“የቃሊቲ ምስጢሮች” ወሰንሰገድ ገብረኪዳን, Yekaliti Mistroch by Wosenseged Gebrekidanተስፋዬ ገብረአብ

ስለ ሁሴን ታሪክ ያወቅሁት፣ “የቃሊቲ ምስጢሮች” በሚል ርእስ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን በቅርቡ ያሳተመውን መጽሐፍ ሳነብ ነው። ወሰንሰገድ ዝዋይ እስር ቤት እንደገባ ነበር ከሁሴን ጋር የተዋወቁት። እንዲህ አወጉ፣

“የስንት አመት ፍርደኛ ነህ?” ሲል ጠየቀኝ።

“አይ ቀላል ነው። ሌላ ክስ ግን አለብኝ” አልኩት።

 

“ዋናው ጤና ነው። ይኸው እኔ 14 አመት እስርቤት ኖሬያለሁ” አለኝ።

 

“ምን!?”

 

በፍፁም ላምነው አልቻልኩም። አይኔን ተጠራጠርኩ። ገና ወጣት ነው። በእኔ እይታ እድሜው ከ30 ወይም ከ35 አይበልጥም። ሰውነቱ ደልደል አለ ወጠምሻ ነው። ምናልባት እያሾፈ ወይም እኔን እያፅናና መሰለኝ።

 

“ግን አትመስልም”

 

“አዎ አልመስልም። እኔም ራሴ ካለፈ በሁዋላ መለስ ብዬ ስመለከተው ነው እንጂ፣ ይህን ያህል ጊዜ ያሳለፍኩ አይመስለኝም። ሆኖም 14 የመከራ አመታት እዚህ እስር ቤት አሳልፌያለሁ።” አለኝ አይኑን ቡዝዝ አድርጎ።

 

“በነፍስ ገብተህ ነው?” በተራዬ ጠየቅሁት። (በግድያ ለማለት ነበር)

 

“አይደለም። በሌላ ጉዳይ ነው።”

 

እና ሁሴን ታሪኩን ለወሰንሰገድ አጫወተው።

 

ሁሴን የኦነግ ተዋጊ ወታደር ነበር። በ1984 በቁጥጥር ስር ከዋለ በሁዋላ 20 አመት እስር ፈረዱበት። ሁሴን እንዲህ አለው ለወሰንሰገድ፣

 

“… አመክሮዬ ሲታሰብ የምፈታበት ቀን አልፎአል። እስካሁን መፈታት ነበረብኝ። ‘የፍርድ ቤት ፋይል ቁጥር ጠፍቷል’ ተብዬ ነው የቆየሁት።”

 

“ጉዳይ አስፈፃሚው ከኮምዩተር ላይ አያይልህም?” ስል ጠየቅሁት።

 

“በፍርድ ቤት የኮምፕዩተር አሰራር የተጀመረው አሁን ነው። ያኔ ኮምፕዩተር አልነበረም።”

 

“ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጓደኛ … ጉዳይህን ፍርድ ቤት ሄዶ የሚከታተልልህ የለም?”

 

“የ14 አመት ልጅ ሆኜ ነው ተይዤ የታሰርኩትና የተፈረደብኝ። የእናትና የአባቴ ብቸኛ ልጅ ነኝ። ስለያቸው ራሱ አርጅተው ነበር። በህይወት ይኑሩ አይኑሩ አላውቅም። 14 አመታት ሙሉ እስረኞች በዘመዶቻቸው ሲጠየቁ እኔ አንድም ጠያቂ አልነበረኝም…”

 

ጋዜጠኛው ወሰንሰገድ ስለ ሁሴን በሁለት አረፍተነገር ይደመድማል።

 

“እስከዚያች ቀን ድረስ በብዙ ነገር አዝኜ ይሆናል። በሁሴን ህይወት የተሰማኝ ሃዘን ግን ይህ ነው ተብሎ ለመግለፅ አይቻልም!”

 

እነሆ! እኔም ተክዤያለሁ። ሁሴን በኦነግነት ተይዞ የታሰረው ሌንጮ ለታ እና ዲማ ነገዎ የኦነግ አመራር በነበሩበት ወቅት ነው። ልክ እንደ ሁሴን በአስርሺህዎች ከወያኔ ማጎሪያ ተወርውረዋል። የት እንደደረሱና ያሉበት የማይታወቅ የተረሱ እስረኞች ቁጥር ዳርቻ የለውም። ይህን እያሰብኩ የወሰንሰገድን መጽሐፍ አጥፌ ክፉኛ ተከዝኩ።


ተስፋዬ ገብረአብ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!