ሰሞኑን BETSY AND THE SUPERCOPTER በሚል ርእስ አዲስ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለኅትመት በቅቷል። ደራሲው ዓለማየሁ ታዬ ከዚህ ቀደም ባሳተማቸውና “የዓለማየሁ ሩባያት”፤ “ግራፊቲ” እና “ሐይኩ” በተሰኙ የግጥም መድበል መጽሐፎች እንዲሁም “ጣፋጭ ተረቶች” በሚል ርእስ ባሳተመው ትርጉም የህጻናት መጽሐፍ እናውቀዋለን። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በህንድ ፑኔ ዩኒቨርስቲ በሥነጽሁፍና ሳይኮሎጂ አሁንም በአሜሪካ የተለያዩ ኮሌጆች ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ዓለማየሁ ታዬ ኢትዮጵያ ውስጥ በሬዲዮና በኅትመት ጋዜጠኝነት ሰርቷል። በአሁኑ ወቅት በሎስ አንጀለስ ከተማ ቪሌጅ ግሌን ዌስት በተሰኘ ትምህርት ቤት በረዳት አስተማሪነት /Teacher’s Aide/ በመስራት ላይ ይገኛል። የአዲሲቱ መጽሐፍ ለኅትመት መብቃት ምክንያት ሆኖት ታሪኩ ኃይሉ በገጣሚው ስራዎች ላይ ከገጣሚው ጋር ያደረገውን ሰፋ ያለ ቃለምልልስ እነሆ!

 

ሩባይ 1

ሃሳብ ከዜማ ተቃኝቶ ቃል ከብራና ተዋደደ

ምጥ ያክትሞት ሞቱን ሞቶ ወዳለመኖር ተሰደደ

ረቂቃን ምስል ከሥተው ኅያዋን ጉሉሓን ሆኑ

ነፍሴ ማኅሌት ቆመች እሰይ ሩባይ ተወለደ

የዓለማየሁ ሩባያት ገጽ 1

 

ታሪኩ፦ የመጀመርያ ስራህ በሆነችው በዓለማየሁ ሩባያት ጥያቄዬን ልጀምርና እንደው ሩባያትን ለመጻፍ መነሻህ ምን ነበረ?

ዓለማየሁ፦ እሷን መጽሐፍ ስጽፍ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበርኩ። አብዛኛውን ግዜዬንም የማሳልፈው በማንበብ በመመርመር እና በመጠየቅ ነበር። በተለይ ለየት ያለ ያጻጻፍ ስልት የመሞከር ብርቱ ፍላጎትም ውስጤ ነበረ። በወቅቱ የአቤ ጉበኛን ስራዎች እያደንኩ አነባቸውና አጠናቸው ነበር። ታዲያ አቤ ጉበኛ የጻፋቸውን ሩባይ መሰል ግጥሞች ማንበቤና በአጋጣሚ ደግሞ ፊዝጄራልድ በእንግሊዝኛ ያዘጋጀውን የዑመር ኻያም ሩባያት ማግኘቴ እንዲሁም ጋሽ ተስፋዬ የተረጎሙትን መልክዐ ዑመር መጽሐፍ በፍቅር መውደዴ ሩባያትን ወደ መሞከር የገፋፋኝ ይመስለኛል።

 

ታሪኩ፦ አቤ ጉበኛ ሩባያት ጽፏል ማለት ነው?

ዓለማየሁ፦ አቤ ሩባያትን መሰረት አድርጎ የሩባይን ቅርጻዊ ስርዓት ተከትሎ በራሱ መንገድ በርካታ ባላምስት መስመር ግጥሞችን ጽፏል።

 

ታሪኩ፦ ሩባይ ሲነሳ አብሮ የሚነሳ ዑመር ኻያም መሆኑንና ይህ የግጥም ቤት የዑመር ቤት ግጥም እስከመባል መድረሱን በመጽሐፍህ መግቢያ ላይ አብራርተሃል። እስቲ ስለ ሩባይ አጀማመርና ስላጻጻፉ ትንሽ የምትለን ካለህ?

ዓለማየሁ፦ የፋርስ ሰዎች ሩባይ መጻፍ የጀመሩት ጥንት ነው። ከዑመር ኻያም በፊት በርካታ ባለቅኔዎች ሩባያት ጽፈዋል። ዑመር ኻያም ተጠቃሽ የሩባይ ደራሲ የተባለው በርካታ ሩባያት በመጻፉ ስራዎቹም ከፍተኛ ኪናዊ ዋጋ ስላላቸው እንዲሁም ተተርጉመው በመላው ዓለም በመነበባቸው ምክንያት ነው። አጻጻፉን በተመለከተ ሩባያት ባላራት መስመር ግጥሞች ናቸው። አንድን ስራ ሩባይ የሚያሰኘው የቅርጽ እንጂ የይዘት ጉዳይ አይደለም። ሩባይ የራሱ የሆነ ልዩ ቅርጻዊ አሰዳደር አለው።ይህም ከሶስተኛው ስንኝ በስተቀር ሁሉም ስንኞች ቤት መምታቸው ነው። የሶስተኛው ስንኝ ከሌሎቹ ስንኞች ጋር ተስማሚ ድምጽ አለመስጠት ሩባይን ከሌሎች ባላራት መስመር ግጥሞች ይለየዋል።የመጀመርያው የሩባይ ጸሐፊ የግጥሙን አደናቃፊ ዜማ ከአንድ ህጻን ልቅሶ እንደቀዳው ይነገራል።

 

ታሪኩ፦ ሁለተኛውን የሩባያት ስብስብህን መቼ ነው የምናነበው?

