Yederasiw Mastawesha የደራሲው ማስታወሻተስፋዬ ዮሐንስ

... ተስፋዬ ‘የባርነት’ ዘመኑን በመቃኘት ያሳለፈውን ህይወት፣ ገጠመኙን፣ የታዘባቸውን፣ ወዘተ፣ በጭልፋ እየቆነጠረ ያቋድስ ጀመር። ‘የጋዜጠኛው ማስታወሻ’ የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ለንባብ አበቃ። ብዙዎች አበጀህ፣ ደግ አደረግ አሉት። ቀጣፊ ያሉትም ነበሩ። ኤርትራዊ የዘር ሃረጉን በመቁጠር የሻዕቢያ ደጋፊ ያሉትም አልጠፉም። በተለይ የኢህአዴግ ደጋፊዎችና አባላት፣ ገበና አጋለጠ በማለት ብዙ ጽፈውበታል። ሙሉ በሙሉ ከባርነት በወጣበት ‘የጋዜጠኛው ማስታወሻ’ መጽሐፉ ላይ የብዙ ሰዎች ስሞች ተነስቶ ተስፋዬ ከበድ ከበድ ያሉ ክሶችና ውንጀላዎች ደረድሮአል። አንዳቸውም አላስተባበሉም። ለምን? ... ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ ተስፋዬ ሌላ መጽሐፍ ደርሶ ለንባብ አብቅቷል፤ ‘የደራሲው ማስታወሻ’። መጽሐፉ 25 ራሳቸውን የቻሉ ክፍሎች አሉት። ይህ አቃቂር በሦስት ዐብይት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። 1/ መጽሐፉን መድረስ ለምን አስፈለገ? 2/ መጽሐፉ ያቀፋቸው ዋና ዋና ጭብጦች ምንድናቸው? 3/ የመጽሐፉ ደካማ ጎኖችስ? ...

ርዕስ - የደራሲው ማስታወሻ

ደራሲ - ተስፋዬ ገብረአብ

ገጽ ብዛት - 422

የታተመበት ዓመት - ዓ.ም. 2002

ወደ ዝርዝር ሃሳቦቹ ከመግባቴ በፊት፣ መጽሐፉ ውስጥ ያገኘኋቸውን አንዳንድ አገላለጾች ላካፍላችሁ፤

“የሆነ አውራ ዶሮ አለን።…በደሞዝ ተከፍሎ የሚሰራ ይመስል ገና ሳይነጋ አቦሬውን ይከፍተዋል።’ (24)

“እኛ ፈገግ ስንል የምናለቅስ ሊመስል ይችላል። ሳቅ የሚያምርበት የተመቸው ነው። ያልተመቸው ሰው ከሚስቅ ስቅስቅ ብሎ ቢያለቅስ ያዋጣዋል። እንደተቦረቦረ መሬት ወደ ውስጥ የገባ ጉንጭ! የከረዩን ጎራዴ መስሎ የተጋደመ መንገጪላ!’ (25)

“ሌንሳ በደስታ ሳቅ በሳቅ ሆነች። … በየተራ አቀፈችን። … እንኳን ማቀፍ በስህተት ስንነካካ እንኳ ከሳቴ ብርሃን እንዳጨሰ ሰው ያለንበት ነው የሚጠፋን!” (34) ለመሆኑ ከሳቴ ብርሃን ምን ይሆን?

“እነሆ ሌንሳ ምርጥ ጓደኛችን ሆነች። አልፎ አልፎ እጅ ለእጅም መያያዝ ጀምረናል። ወዲያው ግን ፊታችን ድልህ እየመሰለ ቶሎ እንላቀቃለን።…ነብዩን አንድ ጊዜ ትከሻውን ስትደገፈው የሚያወራው የነበረው ሁሉ ጠፋበት። … እንደ ሽኮኮ የሚፀልይ መስሎ ባለበት ድርቅ ብሎ ቀረ።” (38) ከመቼ ጀምሮ ይሆን ሽኮኮ የምትፀልየው?

“በውነቱ ከክፍል ማለፌ ባይቀርም፣ የትምህርት ካርዶቼ እንደ ውዳሴ ማርያም በቀይ ያጌጡ፣ በቀይ የተሸለሙ ባለ አበባ ወላንሳ ይመስሉ ነበር።…አፄ ቴዌድሮስን ከነሹሩባቸው መሳል ብቻ ነበር የምችለው። እሱም ቢሆን ሹሩባው እንጂ መልካቸው እሳቸውን አይመስልም። ‘መንዶሴ የተባሉትን ጥሩንባ ነፊ ይምስላል’ (43) እያሉ ከሚቀልዱብኝ አንዱ ራሱ ነብዩ ነበር።

“ስለጦርነቱ ምን ልንገርሽ?...የሚያብዱም አሉ። የሚያሳብደው ምኑ መሰለሽ? ተርበሽ እያለ የሞት ሽታ በጥብስ ተመስሎ ይሸትሻል። የተራበ ሆድ ይህን ሽታ መለየት ሲያቅተው አስተሳሰብ ይናጋል።” (119-120)

“እስከሚቀጥለው ዓመት፣ ልቤን የምትማርክ፣ መልኳ ጨረቃ፣ ቅጥነቷ እንደ መቃ፣ ለባሏ ጠበቃ፣ ዘሯ መጢቃ፣ የሆነች ሚስት ካገኘሁ እዚህ መጥቼ አንድ ጣቃ ለመስጠት እያሰብኩበት ነው።” (181)

“አቦይ ስብሃት እሩብ የእንግሊዝ ዘር አለባቸው። በጄኔራል ናፒር መሪነት አፄ ቴዎድሮስን ሊወጉ መቅደላ አምባ ከመጡት ወታደሮች አንዱ መልኩን ሳይሆን ከፋፍሎ የመግዛት ተንኮሉን አቦይ ስብሃት ዘንድ ትቶልን ሄዷል።”(211)

“ልጆቹን አውቃቸዋለሁ። የለየላቸው ቀበጥ ናቸው።…በሽቦ አለንጋ ሚኒስቴሮችንና የጦር መሪዎችን እየገረፉ ሊጫወቱ ይሞክራሉ። ክራቫቱን አሳምሮ ቁጭ ያለ አማራ ወይም ኦሮሞ ሚኒስትር በስብሃት ቀበጥ ልጆች ሳያስበው “ሾጥ” ሲደረግ፣ መጀመሪያ ይቆጣል። ቀጥሎ የስብሃት ነጋ ልጆች መሆናቸው ትዝ ሲለው ይስቃል።” (217)

“ዋለልኝና ማርታን አይሮፕላን ላይ ተኩሶ የገደላቸው ማን መሆኑን ለማወቅ የደሴ ልጆች መከታተል ጀምረን ነበር።…የጓደኞቼ ገዳይ የዛሬው ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተ ማርያም መሆኑን በቅርቡ ነበር የሰማሁት። ስሰማ በጣም ደነገጥኩ።” (264)

“መንግሥቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያን ያፈቅራት ነበር። … ጉሮሮዋን አንቆ ለዓመታት ከንፈሯን ሳማት። ሳማት ከማለት እየነከሰ አደማት ማለት ይቀላል። … ጉሮሮዋ ታንቆ፣ ትንፋሽ አጥሮአት በአፍንጫዋ ብቻ እየተነፈሰች ከንፈሯን መሳም የምትሻ የለችም።” (266)

“ስድብ የሌለበት ጽሑፍ ለመፃፍ ሞከርኩና አቃተኝ። ለካስ መከራከሪያ ሃሳብ ካጠረህ ጭንቅላትህ ውስጥ የሚቀረው የመመከቻ ዱላ ስድብ ብቻ ይሆናል።” (294)

“ወዴት እያመራን ይሆን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት የፖለቲካ ጠበብት ቁምስቅላቸውን እያዩ ነው። ልዩነታችን ሰፍቷል። የሚያጣላ በዝቷል። የሚያስታርቅ ጠፍቷል። የእብድ ገላጋይ በርክቷል። የሚናገር እንጂ የሚያዳምጥ ጆሮ የለም።”(321)

 

ቀጥሎ ወደ አቃቂሩ እንሂድ

መጽሐፉ ልክ እጄ እንደገባ ነበር ማንበብ የጀመርኩት። አፍታም አልፈጀብኝ፤ በአንድ ትንፋሽ ጨረስኩት። ወደማለቂያው ገደማ ቅር ቅር አለኝ። ይህን መጽሐፍ ብዙ ሰው ቢያነበው ጥሩ ነው ብዬ አሰላሰልኩ። አስተዋጽኦዬ ምን ይሁን ብዬም አሰብኩ። አንባቢውንም ሆነ ደራሲውን ለማገዝ የመጽሐፉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ አቃቂር ለመጻፍ ወሰንኩ።

 

የተስፋዬ ገብረአብን ሥራዎች በከፊልም ቢሆን አውቃቸዋለሁ። ‘ተራራ ያንቀጠቀጠ ትውልድ’ በሚል ስም ይወጡ የነበሩ የተወሰኑ መጣጥፎቹን አንብቤያለሁ። አልጨረስኳቸውም። “በባርነት” ዘመኑ የጻፋቸው መጽሐፍቱ ውስጥ የተካተቱት ትረካዎች መነሻ ቢኖራቸውም፤ ኢህአዴግን ለማግነን የተደረሱ በመሆናቸው ፕሮፓጋንዳና ውሸት ይበዛባቸዋል። እኔ ራሴ የማውቃቸውን ታሪኮች አጣመውና አወላግደው አቅርበዋቸው አንብቤያለሁ። አንዳንዶቹም እንጨት እንጨት ይላሉ፣ ያውም የግራዋ። ስለሆነም ንባቡን አቋረጥኩ።

