ዳዊት ከበደ ወየሳ - አትላንታ

ምሽት ላይ ከአንዳርጋቸው ጽጌ ታናሽ እህት ጋር ቀጠሮ ነበረን። ወሬያችንን በስልክ ላለማባከን ስንል በአካል ተገናኝተን ለመጨዋወት ነው የተቃጠርነው። ከእስከዳር ጋር የሚኖረኝ ቀጠሮ የአሁኑን የአንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ ለመነጋገር ቢሆንም፤ ሳልወድ በሃሳብ ወደኋላ እንድመለስ መገደዴ አልቀረም። በምርጫ 97 ወቅት (ከዘጠኝ አመታት በፊት) አንዳርጋቸው ጽጌ በየእለቱ ወደ ቅንጅት ቢሮ በማምራት የማደራጀት እና የቅስቀሳ ስራዎችን ያከናውን ነበር። የሰኔ የመጀመሪያ ሳምንት ግን ወጣቶች መንገድ ላይ የሚረሸኑበት፤ የቅንጅት ደጋፊዎች የተባሉ ሰዎች በገፍ እየታፈኑ ወህኒ ያሚጋዙበት ወቅት ሆነ።

አንድ ቀን ለአንዳርጋቸው ጽጌ ስልክ ተደወለለት። ጓደኛው ዶ/ር ስለሺ ነበር። “ተገናኝተን ቡና እንጠጣ” አለውና አንዳርጋቸው ከቤት ወጣ። እንደወጣም ቀረ - አልተመለሰም። መንገድ ላይ የጠበቁት የወያኔ ደህንነት አባላት ዶ/ር ስለሺን ጨምረው ወደ ዝዋይ እስር ቤት ወሰዷቸው። እዚያ ከሌላው እስረኛ ተለይተው፤ በተለምዶ “ግንብ ቤት” የሚባለው ስፍራ ነበር የታሰሩት። ይህ ደግሞ እስረኞች ላይ አስፈላጊው እርምጃ የሚወሰድበት ቦታ ነው። አንዳርጋቸው እዚህ ሲገባ ከፍተኛ ድብደባ ደረሰበት። ገና እስር ቤት እንደገባ አንድ የወያኔ ካድሬ፤ አንዳርጋቸውን ደጋግሞ ጭንቅላቱና አይኑን በሰደፍ ስለመታው ለብዙ ግዜ አንድ አይኑ ላይ ብዥ የማለት ስሜት ፈጥሮበት ነበር።

እስከዳር ጽጌ… የአንዳርጋቸውን መታሰር ስትሰማ ከለንደን ወደ አዲስ አበባ አቀናች። እስከዳር በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ስታስታውስ እንዲህ ትላለች። “ዝዋይ እስር ቤት ልጠይቀው የሄድኩት ከወንድሜ ጋር ሆኜ ነበር። በር ላይ ማንን ለመጠየቅ እንደመጣን ነገርናቸው። ካሁን አሁን ይጠሩናል ብለን በማሰብ ቁጭ አልን። ነገር ግን ደቂቃዎች ነጎዱ። ሰአታትም ተቆጠሩ። እዛው ሆነን፤ ከኛ በኋላ የመጡ ሰዎች፤ ቤተሰባቸውን እየጠየቁ ሲመለሱ፤ እኛ ግን ቁጭ ብለን ቀረን።

“በር ላይ ለሚገኙት ፖሊሶች ሁኔታውን ብንነግራቸውም ሊረዱን የሚችሉ አልሆኑም። በዚህ መሃል አንድ ሲቪል የለበሰ ወጣት እኛ ወዳለንበት አካባቢ መጥቶ ቆመ። ወንድሜ ገና ሲያየው፤ ‘ይሄ ልጅ…’ ብሎ በጥንቃቄ ይከታተለው ጀመር።

