Yederasiw Mastawesha / የደራሲው ማስታወሻደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ (ከነፃነት አሳታሚ ኤጀንሲ)

“በአዲሱ መጽሐፍ ቀደም ሲል ልገልፃቸው ያልፈለግሁትን ጭምር ይፋ አድርጌያለሁ” ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ

የኢትዮጵያውያን ባለአክስዮኖች ንብረት የሆነው “ነፃነት የመጻሕፍት አሳታሚና አከፋፋይ” በቅርቡ፣ “የደራሲው ማስታወሻ” የተባለውን መጽሐፍ አሳትሟል። መጽሐፉ አፕሪል 10 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. ለህዝብ ይቀርባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። አሳታሚው ከመጽሐፉ ደራሲ ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር በመጽሐፉ ዙሪያ አጭር ቃለመጠይቅ አካሂዷል። የመጽሐፉ አንባብያን ስለመጽሐፉ ይዘት ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ የቃለመጠይቁን ጭማቂ በዚህ መንገድ ቀርቧል።

 

Yederasiw Mastawesha / የደራሲው ማስታወሻነፃነት፦ “የደራሲው ማስታወሻ” ተፅፎ ማለቁን የሰማነው 2009 ማብቂያ ላይ ነበር። እስካሁን ለምን ዘገየ? ምን ችግር ገጠመህ?

 

ተስፋዬ እንዳሰብኩት አልሆነልኝም። ካቀድኩት ሦስት ወራት ዘግይቼያለሁ። አስተማማኝ አሳታሚ የማግኘቱ ሂደት እንደገመትኩት ቀላል አልነበረም። ለማሳተም ፈቃደኛ የነበሩ ግለሰቦች ጥሩ የስርጭት መዋቅር አልነበራቸውም። በርከት ያለ ቁጥር ለማሳተምም አስተማማኝ ካፒታል ይጠይቅ ነበር። ለማንኛውም መጽሐፍ ለማሳተም ሦስት ወራት መዘግየት አጭር ጊዜ ነው። ዋናው ነገር አሁን ተሳክቷል። ነፃነት አሳታሚ በምፈልገው መንገድና ጊዜ መጽሐፉን በማሳተሙና ለማሰራጨት በመዘጋጀቱ ከልብ አመሰግነዋለሁ።

 

ነፃነት ቀዳሚው መጽሐፍህ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ነበር ስሙ። ይህን “የደራሲው ማስታወሻ” ብለኸዋል። ልዩነቱ ምንድነው?

 

ተስፋዬ ልዩነት የለውም። አንባብያን ሁለቱን መጻሕፍት በቀላሉ መለያየት እንዲችሉ ብቻ ነው ስሙን የለወጥኩት። “ክፍል 2” ማለቱን አልወደድኩትም። በተቀረ ደራሲውም ሆነ ጋዜጠኛው እኔ ነኝ። እዚህም ላይ በተመሳሳይ የአፃፃፍ ዘዴ ማስታወሻዎቼን ነው ያሰፈርኩት።

 

ነፃነት ቀዳሚውን ከዚህኛው እንዴት ታወዳድረዋለህ።

 

ተስፋዬ ሁለቱንም በጥንቃቄ እንደሠራሁ ይሰማኛል።

 

ነፃነት “የደራሲው ማስታወሻ”ን ፅፈህ ለመጨረስ ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?

 

ተስፋዬ ስምንት ወራት።

 

ነፃነት ማወዳደር ካለብህ ከሁለቱ የትኛው የተሻለ ነው?

 

ተስፋዬ አንባቢ ሊያወዳድራቸው ይችላል። በኔ በኩል ሁለቱም በተመጣጣኝ ደረጃ ላይ እንዳሉ እገምታለሁ። በመረጃ ደረጃ ግን ይህኛው ሳይጠነክር አይቀርም። የሰው ልጅ ከዕለት ዕለት ወደ ሙሉ ነፃነት የመጓዝ ልምዱን ማዳበር እንደሚችል አዲስ እውቀት አግንቼያለሁ።

 

ነፃነት የኢትዮጵያን ሪቪው (www.ethiopianreview.com) ድረገጽ ዋና አዘጋጅ አስመራ ላይ አግኝቶህ እንደነበርና የወያኔን የተቀበሩ ታሪኮች ፍለጋ ላይ እንደነበርክ ፅፎ ነበር። አስመራ ላይ ምን አገኘህ?