ዓለማየሁ፦ የዓለማየሁ ሩባያት ከታተመ በኋላ ሌላ ሩባይ አልጻፍኩም። አሮጌውንና የለመድከውን ነገር ተወት ካላረከው ሐዲስ ብርሃን አይላክልህም ስለዚህ ሐዲስ ብርሃን ፍለጋ ሩባይን እርግፍ አድርጌ ተውኩት። አንዳንዴ በህልሜም ይሁን በታህተ ህሊናዬ ሩባያት ተወልደው በመንፈሴ ይደመጡኛል፤ ግን አልጽፋቸውም። በቸልተኝነት እዘጋቸዋለሁ። እናም ሁለተኛ የሩባይ ስብስብ አሁን የለኝም። ወደፊት ግን ምናልባት ሩባያትን እመለስበት ይሆናል።

 

የደመና ግላጭ

የክረምት ሰማይ

ደመና ደፍኖ

ጭጋግ ጨፍኖ

ፀሃይ በደመና ግላጭ

ተሠርቃ

አንገቷን አስግጋ

አይኗን አጮልጋ

አንዳፍታ!

ባይናፋር ብርሃን ብትጣቀስ

ምድር

ብትን ብላ ተሽኮረመመች።

ግራፊቲ ገጽ 16

ሐይኩ

ታሪኩ፦ ከሩባያት ቀጥሎ ያሳተምከው መጽሐፍ ግራፊቲ ነው። ለምን የመጽሐፉን ርእስ ግራፊቲ አልከው?

ዓለማየሁ፦ ርእሱን ግራፊቲ ያልኩት ቃሉ ግራፊቲ በአንባቢዎቼ ልቦና ውስጥ በጉልኅ እንዲታተም ነው። ግራፊቲ እያልኩ የምጽፋቸው ጽሑፎች የራሳቸው የሆነ ኪናዊ ስነጽሁፋዊና ስነልቦናዊ ዳራ አላቸው። የጥበብ አምላክ ፈቃዱ ሆኖ ግራፊቲዎቼን ወጥ በሆነ ደረጃና በተብራራ ሁኔታ ይዤ እስክቀርብ ድረስ በየመጽሐፎቼ ላይ በተደራቢነት የሚወጡት ነገርዬዎች ካንባቢ ጋር ተዋውቀዋል።

ግራፊቲ

The moon was really far, but warm and jolly; talking to me all night long she disappeared at dawn even before I get the chance to say “ciao gorgeous!” this winter

ግራፊቲ ገጽ 13

 

ታሪኩ፦ በግራፊቲ ውስጥ ያሳተምካቸው ግጥሞች ትንሽ ለየት ያሉና ያልተለመዱ ይመስላሉ፤ የራስህ የሆነ የአገጣጣም ብልሃት እያዳበርክ የራስህ የሆነ አንባቢም እያፈራህ ያለ ይመስላል። አዲስ ነገር ሁል ጊዜም አስቸጋሪነት አለውና ከአንባቢዎች ያገኘኸው አቀባበል ምን ይመስላል?

ዓለማየሁ፦ ግራፊቲ ውስጥ የተለያየ ቅርጽና ይዘት ያለቸው ግጥሞች ታትመዋል። ከሶስት መቶ በላይ ከሚሆኑ የግጥም ስብስቦቼ መሃል መርጬ ነው ያቺን መጽሐፍ ያዘጋጀሁት። ግጥም መጻፍ ስጀምር ከሞከርኳቸው በርካታ ስራዎች መካከል ለአብነት ያህል በትንሹ፤ የግጥም አጻጻፍ ስርዓት ከገባኝ በኋላ ከሞከርኳቸው ስራዎች በጥቂቱ ከዚያ በኋላ ደግሞ ከመደበኛው ያገጣጠም ስርዓት ካፈነገጥኩባቸው ስራዎች በከፊል አድርጌ ነው ግራፊቲን ያሳተምኩት። ዘመኑ የቴክኖሎጂ የኢንተርኔት ዘመን ነውና ግራፊቲን በተመለከተ እጅግ በጣም በርካታ አስተያየቶች በአካልም ሆነ በኢሜል ደርሰውኛል። አንዳንዶቹ ግጥሞቼን እንደወደዷቸው ነግረውኛል። እነዚህ ቀሽም ግጥሞች ናቸው ያሉም ይኖራሉ። በዚህ አጋጣሚ ግጥሞቼን አንብበው የተሰማቸውን በኢሜልም ሆነ በአካል እንዲሁም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ላካፈሉኝ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

 

ታሪኩ፦ ግራፊቲ ውስጥ በጻፍካቸው አንዳንድ ግጥሞች ውስጥ በተለምዶ /taboo/ አይነኬ የተሰኙ ቃላት ተጠቅመሃል በግጥም አጻጻፍ ደንብ ይህ ተገቢ ነው ትላለህ?

ዓለማየሁ፦ የገጣሚ ዋነኛ መሳርያ ቃላት ናቸው። የተኮረኮረበትን ፍልስፍናውን ህልሙን ራእዩን ገጣሚ የሚያስተላልፈው በቃላት ነው። ቃላት በግጥም ውስጥ ከተራ ቃልነታቸው በላይ እጅግ የረቀቀና የደመቀ ትርጓሜ አላቸው። እንደ አውደምንባባቸው እንደ ማህበራዊና ተለምዷዊ አገባባቸው አንዳንድ ቃላት ከተራ ቃልነታቸው አልፈው ቱባ መልእክት ያስተላልፋሉ። እናም ቃላት በግጥም ውስጥ ወሳኝ የሆነ ትርጉም፥ አስፈላጊነትና ተገቢነት እንዳላቸው አንባቢ ልብ ማለት አለበት። እኔም አሁን ያልካቸውን አይነት ታቡ መሰል ግን ተለምዷዊ የሆኑ ቃላት ስጠቀም ግጥሙን ከጻፍኩበት አጠቃላይ መንፈስ ጋር እጅግ የተቆራኘና ሊለያይ የማይችል ተዛምዶ ስላላቸው ነው።

