ይርጋ አበበ

Prof Fikre Tolossa. ፕሮፌሠር ፍቅሬ ቶሎሳ

ፕሮፌሠር ፍቅሬ ቶሎሳ በቅርቡ “የኦሮሞ እና አማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በሚል ርዕስ አንድ ታሪካዊ ዘውግ የተላበሰ መጽሐፍ አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል። ፕሮፌሠር ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በኢትዮጵያ ጥንታዊና የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ስለ ኢትዮጵያ የቆየ የፌዴራሊዝም አስተዳደር ሥርዓት፤ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ በስፋት ስለሚነገረው “የአማራ ገዥ መደብ” እና የኦሮምኛ ቋንቋ ለጽሁፍ የላቲን ፊደልን (ቁቤ) መጠቀሙን በተመለከተ እንዲሁም ስለ መጽሐፋቸው ይዘት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የቃለ ምልልሳችንን ሙሉ ቃል ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፦ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት የታሪክ መጽሐፍ (የኦሮሞ እና የአማራ ትክክለኛ ማንነት) አወዛጋቢ ነው እየተባለ ይነገራል። ለመሆኑ ለእርስዎ የደረሰዎት ግብረ መልስ (Feedback) ምን ይመስላል?

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- የመጀመሪያው ዙር አልቆ (5000 ቅጂ) ሁለተኛው ዕትም ዛሬ (ዓርብ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም.) ለገበያ ቀርቧል። ከአንባቢያን የሚደርሰኝ አስተያየት በጣም አስደሳች ነው። “መጽሐፍህ ፍቅርን ይሰብካል ማንነታችንን አሳውቆናል” እያሉ ነው የሚነግሩኝ።

ሰንደቅ፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የተለመደ አንድ የመጽሐፍ ገበያ አለ። በሽፋን ስዕል እና ርዕስ በማጮህ ገበያ በመሳብ መሸጥ። የእርስዎ መጽሐፍስ እንዲህ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከገበያ አልቆ በድጋሚ ለመታተም ያበቃው እውነት በይዘቱ ብቻ ነው ማለት ይቻላል?

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- አንባቢያን መጽሐፉ በጣም አስደስቶናል። የኢትዮጵያን ታሪክ እንደገና የሚጽፍ ነው፤ እንዲያውም አብዮታዊ ነው። ሌላው ደግሞ መጽሐፉ ጥሩ መልዕክት አለው እያሉኝ ነው። አሁን በኢትዮጵያ ያሉት እና በውጭ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ከፍ ሲል የዛሬ 4000 ዓመት ኢትዮጵ ከሚባል በስሙ ኢትዮጵያ ብሎ ያስጠራት ጠቢብ ሰው ነበር። ጠቢብ ብቻ ሳይሆን ሊቀ ካህንም ነበር። እሱ የወለዳቸው አስር ልጆቹ አስር ጎሣ ሆነው እየተባዙ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁሉም ሰዎች (ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች) በውስጣቸው የዚያ ሰው (የኢትዮጵ) ደም አለ። የሁላችንም አባት ኢትዮጵያ ሲባል፣ እናታችን ደግሞ እልቅዮፓ ጊዮን ትባላለች። እኛ ሁላችንም ከእነሱ ነው የወጣነው። ስለዚህ እኔ በማስረጃ ከዚያ መውጣታችንን በማቅረቤ ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የአንድ ዘር ፍሬዎች መሆናችንን ስለገለጽኩኝ፤ አዲስ ሃሳብ ይዞ ቀርቧል መጽሐፉ። እንዲሁም እኛ የአንድ ዘር ፍሬዎች ከሆንን ይህችን የጋራ ሀገራችንን ተሳስበንና ተዋደን በፍቅር እና በሰላም ልንኖርባት ይገባል የሚል የፍቅርና የሰላም መልዕክት ስላለው ነው ህዝቡ የወደደው።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአማራ እና በኦሮሞ መካከል አለመግባባት እና እንዲያውም እራሳቸውን አያውቁትም። ለምሳሌ ኦሮሞዎቹ ከእስያ ፈልሰው በማዳጋስካር በኩል ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው እየተባለ ይወራ ነበር። እነሱም አምነውበት ነበር። አማራንም ደግሞ እንደ ተክለጻድቅ መኩራያ ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች ከደቡብ ዐረቢያ የመጣ ነው ብለው ያስቡ ነበር። እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች የተሳሳቱ መሆናቸውን እኔ በምርምር አረጋግጫለሁ። ሁለቱም ነገዶች ከአንድ ግንድ የወጡ ናቸው። በዚህም ምክንያትም መጽሐፉ በሰዎች ዘንድ ሊወደድ ችሏል።

ሰንደቅ፦ የኦሮምኛ ቋንቋ የጽሁፍ ፊደል የሚጠቀመው የላቲንን ፊደል (ቁቤ) ነው። ቁቤን መጠቀም ለምን አስፈለገ? ከቁቤ ይልቅ ሌላ ኢትዮጵያዊ ፊደል መጠቀም አይቻልም ነበር?

