የመጽሐፍ ምረቃ

ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ

የመጽሐፉ ርዕስ፦ ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ

የኢትዮጵያ ባለውለታና ታዋቂው አትሌት አበበ ቢቂላ አሠልጣኝ ስለነበሩት ኦኒ ኒስካነን የተጻፈው መጽሐፍ ምረቃ ላይ ከጓደኞችዎ፣ ከወዳጆችዎና ከቤተሰብዎ ጋር ይገኙ ዘንድ ተጋብዘዋል!

ደራሲ፦ ሰለሞን ሐለፎም

ቀን፦ 14 April 2018

ሰዓት፦ 11:00 - 16:00

ቦታ፦ Bredängsskolan

Bredängstorget 21, 127 32 Skärholmen

መርኀ ግብር፦ (ሰዓት አቆጣጠሩ በአውሮጳውያን ነው)

11:00 ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ተሰብሳቢዎች በአዳራሹ ይገኛሉ

11:30 የመጽሐፉ ደራሲ ሰለሞን ሐለፎም ንግግር ያደርጋሉ

12:30 ተጨማሪ ተናጋሪዎች

- ኡልፍ ኒስካነን (የኦኒን ኒስካነን የወንድም ልጅ)

- ዶ/ር ቢንያም ወንድሙ (የስዊድንና የኢትዮጵያ ማኅበር ሊቀመንበር)

13:30 የፎቶና የሻይ ጊዜ

16:00 የዝግጅቱ ፍጻሜ

ኦኒን አፍሪካዊ አጎቴ ነበር የምለው። ሕጻናትን በጣም ይወድ ነበር። አስማት ይችላል። … በተለይ የማልረሳው ማታ ማታ እምተኛበት አልጋ ግርጌ ቁጭ ብሎ በአፍሪካ ስላከናወናቸው ጀብዱዎች የሚተርክልኝን ነበር። ለአንበሳ አደን ከጓደኛው ጋር ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በሄደበት ጊዜ በለስ ሳይቀናቸው ቀርቶ እንቅልፍ ሸለብ እንዳደረጋቸው አንዲት እንስት አንበሳ ከየት መጣች ሳትባል እድንኳኑ በር ላይ ተገትራ እንዳያት የነገረኝን አስደንጋጭ ገጠመኞቹንና ሌሎቹንም እስከዛሬ ድረስ አስታውሳቸዋለሁ። ኡልፍ ኒስካነን
ኦኒ በፊንላንድኛ መልካም ዕድል ማለት ነው። … ስምን መልአክ ያወጣዋል እንዲሉ እሱም ዕድለኛ ነበር ማለት ይቻላል።በዓለም ላይ ብዙ ቦታዎችን ጎብኝቷል። የልጅነትና የወጣትነት አፍላ ጊዜውን ያሳለፈበት ሶልና እና ለሁለት ዓመት ኮንትራት ሄዶ የዕድሜውን እኩሌታ ያህል የኖረባት አዲስ አበባ ግን በኦኒ ልብ ውስጥ እጅግ ላቅ ያለ ስፍራ ነበራቸው። ማሪያነ ሳውተር ሚስተር

አበበ በዚያ ምሽት ሀውልቱን ቀና ብሎ ሲመለከት ደሙ ፈላ። ሀውልቱ በጨለማው መሃል እንደጆቢራ ተገትሯል። ቆፍጣናው ወታደር በግፍ የተጨፈጨፉት ወገኞቹ ታሰቡት። በባዶ እግራቸው እስከ መጨረሻው እስትንፋስ ድረስ ለተዋጉት የኢትዮጵያ አርበኞች ደም መላሽ ሆኖ ፋሽስቱን የጣሊያን መንግሥት ሊበቀለው ቆረጠ። ትንፋሹን አሰባስቦ ፍጥነቱን ጨመረ። እስካሁን ድረስ ከጎኑ እየተከታተለ አላፈናፍን ያለውን ሞገደኛውን የሞሮኮውን ራህዲ ትቶት ወደፊት ሸመጠጠ። መዳረሻው ላይ ጣሊያን ሰራሹ ድንጋያማው ኦሎምፒያድ ስታዲዮም ባልደፈርም ባይነት እየራደ ነው። አበበና የኮንስታንቲን ቅያስ ፊት ለፊት ተፋጠጡ። የኢትዮጵያን ሕዝብ አደራ ያነገበው ጥቁሩ አፍሪካዊ ከፊት ለፊቱ ተገትሮ የሚርደውን ግምብ ድጋሚ በዓለም ፊት ለማዋረድ ፍጥነቱን ጨምሮ በቁርጠኝነት ወደፊት ተፈተለከ።

የመጨረሻውን ክር ሲበጥስ የድካም ስሜት ፈጽሞ አልታየበትም። ሁለት ሰአት ከአስራ አምስት ደቂቃ ከአስራ ስድስት ሴኮንድ። አኩሪ ሰዓት። እየተቅበጠበጠ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረው አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን በሰዎች መሃል እየተሽሎከሎከ መጥቶ አበበ አንገት ላይ ተጠመጠመ። ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ በአንገቱ ላይ አጠለቀ። ያገሩ ልጅ አበበ ዋቅጅራም በጣም ብዙ ታዋቂ አትሌቶችን ቀድሞ በሁለት ሰአት ከሃያ አንድ ደቂቃ ሰባተኛ ሆነ። ጉሮ ወሸባዬ! ድል ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ሆነ።ነጭ አምላኪው አለም ተገረመ፤ አፈረም። ኢትዮጵያና አፍሪካ ግን አንገታቸውን ቀና አድርገው በልጃቸው ኮሩ። አንዳንድ የጣሊያን ጋዜጦችም “ኢትዮጵያን ለመውረር ድፍን የጣሊያን ሠራዊት ዘመተ። ጣሊያን ግን በአንድ ቁርጠኛ የኢትዮጵያ ወታደር ተወረረች” በማለት በበነገታው በፊት ገጾቻቸው ላይ ጻፉ።

(ከመጽሐፉ የተወሰደ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