ተመስገን ደሳለኝ

ከኢህአፓ ወደ ኢኮፓ፤ ከኢኮፓ ወደ ኢህዴን፤ ከኢህዴን ወደ ብአዴን… እነዚህ ሁሉ የዛሬው እንግዳችን የፖለቲካ ዝውውሮች ናቸው። መቼም ‹‹በዚህ ትውልድ›› ዝውውር ተፈፀመ ወይም ተዘዋወረ ከተባለ ከማንችስተር ዩናይትድ ወደ ሪይል ማድሪድ፤ አሊያም ከአርሰናል ወደ ባርሴሎና ነው። ‹‹በያ ትውልድ›› ደግሞ ከአንዱ ፓርቲ ወደ ሌላው ፓርቲ፤ ከሶሻሊዝም ወደ ካፒታሊዝም፤ ከኢምፔሪያሊዝም ወደ ኮሚኒዝም፤ ከአልባኒያኒዝም ወደ ማሌሊትዝም፤ ከማሌሊትዝም ወደ አብዮታዊ ዲሞክራቲሲዝም … ሲሆን ይሄ አይነቱ ዝውውር ‹‹የብልህ›› ስልት ተደርጎ ከመወሰዱም ባሻገር ለተዘዋዋሪዎቹ ጫማ ከመቀየር የቀለለ ነበር።

 

 

የሆነ ሆኖ ዛሬ ሚኒስትር፤ በድሮ ጊዜ ፕሮፌሽናል (ተዘዋዋሪ) ታጋይ የነበሩት ዝነኛው በረከት ስምኦን መጽሐፍ መፃፋቸውን ሰምተን ሳናበቃ፤ መጽሐፉ የሚታተመው በሀገር ውስጥ እንዳልሆነ ተነገረን። የዚህ ምክንያትም እንዲህ የሚል ሆነ። የኢትዮጵያ መንግስት የህትመት ዋጋን ያለቅጥ በመቆለሉ ነው፡፡ እናም በረከት መፃህፋቸውን በሀገር ውስጥ ለማሳተም አቅም ስላጠራቸው በኬንያ ለያሳትሙ እንደሆነ መጀመሪያ አካባቢ ውስጥ ውስጡን ተወራ፣ ቆይቶ ደግሞ በድህረ ገፆች እና በሀገር ውስጥ ጋዜጦች ዜና ሆኖ ሲቀርብ ደነገጥን፡፡ በእርግጥ በረከት ስምኦንን የመሰለ ታጋይ አንድ ሀባ መጽሐፍ ለማሳተም የዋጋ ቅናሽ ፍለጋ ከሀገር ሀገር መንከራተታቸው ሲሰማ ብዙዎቻችን ከልብ አዘንን። በተለይ ብአዴን ፓርቲያችን ያልን ደግሞ ሀዘኑ ይበልጥ በረታብን።

 

በነገራችን ላይ ኤርትራውያን ከሆኑ ቤተሰቦች በጎንደር ተወልደው በጎንደር አድገው፤ በጎንደር እና አካባቢው ታግለው ሚኒስትር ለመሆን የበቁት በረከት ስምኦን ትግል የጀመሩት የኢህአፓ አባል በመሆን ነው፡፡ በኋላም ኢህአፓ ውስጥ ክፍፍል ሲፈጠር በረከትን ጨምሮ ጥቂት ሰዎች የኢትዮጵያ ኮሚኒስት ፓርቲን (ኦኮፓን) መሰረቱ። በወቅቱም እዛው ኢህአፓ ውስጥ የቀሩ አሿፊዎች ኢኮፓን፡- ‹‹የኢትዮጵያ ኮሚኮች ፓርቲ›› እያሉ ያላግጡበት ነበር። ሆኖም ኢኮፓ ብዙም ሳይሄድ ቀልጦ ቀር።

 

ኢህዴንም በእነበረከት አጋፋሪነት ተመሰረተ። ከድል በኋላ ደግሞ ኢህዴን ወደ ብአዴን በደብተራ ጥበብ፣ ጠበበ። እነሆም ብአዴን ከሌሎች ሶስት ብሄር ተኮር ድርጅቶች ጋር ተጋግዞ ሀገር ማስተዳደር ከጀመረ ዘንድሮ 21ኛ አመቱን ይዟል። ማን ያውቃል? እኛም እንዲሁ እንደተበሳጨን፤ እነሱም እንዲሁ እያሾፉ 42ኛ አመታቸውንም ሊያከብሩ ይችላሉ። በእርግጥ ይሄ ግምት ነው። ከግምት ስንመለስ ግን ቀጥለን የምናየውን ርዕስ እናገኛለን።