 

ለተስፋዬ ሌላ ዕድል ሰጠሁት፣ ‘የቡርቃ ዝምታ’ የተባለውን መጽሐፉን አነበብኩ። ምንም እንኳን አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩበትም፣ ማራኪና የተዋጣለት መጽሐፍ ነበር። በዚህ ሥራው የደራሲውን የመድረሰ ጉልበትና አቅም ማየት ቻልኩ። ተስፋዬ ‘ከባርነት’ ወደ ነፃነት ጉዞ ጀምሮ ስለነበር፣ አእምሮው ውስጥ ትግል ያካሄድ እንደነበር መገመት ከባድ አልነበረም። የአቀበት ጉዞ። ተስፋዬ ‘በባርነት’ ዘመኑ የአለቆቹ ‘አለቅላቂ’ ሆኑ በመቆየቱ በሥርዓቱ ጋሻ ጃግሬነት ነበር በህዝቡ ዘንድ የሚታወቀው። የህዝብ አመኔታ አልነበረውምና ’ሀ’ ብሎ መገንባት ነበረበት። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ‘በቡርቃ ዝምታ’ የሚነሱ ሃሳቦችም ሆኑ ትረካዎች አለቆቹን ሠላም የሚሰጡ አልነበሩም። ጥርስ ያስነክሳሉ፣ አስነክሰውበታልም። ተስፋዬ የነፃነት ጉዞውን ቀጠሎ ‘የቡርቃ ዝምታ’ን ይፋ አደረገ። አንድ ከባድ እርምጃ ተራመደ፣ ‘የባርነት’ ሰንሰለቱን በጠሰና አሽቀንጥሮ ጣለ። ከዚያም፣ ዐይነ ስጋው ተገፎ ወደ ውስጡ በመመልከት ራሱን ይመረምር ጀመር። ያን አድርጎ ግን ሀገር ውስጥ መቆየት አልቻለም። ተሰደደ። ከበዓሉ ግርማ ተምሯልና! በዓሉ ግርማ ‘የባርነት’ ሰንሰለቱን እንደበጠሰ፣ ያ እርምጃ ሊያስከትል የሚችለውን አልገመተም። ኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማርያምን ‘ነበሩ’፣ ‘አንበሳው’ እያለ ችግሩን ሊወጣ የሚቸል መስሎት ነበር። አልሆነም፣ ተቀደመ። ደብዛውን አጠፉት። የተስፋዬም ዕጣ ፈንታ ከዚህ ብዙም ሊለይ የሚችል አልነበረም። ውስጥ አዋቂ ነውና ብዙ ሳያበላሽ ያቀላጥፉት ነበር። ቆቅ ነው፣ ቀደማቸው።

 

ተስፋዬ ‘የባርነት’ ዘመኑን በመቃኘት ያሳለፈውን ህይወት፣ ገጠመኙን፣ የታዘባቸውን፣ ወዘተ፣ በጭልፋ እየቆነጠረ ያቋድስ ጀመር። ‘የጋዜጠኛው ማስታወሻ’ የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ለንባብ አበቃ። ብዙዎች አበጀህ፣ ደግ አደረግ አሉት። ቀጣፊ ያሉትም ነበሩ። ኤርትራዊ የዘር ሃረጉን በመቁጠር የሻዕቢያ ደጋፊ ያሉትም አልጠፉም። በተለይ የኢህአዴግ ደጋፊዎችና አባላት፣ ገበና አጋለጠ በማለት ብዙ ጽፈውበታል። ሙሉ በሙሉ ከባርነት በወጣበት ‘የጋዜጠኛው ማስታወሻ’ መጽሐፉ ላይ የብዙ ሰዎች ስሞች ተነስቶ ተስፋዬ ከበድ ከበድ ያሉ ክሶችና ውንጀላዎች ደረድሮአል። አንዳቸውም አላስተባበሉም። ለምን?

 

ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ ተስፋዬ ሌላ መጽሐፍ ደርሶ ለንባብ አብቅቷል፤ ‘የደራሲው ማስታወሻ’። መጽሐፉ 25 ራሳቸውን የቻሉ ክፍሎች አሉት። ይህ አቃቂር በሦስት ዐብይት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። 1/ መጽሐፉን መድረስ ለምን አስፈለገ? 2/ መጽሐፉ ያቀፋቸው ዋና ዋና ጭብጦች ምንድናቸው? 3/ የመጽሐፉ ደካማ ጎኖችስ?

 

‘የደራሲው ማስታወሻ’ የተሰኘውን ይህን መጽሐፍ ለምን መድረስ አስፈለገ?

በብዙ ሰው ህሊና ውስጥ ተሸንቅረው አደብ የሚነሱ፣ የሚያብሰከስኩና የሚያበሳጩ አንኳር አንኳር ጭብጦችን እያነሳ ለዛ ባለው አቀራርብ፣ ቀልዶች በመቀላቀል፣ አንዳንዴም በራሱ በመሳቅና በማሳቅ ይተርክልናል ደራሲው። መጽሐፉን የሚያነብ አንድ ሰው ብስጭት ብሎ ከቆየ በኋላ ድንገት ክት ክት ብሎ ቢስቅ አያስገርምም። እኔ በቀላሉ አልስቅም፣ ሳቄ ሩቅና ተፈልጎ የሚገኝ ቢሆንም፣ ደርሶብኝ አይቼዋለሁ። ሰውነቴን እስከሚነዝረኝ ድረስ ተናድጄ ወዲያው ደግሞ ክትክት ብዬ ስቄያለሁ። አንባቢው እንዲህ እኔ እንደሆንኩት እንዲሆን ማድረግ ችሎታን ይጠይቃል። ተስፋዬ ያ ጉልበት አለው፤ የስነ ጽሁፋዊ የአቀራረብ ጉልበት።

በመጽሐፉ የተነሱ ጭብጦችን ስናይ ደግሞ፣ ተስፋዬ ራሱን እያፀዳ እንደሆነ እንረዳለን። ጳጉሜ ሦስት በመጥምቁ ዮሐንስ ዕለተ-ቀን፣ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ብዙ ሰው እንደ አቅሙና ፍላጎት ወንዝ ድረስ በመውረድ ራሱን ካፀዳዳ በኋላ አሰሴን ግሳንግሴን ጥርግ አድርገህ ውሰድልኝ እንደሚለው፣ ተስፋዬም ‘በባርነት’ ዘመኑ ያደፈውንና የጨቀየውን ነብሱን በህዝብ ፊት ንስሃ በመግባት ራሱን ያፀዳል። የህሊና ደዌ ሆኖ የቆየበትን ‘ጭቅቅቱን’ በአደባባይ፣ በህዝብ ፊት ያነፃል። ስለሆነም፣ ተስፋዬ ይህን መጽሐፍ ለምን ደረሰ ለሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ ‘በባርነት’ ዘመኑ ለደረሰበት የህሊና ቁስልና ስብራት ፈውስ ለማግኘት ነው ቢባል ትክክለኛ ግምት ነው። ተስፋዬ ወደ ሆዱ ያነባል፣ ስቅ እያለና እየተንሰቀሰቀ ያለቅሳል። የወያኔ ሥርዓት በግሩ እንዲቆም ትንሽም ብትሆን አስተዋጽኦ ያደረገ እነደመሆኑ፣ የውሃ ሳይሆን የደም ዕንባ ነው የሚያነባው። እሮሮውንና ሃዘኑን ለብቻው አልችለው ስላለ አብራችሁኝ አልቅሱ ብሎ መጽሐፉን ደርሷል። እንደጅረት የሚፈሰውን የተስፋዬን ዕንባ በመጽሀፎቹ የመጀመሪያ ገጾች አናይም። ስለመህቡባ በሚጽፍበት የመጨረሻ ገጾቹ ላይ እንጅ!

 

መህቡባ፣ እንደ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን ዐረብ ሀገር ውስጥ በግርድና የምትተዳደር የ23 ዓመት ወጣት ናት። በወር አንድ ቀን የሚሰጣትን የ24 ሰዓታት የዕረፍት ጊዜ ተጠቅማ በወጣችበት ወቅት ነበር ተስፋዬ አንድ ቤት ውስጥ ያገኛት። እንደእሷ በግርድና የሚተዳደሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም በዚሁ ቤት ተሰብስበዋል። መህቡባ ነበረችና ቀልቡን የሳበችው፣ ተስፋዬ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ለብቻቸው ጨዋታ ጀመሩ። መህቡባ የሙት ልጅ ናት። በጅማ የቡና ነጋዴ የነበሩት ኦሮሞ አባቷ በኦነግ አሸባሪነት ተግደለዋል። ይህ ችግር እንደተፈጠረም፣ አማራ እናቷ፣ ወንድሞቿን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ሸሹ። ይሁንና፣ ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ጠፋ። ‘መህቡቤ! ተስፋችን ሁሉ አንቺ ነሽ! አንቺ ከበረታሽ ያልፍልናል። ካልበረታሽ ደግሞ ትቀብሪናለሽ’ (411) ብለው ያለ የሌለ ጥሪታቸውን ሰጥተው ለግርድና ወደ ዐረብ ሀገር ላኳት እናቷ። መህቡባ የግርድና ህይወት አስከፊ ገጽታዎቹን አንስታ ተስፋዬን ታወያየዋለች፣ ‘ሁለቱ መንታ ህፃናት ልጆቹ ደግሞ ባለጌዎች ናቸው። አጎንብሼ እያፀዳሁ እያለ ከሁዋላ ቀስ ብለው እየተጠጉ ይሸኑብኛል።’ (414) የቤቱ አባወራም ቢሆን ሊደፍራት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን ትገልጻለች። እስከአሁን ግን አልተሳካለትም፣ በእሷ አገላለጽ። ያ ሁኔታ እስከመቼ ይቀጥል ይሆን?