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- ኦሮምኛን በቁቤ መጻፍ የተጀመረው በሐረር አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሚሲዮናዊያን የአካባቢውን ሰው ለማስተማር የኢትዮጵያን ፊደል ስለማያውቁ ራሳቸው በላቲን ጽሁፍ ማስተማር ጀመሩ። በወቅቱ ከሚሲዮናዊያኑ ጋር አብሮ ይሠራ የነበረው ኃይሌ ፊዳ፤ የላቲኑን አጻጻፍ ከተመለከተ በኋላ “ኦሮምኛ ቋንቋ መጻፍ ያለበት በቁቤ ነው” እያለ ይናገር ነበር። ከዚያ የተነሳ ነው ኦሮምኛን በቁቤ ቋንቋ መጻፍ የተፈለገውና የተጀመረው።

ከቁቤ በተሻለ በሌላ ሀገርኛ ፊደል መጠቀም አይቻልም ነበር ወይ ላልከው፤ እኔም መጽሐፌ ላይ ገልጨዋለሁ፤ ከቁቤው ይልቅ ግዕዙን መጠቀም በብዙ መንገድ የተሻለ ነበር። ይህን ለማሳየትም መጽሐፌ ላይ እንደገለጽኩት ሁለቱን ገጽ የግዕዝ ፊደል በቁቤ ስጽፈው ወደ ስድስት ገጽ ደርሷል። ይህ የሚያሳየው ቁቤን ከመጠቀም ይልቅ ግዕዙን መጠቀም ከጊዜ፣ ከኢኮኖሚ እና ከአናባቢ (ፕሮናውንሴሽን) አንጻር የተሻለ እንደነበረ ነው።

ሰንደቅ፦ መጽሐፍዎን በኦሮሞ እና አማራ ህዝብ የማንነት ታሪክ እንዲያጠነጥን ያደረጉት በሁለቱ ብሔሮች መካከል ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ተመልክተው ገበያውን አጥንተው ነው የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ። በአጭሩ መጽሐፉን ያዘጋጁት ገበያውን ትኩረት አድርገው ነው?

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- መጽሐፉ ላይ በጣም ተዘርዝሯል የሁለቱ ብሔሮች ዝምድና። በኢትዮጵያ ህዝብ ዝምድና በጥልቀት ብጽፍ ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን ሁለቱ ህዝቦች (ኦሮሞ እና አማራ) በቁጥርም በዛ ያሉ ስለሆኑና በመካከላቸውም አለመግባባት ተፈጥሮ፤ አለመተዋወቅ አለመግባባት በመፈጠሩ ምክንያት እነዚህ ህዝቦች እርስ በእርሳቸው ሲቃረኑና ሲፋተጉ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጦሱ ይተርፋል። ምክንያቱም ሁለት ዝሆኖች ቢጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው እንዲሉ፤ ሁለቱ በሰላም መኖር ካልቻሉ ሌሎቻችን በሰላም እንኖራለን ማለት ዘበት ነው። ስለዚህ እነዚህ ሁለቱ ህዝቦች እውነተኛ ማንነታቸውን ቢያውቁ በኢትዮጵያ ሰላም እኩልነት እና ፍቅር እንዲሰፍን ይረዳል። እኔም ይህንን በማሰብ ነው ያዘጋጀሁት እንጂ ለገበያ አይደለም። ለገበያ ብዬ አራት ዓመት ሙሉ ገቢዬን እያጣሁ ጥናት (ሪሰርች) አላደርግም። ከመጽሐፉ የማገኘው ገንዘብ አሜሪካን ሀገር እያስተማርኩ ከማገኘው ጋር ሲወዳደር ሰፊ ልዩነት አለው። በዚህ ላይ ደግሞ መጽሐፉ ከያዘው ጭብጥ አኳያ ዋጋው ከ200 ብር ማነስ የሌለበት ቢሆንም ህዝብ በቀላሉ ገዝቶ እንዲያነበው ሲባል ነው ዝቅ እንዲል (91 ብር ነው) የተደረገው።

ሰንደቅ፦ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በስፋት የተለመደ መግለጫ አለ “የአማራ ገዥ መደብ” የሚል። ለመሆኑ የአማራ ገዥ መደብ የሚባል ሥርዓት በኢትዮጵያ ነበረ? ከነበረስ በየትኞቹ ዘመናት ነው?

