"እኛና አብዮቱ" በሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስስሜነህ ታምራት (ስዊድን)
የቀድሞው ባለሥልጣን ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ "እኛና አብዮቱ" በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል። ይህንኑ መጽሐፍ መነሻ አድርገው፤ ወይም የቆየ የፖለቲካ መስመር ልዩነት አነሳስቷቸው ይሁን ብቻ አቶ ሰለሞን ገ/የስ በኢትዮ-ሚዲያ ድረ-ገጽ ላይ "የመጽሐፍ ግምገማ" በሚል ርዕስ የጻፉትን አንብቤ እንደጨረስኩ ሁለት ሀሳቦች መጡብኝ። 

አንደኛው ስለቀረበው ነጠላ ግምገማ (በግሌ ነው) ታሪኩን ከጅምሩ እስከፍጻሜው የሚያውቁት፣ በሂደቱም ዋና ተዋናኝ የነበሩት እራሳቸው የመጽሐፉ አዘጋጅ መልስ ይስጡበት የሚል ነው። ሌላኛው ደግሞ የለም ፀሐፊው ስለመጽሐፋቸው ወጥነት ባለውና በጥቅሉ ተጠያቂነት ቢኖርባቸውም፤ በአንዳንድ ነጠላ ጉዳይ ለሚቀርቡ ሁሉ መልስ መስጠት ግን የፀሐፊው ብቻ ሊሆን አይገባውም። ሁሉም አንባቢ (እድምተኛ) አስተያየት መስጠቱ ለሚዛናዊ ብይን ይረዳል የሚሉ ናቸው። የሁለተኛው መሰረተ ሃሳብ እኔም እንደ አንባቢ የሚሰማኝን አስተያየት እንድሰነዝር ገፋፍቶ አነሳሳኝ።

የአቶ ሰለሞንን የሦስት ገጽ ግምገማ በሁለት ገዢ ሃሳቦች አጠቃሎ መመልከት ይቻላል እነሱም፤
1. የመጽሐፉ አዘጋጅ (ፀሐፊ) ለሚያቀርቧቸው ክሶችና ሐቅ ተብየዎች ማስረጃ አይታይበትም ወይም የላቸውም
2. የእርሳቸውን ድርጅት (ኢሠፓን ለማለት ነው) አሳብጠው ሌሎቹን (ኢህአፓን ለማለት ነው) አለምንም ማስረጃ አሳንሰውና አጥቁረው አቅርበዋል የሚሉ ይሆናሉ።

እስቲ ከመጀመሪያ አስተያየታቸው (ግምገማቸው) ልነሳ። በደርግ ዘመን በጎም ሆኑ አፍራሽ ተግባራት ከደርጉ ሁለተኛ ሰው ከሻምበል ፍቅረሥላሴ የላቀ መረጃ ወይም ማስረጃ ማንን ማቅረብ ይችላሉ?

ወደኋላ ተመልሰን ያለፈ ታሪካችንን እናስታውሰው። እርስ በርሳችን የተላለቅንበትን ጠባሳ አሻራም እንመርምረው። ለዚያ ትውልድ እልቂት ምክንያቱ "የተማሩ ወገኖች የኔ አካሄድ ይቅደም ባይነት አልነበረም?" ለዛም ወደአንድ የሶሻሊዝም ጎዳና ለመጓዝ በወዝአደርና በላብ አደር አጠቃቀም የሰዎች አመለካከት እየተፈረጀ ብዙ ግፍ አልተፈጸመም? በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ትናንትና ባጨመላለቅነው የደም ታሪክ ዛሬ አንዱ ተነስቶ እኔ እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂው ይህ ክፍል ብቻ ነው በማለት የኋላቀርነት ድልድይን መሸጋገር ከቶውንም አይቻልም። ጺላጦስም እንኳን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጥፋት ባለማግኘቱና ስቅላቱንም ላለማረጋገጥ ያንን ተናገረ።