 

የመህቡባ ታሪክ ልቡን ሰበረው። የተስፋዬን። ‘ተስፋ የሚባል ነገር ጥርግርግ ብሎ ከውስጤ የሚጠፋበት ጊዜ አለ። … እንደ ብረት የጠነከረ እያልኩ የምመካበት መንፈሴን ይህች የ23 ዓመት ልጅ ድራሹን አጠፋችው።… ልቤ አካባቢ እንደ ጩቤ የሚወጋኝ ነገር አለ። አይኖቼ ዙሪያ ደግሞ መርፌ ነገሮች ይጠቀጥቁኛል’ (415) ሲል ተስፋዬ ያነባል። መህቡባ የወር እረፍቷን ለማሳለፍ የሄደችበት ቤት ‘የጋዜጠኛው ማስታወሻ’ የተሰኘው የተስፋዬ መጽሐፍን አግኝታ ጥቂት ገጾች አንብባለች፣ እናም፣ በወጋቸው መሀል ‘ፖለቲካ ውስጥ አትግባ!...ወያኔዎቹ ይገድሉሃል። እነሱ ማንን ፈርተው ልጄ?’ ትለዋለች። ቀጥላም፣ ‘እነሱ ልጄ ተንኮለኞች ናቸው። … ባለፈው ምርጫ … ቅንጅቶችን መንገድ ላይ ሳይቀር እንደገደሏቸው አልሰማህም? ... እንዴት እንደዚህ ይጨክናሉ? ... የእናት ጡት ጠብተው አይደለም እንዴ ያደጉት?’ (417) ስትል መህቡባ ሞገተችው ተስፋዬን። ስለጅማው ግድያ ጽፎ እንደሆነም ጠየቀችው። የቱን ብሎ ሲጠይቃት፣ ‘ራሳቸው ፖሊሶቹ እስላም መስለው ክርስቲያኖቹን በቆንጨራ አርደዋቸው የለምንዴ’ ስትል አብራራችለት። ደራሲው ቆንጸል አድርጎ አቀረበው እንጅ፣ መህቡባ ስለጉዳዩ ዘርዘር አድርጋ ሳታጫውተው አልቀረችም። ህዝብን ከህዝብ የሚያጣሉና የሚያራርቁ ብዙ ነገሮች አውቃለሁ የሚለው ተስፋዬ፣ የነገረችው ጉዳይ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል ብሎ አስቦ የተወው ይመስላል። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጠቅላይ ሚንስቴር የነበሩት አቶ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ በኋላ ላይ የኦሮሞ መሪ ከነበሩት ከሜጀር ጄኔራል ታደሰ ብሩ ጋር ሲጨዋወቱ፣ ተናገሩ የተባለው ሃሳብ ለዘመናችን የኦሮሞዎች ትግል መቀስቀስ ምን ያህል ክብሪት ሆኖ እንዳገዘ ተስፋዬ በመጽሐፉ ይጠቅሳል። (341)

 

ከመህቡባ ጭውውት በኋላ ተስፋዬ ከራሱ ጋር የእሰጥ አገባ ሙግት ውስጥ ገባ። ያቺ “ሃሰበ-ድንግል” (pristine) ልጅ፣ ፖለቲካ ውስጥ አትግባ እሳት ነው ይፋጃል ብላ ከባድ ፖለቲካ ተናገረች። እናም፣ ‘በባርነት’ ዘመኑ የሰራቸው ሁሉ ትዝ አሉት። ‘ሰውነቴን የሚያልፈሰፍስና ተስፋ የሚነፍግ፣ ነፍስን የሚያደቅቅ ገዳይ መርዝ በሰራ አካላቴ ሳይሰራጭ አልቀረም። ፈጽሞ ተዳከምኩ። … ከወያኔ ጋር በሰራሁባቸው ዘመናት ህዝብ የሚባሉት እነ መህቡባ መሆናቸውን እንዴት ሳላስተውል ቀረሁ?’ በማለት የፀፀት እሮሮውን ያስደምጠናል ተስፋዬ። በእኔ አስተያየት፣ በዚህ ርዕስ ውስጥ ተስፋዬ ለነፃነት ሲሟገት አይደለም የተገነዘብኩት፣ በፀፀት ወደ ሆዱ የደም ዕንባ ሲያነባ እንጅ!

 

ሌላም ማስረጃ አለ። መኪና እየነዳ ሲሄድ አንዲት ልጅና ዘመዷ እንዲያደርሳቸው ይጠይቁታል። ልጅቱ ችግረኛ ናት፣ ‘በአደፈ ነጠላዋ ስር ምላሱን ያወጣውን ሰማያዊ ሹራብ ደጋግማ ታስተካክለዋለች። … ከነጠላዋ ሾልኮ የወጣው ጠጉሯ እስኪበቃው አቧራ መጥምጧል’ (140) በማለት ነበር ተስፋዬ የልጅቱን ችግረኝነት ያስረዳው። እናቷ በሽተኛ ናቸው። አባቷ ሻምበል የነበሩ ሲሆን፣ አርፈዋል/ተገድለዋል። እነዚህ የወታደር ቤተሰቦች እንደአልባሌ እቃ ተወርውረው ለችግር ተዳርገዋል። ልጅቱ ትማፀነውና ተስፋዬ ለእናቷ አስቤዛ ገዝቶ ይጎበኛቸዋል። ከቤት ሊወጣ ሲል፣ ያቺ የ16 ዓመት ወጣት ሌላ ጊዜ መጥቶ እንዲጠይቃቸው ትማጸናለች። ተስፋዬ ቃል ቢገባላትም ሳያከብረው ይቀራል። አንድ ቀን ታዲያ ወሎ ሰፈር ‘ሸሌ’ (በዘመኑ አጠራር ሴተኛ አዳሪ ማለት ነው መሰለኝ - እኔም ከተስፋዬ ነው የተማርኩት) ሆና ያያታል። ቃል ዐባይ መሆኑ ይሰማውና ልቡ ይሰበራል፣ ‘ይህች ልጅ እያለቀሰች እናቷን እንድረዳላት ስትጠይቀኝ ለምን ችላ አልኩ? ምን ሆኛለሁ? ይህን አውሬነት ከየት ወረስኩት? ወይስ ተፈጥሮዬ እንዲያ ይሆን?’ (147) ብሎ ራሱን ይጠይቃል። ባለፈው ዘመናቸው በሰሩት በደል ተፀፅተው ይቅርታ የሚጠይቁና ካሣ እንክፈል የሚሉ ጥቂት ናቸው። ከእነዚህ አንዱ ተስፋዬ ገብረ አብ ነው። ተስፋዬ በወያኔ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረው ሰው አልነበረም። ይሁንና፣ በድያለሁና ሀገሬን ልክስ የምችለው ያጠፋሁትን ለህዝብ ይፋ አውጥቼ ይቅርታ ስጠይቅ ነው ይላል።

 

ተስፋዬ ‘በባርነት’ ዘመኑ ያየውን አይቷል፣ የሰማውን ሰምቷል፣ የወያኔን ኑሮ ኖሯል፣ የወያኔን ትንፋሽ ተንፍሷል፣ እንደወያኔ አስቧል፣ ወያኔ ጠላቶች የሚሉትን ታግሏል፣ ሰድቧል፣ አዋርዷል፣ … ዛሬ ተስፋዬ የያኔው ተስፋዬ አይደለም፣ ወደ ውስጥ መርምሮ ራሱን አግኝቷል። ከእንቅልፉ እንደባነነም እየተከናወነ ያለውና የሚሆነው ነገር ሁሉ ክፉኛ አሳስቦታል፣ አስደንግጦታል። ሁለተኛውና ሌላው የመጽሐፉን ጭብጥ የምናገኝበት ቦታ ‘ሮሮና ይቅርታ’ በሚል ርዕስ ስር የሰፈረው ትረካ ሲሆን፣ ጅማ ውስጥ ከተገናኘው ከሮሮ መገርሳ ጋር ያደረገውን ጭውውት መሰረት አድርጎ ነው ተስፋዬ የሚተርከው። ታሪኩ እንዲህ ነው። አንድ ሰው ይሰድብሃል፣ ይመታሃል፣ ወንድምህንም ይገድላል። ይህ ሁሉ ግፍ ተብሎ የሚቆጠር ቢሆንም፣ እንደ ሮሮ መገርሳ ከሆነ ሮሮ የሚያደርስ አይደለም። ‘ፍርድ ቤት ሂደህ ታመለክትና ዳኛ ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ ባንተ ላይ ይፈርድና ገዳዩን ወንጀለኛ ነፃ ይለቀዋል።’ (338) ያኔ ያ ግፍ ሮሮ ይሆናል ይላል ሮሮ መገርሳ። ‘ሮሮ ደረጃ የደረሰ ግልሰብም ሆነ ህዝብ ሁለት ምርጫዎች ብቻ ነው ያሉት። መግደል! ካልሆነ መሞት።’ (343) በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የተካሄዱትና የሚካሄዱት ትግሎች የሮሮ ውጤቶች ናቸው እንደ ተስፋዬ እምነት። ‘ወያኔ ሆን ብሎ የህዝቡን ግንኙነት ሮሮ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት እያደረገ ነው’ ይላል በቅርቡ ከእንቅልፉ የባነነው ተስፋዬ። ያ እንዳይሆን ግን፣ ‘ነፃነት ፈላጊው ህዝብ ከእለታት አንድ ቀን ይሳካለታል!! በተሳካለት ጊዜ ሊመጣ የሚችለውን የማይፈለግ አደጋ ለማስቀረት የሚቻለው ግን ነገ አይደለም። ዛሬ ብቻ ነው! ዛሬ ብቻ!’ (349) በማለት የተስፋ ስንቅ የሰነቀው ተስፋዬ እንድንቋደስ ይማጸናል።

 

መጽሐፉ ያቀፋቸው ዋና ዋና ጭብጦች ምንድናቸው?