በርግጥም እኛ ወዳለንበት መጥቶ ሁኔታችንን ሲሰልል የነበረው ወጣት የህወሃት ሰው ነው። ትንሽ ቆየና በእጅ ምልክት ጠራን። ‘እኛን ነው?’ ጠየኩት-በመገረም።

‘አዎ’ አለን - በትዕቢት ስሜት።

“ወደ’ሱ ስንሄድ… ‘አንዳርጋቸው አይመጣም። እናንተም አካባቢውን ለቃቹህ እንድትሄዱ’ ተባልን። እኛ የመጣንበትን ጉዳይ ሳንጨርስ የማንመለስ መሆኑን ነግረናቸው ትንሽ አንገራገርን። ‘ቢያንስ በህይወት መኖሩን ማወቅ እንፈልጋለን’ አልናቸው። በኋላ ላይ ሁኔታውን የሚያውቁ ሰዎች፤ ‘አንዳርጋቸው እና ከፍተኛ የቅንጅት አመራሮች ‘ግንቡ ቤት ውስጥ ናቸው። በአንዳርጋቸው ላይ ድብደባ ስለፈጸሙበት፤ ምናልባት ያንን እንዳታዩ ይሆናል ያላቀረቡት’ አሉን።

ምሽት ሲሆን… እስር ቤቱን ብቻ ሳይሆን፤ የዝዋይ ከተማንም ለቀን ሄድን። (በወቅቱ ስለተፈጠረው ግርግር… ተቀያሪ ልብስ እና ምግብ እንዳይገባ መከልከሉን፤ በተለይም ምሽት ላይ የዝዋይ ሰዎች እንዴት እንደተባበሯቸው የነበረውን ዝርዝር ታሪክ ለግዜው ሳንጠቅስ አልፈነዋል።)

የሚቀጥሉት ቀናት ለእስከዳር ጽጌ እና ለወንድሟ ከባድ የፈተና ቀኖች ነበሩ። (ስልክ ቁጥሩን እንዴት እንዳወቁት እስካሁን ይገርማታል።) በወንድሟ ስልክ ቁጥር ደውለውለት እና ‘ኢሚግሬሽን ቁጥር 87 እንድትመጣ’ ይሉታል። ወደ ኢሚግሬሽን አልሄደም። እነሱ ራሳቸው እሱ ወዳለበት መጥተው፤ “ዛሬውኑ አዲስ አበባን ለቀህ ውጣ።” አሉት።

“ነገ ወደ ለንደን ለመሄድ ትኬት ቆርጫለሁ።” ብሎ ቢያሳያቸውም፤ “ዛሬን ካደርክ ትታሰራለህ። ዛሬውኑ ወደ ኬንያ የሚሄድ አውሮፕላን አለ። መሄድ አለብህ።” ተብሎ በግድ አዲስ አበባን ለቅቆ እንዲወጣ ተደረገ።

በመጨረሻ ከብዙ ምልልስ በኋላ… እስከዳር አንዳርጋቸውን ዝዋይ እስር ቤት አግኝታ ተነጋገሩ። “ደበደቡህ እንዴ?” አለችው።

“ስንቱን ወጣት በየቀኑ ሲደበድቡ አይደለም እንዴ የሚውሉት? የኔ መደብደብ ምን ይገርማል?” አላት። በእንግሊዘኛ ማውራት ሲጀምሩ፤ የተመደበባቸው ጠባቂ፤ “በእናታቹህ ቋንቋ አውሩ” አላቸው።

“ምን ማለት ፈልገህ ነው?” አሉት።

“በፌዴራል ቋንቋ አውሩ” አላቸው (በአማርኛ ላለማለት የፈለገም ይመስላል)

አንዳርጋቸው የጠባቂው ሁኔታ ስላናደደው፤ “የፌዴራል ቋንቋ የሚከበር ቢሆንማ፤ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሆናቹህ ከጠዋት እስከማታ በራሳቹህ ቋንቋ ብቻ አታወሩም ነበር” አለው። እንዲህ እንዲህ አይነት በነገር መጎነታተል በብዛት ይስተዋላል። (የእስር ቤቱን ጉዳይ ትተነው ወደ ፍርድ ቤት ልንወስዳቹህ ነው)

