The Hidden and Untold History of the Jewish People and Ethiopians by Fikre Tolossa

"ስውሩና ያልተነገረው የአይሁዳውያን እና የኢትዮጵያውያን ታሪክ" ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ

የመጽሐፍ ርዕስ፦ ስውሩና ያልተነገረው የአይሁዳውያን እና የኢትዮጵያውያን ታሪክ

ደራሲ፦ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ

አሳታሚ፦ ንባዳን ኃ.የተ.የግል ማኅበር (Nebadan plc)

የገጽ ብዛት፦ 234 (ከአባሪዎችና ምስሎች ጋር)

ዳሰሳ አቅራቢ፦ ሚኪያስ ጥ.

ሰውዬው በትምህርቱና በሥነ-ጽሁፉ ዓለም ከከረሙ፣ ዘመን አልፏቸዋል። ኢትዮጵያ እያሉ ካሳተሟት፣ “ወለላ” ከተሰኘች የአጫጭር ልቦለዶች መድበል አንስቶ እስከዛሬ እስከጻፏቸው ታሪክ-ቀመስና ልቦለዳዊ ሥራዎቻቸው ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አትርፈዋል። በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሊንኮልን (university of Lincoln) በመምህርነት እየሠሩ ይገኛሉ፤ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ።

የፕ/ሩ ስም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጉልህ ይነሳል፤ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” መጽሐፋቸው፣ የበርካታ ውይይቶች ማዕከል ሆኖ ሰንብቷል። ጉዳዩን ወረድ ብለን የምናነሳው ይሆናል። በቅርቡ ያሳተሙት “ስውሩና ያልተነገረው የአይሁዳውያን እና የኢትዮጵያውያን ታሪክ” ከቀደመው መጽሐፋቸው በጭብጥ ይለያል። በአብዛኛው የሚተርከው ኢትዮጵያውያን ከአይሁዶች ጋር ስላላቸው ስር የሰደደ ትስስሮሽ ነው።

ደራሲው የመጽሐፉ መታሰቢያነት የሰጡት “ብርቅዬና ጥንታዊ ታሪካችንን መዝግበው ላቆዩ ባለውለታዎቻችን” ነው። ከስሞቹ መካከል የመሪራስ አማን በላይ ስም ተጠቅሷል። ፕ/ሩ ለዚህ መጽሐፍ እንደግብዓትነት የተጠቀሙት የመሪራስ አማን በላይን ሥራዎችን፣ መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች የታሪክ መጻሕፍትን ነው። ሁለቱ መጻሕፍት፣ “ዣንሸዋ”ና “ያሻር” በጥንት ዘመን ከመጽሐፍ ቅዱስ በፊት የነበሩ ናቸው፤ (ገጽ 29)። እነዚህ መጻሕፍት ያለፈውን ዘመን ታሪክና የኢትዮ-አይሁድ ትስስሮሽን ለማሳየት፣ ፕ/ሩ በእጅጉ ተጠቅመውባቸዋል። መጻሕፍቱ “ሱባ” በሚባል፣ በቅድመ-መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ በነበረ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው። የሱባ ቋንቋ ነባር መሆኑን ለማሳየት በዚህ መጽሐፋቸው የምስል ማስረጃ አካትተው ቀርበዋል፤ (ገጽ 32ና 33 ላይ)። ፊደላቱ ለላቲን ፊደል መነሻ በመሆን አገልግለዋል። (ገጽ 31)

ግራ ሲያጋባን ለኖረው፣ ኢትዮጵያ የሚለው ስም “ከየት መጣ?” ለሚለው ጥያቄ፣ ፕ/ር ፍቅሬ “ኢትዮጵያ ማለት ቢጫ ወርቅ (ለእግዚአብሔር) ማለት ነው።” (ገጽ 222) የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ለ'ኔ፣ ትክክለኛው ቃለ-ብያኔ የፕ/ር ፍቅሬ ቃለ-ብያኔ ነው።