ግራፊቲ

I have only one lover, because it is costly to have three, አንዷም ፍቅሬ እንፋሎት ናት እንዳላቅፋት ምትሃት ናት እንዳልዘነጋት ውጋት ናት ብርሃን ጨረር እሳት አላት, then it is better to let go እንፋሎት and move on to love three, when one evaporates, the other may blossom, if the blossomed falls, a stranger may appear and so on and so forth…

Haiku page 40

 

ታሪኩ፦ በግጥም ስራዎች ላይ አርትዖት ሊደረግበት ይገባል ትላለህ?

ዓለማየሁ፦ ግጥም እጅግ ግላዊ የሆነ ከገጣሚው ሰብእና አስተሳሰብ አስተዳደግ ባህላዊ እውቀት የንባብ ልምድ የማፈንገጥ ወይም ያለማፈንገጥ ዝንባሌ ወዘተ ጋር የተያያዘ የስነጽሁፍ ዘርፍ ነው። በወጉ የተጻፈን የአንድን ሰው ግጥም ሌላ ሰው ላርም ብሎ መነሳት ነውር ነው። የገጣሚውን የነፍስ ዜማ የቋንቋ አጠቃቀም ብልሃትና ምርጫ የአሰነኛኘት ውርድና የአመለካከት አቅጣጫውን መዝረፍ ነው የሌላን ሰው ግጥም ላርም ብሎ መነሳት። እያንዳንዳችን ልዩ ሆነን እንደተፈጠርነው ሁሉ እያንዳንዱ ግጥምም ግላዊ ልዩና ከገጣሚው አጠቃላይ ሁነት ጋር ጥብቅ የሆነ ዝምድና እንዳለው ልብ ማለት ያስፈልጋል። ገጣሚ ሆን ብሎ ዜማ ቢሰብር ተከምዷዊውን ያገጣጠም ስርዓት ቢጥስ ሃርመኒ ቢያፋልስ እንኳ እንደዚያው እንደእሱነቱ የራሱን አሻራ ይዞ ነው መነበብ መጠናት ለትውልድ መተላለፍ ያለበት። ስለዚህ በበኩሌ ግጥሞቼ የማንም ሰው እጅ እንዲነካቸው አልፈቅድም። ከተነበቡ ከታተሙ በኋላ ግን አንባቢ እንደመነካቱ መጠን እንደገባው ቢተረጉማቸው ያ የኔ ጉዳይ አይሆንም።

 

ታሪኩ፦ በዚህ አካሄድ እንግዲህ ግጥም መተቸት ማለት በግጥም ላይ ኂስ መቅረብ የለበትም እያልክ ነው?

ዓለማየሁ፦ በፍጹም! ኂስ የጥበብ ስራዎችን ከ አንባቢ ከተመልካች ከተደራሲ ጋር የሚያገናኝ ቀና መንገድ ነው። ኂስ ተናጋሪና አድማጭን የሚያደማምጥ የሬዲዮ ሞገድ ነው። ኂስ የጥበብ ሰውን ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ የሚኮረኩር የሚያነቃቃ ቅመም ነው። የኂስ ጥበብ በዳበረባቸው አገሮች የጥበብ በረከቶችም አስደናቂ በሆነ ፍጥነትና ልእልና እያደጉ መሆናቸውን የዓለም የስነ ጽሑፍ ታሪክ ያስረዳል። የግጥም ስራዎች ያለ ኃያሲ የጽልመት እንቁዎች ናቸው። ያብረቀርቃሉ ዋጋቸው ከፍተኛ ነው ግን አይታዩም ልልህ ፈልጌ ነው። ግጥም የሚፈከር የሚተነተን የሚተረጎም የሚወረስ የጥበብ ዘርፍ ነው። ታዲያ ግጥምን ከኃያሲ እንደምን እንለየዋለን? ሆኖም ግን አንድ ተገቢ የሆነና ማንም ሊክደው የማይችል ሃቅ አለ። ማሽሟጠጥ አሽሙርና አግቦ ከኂስ ተርታ የማይሰለፉ ምናምንቴዎች ናቸው።

 

ታሪኩ፦ በግራፊቲ መጽሐፍ መግቢያ ላይ እስቲ ግጥም ልጻፍ ተብሎ ግጥም አይጻፍም! ትላለህ ታዲያ እንዴት ነው ግጥሞችህን የምትጽፈው?

ዓለማየሁ፦ የግጥም ነገር ለኔ ሁል ጊዜ እንግዳ ነው። ግጥም እጽፋለሁ ብዬ ግጥም መጻፍ አይቻለኝም። ግጥም አልጽፍም ብዬም ከመጻፍ አልታቀብም። ግጥም ስጽፍ አብሮኝ ግጥሙን የሚያምጥና የሚወልድ ሰብእና ውስጤ አለ። ግጥም ስጽፍ ብእሩን ጨብጦ ተመስጦዬን ወርሶ ልምድና ባህላዊ እውቀቴን ገንዘቡ አድርጎ ቃላት የሚያቀብለኝ ዜማ የሚያወርድልኝ ቀለም የሚገፋልኝ ሰብእና ውስጤ አለ። ያ ስውር ሰብእና ግዘፍ ካልነሳ ግጥም አይሆንልኝም። ለዚህ ነው እስቲ ዛሬ ግጥም ልጻፍ ብሎ መነሳት አዳጋች የሚሆነው። እንዲያውም አንድ ጊዜ የሥነ ጽሑፍ ስራዎቼን ለመስራት መደበኛ ስራዬን አቁሜ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ አንዲት ግጥም ጠብ እንዳላለች አስታውሳለሁ።

 

ታሪኩ፦ ሌላው የተለየና ከዚህ በፊት ያልተሞከረ ስራህ ሐይኩ ነው። ሐይኩ ብሎ ግጥም ለመጻፍ ምን አነሳሳህ እንዴትስ ጀመርከው?