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- የአማራ ገዥ መደብ የሚመባል ሥርዓት በኢትዮጵያ ታሪክ ተፈጥሮ አያውቅም። በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ ከንግሥተ-ሳባ ልጅ ከቀዳማዊ ሚኒልክ እስከ ዮዲት ጉዲት (አስቴር) መነሳት ድረስ ያለው 1000 ዓመት የሰለሞን ስርወመንግሥት ይባላል። ከዮዲት ህልፈት በኋላ ባለቤቷ መራ ተክለኃይማኖት አገው ላስታ ላይ ጀምሮ ለ360 ዓመታት በቆየው ሥርዓት የዛጉዌ ስርወመንግሥት መሰረተ። ከዛ በኋላ እንደገና ሰለሞናዊ ነኝ ብሎ ኦሮሞው የጊፍቲ አዊ መንዲያ ልጅ ተስፋየሱስ በአማራ ጦር እርዳታ የንግሥና ስሙን ይኩኑአምላክ ተብሎ ነገሠ። ከእሱ ጀምሮ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ ድረስ (ለ700 ዓመታት) ኦሮሞዎች ገዙ። በሰለሞን ስርወመንግሥት ስር የኦሮሞ ግዛት ነው። በእነዚህ ዘመናት ውስጥ የአማራ ግዛት የሚባል የለም።

ሰንደቅ፦ የሩቁን ትተን ከመካከለኛው ዘመን ብንነሳ እንኳ አጼ ቴዎድሮስን ጨምሮ አጼ ዮሃንስ፣ አጼ ምኒልክና አጼ ኃይለሥላሴ የዘር ሀረጋቸው ኦሮሞ እንዳልሆኑ ነው የሚነገረው። ከአጼ ዮሃንስ ውጭ ያሉት እንዲያውም የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው። ታዲያ እንዴት የአማራ ግዛት የለም ማለት ይቻላል?

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- እንዴት መሰለህ አጼ ቴዎድሮስም ሆኑ አጼ ምኒልክ አማራ ሆኑ አልሆኑ “የአማራ ስርወ መንግሥት” ብለው አልነገሡም። የሰለሞን ስርወ መንግሥት ነን ብለው ነው የነገሡት። የአጋዚ ወይም የእስራኤል ነን ብለው ሞ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ እያሉ ነው የነገሡት። በሀገራችን አንድ አባባል አለ “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” ይባላል። ዘሬ አጋዚ እንጂ አማራ አይደለሁም፣ ቋንቋዬም ግዕዝ ነው ካለ መቀበል አለብህ እሱ የሚልህን። እንዲያውም አለቃ አጽመጊዮርጊስ የሚባሉ ባለታሪክ እንደሚነግሩን አጼ ቴዎድሮስ በዘራቸው “ቋራ ናቸው” እንጂ አማራ አይደሉም ይላሉ። በመንግሥታቸው አማራንም አያቀርቡም ነበር ነው የሚሉት። ምኒልክም እንዲሁ በውስጣቸው ኦሮሞ አለባቸው። ምክንያቱም የአጼ ልብነ ድንግል ዘር ናቸው። አጼ ልብነ ድንግል ደግሞ እናታቸው ኦሮሞ ናቸው። አጼ ምኒልክ የዚያ ዘር ናቸው።

ዋናው ነገር በዘር እና በቋንቋ ምንም ሆኑ ምን፤ እኛ አጋዚ ነን ብለው የሰለሞን ስርወ መንግሥት እስከወከሉ ድረስ የአማራ ስርወ መንግሥት ናቸው ማለት አይቻልም። አንዳንድ ሰዎች ግን አማራው በእነዚህ ስርወ መንግሥቶች ተካፍሏል ይላሉ። እኔ ባደረኩት ምርምር በአክሱም ግዛት ጊዜ ሁለት ሴቶችን ነው ያገኘሁት አንዷ ሙሉ አማራ ሌላዋ ግማሽ አማራ የሆነች። የእነሱ ልጆች ንጉሠ ነገሥት ሆነው ነግሠዋል። ያለው እውነታ ይኼው ነው።

ሰንደቅ፦ እውነታው ይህ ነው ካሉ ታዲያ ለምን የአማራ ገዥ መደብ የሚባል ሥርዓት አለ ተብሎ ሊነገር ቻለ?

