ሐዲስ ዓለማየሁ Haddis Alemayehuዳንኤል ክብረት
የዛሬ 600 ዓመት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የተባለ ኢትዮጵያዊ ደራሲ "አርጋኖን" የተሰኘ መጽሐፍ ይደርሳል። ይህንን መጽሐፍ የተመለከቱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም እጅግ ያደንቁና ለንጉሡ ለዐፄ ዳዊት ያቀርባሉ። ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም መጽሐፉን ተመልክተው በማድነቅ በወርቅ ቀለም እንዲጻፍ አዘዙ። አባ ጊዮርጊስንም ሸለሙ።

 

ከተወሰነ ጊዜ በኋላም አባ ጊዮርጊስ "መጽሐፈ ምሥጢር" የተባለ መጽሐፍ ደረሰ። ይህንን የተመለከቱ ሊቃውንትም አድናቆታቸውን "ቄርሎስና ዮሐንስ አፈወርቅ በሀገራችን ተገኙ፤ ኢትዮጵያም እንደ ሮምና ቁስጥንጥንያ፣ እንደ እስክንድርያም ሆነች" ብለው በማሸብሸብ ነበር የገለጡት።

ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላ ያለችው ኢትዮጵያ ግን ለደራሲዎቿ ቦታ የሌላት፣ ማንበብና መጻፍም ብርቅ የሆነባት፣ ድራፍት ቤት እንጂ መጻሕፍት ቤት፣ ጫት ቤት እንጂ የመጻሕፍት ማከፋፈያ ቤት የማይበረታታባት ሀገር ሆናለች። ክልል ያላት በክልል ደረጃ የሚጠቀስ ቤተ መጻሕፍት የሌላት፣ መንግሥት ያላት፣ ነገር ግን መንግሥት ዕውቅና የሚሰጠው ድርሰትና ደራሲ የሌላት ሀገር ሆናለች። ለጀማሪ አቀንቃኞች የሰጠችውን አይዶል እንኳን ያህል ለበካር ደራስያን ለመስጠት ያልፈቀደች ሀገር ሆናለች። ለአርተር ራምቦ እንጂ ለጸጋዬ ገብረ መድኅን ቦታ የሌላት ሀገር ሆናለች። ለፑሽኪን እንጂ ለሐዲስ ዓለማየሁ አደባባይ የሌላት ምድር ሆናለች። ደራሲዎቿ ሲኖሩ ሳይሆን ሲሞቱ ዜና የምትሠራ ሀገር ሆናች።

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መጽሐፈ ብርሃን በተሰኘው መጽሐፉ ላይ "እስመ ጽሙዐን ለትምህርት ብሔረ ኢትዮጵያ ኄራን - ምርጦቹ የኢትዮጵያ ሰዎች ትምህርትን የተጠሙ ናቸው" ይላል። በዚህ ጥማታቸውም የተነሣ ሕንድ ተሻግረው እነ መጽሐፈ በርለዓምን፣ ግሪክ ገብተው እነ ዜና እስክንድርን፣ አምጥተው ነበር። ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ እንኳን ወደ ሰሎሞን የሄደችው "ጥበብን ፍለጋ" መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ። እዚህች ሀገር ውስጥ ቆዳ ለጫማ ከመዋሉ በፊት ለመጽሐፍ ነበር የዋለው፤ ብርዕ ለማገዶ ከመዋሉ በፊት ለጽሕፈት ነበር የዋለው፤ ቀለም ለግድግዳ ከመዋሉ በፊት ለፊደል ነበር የዋለው።

"አልወለድም" የአቤ ጉበኛው መጽሐፍ Aleweledem by Abe Gubegnaበዚህች ሀገር ጥንታዊ ታሪክ መጻሕፍትን መጻፍ ብቻ ሳይሆን፤ ማንበብ፣ ማስነበብ፣ ማስጻፍ፣ ሲነበቡ መስማት ጭምር እጅግ የተከበረ ነገር ነበር። የተከበረ ብቻም ሳይሆን የቅድስናም ምንጭ ነበር። በየገድላቱና ድርሳናቱም "የጻፈ ያስጻፈ፣ ያነበበ የተረጎመ፣ የሰማ ያሰማ" የሚሉት ቃል ኪዳኖች መጻፍን ብቻ ሳይሆን የተጻፈውን ማንበብ፣ ማንበብ ለማይችሉትም ድምጽን ከፍ አድርጎ እያነበቡ ማሰማት፣ ሲነበብም በጽሞና መስማት ጭምር ዋጋ እንዲኖራቸው ያደረጉ ነበሩ። የደራስያኑ መጻሕፍት እንዳሁኑ በማተሚያ ማሽን በብዛት አይባዙም ነበርና ለጸሐፊዎች ከፍሎ ማስጻፍ፣ ዋጋ ተቀብሎ በሚገባ መጻፍ የሚያስመሰግን የሚያጸድቅም ነገር መሆኑን ኢትዮጵያውያን ያምኑ ነበር።

