ገ/ኢ. ጐርፉ

The meaning of the name Ethiopia

“ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ትርጉሙንና አመጣጡን ለመመርመር በ፲፱፻፹፩ (1987 እ.ኤ.አ.) በወጣው ሰምና ወርቅ በተባለው የምርምር መጽሔት ፪ኛ ዓመት፣ ቁጥር ፬ አጥር ያለ ጽሑፍ አቅርበን፣ አንዳንድ ምሁራን፤ “ኢትዮጵያ ማለት ከግሪክ ቋንቋ የመጣ ቃል፣ ‘ፊቱ በፀሓይ የተቃጠለ፣ የተጠበሰ፣ ያረረ’ ማለት ነው ...” የሚሉት ትክክል እንዳልሆነ ለማሳየት፤ ናይጀርያ የሚባል አገርና፣ (Nigeria) ኒጀር (Niger) የሚባሉ አገርና ወንዝ በአፍሪካ እንዳሉ ጠቅሰን፣ ኔግራ፣ ኔግሮ፣ ኒገር፣ ኔግሪትዩድ (Negra, Negro, Nigger, Negritude) ለሚሏቸው ቃላት ወደ ላቲን/እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመግባት ምክንያት ሆኑ እንጂ፣ ከላቲን ቋንቋ ተወስዶ ለአፍሪካ አገሮችና ወንዝ የተሰጠ ስም አይደለም በማለት፣ ኢትዮጵያ የሚለውም ቃል እንዲሁ ጥንታዊ ምንጩ ከግሪክ ሳይሆን ከአገራችን የወጣ ቃል መሆኑን ለመግለጽ ሞክረን ነበር።

አንድ-አንድ ቃላትን ስንመረምር በውስጣቸው የተደበቅ ምስጢር እናገኛለን። የተደበቀውን ምስጠር ለማግኘት ጥልቅ የታሪክና የቃላት ምርምርና ጥናት (Philology / Etimology) ማድረግ ያስፈልጋል። በብዙ ምርምርና ጥናትም ምስጢሩ የሚገለጥበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ በግዕዝ፣ በትግርኛና፣ አማርኛ ‘አነ’፣ ‘እኔ’ የሚሉ ቃላት ስናገኝ፣ በላቲን/በእንግሊዝኛ ደግሞ ‘አይ’ (I - እንግሊዝኛ)፣ ‘ኢዮ’ (Io -ጣልያንኛ) አሏቸው። በግዕዝ፣ ትግርኛና፣ አማርኛ ‘ዓይን’ ‘ዓይኒ’ ለሚሉ ቃላት ደግሞ፣ በእንግሊዝኛ አይ (eye) እናገኛለን። በአማርኛና ትግርኛ፤ ‘ያለቀለት ጉዳይ’ ለማለት ‘ሙት፣ የሞተ ነገር’፣ ስንል በእንግሊዝኛ ‘ሙት ኢሹ’ (moot issue) ይላሉ። በግዕዝና፣ ትግርኛ፣ ‘መርዓ’ ስንል፣ በእንግሊዝኛ (marriage) ‘መረጅ’ ይላሉ። ፈርኦን (Pharaoh) ከሚባል ጥንታዊ የግብፅ ንጉሥም ወደ ግዕዝ፣ ትግርኛና አማርኛ፣ እንዲሁም ወደ እንግሊዝኛ ቃላት፤ ‘ፈሪሃ’ ‘ፍርሓት’ ‘fear’ (ፊር) ለሚሏቸው ቃላት ምንጭ የሆነ ይመስላል። ንጉሡ ታላቅና የሚፈራ የነበረ ነው የሚመስል። እነዚህን ለምሳሌ አቀረብን እንጂ እንደዚህ ብዙ የቃላት መቀራረብ እናገኛለን። “ማን ከማን ወሰደ? ታሪካዊ አመጣጡና አወራረዱስ እንዴት ነው?” የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ነው የቃላት ጥናትና ምርምር የሚያስፈልግ።