 

በእለተ ማክሰኞ (10/2004) ከቀኑ 11 ሰዓት በበረከት ስምኦን የተፃፈውን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› በሚል ዋና ርዕስ እና ‹‹ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ›› በሚል ንዑስ ርዕስ የታተመው መጽሐፍ ሸራተን አዲስ ይመረቃል በሚል ሽር ጉድ ተይዞአል።

 

… ሚንስትር በረከት ስምኦንም እንደተለመደው ጥቁር ሱፍ፣ ያለከረባት ለብሰው፤ ፊታቸው ጥርስ በጥርስ ሆኖ ነው ሸሰራተን- ላሊበላ አዳራሽ የተገኙት። በእርግጥ በአዳራሹ የተገኙት በረከት ብቻ አይደሉም። አገሪቷን የሚገዙት (ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀር)፣ ሰርተው ሳይሆን ተጠግተው የበለፀጉ ባለሀብቶች፣ ወግ ከተፃፈለት ምርጫ 97 በኋላ ነባር ካድሬዎችን ሳይቀር እያስናቁ የመጡት ስፍር ቁጥር የሌላቸው አርቲስቶች… የመሳሰሉት ተገኝተዋል።

 

የመድረኩ መሪ ሴኩቱሬ ጌታቸው ናቸው። ሴኩቱሬ ምንም እንኳ አማራ ቢሆኑም የህወሓት አባል ናቸው፡፡ ለነገሩ በረከትም ምንም እንኳ ኤርትራዊ ቢሆኑም የአማራ ድርጅት መሪ ናቸው። (ማስታወሻ፡- የዛሬን አያድርገውና በረከትን በኢህአፓ ወቅት የሚያውቋቸው ነባር የኢህአፓ ሰው እንዳጫወቱኝ በረከትን የኤርትራ፣ የትግራይ፣ የአማራ ምናምን የሚባል ፖለቲካ እንደማይመቻቸው ነው። እናም ከብሄር /ከዘር/ ፖለቲካ ይልቅ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ እንደነበሩ ነው። ዛሬስ? እንጃ። ለነገሩ ትግሉ ራሱ አድካሚ ከመሆኑ የተነሳ ከተራራ ተራራ፣ ከቋጥኝ ቋጥኝ ሲዘለል በድካምና በእንቅፋት ብዛት ከውስጥ የነበረ አቋም ሊንጠባጠብ አይችልም ብላችሁ ነው?)

 

… ወደ ሸራተን እንመለስ። ሴኩቱሬ በአዳራሹ ከተገኙት ከብርቅዬ አርቲስቶቻችን መሀል ጥቂቶቹ (ፍቃዱ ተ/ማርያም፣ ደበሽ ተመስገን፣ ባዩሽ አለማየሁ፣ ሀገረወይን አሰፋ፣ እመቤት ወ/ገብርኤል …) መፅሐፉን አንብበው በመደሰታቸው፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ይበልጥ የማረካቸውን አንቀጽ መዘው ለአንባቢያን ለማቅረብ ጥያቄ ስላቀረቡ… በሚል ማስታወቂያ አርቲስቶቹን ወደ መድረክ ጋበዙ። እነዚህ ተጋባዥ አርቲስቶችም ገና ያልተመረቀን መጽሐፍ የት አግኝተው እንዳነበቡት ባይታወቅም ‹‹ስናነበው ደስ ያለን…›› እያሉ ጥቂት አነበቡልን። በተለይ ባዩሽ አለማየሁ በጣም ያስደሰታትን አንቀጽ እንደ ቲያትር አጥንታው ኖሮ፣ ከወዲህ ወዲያ እያለች መነባነብ አድርጋ አቀረበችው (ሆን ብለው ይሁን ወይም በአጋጣሚ ሁሉም አርቲስቶች የመረጧቸው አንቀጾች የ97ቱ ቅንጅትን ወይ የሚያወግዙ፤ አሊያም የሚያሾፉበትን ነው)

 