ለዚህም ነው በዚያ ሁሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ውስጥ አልፋ፣ አንዳንድ ጊዜም ሀገሪቱ ራስዋ ከጥፋት በተአምራት የተረፈችባቸውን ታሪኮች አስመዝግባ፣ ነገር ግን አያሌ የብራና መጻሕፍትን እስከ ዛሬ ድረስ ጠብቃ ለማቆየት የቻለችው። በመከራም ጊዜ ከከብቶቿና ከበጎቿ፣ ከእህሏና ከማሯ፣ ከወርቋና ከብሯ ይልቅ መጻሕፍቷን ለማቆየት ነበር ሩጫዋ። በገድለ ዜና ማርቆስ ላይ በ15ኛው መክዘ መጨረሻ ላይ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ጦርነት በመሸሽ የገዳሙ መነኮሳት ከሸዋ ወደ ደቡብ ጎንደር ሲሰደዱ ከአንድ ሺ የሚበልጡ መጻሕፍትን በሦስት ቦታ ዋሻ ውስጥ ደብቀው ማስቀመጣቸውን ይነግረናል።

ከበደ ሚካኤል Kebede Michaelየደራስያኑ የድርሰት ሥራ የተወደደ፣ ባለቤትነቱም የተከበረ በመሆኑ በቃል የሚፈስሰው ቅኔ እንኳን "የእገሌ ቅኔ; እየተባለ ይጠቀስ ነበር እንጂ የባለቤትነት መብቱን የሚያስከብርለት ሕግና ሕግ አስከባሪ አካል የለም ተብሎ አይደፈርም ነበር። በአንድ ወቅት ጎጃም ከመምህሩ የሰማውን ቅኔ ትግራይ ሄዶ እንደራሱ አድርጎ ሲቀኝ የተሰማ ተማሪ ቅኔውን ሲጨርስ "ቅኔያቸውስ ደረሰን፣ ለመሆኑ የኔታ ደኅና ናቸው?" የሚል ውርደት የገጠመው ለደራስያኑ የባለቤትነት መብት ጠበቃ የሆነ ማኅበረሰብ ስለነበረን ነው። የጎንደሩ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ለሸዋው ደብረ ብርሃን ሥላሴ 2000 መክሊት ወርቅ "ደብረ ብርሃን" የሚለውን ስም ለመጠቀም የከፈለውኮ ለባለቤትነት መብት ክብር የነበረው ሕዝብ ስለነበረን ነው።

ዛሬ ግን በዚህች ታሪካዊት ምድር፤ በዚህች ሥነ ጽሑፍ ተፈጥሮ፣ አድጎ፣ ዳብሮ፣ ሠልጥኖ ለወግ ለማዕረግ ደርሶባት በነበረች ሀገር፤ ደራስያንና ድርሰት የተረሱ ዕቃዎች ሆነዋል። እነርሱን የሚያበረታታ፣ የሚሸልም፣ ዕውቅና የሚሰጥ፣ ማዕረግ የሚሰጥ፣ በዝተውና መልተው ምድርን እንዲሞሏት የሚያደርግ ማኅበረሰብም፣ ተቋምም መንግሥትም አጥታለች።

በታደሉት ሀገሮች የዓመቱ ምርጥ ደራሲ፣ የዓመቱ ምርጥ መጽሐፍ፣ በዓመቱ በብዙ ቅጅ የተሸጠ መጽሐፍ እየተባለ ደራስያንንና ድርሰትን የሚያበረታታ፣ እንደ ጻፉበት ጉዳይም በየዘርፋቸው የሚሸልም ተቋምና መንግሥት አለ። በስማቸው መንገዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ አደባባዮችን፣ ፓርኮችን፣ ሙዝየሞችን የሚሰይም መንግሥትና ሕዝብ አላቸው። ሥራዎቻቸው ብቻ ሳይሆን የሠሩባቸው ቤቶችና የተጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች ሳይቀር የሀገሪቱ ታሪክና ቅርስ ሆነው ይጎበኛሉ።