በጥቅሉና በግርድፉ የተስፋዬን ትረካዎች በሦስት መክፈል ይቻላል። የመጀመሪያውና አብዛኛውን የመጽሐፉን ክፍል የያዘው ‘በባርነት’ ዘመኑ የቅርብ ተመልካች ሆኖ ያያቸውንና የታዘባቸውን የወያኔ ባለሥልጣናትንና የወያኔ ሥራዎችን መዘከር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኦሮሞ ባህል ላይ የተመሰረቱ ትረካዎችን በልዩ ፍቅር ማቅረብ ነው። ስለኦሮሞ ብዙ እንድናውቅ ለማድረግ ይጥራል። ሦስተኛው ክፍል ውስጥ የቀረቡት ትረካዎች ከላይ ከተጠቀሱት ከሁለቱም የማይደመሩ ሲሆን፣ ለእኔ ብዙ ትርጉም አልሰጡኝም። ለምሳሌ፣ የቁልቢ ሌሊት ውስጥ፣ ስብሃት ነጋ በጨረፍታ፣ ወዘተ። (ዝርዝሩን በመጨረሻ ላይ እመለስበታለሁ።) ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱ ደካማ ጎኖች ባሻገር፣ ተስፋዬ አንቱ የሚባል ሥራ አበርክቷል።

 

በሁለተኛው ተርታ ከተሰለፉ ትረካዎቹ መሀል የኦሮሞ ክብረ በዓሎች ይገኙበታል። ኢሬቻ አንዱ ሲሆን፣ ‘የኢሬቻ በዓል ቅዱስ በዓል ነው። የእግዚአብሔር ስጦታ ተመልሶ ለእግዚአብሔር የሚሰጥበት በዓል ነው። የዋቀዬ ስጦታ የሚባሉት ውሃና ልምላሜ ናቸው’ (38-39) በማለት የሌንሳ አባት አቶ አበበ ያስረዱታል። ሌንሳ፣ ተስፋዬ በልጅነቱ የተዋወቃትና ‘ሊያወርዳት’ አስቦ እንዲሁ እንደተቃጠለ ሳይሳካለት የቀረች ልጅ ናት። ተስፋዬ ‘በቱሪስት’ መሪነት ሌንሳን ቢያገለግልም አልሆነለትም። ድፍረት ከዳው፤ ወይ ከነአካቴው አልነበረው ይሆናል። ተስፋዬ፣ ሌንሳን መነሻ አድርጎ ስለኦሮሞ ባህል ያስተዋውቀናል። ኦሮሞዎች ክረምቱን በሠላም ሲወጡ እንደሚያመሰግኑት ሁሉ፣ ክረምት ሲገባም ይዘክራሉ፣ ‘የመልስ ጉዞ ስናደርግ እግረመንገዳችንን ዱለቻ የተባለውን ተራራ በሩቅ አሳየናት። ግንቦት ወር ላይ ሃርፋሳ የሚባለው በዓል ተራራው አናት ላይ ይከበራል። ገበሬዎች፣ “ጨለማውን ክረምት በሠላም አሳልፍልን” ብለው ፀሎት ያደርጋሉ’ ይለናል። (41)

 

ሌንሳ ብዙ አውግታቸዋለች። ጅማ ውስጥ ጌራ የተባለ ቦታ ትሄድ ነበርና፣ ‘ጌራ የሄድኩ ጊዜ ማታ ማታ እንደዚሁ ደጁ ላይ ቁጭ ስንል አያቴ ስለ ከዋክብት ይነግረኝ ነበር….የጌራ ሰዎች ቀን የሚቆጥሩት በከዋክብት ነው’ ብላ አወጋቻቸው።’ እነተስፋዬ ልጆች ነበሩና ሰሟት እንጅ ወጉን አልቀጠሉበትም። አሁን በቅርቡ ተስፋዬ አስመራ ሂዶ ስለ ገዳ ሥርዓት መጽሐፍ የደረሱትን ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠን ያገኛል። ከዚያም፣ ስለኦሮሞ የከዋክብት ዕውቅት አስገራሚ ነገር ይናገራሉ። ‘ጨረቃ ስትወጣ በቀን በቀን ቦታዋን ትቀያይራለች። በመጀመሪያው ቀን ከአንደኛው ኮከብ ጋር ከወጣች በነገታው ከሁለተኛው፣ በመቀጠል ከሦስተኛው … ሁለተኛው ወር ሲጀመር ከሁለተኛው ኮከብ ጋር ነው የምትጀምረው። … ይሄን ሊያስረዳኝ ይሞክራል ይሄ ሽማግሌ (አራሮ ረመታ)። ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም።’ (360) ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠ ተስፋ አልቆረጡም ነበርና ከሽማግሌው ጋር አዲስ አበባ እንጦጦ ላይ ወጥተው ከዋክብት ይቆጥራሉ። ‘ይሄ ላሚ … ይሄ በከልቻ … የሁሉንም አስረዳኝ። ጨረቃዋ ስትወጣ ከየትኛዋ ኮከብ ጋር እንደወጣች አስረዳኝ። አንድ ወር ነው የቆየነው እዚያ። በወሩ ጨረቃዋ ስትወጣ ከሁለተኛው ኮከብ ጋር እንደወጣች አስረዳኝ። በወቅቱ ታዲያ አንጎሌ ላይ የተቀረጸው ምንድነው permutation በሚባል የማቲማቲክስ ቴክኒክ የተመሰረተ የቀን አቆጣጠር ዘዴ ነው። ዓመት ሙሉ ዞራ ስትመጣ ቢቶቴሳ በምትባል ወር፣ ቢታቃራ በምትባል ቀን የመጀመሪያዋ አዲሷ ጨረቃ ከአንደኛው ኮከብ ጋር ትወጣለች። ይሄ የአመቱ መጀመሪያ ይባላል። በዚህ ጊዜ ሁሉም ተገለጸልኝ’ በማለት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠ ኤርትራ ውስጥ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ያቀረቡትን ሃሳብ ተስፋዬ ያስነብበናል። ይህን ‘ግኝታቸውን’ መሰረት አድርገው አንድ መጽሐፍ ይደርሳሉ ፕሮፌሰር አስመሮም። ‘ናሳ NASA የሚሰራ ፈረንጅ አስትሮኖመር መጽሃፌን ያነባል። ... ይሄ ነገር ባስትሮኖሚ ይሰራል አይሰራም ሲል መረመረ። ... በደንብ ሊሰራ ይችላል አለ።’ (361) ስለዚሁ ስለ አስትሮኖሚ ጉዳይ ከገጽ 361-363 ሌሎች የሚያስደንቁ ትረካዎችን አካቷል መጽሐፉ።

 

እንደሚታወቀው፣ በ1950ኛዎቹ ዓመታት በባሌ፣ ከዚያም በአዲስ አበባና በአርሲ የተነሳው የኦሮሞዎች ትግል መልኩን እየቀያየረ እስከአሁን ዘልቋል። በሌላ ቦታ እንደተጠቀሰው፤ የ1953 ዓ.ም. የጄኔራል መንግሥቱ ነዋይን መፈንቅለ መንግሥት ካከሸፉ ወታደራዊ ባለሥልጣናት መሀል አንዱ ኮሎኔል በኋላ ጄኔራል ታደሰ ብሩ እንዴት የኦሮሞ ህዝብ መሪ ሊሆኑ እንደቻሉ ተስፋዬ ጠቀስ አድርጓል። (341)

 

መጽሐፉ ላይ ከሰፈረው መረዳት እንደሚቻለው፣ የኦሮሞ ህዝብ ባህልን ማስተዋወቅ ብቻ አይደለም የብሾፍቱው ልጅ ዒላማ። በአሁኑ ዘመን የወያኔ መንግሥት የሚፈጽመው ግፍና አሰራር አሳስቦታል። ‘ወያኔ ሆን ብሎ የህዝቡን ግንኙነት ሮሮ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት እያደረገ ነው’ ይልና ‘ከሃያ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ምድር ላይ አማርኛ መናገር የሚችል አንድም ኦሮሞ አይኖርም’ (322) ሲል የጭንቀት ጩኸቱን ያስደምጠናል። ‘ኢትዮጵያን ከካርታ ላይ ለመደምሰስ የሚሮጡ ሃይሎችን መቋቋም የምንችለው ከብጥስጣሽ የጎሳ ስሜቶች ባሻገር ሰፊ ራዕይ ካለን ብቻ ነው’ ሲል ይደመድማል።

