ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ አሳልፈዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!