የሆነ ሆኖ በቀጥታ ወደ መጽሐፉ ከመሄዳችን በፊት፣ እስቲ ስለመድረክ መሪው የእለቱ ውሎ ጥቂት ነገር እናውራ። አዎ! የመድርኩ መሪ ሴኩቱሬ የበረከት የትግል ጓድ በመሆናቸው ስለ በረከት ብዙ ተናገሩ። ምስክርነትም ሰጡ። ከምስክርነት ቃላቸውም ለምሳሌ ያህል መጥቀስ ቢያስፈልግህ ‹‹…ስለአቶ በረከት የፖለቲካ ህይወት ያገኘኋቸውን ሰዎች ስጠይቃቸው፤ አብዛኞቹ የተሳሳተ ምልከታ ነው ያላቸው። አቶ በረከት ግን ለኪነጥበብ የቀረበ ህይወት ነው ያለው። ይህንንም በመፅሐፉ አሳይቷል›› ያሏትን ልናይ እንችላለን። እንግዲህ የበረከትን የፖለቲካ ህይወት (አቋም) የሚተቹ ሰዎች፣ በሚከተሉት ርዕዮተ-አለም እና በአምባገነንተቻው ሳይሆን በረከት ለኪነጥበብ የቀረቡ ወይም አርቲስት መሆናቸውን ባለማወቅ ነው፡፡ በሴኩቱሬ ማብራሪያ መሰረት።

 

አሁንም ከሴኩቱሬ ጥልቅ ማብራሪያ አንድ ልጨምር። ‹‹ስለአቶ በረከት ቤተሰባዊ ህይወት በጣም የገረመኝን አንድ ነገር ልንገራችሁ። አቶ በረከት ምን ያህል የቤተሰብ ሀላፊነቱን የሚወጣ እንደሆነ ያየሁበት ነው። አንድ ቀን ስራ አምሽተን መውጫችን ሰዓት አካባቢ አቶ በረከት በጣም ይጣደፍ ነበር። እኔ ደግሞ ከዚህ በኋላ ስብሰባ አለብህ ወይ? ስል ጠየኩት። አቶ በረከት የመለሰልኝ መልስ በጣም አስገራሚ ነው ‹ልጄን ላስጠና ነው› ሲል መለሰልኝ።›› (እንግዲህ ለሴኮቱሬ የአንድ ሚኒስትር ብቁነት እና ሀገራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣቱ ማረጋገጫው ህፃን ልጁን ፊደል በማስቆጠሩ እና ባለማሰቆጠሩ ነው። ምንአልባት ሌሎች ክቡራን ሚኒስትሮች ሀገሪቷን ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸውንም ዞር ብለው አያዩ ይሆን እንዴ? ሴኩቱሬ በበረከት እንዲህ የተገረሙት? በነገራችን ላይ በእኔ እይታ የበረከት መፃሀፍ ሙሉ በሙሉ በእንዲህ አይነት ጨቅላ መከራከሪያዎች እና እርግማኖች የተሞላ ነው)

 

… አሁን ወደ መጽሐፉ እንመለስ፡፡ በሁለት ክፍል እና በአስር ምዕራፎች የተከፈለው ይህ መጽሐፍ 314 ገፆች ያሉት ሲሆን፤ የምርቃቱ እለት በ90 ብር ዋጋ ነው ለገበያ የቀረበው፡፡ (በእርግጥ የመሸጫ ዋጋው 75 ብር ነው። ምን አልባት በሸራተን የተሸጡት መፅሀፎች ላይ የበረከት ፊርማ ስላለ ይሆናል፡፡ ዋጋው 90 ብር የሆነበት ምክንያት ይሄ ከሆነ ግን በረከት ስምኦንን የመሰሉ ታግሎ አታጋይ መሪ የፊርማ ዋጋ 15 ብር ብቻ መሆኑ በጣም ያሳዝናል። መቼም በዛሬ ጊዜ 15 ብር አንድ ሽሮ እንኳ ሊገዛ አችልም። ሌላው ሌላው ቢቀር እንኳ አሁን ይሄ ፊርማ የህወሓት ሰው ፊርማ ቢሆን በዚች ብር ይገኛል? ኧረ በጭራሽ። እስቲ እንደው ቢያንስ በዚህ በዚህ እንኳ ብአዴን እና ህወሓት አቻ ቢሆኑ ምን ክፋት ነበረው? አይሰው! አይ ውለታ አለመቁጠር!)