 

‘ወያኔ ሆን ብሎ የህዝቡን ግንኙነት ሮሮ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት እያደረገ ነው’ በማለት ተስፋዬ በወያኔ ላይ ከባድ ክስ ያቀርባል። ማስረጃዎቹ በመጽሐፉ የተለያዩ ክፍሎች ሰፍረዋል። ሁሉንም ተንትነን አንዘልቀውም። ያ ሥራ የዚህ አጭር መጣጥፍ ሃላፊነት ሳይሆን የተስፋዬ ነው። ዋና ዋና የሆኑትን አንድ ሁለት ሦስቱን ብቻ ጠቀስ ጠቀስ እናደርጋለን።

 

ወያኔዎችና ኢትዮጵያዊነት

በኢህአዴግ ክፍፍል ጊዜ አንድ ስብሰባ ይደረጋል፣ ‘በዚህ ጊዜ ነበር ሌኒን (የብአዴን ታጋይ የድርጀት ስም) ቆፍጠን ብሎ ከመቀመጫው የተነሳውና (የተናገረው)።…ከብአዴን አመራር አባላት መካከል ሃይሌ ጥላሁን ብቻ ነው አማራ። ሌሎቻችሁ አማራ አይደላችሁም።…አመራሩ አማራ ሳይሆን እንዴት ነው በአማራ ጉዳይ ላይ እዚህ የምንነጋገረው?...የአማሮች ስብሰባ ከተባለ አማራ ያልሆኑ ከዚህ ስብሰባ ይውጡ! ወይ ደግሞ እንደቀድሟችን ህብረ ብሄራዊ ሆነን ከቀጠልን ልትመሩን ትችላላችሁ’ ይላል። (132) ይህ አነጋገሩ ሌኒንን ጥርስ ውስጥ አስገባው። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ፣ ውጊያ በማስተባበር ላይ በነበረበት አንድ ወቀት፣ ከላይ በተጠቀሰው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የነበረውና ከስብሰባው እንዲወጣ የተጠየቀው ሳሞራ የኑስ ‘“ሌኒንን ግደሉት” ብሎ ትእዛዝ ሲሰጥ አብረውት የነበሩት አራቱም መኮንኖች ሰምተውታል።…ትእዛዙ ሲተላለፍ በወቅቱ የመድፈኛ አስተባባሪ የነበረው ኮሎኔ ገመቹ አያና እዚያው ነበር። ትእዛዙን መስማቱን አረጋግጦልኛል።’ (134) በሌኒን ላይ የሞት ትእዛዝ በተላለፈበት ጊዜ፣ እሱ የተሰጠውን ወታደራዊ ትእዛዝ ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ነበር፣ ‘ሌኒን በበኩሉ ለአራተኛ ጊዜ ጉብታዋን ለመቆጣጠር በቀለጠ ውጊያ ላይ ነበር።’ በውጊያው ላይ ሌኒን ሞተ፣ የሳሞራ የኑስም “የግደሉት” ትእዛዝ ሳይፈጸም ቀረ።

 

ይህን ታውቁ ኖሯል?

‘ከመከላከያ የሰው ሃይል አስተዳደርና ልማት መምሪያ ሰነዶች ያገኘሁት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በጠቅላላ በኢትዮ-ኤርትራ ውጊያ 98700 ወታደር ሲሞትብን፣ 194300 ቁስለኛ ተረክበናል። ከኦርዲናንስ ያገኘሁት መረጃ ደግሞ፣ መጀመሪያ ለውጊያ ከተዘጋጀው ከባድ መሳሪያ 2/3ኛው መውደሙን ነግረውኛል። … የጦርነቱ ማዕከላዊ ዕዝ አባላት ደግሞ፣ መለሰ ዜናዊ፣ ስዬ አብርሃ፣ ተወልደ ወልደማርያም፣ ዓለምሰገድ ገብረአምላክ፣ ተፈራ ዋልዋ፣ ፃድቃን ገብረትንሳዔ እና ክንፈ ገብረመድህን ነበሩ።’ (249-250)

 

ከላይ የተጠቀሰውንም ሆነ የሚከተለውን የሚተርከው ኮሎኔል አበበ ገረሱ ነው። በአንድ የመኮንኖች ስብሰባ ላይ የተፈጸመውን ነው የሚገልጸው። ኦሮሞ መኮንኖች ተበድለናል ብለው ይናገራሉ። በስብሰባው ላይ ተገኝቶ የነበረው ክንፈ (የፀጥታው) የተናገሩትን ካዳመጠ በኋላ፤ ‘የደቡብ ህዝቦችን ምን እንደምናደርጋቸው ብታዩ በጣም ታዝኑ ነበር። በእኛ አስተዳደር የደቡብ ህዝቦች ያሳለፉት ዘመን አሰቃቂ ነው። … አዲስ ቋንቋ ለመፍጠር ሞክረን ርስበርስ እንዲጫረሱ አድርገናል። የአዋሳ መሬት በሙሉ ለትግሬ ተሸጦ አልቋል። … ኢህአዴግ እንደአሳ ከጭንቅላቱ ነው የገማው፣

 

… አቋረጥኩት (ተስፋዬ)

‘ክንፈ ይህን ተናገረ?’ ተስፋዬ

‘ቃል በቃል ነው የምነግርህ። … በነጋታው ግን እዚያው እፊታችን በአራት ጥይት ጭንቅላቱ ላይ ተደብድቦ ተገደለ።’ (243) ኮሎኔል አበበ ገረሱ ከጦሩ ከከዳ በኋላ አሁን ኤርትራ ነው የሚገኘው። ኮሎኔል አለበል አማረ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት አማራ መኮንኖችን ታሰባስባለህ ተብሎ ታሰረ። ከእስር እንደተፈታም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ አነጋገረው። በውይይቱ አልተጣጣሙም ነበርና ጄኔራሉ እንዲህ አለው፤ ‘የቀበርናቸውን የአያቶቻችሁን አጽም ቆፍራችሁ ለማውጣት እየሰራችሁ ነው። አይሳካላችሁም። አርቀን ቀብረናቸዋል። ቆፍራችሁ ልታወጧቸው አትችሉም። እናንተንም በተመሳሳይ ጉድጓድ እንቀብራችኋለን። (288)

 

የወያኔ ሙስናና ንቅዘት

“በደራሲው ማስታወሻ” ውስጥ ጉልህ ቦታ ተሰጥቷቸው ከተተረኩ ጉዳዮች መሀል አንዱ ሙስና ሲሆን፣ ትረካው በኮሎኔል አበበ ገረሱ ጭውውት ላይ የተመሰረተ ነው። በኤርትራ ጦርነት በርካታ ወታደራዊ መኮንኖች በዝርፊያ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚገልጸው ኮሎኔል፣ (238) ከዝርፊያ ስልቶቹ አንደኛው ምን እንደሚመስል እንዲህ ሲል ያስረዳል፣ ‘መከላከያ ሚኒስቴር ለበቅሎ ቀለብ በዓመት አንድ ሚሊዮን ብር መድቦ ነበር። በእኛ እዝ ግን አንድም በቅሎ አልነበረም። የእኛ በቅሎ ጄኔራል አበባው ነው። እነ ሳሞራ ደግሞ ከአበባው በእጅ አዙር ይቀበላሉ።’ (239) ራሱ ኮሎኔል አበበ ገረሱም የዝርፊያው ተቋዳሽ መሆኑን አልሸሸገም። ሂሳብ አታወራርዱም ወይ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‘ይወራረዳል። ለበቅሎ ቀለብ ያቀረቡ ሰዎች ስም ዝርዝር እየሞላን እጃችን እስኪደማ ድረስ ራሳችን እንፈርማለን። ምን ይሄ ብቻ? ... “ለምሽግ ሥራ” በሚል ወጪ ይደረጋል። የተሰራ ምሽግ ግን የለም። ስኳር ለሰራዊቱ ሲታዘዝ መቀሌ ላይ ይራገፍና ይሸጣል። ሰራዊቱ ሻይ አያገኝም። … ነፍጠኛ ሥልጣን ላይ በነበረ ጊዜ የጅማን ጫካ የኔ ነው ብሎ ስላመነ አልነካውም። እነዚህ እኮ አጭደውና ፈልጠው ለመሸሽ የመጡ ወሮበሎች ናቸው። ለሰራዊቱ ዕለታዊ ካምፕና ለሽሮ መቀቀያ 500 ዓመት ዕድሜ ያለውን የቀረሮ ዛፍ ያስቆርጣሉ። … ከምርጫ 97 በኋላ ለይቶላቸዋል። ዛፉንም መሬቱንም በቁም እየቸበቸቡት ናቸው። እስከ ኮሎኔል ያሉት ትግሬዎች በሙሉ ቤተሰባቸውን ወደ አሜሪካ አሽሽተዋል። በስደት ላይ ያሉ የባለሥልጣን ቤተሰቦች ዶላር የሚላክላቸው ከሀገር ውስጥ ነው። የተገላቢጦሽ።’ (240)

 