ገምጋሚውን እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ላቅርብላቸው፤ ኢህአፓ ያ ሁሉ ወጣት እንዲጨፈጨፍ መነሻ ምክንያት የሆነው ፍጹም የተሳሳተ የትግል አቅጣጫ ዛሬም አይጸጽተውም? ወይም በነጭ ሽብር እርምጃ የፈሰሰ ደምስ የወገኖቻችን አይደለምን? የትናንትናውን ቁስል በማንሳትና በመጣል ብቻ ይቅርታና ምህረትን፤ የጋራ ተጠያቂነትና አብሮነትን እስካላስቀደምን ድረስ ሀገራችን በእድገት ጎዳና ትራመዳለች ማለት ዘበት ነው። በአናቱም ግራ ቀኙን ቃኝቶ፤ ልማትና ጥፋትን መርምሮ፤ ጊዜ ቦታና ሁኔታን አገናዝቦ፤ ለምንና እንዴት? ብሎ ወደ ትክክለኛው አመለካከት መምጣት የሚገባውን ወጣት ትውልድም በጠማማ መንገድ መምራት ይሆናል። ዛሬም እንደትናንቱ በጭፍን እምነት (አመለካከት) የአንድ ጎራ አጨብጫቢ እንዲሆን ማዘጋጀት፤ ብሔራዊ ኃላፊነት የጎደለው የድርጅት ፍቅር ነው። በእውነት በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ኢህአፓ ገድሎ ከመሞት የዘለለ ለሀገር እድገት በቅርስነት ትቶልን ያለፈው ታሪክ ምንድነው? እንደ እውነትስ ከሆነ


• የሥርዓት ለውጥ ግለሰቦችን በማስወገድ ይፈጠራል ብሎ ባመነበት የጥፋት ጎዳና (ነጭ ሽብር) ሰውን በአደባባይ መረሸን የጀመረው ኢህአፓ አልነበረምን?
• ደርግን ጥሎ ሥልጣን ለመያዝ ብቻ፤ አገር በውጪ ጠላት በሶማሊያ ስትወረር፤ ወረራውን ለመከላከል የተሰለፈውን አገር ወዳድና የጦር አባላት "ከዚህ መከላከል በፊት ደርግን እንጣለው" በማለት በማናቸውም ሀገር ታሪክና ተሞክሮ ያልታየ አሳፋሪ ተግባር የሠራው ኢህአፓ አልነበረምን? ከዚህ የበለጠ ሀገርና ህዝብን የበደለ ማስረጃ ምን ይፈለጋል?
• የትግል ልምድ በሌላቸው የሲቪል ማኅበራት ውስጥ ሰርጎ በመግባት የራሱን የብቸኛ ጎዳና በማመቻቸት ሥልጣን መወጣጫ ለማድረግ ከፍተኛ ውስጣዊ ሴራና ደባ የፈጸመ ኢህአፓ አልነበረም?
• እንጭጭ የነበረውን ብሔራዊ ኢኮኖሚ ይበልጥ ለማንኮታኮት በማምረቻ ተቋማት ላይ የተወሰደው የውድመት ዘመቻስ አንድ ለሀገርና ለህዝብ ቆሜአለሁ ከሚል የፖለቲካ ድርጅት የሚጠበቅ ነበር?

ታዲያ ኢህአፓን አስመልክቶ ምኑ ላይ ነው ክሱ ሐሰት የሚሆነው? በምኑስ ነው ማስረጃ የታጣለት? ዛሬ እኛ የሚበጀን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ትናንት ለተፈጸሙ ብሔራዊ ጥፋቶችና ክሽፈቶች ትክክለኛ ባልሆኑ አካሄዶችና አፈጻጸሞች ኃላፊነቱንና ተጠያቂነቱን በድፍረት መቀበልና ካለፈው ትልቅ አስተምሮ መቅሰም ብቻ ነው።