አንድ-አንድ ቃላትም ከቋንቋችን ፈልቀው ይወጡና ዓለምን ዞረው ተመልሰው ሲመጡ ብርቅ አድርገን እንቀበላቸዋለን። ለምሳሌ በኃይለሥላሴ ዘመን ያኔ ልዕልት ፀሓይ ሲባል ከነበረው ሆስፒታል ጎን አዲስ የሕንፃ ኮሌጅ ተከፍቶ፣ ‘የመሃንድስ ኮሌጅ’ በመባል ይታወቅ ነበር። መሃንድስ ማለት ምን ማለት ነው? መሃንድስ ማለት መሃናስ/መሃንዳሰ ከሚል የዓረብኛ ቃል የመጣ ሲሆን፣ እርሱ ደግሞ ሃነፀ፣ ይሃንፅ፣ ማነፅ፣ ማሕፀን (ሕፃን የሚታነፅበት ቦታ) ... ወዘተ ከሚሉ የግዕዝ፣ የትግርኛና፣ የአማርኛም ቃላት ይዛመዳል። እንግዲያውስ ማነፅ ከሚለው ቃል መሃንዳስ ሆኖ ተጣመመና፣ ከዚያም መሃንድስ ተብሎ፣ ዞሮ ተመልሶ ብርቅ ቃል ሆኖብን ለሕንፃ ኮሌጀ መጠሪያ ሆነ። አሁንም ቢሆን ኢንጂኔር ለማለት መሃንድስ ሲባል እንሰማለን።

ሌላም ቃል ፋጡማ/ፋጢማ የሚል ስም ስንመለከት፣ ከነብዩ ሙሓመድ ሴት ልጆች ለአንዷ የተሰጠ መጠሪያ ነበረ። በዓረብኛ አባባል ግን ጠ/ጸ የሚለው ሳይሆን ተ የሚለው ፊዴል ድምፅ ነው። ይህም ማለት፣ ቃሉ “ፈቲማ” ብለው ሲሉ፣ ትርጉሙም፡ ፍጽምት፣ (Perfect) ማለት ነው። ስለዚህ ፈቲማ ማለት፣ ፈጺማ (ትግረኛ) ፈጸመች (አማርኛ) ማለት ነው።

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ሰምና ወርቅ በተባለው የምርምር መጽሔት (1987 እ.ኤ.አ.) ያቀረብነው፣ “ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ትርጉሙ ምን ማለት ነው? ኢትዮጲስ የሚባለው ንጉሥስ ለምን ይህ ስም ተሰጠው ... ብለን በጠየቅንበት ጊዜ አጥጋቢ መልስ ባለማግኘታችን ቋንቋ ለሚመረምሩ (liniguists) እንዲያተኩሩበት በዚሁ እንተወዋለን” በማለት ምርምሩን ደመደምነው። ይሁንና ካለፉት ሃያ አምስት ዓመታት እስከ ዛሬ የቀረበ መልስ ስላላገኘንና፣ ጥያቄውም በአዕምሮአችን ሲብላላ ስለቆየ፣ የዚህ ጥያቄ መልስ ይህ ይመስላል ብለን የደረስንበትን ጭብጥ በዚህ የምርምር ጽሑፍ ለማቅረብ ተነሳን።

፩ኛ የታሪክ ምርምር

በተክለ ጻድቅ መኩሪያ የተጻፈው “የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ኑብያ፣ (ናፓታ-መርዌ)” በተባለው መጽሐፍ በገጽ19-22 የካም ወገን የሆኑ 22 ነገሥታትን ስምጠቅሶ፣ 55 ዓመት ከገዛው ከአክናሁስ ወይም ሳባ ፪ኛ (1985-1930 BC) ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ የ29 ነገሥታትን ስም አስቅምጦ፤ “... ራማ የተባለ የህንድ ንጉሥ ወደ ኢትዮጵያ ዘምቶ ማሸነፉንና ሕዝቡን እንደ ባርያ ...” ይገዛው እንደ ጀመረ ያትታል። ከዚያ ግን ሦስት የዮቅጣን ልጆች ተባብረው ተነስተው እሸነፉት፥ ገድለውም፣ አግዓዝያን (ነፃ አውጭዎች) ተብለው መንግሥቱን እንደ ያዙ ገልጾ፣ ከዚያ ቀጥለው የነገሡትን የ52 የኢትዮጵያ ነገሥታት ስም ይዘረዝራል። ከፊተኞቹ 29 ነገሥታትም የመጀመሪያዎቹ 10 ነገሥታት የሚከተሉት ናቸው:-