‘ጎሬ እና ሞቻ ከጫፍ እስከ ጫፍ ቡና ነው። ይህ ቡና ትግሬ ለሆኑ ሰዎች ብቻ መጠቀሚያ እየሆነ ነው። … መዝረፍ ከሆነ እኩል መዝረፍ እንኳ ይሻላል። ለሚዘርፉት አጨብጫቢ መሆን ግን ቁጭት የሚፈጥር ሆነብኝ። … ከተወለድክበት መሬት ላይ እነሱ በበርሜል ወስደው ላንተ በጭልፋ ሲሰጡህ ግን ልትቋቋመው ትቸገራለህ’ ይላል ኮሎኔል አበበ ገረሱ። (233)

 

ሌላው የወያኔ ባለሥላጣኖች ችግር የሴት ጉዳይ ነው። ‘በፖሊት ቢሮ ደረጃ ያሉ አመራር አባላት ሦስት ጊዜ ሚስት እየፈቱ አዳዲስ ሚስት ያገቡ አሉ። ከሦስት ሴቶች የወለዷቸውን አንድ ላይ ሰብስበው የሚያሳድጉ የአመራር አባላትም አሉ። አዲሱ ለገሰ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ታጋይ ሚስታቸውን እስር ቤት ልከው የከተማ ቆንጆ ያገቡ አሉ። … አረጀችብኝ እያሉ ሚስታቸውን የፈቱና ወጣት ቆንጆ እየመረጡ ያገቡ እንደ ተፈራ ዋልዋ አይነቶች አሉ።’ (245) ‘ተፈራ ዋልዋ የበረሃ ሚስቱን መፍታት ብቻ ሳይሆን፣ እንዳትረብሸው ታጠቅ ጦር ሰፈር ወስዶ አሳስሯት ነበር። … አባተ ኪሾ ሚስቱን እስር ቤት አስገብቶ በጠለፋ አይደለም እንዴ አንዲት ቆንጆ ያገባው? ገብሩ አሥራት ባለቤቱ ፓራላይዝድ (ሽባ) ስትሆንበት ፈቷት የለም እንዴ? አይኗን ማየት ባለመፈለጉ አዲስ አበባ ቦሌ ማተሚያ ቤት አጠገብ አንድ አፓርታማ ውስጥ አልቀረቀረባትም? በወቅቱ ይሄን እንደሰማሁ በአካል ሄጄ አልቅሳ ነግራኛለች። … ስብሃት ነጋ የልጆቻቸውን እናት ፈትተው የ18 ዓመት ኮረዳ አግብተው የለም እንዴ?’ (308) እንደ “የደራሲው ማስታወሻ”፣ ሚስቶቻቸውን ማባረር ብቻ ሳይሆን፣ መለዋወጡም በሽ ነው። ‘የጀቤ (ጄኔራል አበበ ተክለ ኃይማኖት) እህት የዓለም ሰገድ ሚስት ናት። የዓለም ሰገድ ሚስት ቀደም ሲል የሳሞራ ሚስት ነበረች። የጀቤ ሚስት ደግሞ የሳሞራ ሚስትም ነበረች። የቀድሞዋ የዓለም ሰገድ ሚስትና የአሁኗ ሚስቱ ዘመድ ናቸው።’ (72) የተቆላለፈና ውሉ የጠፋ ግንኙነት። ‘ስዩም መስፍን…አብራው የታገለች፣ የትግራይ የገጠር ሴት ነበረች። ወዲያው አባረራትና የኤርትራ ሬፈረንደም ዋዜማ ላይ ማዶናን የመሰለች ኤርትራዊት አገባ። ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በኋላ ደግሞ ከእሷም ተፋታና ጄት የመሰለች ነጋዴ የትግራይ ሴት አገባ።’ (307)

 

የወያኔ አመራር መንቅዝ ብቻ ሳይሆን በትእቢት ተወጥሯል። ቦታው ጦር ሃይሎች አካባቢ ያለው የመኮንኖች ክበብ ነው። ባለሥልጣናቱ ከረንቦላ ይጫወታሉ። አንዱ አቶ ስብሃት ነጋ ነበሩ። እሳቸውን የሚመለከት ቀልድ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ጣል አደረገ። አቶ ስብሃት አልወደዱለትም። ተበሳጩ። ‘ወደ ኮለኔሉ አፈጠጡ፣ ሲንጫጫ የነበረው ሁሉ ትንፋሹን ውጦ ጸጥ አለ። አቦይ ስብሃት የከረንቦላ ኳሱን በርጋታ አነሱ። አንድ እርምጃ ወደ ኮለኔሉ ተጠጉ። የከረንቦላ አሎሎውን በሚንቀጠቀጥ እጃቸው ጨብጠውታል። ኮሎኔሉ ፊቱ የሽሮ ቅል መስሎ አቦይ ስብሃት ላይ በድንጋጤ አፍጥጦ ነበር። … እኔና ግርማ ብሩ ኮሎኔሉን ወደ በረንዳው ይዘነው ስንወጣ የኮሎኔሉ ፊት ከሽሮ ቅል ወደ ድልህ ቅል ተለውጦ ነበር። …በዚያ አሎሎ መትተውት ቢሆን እዚያው እፊታችን አንጎሉ ይበታተን እንደነበር በማሳብ ሰውነቴን እንደ ኤሌክትሪክ አጨማዶ ነዘረኝ። … ኮሎኔሉ … በረንዳው ላይ ቁጭ ብሎ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።’ (231)

 

ወያኔና የ1997 ዓ.ም. ምርጫ

በ1997 ዓ.ም. ስለተካሄደው ምርጫ ብዙ ተብሏል። ምርጫው ወያኔና ሕዝቡን እሳትና ጭድ አድርጎ ማለፉን፣ የወያኔ ጭምብል ተገፎ መለ መላውን መቅረቱን፣ የዕውነተኛው ወያኔ ገጽታ ምን እንደሆነ፣ ወዘተ፣ ግልጽ ሆኗል። ብዙም ያልተነገረለት ጉዳይ ቢኖር በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ምክንያት ወታደሩ ውስጥ ስለደረሰው ሁኔታ ነው። ተስፋዬ አንዳንድ ማስረጃዎች አሉት። ‘ቤተ መንግሥት ውስጥ 270 የሚሆኑ የጠቅላይ ሚንስትሩ የውስጥ እጀባ አሉ። ሙሉ በሙሉ የአድዋ ትግሬዎች ናቸው። የቤተ መንግሥቱ ዙሪያ ጥበቃ 550 የሰው ሃይል ይዟል። በአብዛኛው ትግሬዎች ናቸው። ጥይት ቤት ካምፕ ከ500 ያላነሰ ወታደር አለ። ሚስቶቻቸው አሉ። ሰራተኞቻቸውም አሉ። አብዛኞቹ ትግሬዎች ናቸው። የእነዚህ ሁሉ ድምር ከ2000 በላይ ነው። እነዚህ ሁሉ በምርጫው ተመዝግበው እንዲመርጡ ተደርጓል። እነዚህ 2000 ሺህ ትግሬዎች በተሳተፉበት ቀበሌ፣ ኢህአዴግ 165 ድምፅ ብቻ ነው ያገኘው።’ (206-207) ተስፋዬ ይህን የሚያስገርም ማስረጃ አቅርቧል፣ ይሁንና ከየት እንዳገኘው አልጠቀሰልንም።

 

የሕዝቡን ትግል ለማዳፈን ከፍተኛ ድርሻ ወስደው ከነበሩት ሃይሎች መሀል አንዱ የአግአዚ ጦር ሲሆን፣ ‘አግአዚ በ9 ሻለቃና በ3 ብርጌዶች ተዋቅሮ “አግአዚ ኮማንዶ ክፍለጦር” የሚል ስያሜ አገኘ። ’… ምርጫው ሳምንታት ሲቀሩት የወያኔ ከፍተኛ አመራር አባላት … በአንድ ጉዳይ ላይ መግባባት የጀመሩ ይመስለኛል።’ ይህን የሚለው የአግአዚ ክፍለ ጦር አዛዥ የነበረውና አሁን ኮብልሎ በስደት ላይ የሚገኘው ኮሎኔል አለበል አማረ ነው። የምርጫ ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ። የኮማንድ ፖስቱ አባላት፣ ‘መለሰ ዜናዊ፣ በረከት ስምኦን፣ አባዱላ ገመዳ፣ ሙሉጌታ አለምሰገድ መሆናቸው ተነገረን።….ኦፐሬሽናል አመራር ደግሞ ጌታቸው አሰፋ (የደህንነቱ)፣ ሳሞራ የኑስ፣ ኢሳይያስ ወልደጊዮርጊስ፣ ግርማይ ማንጁስ፣ ተስፋዬ መርሳ፣ ታደሰ መሰረት፣ ታደሰ ወረደ፣ ዮሀንስ ገብረመስቀል፣ ገብረእግዚአብሔር መብርሃቱ፣ ሙሉጌታ በርሄ መሆናቸው ተገለጸልን።’ (197) ስለሁኔታው ‘ጄኔራል ሳሞራ የኑስ የሚመለከተንን ስድስት መኮንኖች ሰብስቦ ገለፃ አደረገልን። ከስድስታችን አምስቱ የወያኔ መኮንኖች ነበሩ። እነርሱም ገዛኢ አበራ፣ ዮሃንስ ገብረ መስቀል፣ ገብረ እግዚአብሔር መብርሀቱ፣ ሙሉጌታ በረሄ፣ ገብረ መድህን ፈቃዱ ሲሆኑ’ ስድስተኛው ራሱ ኮሎኔል አለበል ነበር። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ባለሥልጣናት በ1997 ዓ.ም. የተካሄደውን ግድያ ያካሄዱ ናቸው በተስፋዬ መጽሐፍ ገለጻ መሰረት። ታሪክ ይመዝግባቸው።