በሶስተኛው ሳምንት አካባቢ እነ አንዳርጋቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ። በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ብዙ ወጣቶች ከተገደሉ በኋላ፤ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሚዲያ ላይ ወጥተው፤ ‘ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ነው የገደልናቸው’ ማለታቸው ይታወሳል። እነአንዳርጋቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ በሱ ላይ የተመሰረተው ክስ፤ “ባንክ ቤቶችን ለማዘረፍ አስተባባሪ” ተብሎ ነበር።

በወቅቱ ለፍርድ ቤቱ ሲናገር፤ “እኔ ታስሬ ስጠየቅ የነበረው፤ ታትሞ ገበያ ላይ ስለዋለው መጽሃፌ ነበር። አሁን ደግሞ እዚህ ፍርድ ቤት የምሰማው ነገር አዲስ ሆኖብኛል።” አለ። (በወቅቱ “ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጪ” የሚል መጽሃፍ አሳትሞ ነበር)

የዚያን ቀን ፍርድ ቤቱ አብዛኛውን እስረኛ በ500 እና አንድ ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ሲያደርግ፤ አንዳርጋቸው ጽጌ 3ሺህ ብር ዋስትና ከፍሎ እንዲፈታ ፍርድ ቤቱ ወሰነ።

እስከዳር ይህንን እለት፤ እንደትላንትና ነው የምታስታውሰው። መከፈል የሚገባውን ብር ከፍላ፤ የፍርድ ቤቱን የማስፈቻ ዋራንት ወረቀት ይዛ እስር ቤት ከደረሱት ውስጥ እሷ የመጀመሪያዋ ነበረች። ወረቀቱን በር ላይ ለፖሊሶቹ ሰጥታ፤ የወንድሟን መፈታት ትጠብቅ ጀመር። ምንም ነገር የለም። ከሷ በኋላ የመጡ ሰዎች ከተፈቺዎች ጋር ወደየቤታቸው ሲሄዱ፤ እስከዳር ግን እዚያው ቀረች። በመጨረሻ “ምንድነው ነገሩ?” ስትል፤ ያስገባችው የፍርድ ቤት ማስፈቻ ዋራንት የሌላቸው መሆኑ ተነገራት። የመፈሻውን ወረቀት “አላየን” - አሏት።

ከፍተኛ ጭቅጭቅ ተነስቶ ሊያስሯት ሲሉ፤ እስረኛ ለማስፈታት የመጡት ሰዎች ተከላከሉ። “እኛንም አብራቹህ እሰሩን እንጂ አታስሯትም” አሏቸው። በዚህ አይነት መሸ።

በሚቀጥለው ቀን… በጠዋት ስፍራው ድረስ ሄደች። የእስር ቤቱ ደጃፍ ስራ እስኪጀምር መኪናዋን ውጪ ቆመች። መጀመሪያ ቀን ያገኙት ወጣት ህወሃት ወደሷ መምጣት ብቻ ሳይሆን ፊቷ ላይ በጣም ተጠግቶ፤ “እዚህ ጋር መኪና ማቆም አይቻልም” አላት። ልትመልስለት ስትል፤ አንዲት አሮጊት ክርኗን ጎትተው “ልጄ በመድኃኒአለም ምንም እንዳትመልሺለት” እያሉ አጥብቀው ጎተጎቷት። መንገዱን አሻግራ አቆመች፤ “እዚያም ተከትሎ መጥቶ አስነሳት። በዚህ አይነት አራት ግዜ አስነሳት።