 

በመጽሐፉ መቅደም ላይ ይሄ መጽሐፍ የተዘጋጀው ለታሪክ ተመራማሪዎች ግብአት ይሆን ዘንድ ታስቦ እንደሆነ ፀሐፊው ገልፀዋል፡፡ (እዚህች ጋም ተጨማሪ ማስታወሻ፡- አደራ በመቅደሙ ላይ ‹‹ለታሪክ ተመራማሪዎች …›› ተብሎ የተፃፈውን ብቻ አምናችሁ በመጽሐፉ ውስጥ እውነተኛ ታሪኮችን እናገኛለን ብላችሁ እንዳትቋምጡ፡፡ ምክንያቱም ሲያምራችሁ ነውና የሚቀረው።)

 

ሌላኛው በመቅደሙ ላይ የተገለፀው፣ መጽሐፉ እንዲታተም ባደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ስለቀረበላቸው ሰዎች ነው። ምስጋናውም እንዲህ ሲል ይጀምራል ‹‹በዚህ መጽሐፍ ዝግጅት ላይ ውድ ባለቤቴና ልጆቼ ላደረጉልኝ ትብብር ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። አሲ ይህች አገርና ህዝቦቿን ለማገልገል ባለፍኩበት ሁሉ ከጎኔ ሆነሽ ለከፈልሽው መስዋእት ምንጊዜም ውለታሽን አልረሳውም። ለራስሽ ዓላማ ስትይ ያደረግሽውም ቢሆን ለእኔ ሁሌም የተለየ ድጋፍ ነበር። ያላንች ከባዶቹን ዓመታት እንዳላለፍኩ አውቃለሁና የወደፊቱን ህይወቴንም ባንችው ድጋፍ እንደምዘልቅበት አልጠራጠርም። ልጆቼ ኮበል፣ ፍሰሃና ህሊና ለእናንተ ልመድበው ይገባኝ ከነበረው ጊዜ ተበድሬ አብዛኛውን ላነገብኩት ዓላማ ያዋልኩት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጋር ተመችቷችሁ እንደሰው ተከብራችሁ የምትኖሩባት አገር እንድትኖራችሁ ነበርና ለእናንተም ቢሆን የባከነ ጊዜ አልነበረም። የአባትነት ፍቅሬን ብቻ ተማምናችሁ ላሳያችሁኝ ትእግስት፣ ለሰጣችሁኝ ፍቅርና ላበደራችሁኝ ጊዜ መቼም ቢሆን ሳላመሰግናችሁ አላልፍም …›› (ገፅ 11 እና 12) ይልና መጽሐፉን ገና በረቂቅነቱ ደረጃ አንብበው ‹‹እጅግ በጣም ጠቃሚ እና አስተማሪ አስተያየት›› ሰጡኝ ያሏቸውን ጓዶች ስም ለምስጋና ይዘረዝራሉ። ‹‹ህላዊ፣ ታደሰ፣ ደመቀ፣ መለስ፣ ተፈራ፣ አርከበ፣ ካሱ፣ ሬድዋን፣ ሙክታር፣ ገናናው፣ ሽመልስ፣ አባይ፣ ወልዴ፣ ረታ፣ ሁለቱ ታምራቶች …›› እያለ ይቀጥላል። በእርግጥ እዚህ ድረስ ስማቸው የተጠቀሱትን ሰዎች እውቃቸዋለው። ሆኖም ‹‹ሁለቱ ታምራቶች›› የተባሉት ግን እነማን እንደሆኑ አላወኳቸውም፡፡ ምናልባት ታምራት ላይኔ እና ታምራት ገለታ (እያንጓለለ) ይሆኑ እንዴ?

 

የመጽሐፉ ጭብጥ

 

የመጽሐፉ ምዕራፍ አንድ እንደተለመደው ስለሀገሪቱ የ11.5 የኢኮኖሚ እድገት ያውራና ድንገት ወደ 1993ቱ የህወሓት ክፍፍል ይሄዳል። እዚህ ጋርም እንደተለመደው የእነ ተወልደን እና ስዬን ቡድን ያወግዛል። በእርግጥ አውግዞ ብቻ አያበቃም። የክፍፍሉን ምክንያትም እንዲህ ሲል ይገልፃል ‹‹እየዋለ እያደረ ጦርነቱ በኢህአዴግ አመራር መካካል ለሀሳብ ልዩነት መነሳት ምክንያት ወይም ለም አፈር መሆን ጀመረ።›› (ገጽ 21) በክፍፍሉ ወቅትም እኮ እነስዬ ለክፍፍሉ ዋነኛ ምክንያት ‹‹የሉአላዊነት ጥያቄ ላይ የተፈጠረ የአቋም ልዩነት ነው›› ሲሉ ነበር። እነ መለስ ደግሞ ‹‹የክፍፍሉ መንስኤ ሙስና እንጂ የኤርትራ ጦርነት አይደለም›› ሲሉ ከራክረዋል። በረከት ደግሞ በወቅቱ ምንም እንኳ መለስን ደግፈው የቆሙ ቢሆንም፤ ከ11 አመት በኋላ በመጽሐፋቸው ከእነ ስዬ ጎን ተሰልፈዋል።