The meaning of the name Ethiopia

ከዚህም ዓምድ እንደሚታየው ኢትዮጲስ ፩ኛ ከ1856-1800 ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ለ56 ዓመት መንገሡ፣ ኢትዮጲስ ፪ኛው ደግሞ ከ1730-1700 ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ለ30 ዓመት ያህል መንገሡ በታሪክ ተጽፏል። ይህንን ያላነበቡ ምሁራኖቻችን ግን ኢትዮጵያ ማለት ከግሪክ ቋንቋ የመጣ ቃል፤ ‘ፊቱ በፀሓይ የተቃጠለ፣ የተጠበሰ፣ ያረረ ማለት ነው’ ይሉናል።

ታላቁ የግሪክ ተራኪና ባለ ቅኔ፣ ሆመር የኖረው 800 - 700 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን፣ የግሪክ ስልጣኔ ዘመን ወይም የሄሌኒስቲክ ኤጅ (Hellenistic Age) ተብሎ የሚታወቀውም ከታላቁ እስክንድር ዘመን አንስቶ፣ ማለትም 300-30 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ ያለው ጊዜ ነው። ይህ ማለት ኢትዮጲስ ፩ኛ ከባለቅኔው ከሆመር በፊት አንድ ሺሕ ዓመት ቀድሞ የነገሠ ንጉሥ ነው።

እንግዲያውስ ምሁራኖቻችን ኢትዮጵያ ማለት ከግሪክ ቋንቋ የመጣ፤ ‘ፊቱ በፀሓይ የተቃጠለ፣ የተጠበሰ፣ ያረረ ማለት ነው’ ሲሉን፣ ሊመልሷችው የማይችሉ ሁለት ጥያቄዎች አሉን፣

1 - የጥንት የአገራችን ነገሥታት የግሪክን ቋንቋ ከሆመር መወለድ በፊት አንድ ሺሕ ዓመት አስቀድመው እንደምን ዐወቁት? ዘመኑ አቴናውያንና ስፓርታውያን የእርስ-በርስ ጦርነት (peloponnesian war 431-404 ከክርስቶስ ልደት በፊት) አንድ ሺሕ አራት መቶ ዓመት በፊት ነው። የግሪክ ቋንቋም በአካባቢው ከነበሩ መቄዶንያ፣ ማግያር፣ አናጦልያ ... ወዘተ ከመሳሰሉት ቋንቋዎች በምኑም ተለይቶ የሚታወቅ፣ ወይም የገነነ ልሳን አልነበረም። ስለዚህ እንዴት ተብሎ ይህንን ስም የአገራችን ነገሥታት ከግሪክ ቋንቋ ወሰዱት ማለት ይቻላል?

2 - ቋንቋውን ቢያውቁና ቃሉን ከግሪክ ወሰዱት ብንልም፣ እንዴት የአገራችን ነገሥታት ራሳቸውን፤ “ፊታችን በፀሓይ ያረረ፣ የተጠበሰ፣ የተቃጠለ ነውና ራሳችንን ኢትዮጲስ፤ ‘ፊታቸው በፀሓይ ያረረ፣ የተጠበሰ፣ የተቃጠለ’ ብለን እንጥራ ...” ብለው የራሳቸውን የንግሥ ስም አወጡ? ይህ ዓይነቱ አባባል ይታመናል? ፈጽሞ የማይመስል ወሬ ነው።

ምሁራኖቻችን እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች ሲጠየቁ፣ “አፋፍ-ላፋፍ ስትሄድ አግኝቸ ሚዳቋ፣ በጅራቷ ብይዛት ዓይኗ ፍጥጥ አለ ...” እንደሚሉት ዓይናቸውን ከማፍጠጠና ከመቅበዝበዝ በቀር ሌላ የሚያድርጉት ሆነ የሚሰጡት ምንም መልስ የላቸውም።

