PM Meles Zenawiየታይም መጽሔት ዘጋቢ በአዲስ አበባ ተገኝቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ስለ ወቅታዊ የረሃብና እርዳታ ጉዳዮች ያደረገውን ቃለምልልስ ሙሉ ቃል በዛሬው ዕለት (እሁድ ነኀሴ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. / August 10, 2008) የተነበበውና ሀገር ቤት የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ በአማርኛ ተርጉሞ እንደሚከተለው አቅርቦታል።

 

ታይም፡- በኢትዮጵያ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ መጠን ላይ አለመግባባት አለ። የእርስዎ አመለካከት ምን ይመስላል?

 

አቶ መለስ፡- በአንዳንድ መረጃዎች የምግብ አለመመጣጠን ችግሮች አሉን። ይህም በሶማሊያና በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ወረዳዎች የተከሰተ ነው። ለተጎዱት በእርግጥ ትንሽ አይደለም። ይሁን እንጂ መቆጣጠር የምንችለው ችግር ነው።

 

ታይም፡- ከዩኒሴፍ ጋር በዚህ ጉዳይ አልተግባባችሁም። በመጀመሪያ 6 ሚሊዮን ሕዝብ አደጋ ላይ መውደቁን ዘግቦ ነበር። የእርሶን መንግስት ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥሩን ወደ 4.6 ሚሊዮን ሕዝብ ዝቅ አድርጎ 75ሺህ ሕፃናት ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው ገልጿል።

 

አቶ መለስ፡- ሪፖርታቸው በውሸት ላይ የተመሰረተ ነው። ሌላ መጥፎ ተልዕኮ አላቸው ብዬ አላምንም። ሁሉም አገራት የአደጋ ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ይረባረባሉ። ያለውን ስዕል ማግዘፍ የተሻለና ትልቅ እርዳታ ለማግኘት ያስችላል የሚል እምነትም አለ።

 

ታይም፡- ስላለው የአስቸኳይ እርዳታ ፍላጎት ምን ዓይነት አመለካከት አለዎት?

 

አቶ መለስ፡- የተቀየጠ ስሜት ነው። አስቸኳይ እርዳታ ሲያስፈልግ ሕዝቡ እርዳታውን እንዲያገኝ ሁሉንም ነገር ማድረግ ይጠበቅብሃል። ያ ማለት ግን መልዕክት አስተላልፎ እርዳታ ማግኘት ማለት ያለውን ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ አስመስሎ ማቅረብ ማለት አይደለም። ይህን ማድረግ በራሱ የከፋ አደጋና ችግር ሊያስከትል ይችላል። ሁሉም እርዳታ ሰጪ አካላት መረጃውን ወስደው በ24 ሰዓታት ውስጥ ያለውን እውነታ ሊያውቁ ይችላሉ። ረሃብ ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜያት አጥቅቷታል። ይህንን አለመገንዘብ በራሱ ማስተዋል አይደለም። በአሁኑ ወቅት በእኛ ዕይታ ረሃብ የለም። አስቸኳይ እርዳታ እንፈልጋለን፤ ረሃብ ግን የለም።

 

ታይም፡- ኤስ.ኤፍ ስዊዘርላንድ በሶማሊያ ክልል አካባቢ ለመስራት ብዙ መሰናክሎች ይቀመጣሉ በማለት አካባቢውን ጥሎ ወጥቷል የጸጥታና የፖለቲካ ጉዳይን ከሰብዓዊ ግልጋሎት ታስበልጣላችሁ ማለት ነው?

 

አቶ መለስ፡- ይህ እውነት አይደለም። አብዛኛዎቹ የሰብዓዊ ግልጋሎት ድርጅቶች በሶማሊ ክልል እየሰሩ ነው። የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና የሰብዓዊ አገልግሎት ሥራ መለየት ያልቻሉት ናቸው መስራት የከበዳቸው። ኦጋዴን እንደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉ እኩል ትኩረት እንዳገኘ ግን ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ።

 

ታይም፡- እርዳታ ሰጪዎችና ተቀባይ መንግስታት በምግብ እርዳታና በልማት እርዳታ ተመጣጣኝ ሥራ ይሰራሉ ብለው ያምናሉ?