ለመሆኑ የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ የብላታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ የአለቃ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ የአቤ ጉበኛ፣ የበዓሉ ግርማ፣ ቤታቸው የት ነው? የት ነበር የጻፉት? ረቂቃቸው አለን? የጻፉበት ብዕር አለን? ምን ሰየምንላቸው? በምን እናስታውሳቸዋለን? ለመሆኑ የኢትዮጵያን የድርሰት ጉዞ የሚያሳይ አንድ ሙዝየም እንኳን አለን? የሺ ዓመታት የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የምንደሰኩር ጀግኖች ሥነ ጽሑፋችን ከየት ተነሥቶ የት ደረሰ? የድርሰት ጉዟችን ከየት መጥቶ የት ጋ ደረሰ? የዕውቀት አባቶቻችንና እናቶቻችን እነማን ነበሩ? እስካሁን ምን ያህል ደራስያንን አፍርተናል? እነማን መቼ ተነሡ? እነማንስ ምን ሠሩ? የመጀመሪያው ገጣሚ፣ የመጀመሪያው የልቦለድ ደራሲ፣ የመጀመሪያው የወግ ጸሐፊ፣ የመጀመሪያው የቴአትር ደራሲ፣ የመጀመሪያው ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ደራሲ፣ የመጀመሪያው የጋዜጣ ጽሑፍ ጸሐፊ፣ የመጀመሪያው የፊልም ጽሑፍ ጸሐፊ፣ የመጀመሪያው የጉዞ ማስተዋሻ ጸሐፊ ማነው? ብንባል አንዳች ስምምነት አለን? የምናሳየውስ ነገር አለን? የትስ ነው መረጃው ያለው? ለተተኪው ትውልድስ የት ወስደን ነው የምናሳየው?

የሀገር የሥልጣኔ ሕዳሴ የሚጀምረው ከዕውቀትና ከኪነ ጥበብ ሕዳሴ ነው። የአውሮፓንም ሆነ የእስያን የሕዳሴ ታሪክ ብንመለከት ዕውቀት ያልመራው ኪነጥበብ ያላቀጣጠለው ሕዳሴ አናገኝም። የኢኮኖሚውንም፣ የባሕሉንም፣ የፖለቲካውንም ሕዳሴ ዕውቀት ሊመራ ኪነ ጥበብም ሊያቀጣጥለው ይገባዋል። ኪነ ጥበቡ ደግሞ ፖለቲካ መር፣ ብሔር መር፣ ገንዘብ መር ሳይሆነ ዕውቀት መር መሆን አለበት። ሕዳሴ የተሳካና የጸና እንዲሆን የዕውቀት አባቶችና እናቶች ያስፈልጉታል። የሚታወቁ ሳይሆን የሚያውቁ፣ የሚናገሩ ሳይሆን የሚነገርላቸው፣ "አለን አለን" የሚሉ ሳይሆን "አሉ አሉ" የሚባልላቸው የዕውቀት ምንጮች ያስፈልጋሉ።

ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን Tsegaye Gebermedhinእነዚህ የዕውቀት ምንጮች ዕውቀታቸውን እንደ ጉንፋን ማጋባት እንዲችሉ መጻፍ አለባቸው። ጊዜ ወስደው፣ ዐቅም ሰብስበው፣ መረጃ አስሰው፣ ሰርዘው ደልዘው፣ ቀምረው ሰድረው መጻፍ አለባቸው። የምንጠቅሰው፣ የምንመራበት፣ ብርሃን የምናይበት፣ ዓይነ ልቡናችንን የምናበራበት የዕውቀት ማዕድ ማዘጋጀት አለባቸው። ይኼ ደግሞ የደራሲው የጸሐፊው ድርሻ ብቻ አይደለም። የጥንት እናቶቻችንና አባቶቻችን ቀለም ገዝተው፣ ብራና አስፍቀው፣ ለጸሐፊው ድርጎ ሰጥተው፣ ርስት ከፍለው፣ ዋጋ ቆርጠው፣ ሲጨርስም ሸልመው ያስጽፉ እንደነበረው ሁሉ ደራስያኑን የሚያበረታታ፣ የድካማቸውን ዋጋ እንዲያገኙ የሚያደርግ፣ ለውጥ የሚያመጣ ዓይነተኛ ሥራ ሠርተው ሲገኙም የሚሸልም መንግሥትና ሕዝብ ያስፈልጋል። ከወረቀትና ከማተሚያ ዋጋ እስከ ሥራ ግብር፣ ከማከፋፈያ ችግር እስከ መብት ማስከበር፤ ከትምህርት ቤት የንባብ ባህል እስከ ሀገራዊ የጽሕፈትና የንባብ አብዮት፣ ከዓመታዊ ሽልማት እስከ የማዕረግ ስሞች፣ የሚሰጥ ተቋማዊ አሠራርና ባህል ያስፈልገናል። የሀገር ሥልጣኔ ከድርሰት ሥልጣኔ እንደሚጀምረው ሁሉ የሀገር ሞትም ከድርሰት ሞት ይጀምራልና።

ዳንኤል ክብረት
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!