 

ይህንን ሁኔታም በገጽ 22 ላይ አጠናክረው በደንብ ያብራሩታል። ‹‹አቶ ስዬ በርከት ባሉ አጋጣሚዎች መሳሪያና ተተኳሽ ለመሸመት ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት አካባቢ ይመላለስ የነበረ ይሁን እንጂ በኢህአዴግ ውስጥ በተነሳው ልዩነት ጦርነቱ የወሰደውን ጊዜ ይውሰድ። ኤርትራን ለማንበርከክና ከተቻለም አሰብን ቆርሰን ለማምጣት ልንቆጥበው የሚገባን ህይወትና ሀብት ሊኖር አይገባም። የሚለውን አቋሙን ለማራመድና በዚህ አቋሙ ዙሪያ የተቧደነ አንጃ ለመፍጠር የሚሆን ከበቂ በላይ ጊዜ ግን ነበረው።››

 

ሌላኛው የመጽሐፉ ትኩረት ሳቢ የኢህአዴግ አመራር ሙሰኛ እና ለግል ጥቅሙ ብቻ የሚጨነቅ መሆኑ የተገለፀበት ነው ‹‹በአገራችን በቦና ፓርቲስታዊ ዝቅጠት መልክ የተሰየመው አደጋ ተጨባጭ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት የነበረው ሲሆን የአመራሩ ባህሪም ለዚህ የተመቸ ነበር፡፡ አመራሩ በተፈጥሮው የንዑስ ከበርቴ ኃይል ነው። እንደማንኛውም ንዑስ ከበርቴ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚካሄደው ትግል ሲስፋፋም ተአምር የሚሰራ፣ ትግል ሲቀዘቅዝ ደግሞ የሚፈዝ፣ ከዚህም ራቅ ሲል ወደ ግል ኑሮው የሚያዘነብል ኃይል ነው። የኢህአዴግ አመራር ከሞላ ጎደል ትምህርቱን ወይም የጀመረውን ስራ አቋርጦ ወደ ትግል የገባና የህዝቡን ንቅናቄ መርቶ ደርግን ያህል ግዙፍ መንግስት አስወግዶ የወጣ ሀይል ነው።

 

አመራሩ የአርሶ አደሩ ትግል በከፍተኛ ደረጃ በተፋፋመበት ወቅት ተአምር የሰራ የንዑስ ከበርቴ ሀይል ነው። አርሶ አደሩ የመሬት፣ የብሄር፣ የምርት ነፃ ተጠቃሚነት ጥያቄው ተመልሶለት፣ ከትግሉ ርቆ አርሶ በመብላት ላይ በተወሰነበትና ለመንግስትና ለኢህአዴግ ጠንካራ ድጋፍ እንጂ ተቃውሞ የሌለው በሆነበት በዚህ ወቅት አመራሩ ስለኑሮውና ምቾቱ የሚጨነቅና ለዚህም ቅድሚያ ሊሰጥ የሚችል ነበር።›› (ገጽ 28) ይህንን እንኳን እርስዎ የቅርቦቻቸው ቀርቶ፤ እኛም የሩቆቹ ጠንቅቀን እናውቃለን። ምናልባት ስም ጠቅሰው ቢሆን ኖሮ ግን ቢያንስ አዲስ ነገር እንደነገሩን አድረገን እናመሰግንዎት ነበር። ግን … የመጨረሻው ከመፅሀፉ የሚገኘው እውነት ለ20 አመት ያህል የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የፖለቲካ ተንታኞች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በህገ መንግስቱ ላይ እንደተገለፀው ገለልተኛ ሳይሆን ለኢህአዴግ የሚወግን ነው የሚለውን ወቀሳ በረከት ስምኦንም ያረጋገጡበት አንቀጽ ነው፡፡ ‹‹አንዳንዴ በቀላሉ ይገባቸው (በ97 ምርጫ ማግስት ለቅንጅት አመራሮች የተናገሩት ነው) እንደሆነ ብለን ሰራዊቱን በአንድ ወቅት የኢህአዴግ መንትያ ፍጥረት እንደነበርና ክፉ ነገር ከመጣ አሰላለፉ ከማን ወገን እንደሚሆን የሚገነዘብ መሆኑን ብንነግራቸውም ከልባቸው አልጠፋ ብሏል።›› (ገጽ 119)፡፡ እና በገፅ 233 ላይ ደግሞ ‹‹እንደመስቀል ወፍ በዓመት አንዴ ብቅ የሚለው ታላቁ ሩጫም በተወሰነ ደረጃ የተቃውሞው ማስቀጥያ ሆኖ እንዲያገለግል ተሞክሯል›› የሚለው ሀረግ ነው። ለነገሩ ታላቁ ሩጫ ዘንድሮም ጠንካራ የፖለቲካ ተቃውሞ የቀረበበት ሆኖ ነው ያለፈው።