 

ተስፋዬ አስመራ ላይ መገመት ከሚቻል በላይ ኢትዮጵያውያን አሉ። የሚገባው የሚወጣው ሳይቆጠር በርካታ አስፈላጊ ሰዎችን አግንቼያለሁ። እንደአስፈላጊነቱ በመጽሐፌ ላይ ገልጬዋለሁ። በተለይም የወያኔ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሁለት ኮሎኔሎች ጋር ያደረግሁት ቆይታ በጣም ጠቃሚ ነበር። መጽሐፌ ላይ እንደወረደ ቀርቧል። መረጃው ለኔ ሙሉ በሙሉ አዲስ ባይሆንም በኅብረተሰባችን በዝርዝር የማይታወቁ የሥርዓቱን ውስጣዊ አሠራርና ጠባይ የሚያጋልጡ በርካታ መረጃዎችን አግንቼያለሁ። የኢትዮጵያ የሱዳንና የኤርትራ ድንበሮች ላይም ጥቂት ቀናት ቆይቻለሁ። ከገበሬዎች ጋር ረጅም ቆይታ በማድረግ በርካታ ማስታወሻዎችን ይዣለሁ። “ቦ ጊዜ ለኩሉ” እንዲሉ ከዕለታት አንድ ቀን እፅፈዋለሁ።

 

ነፃነት “የደራሲው ማስታወሻ”ን ይዘት ባጭሩ ልትገልፅልን ትችላለህ?

 

ተስፋዬ 424 ገፆች ያሉትን መጽሐፍ በአጭሩ መግለፅ ያስቸግራል። በጥቅሉ ግን የ“ደራሲው ማስታወሻ”ን የሚያነብ ሰው ኢትዮጵያ የተባለችውን ሀገር የሚመሩት ሰዎችን ስብዕና በትክክል ለመረዳት ይችላል። ቀደም ሲል ልገልፃቸው ያልፈለግሁትን ጭምር ይፋ አድርጌያለሁ።

 

ነፃነት የግንቦት 7 የድርጅት አባል ሆነሃል ይባላል። እውነት ነው?

 

ተስፋዬ የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል አልሆንኩም። እኔ ደራሲ ነኝ። የዘረኛውን አገዛዝ ስርአት ለመገልበጥ ለሚታገሉ ኢትዮጵያውያን ሃይሎች ሁሉ ድጋፍ እሰጣለሁ። ወያኔ መወገድ አለበት። ከኔ በላይ የወያኔን አደገኛነት ቀርቦ የሚያውቅ ማንም የለም።

 

ነፃነት በቀዳሚውና በአዲሱ መጽሐፍህ ከተገለፀው ባሻገር ስለወያኔ ያልነገርከን ምስጢር ይኖር ይሆን?

 

ተስፋዬ ተሳቅቄ ያልፃፍኩት ብዙ ነገር አለ። የህዝቡን ስሜት ሊጎዳ ይችላል ብዬ የተውኩት ታሪክ ከደርዘን ምዕራፍ በላይ ነው። የወያኔ አመራር አባላት (በተለይ ስብሃት ነጋ) ከሌሎቹ የበለጠ ያምኑኝና ያቀርቡኝ ስለነበር ብዙ ምስጢር የማወቅ ዕድል ገጥሞኝ ነበር። ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲቆጣ የሚያደርጉ መረጃዎች ለዘልዓለሙ ተቀብረው ቢቀሩ ይሻላል።

 

ነፃነት ህዝቡ የማወቅ መብት የለውም ትላለህ?

 

ተስፋዬ በዚህ ወቅት መፃፍ ያለበትን እየፃፍኩ ነው።

 

ነፃነት ህዝቡ ማወቅ የማይገባው ምንድነው?

 

ተስፋዬ ጄኔራል ታደሰ ብሩ ለህዝብ መግለፅ ያልነበረባቸውን ምስጢር ይፋ በማድረጋቸው የተፈጠረ አደጋ አለ። ያ መረጃ አደጋውን እንደ ሰደድ እሳት አቀጣጥሎታል። ያንን መድገም አልፈልግም።

 

ነፃነት ምንድነው ጄኔራሉ የገለፁት ምስጢር?

 

ተስፋዬ “የደራሲው ማስታወሻ” ላይ ገልጬዋለሁ። በጥቅሉ እውነት ሁሉ መገለፅ አለበት ብዬ አላምንም። እውነትን መግለፅ መጪውን አደጋ የሚያድንና ለአንድነታችን የሚበጅ ከሆነ ብቻ ነው መገለፅ ያለበት። አለመረጋጋትን የሚያባብስ እውነት በተቻለ መጠን ተቀብሮ መቆየት አለበት። አሜሪካኖች እንደሚያደርጉት ባለታሪኮቹ ከሞቱ በኋላ በ50ኛው ዓመት ቢገለፅ ይሻላል።

 

ነፃነት የወያኔ ባለሥልጣናት “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን አንብበውታል?