የፍርድ ቤት ትእዛዝ መጥቶም አንዳርጋቸው ጽጌን ለመፍታት አልፈለጉም። ጠዋት የጀመሩ እስከ-ከሰአት ድረስ እስከዳርን ብዙ አጉላሉዋት። እስር ቤቱ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለሆነ፤ በር ላይ የሚጠብቁት ኦሮሞዎች ሲሆኑ አሳሪና ፈቺዎቹ ግን የህወሃት ሰዎች ነበሩ። አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈታ ትእዛዝ ተሰጥቶም ቢሆን፤ አለመፍታታቸው እርስ በርስ ጭምር አነጋገራቸው። በመጨረሻ አሳሪዎቹ ላይ ግፊት በመደረጉ አንዳርጋቸው ጽጌ ተፈታ።

አንዳርጋቸው ከተፈታ በኋላ አገሩን ለቅቆ እንዲወጣ ቢጠየቅም “የጀመርኩትን መጨረስ አለብኝ” በማለት ከሶስት ሳምንታት በኋላ ነው ኢትዮጵያን ለቅቆ የወጣው። ሰንአ፣ የመን ላይ ታፍኖ እስከሚወሰድ ድረስ፤ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ አልተመለሰም።

እርግጥ ከዘጠኝ አመት በኋላ ሰንአ የመን ላይ መታፈኑን ስንሰማ ነገሩን ማመን አቃተን። የየመን መንግስት ለኢትዮጵያ አሳልፎ እንደሰጠው ስናውቕ ደግሞ፤ ነገሩ አበገነን። ከዚህ ቀደም በታሰረበት ወቅት የተፈጸመበት ኢሰብአዊ ተግባር በድጋሚ እንደማይፈጸም ለማወቅ ምንም ዋስትና ስለሌለን፤ የዳግም እስሩን ጉዳይ ይበልጥ አሳሳቢ ያደገዋል።

ከታናሽ እህቱ ከእስከዳር ጽጌ ጋር ለመገናኘት ምክንያት የሆነን የአሁኑ ዳግም እስረኛ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ዘለግ ላለ የጨዋታ ግዜ ወደ ስታርባክስ ስንሄድ… ለመጨረሻ ግዜ ከአንዳርጋቸው ጋር በአካል የተለያየንበትን አጋጣሚ እያጫወትኳት ነበር።

ከአንዳርጋቸው ጽጌ ጋር የቅንጅት አለም አቀፍ አመራር ውስጥ ሆነን አብረን ሰርተናል። አስራ ሁለት የነበርነው ሰዎች ተከፋፍለንና ተመናምነን ስድስት አመራሮች ስንቀር የቅንጅት ፓርቲ የመጨረሻው ምዕራፍ እየተገባደደ እንደሆነ ልቦናችን እያወቀው ነበር። የመጨረሻዎቹ ስድስት ሰዎች የታሰሩት የቅንጅት መሪዎች እስኪፈቱ ድረስ፤ በፕ/ር ይስሃቅ ኤፍሬም አማካኝነት ስንደራደር ቆይተን መሪዎቹ ሲፈቱ ራሳችንን አከሰምን። ከኛ ማክሰም ጋር ተያይዞ… በወቅቱ በርካታ የወሬ አውሎ ንፋሶች ይነፍሱ ነበር። በዚህ የወሬ ወጀብ መሃከል የዋሺንግተን ነዋሪ ለስድስታችን የክብር አሸኛኘት ሲያደርግልን፤ ሁላችንም ሩጫችንን የጨረስን ያህል ነበር የተሰማን። አንዳርጋቸው ግን የትግል ሩጫውን እንደገና ጀመረ።

ግንቦት ሰባት ሲመሰረት በተከታታይ ስንገናኝ ቆየንና በመጨረሻ ተለያየን። ስራዎች እና ያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን እንደጓደኛ ሳይሆን፤ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከዳር ሆኜ ማየት እና መስማት ጀመርኩ። በዚህ የዳር ቆሞ ምልከታ ላይ እያለሁ ነው፤ የመታሰሩን ወሬ የሰማሁት። የመታሰሩንም ሆነ፤ ወደ ኢትዮጵያ የመላኩን ዜና ማመን እያቃተኝ ነበር የጻፍኩት።