ስለዮዲት ጉዲት (አስቴር) “ሊታመን የማይችል” አዲስ ታሪክ፣ ፕ/ር ፍቅሬ ይዘው ከተፍ ብለዋል። ዮዲት ጉዲትን ሲገልጿት፣ “እንደባለውለታ” አድርገው ነው። ለዓመታት “የተጋትነው” የዮዲት አውዳሚነት ትርክትን የሚገለብጥ መረጃ ያገኘን ይመስለኛል። ይህቺ ሴት ለግዕዝ ቋንቋ “ባለውለታ ናት” ይሏታል። እንዴት “ባለውለታ” እንደሆነች በዝርዝር እንመልከት።

አንድ ጊዜ ዮዲት የእንቁዮጳግዮን ወታደር ለመሆን ትበቃለች። በወታደርነት ለመሥራት የተነሳችበት ሰበብ፣ አይሁዳውያን ወገኖቿ “ህዝበናኝ” በተባለ የአክሱም ንጉሥ የደረሰባቸው ግፍ ነበር፤ (ገጽ 139ና 140)። በሌላ በኩል፣ “መራሪ (መሪ)” የሚባል የአዜብ (አዘቦ) ንጉሥ፣ እንቁዮጳግዮን የተባለች ልጅ ነበረችው። ትንቢት ተናጋሪዎች “ንጉሥ ያልሆነ ባል ታገባና የቆየውን ያ’ንተን ሥርዓት የሚለውጥ ልጅ ትወልዳለች።” ብለው ለመራሪ ስለነገሩት፣ ልጁ ከማንም ወንድ ጋር እንዳትገናኝ ይከለክላታል፤ (ገጽ 140፣ 141)። ንጉሥዬው ወደ አክሱም በሄደ ሰሞን፣ ሰለሞን የሚባል ከሌዊ ወገን የሆነ አናጢ ያገኝና ወደእልፍኙ ያመጣዋል። እንቁዮጳግዮን ወዲውኑ በፍቅር ትከንፋለች። ንጉሡ ይህንን ሲያውቁ፣ ሰለሞንን የግንድ ቀፎ ውስጥ ከምግብ ጋር ከትቶ በአትባራ (በኋላ በንጉሡ ትካዜ ምክንያት ተከዜ) በተባለው ወንዝ ውስጥ ጨመረው፤ (ገጽ141)። ወደ አክሱም ልኮት “ይሆናል” ብላ ወደ አክሱም ተራ ሴት መስላ ሄዳ ስትፈልግ፣ አንድ እሱን የሚመስል ሰው አየች። ሰለሞን መስሏት ተጠመጠመችበት። እሱም “ንጉሴ ነኝ፤ ወንደሙ ነኝ። ሰለሞን ሳይሰናበተን እንደወጣ ከቀረ ዓመታት አልፈዋል፣ የት እንዳለ እንጃ!” አላት። ንጉሴን ይዛ ወደ ቤተ-መንግሥት መጣች። አንዴ አባቷ ፈርቷልና “ጀግንነቱን ለማረጋገጥ” በሚል ሰበብ ጦር ሜዳ ልኮ ያስገድለዋል፤ (ገጽ142)። የዮዲት ወታደር መሆን የሚጀምረው እንቁዮጳግዮን ህዝበናኝን አንቃ ከገደለች በኋላ ነው።

ዮዲት የነበራት ጥንካሬና ተዋጊነት፣ በሌሎች ዘንድ አስፈሪ እንድትሆን አድርጓታል። እንቁዮጳግዮንና ዮዲት በዝምድናም ተሳስረዋል፤ የእንቁዮጳዮግዮን ልጅ መራ ተክለሃይማኖትን ዮዲት አግብታለችና። (ገጽ 146-147)

የግዕዝን ቋንቋ ከዐረባዊ ድምሰሳ የታደገችው፣ የዐረብ “ብክለት” ያጋጠማቸውን ቤተ-ክርስቲያናትን በማቃጠል፣ ዐረብ ጳጳሳትን አስሮ “በመግደል”ና ከአጋዝዕያን ጋር የተነካኩና የግዕዝ ቋንቋን መለያ ያደረጉ ቤተ-ክርስቲያናት እንዲቋቋሙ በማድረግ ሲሆን፣ ድርጊቷ በእስክንድሪያና በሮማ ጳጳሳት አስወግዟታል።