በግሪክ ቋንቋ Αιθιοπία (አይትዮፕያ) ማለት ፊቱ በፀሓይ የተቃጠለ፣ የተጠበሰ፣ ያረረ ማለት ለመሆኑ አያጠያይቅም። ጥያቄው፤ የትኛው ቃል ከየትኛው መጣ? ነው። ግሪኮች የአገራችን ጥቁር ሰው አይተው ነው ቃሉን ወደ ቋንቋቸው ያስገቡት፣ ወይስ የአገራችን ነገሥታት ናቸው ስማቸውን ከግሪክ ቋንቋ ወስደው ለራሳቸው መጠሪያ ያደረጉት? ጥያቄው ይህ ነው!

የዚህ ዓይነቱ የተዛባ አስተሳሰብ የተላበሰ አንድ የሃይማኖት መሪ፤ “... ድንቅና ተአምር የሆነ የእግዚአብሔር ጥበብ የሚገርም ነገር አለ፣ ዓይናችን፣ አፍንጫችንና፣ ጆሮአችን እንዴት ብሎ ለመነጽር እንደሚገጥም ሆኖ መፈጠሩ ዕጹብ አይደለም?” እያለ ሰብኳል ይባላል። ይህ ግን የትኛው ቀዳሚ፣ የትኛው ኋለኛ መሆኑን ባለማወቁ ነው። መነጽር ነው ለዓይን፣ ለአፍንጫና ለጆሮ እንዲገጥም ሆኖ የተሠራ እንጂ፣ ፊታችን ለመነጽር እንዲገጥም ሆኖ አልተፈጠረም። ጥልቀት የሌለው ዐውቃለሁ ባይነት ግን ለእንዲህ ዓይነቱ መዘላበድ ያጋልጣል።

፪ኛ የቃላትና የፊዴላት ምርምር

‘ፐ’ ‘ጰ’ ‘ጠ’ ‘ተ’

በመጀመሪያ (Αιθιοπία) ‘አይትዮፕያ’‘ኢትዮጵያ’ የሚሉ ቃላት ለመሆኑ የአገራችን ቃላት ናቸው ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ለመሆኑ ከግዕዝ፣ ከአማርኛና፣ ከትግርኛ ቋንቋዎች “ጰ” ወይም “ፐ” የሚል ፊዴል ያላቸውን ቃላት ብንፈልግ ምን እናገኛለን?

በግዕዝፅ በትግርኛና በአማርኛ ፖሊስ ከሚል ቃል ሌላ ‘ፐ’ ፊዴል ያለበት ምን ቃል አለ? ምንም ያለ አይመስለንም። የአገራችን ሰውም ፓሊስ ከማለት ‘ቦሊስ’ ማለት ነው የሚቀናው፥ ኢትዮጵያ ከማለትም ይጦብያ ማለት ይቀልለዋል። ‘ፐ’ እና ‘ጰ’ የሚባሉ ፊዴላትም ወደ አገራችን የፊዴል ሰነድ የገቡት በቅርብ ጊዜ ከመሆኑም በላይ፥ የውጭ ቃላትን ለመጻፍ እንዲያመቹ ተብሎ መሆኑ ግልጽ ነው። በፊደላት ሰንጠረጅም ከሁሉ በታች፣ ወይም ከመጨረሻ ቦታ መስፈራቸው ኋላ የመጡ ለመሆናቸው ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