ዓለማየሁ፦ እንደነገርኩህ ለየት ያለ ነገር መሞከር እወዳለሁ። ከሐይኩ ጋር የተዋወኩት በንባብ ነው። ሐይኩን ገፍቼ እንድጽፍ የገፋፋኝና ከአጻጻፍ ጥበቡ፤ ከፍልስፍናው ጋር ያቀራረበኝ Poets.com የተሰኘ ዓለም አቀፍ የባለቅኔዎች ማህበር አባል መሆኔ ይመስለኛል። በወቅቱ ሐይኩን በመጻፍና በመተንተን እሳተፍ ነበር። የአጻጻፍ ጥበቡ እየገባኝ ሲመጣም በአማርኛ ሞከርኩትና ያቺ መጽሐፍ BI-LINGUAL ሆና ለመታተም በቃች።

 

ታሪኩ፦ እስቲ ስለሐይኩ አጀማመር ምን የምትለው ነገር አለህ?

ዓለማየሁ፦ በመጽሐፌ መግቢያ ላይ እንዳብራራሁት ሐይኩ ሬንጋ ከተሰኘ የቅኔ መንገድ ተገንጥሎ የወጣ እራሱን የቻለ የቅኔ ቤት ነው። ሬንጋ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የቡዳ መነኮሳት/ፈላስፎች በደቦ የሚዘርፉት ረዘም ያለ የጃፓኖች ቅኔ ነው። ልብ በል ያገራችን ባለቅኔዎች ቅኔ ሲዘርፉ አንዱ የጀመረውን ሌላው ከምላሱ ነጥቆ እንደሚሞላውና እንደሚጨርሰው አይነት ነገር መሆኑ ነው። ታዲያ ማትሱኦ ባሾ የተሰኘ ባለቅኔ የሬንጋ መክፈቻ የሆነውን ባለሦስት ቤት ስንኝ ማለትም ሖኩ እራሱን የቻለ ምሉእ የሆነ ቅኔ ነው የሚል ሃሳብ አመነጨና በርካታ ወጥ ሖኩዎች ጻፈ። ሌሎች ደቀመዛሙርት መልምሎም ሖኩን ተወዳጅ የቅኔ ቤት አደረገው። ከዚያ በኋላ የመጣ ሺኪ የተሰኘ ሌላ ባለቅኔ ደግሞ ሖኩ የሚለውን ስያሜ ወደ ሐይኩ ቀየረው።

 

ታሪኩ፦ አጻጻፉስ፤ ሐይኩን ከሌሎች ግጥሞች የሚለየው ምንድን ነው?

ዓለማየሁ፦ ሐይኩ ቅልል ያለ የቅኔ ቤት ነው። እንዲያው በጥቅሉ እጅግ በጣም ተለምዷዊ የሆኑ የንግግር ቃላትን ነው ሐይኩን ስንጽፍ መጠቀም ያለብን። የሐይኩ ውበቱ የቃላቱ ቅለትና ተራነት ነው። ተራ የሆነውን የተፈጥሮ ትእይንት በተራ ቃላት ለማንኛውም አንባቢ መጻፉ ነው የሐይኩ ምጥ። ከዚህም ሌላ ሐይኩ ቁጥብ ነው። እንደሌሎቹ የግጥም ዘሮች ቃላት አያዝረከርክም ሃሳብ አያንዛዛም። ታዲያ ያ ቅልል ያለ ቁጥብ ቅኔ ስእል መሳልም ይኖርበታል። በተደራሲው ልቦና ውስጥ የሚታይ የሚሸተት የሚደመጥ የሚዳሰስና የሚቀመስ ጉልህ ስሜት ማስረጽ መቻልም አለበት ሐይኩ።

 

ታሪኩ፦ በመጽሐፍህ መግቢያ ላይ እንዳሰፈርከው ( ላንብብልህና ) በአጠቃላይ ሐይኩ በተፈጥሮ በመማረክ ተጸንሶ በተቆጠሩ ቀለማት ተሰድሮ በቀላል ቋንቋ በምስል ከሳች ቃላት የሚዘረፍ ፍልስፍናዊ ቅኔ ነው ብለሃል። በተለይ ሐይኩ ፍልስፍናዊ ቅኔ የተሰኘበትን ምክንያት ብታብራራልን?

ዓለማየሁ፦ የዚህ ዘመን እውቀትና የቡዲዝም አስተምህሮ አጠቃላይ ይዘት ቡዲዝም ከሐይማኖት ይልቅ ፍልስፍና መኾኑን እንደሚያመለክት ልብ እንበልና ጨዋታችንን እንቀጥል። ለአብዛኛው ሐይኩ ፍልስፍናዊነት የባህሪው ነው። ሐይኩ ዐይነ ጉዳዩ ተፈጥሮ በመሆኑ ምክንያት ከቡዲዝም ፍልስፍናና አስተምህሮ ጋር የጠበቀ ቁርኝት አለው። ያገራችን የግእዝ ቅኔያት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከነገረ መለኮት ጋር የጠበቀ ትስስር እንዳላቸው አይነት መሆኑ ነው። አንድ ሐይኩ የቡዲዝምን አስተምህሮ ለማያውቅ ሰው የአንድ የተፈጥሮ ቅጽበታዊ ሁነት ቅጂ ቢሆን ያው ሐይኩ የቡዳን ፍልስፍና ላዋቀ ሰው ግን ተጨማሪ ትርጓሜ አለው። ነገሩን ለማብራራት ሁሌ የምጠቅሰውን ካገራችን የግዕዝ ቅኔ አንድ ጉባኤ ቃና ልውጣል?