እስከዛሬ የምንሰማው ስም “ማጥፋት” ከንቱ እንደነበርና እንደሆነ፣ ፕ/ር ፍቅሬ በጥናትና ምርምር አስደግፈው አቅርበውልናል። አዕምሯችን ላይ ስር የሰደደን ታሪክ፣ በአንድ አዳር ነቅሎ መጣል ከባድ ነው። አዲሱን ታሪክ ያኛውን ለመሞገት ብንጠቀምበት ጥሩ ይመስለኛል። “እሳቶ፣ ዮዲት ጉዲት” እያልን የምንጠራት ሴት፣ ምን ያህል ለግዕዝ ቋንቋ “ባለውለታ” እንደሆነች እንረዳለን - ከመጽሐፉ።

ሌላው፣ ለኔ አዲስ የሆነብኝ፣ የንግሥተ-ሳባ (ኢትያኤል) ታሪክ ነው። ብዙ ጸሐፍት፣ “የንግሥተ-ሳባ ታሪክ ተረት-ተረት ነው።” በማለት ይናገራሉ - ይጽፋሉ። ፕ/ር ፍቅሬ ይህንን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከላይ ከተጠቀሱት (“ያሻር”ና “ዣንሸዋ”) አጣቅሰው፣ እውነተኝነቱን አረጋግጠውልናል። ንግሥተ-ሳባ ወደሰለሞን ስትሄድ፣ ሁለት ሴቶችን አስከትላ ነው፤ እንዷ የግል ዘመዷ የሆነችው ሳሆይ የተባለች የአገው፣ የራያና ቆቦ ንግሥት ስትሆን፣ ሌላኛዋ ደግሞ ቢልቂስ፣ አዜብ ከምትባል ኢትዮጵያዊትና በወቅቱ የየመን (በዛን ጊዜ የመን ናግራን ትባል ነበር) ንጉሥ ከነበረ ሰው በየመን የተወለደች ልዕልት ነበረች። (ገጽ 109)

ከሦስቱ፣ ሁለቱ ሴቶች ከሰለሞን ጸንሰዋል። ንግሥት ሳሆይ “ዜጋዬ”፣ ንግሥተ-ሳባ (ኢትያኤል) “ምኒልክ”ን ወልደዋል። በአፈ-ታሪክ ደረጃ የሚወራውን በእውነተኛ ሰነዶች አማካይነት አረጋገጥን ማለት ነው።

የኢትያኤል (ሳባ) እናት “እስያኤል” በተባለ ዲበ-ሰብ ንጉሥ ተገድላለች፤ ምክንያቱም ከሌላ የንጉሥ አገልጋይ ጋር ፍትወተ-ስጋ ስትፈጽም ተገኝታ። ኢትያኤል (ንግሥተ-ሳባ) የነገሠችው “እስያኤል”ን በመግደል ነበር። እንደአጋጣሚ ሆኖ ማንነቷን ደብቃ ንጉሡን ስታገለግል ቆይታ፣ ጊዜና ቦታ ሲመቻችላት ትገድለዋለች። በኋላም፣ ንስሃ ለመግባት ጸሎት ስታደርስ፣ እግዚአብሔር ተገልጦ፣ በደለኛ እንዳልሆነች ይነግራታል። ንግሥተ-ሳባም ከጸጸት ትድናለች ማለት ነው። (ገጽ 103፣ 104)