 

ምርጫው በፈለጉት መንገድ እንዳልሄደላቸው የወያኔ መሪዎች ተረዱ። መጪውን ሁኔታ ለመቋቋምም ዝግጅቱ ተጠናቀቀ። ‘በዚያው በምርጫው እለት ምሽት የተዘጋጀው የጦር ሰራዊት ሃይል ወደ አዲስ አበባ መግባት ጀመረ። የአግአዚ ሦስት ክፍለ ጦሮች ሌሊቱን ከአዋሳ ተጉዘው አዲሳባ ገብተው አደሩ። ደብረዘይት አየር ሃይል ግቢ ውስጥ የነበሩ 23 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ሌሊቱን ተጉዘው አዲስ አበባ ምድር ጦር ግቢ ገብተው አደሩ። ከየእዙ የተውጣጡ 30 ያህል ዙ23 ከባድ መሳሪያዎች ወደ አዲስ አበባ ገቡ። ከ60 በላይ ዶሽቃ የጫኑ ፒክአፕ መኪኖች በፓትሮል መልክ ሊነጋጋ ሲል አዲሳባ ገቡ። … ይህ እንግዲህ የመከላከያ ሃይል ዝግጅት ብቻ ነበር። የፊዴራል ፖሊስ በበኩሉ ከፍ ያለ ዝግጅት ማድረግ ችሎ ነበር።’ (198) ‘በአዲስ አበባ ብቻ ከ30 ሻለቃዎች በላይ፣ … ማለትም ከ18ሺህ ወታደሮች በላይ ተሰማርተው ነበር።’ (203) ይህ ሁሉ የሚሆነው ምርጫ እንደተካሄደ ግንቦት 7 አካባቢ መሆኑ ነው። በዚያን ወቅት ተቃዋሚው ምን ያደርግ ነበር? ይህን የመሰለ ዝግጅት እንደነበረ ገምቶ ይሆን? በጭራሽ አይመስለኝም።

 

ከሰኔ ወር 1997 ዓ.ም. ጀምሮ ግድያው ተካሄደ። ብዙ ሰው አለቀ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በእየእስር ቤቱና በየበርሃው ተወረወሩ። በዚህ መሀል፣ ‘የአግአዚ ክፍለ ጦር ወታደሮች “የገዛ ወገናችንን አንጨፈጭፍም” በሚል ትጥቃቸውን እየተዉ በመኮብለላቸው በ1997 ክረምት ላይ የአግአዚ ክፍለ ጦር መኮንኖች አዋስ ላይ ግምገማ እንዲያደርጉ ሳሞራ የኑስ ወሰነ።’ (204) ስብሰባውን የመራው ጄኔራል ሙሉጌታ ሲገልጽ ‘…የአግአዚ ሁሉም አባል ማለት ይቻላል ቅንጅትን ነው የመረጠው። … ይህ ችግር በተለይ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ ጎልቶ …’ ይታያል አለ። (204) ‘መስከረም ላይ … (በስብሰባው ላይ ከነበሩት) ጥቂቶቹ ታሰሩ። እነዚህም ሻለቃ አዱኛ አለማየሁ፣ ሻለቃ ምስጋናው ተሰማ፣ ሻለቃ ብርሃኑ፣ ሻምበል ውበቱ፣ ሃምሳ አለቃ ዘለዓለም፣ ሃምሳ አለቃ ተስፋዬ ናቸው። … በመጨረሻ ቤተ መንግሥቱ አካባቢ የነበሩ አማሮችን በሙሉ ከአካባቢው በማራቅ፣ አንዳንዶቹን በማሰር ሥራቸውን አጠናቀቁ።’ (208-209)

 

ኮለኔል አለበል አማረም አልቀረለትም፣ ታሰረ። ‘እዚያ እኔ በነበርኩበት እስር ቤት አካባቢ ከቅንጅት ጋር በተያያዘ ብቻ 1700 አማራ ወታደሮችና ኦሮሞዎች ታስረው ነበር።’ (283) የምርጫው ግርግር ካለፈ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኮሎኔል ከማል ገልቹና በኮሎኔል አበበ ገረሱ የሚመራ 250 የሚሆን የጦሩ አባል ኮብልሎ ኤርትራ ገባ። ከዚህ ኩብለላ በኋላ ‘ወያኔ 23ሺ ኦሮሞዎችን ከሰራዊቱ አባረረ።’ (232) ይህን ገለጻ ለተስፋዬ የሰጠው አሁን ኤርትራ የሚገኘው ኮሎኔል አበበ ገረሱ ሲሆን፣ እብሪተኛው የወያኔ መሪ ስብሃት ነጋ በከረምቦላ አሎሎ ጭንቅላቱን ሊፈረክሰው እንደነበር ቀደም ሲል ተገልጿል።

 

ኮሎኔል አለበል አማረ በ2001 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለማካሄድ ሞክረዋል ተብለው ከተከሰሱት መሀል የተመደበ ሲሆን፣ በሌለበት የዕድሜ ልክ እሥራት ተበይኖበታል። (305)

 

ወያኔዎች ሁሉ ዲያብሎሶች እንዳልሆኑ እንድንረዳ፣ በረሄ - ጎማ እግሩ የተባለ ታጋይ ታሪክ በመጽሐፉ ቀርቦልናል። እርፉን ሰቅሎ መስቀሉን አስቀምጦ ለትግል የገባ ተራ ታጋይ ነው። በወያኔ ሙሉ እምነት አለው። ደርግ እንደወደቀ የእሱ ፍላጎት፣ ‘እኛ ወደማናውቀው የአማራ ሀገር ሄደን ከምንሞት፣ ‘ፅዮናዊት ትግራይ’ ብለን ከእሥራኤል ጋር ስምምነት ማድረግና ገዳማትን ማስፋፋት ነበር ምኞቴ’ ይላል። (85) ወያኔ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የሚደረገው ሁሉ አልዋጥልህና አልጥም ብሎታል በረሄን፣ በተለይ ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተባለው መመሪያቸው። ከተስፋዬ ጋር ጭውውቱ የተጀመረው አንድ የካድሬ ስብሰባ ላይ ከተዋወቁ በኋላ ነበር። በረሄ ወደ ስብሰባው ተገዶ ስለመጣ ተበሳጭቷል፣ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠመንጃ ይሁን፣ ታቦት ይሁን፣ ምን ይሁን ገና አልገባኝም። “ስላልገባኝና ሊገባኝ ስለማይችል ውይይቱ ላይ ባልሳተፍ ይሻላል” ብዬ አልተቀበሉኝም።’ (80)በረሄ መለስ ዜናዊን ብዙም አይፈቅደውም፣ ‘መለስ የወሬ ሰው ነው።…ዛሬ የሚናገረውን ነገ ይገለብጠዋል። … ተመልከት ጋራዥ ውስጥ ስምንት መኪና ተበላሽቶ ቆሟል’ ይላል መካኒኩ በረሄ፣ ወደ ሥራው ለመሄድ ጓጉቶ። (85)

 

በረሄ ቤተ ክርስቲያን ሳሚ ነው። ይህን ድርጊቱን የወያኔ አባላት አልፈቀዱትም። አዘውትሮ ከሚሄድባቸው ቤተክርስቲያናት መሃል አንዱ አዲስ አበባ የሚገኘው የጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን፣ ‘የጊዮርጊስ ጠበል በብልቃጥ ይዤ አይተውኝ (የወያኔ አባላት) እንደ አህያ መሬት ላይ እየተንከባላሉ ሳቁ። “ጠበል ሲያይ የሚንፈራፈረው ዲያብሎስ ነው” ብዬ ስላቸው ብሶባቸው እንባቸው እየተዝረበረበ ይስቃሉ።’ (92) በረሄ ብዙ ነገሮች አልዋጥልህ ብልውታል። ‘ወጣት እያለሁ አማሮች ጠላታችን ይመስሉኝ ነበር። ይኸው አገራቸው መጥተን አየናቸው። ሃይማኖተኞችና ሰው አክባሪ ደግ ሰዎች ናቸው። ግፍ እየሰራንባቸውም ችለውን ተቀምጠዋል።’ (92)

 

ስለመጽሐፉ አንዳንድ አስተያየት

አስተያየት ለመጻፍ ሳስብ፣ በህሊናዬ የመጣብኝ የመጀመሪያው ሃሳብ፣ ‘የተስፋዬን የአፃፃፍ ዘርፍ (genre) እንዴት መፈረጅ ይቻላል የሚለው ነበር።’ ተስፋዬ የአፃፃፍ ስልቱ የተባ ነው። ሥራው ግን የፈጠራ ሥራ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አጫጭር ታሪኮች ናቸው ማለትም አይቻልም። ከአጫጭር ታሪኮች አፃፃፍ ዘይቤ አኳያ ሲታዩ የሚጎድላቸው ብዙ ነገር አለ። በግርድፉ ብዙዎቹ መጣጥፎች ጋዜጣዊ ቃና አላቸው። ‘ሪፖርታዥ፣ ወይም feature stories’ ተብለው ሊመደቡ ይችሉ ይሆናል። የተስፋዬ መጽሐፍ ብዙ ማስረጃዎችን አቅርቧል። ገሚሶቹ የራሱ ሲሆኑ የተቀሩት ከተለያዩ ሰዎች ጋር ባደረጋቸው ጭውውቶች ላይ ተመርኩዞ የጻፋቸው ናቸው። አንዳንዶቹ መረጃዎቹ ከየት እንደተገኙ አይገልጽም። ስለሆነም፣ ሙሉ በሙሉ ለመቀበል ያዳግታል። ቢያስተካክለው!