ጥፋተኛነትን በድፍረት የመቀበል የሞራል ጥንካሬ ካለን፤ ይቅር ባይነትና አብሮነትን አዳብረን በሌላው ላይ የሰረጽነውን ጥላቻ በፍቅር ልናሸንፈው ይቻለናል። የመቻቻልና የአብሮነት ፀጋን ከተጎናጸፍን መፈቃቀርና ይቅር ባይነት ከራሳችን ታሪክ እንጂ የኒንሴን ማንዴላን ታሪክ ማገላበጥ አያስፈልገንም። ከዚህ በመቀጠል አቶ ሰለሞን ወደጠቀሱት ሁለተኛው ጉዳይ እወስዳችኋለሁ። በዚህ ላይ ገምጋሚው ወንድሜ ሻምበል ፍቅረሥላሴን የሚተቹባቸው መሰረተ ነጥብ "የራሳቸውን ድርጅት አሳብጠው ሌሎችን አለምንም ማስረጃ አሳንሰው አቅርባዋል" ይላሉ።

ማንኛውንም ድርጅት ሲቃኙ የድርጅቱን ጠንካራ ጎን ከደካማ ጎኑ፤ የውስጥ ፖሊሲውን ከውጪ ጉዳዩ፤ ውስጠ ደንቡን ከፓርቲው ውስጠ ዲሞክራሲያዊ ሕይወት ጋር ፈትቶና በታትኖ በዝርዝር በማየት፤ "ይህ ፓርቲ ይህን ይመስላል" ማለቱ ተገቢነት ያለው ይመስለኛል። ያም ቢሆን አቶ ሰለሞን ያላስተዋሉት አንድ አብይ ጉዳይ አለ። ይህም ሻምበል ፍቅረሥላሴ ከሚከተሉት ርዕዮተዓለምና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የማይጣጣም፤ አልፎ ተርፎም ከሳቸው ጋር ተሰልፈው በራሳቸው ነፃ አመለካከት ያመኑበትን ለመሥራት የተሰለፉ ጓዶቻቸውን በጠራራ ፀሐይ እያሳደደ ያጠቃቸውን የፖለቲካ ድርጅት (ኢህአፓን) ለዚህ መነሳሳቱ ትክክል ነበር ብለው እንዲመሰክሩላቸው የመጠበቃቸው ፋይዳ ነው። ይህን ከየዋህነት ተመልክተውት ከሆነ "ጨረቃ ዳቦ ጣይልኝ ማታ" አይነት ጨዋታ እንጂ ፖለቲካዊ እሳቦት ከቶውንም ሊሆን አይችልም።

ኢሠፓ በቀይና ነጭ ሽብር ጊዜ አልተመሰረተም ነበር። ቢሆን እንኳን ኢሠፓንና ኢህአፓን ሊያስማማ የሚችለው አንድ ነገር ነው። እሱም፤ ለተፈጸመው የትውልድ እልቂት የጋራ ተጠያቂነትን አምኖ መቀበል ብቻ ነው። አንዱ ጀመረው ሌላው ጨረሰው። አንዱ የነጭ ሽብር ዘመቻ አወጀ ሌላው ነጭ ሽብርን በቀይ ሽብር የሚል አፈጻጸም አወጣ። ለአንድ ነገር ውጤት መነሻ አለው፤ (Cause of effect) የሚሉት ነጮቹ። ደርግ በደርግነቱ ራሱ ተነሳስቶ በወሰዳቸው ርምጃዎች ብቻውን ሊጠየቅበት ይችላል። በወጣቱ እልቂት ግን ጥፋቱን ከኢህአፓ ጋር የሚጠየቅበት እንጂ የብቸኛ ተጠያቂ የሚሆንበት አንዳችም የታሪክ መነሻና መድረሻ አይገኝም።