 

አቶ መለስ፡- የተወሰነ የሰብዓዊ ግልጋሎት እርዳታ ያስፈልጋል። እኛም ይህንን አይነቱን እንቀበላለን። ይህም በአባኛው መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በኩል የሚያልፍ ነው። ገንዘቡ ለልማት በሚጠቅም መልኩ ምን ያህል ይውላል በሚለው ላይ እርግጠኛ አይደለሁም። በጣም ጥሩ ኤን ጂ ኦዎች አሉ። በዚያው ልክ ምንም እርባና የሌላቸው ኤን ጂ ኦዎችም ሞልተዋል። ሌላው ነጥብ መሆን ያለበት ልማት ከውጭ በሚገኝ እርዳታ ሊረጋገጥ እንደማይችል ማወቅ ያስፈልጋል። የውጭ እርዳታ ቢያንስ ልማት ተስተጓጉሏል ማለት አይደለም።

 

ታይም፡- እርዳታ በራስ መተማመንንና የሥራ ፈጠራን ይጎዳል የሚባለውን እንዴት ያዩታል?

 

አቶ መለስ፡- የሰው ልጆችን ጥምረት በሃምታምና በደሃ ከፍሎ ተጠቃሚዎችን መጉዳት አይቻልም። አንዳንድ ድርጅቶች እነሱ መንግስትን እንደሚያቋቁሙ ያስባሉ። አፍሪካዊያን አሁን ያሉበትን ችግር ራሳቸው ያመጡት አድርገው የሚያስቡና ራሳቸውን ከተጠያቂነት የሚያርቁ አሉ። አሁን ይህ አስተሳሰብ እየጠፋ ነው። አንዳንድ ጥሩ ኤን ጂ ኦዎች ስራቸው የእርዳታ መሆኑንና የመንግስት የልማት ሥራን የመደገፍ እርባና እንዳላቸው ጠንቅቀው የሚረዱ አሉ።

 

ታይም፡- የአገሪቱን ግብርና ለመቀየር ምን እያደረጉ ነው?

 

አቶ መለስ፡- በአነስተኛ ማሳዎች ላይ የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ራስን በመቻል ላይ ያተኮረው የመጀመሪያው ክፍል ነው። የመስኖ ልማቶች፣ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች መጠቀም እና ግለሰቦች በታላላቅ የእርሻ ሥራዎች እንዲሰማሩ ማድረግ ሌላው አቅጣጫ ነው። ግብርናሕው ኢንዱስትሪውን እንዲመራው እንፈልጋለን። ገበሬዎች እንደ ቡናና ሰሊጥ ያሉ ምርቶችን ያቀርባሉ። ይህም በወጪ ንግዳችን ላይ ይስተዋላል። 25 በመቶ ዕድገትም በየዓመቱ እያሳየ ይገኛል። በገጠር አካባቢዎች አርሶ አደሮች ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የግብርና እድገታችንም በሁለት አሃዝ እድገት አሳይቷል። ይህ ማለት ግን ቀዳዳውን በሙሉ ደፍነናል ማለት አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ከአሜሪካ የማኅበራዊ ክብካቤ ፕሮግራም ጋር ተመሳሳይ ነው። ፈንዱም የሚሸፈነው በውጭ እርዳታ ነው። በዚህም ሀሳብም ሆነ ተረጂነት አይሰማንም። ሁልጊዜ አንዳንድ የረሃብ ቀጠናዎች ይኖሩናል ብዬ እጠብቃለሁ። ዋናው ነገር ኢኮኖሚያችን ይህንን ለመመለስ በቂ የሆነና ለሴፍቲ ኔት ፕሮግራሙ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው ማድረግ ነው። እዛ ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም።


 

ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ ነኀሴ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. / August 10, 2008 ዕትሙ

(http://www.ethiopianreporter.com/content/view/2643/54 )

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!