 

ከላይ ከተጠቀሰው ሃሳብ ጋር የተዛመደ ሌላ ነጥብ ላንሳ። ተስፋዬ የመጽሐፉን ርዕስ “የደራሲው ማስታወሻ” ሊለው የበቃው ከፊተኛው መጽሐፍ ለመለየት ፈልጎ እንጅ የተለየ ምክንያት ኖሮት አይደለም።(12) አብዛኛዎቹ ታሪኮች ጋዜጣዊ እንጅ የፈጠራ ሥራ ባህርይ እንደሌላቸው ከላይ አሳይተናል። ስለሆነም፣ በመጽሐፉ የተካተቱ ታሪኮችን በትክክል ሊገልጽ ይችል የነበረው “የጋዜጠኛው ማስታወሻ፣ ክፍል 2” የሚለው ስያሜ ይመስለኛል። ያልሆነውን ሆነ ብሎ ከማቅረብ፣ ቅጥያ፣ ማለትም ክፍል 2 ብሎ መሰየሙ ብዙም ባልከፋ!

 

በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱ፣ ለእኔ ትርጉማቸው ያልገቡኝ አንዳንድ ታሪኮች አሉ። ለምሳሌ፣ የቁልቢ ሌሊት ውስጥ፣ ስብሃት ነጋ በጨረፍታ፣ ወዘተ። የቁልቢውን በምሳሌነት ብወስድ፣ ቁልቢ ስላገኛት አንዲት ሴት ተስፋዬ ያጫውተናል። ስለስለቷም ይገልጻል። ቀጥሎ ምን ሊል ነው ብሎ አንባቢ ሲጠብቅ፣ ታሪኩ ቅልብጭ ብሎ ያልቃል። ተስፋዬ ምን መልእክት ሊያስተላልፍ እንደፈለገ ግልጽ አይሆንም። አጭር ትረካ እንዳልለው (short story) ትረካውን ደንገት በአጭር ይቀጨዋል። የትረካውን ሃተታ (the plot) ያቀርብልንና፣ ማጠንጠኚያና ማሳረጊያው (climax and anticlimax or resolution) ምን እንደሆነ አያሳየንም። ከሴትየዋ ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ላይ ደረሰ? ተጋቡ? ተፋቀሩ? ከዚያስ? እንዴት ተለያዩ? ተስፋዬ ምንም ፍንጭ አይሰጥም። ‘ስብሃት ነጋ….’ የሚለው ክፍልም ምንም አዲስ ነገር የለውም። ለምን እንዳካተተውም ግልጽ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ፣ የአንድ ሰው ሥራ፣ ማለትም “ያልተጻፈ መጽሐፍ” የሚል ርዕስ የተሰጠው፣ ከተስፋዬ ሥራዎች ጋር ተቀላቅሎ ቀርቧል። ጨርሶ ልክ አይደለም። ያ ሥራ የተስፋዬ ሥራ ተብሎ መቅረብ አልነበረበትም።

 

ተስፋዬ ክፉኛ ይናደዳል። አትንኩኝ ባይ ነው። ምዕራፍ 19 ላይ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተናገሩ የተባለውን ይሰማና፣ በቀላሉ ልክ ነው አይደለም ብሎ መመለስ ሲችል፣ ለምን ተነካሁ ብሎ ‘ኮረንቲ ይጨብጣል’። የሆኑ ያልሆኑ ብዙ ነገሮች ውስጥ ገብቶ ይውተፈተፋል። ለምን እኔን ብቻ ይናገራሉ፣ ለምን እነ እገሌን አይናገሩም ሲል ይወቅሳል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሰፈሩት አብዛኛዎቹ ሃሳቦች እንቶ ፈንቶዎች ናቸው። የተስፋዬን የደራሲነት ተክለ ሰውነት ይፈታተናሉ። አንድ ደራሲ መጽሐፍን ያህል ነገር ጽፎ ትችት አይቀረብብኝም ብሎ መጠበቅ አይኖርበትም። እንዲያ የሚያስብ ከሆነም ተሳስቷል። ተስፋዬ በትንሽ ጉዳይ ሊናደድ እንደሚችል የሚያውቁ ጠላቶቹ ብዙ ሊጎዱት ይችላሉና ሊያስብበት ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ብዕሩን አዎንታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊያሳርፍ ቢችል ታላላቅ ደራሲዎች የደረሱበት ላይ እሱም ይደርሳል። ታላላቅ የዓለማችን ደራሲዎች፣ እነ Victor Hugo, Honore Balzac, Chinua Achebe, Charles Dickens, Ernest Hemmingway, Pushkin, Chekov, Dostoevesky, አዲስ ዓለማየሁ፣ አቤ ጉበኛ፣ አንቱ ሊባሉ የቻሉት ፍቅርን ስላስተማሩና ስለፍቅር ስለፃፉ ነው፤ የሰው ፍቅር፣ የሀገር ፍቅር።

 

በእርግጥ ተስፋዬ ከላይ የተጠቀሰውን ድክመቱን ያውቃል። ተስፋዬ ያለው፣ ሌሎች ብዙ ሰዎች የሌላቸው ባህርይ ራስን በአደባባይ መስደብ ነው። ተስፋዬ በራሱ ስቆ ማሳቅ ይችላል። ታላቁ ደራሲ አቶ መንግሥቱ ለማ እንደዚያ ነበሩ ይባላል። ያነበብኩትን ላካፍላችሁ። በተማሪነት ዘመናቸው እንግሊዝ ሀገር ሚሪ ታደሰ የምትባል ተማሪን (በኋላ እሳቸውም ሆኑ ወንድማቸው አቶ ማሞ ታደሰ ከፍተኛ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣን ነበሩ) ይወዳል። ልጅቱን ሲኒማ አድርሶ ቤቱ የመልሳል ተማሪ መንግሥቱ። ጓደኞቹ ‘እህስ’ ይላሉ። ‘ምንም አዲስ ነገር የለም’ ይላል ተማሪ መንግሥቱ። በሳምንቱም፣ በአሥራ አምስተኛ ቀኑም፣ በወሩም ሁኔታው በዚያው ቀጠለ። ተንኮለኛ መከረው። ጨበጥ አድርገህ ሳማት ብሎ። አንድ ቀን ምሽት ላይ የተባለውን አደረገ። ልጅቱ ገፍተር አደረገችው። ጓደኞቹ ጠብቀው ‘እህስ’ ሲሉ ጠየቁ። ‘ገፈተረችኝ’ ሲል ተናገረ ተማሪ መንግሥቱ። ወሬው ተጨማምሮበት ተዛመተ። ‘በጥፊ አጮለችው ተባለ።’ በኋላ ላይ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት ተማሪ እንዳልካቸው መኮንን ጭምር ተማሪ መንግሥቱን ሲያይ ሆዱን ይዞ ይስቅ ጀመር። ተማሪ መንግሥቱ፣ የተማሪ መሳቂያ መሳለቂያ ከመሆን ለማምለጥ መላ ፈለገ። እሳትን በእሳት እንዲሉ፣ የተማሪውን ሳቅ ለማጥፋት በራሱ መሳቅ እንዳለበት አመነ። ‘በጠራ ጨረቃ..’ የተባለችውን ዝነኛ ግጥሙን ቋጥሮ በአንድ የተማሪ ስብሰባ ላይ አነበበ። ዓይነስቡ እንዴት በጥፊ እንደጋየ ተረከና ተማሪውን አሳቀ። ልጅቱም እዚያው ነበረችና አፈረች፣ ተማሪ መንግሥቱ ግን ደረቱን ነፋ።

 

ተስፋዬ የደራሲነት ጉልበት አለው፤ ራሱንም ይተቻል። ገጽ 419 ላይ እንዲህ ያላል፣ ‘የብዕሬን ቁጣ እኔው ለራሴው እፈራዋለሁ። ከጫፉ እሳት የሚተፋ ያህል ይፈላል። ይህን መሰል ማስታወሻዎቼ ለህትመት እንዳይበቁ በጣም እጠነቀቃለሁ። ብዙውን ጊዜ ቀዳድጄ እጥላቸዋለሁ።’ እንኚህ እንደ እሳት የሚፋጁ ሥራዎቹ ለህትመት አለመብቃታቸው ደግ ነው፣ ግን አይጣላቸው፤ መማሪያ ይሆኑታል። ሰው እጅ እንዳይገቡ ግን መጠንቀቅ ይኖርበታል።

 

ተስፋዬ እንዲህ ሲል ነው የሚሰናበተን፣ ‘ፍቅርና እውነት አሸንፈው ይነግሳሉ። … ነገ ማለዳ ከምትወጣው ጀምበር ጋር የነፃነት ቀን አብራ ብቅ ትላለች።’ (422)


ተስፋዬ ዮሐንስ - ሚያዝያ 12 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