ከአንዳርጋቸው እህት ጋር ተገናኝተን ሻይ ቡና ለማለት ወደ ስታር ባክስ ስናመራ ከአንዳርጋቸው ጋር የነበሩኝን የአብሮነት ቆይታ፤ በተፍታታ ሁኔታ እያጫወትኳት ነበር። የአትላንታ የምሽት አየር ደስ ይላል። እናም ውጭ በረንዳው ላይ ቁጭ ብለን ጨዋታችንን ጀመርን።

አብዛኛው ጨዋታችን በአንዳርጋቸው ጠንካራ ሰብእና ላይ የተመሰረተ ነበር። ከዚያም በመነሳት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስለተላለፈው የአንዳርጋቸው ጽጌ ንግግር ጠየኳት። “ንግግሩን ሰማሁት። ፊልሙ በጣም ኤዲት እንደተደረገ ያስታውቃል። የሱ ያልሆነ ድምጽም አለበት። ለምሳሌ በንግግሩ መሃል፤ ‘ቱሪስት’ የምትል ቃል ገብታለች። ከንግግሩ ጋ ምንም ግንኙነት የሌለው ነገር ነው። ንግግሩ እና በመጨረሻ ያሳየው ፈገግታም ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን ማንም ሊረዳው ይችላል። ከዚያ በተጨማሪ ይህ ቪዲዮ በድብቅ ካሜራ የተቀረጸ ነው የሚመስለው። ሌላው ነገር ደግሞ ቪዲዮውን ያነሱት ‘ያዝነው’ ባሉበት ቀን ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም አንዳርጋቸው ከአንድ ቀን በኋላ ጺሙ ቶሎ ያድጋል። እዚህ ላይ አይተኸው እንደሆነ ግን፤ ጺሙን ተስተካክሎ ያለበት ነው የሚታየው። ስለዚህ ከዚህ የመጀመሪያ ቀን ቪዲዮ በኋላ ምን እንደተፈጸመ ለማወቅ አይቻልም። ምንም ይሁን ምን ግን…

ንግግሩን ስሰማ ደስ ነው ያለኝ። ለነገሩ እንደቤተሰብ ወይም እንደእህቱ ቅድሚያ የምሰጠው የሱን ደህንነት ነው። በቅድሚያ እሱ ደህና ይሁን እንጂ፤ ቀሪውን ነገር አብረን የምናየው ይሆናል። አንዳርጋቸው ህይወቱን በሙሉ ለራሱ አልኖረም። ከወጣትነት እድሜው ጀምሮ ለህዝብ የበላይነት እና ለፍትህ ሲሟገት ነው የኖረው። ይህን አስተሳሰቡን በምንም አይነት መንገድ ሊቀይረው አይችልም።

ጥያቄ- ለመጨረሻ ግዜ አንዳርጋቸውን በአካል ያገኘሽው መቼ ነው? ስሜቱስ እንዴት ነበር?

መልስ- ከአንዳርጋቸው ጋር በአካል የተገናኘነው ባለፈው አመት ሴፕቴምበር ላይ፤ አንድ አፍታ አትላንታ መጥቶ ነው። እንደበፊቱ የተጨናነቀ መንፈስ አላየሁበትም። በፊት ሳገኘው ሁልጊዜ ያልጨረሰው ነገር እንዳለ ሆኖ ይሰማው ነበር። ባለፈው ሳገኘው ግን የተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ነበር። የጀመረውን ጉዳይ እንደጨረሰ ነበር የሚሰማው።

ጥያቄ- መታሰሩን ስትሰሚ ምን አሰብሽ?