 

ተስፋዬ መለስ ዜናዊ እንዳነበበው መረጃ አለኝ። መረጃውን ያገኘሁት ከአንድ የወያኔ ዲፕሎማት ነው። መለስ ካነበበው በኋላ፣ “የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ጠይም ይሁን ጥቁር ትዝ አይለኝም” ብሎ መናገሩን ዲፕሎማቱ ፕሪቶሪያ የመጣ ሰሞን ነግሮናል። ተፈራ ዋልዋና በረከት ስምዖን እንዳነበቡትም ከሌላ የመረጃ ምንጭ ሰምቻለሁ። የወያኔ ካድሬዎች በአንድ ስብሰባ ላይ ስለመጽሐፉ ጉዳይ ለበረከት አንስተውለት ጠረጴዛ እየደበደበ መሳደቡን ነግረውኛል። ተፈራ ዋልዋ ባንፃሩ “የተፃፈው ልክ ነው” ማለቱን ሰምቻለሁ። ስብሃት ነጋ፣ “የኮበለለ ሰው ውዳሴ እንዲዘምርልን አንጠብቅም። እንኳን የሚያውቀውን የማያውቀውንም ቢፅፍ አይገርመኝም። ስህተት የተፈጠረው የአባላት አያያዛችን ላይ ነው” ብሎ ተጠያቂነቱን በረከት ላይ እንደጫነበት ሰምቻለሁ። የፋና ሬድዮ ጋዜጠኞች “በረከት ስምዖንና ሴኮ በመጽሐፉ ውስጥ በትክክል ተገልፀዋል” ብለው እንደሚያምኑ ከሚታመን ምንጭ አረጋግጬያለሁ። የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አማረ አረጋዊ፣ “ጥቂት ማጋነን አለበት እንጂ የተፃፈው ሁሉ እውነት ነው” ብሎ ስለመናገሩ መረጃው ደርሶኛል። ከዚህ ባሻገር የወያኔ ካድሬዎች በተለያዩ የብዕር ስሞች መጽሐፉን በማውገዝ ፅፈዋል። በአብዛኛው “አይጋ ፎረም” እና “ኢትዮ ሚዲያ” የተባሉትን ድረገፆች በመጠቀም ቁጣቸውን አንፀባርቀዋል። ይህም በመጽሐፉ የተጋለጡት ሐቆች እንዳበገናቸው የሚያሳይ ነው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ላይ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ተነቧል። ለአንድ ደራሲ ከመነበብ በላይ ግብ እና እርካታ የለውም። አዲሱ መጽሐፍ ከቀዳሚው የመረረ ነው።

 

ነፃነት “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ መለስን በአግባቡ አልነካኸውም የሚል ትችት አለ። በዚህኛውስ?

 

ተስፋዬ “የደራሲው ማስታወሻ” ላይ መለስ ዜናዊ እና ስየ አብርሃን ቀረብ ብለን እንድናውቃቸው ለማድረግ ሞክሬያለሁ። “ሁለቱ ዝሆኖች” የሚለው ምዕራፍ ስየና መለስን ይመለከታል።

 

ነፃነት ቀዳሚውን መጽሐፍ ያነበቡ ‘በረከት ስምዖን ላይ ጥላቻ አንፀባርቋል’ ሲሉ ገልፀዋል። ምን አስተያየት አለህ?

 

ተስፋዬ በረከት ላይ በግል የተለየ ጥላቻ የለኝም። የጋንግስተር ጠባይ ስላለውና ችኩል በመሆኑ ለመሪነት አይመጥንም ብዬ ግን አምናለሁ። ይህን እዚያው አዲሳባ እያለሁ አሰፋ ማሞ የተባለ የወያኔ ካድሬ ይመራው የነበረ ስብሰባ ላይ በግልፅ ተናግሬያለሁ። በጥቅሉ በረከት ስምዖን ግራ የተጋባ ሰው ነው። አማርኛ የመናገር ፍላጎት እንደሌለው ይታወቃል። ይሄ ለሀገሪቱ ፀያፍ ስድብ ነው። በረከት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያዊነት ቢታገል ባከበርኩት ነበር። በዘር ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መንቦጫረቁ ሳይበቃ፣ አማራ ሳይሆን በድርቅና ‘የአማራ ድርጅት መሪ ነኝ’ ብሎ የህዝቡን ስቃይ ማራዘሙን እንደ ከባድ ወንጀል አይበታለሁ። በመጽሐፌ ላይ በረከትን የተመለከተው አንቀጽ ሰፋ ብሎ የቀረበው ግን የቅርብ አለቃዬ ስለነበር ነው።

 

ነፃነት በቀጣይ ካንተ ምን ልንጠብቅ እንችላለን?

 

ተስፋዬ “የስደተኛው ማስታወሻ” የተባለ መጽሐፍ ጀምሬያለሁ።


Netsanet Publishing Agency.

Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

http://www.NPAbooks.com 

Tesfaye Gebreab

Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!