 

እነሆም አዲስ ዘመን ገጽ 3 ላይ ነፃ ጋዜጠኞችን እና የመድረክ አመራሮችን ለማውገዝ በሚፃፉት ፁህፎች አይነት /ስታየል/ ከተፃፈው የበረከት መጽሐፍ የሚገኙት እውነቶች እነዚህ ብቻ ናቸው። በቃ! ከዚህ ውጭ እርግማን፣ ሀሜት፣ መለስን ማሞገስ፣ የራሳቸውን ብልህነት፣ የኢህአዴግን የመላዕክ ስብስብነት፣ ኢህአዴግን ህዝቡ ከነፍሱ አብልጦ እንደሚወደው … ወዘተ የዘረዘሩበት እንቶፈንቶ ነው፡፡ በእርግጥ ከገፅ 119 ላይ የጠቀስኩት በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ምርጫ 97ን ተከትሎ በተነሳው ሁከት ከ198 በላይ ሰው የተገደለው በሰራዊታችን ነው። እስከዛሬ ድረስ የሚነገረን ደግሞ ሰራዊቱ ጣልቃ የገባው የህዝብን ሰላም እና ህገ መንግስቱን ለማስከበር እንደሆነ ነበር። የበረከት መጽሐፍ ዛሬ ደግሞ የሚነግረን ሰራዊቱ የኢህአዴግ መንትያ እንደሆነና ምንም ይፈጠር ምን ምንጊዜም የሚቆመው ከኢህአዴግ ጋር እንደሆነ፤ ይሄንንም ለእነ ብርሃኑ ነጋ እንደነገሯቸው ነው።

 

እርግማን፣ ውግዘት፣ ውንጀላ …

 

በረከት ስምኦን ለምን ይህን መፅሀፍ እንደጻፉ በመቅደሙ ላይ ቢገልጹም፣ መጽሐፉ እና መቅድሙ ግን ሀራምባና ቆቦ በመሆናቸው ተአማኒነት ያሰጣዋል። ምክንያቱም መጽሐፉ የሚያተኩረው ለታሪክ ተመራማሪ የሚሆን ግብአት ላይ ሳይሆን በዋናነት ብርሃኑ ነጋን እና ነገደ ጎበዜን ማውገዝ፣ መወንጀል፣ ማጥላላት፣ መርገም ላይ ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ መራራ ጉዲናን እና በየነ ጴጥሮስን እርስ በእርስ ለማጣላት ‹‹እንዲህ አለው … እንደህ ተባባሉ …›› የሚሉ አሉባልታዎች፣ እንዲሁም እነ ስዬ አብርሃን በማጣጣል እና በመሳሰሉት ላይ ያነጣጠረ ነው።

 

በበረከት መፅሀፍ በዋናነት ከተብጠለጠሉት ውስጥ ነገደ ጎበዜ በትግል እድሜም ሆነ በእናት ፓርቲ የተለዩ ሲሆን፤ ብርሃኑ ነጋ እና በረከት ስምኦን ግን በብዙ መልኩ ይመሳሰላሉ። ሁለቱም የኢህአፓ ታጋዮች ሲሆኑ ሁለቱም ኢህአፓን አውግዘው ከኢህአፓ ተለይተዋል፡፡ በእድሜምም እኩያ ናቸው። በባህሪም ይመሳሰላሉ። (በሽወዳ ፖለቲካ ላይ ማለቴ ነው) ሁለቱም ምርጫ 97 ላይ የፓርቲያቸው ዋነኛ ተደራዳሪ የነበሩ ሲሆን፤ ሁለቱም በዚሁ ምርጫ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ፅፈዋል። ምንም እንኳ በይዘት መጽሐፎቻቸው ነጭ እና ጥቁር ቢሆንም። (ስለሁለቱ መጽሐፎች ምት እና የመልስ ምት እንዲሁም ከዚህ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን ወደ ታች እመለስበታለሁ።)

 

አሁን ስለውግዘቱ እና ስለሀሜቱ ማየታችንን እንቀጥል ...