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- አማራው ገዥ መስሎ የታየው በመጀመሪያ አጼ ላሊበላ የሚባለው ላስታ ላይ የነበረው ንጉሥ ሀርጴ ከሚባለው ወንድሙ ጋር ተጣልተው ሊገድለው ሲል ወደ እየሩሳሌም ሄደ። ቆይቶ ወደ ሀገሩ ሲመለስ በግብጽ ሲያልፍ ከላሊበላ 1850 ዓመት በፊት ቀድመው የሰፈሩ አማራዎች ነበሩ። እነዚያ አማራዎች የሚኖሩበት አካባቢ “አማርና ደልታ” ይባላል። አሁንም ድረስ አለ። ላሊበላ ወደ ሀገሩ ሲመለስ እዛ የቆዩትን አማሮች ይዞ መጣ። እናንተ ወንድሜን ታግላችሁ ጣሉልኝና አንግሡኝ፤ እኔም በመንግሥቴ አሠለጥናችኋለሁ (እሾማችኋለሁ) አላቸው። ከ1850 ዓመታት በኋላም ከወንድሞቻቸው ጋር ተገናኙ። ላሊበላ በአማራዎች ድጋፍ ሲነግሥ ለውለታቸው ቋንቋችሁ ልሳነ ንጉሥ ይሁን ብሎ አማርኛን የንጉሠ ነገሥቱ ቋንቋ አደረገላቸው። እነሱንም የባለሟልነት ሥልጣን ሰጣቸው እንጂ ዘውዱን አልሰጣቸውም። ዘውዱን የሰጠው ለራሱ እና ለልጁ ለይትባረክ እንጂ ለአማራዎቹ አልነበረም።

እንደገና የኦሮሞዋ ጊፍቲ መንዲያ ልጅ ተስፋየሱስ በአቡነ ተክለኃይማኖት አማካኝነት ሲነግሥ አማራዎች ከኦሮሞዎቹ ጋር ሆነው የዛጉዌን ንጉሥ ጥለው ነው ያነገሡት። ተስፋ የሱስ ሲነግሥ ለአማሮች ውለታ እኔ ቤተመንግሥት እና እኔ ጋ የሚመጣ አማርኛ የማይናገር እንዳይመጣ። አማርኛ የማይናገርም በመንግሥቴ እንዳይሠለጥን ሲል አወጀ። በዚህ የተነሳ ሁሉም ለመሾም እና ለመሻሻል አማርኛን መልመድ ጀመረ። ይህ ሁሉ ሲሆን አማሮቹ ዝም ብለው ነው የሚያዩት እንጂ ምንም የሚሉት አልነበረም። ምክንያቱም ሥልጣን አልነበራቸውም። ስለዚህ አማሮች ገዥ መስለው የታዩት ቋንቋቸውና ባህላቸው ስለ ሠለጠነ ብቻ ነው። በተለይ በጊፍቲ መንዲያ ልጅ ጊዜ በግዕዝ የነበሩትን የማዕረግ ስሞች “ራስ ቢትወደድ ባላንምባራስ ወዘተ …” ወደ አማርኛ ቀይሮ በአማርኛ እንዲሆን ተደረገ። ይህ ነው እንጂ ዋናውን ሥልጣን ግን አላገኙም።

ሰንደቅ፦ አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ አማርኛ የመንግሥት ቋንቋ መሆን የጀመረው በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚያ በፊት ግዕዝ ነበር ነው ይባላል። እርስዎ ደግሞ አማርኛ የመንግሥት ቋንቋ መሆን የጀመረው ቀደም ብሎ እንደሆነ እየተናገሩ ነው። ይህን ያስታርቁልኝ።

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- ምኒልክ የሚለው ስም ራሱ እኮ አማርኛ ነው። አባትህ ቢያይህ ምን ይልህ ለማለት ነው። ከምኒልክ 500 ዓመት ቀደም ብሎ ደግሞ መረብ ሳቢ የሚባል ንጉሥ ነበር። አማርኛ ከጥንት ጀምሮ የቆየ ቋንቋ ነው ቢያንስ ከ3700 ዓመት በላይ ይሆነዋል።

ሰንደቅ፦ እርስዎ አሁን ሲናገሩ ቀደም ባሉት ዘመናት ሀገራችን በንጉሠ ነገሥት ዋና ማዕከላዊነት ስትመራ በየአውራጃውና ንዑስ ግዛቶች ውስጥ አስተዳዳሪ የሆኑ ንጉሦች እንደነበሩ ይናገራሉ። ይህን ስንመለከት ደግሞ ሀገራችን የፌዴራሊዝም ሥርዓትን መጠቀም ከጀመረች ቆየት ያለች መሆኗን ነው። በቀዳሚው ዘመን እና በአሁኑ ዘመን ያለውን ፌዴራሊዝም የሚያመሳስላቸውና የሚያለያያቸው ምንድን ነው ይላሉ?