 

ታሪኩ፦ በሚገባ ቀጥልልኝ

ዓለማየሁ፦ ነዳያን ለኤዶም

በነገራችን ላይ ይህቺን ጉባኤ ቃና ያገኘኋት ከጥቂት ዓመታት በፊት የዝዋይን መንደሮች በጋሪ ሲያስጎበኘኝ ከነበረ ባለጋሪ ነው። ባለጋሪው ጉባኤ ቃናዋ የኔ ሳትሆን የሌላ ባለቅኔ ናት ብሎ እንዳጫወተኝም አስታውሳለሁ። ልቀጥልልህ

ነዳያን ለኤዶም እምንዳቢሆሙ ድህኑ

ቀይህ መስቀል ይረድኮሙ አኮኑ

የጉባኤ ቃናው ትርጓሜ የዚህ መንደር ችግረኞች /ደሃዎች/ ከመከራቸው ዳኑ። ቀይ መስቀል የተባለው ድርጅት ይረዳቸዋልና የሚል ነው። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ እማያቅ ሰው ይህን ቅኔ በጥሬው ነው የሚረዳው። ማለት ችግረኞቹ በቀይ መስቀል ድርጅት መረዳታቸውን ከችግራቸውም መላቀቃቸውን ነው። ነገር ግን ክርስትናን የሚያቅ ምስጢረ ሥላሴን ያነበበ ሰው ከላይ ላይ ትርጓሜው በተጨማሪ የቅኔውም ምስጢር ይገባዋል። የኤደን ገነት ችግረኞች የሆኑት አዳምና ሔዋን በክርስቶስ ደም ከሞት እዳ ነጻ መውጣታቸውን ይረዳል ማለት ነው። ሐይኩም እንዲሁ አንባቢውን ይፈልጋል። የሐይኩ ትርጓሜና የመወረስ ኃይል እንዳንባቢው የመረዳት የመተርጎምና የመነካት አቅም ይወሰናል። ለዚህም ነው ሐይኩ Deceptively Simple የግጥም አይነት የሚባለው።

 

ታሪኩ፦ ሐይኩን ከቡዲዝም ጋር የሚያዛምደውን ተንተን አድርገህ ልታስረዳን ትችላለህ?

ዓለማየሁ፦ ታሪኩ! በሐይኩና በቡዲዝም መካከል ያለውን ዝምድና ለማስረዳት ሁልጊዜም የሚጠቀስ አንድ ፖፑላር ጥቅስ አለ እሱን ልበልልህና ትርጓሜውን እንወያይበት።

 

ታሪኩ:- መልካም ነው ቀጥል

ዓለማየሁ፦ Inaddition to its explicit reference to nature, haiku usually consists some sort of implicit Buddhist reflection on it. In Buddhist metaphysics are three important ideas about natural things that they are transient, that they are contingent and that they suffer

ሐይኩ ማለት ውዳሴ ተፈጥሮ ወይም ነገረ ተፈጥሮ የሆነ የቅኔ ቤት መሆኑን እያሰብን ውይይታችንን እንቀጥል። በቡዲዝም ሜታፊዚክስ ተፈጥሮን በተመለከተ ሦስት ዓቢይ ቁምነገሮች ይነገራሉ። እነሱም ተፈጥሮ ማለት ወቅቶች ዘመናት ሰዎች አራዊትና እጽዋት በሙሉ ጊዜያዊና ኃላፊ መሆናቸው። እነዚሁ የተፈጥሮ ግለኛ ወኪሎች በስቃይ ዑደት ውስጥ መመላለሳቸውና በተፈጥሮ ውስጥ የሚከናወኑ ሁነቶች በምክንያትና ውጤት ሰንሰለት የተሰናሰሉም ያልተሰናሰሉም መሆናቸው ነው። ... እየተከተልከኝ ነው? ...

 

ታሪኩ:- በሚገባ ቀጥልልኝ

ዓለማየሁ:- ሐይኩ የሚጻፈው ስለተፈጥሮ ነው ብለናል። ታዲያ በሐይኩ ውስጥ የሚወሳ የቅጠላት መርገፍ፤ ያበቦች መጠውለግ የወንዞች መጉደል የጸሐይ መጥለቅ ወዘተ ተፈጥሮ በስቃይ ዑደት ውስጥ መመላለሷን ያመለክታል። የወቅቶች መፈራረቅ የዘመናት ጉዞ የአበቦች መፍካት የጸሐይ መውጣት የኅጻናት መወለድ የፍጡራን ተራክቦ ወዘተ ደግሞ ነገሮች በሙሉ ጊዜያዊና ኃላፊ መሆናቸውን እንዲሁም የተፈጥሮ ክስተት ሁሉ በምክንያትና ውጤት ሰንሰለት የተሰናሰለም ያልተሰናሰለም መሆኑን ያመለክታል ሲሉ የሐይኩ ተንታኞች ያስረዳሉ። ለዚህም ነው ሐይኩን ከቡዲዝም ጋር የሚያዛምዱት።

 

ታሪኩ፦ አሁንም ከመጽሐፍህ መግቢያ ልጥቀስና ሐይኩ ለመጻፍ የተነሳሳ ሐይካቢም ከተፈጥሮ ጋር መዋደድ መፋቀር መተጫጨት በስጋ ወደሙም መጋባት አለበት ትላለህ፤ ታዲያ አንድ ሰው ሐይኩን ለመጻፍ ተፈጥሮን ከመውደድ በተጨማሪ የቡዲዝምን ፍልስፍና ማወቅ አለበት ማለት ነው?