ደግሞስ ስለኢህአፓ ታላቅነት ወይም ትክክለኛነት ጊዜ ቆጥሮ፤ ማስረጃ ተንትኖ ስለድርጅቱ መከራከርና ጥብቅና መቆም ያለበት ራሱ ኢህአፓ ነው? ወይስ የሻምበል ፍቅረሥላሴ መጽሐፍ? ገምጋሚው ሻምበል ፍቅረሥላሴ አሁንም አመለካከታቸውን አለወጡም ብለው ጠቁመዋል። እሳቸው ግለሰብ ናቸው። ባሁኑ ጊዜ ድርጅታቸው ፈርሷል። በድርጅት ደረጃ አሁንም አለሁ የሚለው ኢህአፓ እንኳን ከአርባ ዓመታት በኋላ አመለካከቱን ቀይሮ ለህዝብ ጥቅም ከህዝብ ጋር ለመታገል ራሱን አዘጋጅቷል ወይ? ተብለው ቢጠየቁ ማስረጃ የሚያጥራቸው ገምጋሚውን ራሳቸውን ይመስለኛል። ከዚህ አንጻር የኢህአፓ ጥንካሬ መለኪያ ደርግን ለመጣል መቻል አለመቻል ብቻ አይመስለኝም። ያማ ሳይሆን ቀርቶ የወደቀ ታሪክ ሆኗል።

ጥንካሬው የሚለካው ግን ከወደቀ ታሪክ ላይ ተነስቶ ለአወዳደቁ አንኳር አንኳር ምክንያቶቹ ምንድናቸው? አሁን ደግሞ ምን ብሔራዊ ድርሻ ይኑረኝ? ድርሻዬን ከነማን ጋር አብሮ በመሥራት ልወጣ? ... ጥያቄዎችን ወዘተ ማስተናገድና ተመልሶ በእግር የመቆም ጥረቱ ጎልቶ አለመውጣቱ ይመስለኛል። ይህን ለማድረግ ቆርጦ ሲነሳ ብቻ ነው በተናጠል የማይወድቀው (የማይመታው)። ይህንን ሲያደርግ ብቻ ነው የቀድሞው ኢህአፓ አባላት ሕይወታቸውን የሰዉለትን ዓላማ ዳር የሚያደርሰው። የነፃነት ሐውልትም የሚተክለው። አልያ የትናቱን መስዋዕትነት በማውሳትና በብቸኛ የትግል ጉዞ የብዙኀንን ጥቅም ማስከበር በጣም ይከብዳል። ለሀገር ጥቅም ያልዋለ መስዋዕትነት ደግሞ ሺ ጊዜ ሲዘከር ቢውል ውጤቱን መመዘን ያስቸግራል።

በተለይ ባለፉት አርባ ዓመታት በፖለቲካው ውዝግብ ውስጥ ያለፍን ክፍሎች ብዙ ነገሮች መልሰን መላልሰን ማየት ቢኖርብንም፤ በዋናነት ግን በራሳችን ላይ የተሃድሶ ዘመቻ እጅግ ያስፈልገናል። የራሳችን ባህሪና የራሳችን ድርጅት ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር አብሮና ተቻችሎ ባለመሥራቱ ለደረሰውና ለተከሰተው ችግር ሁሉ ተጠያቂ መሆናችን እንቢ ቢለንም መቀበል ግድ ይላል። ሀገራችንና ህዝባችን ላቅ ወዳለ የእድገት እርከን ላይ እንዲደርሱ የምንፈልግ ሁሉ የአመለካከት አድማሳችንን ከድርጅት ማዶ ካላሰፋነው ስንነታረክ ዘመናት ከማስቆተር በቀር ጠብ የሚልልን አንዳችም ፋይዳ አይኖርም።