 

በእርግጥ በበረከት መፅሀፍ ከሀይሉ ሻውል እስከ ልደቱ አያሌው፤ ከብርሃኑ ነጋ እስከ መራራ ጉዲና፤ ከአዲስ ነገር ጋዜጣ እስከ ቪኦኤ እና ዶቼቬሌ፤ ከአና ጎሚዝ እስከ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች … ያልተረገመ፤ ውጉዝ ከመአርዮስ ያልተባለ የለም።

 

ምን አልባትም በረከት ይህን መፅሀፍ ለመፃፍ የተነሱት በምርጫ 97 ኢህአዴግ ያ ሁሉ ሽንፈት ሲደርስበት የፓርቲው ቋሚ ተጠሪ የነበሩ መሆኑን ተከትሎ በሊቀመንበር መለስ ዜናዊ ለሽንፈቱ ተጠያቂ ተደርገው መወቀሳቸው ሲከነክናቸው የቆየ በመሆኑ ሊሆን ይችላል።

 

የሆነ ሆኖ በረከት ለመፅሃፈቸው ግባት ይሆን ዘንድ ኢህአዴግ በተለያየ ጊዜ ያሳተማቸው መጽሐፍቶች፣ ቃለጉባኤዎች፣ የመለስ ዜናዊ ንግግሮች፣ የስራ አስፈፃሚ ሪፖርቶች፣ የቡዳ ታሪክ፣ ሽፍቶች እና ሌቦች ሪፈረንስ (ማጣቀሻ) ተደርገዋል።

 

ለምሳሌ የቅንጅት አመራሮችን ከሽፍታ ጋር በገጽ 234 ላይ እንዲህ ሲሉ አነፃፅረዋል። ‹‹ይህንን የተገነዘቡት የቅንጅት መሪዎች የማታ ማታ ጥፋተኝነታችንን አምነን መንግስትን ይቅርታ መጠየቅ ነው የሚያዋጣን የሚል አቋም ላይ ደረሱ፡፡ እናም ከህግ የበላይነት ለማምለጥ ሞክሮ ሳይሳካለት ሲቀር የቤተክርስቲያን ደውል ውሎ ምህረት እንደሚጠይቅ ሽፍታ መንግስትን ይቅርታ ለመጠየቅ ከጀሉ።›› በዚህ አንቀፅ፤ በዚሁ ገጽ ላይ ደግሞ፣ በረከት ስምኦን ከዋነኞቹ የኢህአዴግ አለቆች አንዱ መሆናቸውን እረሱት መሰለኝ እንዲህ ሲሉ ቀለዱና ሳቅ በሳቅ አደረጉን። ‹‹በዚያም አለ በዚህ፣ የፍርድ ቀን ከመድረሱ ጥቂት ቀናት በፊት የቅንጅት መሪዎች ምህረት ሊጠይቁ ነው! የሚለው ወሬ በአገር ምድሩ ተናኘ።

 

እንደወሬው ከሆነ ነገ ሊበየንባቸው እንደ ትላንት ለጠ/ሚኒስትሩ የይቅርታ ደብዳቤያቸውን አስገብተው ነበር።›› እንግዲህ እግዜር ያሳያችሁ! የቅንጅት እስረኞች ይቅርታ መጠየቃቸውን በረከት ስምኦን የሰማሁት በወሬ ወሬ ነው ለማለት ‹‹እንደወሬው ከሆነ…›› ብለው ሲጀምሩ። ሆኖም በየዋህነት ይህንን እንዳናምን እንኳ ከዚህ የሚጣረስ ሌላ ነገር በሌላ ገጽ ላይ እናገኛለን። የቅንጅት ታሳሪዎች አንዳንዴ ሽማግሌዎችን እንደማያዳምጡ ከነገሩን በኋላ፤ ሽማግሌዎቹም በዚህ ተማረው ‹‹እንግዲህ እኛ ይቅርታ እንዲሰጣችሁ ባሳያችሁት ፍላጎት መሰረት ልናግዛችሁ ብንፈልግም፤ የእናንተ ነገር ግን ለእኛም ክብር የማያሳይ ሆኗልና ካልፈለጋችሁት በዚሁ ሊቀር ይችላል›› ማለታቸውን ተከትሎ፣የሽማግሌዎቹ ማምረር የታያቸው ኢንጂነር ግዛቸው በግላቸው ‹‹እባካችሁ እነዚህን ጉረኞች ሰምታችሁ የጀመራችሁትን የይቅርታ ሂደት እንዳታቋርጡብን››የሚል ደብዳቤ ፅፈው ከሽማግሌዎቹ መካከል በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ኪስ ውስጥ አስገቡ›› ሲሉ ውስጥ አወቅ ሆነው እናገኛቸዋለን።