ዓለማየሁ፦ በፍጹም የቡዳን ትምህርት ምንም ሳያውቁ ድንቅ ሐይኩ መጻፍ ይቻላል። ለዚህም ነው ሐይኩና ቡዲዝም ባህርያዊ የሆነ ትስስር አላቸው የሚባለው።

 

ታሪኩ:- ሐይኩን ለመጻፍ የተነሳ አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ ቢኖር ምን ትመክረዋለህ? የአጻጻፍ ጥበቡን ከማን መማር ይችላል?

ዓለማየሁ:- ሐይኩን መጻፍ የሚማሩት ትምህርት ቤት በመግባት ወይም ታላላቅ መጻህፍትን በማንበብ ወይም የቡዳን አስተምህሮ በመሸምደድ አይደለም ባሾ እራሱ እንዳለው Learn of the bamboo from the bamboo and learn of the pine from the pine tree ባሾ ይህን ያለው ድንቅ የሐይኩ ጸሐፊ ለመሆን በየእለቱ ቸል የምንላቸውን የተፈጥሮ ክስተቶች አትኩረን ብናስተውላቸውና ብንመራመርባቸው ከነሱ ብቻ ብዙ መማር እንችላለን ሊል ፈልጎ ነው። ሐይኩ እዚያው ጉርስ እዚያው ትፍት የሚደረግ የቅኔ ቤት ነው። ብዙ ማሰላሰልና ቃላት መምረጥ ማጋነን ወይም ማኮሰስ ሃሳቡን ማብሰልሰልና መሰለቅ የሐይኩ ጸሐፊ ስራ አይደለም። ጀማሪ ሐይካቢ ሌላው እራሱን ማስተማር ያለበት አቅልሎ መጻፍን መልመድ ነው። ቃላት መቆጠብን በፊደል ስእል መሳልን መልመድ ያስፈልጋል። የቡዲዝም ትምህርት ማንም ሊረዳው በሚችል ቀላል ቋንቋ ነውና የተጻፈው መለስ ቀለስ እያሉ እሱን ማንበብም የሚጎዳ ነገር አይሆንም።

 

ታሪኩ:- እንዲያው ሐይኩ ቀላል የግጥም ዘር ነው ተባለ እንጂ ለኔ ቀላል ሆኖ አላገኘሁትም። አንድ ሰው እንደአንባቢ ሐይኩ ሲያነብ በቀላሉ ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?

ዓለማየሁ:- ከራሴም ልምድ ከሌሎች ሰዎች ተሞክሮም እንደተረዳሁት ሐይኩን አንብቦ ለመረዳትና ለማጣጣም ልምምድ ይጠይቃል። ይህ አይነቱ ልምምድ አስፈላጊ የሆነው ታዲያ ሐይኩ በባህርይው ከብዶ ሳይሆን ነገርዬው እንግዳ ጥበብ በመሆኑ ብቻ ነው። ሐይኩ እንደለመድነው መደበኛ የግጥም አይነት ስሜትና ትርጓሜ የለውም። የሐይኩ መጽሐፍ የፎቶግራፍ አልበም ማለት ነው። በያንዳንዷ ሐይኩ አንባቢ መፈለግ ያለበት ምስል ነው። ባለሐይኩው የቀዳውን የተፈጥሮ ትእይንት ማየትና ያቺን ቅኔ በወለደበት ቅጽበት የተሰማውን ስሜት ለማግኘት መታተርና መፈለግ ነው የሐይኩ አንባቢ ፈንታ።

 

ታሪኩ:- ለዚህ ቃለምልልስ ስዘጋጅ ስለሐይኩ ትንሽ ለማንበብ ሞክሬ ነበር። ጃፓን ውስጥ ከዘመናት በፊት የተጀመረው ሐይኩ ዛሬ ላይ እንዲህ አይነቱን ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዴት ሊያገኝ ቻለ?

ዓለማየሁ፦ በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝኛና በሌሎችም የእስያና የአውሮፓ ቋንቋዎች በርካታ የሆኑ ሐይኩዎች በየእለቱ ይጻፋሉ ይታተማሉ። የአሜሪካ ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች ሐይኩን ለልጆቻቸው በሚገባ ያስተምራሉ። ሐይኩን ዛሬ ድረስ ተወዳጅ የግጥም ዘር ያደረገው ቀለል ያሉ ቃላት መጠቀሙ ተፈጥሮን ዓይነ ጉዳዩ አድርጎ መነሳቱ እንዲሁም በጥቂት ስንኞች መቋጨቱ ይመስለኛል። በዚህ ጥድፊያ በተዋከበ ዓለም ውስጥ የነ ሼክስፒርን ዎርድስዎርዝን ብሌክን ዊትመንን ፑሽኪንን እጹብ ድንቅ ቅኔዎች ማን ትእግስት ኖሮት ያነባል?