Trapezium‘ጰ’ የሚል ፊዴል ያላቸውን ቃላት የአገራችን ቋንቋዎች ብንፈልግም፤ ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ፣ ቆጵሮስ፣ ጠረጴዛ ወዘተ... እናገኛለን። ይሁንና እነዚህ ሁሉ የውጭ ቃላት፣ ከመካከለኛው ምስራቅና ከኤውሮጳ የገቡ እንጂ የአገራችን ቃላት አይደሉም። ‘ጠረጴዛ’ የሚል ቃልም ትራፔዞይድ (trapezoid: a rectangular shaped object) ከሚለው የላቲን/የእንግሊዝኛ ቋንቋ የተገኘ እንጂ በመሰረቱ የአማርኛ ቃል አይደለም። በጥንታዊ ግዕዝ ጽሑፍም ስንመለከት፤ ‘ክሊዎፓትራ፣ የፕቶሎሚ ልጅ’ ለማለት፤ “አከልኡበጥራ፣ ወለተ በጥሊሞስ” ይላታል። ይህ የሚያሳየው “ፐ” የሚባል ፊዴል በጥንታዊ የአገራችን ቋንቋዎች ፈጽሞ እንዳልነበረ ነው። ክሊዎፓትራና አባቷ ፕቶሎሚ ግን ዘራቸው ግሪክ፣ ታላቁ እስክንድር ግብፅን አሸንፎ ከዚያው በኋላ ተክሏቸው የሄደ የግሪክ ገዢዎች ስለሆኑ፣ ስማቸው የግሪክ ስም ነው። ‘ፐ’ የሚል ፊዴልም አለበት።

ይህንን የፊዴላት ጥያቄ ያመጣነው ጥንታዊው የሁለቱ ነገሥታት ስም አጠራር ‘ኢትዮጲስ’ ወይም ‘ኢትዮፒስ’ ሊሆን እንደማይችል ለማስረዳት ነው። እንግዲያውስ ከዚህ የቃላት ምርምር የምናገኘው ነገር ካለ ይኽ ነው፤ በትክክለኛው ጥንታዊ አባባል ኢትዮጲስ፣ ኢይቶጲስ፣ ኢቶፒስ፣ አይቶፒስ... የሚሉ ስሞች ፈጽሞ የአገራችን ንገሥታት ስም ሊሆኑ እንደማይችሉ ነው።

ስለ ‘ጠ’ ፊዴል ካነሳን ደግሞ በግሪክ ቋንቋና በሌሎችም የኤውሮጳ ቋንቋዎች ‘ጠ’ የሚል ድምፅ የላቸውምና ‘ጠ’ የሚለውን በ ‘ተ’ እና ‘ፐ’ በሚሉ ፊዴላት ይተኳቸዋል። እንግዲያው ትክክለኛው አባባል ‘ይቶፒስ’ ሳይሆን “ይጦብስ” መሆን ይገባዋል እንላለን። ግሪኮች ‘ጠ’ ማለት ስላልቻሉ ነው (Αιθιοπία) ‘አይትዮፕያ’ ያሉት። እኛም ይኸው እስከ ዛሬ ኤውሮ‘ፓ’ ከማለት ኤውሮ‘ጳ’ እንደሚቀናን ማለት ነው።

የውጭ ታሪክ ጸሓፊዎች እነ ዮሴፍ ሃለቪ (Josph Halevi)፣ እኖ ሊትማን (Enno Litman)፣ ኤድዋርድ ግላሴር (Edward Glaser)፣ ኮንቲ ሮሲኒ (Conti Rossini)፣ ጂ. ሪክማንስ (G. Rickmans) የመሳሰሉትና ሌሎችም የውጭ አገር ሰዎች ያቀረቡት ጽሑፍ ይጦብያ ለማለት ስላልቻሉ ይቶፕያ፣ ኢቶፕያ፣ ሆኖ ወደ ቋንቋችን ሲተረጐም ‘ኢትዮጵያ’ ተብሎ ሊጸና ቻለ እንጂ ይህ ስም ትክክለኛ የአገራችን ይሁን የንጉሦቻችን ስም እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

በአገራችን ታሪክ የምናገኘው ሓቅ ደግሞ፣ “ይጦብያ”፣ “ይጦብስ” የሚል ስም ለሕዝብና ለአገር ቀርቶ ለተራ ንጉሥም የማይሰጥ እንደ ነበረ ነው። ሕዝቡ ነገደ አግዓዝያን፣ አገሩ ብሔረ አግዓዚ፣ ቋንቋው ልሳነ ግዕዝ ነበር። ነገሥታቱም በየክፍለ-ሃገሩ ስም፤ የትግራይ ንጉሥ፣ የወሎ ንጉሥ፣ የጎጃም ንጉሥ፣ የሸዋ ንጉሥ... ወዘተ፣ ይባሉ ነበር። “ይጦብያ” ተብሎ የሚታወቀው ሁሉን የጠቀለለ ንጉሠ-ነገሥቱ ብቻ ነበር። ይህም የጥንቱን የይጦብስ ንጉሥን ጠቅላይ ስም ወራሽነት መያዙ ለማሳየት ሆን ብሎ የተደረገ ብልሓት ይመስላል።