ፕሮፌሠር ፍቅሬ:- በመሰረቱ ሁለቱም ተመሳሳይ ናቸው። የሚያመሳስላቸው አሁን እዚህ ያለው ማዕከላዊ መንግሥት እንዳለው ሁሉ ጥንትም ጠንካራው ንጉሠ ነገሥት የማዕከላዊ ሥልጣኑን ይይዛል። እሱ ደሞ የአካባቢ ንጉሦችን ይሾማቸዋል። ንጉሠ ነገሥቱ የአካባቢ ንጉሦችን ከሾመ በኋላ በመካከላቸው አይገባም። ግብሩን እስካስገቡና ትዕዛዙን እስከፈጸሙ ድረስ በአስተዳደር ገብቶ አያውካቸውም። ሙሉ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል መጀመሪያ።

አሁን ያለውን ፌዴራሊዝም ከድሮው የሚለየው በስም ብቻ ነው። ለምሳሌ የድሮው ጠቅላይ ግዛት ሲባል አሁን ክልል ይባላል። የድሮው ማዕከላዊው መንግሥት ንጉሠ ነገሥቱ ሲሆን አሁን ፓርቲው (ኢህአዴግ) ነው። ሌላው ልዩነታቸው ድሮ አንድ የጠቅላይ ግዛት ንጉሥ ህዝብን ቢበድል፤ ህዝቡ ብሶቱን ይዞ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ በመቅረብ “አቤት” ይላል። ህዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዞ የእህል መያዣ እንቅብ ዘቅዝቆ በመያዝ ተበደልን ተበዘበዝን እያለ በደሉን ያሰማል። ንጉሠ ነገሥቱም የህዝቡን አቤቱታ ሰምቶ ንጉሡን በመጥራት በሁለቱም ወገኖች መካከል ያለውን ውይይት ያደምጣል። ንጉሡ በድሎ ከተገኘ ይቀጣል፤ ካሳም እንዲከፍል ይደረጋል። በዚያ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ከዙፋኑ ወርዶ ፍርድ ሸንጎ ላይ ተቀምጦ የድሃን ጩኸት ይሰማ ነበር።

አሁን ባለው ሥርዓት ግን በደል የደረሰበት ህዝብ ተበደልኩ ብሎ ወደ ማዕከላዊ መንግሥት መጥቶ ሲያመለክት “እዚያው ተመለሱና ችግራችሁን ፍቱት” ተብለው የተመለሱበትን አጋጣሚ እናስታውሳለን። እንደዚህ አይነት ነገር ሲፈጠር (ችግራቸውን ማዕከላዊ መንግሥት አላዳምጥ ሲል) ለማን አቤት እንበል እንባችንን የት እናብስ እያለ ህዝብ ያዝናል። ስለዚህ በህዝብ እና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል ቅራኔ ይፈጠራል። መሆን ያለበት ህዝቡን በማዳመጥ ክልል ያለውን ባለሥልጣን ጠርቶ በመጠየቅ በደል ፈጽሞ ከሆነ መቅጣት አለበት። ህዝብ አጥፍቶ ከሆነም ህዝብን ጥፋተኛ እንደሆነ ማሳወቅ ይገባል።

ከእነዚህ ልዩነቶች (ከስያሜ እና ማዕከላዊ መንግሥት የህዝብን ጥያቄ ከማዳመጥ እና ካለማዳመጥ) በስተቀር አወቃቀሩም ሆነ ሥርዓቱ አንድ አይነት ነው። እኛ ግን የድሮውን ስለማናውቀውና “ፊውዳል” ብለን ስለምንበትነው ፌዴራሊዝም አዲስ ይመስለናል። እንደዚያ ባይሆንማ ኖሮ ሀገራችን እንዴት ትኖር ነበር። እንደዛ አይነት የመንግሥት አወቃቀር ተፈጥሮ የፍትህ ሥርዓት ባይኖር ፍጹም ቀውስ ተፈጥሮ ዳር ድንበር አይተርፍልንም ነበር።

ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