ሐይኩ 42

ግርማ ሌሊት

ሙሉ ጨረቃ የደመና አይነርግብ አጥልቃ

ከዋክብት ሙድ ያዙባት

ሐይኩ ገፅ 29

 

ታሪኩ:- በሐይኩ ላይ ተጨማሪ ጥያቄ ካለኝ እመለስበት ይሆናል፤ ከዚያ በፊት ግን አንድ ጸሐፊ ካገሩ ከወጣ ከባህር እንደወጣ አሳ ነው የሚባል አባባል አለ። ይህ አባባል የፈጠራ ችሎታውና ደጋግሞ የመጻፍ ዕድሉ ይመክናል ለማለት ይመስለኛል። በዚህ ረገድ አንተ ከጽሁፍ ስራህ የተለየህ እንዳልሆንክ የምታሳትማቸው መጽሐፎች ይመሰክራሉ ይህ እንዴት ሊሆንልህ ቻለ?

ዓለማየሁ:- ለመጻፊያ ጊዜ ወስኜ አላቅም። አገር ቤት ሳለሁም የምጽፈው አንዳንዴ ነው አሁንም የምጽፈው አንዳንዴ ነው። የምጽፈው ነገር ከመጣልኝ የትም ቢሆን ከመጻፍ አልታቀብም ለመጻፍ ብዬ የማደርገው ከመደበኛው ሩቲን የወጣ ነገር የለም። የወደድኩትን ብቻ አነባለሁ ሲመጣልኝም እጽፋለሁ።

 

ታሪኩ:- ስራዎችህን እንዳነበብኳቸው በዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ህይወትና አጠቃላይ ገጽታ ላይ ብዙ የጻፍክ አይመስልም ይህ ለምን ሆነ ትላለህ። ለወደፊቱስ ምን ታስባለህ?

ዓለማየሁ:- ካገሬ ከወጣሁ ገና ጥቂት ጊዜ ነው። ቶሎ ቶሎ መለስ እያልኩም ከምወዳት አገሬ እና ያለኝን ሁሉ ከሰጠኝ ማኅበረሰብ ፍቅር መቀላወጤ አልቀረም። ውስጤ አሁንም የሚኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የምነካበትና የምኮረኮርበት እሴት እዚያው አገር ቤት ያለው ነው። ከሆነልኝ ደግሜም ሰልሼም የምጽፈው ስላገር ቤት ጉዳይ ቢሆን ደስ ይለኛል። ምናልባት በውጭ አገር ከቆየሁና ኪናዊ ኩርኮራው ካለ ግን ስለዚሁ አገር መጻፍ እችል ይሆናል።

 

ታሪኩ:- ከገጣሚነት በተጨማሪ በጋዜጠኝነት ትታወቃለህ ጋዜጠኛ መሆን ለደራሲነት ምን የሚፈይደው ነገር አለ? ይህን ያመጣሁት እንደ በዓሉ ግርማ፤ ብርሃኑ ዘርይሁን ሌሎችም ብዙ መጥቀስ ይቻላል ያሉት ደራሲዎች ጋዜጠኛም ነበሩ እስቲ ስለሁለቱ የሙያ ዘርፎች መደጋገፍ ምን የምትለው ነገር አለ?

ዓለማየሁ:- ጋዜጠኛ ሁሉ ደራሲ ወይም ገጣሚ መሆን የሚችል አይመስለኝም። ጋዜጠኝነት በስራ ልምድና በትምህርት የሚያገኙት በፍላጎትና በሙከራ የሚያዳብሩት የተከበረ ሙያ ይመስለኛል። ደራሲነት ግን ከዚህ የተለየ ነው የድርሰት ትምህርት የተማረ ሁሉ ደራሲ መሆን የሚችል አይመስለኝም። ደራሲ ይወለዳል ልልህ ፈልጌ ነው። የሁለቱን ሙያዎች መደጋገፍን በተመለከተ ግን በጋዜጠኝነት ህይወት ማለፍ ለደራሲ ሃሳብን ለመቆጣጠር ቋንቋን ለማዳበርና ለመግራት ተጨማሪ ትምህርት ቤት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በጋዜጠኝነት ደጃፍ ሳያልፉ ግን አስደናቂ የመተረክ ችሎታቸውን ያሳዩ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ድንቅ ደራሲያን በዓለም ዙሪያ መኖራቸውን ልብ እያልን።

 

ታሪኩ:- ሌላው ጥያቄዬ ቋንቋን የተመለከተ ነው። ለህጻናትም ትጽፋለህ በወዲህ በኩል ደግሞ ግጥሞችህ አሉ። በግጥሞችህ ላይ የሚታየው የዳበረ የቃላት አጠቃቀም ሲሆን የኅጻናቱ ደግሞ ቀለል ብሎ ነው የተጻፈው። ይህ ከበድ ያለ ነገር ይመስለኛል። አንተ እንዴት ልታስማማው ቻልክ?

ዓለማየሁ:- ሕጻናት ልጆች መላእክት ነው የሚመስሉኝ። ልጆች በጣም ይገቡኛል። ከልጆች ጋር በመተያየት ብቻ እናበባለሁ። የሚያስቡትንና የሚወዱትን የፈለጉትንና ያልፈለጉትን ነገር ለማወቅ አፍታም አይፈጅብኝ። ስለዚህ ለነሱ ስጽፍ ትንሽ ለዘብ ትንሽ ጸዳ ትንሽ ፈካ ማለትን እየተማርኩ ነው። ይህም ሆኖ ግን ጥሩ የህጻናት ድርሰት ጸሐፊ ነኝ ብዬ አላስብም። ከህጻናት ገና ብዙ መማር ገና አብሬያቸው መሳቅና ከፍንደቃቸው ንጽህናን መውረስ ይጠበቅብኛል። ዓለምን በገራገር አይን መመልከትን ሰዎችን በእኩል አይን ማየትን ተፈጥሮን በግልቧ መረዳትን ከነሱ መማር እፈልጋለሁ።

ያላለቀ ግራፊቲ

ሳትፈልጋት ሳታውቀው እጅህ የገባች ሚዳቆ በሄደችበት ትከተላታለህ እንጂ አንተ ወዳሻህ አትመራትም። No matter how hard you may try, you have no control over your own life and your own destiny, like a piece of trunk on a mighty river…

Haiku page 44

 

BETSY AND THE SUPERCOPPTERታሪኩ:- BETSY AND THE SUPERCOPPTER አዲሱ መጽሐፍህ ነው ማነው ያተመልህ? የት ነው የታተመው? ታሪኩስ ስለምንድን ነው?