 

በእርግጥ በመቅደሙ የተጠቀሱት የኢህአዴግ ዋና አመራሮች (መለስን ጨምሮ) መፅሐፉን ገምግመው አስተያየት የሰጡ በመሆኑ መጽሐፉ የኢህአዴግ አቋም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለነገሩ እንኳን የበረከት መፅሀፍ የሰለሞን ተካልኝም ዘፈን በኢህአዴግ ሳይመረመር አይለቀቅም። የሆነ ሆኖ የበረከት መጽሐፍ እርስ በእርሱ በሚጣረስ ታሪክ (ገጠመኝ) የተሞላ ነው፡፡ ለምሳሌ ገፅ 45 ላይ ያለውን ማነፃፀሪያ ብናየው ለዚህ አስረጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የ97ቱን ምርጫ ከፈረንሳዊው ደራሲ ቻርለስ ደክንስ “The tale of two cites” (የሁለትከተሞች ወግ) መጽሐፍ ጋር ማነፃፀራቸው ነው፡፡ ‹‹ወቅቱ ከመቼውም የተሻለ ነበር። ከወቅቶቹ ሁሉ የከፋውም ነበር። የብስለት ዘመን እንደነበረው ሁሉ የየዋህነት ዘመንም ነበር፡፡ መተማመን እንደሰፈነበት ሁሉ ተጠራጣሪነት ያየለበትም ነበር፡፡ ፍንትው ካለ ብርሃን ጎን ድቅድቅ ጨለማ ነበር፡፡ የተስፋ ፀደይ እንደሆነው ሁሉ፣ የጭንቅ ክረምትም ነበር። ሁሉም ነገር ከፊታችን፣ በኋላም ማዕዳችን ባዶ የሆነበት ወቅት ነበር፡፡ ሁላችንም ወደ ገነት እየተጓዝን እዚያው ሳለንም በሌላ አቅጣጫ እንተም ነበር፤ በአጭሩ ወቅቱ፣ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚናገሩ አዋቂዎችን እጅግ ከፍተኛ በሆነ ንፅፅር ተመልክተን በመልካምነቱም ይሁን በመጥፎነቱ ልንቀበለው ይገባናል እንደሚሉት እንደአሁኑ አይነት ወቅት ነበር›› የሚለውን አንቀፅ ጠቅሰውታል።

 

እንግዲህ የሪቻርድ ዲክንስ መጽሐፍ የሚያጠነጥነው በ1789ዓ.ም በተካሄደው የፈረንሳይ አብዮት ላይ ነው። ያ አብዮት አላማው ያደረገው ደግሞ የሉዊስ 16ኛ እና የባለቤታቸውን የማዳም አንቶኖቲ አምባገነን አገዛዝ መገርሰሱ ላይ ነው። ከታሪክ እንዳነበብነውም የፈረንሳይ ህዝብ ተርቦ አደባባይ በመውጣት ‹‹ዳቦ አጣን›› የሚል ተቃውሞ ሲያሰማ፣ ማዳም አንቶኖቲ ‹‹ህዝቡ ምንድነው የሚለው ብላ ስትጠይቅ ‹‹ዳቦ አጣን›› እያለ እንደሆነ ሲነገራት ‹‹ለምን ኬክ አይበሉም›› ስትል የመለሰች ደፋር እንደሆነች ነው። አናም ይሄ ዝነኛ አመፅ የተመራው በተላላቆቹ ፈላስፋዎች በMonesque፣ Rousseau፣ Voltair እና Diedrot ነው። አብዮቱም ግቡን መቶ ንጉሱ እና ንግስቲቱ የጊሎቲን ማሽን በሚባለው አንገት መቅሊያ በህዝብ የተባበረ ክንድ አንገታቸው ተቀልቷል።

 

እነሆ በረከት ስምኦን የተባሉ ስልጣን ላይ ከወጡ 20 ዓመት ያለፋቸው ሚኒስትር ደግሞ ‹‹በቃችሁ›› በሚል ህዝብ አምፆባቸው በጥይት ላከሸፉት አመፅ ትክክለኛነት ይህንን መጽሐፍ ጠቅሰው በድፍረት ፅፈዋል።

 

ቀሪውን የሳምንት ሰው ከሆንን ሳምንት እመለስበታለሁ።

 


ፍትሕ ጋዜጣ (አዲስ አበባ)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!