መልስ- መታሰሩን ስሠማ፤ የታሰረበት ቦታ ሄጄ ለመጠየቅ ነበር የፈለኩት። ‘ወደየመን ላኩኝ’ አልኳቸው። ሆኖም ‘አንቺ ሴት ነሽ። አረብ አገሮች ደግሞ በሴት ላይ ያላቸውን ንቀት የምታውቂው ነው…’ የሚል አይነት ምላሽ ነው ያገኘሁት። ምንም ሆነ ምን ግን… ሴትም ሆነ ወንድ ወደ የመን ሳይሄድ፤ አንዳርጋቸው ወደ ኢትዮጵያ መወሰዱን ሰማሁ። (ቁጭት ፊቷ ላይ ይታያል)

ጥያቄ- አሁን ያለውን እንቅስቃሴ እንዴት ታይዋለሽ?

መልስ- በቅድሚያ የአንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ እንደራሳቸው ጉዳይ አድርገው እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን በሙሉ ለማመስገን እወዳለሁ። ከዚያ በተረፈ አንዳንድ ሰዎች እየደወሉ የሚያለቅሱ አሉ። ለቅሶው ለማንም አይጠቅምም። መጠንከር አለብን።

ከስሜታዊነት ርቀን በሰከነ መንፈስ ስራችንን መስራት ይኖርብናል። ለምሳሌ በአገር ውስጥ ወንጀል የሰሩ፤ አሁን ደግሞ በውጭ አገር ጥገኝነት ጠይቀው የሚኖሩ፤ የኢህአዴግ ቀንደኛ ሰዎችን በያለንበት አገር ለፍርድ ማቅረብ መቻል አለብን። ይህ ሲሆን ነው ደጋፊዎች እና ተባባሪዎቻቸው ቅስማቸው የሚሰበረው። በስሜታዊነት ተነሳስተን እንድንሳደብ እና እንድንደባደብ ነው የሚፈልጉት። ከዚህ ነጻ መውጣት አለብን። ከስድብም ሆነ ከድብድብ ነጻ ሆነን በህጋዊ መንገድ ማሸነፍ ይኖርብናል።

ጥያቄ- አንቺ እንደአንዳርጋቸው እህትነትሽ ብቻ ሳይሆን፤ እንደኢትዮጵያዊነትሽ ምን ለማድረግ አቅደሻል?

መልስ- ቅድም እንዳልኩት፤ አንዳርጋቸው ‘አሁን እረፍት እፈልጋለሁ’ ብሏል። አዎ እረፍት ያስፈልገዋል። ለፍትህ ሲል እድሜውን የጨረሰው በትግል ነው። ከዚህ በኋላ በምናምንበት መንገድ እሱ የጀመረውን ትግል ከዳር ማድረስ ይኖርብናል። እኔ በበኩሌ ፍትህ ለማግኘት የማያቋርጥ ስራ መስራት እንዳለብኝ አውቃለሁ። ይህንንም ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም።

(ከእስከዳር ጽጌ ጋር አብረን ሆነን ብዙ ስልኮች ይደውሉላት ነበር። አንዱንም አልመለሰችም። የሚጮኸውን ስልክ አጠፋችውና ወሬዋን ቀጠለች)

ይገርምሃል። ብዙ ሰዎች የሚደውሉት ሊያጽናኑኝ ነው። ይህን ነገር አልወደውም። አንዳርጋቸው በህይወት አለ። አንዳንዶች እየደወሉ ስሜታቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው የሚያለቅሱ አሉ። እኔ መልሼ እነሱን አጽናናቸዋለሁ። ይህ ግን መሆን የለበትም። በስራ እንጂ፤ በማልቀስ የምናመጣው ለውጥ የለም።

(ብዙ ተጨዋወትን። በመጨረሻም እንዲህ አለች።)