ዓለማየሁ:- ሰሞኑን የታተመችው የኔዋ አነስተኛ መጽሐፍ ያሳተማት ፐብሊሽ አሜሪካ የተሰኘ ሜሪላንድ ያለ አሳታሚ ነው። ታሪኩም ቤትሲ ስለምትሰኝ ስለ አንዲት ጎበዝ ተማሪ ነው። ታሪኩ በጥቂቱ አድቬንቸርን ማሳየትን በጥቂቱ ሞራልን ማስረጽን በጥቂቱ ደግሞ ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅን ያካተተ ነገር ይመስላል።

The moment she completed the sentence, the roof of the classroom slid and opened. All the kids and the teacher were surprised to see the roof open and as they were enjoying watching the clear sky, a helicopter appeared and the pilot called for Betsy with a loud speaker.

He said “Dear Betsy, here is my Supercopter, come aboard and I will take you to the place you wish to visit. I will take you to Paris and we will visit the Eiffel Tower.”

“What is a Supercopter and who are you?” Betsy asked

“I am Uncle Michael and I am in charge of rewarding kids who are diligent, obedient and nice. I could see you are the only student who started to complete the sentence and I will happily grant you your wish.”

Betsy and the Supercopter page 6

Betsy and the Supercopterታሪኩ፦ የዓለማየሁ ሩባያትን ከጻፍክ በኋላ ያሳተምከው ግራፊቲ ጥቂት የእንግሊዝኛ ግጥሞች አሉበት ቀጥሎ ደግሞ ሐይኩ ግማሹ እንግሊዝኛ ነው። የሰሞኗ BETSY AND THE SUPERCOPTER ሙሉዋን በእንግሊዝኛ ነው የተጻፈችው። ነገሩ እንዴት ነው ማለቴ የምን ጠጋ ጠጋ ነው?

ዓለማየሁ፦ አጋጣሚ ነው እንጂ ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር አይደለም። እንግሊዝኛ ለኔ በትምህርት በንባብና ከተናጋሪዎቹ ጋር አብሮ በመኖር ያገኘሁት ደባል ቋንቋ ነው። እንዳማርኛው እንዳሻኝ የምቦርቅበት ያለምኩትን የቃዠሁትን የተሰማኝን እና የተነካሁበትን ሁሉ የምተነፍስበት ቋንቋ አይደለም። ግን አንዳንድ ሃሳቦች አሉ በሃበሻ ቋንቋ እሺ ብለው የማይወለዱ፤ ቢወለዱም እንኳ ስሜት የማይሰጡና ባእድ ባእድ የሚሸቱ። እንደዚህ አይነቶቹ ሃሳቦች ወደኔ ከመጡ ብቻ ነው በእንግሊዝኛ የምሞክራቸው።

 

ታሪኩ:- በውጭ ያለው የኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ደረጃ በአንተ እይታ ምን ይመስላል ያገር ቤቱስ?

ዓለማየሁ:- ያገራችን ሥነጽሑፍ በተለይ ደግሞ ሥነግጥም እያደገ መሆኑ ነው የሚሰማኝ። አገራችን ድንቅ ባለቅኔዎችን እያፈራች ነው። ክብሩ ይስፋ ለጥበብ አምላክ! በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚታተሙ መጻሕፍት በቁጥርም በጥራትም እያደጉ መምጣታቸው ዘመኑ የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ እመርታ ያሳየበት መሆኑን የሚያመለክት ይመስለኛል።

 

ታሪኩ:- በስነግጥሞችህ ላይ ተጽእኖ ያሳደረብህ ኢትዮጵያዊ ገጣሚ ካለ ማነው?

ዓለማየሁ:- ድምቅ ብሎ የሚታይ ተጽእኖ ያሳደረብኝ ገጣሚ ያለ አይመስለኝም። ይህም የሆነው የመርጋትና አንድን ያጻጻፍ ብልሃት ሙጥኝ ብሎ የመያዝ ዝንባሌ ስለሌለኝ ይመስለኛል። ካንዱ ያጻጻፍ ብልሃት ወደሌላው መዝለሌ ከዚህ ክብር ሳይነሳኝ አልቀረም። በተረፈ የቀድሞዎቹ ያገራችን ገጣሚያን በሙሉ የግጥም አጻጻፍ ጥበብ መምህሮቼ ናቸው። አሁንም በመጠየቅ በመመርመርና በመፈለግ ላይ ነኝና ወጣቶቹ ገጣሚያንም ጭምር የኔ መምህራን ናቸው። ገጣሚዎቻችንን በሙሉ በተቻለኝ መጠን አነባቸዋለሁ አጠናቸዋለሁ እማርባቸዋለሁ።

ታሪኩ:- ስለ ቃለምልልሱ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ!

ዓለማየሁ:- እግዚአብሔር ያክብርልኝ ታሪኩ! ግን ሐይኩ ግጥም ኂስና ሕይወት አሁን የተወያየንባቸው ሁሉ እና ሌላም ብዙ ብዙ ብዙ ነገር መሆናቸውን እያብሰለሰልክ ልለይህ?


ታሪኩ ኃይሉ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!