"እኛና አብዮቱ" በሚለው የሻምበል ፍቅረሥላሴ መጽሐፍ ግምገማ (ምልከታ) በመጨረሽ ላይ አቶ ሰለሞን እንደግድፈት (ስህተት) አድርገው ያወሱት፤ ስለኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ብዙ አለመጠቀሱ ነበር። ርዕሱ እንደሚናገረው "እኛና አብዮቱ" ሲል የብዙኀኑን ሚና እና የ1966ቱን ማዕበል በሂደቱ ያለፈባቸውን ውጣውረዶች አጠቃሎና ብሔራዊ ይዘት በመስጠት የተዘጋጀ ይመስላል። በመሆኑም ትግሉ የግለሰብ ባህሪን፤ ተግባርን፤ ጭካኔንና ርህራሄን ወይም ብልህነትና ሞኝነትን፤ ቆራጥነትና ወላዋይነት ... ወዘተ ሳይሆን፤ ስለሀገርና ስለህዝብ ጉዳይ አተኩሯል። ኮ/ል መንግሥቱማ "ትግላችን" በተሰኘው በራሳቸው መጽሐፍ እና በገነት አየለ በተጻፉት ሁለት መጻሕፍት "የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች" የሚሉትን ብለዋል። ቀሪ አለኝ የሚሉትንም በሁለተኛው ሊመለሱበት ተናግረዋል። ለነገሩ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ስለኮ/ል መንግሥቱ፣ ሻለቃ ፍስሀ፣ ስለሻለቃ ብርሃኑ፣ ... ወዘተ ቢፃፃፉ ቢወዳደሱ ወይም እርስ በእርስ ቢወነጃጀሉ አሁን ምን ይፈይዳል? ጊዜው አልፏል (The time is over)። ደግሞስ አንድ ፀሐፊን ለምን ስለነእገሌ አልጻፍክም ማለት አግባብነት ያለው ተጠየቅ አይመስለኝም።

በመጨረሻም አንድ ማስታወሻ አለኝ። በብዙ ሀገሮች በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች ሥልጣን አልባ በሚሆኑበት ቀሪ የሕይወት ዘመን ህዝቡ እንዲያውቅ የሚፈልጉትን ጉዳይ እንደኑዛዜም እንበለው እንደንስኀ ወይም ለትውልድ ቅብብሎሽ ብቻ መጽሐፍ ጽፈው ለንባብ ያቀርባሉ። እያንዳንዱ ይህን የመሰለ ታሪክ እየተወ ማለፉ ለመጭው ትውልድ ሀገሩ ምን ምን ሁኔታን እንዴት እንዳሳለፈች ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ አጉሊ መነጽር ሆኖ ያገለግላል። ለዳበረ ታሪክ ለመጻፍና ለምርምር ተግባራትም የራሱ የሆነ ተዋፅኦ ይኖረዋል። በዚህ ረገድ ከሃያ ዓመት እስር በኋላ፤ በአስራ አንድ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ስለነበረው ሁኔታ ህዝብ ማወቅ አለበት ያሉትን በመጽሐፍ ለማቅረብ በመነሳሳታቸው የቀድሞው ጠ/ሚ/ር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ሊመሰገኑና የሞራል ጥንካሬአቸውም ሊወደስ ይገባል እላለሁ።

መቼም ከአዲስ መጻሕፍት ጋር አዲስ ግምገማም እንደዚሁ አብሮ ስለሚፈጠር ጤናማ አስተያየቶች ሌሎችም እንዲጽፉ ሲያበረታታ፤ አፍራሽ መልዕክት ያላቸው ደግሞ በአንጻሩ ሞራል ይነካሉ። እኔ በግሌ ስለመጽሐፍ ግምገማ ብዙ ዕውቀት የለኝም። እንደውም ትንሽም የለኝም። አንድ ነገር በትክክል አውቃለሁ። የመጽሐፍ ግምገማ ተጨባጭ ፋይዳ የሚኖረው የአንድ ግለሰብ፤ የአንድ ቡድን ወይም የአንድ መንግሥት ወገንተኛ ሳይሆኑ በነፃነት መገምገም ሲቻል ነው። ይኽን ማድረግ ሲቻል ሌላው ቢቀር ከአዕምሮ ተጠያቂነት ያድናል። እኔም ግላዊ አስተያየቴን በዚሁ እቋጫለሁ።

ስሜነህ ታምራት፣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!