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለፍትህ የቆሙ ሰዎች፤ በፍትህ ስም ሲታሰሩ እና ሲንገላቱ፣ ሲገደሉ እና ሲሰደዱ ኖረዋል። አንዳርጋቸው ጽጌ ለፍትህ በመቆሙ ምክንያት የታሰረ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አይደለም። እነ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙ፣ አንዷለም አራጌ እና ሌሎችም ለፍትህ በመቆማቸው በፍትህ ስም “ሽብርተኛ” ተብለው ታስረዋል። አሁን እንደምንሰማው ደግሞ ሌሎችም እየታሰሩ ነው። እናም አንዳርጋቸው ብቻ አይደለም ለፍትህ ሲል የታሰረው ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል። በሺህ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች ደግሞ ፍትህ ተርበው አሁንም ድረስ አሉ። እናም በመቶ ለሚቆጠሩት እስረኞች ብቻ ሳይሆን፤ ፍትህ ላጡት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጭምር መቆም አለብን። እናም “ለአንዳርጋቸው ጽጌ አታልቅሱ” የሚል ጠንካራ መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።

መሽቷል። ከምሽቱ 10፡30 ነው። የእስከዳር ስልክ እንደገና መጮህ ጀመረ። ሴት ልጇ ናት። እሷን አውርታ እንደጨረሰች… ሁለታችንም ወደቤት ለመሄድ ተነሳን።

ስልኩን ከዘጋችው በኋላ ስለልጆቻችን ብቻ ሳይሆን ስለአንዳርጋቸውም ልጆች አወራን። “የአንዳርጋቸው ልጆች ስንት አመት ሆናቸው?” አልኳት።

“ሰባት አመት አለፋቸው።” አለችኝ እስከዳር። ጊዜው እንዴት ይሮጣል?

በቅንጅት አለማቀፍ አመራር ውስጥ እያለን የተወለዱ መንታ ልጆች ናቸው። አንዳንዴ ልጆቹን እያስተኛ ስለአገር ጉዳይ እናወራለን… ስለፍትህ እንወያያለን። ሰባት አመታት ወደኋላ ተመለስኩ።

ከእስከዳር ጽጌ ጋር ከመለያየታችን በፊት ስለፍትህ አወራን - ፍትህ የእስከዳር ልጅ ስም ነው (በአማርኛ)። የ13 አመቷ ፍትህ በትምህርት ቤቷ ብቻ ሳይሆን በስቴት ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያመጣች ልጅ ናት። ገና ካሁኑ በበጋ ወራት ለጎበዝ ተማሪዎች የሚሰጠውን የዩኒቨርስቲ ኮርስ እየወሰደች ነው። ወደፊት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት መሆን ነው የምትፈልገው። ፍትህ ከፍትህ ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ከአጎቷ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ጥብቅ የሆነ ትስስር አላቸው። ወሬያቸው ስላነበቡት መጽሃፍ ነው። ሁልግዜም የታሸገ ነገር በፖስታ ከመጣ፤ አንዳርጋቸው ለፍትህ የላከላት መጽሃፍ ነው የሚሆነው።

ታዳጊዋ ፍትህ የአንዳርጋቸው ጽጌን መታሰር እንዳትሰማ ጥረት ቢደረግም፤ ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዙ ድረ ገጾች ስለሱ ስለሚያወሩ ዜናውን መደበቅ አልተቻለም። እናም የመታሰሩን ዜና ስትሰማ የምታዝን መስሏቸው ነበር። ፍትህ ግን “እንዲያውም አጎቴ በመሆኑ ኮራሁበት” ነው ያለችው። ዛሬም ሆነ ነገ አጎቷ አንዳርጋቸው ፍትህ እንዲስተካከል መታገሉን ለጓደኞቿ ጭምር በኩራት ትናገራለች።

ዛሬ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማሸማቀቅ እና አንገት ለማስደፋት እነአንዳርጋቸው ጽጌን እና ሌሎችንም ሊያስሩ ይችላሉ። ይህ እስር ግን ለፍትህ ሲባል የተገኘ ሊሻን ተደርጎ ሊቆጠር ይገባዋል።

እያለቀስን ሳይሆን… አንገታችንን ቀና አድርገን፤ በምናምንበት መንገድ… “ትግሉ ይቀጥላል!” ማለት ይኖርብናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!