ይጦብስ ማለትስ ምን ማለት ነው? በግዕዝ በትግርኛና በአማርኛም “መጥበስ” የሚል ቃል አለ። ቃሉም ሲራባ፤ ጠበሰ፣ ተጠበሰ፣ ይጠብስ፣ ትጠብስ፣ ጥቡስ፣... ወዘተ፣ እያለ ይራባል። እንግዲያውስ ይጦብስ ማለት ጥንታዊ ትርጉሙ፤ ይጠብሳል፣ ያቃጥላል፣ ኃይለኛ ንጉሥ ነው! ተብሎ ጠላቶችን ለማስፈራሪያ የወጣ ስም ይመስላል እንጂ ከግሪክ ቋንቋ ተወስዶ ለአገራችን ነገሥታት ‘ፊቱ የተጠበሰ፣ በፀሓይ የተቃጠለ’ ተብሎ የተሰጠ ስም ነው ማለት አይቻልም።

ይህንን የምንለው ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪኮች የመጣ ነው ለሚሉት አጉል ምሁራን ስሕተታቸውን ለማሳየት ነው እንጂ፣ በየዘመናቱ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ልዩ-ልዩ ትርጉሞች እንደ ተሰጡት አይጠረጠርም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ማለት መልካም መዓዛ ያለው ዕጣን ነው የሚሉ አሉ። የለም፣ ታላቅና ጠቅላይ ማለት ነው የሚሉም አሉ። ከዘመናት ብዛትልዩ-ልዩ ትርጉሞች እንደተሰጡት አያጠራጥርም። የሚደንቀው ነገር ግን መሃነስ/መሃንደስ የሚል ቃል ዓለምን ዞሮ ወደኛ መሃንድስ ሆኖ ሲመለስ ህንፃ የሚለውን ትርጉሙን እንዳልሳተ፣ ‘ይጦብስ’ የሚለውም ቃል እንዲሁ የቃሉ አባባል ትንሽ ተወላግዶ በግሪኮች አነጋገር ‘ይቶፒስ’ ቢባልም የመቃጠልና የመጠበስ ትርጉሙን ሳይስት እንደ ተቀመጠ ለብዙ ዘመናት የቆየ ይመስላል።

እዚህ ላይ ‘ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?’ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ምናልባት በይጦብስ ዘመን የአገራችን ተጓዦች ወይም ነጋዴዎች ከግሪክ ሰዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ፤

“እናንተ እነማንናችሁ?”ብለዋቸው ይሆናል።
“የይጦብስ ሰዎች ነን”፣ብለው መልሰዋል።
“ይጦብስ ማለትስ ምን ማለት ነው?” ብለው ሳይጠይቋቸው አልቀሩም።
“የሚያሳርር፣ የሚያቃጥል፣ የሚጠብስ ኃይለኛ!” ማለት ነው ብለው አስረድተዋቸዋል።

ከዚያ ወድያ ግሪኮችጠቆር ያለውን ሰው ባዩ ቁጥር (Αιθιοπίs) “ይጦብስ” እያሉ መጥራት ጀምረው፣ ቃሉም ወደ ቋንቋቸው ከመግባቱም በላይ፣ “ይጠብስ” የሚለውን ጥንታዊውን ትርጉም ሳይስት ለጥቁር አፍሪካዊ ሁሉ ‘ፊቱ የተጠበሰ፣ በፀሓይ የተቃጠለ’ (Αιθιοπία) ‘ኢትዮጵያ’ የሚል መጠሪያ ለመሆን የበቃ ነው የሚመስል።

ምርምራችን በዚህ ያበቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