በስሙ አህጉር ስለተሰየመለት-ስለንጉሥ “እስያኤል” እናንሳ! እስያኤል ዲበ-ሰብ የሆነ ንጉሥ ነበር፤ 150 ከሚደርሱ አንበሳዎች ጋር የተፋለመና በቅሎን ለመጀመሪያ ጊዜ በ genetic engineering ያስገኘም ንጉሥ ነበር። እርጅናን የሚከላከልበት መንገድ (mechanism) የነበረው ንጉሥ እንደእርሱ ያለ አይመስለኝም። ለ480 ዓመታት ኖሮ፣ ከዚህ በኋላ መክረም ስለሰለቸው፣ እግዚአብሔርን እንዲገድለው ተማጸነ። ኢትያኤልን ጌታ አሳሰበና አስገደለው። (ገጽ 98፣ 99ና 102)

ወደመጀመሪያ አካባቢ ስለኢትዮጵያ አሰያየም ስናወራ፣ አብረን ያላነሳነው ነገር አለ፤ ስለኢትዮጵና መልከጸዲቅ!

ኢትዮጵ የመልከጸዲቅ ልጅ ሲሆን፣ የሁላችንም “የዘር ግንድ” ነው። መጀመሪያ ላይ ስሙ “ኢትኤል” ነበር። በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደኢትዮጵያ አምርቶ፣ ኢትዮጵያ ላይ ነግሦ፣ 10 ወንድ ልጆችን ወልዶ፣ እነርሱ ተባዝተው፣ በ4000 ዓመታት ውስጥ አሁን በስሙ ለሚጠሩት ወደ100 ሚሊየን ለሚጠጉት ኢትዮጵያውያን አባት ሆነ ማለት ነው። (ገጽ 41)

ስሙ ከ“ኢትኤል” ወደ “ኢትዮጵ” የተቀየረው በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነበር። እግዚአብሔር “ጣና ሃይቅ ስትደርስ ‹ዮጵ› በሚባል ቢጫ ወርቅ ትከብራለህ። ‹ኤል› የሚለውን ቃል ከስምህ አውጥተህ፣ ‹ኢት› የሚለውን ከፊለ-ስምህን አስቀርተህ መጠሪያህን ‹ኢትዮጵ› ታደርጋለህ።” አለው፤ (ገጽ 41ና 42)። ከደረሰ በኋላ ነው - ያረፈባት አገር “ኢትዮጵያ” የተባለችው።

በግርድፉ ለማየት እንደሞከርነው፣ መጽሐፉ ስለኢትዮ-አይሁድ ትስስርና ከዚህ በፊት በስህተት ስናነሳው የነበረውን ታሪክ ለማጥራትና ለማስተካከል የሞከረ ነው። ጥቂት የአርትዖትና የዐረፍተ ነገር አሰካክ ግድፈት ቢታይም፣ ግድፈቱ ግን የመጽሐፉን ድንቅ የትረካ ፍሰት አላደናቀፈም።

የቀዳማዊ ምኒልክ ከታቦተ-ጽዮኑ ጋር 40,000 አይሁዳውያንን ማምጣቱን፣ ከዚህ በፊት ሰምተን አናውቅም።

በአጠቃላይ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ለኢትዮጵያዊነት ከባለፈው መጽሐፋቸው በበለጠ ሁኔታ፣ በዚህ መጽሐፍ ተቆርቋሪነታቸውን አሳይተዋል፤ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን ተጠቅመዋል። የእስራኤል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ዮኤል ኤደልስቲን መጽሐፉን አንብበው፣ “… ስላለፈው ዘመን የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ በኢትዮጵያዊ ዕይታ ላከናወኑት ጥናታዊ ሥራ አድናቆቴን ልግለጽልዎ እወዳለሁ።” በማለት፣ አድናቆታቸውን ለግሰዋል፤ (ገጽ 6)። ይህ “ብዙ” የተባለለት መጽሐፍ፣ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የሚጨምረው አንዳች ነገር እንደሚኖር አምናለሁ፤ ከኢትዮጵያዊያን ባሻገር፣ እስራኤላውያን በእብራይስጥ ተተርጉሞ ቢያነቡት (በቅርቡ መጽሐፉ ተተርጉሟል)፣ የበለጠ አዕምሯቸውን እንደሚያሰፉበትም አምናለሁ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